- 05 May 2013
የብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የ2005 ዓ.ም የጌታችን ትንሣኤ በዓል መልእክት
ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የ2005 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤን በዓል በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት፡፡
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
"እርሱ ግን እንዲህ አላቸው አይዞአችሁ አትደንግጡ እናንተ የምትፈልጉት ተሰቅሎ የነበረውን የናዝሬቱን ኢየሱስ እንደሆነ አውቃለሁ እርሱ ተነስቶአል፤ እዚህ የለም የተቀበረበት ቦታ ይኸውላችሁ ተመልከቱ" (ማር 16፡ 16)፡፡
የተወደዳችሁ ምዕመናን፣
ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ በሀገር ውስጥና እንዲሁም ከአገር ውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፣ በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሰዎች በሙሉ፡-
ከሁሉ በማስቀደም እንኳን ለ2005 ዓ. ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴም ስም መልካም ምኞቴን እገልጽላችኃለሁ፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ፍጡሩን ከፈጣሪው የለየውን የሰውን ኃጢአት ስላስተሰረየ ለሰውም የተገባውን ፍርድ ራሱ ተቀበሎ ስላስወገደና ኃጢአተኞችን ከኃጢአት አንጽቶ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባቸው ስለቻለ እኛም በመስቀል ላይ ሞቶ ከአምላክ ጋር ያስታረቀንን እስከ ዛሬ ከኛ ያልተለየውን ኃጢአት ካላስወገድን በቀር ከእግዚአብሔር ጋር መራመድ አይቻለንም፡፡ ኃጢአትን በመውደድና ከምንሠራው ክፋት ለመራቅ ባለመፍቀድ ከእግዚአብሔር ተለይተን ብንኖር የተቀበልነውን ፀጋ ያጠፋብናል ስለሆነም ክርስቲያን የሆነ ሰው ባለበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር መኖሩን በማወቅ ትንሣኤያችን የሆነውን ክርስቶስን ተቀብለን እምነታችንንም በእርሱ አድርገን ልንጓዝ ይገባናል፡፡
እግዚአብሔር በጌታችን ትንሣኤ አማካይነት ለእኛ ለክርስቲያን ወገኖቹ ያቀደልንና የወሰነልን ዕቅድ አለው ለሕይወታችንም መንገድ አለው በዚህም የፈጠራቸውን ሁሉ ወደ እርሱ ግብ የሚያደርሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ በፈፀመው ሥራ በኩል ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሞትን ለመቀበል የመጣው እግዚአብሔር አብ ከመጀመሪያ ጀምሮ የወሰነውን ዕቅድ ለመፈፀም አስቦ ስለላከው ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ የእግዚአብሔርን ተቃዋሚዎች ስላሸነፈና ከሁሉም በላይ ስለሆነ ፍጡራን ሁሉ ለእግዚአብሔር አብና ለእርሱ ይገዛሉ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ያደረገውን ጳውሎስ ሲናገር "አለቆችንና ባለሥልጣኖችን በመስቀሉ ድል ነስቶ ትጥቃቸውን ካስፈታ በኋላ ምርኮኞች ሆነው በይፋ እንዲታዩ አደረጋቸው" ይላል (በቆላ 2 ፡ 15)፡፡
በዮሐንስ ወንጌል (3 ፡ 33) ላይ ደግሞ "ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገረ ሁሉ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደሆነ ያረጋግጣል" ይላል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ይህንን በመመስከር የምንፈልገውን ዕርዳታ በእርሱ አማካይነት ስላገኘን ወደ ክርስቶስ ስንቀርብ በፍቅሩ ሙላትም ደስ ሲለን በፊቱ ብርሃን ጨለማችንና መጠራጠራችን ይወገዳል፡፡
የተወደዳችሁ ምዕመናን ሁላችንም በክርስቶስ መኖር መቻል አለብን ምክንያቱም ከእርሱ ጋር መኖር ዕረፍት የሞላበት ኑሮ ነው፡፡ ተስፋችንን የምናገኘው ከክርስቶስ ነው፡፡ መታመኛችንም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ሀሳባችንን በክርስቶስ ላይ ማድረግ አለብን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ መስጠቱና መዋረዱ ለኛ ለሰው ልጆች ያሳየንና የገለጠልን ወደር የሌለው ፍቅር ነው፡፡ እርሱን መምሰል የሚገኘው ደግሞ እርሱን በመውደድና ፈጽሞ እርሱን መስሎ በእርሱ ዘንድ በመገኘት ነው፡፡
በክርስቶስ ትንሣኤ ሰዎች ያገኙትን የብርሃን ጸጋ ለሌሎች ወንድሞችና እህቶች በእምነታቸው መልሰው ሊያሳዩአቸው ይገባል፡፡ ይህም ማለት ሁላችንም በእምነታችንና በክርስትናችን መልካም ምሳሌ መሆን ይገባናል ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በመነሳቱ ለዘላለዓም ህያው ነው፣ እኛም ደግም ከእርሱ ጋር ከሞት ከተነሳን ወደ ኃጢአት ባለመመለስና በመንፈስ ሳንደክም ፀንተን እንኑር የክርስቶስ ትንሣኤ የሰጠንንም ሰማያዊ ብርሃንና ሰላም የተቀበልነውን የድኅንነት ሀብት ሳናጠፋ ሐሳባችንና ጥረታችን ወደ ሰማይ ከፍ እናድርግ፡፡
የተወደዳችሁ የአገራችን ህዝቦች፣ ዛሬ አገራችን ከድህነት ለመላቀቅ የተያያዘችውን የዕድገት ጎዳና በተለያየ መስኮች አጠናክራ በመሥራት ላይ የምትገኘበትን ዘርፈ ብዙ ዕቅዶች ከመንግሥት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ መሥራታችሁ ያስመሰግናችኋል፤ በመሆኑም በሃሳብ በጉልበት በገንዘብ በሥራ በማገዝ በየተሰማራችሁበት መስክ ጠንክራችሁ በመስራት የአገሪቱን ዕድገት እንድታፋጥኑና ለተፈጻሚነቱም የተቻላችሁን ያህል ርብርብ በማድረግ የልማቱን ጐዳና ከፍጻሜ ይደርስ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡ ከዚህም ጋር ጎን ለጎን መታየት ያለበት የዕድገት ማነቆ የሆኑትን የመልካም አስተደዳደር ጉድለቶችንና ግድፈቶችን በማስተካከል የዜጎች መብት ይከበር ዘንድ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስተገብርና የአፈጻጸም ዕቅዶች የያዘውን ለመከወን ቤተክርስቲያናችን የምትደግፈው መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡
