ንኡሳን ገጾች
Chaplet of Divine Mercy
Home (ቅድመ ገጽ) ቅ. ቁርባን ኢየሱስ ክርስቶስን ይሰጠናል!

ቅዱስ ቁርባን ኢየሱስ ክርስቶስን ይሰጠናል!

ምሥጢራት - ቅዱስ ቁርባን
 
"ቅዱስ ቁርባን ኢየሱስ ክርስቶስን ይሰጠናል!" 
 
እምነታችንን፣ ፍቅራችንን፣ ተስፋችንን እና ይቅር ባይነታችንን በቅዱስ ቁርባን እንጂ በስሜቶቻችንና በሃሳባችን ልናጸናቸው አንችልም። ሁል ጊዜ የጋለ ልብና ግልጽ የሆነ ሃሳብ ሊኖረን አይችልም፤ ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን መንገድ ስለማወቃችንም ዘወትር ርግጠኞች መሆን አንችልም። እንዲሁም በአናኗራችንና በስብእናችን እምነታችን ምን እንደሚጠይቀን መመዘኑ ሁሌም አይሳካልንም። ነገር ግን ጥልቅ በሆነ መልኩ ርግጠኛ ልንሆንበት የምንችለው አንድ ነገር አለ፤ ያም ወደ ቅዱስ ቁርባን ዘወትር መሄድ መቻላችንን ነው። (ፍቅር ትዳርን ያጸናዋል ብለን ዘወትር ከማለት ትዳርም ፍቅርን ያጸናዋል ብሎ እንደማሰብ ነው። በተመሳሳይ መልኩም ያለማቋረጥ ስለምናምን ወደ ቅዱስ ቁርባን በቋሚነት እንሄዳለን ማለት ሳይሆን በቀጣይነት ወደ ቅ.ቁርባን በመሄዳችን እምነታችን ይጸናል ማለት ነው) ሮናልድ ሮልሃይዘር (አባ)  
 
ሌሎች ምሥጢራት ጸጋን ይሰጡናል፤ ቅዱስ ቁርባን ግን ራሱን የጸጋ ባለቤቱን፣ ሰውና አምላክ የሆነውን ኢየሱስ ይሰጠናል። ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውም ሆነ አላት የሚባሉት ነገሮች ሁሉ ማእከል ቅዱስ ቁርባን ነው።
ቅዱስ ማርቆስ የጸሎተ ኀሙስ ራት ሂደትን ሲገልጽ “ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ እንካችሁ ይህ ሥጋዬ ነው ብሎ ሰጣቸው” ይላል (ማር.14:22)። ከአራቱ ወንጌል ውስጥ ሦስቱ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትን በግልጽ ይተርካሉ፦ ማቴ.26:25-29፣ ማር.14:22-25፣ ሉቃ.22:19-23። ቅዱስ ጳውሎስም በመጀመሪያ ቆሮንጦስ 11:23­-25 ጽፎልናል። ቅዱስ ዮሐንስ ከሌሎቹ ሁሉ በመጨረሻ የተጻፈ ወንጌል ስለሆነ (90-100 ዓ.ም.) ምናልባት ሌሎቹ ያልገለጿቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ይመስላል። ከላይ በተጠቀሱት ስለ ቅዱስ ቁርባን የተጻፉት ምንባባት ሁሉ የተንጸባረቀ አንድ እውነት ቢኖር “ይህ ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ…ይህ ደሜ ነው እንካችሁ ጠጡ” የሚለው ነው። 

በዮሐንስ 6:53 ላይ ኢየሱስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ የሆነውን የክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ፤ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም” ይላል። ይህ ጥቅስ በራሳቸው ባልሆነ ጥፋት ይህን ቃል ወይም መልእክት ያልሰሙት አይድኑም ለማለት ሳይሆን ይህን እውነት እያወቁና እየሰሙ እንዳልሰሙ የሚሆኑትን ለማመልከት ነው።

ከስንዴ በተዘጋጀ ኅብስትና የተፈጥሮ ወይን ጭማቂ ላይ ዘላለማዊ የሆኑትን “እንካችሁ…” የሚሉትን የክርስቶስ ቃል ካህን ሲደግም ቅዱስ ቁርባን ዛሬም ለሰዎች ሁሉ ክርስቶስን ሕያው ያደርግልናል። በመሥዋዕተ ቅዳሴያችን የሚከናወነው ነገር ክርስቶስ ራሱ ካደረገው የሚለይ አይደለም። እሱ ኅብስቱን አንሥቶ “ይህ ሥጋዬ ነው” ወይኑንም አንሥቶ “ይህ ደሜ ነው” ሲል የመለወጡ ሂደት ተከናወነ። ይህ እንዴት ይሆናል ካልን እሱ ራሱ ባለቤቱ ያደረገውና ዘወትርም ሊያደርገው ቃል የገባልን ጉዳይ መሆኑን እንጂ አእምሮ ብቻውን እስከ ጥግ ድረስ ሊዘረዝረው አይችልም። ይህን አድርጉ ብሎ ሕያው አደራውን ተወልን፤ ስለዚህም ዛሬም የክርስቶስ ቃል የኅብስትና ወይኑን ውጫዊ ነገራቸውን ብቻ በማስቀረት ማንነታቸውን ግን የራሱ ሥጋና ደም ያደርገዋል። 

