Map St Joseph Cistercians

Top Panel

መጽሐፍ ቅዱስ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ ያሉ ጥናቶችና ሐተታዎች ቦታ

7. ጤነኛ በራስ መተማመን

Jeremiah 2

7. ጤነኛ በራስ መተማመን
“ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ። እኔም። ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም አልሁ። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ። ወደምሰድድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና። ብላቴና ነኝ አትበል።" ኤርምያሰ 1፡5-10፡፡

ኤርምያስ መናገር አልችልም ብሎ ደካማነቱን ከማወቁ የተነሣ በቅንነት ሲናገር የእግዚአብሔር መልስ ግን በኤርምያስ መተማመንን የያዘ ነበር፡፡ እኛ ስለእራሳችን የምናውቀውና እግዚአብሔር ስለኛ የሚያውቀው ምን ያህል የተራራቀ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
በተጨማሪም በእኛ ዘንድ ደካማነት ሆኖ የሚታየው ለእግዚአብሔር ግን ቁጥር ውስጥ የማይገባና የማያሳስብ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ጤነኛ በራስ መተማመን በእግዚአብሔር ፈት ከመቆም የሚመነጭ ነው፡፡ በራስ መተማመኔ የደከመ መስሎ ሲሰማኝ፣ ቀና ብዬ ለመሄድ ድፍረቱ ሲጎድለኝ ያደረግሁት ነገር ምን ነበር? ምን ዓይነት ዝንባሌ በውስጤ ሲቀሰቀስ ተሰማኝ?
ጤነኛ በራስ የመተማመን ስሜትስ ላይ እንዴት ልመለስ ቻልኩ?

በአባ ዳዊት ውብሸት

በድምፅ ለማዳመጥ ከታች ማጫወቻውን ይጫኑ (ንባብ  በዘማሪት ሕይወት መልአኩ)

 

Write comment (0 Comments)

“ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው”

“ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው” መዝሙር 119፡1ዐ5መጽሐፍ ቅዱስ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ  በ21ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ያስተማሩት ትምህርት

ከዚህ የሚከተለው ምክሬ በመዝሙር 1ዐ9፡1ዐ5 ላይ ሲሆን እርሱም ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው፤ የሚል ሲሆን ይህንን መልዕክት የተወደዱ ብጹዕ ጳጳስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከዚህ በታች እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፡፡ “እግዚአብሔርን በጸሎት የሚያመሰግን ሰው ቃሉ ለሕይወቱ ጨለማነቱን የሚያስወግድ ብርሃን ነው”፡፡

እግዚአብሔር እራሱን የሚገልፀው በሰዎች ታሪክ አማካኝነት ነው፤ እርሱ ለሰዎች ይናገራል፤ የሚናገረውም ቃሉ የመፍጠር ኃይል አለው፡፡ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ዳባር” የሚለው ቃል ሁለት ትርጉም ያለው ሲሆን እርሱም የእግዚብሔር ቃል እና መፍጠር የሚል ነው፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን ይፈጥራል፤ የፈጠረውንም ይናገራል በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለእስራኤል ልጆች የመሲሁን መምጣትና የአዲስ ኪዳን መቋቋም ሲያውጅ ቃል ስጋ በመልበስ እንደሆነ የገባውን የተስፋ ቃል በማፅናት ነው፡፡ ይህ አገላለጽ ዛሬ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ ለበሰ፤ ይህም ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነም ሁሉ ያለ እርሱ የሆነው አንድም የለም የሚል ነው፡፡

መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ፀሐፊዎችን የእምነት ልብ እንደከፈተ እንዲሁም ትርጉሙን ይረዱ ዘንድ የምዕመናንንም ልብ ይከፍታል፤ ይህም መንፈስ ቅዱስ በምስጢረ ቅዳሴ ካህናትን ኅብስቱንና ወይኑን ወደ ክርስቶስ ስጋና ደም የሚለውጡትን ቃላት ሲናገሩ በዚያ አለ፡፡ ምዕመናንም ሊኖሩና የሕይወታቸውን ጉዞ ሊጓዙ የሚችሉት በቃለ እግዚአብሔርና በክርስቶስ ሥጋና ደም ሲመገቡ ስለሆነ እነዚህ ሁለት ገበታዎች ሊለያዩ አይችሉም፡፡
ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው

መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ፀሐፊዎችን የእምነት ልብ እንደከፈተ እንዲሁም ትርጉሙን ይረዱ ዘንድ የምዕመናንንም ልብ ይከፍታል፤ ይህም መንፈስ ቅዱስ በምስጢረ ቅዳሴ ካህናት ኅብስቱንና ወይኑን ወደ ክርስቶስ ስጋና ደም የሚለውጡትን ቃላት ሲናገሩ በዚያ አለ፡፡ ምዕመናንም ሊኖሩና የሕይወታቸውን ጉዞ ሊጓዙ የሚችሉት በቃለ እግዚአብሔርና በክርስቶስ ሥጋና ደም ሲመገቡ ስለሆነ እነዚህ ሁለት ገበታዎች ሊለያዩ አይችሉም፡፡ ሐዋሪያት የተቀበሉትና ለእኛም ያወረሱን የመዳን ቃል በጣም ውድ የሆነና የከበረ ስለሆነ በቤተክርስቲያንም ሆነ ከቤተክርስቲያን ውጪ በጥንቃቄ እንድንጠብቅና ይህ አካሄድ እንዳይጠፋ ኃላፊነትን እንውሰድ፡፡

የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ የእግዚአብሔርን ቃልና ቤተክርስቲያናችሁን ውደዱ ይህንንም እንደ ትልቅ ሀብት በመቁጠር ትልቅ ዋጋ በመስጠት እንዴት ምስጋና ማቅረብ እንዳለባችሁ መልካምነትን ተማሩ፤ ፍቅርን በመከተል የእውነተኛ ደስታን መንገድ ለህዝብ በማሳየት ቤተክርስቲያንም ተልዕኮዋን ትወጣለች፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ለመኖር እውነተኛ ደስታን መፈለግና ማግኘት ቀላል አይደለም፤ ብዙውን ጊዜ የህዝብ አዝማሚያ በሀሳብ የገሃነም ምርኮኛ ነውና እነርሱ ነፃ የሆነም ሊመስላቸው ይችላሉ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በአሳሳች አስተሳሰባቸው ሲሄዱ የህይወታቸው ጉዞ ይጠፋባቸዋል፡፡ የተወደዱ አባታችን ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደስቀመጡት የሰውን ነፃነት ወደ እውነተኛ ነፃነት እንድንመራ ያስፈልጋል፡፡ በጨለማ የሚጓዝ የዓለም ህዝብ ወደ ብርሃን እንዲወጣ ያስፈልጋልና ኢየሱስም ይህንን ጉዞ አስተምሮናል “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥም ደቀ መዛሙትቴ ትሆናላችሁ፤ እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ዮሐ. 8፡3ዐ-31 እውነት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነፃ ያደርገናል ሕይወታችንንም ወደ መልካም ይመራዋል፡፡

 

bibbia-copiaየተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል በማሰላሰል መንፈስ ቅዱስ የልባችን አስተማሪ እንዲሆን አድርጉ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንደሰው አለመሆኑን ትረዳላችሁ፡፡ እናንተ እራሳችሁ እውነተኛውን አምላክ መምሰልን ትማራላችሁ እንዲሁም የራሳችሁንና የዓለምን ታሪክ ታውቃላችሁ፡፡ ከልብ የሚመነጭ መሆኑንም ታያላችሁ በዚያን ሰዓት ከእውነት የመነጨ ሙሉ የልባችሁን ደስታ ትቀምሳላችሁ፤በዚህ ዓለም ስትጓዙ ፈተናዎች፣ ችግሮች፣ ህመምም ይደርስባችኋል፤ በዚያን ሰዓት መዝሙረ ዳዊት እንደሚያስቀምጠው “እግዚአብሔር ሆይ ስቃዬ እጅግ ከባድ ነው” ልትሉ ትችላላችሁ፤ /መዝ. 119፡1ዐ7 ነገር ግን በዚያን ሰዓት ከዳዊት ጋር የሚቀጥለውን ስንኝ መጨመርን አትርሱ፤ “በተስፋ ቃልህ መሰረት በህይወት አኑረኝ፣ ስላንተ ሕይወቴ ለማሳለፍ ዝግጁ ነኝ፤ ህግህንም አልረሳም” መዝ. 1ዐ9፡1ዐ7-1ዐ9 የሚወደኝ አምላክ በቃሉ ሁልጊዜ ከጐናችን በመሆኑ ይደግፈናል፤ የፍርሃትን ጨለማ ከልባችን ያስወግዳል በፈተና ጊዜ መንገዳችንን ያበራል፡፡


የዕብራውያን መልዕክት ፀሀፊ እንደፃፈው “በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል ህያውና የሚሰራ ነው ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ ስለታም ነው ነፍስንና መንፈስን ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ የሚቆራርጥ ነው” ዕብራውያን 4፡12 የእግዚብሔር ቃል በጥንቃቄ ለማዳመጥ አስፈላጊና ለመንፈሳዊ ትግላችን እንደ መንፈሳዊ መሣሪያ መውሰድ ያስፈልጋል፣ ትግላችን ውጤታማ የሚሆነው ስንማርና ስንታዘዝለት ነው፡፡ በትምህርተ ክርስቶሳችንም እንደተገለፀው “ለመጽሐፍ ቅዱስ መታዘዝ ማለት ማዳመጥና ቃሉን በህይወታችን መተርጐም ነው” ምክንያቱም እውነት በእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ እርሱ ራሱ እውነት ነው፤ አብርሃምም የእግዚብሔርን ቃል በመስማት ታዘዘለት፣ ሰለሞንም እርሱ እንዳሳየው ጥልቅ በሆነው ስሜትና ጥበብ ባለው ቃል ይገልፀዋል “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ ጠቢብ ንጉስ “ለእኔ ለአገልጋይህ የመረዳት ልብ ስጠኝ” አለው 1ኛ ነገስት 3፡5-9 የመረዳት ልብ ለማግኘት ማለት ልቡን ለማዳመጥ ማሰልጠን ነው፡፡ ይህም የሚገኘው የእግዚአብሔር ቃል በዘላቂና በጥልቀት በማሰላሰልና በተጠናከረ ሁኔታ በትዕዛዙ መሰረት በመቀጠል ነው፡፡