እንደዚሁም አሁን አሳሳቢ ሆኖ እየመጣ ያለው የሰዎች ፍልሰት በአገር ውስጥ በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች ሰዎች በከተማና በክልላቸው ተደራጅትው ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የሚሠሩበት መንገድ በበለጠ እንዲቀየስና ለዚህም በመገናኛ ብዙሃን የሚሰጠው ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡
በዚህ ዓመት የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ የወርቅ ኢዩቤልዩ ዓመት ይከበራል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነትና ሕብረት ያበረከተችው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ለመሆኑ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ አዲስ አበባም የአፍሪካ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤት ከተማ ስለሆነች የአፍሪካ መናገሻ ተብላለች፡፡ ይህም ያኮራናል፡፡ ለዚህም ላበቃን ለቸሩ እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይድረሰው፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት የእንግዳ አቀባበላችንና ሥነ ምግባራችን ልቆ መገኘት ይኖርበታል፡፡ የአፍሪካ ሕብረትም ተጠናክሮ የአፍሪካውያን ሁሉ የሰላም፣ የፍትህ፣ የዕድገት መሰረትና አለኝታ እንዲሆን በጸሎት አምላካችንን አንለምነው፡፡ እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ!
የተወደዳችሁ ምዕመናን በጌታችን በመድኃኒታችን ትንሣኤ ሁላችንም ከቸርነቱ ተቀባዮች ብቻ ሳንሆን ያለንን ለድሆችና አቅመደካሞች ለሆኑት አስተዋሽ ላጡና ለጎዳና ተዳዳሪዎች በመስጠትና በማካፈል ከጌታ ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠናከር እንደዚሁ በእርሱ ዙሪያ ተሰባስበን በክብርና በድል ሞትን ያሸነፈውን የአምላካችንን የትንሣኤ በዓል በደስታ ለማክበር ያብቃን እላለሁ፡፡
በመጨረሻም በአደረባችሁ ሕመም ምክንያት በሆስፒታሎችና በየቤቱ በሕመም ላይ የምትገኙ ሁሉ የምሕረት አባት ምሕረቱን ያውርድላችሁ" በከባድ ሀዘን ውስጥም ያላችሁትን እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጣችሁ" በየማረሚያ ቤቶችም ሆናችሁ ይህን ክብረ በዓል የምታከብሩትንም እግዚአብሔር በምህረቱ ይፍታችሁ" በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻችሁ ርቃችሁ ለምትገኙ፣ በየጠረፉና የአገራችንን ድንበሮች በመጠበቅ ላይ ለምትገኙ ሁሉ፣ እንዲሁም በውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ በማለት በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም መልካም ምኞቴን አስተላልፍላችኃለሁ፡፡
በጌታ ትንሣኤ እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ!!
- 28 April 2013
የር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ስብከት ዘሆሳዕና 2005 ዓ.ም.
የር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ስብከት ዘሆሳዕና 2005 ዓ.ም.
1. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በርካታ ተከታዮቹ ታላቅ በዓል አደረጉለት፤ ልብሶቻቸውን በፊቱ አነጠፉለት፣ እርሱ ስላደረገላቸው ተዓምራት በብዙ ይነጋገሩ ነበር፣ "በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተመሰገነ ነው፤ ምሥጋና በሰማይ ለእግዚአብሔር ይሁን ሰላምም በምድር በጎ ፈቃድ ላላቸው ይሁን" የሚል ታላቅ የምሥጋና ድምፅ ይሰማ ነበር፡፡ (ሉቃ 19፡38)
ተከታዮቹም በምሥጋና፣ በታላቅ በዓል፣ በበረከት እና በሰላም ተሞሉ፤ የደስታ መንፈስ ሰፈነ፡፡ ኢየሱስ በተለይ በድሆች እና በሚስኪኖች፣ በትሑታን እና በተረሱት ሰዎች ልቦና ውስጥ ትልቅ ተስፋ ቀሰቀሰ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዓለም ፊት ለዓይን የማይሞሉ ነበሩ፡፡ እርሱ የሰው ልጆችን ስቃይ ያውቀዋልና የእግዚአብሔርን የምሕረት ፊት አሳያቸው፤ ነፍስን እና ሥጋን ለመፈወስ ሲል ዝቅ አለ፡፡
ይሄ ኢየሱስ ነው፡፡ ይህ ድካማችንን፣ ኃጢአታችንን እንዲሁም እያንዳንዳችንን የሚመለከተን ልቡ ነው፡፡ የኢየሱስ ፍቅር ታላቅ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ፍቅር ወደ ኢየሩሳሌም በመግባት አኛን ይመለከተናል፡፡ በጣም ውብ የሆነ ገጽታ ነው፤ በኢየሱስ ልብ ፍቅር ብርኃን የተሞላ ነው፤ በደስታ እና በበዓል መንፈስ የተሞላ ነው፡፡
በቅዳሴያችን መጨረሻ ላይ እኛም ይህንኑ እንደግመዋለን፡፡
ዘንባባችንን እና የወይራ ቅርንጫፎቻችንን እናውለበልባለን፡፡ አኛም ኢየሱስን በቤታችን እንቀበለዋለን፤ ከእርሱ ጋር በመንገዱ ላይ በመገኘታችን የተነሳ ደስታችንን እንገልፃለን፡፡ ቅርባችን መሆኑን በምናውቅበት ጊዜ፣ በማንነታችን ውስጥ በመገኘቱ፣ ጓደኛችን ሆኖ በመቅረቡ፣ ወንድማችን በመሆኑ እና በንጉሥነቱ እንደሰታለን፤ ይህም ለሕይወታችን የሚያበራ በተራራ ላይ ያለ መብራት ነው፡፡ ኢየሱስ አምላክ ነው ነገር ግን ዝቅ ብሎ ከእኛ ጋር ለመጓዝ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ እርሱ ጓደኛችን እና ወንድማችን ነው፡፡
- 19 April 2013
ቤተ ክርስቲያን ልጆችን የምታስተኛ ሞግዚት መሆን የለባትም!
