ፍኖተ መስቀል
ቤተ ክርስቲያናችን በምስራቃዊና በላቲን ሥርዓት የተለያዩ ብዛት ያላቸው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ላይ ለማስተንተን የሚያግዙ ጸሎቶች አሏት። ከነዚህም ውስጥ በላቲን ሥርዓት ውስጥ በምእመናን ዘንድ ይበልጥ የሚዘወተረው የ"ፍኖተ መስቀል" ጸሎት ነው። በዚህ ገጽ ውስጥ የቀረበውም ይህንኑ ጸሎት መሠረት ተደርጎ "መንፈሳዊ ማሳሰቢያ" በሚል ስያሜ በማኅበረ ሲታውያን ተዘጋጅቶ ከነበረው መጽሐፍ ውስጥ ነው። ጌታ ራሱ ወደ ሕማማቱ የፍቅር መስጢር እንድንገባና እንኖረው ዘንድ ያግዘን።




ጲላጦስ ኢየሱስን ሞት ከፈረደት በኋላ እንደ ባሕላቸው እንዲሰቅሉት ለአይሁዳውያን አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ “ከዚህ በኋላ ጲላጦስ በርባንን አድኖ የተገረፈውን ኢየሱስን እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው” ማቴ. 27፡26 በዚህ የአይሁዳውያን ምኞት ተፈጸመ፡፡
መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ ሲሄድ ሳለ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመስቀሉ ጋር እንደወደቀ ያሳስበናል፡፡ ኢየሱስ ሞት ከተፈረደበት በኋላ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ ፊቱን አመራ፡፡
አይሁዳውያን ኢየሱስን እያዋረዱ፣ እየመቱና እየገረፉ ይወስዱት ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ በትሕትና ይታዘዝላቸው ነበር፡፡ “ተጨነቀ፣ ተሰቃየ አፋንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚዳ ጠቦት በሸላቾችም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም” ኢሳ. 53፡ 1-6 ፡፡ ኢየሱስ ውርደትን ታግሶ ተቀበለ ከባድ መስቀልን በትከሻው ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ ሄደ፡፡ በመንገድ ያች የተወደደች ርኅርኅት እናት ወላዲቱ ቆየችው፤ ስቃዩን አውቃ በወላጅ እናት ፍቅር ተስባ ልታየው ወጥታ ነበር ዓይን ለዓይን የተገናኙት፡፡
አይሁዳውያን ኢየሱስ ከልክ በላይ ደክሞት እንደ ነበር ከተረዱ በኋላ ቀራንዮ ሳይደርስ እንዳይሞት ፈርተው በዚያ መንገድ ያልፍ የነበረ የቀሬናው ስምዖን ለሚባል ሰው የኢየሱስን መስቀል በመሸከም እንዲያግዘው አዘዙት፡፡ እርሱም ታዘዛቸው፡፡ አይሁዳውያን ኢየሱስ መስቀል ከመሸከም እንዲያርፍ የፈለጉት ራርተውለት ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የቆየ ቂማቸው ፍጻሜ ሳያገኝ ግቡን ሳይመታ እንዳይቀር ፈርተው ነው፡፡
ኢየሱስ መስቀል ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ ሲሄድ በመንገድ ላይ ቨሮኒካ የምትባል አንዲት ደግ ሴት ፊቱ በላብ፣ በምራቅ፣ በአፈር፣ በደም አድፎ ባየችው ጊዜ ሰዎቹን ሳትፈራ ወደ እርሱ ቀርባ በመሐረብ ፊቱን ጠረገችለት፡፡