 

የተወደዳችሁ ወጣቶች አሁን የማስገነዝባችሁ እናንተ ራሳችሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንድታለማምዱ ከእጃችሁ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይለይና የግላችሁ ዕቃ አድርጋችሁ በመንገዱ እንድትከተሉ ነው፤ እርሱንም በማንበብ ክርስቶስን ታውቃላችሁ በዚህ ረገድ ቅዱስ ሄሮኒሞስ እንደሚለው “መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ክርስቶስን አለማወቅ ነው”

ቃለ እግዚአብሔርን ለማጥናትና ለመቅመስ ልዩ ስጦታ አለ እርሱም ንባበ መለኮት ይባላል፡፡ እርሱንም እናንተ ደረጃ በደረጃ በመውሰድ የሕይወታችሁን መንፈሳዊ ጉዞ ያሳድጋል፡፡

  • 1ኛ ደረጃ ማንበብ፡- ማንበብ ማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመውሰድ በድጋሚ በጥልቅ ማንበብና ዋናውን መልዕክት ማጥናት ነው፡፡
  • 2ኛ ደረጃ ማሰላሰል፡- በማሰላሰል ጊዜ በስሜት ነፍስን ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ቃሉ ዛሬ ለእኔ ምን ይላል የምንልበት ጊዜ ነው፡፡
  • 3ኛ ደረጃ መጸለይ፡- መጸለይ ማለት በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር የምንነጋገርበት ደረጃ ነው፡፡
  • 4ኛ ደረጃ መመሰጥ፡- በዚህ ደረጃ ጊዜ ልባችንን ለጌታ መምጣት የምንከፍትበት ጊዜ ነው፡፡ ቃሉም “ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችን እስከበራ ድረስ በጨለማ እንደሚበራ መብራት አድርጋችሁ ብትጠነቀቁለት መልካም ነው” 2ኛ ጴጥሮስ 1፡19
  • 5ኛ ደረጃ ማካፈል፡- ቃሉን ማንበብ ማጠናትና ማሰላሰለ ከዚያም ወደ ሕይወት ማስገባት በክርስቶስ ፅኑ ወደ ሆነው እምነት ይጋብዘናል እርሱ ማለት ደግሞ ማካፈል ነው፡፡

ቅድስ ያዕቆብ እንደለው “ቃሉን በሥራ ላይ የምታውሉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ ቃሉን ሰምቶ በስራ ላይ የማያውለው ሰው የተፈጥሮ ፊቱን በመስታወት እንደሚያይ ሰው ነው ምክንያቱም ይህ ሰው ፊቱን በመስታወት ካየ በኋላ ይሄዳል እንዴት እንደሆነም ወዲያውኑ ይረሳዋል፡፡ ነገር ግን ነፃ የሚያወጣውን ፍፁም ሕግ ተመልክቶ በእርሱ የሚፀና እርሱንም ሰምቶ መርሳት ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውለው ሰው በሥራው የተባረከ ነው” ያዕቆብ 1፡ 22-25 “ቃሉን ሰምቶ በስራ ላይ የሚያውል ሁሉ ቤቱን በአለት ላይ የሰራውን ብልህ ሰው ይመስላል ማንም ቃሌን የሚሰና በስራ ላይ የሚያውለው ኢየሱስ እንዳለው ልክ በአለት ላይ ገንብቷል” ማቴዎስ 7፡24 ኃይለኛ ነፋስ ቢመጣ እንኳን አይወድቅም፡፡

ሕይወታችሁን በክርስቶስ ላይ መገንባት ቃሉን በደስታ መቀበልና በተግባር ላይ ማዋል የሕይወታችሁ እቅድ ይሁን፡፡ ሕይወታችሁን በክርስቶስ ላይ መገንባት በዚህ ዓለም ለሚነሱ ችግሮች ራሳችሁን እንደ አዲስ ሐዋሪያት በማዘጋጀትና በስራ በመተግበር ጊዜያችሁን በመጠቀም ወንጌልን በጥልቀትና በስፋት ለማሰራጨት ችሎታ ያላችሁ እንድትሆኑ ይረዳችኋል፡፡ ክርስቶስም የሚጠይቃችሁ ይህንኑ ነው፣ ቤተክርስቲያንም የምትጋብዛችሁ ይህንን ለዓለም በማስገንዘብ እንድትጠብቁ ነው፡፡ ኢየሱስ ከጠራችሁ አትፍሩ፣ በተለይም እሱን እንድትከተሉት የሚጠይቃችሁ ሕይወታችሁን እንድትሰጡ ወይም በክህነት እንድታገለግሉ ሲጠራችሁ አትፍሩ በእርሱም ታመኑ አያሳፍራችሁም፡፡

የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ አሁን በዚህ ሰዓት የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማትና መንፈስ ቅዱስን በመለመን ምስክሮች ትሆኑ ዘንድ ያለምንም ፍርሃት እስከ ዓለም ፍፃሜ ወንጌልን እንድታውጁ እጋብዛችኋለሁ፡፡ እመቤታችን ማርያም ከሐዋሪያት ጋር በመንፈስ ቅዱስን ትጠብቅ ነበር ቃሉን በልቧ በማሰላሰልና በሙሉ ሕይወቷ በመፈፀም ትኖር ነበር የእግዚብሔርን መኖር በግልፅ ልታውጅ በመታዘዝና በእምነት ተነሳሳች፣ በእምነቷና በጸናው ተበስፋዋ ሳትሰለች የእግዚብሔርን ቃል ታሰላስል ነበር፣ በአንድነት በጸሎት እንድንተጋ ከሙሉ ልቤ በአባታዊ ቡራኬዬ እባርካችኋለሁ፡፡

Write comment (0 Comments)

በመጽሐፍ ቅዱስ ዙርያ

በእናንተ ስላለው ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።  1ጴጥ. 3:15

በመጽሐፍ ቅዱስ ዙርያ የሚዘወተሩ ጥያቄዎች

ከዚህ በታች በጥያቄና መልስ መልኩ የቀረበው ትምህርት ሆሣዕና በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ የሲታውያን ገዳም መነኮሳን የተዘጋጀ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ዙርያ በሚነሡ አንዳንድ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ነው። አጠር ያለና ብዙ ነጥቦችን የሚዳስስ ቢሆንም እንኳ በምንም መልኩ ግን ሁሉን ያካተተ ነው ለማለት አንችልም። ስለዚህ በዚህ ትምህርት ውስጥ የተነሡም ሆነ ያልተነሡ አንዳንድ ነጥቦችን እንዳስፈላጊነታቸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደፊት ሰፋ አድርጎ የማየቱ ሁኔታ ይኖራል ብለን እናስባለን። ያንብቡት…

1-ከአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የጻፈው መጽሐፍ አለን? ሐዋርያትስ እንዲጽፉ አዝዟቸዋልን?

ጌታችን መጽሐፍ አልጻፈምም ሐዋርያትም እንዲጽፉ አላዘዘም። ነገር ግን የእርሱን ትምህርት እንዲያስተምሩና እንዲሰብኩ አዟቸዋል። በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ የተሰጠው እሱ (ማቴ.28:18) መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጠ፤ እርሱም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር እንደሚሆን አረጋግጧል።

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻ ለደኅንነት በቂ ቢሆን ኖሮ ራሱ በቀጥታ በመጻፍም ሆነ ሐዋርያት እንዲጽፉ በማዘዝ መንገድን ባዘጋጀ ነበር። ለቤተ ክርስቲያኑ የሰጠው ትእዛዝ የርሱን ትምህርት እንድታስተምር ነው፤ ጽሑፍ የትምህርት አንዱ ክፍል እንጂ የትምህርት ሁሉ ድምዳሜ አይደለም።

2-ከሐዋርያቶች ውስጥ ስንቶቹ ወይም በአዲስ ኪዳን ከጌታ ዕርገት በኋላ ወዲያው የተነሡ ሰባክያን ሌሎች ጸሐፊዎች ዛሬ አዲስ ኪዳን የምንለውን መጽሐፍት ጻፉ?

ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል አዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ መጻሕፍትን የጻፉ የተወሰኑ ናቸው። እነዚህም፦ከሐዋርያት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ይሁዳ፣ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ሲሆኑ ከጌታ ዕርገት ኋላ ከተንሡ ሰባክያን ደግሞ ጳውሎስ ብቻ ነው አዲስ ኪዳን ውስጥ ጽሑፍ የተዉልን።

እያንዳንዱ እንዳሻው በግል የሚተረጉመው መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛ የእምነት መመሪያ ከሆነ ትምህርታቸውንና መልእክታቸውን አዲስ ኪዳን ውስጥ ሳይጽፉልን በማስተማርና በመስበክ ብቻ ዕድሜያቸው ያለፈ የጥንት ሐዋርያትም ሆኑ ከዚያ በኋላ የተነሡ ሰባክያን ሁሉ ከትክክለኛ መንገድ ወጥተዋል ማለት ነው። <<መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ>> የሚሉ ሰዎች አዎ የሚል መልስ ካልሰጡ ራሳቸውን ይቃወማሉ ማለት ነው።

3. ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን አስተማሪ ነበረች ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ቤተ ክርስቲያን?