ቤተ ክርስቲያን ልጆችን የምትወልድ እናት እንጂ የምታስተኛ ሞግዚት መሆን የለባትም!
ወንጌልን የማስፋፋት ኃላፊነት የካህናት ብቻ አይደለም ሲሉ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በረቡዕ ጠዋት ስብከታቸው ከመጋቢት ምርጫ ጀምሮ በሚኖሩበት ዶሙስ ሳንክቴ ማርቴ ተብሎ በሚጠራው የቫቲካን እንግዳ ማረፊያ ቤተ ጸሎት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ አሳሰቡ።
በዚሁ ቤተ ጸሎት በየእለቱ በሚያሳርጉት ቅዳሴ ላይ ቫቲካን ውስጥ የሚሠሩ የተለያዩ ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን በዚህኛው የረቡእ ቅዳሴ ላይ የተገኙት የቫቲካን ባንክ ሠራተኞች ነበሩ፤ ር.ሊ.ጳ. ለእነርሱ ባስተላለፉት መልእክት የእለቱን የሐዋርያት ሥራ ንባብ 8፡1-8 ያለውን ጠቅሰው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ብርቱ ስደቶችን ሲሸሹ የእግዚአብሔርን ቃል በየሄዱበት ይሰብኩ እንደነበር አስታውሰዋል። "ከተጠመቁ ገና አንድ ዓመት ወይም ትንሽ በለጥ ያለ ጊዜ ብቻ የነበራቸው ተራ አማኞች የነበሩ ቢሆንም እየሄዱ ቃሉን ለማወጅ ብርታት ነበራቸው፣ ይታመኑና ተአምራትንም ያደርጉ ነበር" ብለዋል።
በማያያዝም ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ሚሽነሪዎች በ17ኛው ክ.ዘ. ከተባረሩበት ጊዜ ጀምሮ ለ200 ዓመታት ያለካህናት ያሳለፉትን የጃፓናውያን ካቶሊኮች ታሪክ አውስተው በኋላ ሚሽነሪዎች ተፈቅዶላቸው ወደ ጃፓን ሲመለሱ በዚያ የነበሩት ካቶሊኮች በሥርዓቱ የተጠመቁ፣ ትምህርተ ክርስቶስ የተከታተሉና በቤተ ክርስቲያን ፊት የተጋቡ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ር.ሊ.ጳ. ዛሬ በምስጢረ ጥምቀት ኃይል ይህን መሰል እምነት ምእመናኖች ያላቸው እንደሆን ጠይቀዋል። የተጠመቅን ሁላችን "ኢየሱስን በሕይወታችን፣ በምስክርነታችንና በቃላችን" ማወጅ እንዳለብን አሳስበዋል። "ይህንንም ስናደርግ ቤተ ክርስቲያን ልጆችን የምትወልድ እናት ትሆናለች፤ በአንጻሩም ይህን ካላደረግን ቤተ ክርስቲያን ልጅን የምትወልድ እናት ሳይሆን ልጆችን ለማስተኛት የምትጠብቅ ሞግዚት ትሆናለች!" በማለት ስብከታቸውን አጠቃለዋል።
ምንጭ፡- http://www.catholicherald.co.uk
- 11 April 2013
ካቶሊኮች የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ደስታን በማሳየት ዓለምን አገልግሉ
"ዓለም ዓይኖቹን ወደ እግዚአብሔር ማንሳት ተስኖታልና" ካቶሊኮች "የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ደስታን" ለዓለም በማሳየት የሰው ልጆችን ያገለግሉ ዘንድ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ አሳሰቡ።
"የእግዚአብሔር ልጆች የመሆናችንን ደስታና በክርስቶስ እንኖር ዘንድ የሰጠንን ነጻነት እናሳይ፣ ወደ አምላክ ማየት ለተወው ዓለም ይህ ውድ የሆነ አገልግሎት ነው" በማለት ትላንትና ረቡዕ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት 40 ሺህ ሰዎች ተናግረዋል።
"ይህ ማለት በእያንዳንዷ ቀን ክርስቶስ ይለውጠንና እርሱን እንዲያስመስለን መፍቀድ አለብን ማለት ነው፤ ይህም ደካማነታችንን እና ጉድለታችንን ብናውቅም እርሱን ለመከተል በመጣር እንደ ክርስቲያኖች ለመኖር መሞከር ማለት ነው" በማለት ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ አብራርተዋል።
ሲቀጥሉም "በውድቀቶቻችን ተስፋ ሳንቆርጥ በእርሱ መፈቀራችንን ሊሰማን ይገባል፤ ይህ ሲሆን ሕይወታችን በደስታና በርጋታ መንፈስ የተሞላ አዲስ ይሆናል። እግዚአብሔር ብርታታችን ነው! እግዚአብሔር ተስፋችን ነው!" ብለዋል።
ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ የእግዚአብሔር ልጅነታችንን ከክርስቶስ ትንሣኤና የማዳን ዋጋ ጋር በማስተሳሰር ካቶሊካዊ እምነት በትንሣኤ ላይ የተመሠረተና ከዚህም ውጪ ሲሆን ከንቱና እንደሚፈርስ ቤት መሆኑን አስታውሰዋል።
ር.ሊ.ጳ. የእለተ ረቡዕ አስተምህሯቸውን ሐዋሪያዊ ቡራኬ በመስጠት ከደመደሙ በኋላ ከ15 ደቂቃ በላይ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው በመጨረሻም ለሕጻናትንና አካል ጉዳተኞችን ሰላምታን ሰጥተዋል።
- 27 March 2013
ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ከቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው ጋር ተገናኙ
"የትሕትና እና የርኅራኄ መንፈስ አውርሰውናል"
ር.ሊ.ጳ. ፍራነቼስኮስ አዲሱ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እረኛ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው ጋር ቅዳሜ መጋቢት 14 ጠዋት ተገናኝተዋል።
በዚህ ግንኙነታቸው ወቅት ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ "እኛ ወንድማማቾች ነን" ሲሉ ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል። የቅድስት መንበር ፕሬስ ኀላፊ አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ለቫቲካን ሬድዮ በሰጡት ምስክርነት የሁለቱን አባቶች ግንኙነት "በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ" ብለውታል። ሁለቱም ጎን ለጎን ተንበርክከው በቤተ ጸሎት ውስጥ ጸሎት ካደረሱ በኋላ ወደ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የበጋ ጊዜያዊ ማረፊያ ማለትም ካስተል ጋንዶልፎ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ለአንድ ሰዓት የዘለቀ ምስጢራዊ ውይይት አድርገዋል።
አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ እንደገለጹት ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው በአገልግሎት ዘመናቸው ላሳዩት የትሕትና መንፈስ ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ የትሕትና አርአያ የሆነችውን የቅድስት ድንግል ማርያም ምስል በስጦታ ተበርክቶላቸዋል። ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በዚህ ጊዜ ባሰሙት ንግግር "የትሕትና እና የርኅራኄ መንፈስ አውርሰውናል" በማለት ሃሳባቸውን ለቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው ገልጸውላቸዋል።
አባ ፌዴሪኮ አክለው "የቅዳሜው ግንኙነት በታላቅ ፍቅር እና በጥልቅ የአንድነት መንፈስ የታጀበ ነበር" ካሉ በኋላ "አጋጣሚው ለቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው ለአዲሱ ር.ሊ.ጳ ለመታዘዝ የገቡትን ቃል የሚያድሱበት እና አክብሮታቸውን የሚገልጹበት በተመሳሳይም ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ እና መላው የቤተ ክርስቲያን ሕዝብ ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው ላበረከቱት አገልግሎት ምስጋና የሚያቀርቡበት አክብሮታቸውንም የሚገልጹበት የተቀደሰ አጋጣሚ ነበር" ብለዋል።
- 15 March 2013
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ማን ናቸው?
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ማን ናቸው?
የተወለዱት እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 1936 ዓ.ም. በአርጀንቲና ዋና ከተማ ቦነስ አይረስ ሲሆን እሳቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው 5 ልጆች አሏቸው
- ወላጅ አባታቸው የባቡር መንገድ መሀንዲስ ነበሩ
- የአሁኑ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ የቀድሞው ሆርኼ ማሪዮ ቤርጎሊዮ የኬሚካል ምህንድስና ምሩቅ ሲሆኑ በኋላ ላይ ግን እ.ኤ.አ. በ1958 ዓ.ም. የJesuit (የኢየሱሳውያን) ማኅበርን የሴሚናሪ /ዘርአ ክህነት/ ማእከል ተቀላቅለዋል
- በ32 ዓመታቸው የኢየሱሳውያን ማኅበር ካህን ሆኑ
- በወጣትነት ዘመናቸው በመተንፈሻ አካላት ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት አንደኛው ሳንባቸው ሊወጣ ችሏል
- እ.ኤ.አ. በጥቅምት 1992 ዓ.ም. በብጹእ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ዘመን ጵጵስናን ተቀብለው የቦነስ አይረስ ከተማ ረዳት ጳጳስ በመሆን አገልግለዋል...
- 13 March 2013
"አዲስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አግኝተናል!"
"አዲስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አግኝተናል!"