የቀራኒዮ መንገድ ኢየሱስን ብዙ ጐዳው፣ በመጀመሪያ የወደቀውና አካላቱ የተቀጠቀጠው ሳያንሰው በተጨማሪ ከባድ መስቀል ተሸክሞ ሲጓዝ ሁለተኛ ጊዜ በምድር ላይ ወደቀ፡፡ የፊተኛው ሳይበቃው እንደገና የወደቀው ኢየሱስ ስለ እኛ ምስኪን የሆነው ከፊተኛው መውደቅ ሁለተኛው በረታበት ብዙም ጐዳው፣ አቆሰለው፡፡ እንደገና ለመሄድ ተነሣ ነገር ግን ሰውነቱ ዛለ ደከመ፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስበክ በጀመረ ጊዜ ሴቶች በቅድስናውና በተአምራቱ እጅግ ታንጸው ሁሉን ትተው ተከተሉት፡፡ በሞቱ ወቅት እነዚህና ሌሎች ደግ ሴቶች በወረደበት መከራ ደንግጠው ሲያስተውሉትና ሲራሩለት ታዩ፡፡
የኢየሱስ ሰውነት ዝሎና ደክሞ ነበር፤ የኢየሱስ መከራ ወደ ፍጻሜ ሊደርስና በቀራኒዮ ስለ አዳም ልጆች ደኅንነት ሊሰዋ ተቃርቦ ነበር፡፡ ግርፋቱ፣ ድብደባውና እንግልቱ አድክሞና አሸንፎት ሶስተኛ ጊዜ ከመስቀሉ ጋር በመንገድ ወደቀና በጣም ተጐዳ፣ ብርቱ ስቃይ ተሰማው፡፡ ግን በገዛ ፈቃዱ በፍጥነት ይነሣና በታላቅ ትሕትና ወደ ሚሰቀልበት ይሄድ ነበር፡፡
ኢየሱስ ወደ ቀራኒዮ ወጣ፡፡ በአንድ በኩል የአይሁዳውናያን መጥፎ ሐሳብ እርሱን መገደል በሌላ በኩል የተቀደሰ ምኞት ዓለምን በማዳን ተፈጸመ፡፡ በቀራኒዮ የባየ መከራ ይቀብቀው ነበር፡፡ አይሁዳውያን ቀድመው ሊፈርዱበት ብለው ላይና ታች እያሉ ሲያንገላቱቱ ለፌዝና ለቀልድ ሲሉ ቀይ ካባ በልብሱ ላይ ደረቡለት፡፡ በኋላ በቀራኒዮ ልብሱን ሁሉ ገፈፉት ራቁቱን አወጡት፤ ሐሞት ኮምጣጤ አጠጡት፣ ልብሱን በመግፈፍ እንዴት ያለ ውርደት ተሰማው?
አይሁዳውያን ለኢየሱስ መራራ ሐሞት እና ሆምጣጤን ካጠጡት በኋላ ልብሱን ገፈው ሊሰቅሉት ተዘጋጁ፤ መስቀሉን በምድር አስቀመጡት ኢየሱስን በእርሱ ላይ አስተኝተው ያለ ርኅራኄ ያለ ምህረት እጆቹንና እግሮቹን ቸነከሩት፡፡ እንደገና ደሙን እያፈሰሰ እና እያጐረፈ ሲታይ ብርቱ ስቃይ ይሰማው ነበር፡፡ መከረኛው ኢየሱስ መከራው ባሰ፡፡ የመስቀል ስቃይ በጣም ከበደው፡፡
ወታደሮች ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከቸነከሩት በኋላ መስቀሉን ጉድጓድ ውስጥ አቆሙት፡፡ መስቀሉ እንደቆመ ኢየሱሰ ከባድ ስቃይ ተሰማው፣ ቁስሎች ጠዘጠዙት፡፡
ኢየሱስ “ሁሉም ተፈጸመ” በማለት ሞተ፡፡ የቀራኒዮን መስዋዕት አቀረበ ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ይመኘው የነበረውን የአዳምን ዘር የማዳን ሥራ ፈጸመ፡፡ በሞቱ ሞታችንን አሸንፎ ሕይወትን ሰጠን፡፡ እኛ ታስረንበት የነበረውን ሰንሰለት ከእኛ አስወግዶ በእኛ ምትክ አስሮን የነበረውን ዲያብሎስን አሰረው፡፡ “አስሮ ለሰይጣን ወአግዓዞ ለአዳም”
እነዚህ ሶስት ጻድቃን ኢየሱስን ከመስቀል ካወረዱት በኋላ ሳይመሽ ሊቀብሩት ተቻኰሉ፡፡ እዚያ የነበሩት የዋህ ሴቶች በመታገዝ እንደ አይሁዳውያን ልማድ የኢየሱስን አስከሬን ሽቶ ቀብተው ከፈን ከፍነው በአጠገባቸው በነበረው መቃብር ቀብረው መቃብሩ ላይ ትልቅ ድንጋይ ጫኑበት፡፡ ማቴ. 27፡59-61 የህንንም አድርገው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