<<እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው>> ሮሜ 10:17።

<<ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው፤ እነሆ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ>> ማቴ.2819-20።

<<ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ>> ማር. 16:15።

እነዚህ የጌታችን ትእዛዛትን ካስተዋልን <<መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ>> የሚለው የተወሰኑ ሰዎች  አመለካከት መሠረተ ቢስ መሆኑን ያሳያል። ምክንያቱም አዲስ ኪዳን እንደ መጽሐፍ ከመቀመጡ በፊት አስተማሪ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ ይህም ማለት አዲስ ኪዳን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሲሆን ትምህርቷ ሁሉ ግን እሱ ውስጥ ይገኛል ማለት አይደለም።

4-ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱ እንዲያስተምሩ ባዘዛቸው ትእዛዝና በአዲስ ኪዳን መካከል መሠረታዊ ልዩነት አለን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተላለፈውን ትውፊት ሁሉ ሐዋርያት እንዲያስተምሩ፤ ያዘዛቸውንም ሁሉ እንዲያስተላልፉ አዟቸዋል (ማቴ. 28:20)። ቤተ ክርስቲያን ጌታዋ የነገራትን ሁሉ ማስተማር አለባት (ዮሐ.14:26)። ነገር ግን አዲስ ኪዳን ራሱ የኢየሱስን ትምህርት ሁሉ እንዳልያዘ ይመሰክራል፦ <<ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር አለ፤ ሁሉም ቢጻፍ ለተጻፉት መጽሐፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ነበር ይመስለኛል>> ዮሐ.21:25።

በዚህ መሠረት <መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ> የምንል ከሆነ ከአዲስ ኪዳን ውጭ ምንም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን የማንቀበል መሆናችንን እንመሰክራለን። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሙሉውን እውነት ሳንይዝ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት እምነት ተከታዮች ነን ማለት ያዳግታል።

 

5. አዲስ ኪዳን በቀጥታ ያልተጻፉ የክርስቶስ ሥራዎችና ትምህርቶች እንዳሉ ይጠቁማልን?

<<ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀመዛሙርቱ ፊት አደረገ>> ዮሐ.20:25።

እነዚህ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያልተካተቱ የክርስቶስ ብዙ ምልክቶች ሙሉ የሚያደርጋቸው ነገር ያስፈልጋቸዋል። ይህም ሐዋርያት በቃል ያስተላለፉት ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተዘግቦ የምናገኘውና በክርስትና ታሪክም <ትውፊት> በመባል የሚታወቀው ነው። ይህ ቃል መሠረቱ የግእዝ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም የተሰጠ፣ የተላለፈ…እንደማለት ነው።

 

6. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያት ያስተማሩት ግን በአዲስ ኪዳን ያልተጻፈው እውነት ምን ሆነ?

ከላይ እንደጠቀስነው ይህን ያልተጻፈውን እውነት ቤተ ክርስቲያን በጥንቃቄ ይዛ እስካሁን ድረስ ትውፊት ተብሎ በሚታወቀው ታሪኳ አቆይታዋለች።

<<እንግዲያውስ ወንድሞች ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ። በቃላችንም ቢሆን በመልእክታችን የተማራችሁትን ትውፊት ያዙ>> 1ተሰ.2:15

<<ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን፤ ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ>> 2ጢሞ.2:2

ስለዚህ ሙሉ የክርስቶስን ትምህርት ለማግኘት አዲስ ኪዳን ብቻ አይበቃም። በአዲስ ኪዳን ብቻ የተመሠረተ እምነት ማደግና መገንባት ካለበት ትውፊት ያስፈልገዋል።

 

7. አዲስ ኪዳን እንደ አንድ መጽሐፍ መቼና የት ተዘጋጀ?

በ397 ዓ.ም. አካባቢ በሰሜን አፍሪካ በካርተጅ ጉባኤ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተዘጋጀ። ካቶሊክ ያልሆኑት ሁሉ አዲስ ኪዳንን ያገኙት ከዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ክርስቲያኖች መልክ  ያልያዙ ጽሑፎች ብቻ ነው የነበራቸው።

መጽሐፍ ቅዱስን ከዚች ቤተ ክርስቲያን የተቀበሉ ሁሉ ሌላውን ትምህርቷን ያለመቀበላቸው ሁኔታ ሊስማማ አይችልም።

 

8. አዲስ ኪዳን በመጽሐፍ መልክ ሳይዘጋጅ የቆየባቸው ብዙ ዓመታት ወቅት የአዲስ ኪዳን ጽሑፋት ሁኔታ እንዴት ነበር?

ከላይ ከተጠቀሰው ዓመት በፊት ብትን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በተለያዩ ካቶሊክ ምእመናን እጅ ይገኙ ነበር። በቤተ ክርስቲያን ላይ የነበረው ስደት የመጽሐፍቱን ትክክለኛነት መርምሮ በአንድ ላይ ለመጠረዝ አልፈቀደም ነበር። በ397 ዓ.ም. ይህ ሥራ ሊሠራ የተቻለው ንጉሠ ነገሥት ቁስጥንጢኖስ ክርስትና በግዛቱ በነጻነት እንዲዘወተር በ313 ዓ.ም. ፈቅዶ ሰላም በመስፈኑ ነበር።

ይህ ሁኔታ እንደገና የሚያሳየው ቢያንስ እስከ 400 ዓ.ም. ድረስ <መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ> የሚል እምነት መሠረት የሌለው መሆኑን ነው።

9. ቤተ ክርስቲያን ጥንት አዲስ ኪዳን መጽሐፍት እነዚህ ናቸው ብላ ስትወስን ያጋጠማት ሌላ ችግር ምንድን ነበር?