ዛሬ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. አመሻሹ ላይ በቫቲካን ከሚገኘው ሲስቲና ቤተ ጸሎት ጭስ ማውጫ ነጭ ጭስ መውጣቱ ለዓለም የአዲስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትን መመረጥ ያወጀ ሲሆን ከዚያም ከአንድ ሰዓት በኋላ አካባቢ በተለመደው ሥርዓት በደብረ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕንጻ መስኮት እጩ ከነበሩት 115 ካርዲናሎች ውስጥ 2/3ኛውን ደምጽ ማለትም ከ77 የምርጫ ድምጽ በላይ በማግኘት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ 265ኛው የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆን በዚህ መንበር ላይ ሆነው እንዲያገለግሉ የተመረጡት ማን እንደሆኑ ተገለጠ።
አዲስ የተመረጡት ር.ሊ.ጳጳሳት አርጀንቲናዊው የቦነስ አይረሱ ጳጳስ ካርዲናል ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ ሲሆኑ የ77 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው። በአዲሱ ጴጥሮሳዊ አገልግሎታቸውም ፍራንቼስኮ /ፍራንሲስ/ የሚል ሥያሜን የወሰዱ ሲሆን ከ1300 ዓመታት ወዲህም ከአውሮጳ ውጪ የሆነ ር.ሊ.ጳ. ሲመረጥ እርሳቸው የመጀመሪያው ናቸው። እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከኢየሱሳውያን ማኅበር ለዚህ ኀላፊነት የተመረጡ የመጀመሪያ ር.ሊ.ጳ. ናቸው። ተጨማሪ የሕይወት ታሪካቸውን ይዘን በሌላ ዘገባ እንመለሳለን። እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን አሁንም በመልካም እረኝነቱ ይጎብኝልን ስለ ሰጠንም እረኛ ይመስገን!
- 07 March 2013
የቅዱስ አባታችን ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛውን ሕይወት የሚዳስስ ምርጥ ዝግጅት ያድምጡ
ከሸገር 102.1 fm ራድዮ "መቆያ" ከሚለው የሰሞኑ ዝግጅት የተገኘውን የቅዱስ አባታችን ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛውን ሕይወት የሚዳስስ ምርጥ ዝግጅት ያድምጡ። ይህን ዝግጅት በሚያዳምጡበት ጊዜ አንዳንድ ጊዜ ጳጳስ አሊያም ሊቀ ጳጳሳት የሚል ለቤኔዲክቶስ 16ኛው የተሰጠውን መጠሪያ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሚል እንዲረዱት ይሁን። መልካም ማዳመጥ! ይህን አድራሻ ይጫኑት http://www.ethiocist.org/Audio/Benedict_16.mp3
- 05 March 2013
ለር.ሊ.ጳ. ምርጫ ዝግጅት የመጀመሪያው የካርዲናሎች ጉባኤ ተካሄደ
ከቤኔዲክቶስ 16ኛው የአገልግሎት ማቋረጥ በኋላ የመጀመርያው የብፁዓን ካርዲናሎች ጉባኤ ሰኞ ጥዋት በካርዲናሎች አፈ ጉባኤ ብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ሶዳኖ መሪነት በቫቲካን ከተማ በጳውሎስ 6ኛው አደራሽ ተካሄደ፡፡ ከሰዓት በኋላም በአስራ አንድ ሰዓት ሁለተኛው ጉባኤ እንደሚካሄድ ከቅድስት መንበር የወጣ ዜና አመልክቷል፡፡ ክቡር አባ ፈደሪኮ ሎምባርዲ የቅድስት መንበር የዜናና የሕትመት ክፍል ኃላፊና የቫቲካን ሬዲዮ ዋና አስተዳዳሪ ከአንደኛው ጉባኤ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
እንደ አባ ፈደሪኮ ሎምባርዲ መግለጫ ይህ ጉባኤ ር.ሊ.ጳ. ለመምረጥ ለሚካሄደው የዝግ ጉባኤ (ኮንክሌቭ) ማዘጋጃ ነው፣ በዚሁ ጉባኤ 142 ካርዲናሎች ተሳትፈዋል ከእነዚህም ውስጥ 103 ሊመርጡና ሊመረጡ የሚችሉ መሆናቸውንም አመልክተው ሌሎች 12 ሊመርጡና ሊመረጡ የሚችሉ ካርዲናሎች ማምሻውን እንደሚደርሱ አስገንዝበዋል፡፡
ዛሬ ጠዋት የተካሄደው ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና በሚለው ጸሎት እንደተጀመረና ጉባኤውን የካርዲናሎች አፈ ጉባኤ እንደከፈቱት ሁሉም ካርዲናሎች በኅብረትና በተናጠል ቃላ መሃላ መፈጸማቸውን አመልክተዋል፣ በጉባኤው የተገኙ መንበረ ጴጥሮስ ክፍት ሆኖ በሚቀርበት ጊዜ ር.ሊ.ጳ እስከሚመረጡ ድረስ የመንበረ ሐዋርያው ቤት ተጠሪ ማለትም ካመርለንጎ ብፁዕ አቡነ ታርቺዝዮ በርቶነ የቤተ ጳጳሱ ሱባኤ ሰባኪ የነበሩ ጥቀ ክቡር አባ ራኒየሮ ካንታላሜሳ በማታው ክፍለጊዜ ጉባኤ የመጀመርያውን አስተንትኖ እንዲመሩ ባቀረቡት ኃሳብ ሁላቸው አባቶች ተስማመተዋል፣ ከዚህ በመቀጠል የካርዲናሎቹ ጉባኤ ለልሂቀ ር.ሊ.ጳ ቅዱስነታቸው የምስጋና መልእክት እንደሚጽፉላቸውም ተስማምተዋል፣