በአንድ ወቅት እውቁ ሊቀ ጳጳሳት ፉልተን ሺን እንዲህ ብለው ነበር ፦ 

በቀን ነገሮችን ለማየት የምትጠቀምበት ዓይንህ ማታም አለህ፤ ሆኖም ግን የቀኑ የፀሐይ ብርሃን የለምና በምሽት ያው ዓይን ነገሮችን ማየት አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታም ተመሳሳይ የማሰብ ብቃት፣ እኩል ትምህርት፤ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ሁለት አእምሮዎች (ሰዎች) በመንበረ ታቦት ላይ ያለውን “ኅብስት” ሲመለከቱ አንደኛው የስንዴ ኅብስትን ሲያይ ሌላኛው ክርስቶስን ሊያይ ይችላል። የተመለከቱት አንደኛው በሥጋ ዓይን ሌላኛው ደግሞ በእምነት ዓይን ነው ማለት ነው። የዚህ ልዩነት ምክንያት ይህ ነው፦ ክርስቶስን መመልከት የቻለው ሰው ሌላኛው የሌለው ብርሃን አለው - የእምነት ብርሃን! 

በዮሐንስ ወንጌል 6:47-67 ውስጥ ክርስቶስ ይህን መሰል ጠጠር ያለ የ “ሥጋና ደም” መመገብን ጉዳይ ሲናገር ብዙዎች እንኳን ማድረጉ መስማቱ አልዋጥላቸው ብሎ ከብዷቸው እሱን ትተውት ቢሄዱም መደራደርንና እንተወው ወይ ቀለል ላድርግላችሁ ብሎ አላመነታም።

ክርስቶስ ይህን ያህል ትኩረት የሰጠበትን እውነታ ቤተ ክርስቲያንም ትኩረት መስጠቱን ቀጥላበታለች። በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ይፈጸም የነበረውን የጌታ ትእዛዝ ተከትለው አበው ቅዱሳን ጥንታዊ ምስክርነታቸውን በጽሑፋቸው ተተው አልፈዋል። ከነዚህም መካከል ክርስቲያን በመሆኑ ለዱር አውሬዎች ምግብ ይሆን ዘንድ የዘመኑ ባለሥልጣናት የወረወሩትና በሰማዕትነት የሞተው ቅዱስ ኢግናጽዮስ ዘአንጾኪያ በ107 ዓ.ም. አካባቢ “ቅዱስ ቁርባን የአዳኛችን ኪየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ነው” ብሎ ጽፎ ነበር። እንዲሁም ስለ እምነቱ ሰማዕትነትን የተቀበለው ሌላ መስካሪ ቅዱስ ዩስጢኖስ በ145 ዓ.ም. ገደማ “የምንመገበው ሰው የሆነው የክርስቶስ ሥጋና ደም መሆኑን ተምረናል” በማለት ጽፏል። ከዚያም ይህ እምነት እንዳለ ሆኖ በ16ኛው ክ.ዘ. ከፕሮቴስታንቶቹ አካባቢ ቅዱስ ቁርባንን የሚቃወሙ ትምህርቶች በመስተጋባታቸው በ1551 ዓ.ም. በትሬንት በተካሄደው ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ቅዱስ ቁርባን ርግጠኛ የክርስቶስ ሥጋ፣ ደም፣ ነፍስና መለኮታዊ ህልውና መሆኑና ክርስቲያኖችም ሊከተሉት የሚገባ እምነት መሆኑ ይፋና ወጋዊ በሆነ መልኩ ጸደቀ።

እንግዲህ በቅዱስ ቁርባን የክርስቶስ ህልውና ይህን ያህል ወንጌላዊ፣ ታሪካዊ፣ ግልጽና ቀጣይ እውነት ከሆነ ዛሬም በየቤተ ክርስቲያኑ መንበረ ታቦት ላይ በኅብስትና ወይን ውጫዊ መገለጫ የሚገኘው ክርስቶስ ተገቢ የሆነ አምልኮና ስግደት ይገባዋል። እንዲሁም ዘላለማዊውና ሁሉን አዋቂው “ሐኪም” ክርስቶስ “ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው” (ዮሐ.6:54) ካለን እሱ ፈጥሮናልና የሚበጀንን አብጠርጥሮ ስለሚያውቅ በሚቻለን አቅምና ሁኔታዎች ራሳችንን ያለቀጠሮ አዘጋጅተን እንታዘዘው።
 
{denvideo clip11.flv}  
 

Last Updated (Wednesday, 24 June 2009 22:46)

 

Add comment


የሳምንቱ መልእክት
"ለሰው ይኽን ያህል ታላቅ ክብር ለመስጠት ያነሳሳህ ምን ይሆን?...ወደር የሌለው ፍቅርህ እንደሆነ አይጠረጠርም! በፍቅሩ ተማርከሃል፤ በአውነትም በፍቅር ፈጥረኸዋል፤ በፍቅርም ዘላለማዊ መልካምነትህን የሚያጣጥም ስብእናን ለግሰኸዋል።" ቅድስት ካተሪና ዘሲየና
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ያን መዝሙሮች (ብዛት 110!)
ባለፉት 12 ሰዓታት የጎብኚዎች አገር
Top 8:
Ethiopia flag 25%Ethiopia (4)
Netherlands flag 19%Netherlands (3)
Unknown flag 19%Unknown (3)
Moldova, Republic of flag 12%Moldova, Republic of (2)
Germany flag 6%Germany (1)
Russian Federation flag 6%Russian Federation (1)
Switzerland flag 6%Switzerland (1)
United States flag 6%United States (1)
16 visits from 8 countries