በወቅቱ ሌሎችም የተጻፉ ብዙ መጽሐፍት ስለነበሩ ዋነኛው ችግር የነበረው የትኛው መጽሐፍ እውነተኛ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የያዘ መሆኑን መለየት ነበር። ሆኖም ጥንቃቄ የተሞላው ጥናት በማድረግና ራሷ በሆነው ጌታ በመመራት ውሳኔ ላይ ደረሰች። በዚያን ጊዜም ቢሆን ብዙ ካቶሊካውያን ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋንና ታሪክን በማጥናት በቅድስት ምድር(እስራኤል) ጊዜያቸውን ያሳለፉ ነበሩ፤ መጽሐፍትን በመለየቱ ሂደት የነዚህ ምሁራን ሚናም ትልቅ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ እንዳለው አመለካከት ቢሆን በዚያን ጊዜ የነበረች ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እነዚያን መጽሐፍት እያንዳንዱ ሰው በግሉ አንብቦ እንዲወስን መተው ነበረባት ማለት ነው። እንደዚያ ቢደረግ ኖሮ ዛሬ አዲስ ኪዳን የሚባል መጽሐፍ ባልኖረንም ነበር። የዚህም መዘዝ አንዲት በሁሉም ቦታ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን እንዳትኖር ያደርጋት ነበር።

 

10. የስህተት ትምህርት ከያዙት መጻሕፍት መካከል ሐቀኛና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉትን መለየት የማን ሥልጣን ነበር?

አስቀድመን እንደጠቀስነው በ397 ዓ.ም. በካርተጅ ባደረገችው ጉባኤ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተሰጣት ያለመሳሳት ስጦታ በመጠቀም በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት መጻፋቸውን ወሰነች። ቤተ ክርስቲያን ይህን ስታደርግ ያልተሳሳተች ከሆነ ዛሬም ቢሆን እምነትንና ሞራላዊ ሕይወትን በሚመለከት ስትወስን አትሳሳትም ማለት ነው። ይህ ስጦታ ባይኖራት ኖሮ አዲስ ኪዳን ባልኖረንም ነበር። ባለመሳሳቷም ምክንያት ዛሬ ተንሥቶ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ክፍል ትክክል አይደለም አስተካክላለሁ ለማለት የሚደፍር የለም። ስለዚህ ዛሬ በብዙ ስም ተለያይተው ለሚገኙ ካቶሊካውያን ያልሆኑ ወገኖች በሙሉ አዲስ ኪዳንን አዘጋጅታ ያቀረበች እርስዋ ናት።

11. እስከ 400 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ አዲስ ኪዳንን በግል እንደፈለጉ መተርጎም ይቻል ነበርን? የኅትመት መኪና እስከተገኘበት ጊዜስ የመጽሐፍ ቅዱስ ሂደት ምን ይመስል ነበር፤ ማንስ አስተላለፈው?

እስከ 400 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ አዲስ ኪዳንን በግል እንደፈለጉ መተርጎም አይቻልም ነበር፤ ምክንያቱም አዲስ ኪዳን የሚባል መጽሐፍ ራሱ እስከዚያ ዘመን ድረስ ስላልነበረ ማለት ነው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የኅትመት መኪና(ማተሚያ) እስከተጀመረበት 1440 ዓ.ም. ድረስ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና ኋላም የተለዩ ኦርቶዶክስ መነኮሳን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በብራና ላይ እየገለበጡ አድካሚ በሆነ ሥራ ሕይወታቸውን እያሳለፉ ከዘመን ወደ ዘመን ይተላለፍ ነበር። በዚህ ሁኔታ የሚባዛው መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት ሊሰራጭና ሰው እጅም ሊገባ ስላልቻለ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል በስዕል፣ በድራማና መሰል መንገዶች ታስተላልፍ ነበር። እንደፈለጉ የመተርጎሙም ዕድል ጠባብ ነበር። የኅትመት መኪና ከተገኘ በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ተለወጠ። የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርጭት ጨመረ በዚሁ መጠንም በፈለጉት አቅጣጫ የመተርጎም ስህተት እየተስፋፋ መጣ። ቤተ ክርስቲያን ለመጽሐፍ ቅዱስ ቦታ የማትሰጥ ሆኖ ሲንገር መስማቱ በጣም ያሳዝናል፤ ምክንያቱም እሷ የመጽሐፍ ቅዱስን ዋጋ ስለምታውቅና ስለምታከብር ነው ለ1500 ዓመታት በአድካሚ ሁኔታም ቢሆን ጠብቃ ያቆየችው።

12. <<አንድ እምነት አንድ መንጋ አንድ እረኛ>> የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት <<መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ>> በሚል አባባል የተኩ ሰዎች ይህን ለማድረግ ማን ሥልጣን ሰጣቸው?

መልሱን በሐዋርያው ጳውሎስ አፍ እግዚአብሔር ይናገራል፦

<<ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፤ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።>> ገላ.1:8

 

13. በታሪክ በሰፋ ሁኔታ <<መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ>> የሚለውን አመለካከትና በየግሉ የመተርጎም ልማድ ያስፋፋው ሉተር መሆኑ ይታወቃል፤ ታዲይ ይህን መሰል አካሄድ ምን ውጤት አስከተለ?