በዛሬው ጉባኤ ከተደረጉ ዋና ዋና መሰረታዊ ሃሳቦች አንዱ ለመንበረ ሐዋርያ ተጠሪ የሚረዱ ሶስት ካርዲናሎችን መርጠዋል፣ ለአቡናት ሥርዓት ብፁዕ ካርዲናል ሬ ለካህናት ሥር ዓት ብፁዕ ካርዲናል ሰፔ ለዲያቆና ሥርዓት ብፁዕ ካርዲናል ሮዴ ተመርጠዋል፣ እነኚሁ ሶስት ካርዲናሎች ከአሁን በኋላ በሚካሄዱት ልዩ ጉባኤዎች የመንበረ ሐዋርያ ተጠሪውን ይረዳሉ፡፡
ምንጭ፡- ቫቲካን ራድዮ
- 11 February 2013
ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የመንበረ ጴጥሮሳዊ አገልግሎታቸውን እንደሚያቋርጡ አስታወቁ።
የካቲት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. - ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የመንበረ ጴጥሮሳዊ አገልግሎታቸውን ከየካቲት 21 2005 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚያቋርጡ ዛሬ ጠዋት አስታወቁ።
በቫቲካን ለተሰበሰቡ ካርዲናሎች ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው ካሰሙት ንግግር ውስጥ "በእግዚአብሔር ፊት በተደጋጋሚ ኅሊናዬን ከመረመርኩ በኋላ ከእድሜዬ እርጅና የተነሣ የመንበረ ጴጥሮስ ኀላፊነቴን ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ እንደሌለኝ ርግጠኛ ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ" የሚል ይገኝበታል።
ስለዚህ አገልግሎት መንፈሳዊ ጎን ሲናገሩም "ይህ አገልግሎት ከቃላትና ከድርጊቶች በተጨማሪ መሠረታዊ መንፈሳዊ ተፈጥሮ ያለው መሆኑንና በመሰቃየትና በጸሎትም እንደሚከናወን ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ ሆኖም ግን በፈጣን ለውጦችና የእምነትን ሕይወት በጥብቅ የሚሹ ጥያቄዎች በተሞላች ዓለም መንበረ ጴጥሮስን ለመምራትና ወንጌልን ለማወጅ የአእምሮም ሆነ የአካል ጥንካሬ አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም ከቅርብ ወራት ወዲህ በአደራ የተሰጠኝን አገልግሎት ለመወጣት ብቁ ያለመወሆኔን እስገነዘብ ድረስ እነዚህ ጥንካሬዬዎቼ ተዳክመዋል።" በማለት ከስምንት ዓመታት በፊት የተረከቡትን የአገልግሎት መንበር ከየካቲት 21 2005 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ጀምሮ እንደሚለቁና ከዚያም ወጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ የአዲስ ር.ሊ.ጳ. ምርጫ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። በቦታው ለተገኙት ካርዲናሎች በዚህ የአገልግሎት ዘመን ስላደረጉላቸው ትብብር አመስግነው እሳቸውም በበኩላቸው ለነበራቸው ጉድለቶች በሙሉ ይቅርታን ጠይቀዋል።
በመጨረሻም "ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ዋና እረኛዋ ለሆነው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠባቂነት እናማጽናለን፤ እንዲሁም ቅድስት እናቱን ማርያምን ካርዲናል አበውን አዲስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ በሚያደርጉት ሂደት በአሳቢነቷና በጥንቃቄዋ እንድትረዳቸው እንለምን። እኔንም በተመለከተ የእግዚአብሔርን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎት በተሰጠ ሕይወት አገለግል ዘንድ ምኞቴ ነው።" በማለት ደምድመዋል።
በቤተ ክርስቲያናችን ሕገ ቀኖና (ላቲናዊው) ቀኖና 332 አንቀጽ 2 ላይ "የሮማው ርእሰ ሊቀ ጳጳሳት የአገልግሎት መንበራቸውን ከለቀቁ ይህ ውሳኔ ብቃት ይኖረው ዘንድ በነጻነት የተደረገና በተገቢ ሁኔታ የተገለጸ መሆን ይገባዋል እንጂ ከሌላ ከማንም ተቀባይነትን (መጽደቅን) አይፈልግም" የሚል መብት አለ። ከ 6 ክፍለ ዘመናት (ከ600 ዓመታት) ወዲህ ይህን መብት ለመጠቀሙ የመጀመሪያው ሲሆኑ ለመንበረ ጴጥሮስ ሢመት ሲመረጡም በጣም እድሜያቸው ከገፉ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አንደኛው ናቸው።
እኛም ከላይ የተገለጸው ጸሎታቸውና ምኞታቸው እውን ይሆን ዘንድ እንጸልይ።
- 07 January 2013
ሁላችን በጌታችን ፍቅር ልንሸነፍ ይገባናል!
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብ. አቡነ ብርሃነየሱስ የ2005 ዓ.ም. የጌታችን የልደት በዓል መልእክት
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
''እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኃል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡ ምልክቱም ይህ ነው፣ በመታቀፊያ ጨርቅ የተጠቀለለ ሕፃን በበረት፣ በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ ተኝቶ ታገኛላችሁ''፡፡ (ሉቃስ 2፡11-12)
የተወደዳችሁ ምዕመናን
ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች
በአገር ውስጥና እንዲሁም ከአገር ውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች
በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሰዎች በሙሉ
በመጀመሪያ እንኳን ለ2005 ዓ.ምየጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት ለመላው ካቶሊካውያን ምዕመናንና ክርስቲያኖች መልካም ምኞቴን እየገለጽኩ ለዚህች ቀን ላደረሰን እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይድረሰው እላለሁ፡፡ እንደሚታወቀው እያንዳንዱን መንፈሳዊ በዓል የምናከብረው በበለጠ ወደ መንፈሳዊነት በመቅረብ በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት በእርሱ እንድንባረክ ነው፡፡
የክርስቶስ ልደት ለኛ ለክርስቲያኞች ታላቅ ዜና ነው፡፡ ይኸውም ለሰው ልጆች አጋርና መድኃኒት ሆኖ በመምጣቱ እግዚአብሔርን ለማግኘትና በቤተልሔም መወለዱንም በማሰብ ራሳችንን በትህትና ዝቅ ማድረግ ይገባናል፡፡ እርሱ ብልፅግናችን ስለሆነ ክብርና ምስጋና ልናቀርብለት ይገባናል፡፡ ፈጣሪያችን እኛ ሰዎችን በመውደዱ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል፤ ይህም የሆነበት እግዚአብሔር የጠፋውንና በኃጢያት የወደቀውን ሰው ከራሱ ጋር በማስታረቅ የጠፉት በጐች ወደርሱ ይመለሱ ዘንድ ነው፡፡
''የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአል'' (ሉቃስ 19፡ 10)
የክርስቶስ መወለድን ተከትሎ ቤተክርስቲያን ተወልዳለች፡፡ እርሷም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ትሠራለች፣ በመሆኑም ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ለመላው ካቶሊካውያን ምዕመናን ከጥቅምት 1/2005 ዓ.ም እስከ ኅዳር 14/2006 ዓ.ም ያለውን ዓመት ''የእምነት ዓመት'' ብለው በመሰየም የዓለም ካቶሊካውያን ምዕመናን ሃይማኖታቸውን በእምነት ምስክርነት ላይ እንዲያውሉ ማወጃቸውን አናስታውሳለን፡፡ እኛም ይህንን ጥሪ ተቀብለን ለመፈፀም እያንዳንዱ ክርስቲያን በግሉ፣ በቤተሰቡና በቁምስናውና በአጠቃላይ በቤተክርስቲያን ውስጥ እምነቱን በማሳደግ መንቀሳቀስ እንደሚገባው ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ሁላችን በጌታችን ፍቅር ልንሸነፍ ይገባናል፡፡ ሕይወታችንም የእርሱ ማደሪያ ሊሆን ይገባል፣ ለዚህምሁላችንም ወደ ራሳችን በመመልከት የእርሱ የልጅነት መንፈስ በውስጣችን አለ ወይ ብለን እንጠይቅ፡፡ምክንያቱም መንፈሳዊነት ወደ ውስጥ ከመመልከት ራስን ከመመርመርና ከመውቀስ የሚጀምር በመሆኑ ዛሬምለእርሱ አልታዘዝም ያለ ልብ ካለን ያን ድንጋዩን ልባችንን እንቀይር ዘንድ የጌታ ልደት በእርሱ ፊቃድ በዚህዓመትም በቸርነቱ ብዛት የተሰጠን የምሕረት ጊዜ ነው፡፡ ለዚህም እንደ አምላክ ፊቃድ በመመላለስ እንድንኖርየእግዚአብሔር ቃል ያስገነዝበናል፡፡ በክርስቶስ ጽኑ ፍቅር መንፈሳዊ ሕይወታችንን
በመመሥረት እስከሞታችን ድረስ ልባችን በእርሱ ፍቅር ሊያዝ ይገበዋል፡፡ ይኽውም ''እርሱ ስለወደደን እኛም እንወደዋለንና'' (1ዮሐ .4፡ 19)
ብዙ ጊዜ እኛ በዓል በመጣ ጊዜ ከላይ የሚታየውን ለማስጌጥና ለማሳመር እንሯሯጣለን፡፡ ሆኖም ቅድሚያ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ነገር ውስጣችንን በማሳመር እውነተኛ የሆነ ውስጣዊ ለውጥ ለማምጣት ራሳችንን ለጌታ ማቅረብ ይኖርብናል፡፡
''የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል'' (1ዮሐ 2 ፡-15) በሚለው መሠረት እግዚአብሔር ችግረኞችን በማሰብ፣ በማብላትና በማጠጣት አቅማችን የቻለውን ያህል በማድረግ በዓሉን የእኛ ደስታ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ደስታ እንዲሆን እንድናደርግና ለዘለዓለም ሕይወት የሚያበቃንን የበጐ ተግባር በመፈፀም ችግረኞች የሚሹትን በጐውን ነገር በመሥራትና ቀረቤታችንን በማሳየት በዓሉን በታላቅ የመንፈሳዊነት ምግባር እንድናከብረው ለቤተክርስቲያናችን ምዕመናን በሙሉና በጐ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ መንፈሳዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በዚህ የጌታ የልደት በዓል ሁላችንም ተለውጠን የእግዚአብሔርን መንፈስ በመቀበል በእምነት በመጽናት ከራሳችንና ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር ጥሩ ክርስቲያን ሆኖ በመገኘት ከእርሱ ጋር ያለን አንድነት ፍፁም እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉት ልማታዊ እንቅስቃሴዎች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ተከናውነው ይፈጸሙና አገልግሎት መስጠት ይጀምሩ ዘንድ እየተካሄደ ያለውን የቁርጠኝነት እንቅስቃሴ እያደነቅን የተያዘውን ራዕይ ለማስፈፀም ሁሉም በየተሰማራበት ጠንክሮ እንዲሠራ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ወጣቶችም ሥራ ጠባቂ ብቻ ሳይሆኑ ሥራን ፈጣሪ ሆነው በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ተደራጅተው የሚሠሩትን ሥራ እንደዚሁም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመርዳት የበቁበትን አሠራር መንግሥት አሁንም በበለጠ አጠናክሮ በመቀጠል ወጣቱ በአገሩ የልማታዊ ዕድገት ላይ የበለጠ ተሳታፊ እንዲሆን ማሳሰብ እንፈልጋለን፡፡