አሁንም መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት።

<<ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጥልና፤ ነገር ግን ጆሯቸውን የሚያሳክክ ስለሆነ እንደገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።>> 2ጢሞ.4:3

በዚህ ምክንያት የአንዱ ትምህርት ለሌላ ስለማይጥመው አዳዲስ ቡድኖች እንደ አሸን ይፈላሉ። ሉተራውያን ራሳቸው በ20 ቡድኖች ይከፈላሉ። መኖናይት በ17፣ ፕረስቢተራን በ10፣ ባፕቲስቶች በ23፣ ሜተዲስቶች በ20፣ ወንድማማቾች የሚባሉ በ8፣ የመጨረሻ ቀን ቅዱሳን በ7፣ አድቬንቲስቶች በ5፣…ወዘተ የተከፋፈሉ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለው መመሪያ ወደ መለኮትዊ እውነት ከማድረስ ይልቅ የራስን ፍላጎት ለማርካት ምቹ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

14. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ቦታ የቱ ጋር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የመለኮታዊ እውነት ምንጭ ነው። ነገር ግን ብቸኛ ምንጭ አይደለም፤ ሌሎች ሁለት ምንጮችም ትውፊትና በቤተ ክርስቲያን እስከ ዘመን ፍጻሜ ድረስ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ በርስዋ ዘወትር የሚያስተምረን ትምህርቶች ናቸው። ከነዚህ አንዱ ከጎደለ በስህተት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መግባት ይከተላል።

 

15. በጊዜያችን መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ነው፤ ሁሉም ሊያገኘውም ይችላል። ታዲያ አሁን ያለው ችግር ምንድነው?

ችግሩ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ መግለጽ ያለመቻሉ ነው። ይህን ሳይረዱ ሰዎች  መጽሐፍ ቅዱስን በየግላቸው በመተርጎማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ቡድኖች እየተከፋፈሉና እየተበታተኑ ይሄዳሉ (በዓመት በትንሹ 100 የፕሮቴስታንት ቡድኖች ይፈጠራሉ)። ይህም የሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ሥልጣን ያለው አካል ማስፈለጉን ነው። በግል መተርጎም እንደማንችልና ሥልጣንም እንደሚያስፈልግ አስረጅ ጥቅሶችን እንይ፦

<<በመጀመሪያ ይህን እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ለተረጉም አልተፈቀደም>> 2ጴጥ.1:20

<<የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፤ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።>> 2ጴጥ.3:16

<<እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ። የገሀነም ደጆችም አይችሏትም>> ማቴ.16:18

<<ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባል። ሰዎችም ከአፉ ሕግን ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል>> ሚል.2:7

<<ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ (ኢትዮጵያዊው አዛዥና ጃንደረባ)  ሰማና በእውኑ የምታነበውን ታስተውላለህን? አለው። እርሱም የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።>> የሐዋ. ሥራ 8:30-31

16. የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና አስተማሪ ማነው?

ብቸኛ አስተማሪው መንፈስ ቅዱስ ነው። እሱም የሚያስተምረውና የሚያስረዳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በመሠረታት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ነው። የእግዚአብሔር ሕግና ቃል ማብራርያ በማን አማካይነት እንደሚመጣ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፦

<<የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የጣለ እኔን ይጥላል። እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል።>> ሉቃ.10:16/ሚል.2:7

 

17. የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ውጤት ምንድነው?

ብዙዎች አሉታዊ አመለካከት ቢኖራቸውም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርስቶስ ከመሠረታት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አንድ መመሪያ አንድ እምነትና አንድ መሪ እንዲኖራት ለመሥራቿም መንፈስ ታማኝ ሆና እንድትኖር አድርጓታል (ዮሐ.17:20-23)።

በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡና የሚተረጉሙ ግለሰቦች መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት እንደሚመራቸው ይናገራሉ። እውነቱ ይህ ከሆነ በዓመት ቢያንስ ቢያንስ መቶ ቡድኖች ይፈጠራሉ? መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ወደ ተለያየ እምነት ይመራቸውልን? መንፈስ ቅዱስ መለያየትን ያመጣልን? ብለን መጠየቅም አለብን።

 

18. ካቶሊክ ያልሆኑ ቤተ ክርስቲያናትና ማኅበራት ለምን ተባዝቶ ይገኛሉ?

መልሱ በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን በተልያየ መንገድ ስለሚተረጉሙ ነው። በዚህም ምክንያት ብዙ ስሕትቶች ይፈጠራሉ፤ ምክንያቱም የመተርጎሙ ዘዴው ራሱ ስህተት ስለሆነ ነው። በዚህ ሁኔታ አንድ መንጋ አንድ እረኛ አንድ እምነትና አንድ ጥማቀት ሊኖር አይችልም (ኤፌ.4:5)።

19. ያለ መለኮታዊ መሪነት ካቶሊካዊት ቤት ክርስቲያን አንድነቷን ጠብቃ እስካሁን መኖር ትችል ነበር?