እንደዚሁም የአገራችንን ገፅታ በባህልና በቱሪዝም መስክ የበለጠ ለማሳደግና ለማስተዋወቅ እየተደረገ ያለው ጥረት በፌደራልና በክልል ከተሞች የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ ህብረተሰባችን በኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ ያመጠውን ግንዛቤ እንዲሁም ደግሞ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚሰጠውን መልዕክት ትኩረት ሰጥቶ በማስተዋል እራሳችንን፣ ቤተሰባችንንና ህዝባችንን ከኤች አይቪ ኤድስና ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ ያላሰለሰ ጥረት እንድናደርግ ማስታወስ እንወዳለን፡፡
‹‹እንዲሁም እናት ሕይወት እየሰጠች የጤና አገልግሎት በማጣት አትሙት!!›› የሚለውን መፈክር ተግባራዊ እንዲሆን ሁላችንም እንትባበር፡፡ የተፀነሰውም ሕፃን እንክብካቤ አገኝቶ ይወለድ፣ይደግ፣ የአገር ተስፋ ነው፡፡ ሕይወት ከፅንስ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ ክቡር ናትና ለአረጋውያንና ለአረጋውያት አባቶቻችንና እናቶቻችን ተገቢውን ክብርና እንክብካቤ እንስጣቸው፡፡
በመጨራሻም በሆስፒታልና በቤታችሁ በህመም ላይ ለምትገኙ፣በማረሚያ ቤት ለምትገኙት፣ በሥራና በተለያዩ ምክንያት ከወላጆችና ከዘመድ እርቃችሁ ለምትገኙት፣ ለአገር ደኅንነትና ለሰላም ዳር ድንበርን በማስከበር ሥራ ላይ ለምትገኙት ወገኖች፣ ከአገር ውጭ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ በድጋሚ እንኳን ለ2005 ዓ.ም የጌታችን የመዲኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ፡፡ በዓሉም የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ ይሁንላችሁ በማለት ልባዊ ምኞቴን እገልጽላችኃለሁ፡፡
- 25 December 2012
በሰባት ዓመቱ ሕፃን ጆሴፍ ራዚንገር /የአሁኑ ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው/ ለሕፃኑ ኢየሱስ የተጻፈ የገና ደብዳቤ
በቅርቡ የተገኘው የሰባት ዓመቱ ሕፃን ጆሴፍ ራዚንገር /የአሁኑ ር.ሊ.ጳ ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው/ ለሕፃኑ ኢየሱስ የተጻፈ የገና ደብዳቤ ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ ያላቸውን መንፈሳዊነትና ካህን የመሆን ምኞታቸውን ያሳያል፤ እንዲህ ይነበባል፡-
“ውድ ሕፃኑ ኢየሱስ፣ ለሕፃናት ደስታን ታመጣለህና ፈጥነህ ወደ ምድር ና! ለእኔም ደስታን አምጣልኝ። የጸሎት መጽሐፍ፣ አረንጓዴ የቅዳሴ አልባስና የኢየሱስ ቅዱስ ልብን ስዕል ብታመጣልኝ ደስ ይለኛል፤ ጥሩ ልጅም እሆናለሁ።
ሰላም ሁን! ጆሴፍ ራዚንገር”
ሕፃኑ ጆዜፍ አረንጓዴ የቅዳሴ አልባስ የጠየቁበትን ምክንያት ካህኑ ታላቅ ወንድማቸው ሞንሲኞር ጆርጅ ራዚንገር ሲያስረዱ ጆሴፍና ወንድሞቻቸው እንደ ካህን በመሆን “እቃቃ” ይጫወቱ እንደነበረና የልብስ ስፌት ባለሙያ የነበሩት እናታቸውም የካህናት ዓይነት ልብስ በመስፋት ይተባበሯቸው እንደነበረ ገልጸዋል።
በደብዳቤው ውስጥ የተጠቀሰው ሌላው ነገር ደግሞ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ሲሆን ይህም ስእሉን መጠየቁ መሆኑንና የመላ ቤተሰቡ ልዩ መንፈሳዊነት እንደሆነ ታውቋል።
ይህ ደብዳቤ ር.ሊ.ጳ ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው ሬገንስበርግ ውስጥ የዩኒቨርስቲ መምህር በነበሩበት ጊዜ ይኖሩበት የነበረ ቤት እድሳት ሲደረግለት ሲሆን በእህታቸው ዘንድ ቆይቶ ይፋ የሆነውም ከአንድ ሳምንት በፊት ታኅሣሥ 9 ቀን ነው። ራዚንገር ይኖሩበት የነበረው ቤት በርሳቸው ስም ትንሽ ሙዚየም የተደረገ ሲሆን የር.ሊ.ጳ. ጸሐፊ እንዳሉት ር.ሊ.ጳ. በደብዳቤው መገኘት ደስ የተሰኙ መሆናቸውና ይዘቱም እንዳስፈገጋቸው ተነግሯል።
ምንጭ፡- http://www.ucatholic.com
More Articles...
- ሢመተ ክህነት በገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን አዲስ አበባ
- መንፈሳዊ ምድረ በዳነት ባጠቃው ወቅታዊው ዓለም ዳግም ክርስቶስን ማወጅ
- የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነው!
- የእግዚአብሔር ሕዝብ በደም ትስስር በመሬትና በአገር ድንበር የቆመ አይደለም
- "ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች በአንድነት ቆመው አመፅ እንዲበቃ የሚያደርጉበት ጊዜው አሁን ነው!"፡ ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው በሊባኖስ
- ሊቀ ጳጳሳት ብ. አ. ብርሃነየሱስ የ2005 ዓ.ም ርእሰ ዐዉደ ዓመትን በማስመልከት ለምእመናን ያስተላለፉት መልእክት፡፡
- ር.ሊ.ጳ. ቤኔዴክቶስ 16ኛው ለጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ህልፈት የኀዘን መግለጫ ላኩ።
- ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ምክንያት የሐዘን መግለጫ መልእክት አስተላለፉ

ዜናዎች