በመንፈስ ቅዱስ ባትመራ ኖሮ ካቶሊክ ያልሆኑት እንደሆኑ ሁሉ እርስዋም ትበታተን ነበር።

ካቶሊኮች መጽሐፍ ቅዱስን ያፈቅራሉ ያከብራሉ ይገለገሉበታልም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን ክርስቶስ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ማንነት አያመለክትም። መጽሐፍ ቅዱስ ክቡር መዝገብ ነው። ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋን ለመፈጸም የምትገለገልበት መሣሪያ ነው፤ ማለትም ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ለመስበክ ከምትገለገልባቸው ከዋና ዋና መሣሪያዎቿ አንዱ ነው። ስለዚህ ከሁሉም ምንጮች በምታገኘው መለኮታዊ መሪነት ብቻ ነው አንድነቷን ጠብቃ የምትጓዘው።

 

20. ከሉተር በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ ነበርን?

በ1440 ዓ.ም. የኅትመት መኪና ግኝት ወቅት በራሱ በዮሐንስ ጊተንበርግ መጀመሪያ ከታተሙት መጻሕፍት አንዱ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሉተር በ1534 ዓ.ም. ካሳተመው መጽሐፍ ቅዱስ በፊት 626 የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱሶች ታትመው ወጥተው ነበር። እነዚህም በልዩ ልዩ የአውሮጳ ቋንቋዎች የታተሙ ነበሩ።

በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በየቀኑ ይነበባል። በቤተ ክርስቲያን መንፈስ ሆኖ እያንዳንዱ ሰውም እንዲያነበው ቤተ ክርስቲያን ታደፋፍራለች። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱሶች በየዓመቱ ይሸጣሉ።

የአብያተ ክርስቲያናት የዘመናት ጉዞን በአጭር አገላለጽ ይመልከቱ (ጽሑፉን ይጫኑት)። 

ይትባረክ እግዚአብሔር!

የቅድስት ሥላሴ ገዳመ ሲታውያን መንኮሳን- ሆሣዕና።

 

 

Write comment (0 Comments)

መግቢያ


ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ተናግሮናል (ዕብ.1:1)  መላ ዓለምን በዘለዓለማዊው ቃሉ ፈጥሯልና (ዮሐ. 1:3) በፍጥረታት አስደናቂነትም ይናገረናል። እንዲሁም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማለትም በሕግ፣ በነቢያት፣ በወንጌልና በሐዋርያት ጽሑፋት በምናገኛቸው የአፈጣጠርና የደኅንነት ታሪክ ይናገረናል።


እነዚህ ሁሉ የተለያዩ መንገዶች ፍጹም ሆነው የሚስማሙት ሥጋ በሆነው ዘላለማዊው ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ነው። በኢየሱስ አማካይነት  እግዚአብሔር ራሱን ሙሉ ለሙሉ ገለጸ። ይህ ቢሆንም ግን በቃል መናገሩን አልተወም። ኢየሱስ ተናገረ፣ ሰበከ፣ መከረ፣ አስተማረ፣ በቃልም ጮኽ ብሎ ጸለየ። ጥያቄዎችን ጠየቀ፣ ታሪኮችን፣ ምሳሌዎችን ተናገረ፣ በአሸዋ ላይም ሳይቀር ቃላትን ጻፈ።


ቃላት ለሰው ልጅ መደበኛና የተለመዱ የመግባቢያ መንገድ ናቸውና እሱ ስለኛ ሲል ከቃላት ጋር ተቆራኘ። እሱ የኛን ቃላት ቢጠቀምም ቅሉ አምላክም ነውና የርሱ ቃላት እንደኛዎቹ ተራ ሆነው መቅረት አይቻላቸውም፤ የርሱ ቃላት ግልጸትን የተሞሉ ናቸው። የሰው ቃላት ሆነው ዘላለማዊውን የእግዚአብሔር ቃል ይገልጻሉ።  በወንድ በሴት፣ በትንሽና በአዋቂ የሚነገሩ ቃላት ሆነው ሳሉ የሕያው እግዚአብሔር ቃል ናቸው።


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕይወት የሌላቸው በድን ቃላትን ሳይሆን ራሱ ኢየሱስን እናገኛለን፦ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው” ዕብ.4:12። ስለዚህም ይህ ቃል እኛ እንደፈለግን አጠማዘን ፍላጎታችንን ለማርካት የምንጠቀምበት ዓይነት ቃል አይደለም። ይህ ቃል በነገሮች እንዲሁም በሞትና ሕይወት ሁሉ ላይ በሚያስፈራ ግርማ ሊመጣ ያለው ኢየሱስ ነው። “ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ… በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሏል።” (ራእይ 19:12-13)።


ወደ እያንዳንዳችን ሕይወት ሲመጣም ይህን በመሰለ ሥልጣን፣ እንደ አስተማሪ፣ እንደ አዳኝ፣ እንደ ወንድምና እንደ አምላክ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በመቀበል ዘላለማዊውን የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስን እንቀበለው።

Write comment (0 Comments)

Subcategories

የሰናብት ወንጌልና መልእክቶች ማሰባሰቢያ ቦታ

በዚህ ርእስ በቀጣይነት የሚቀርቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይሰባሰባሉ

በዚህ ገጽ ሥር የሚካተቱ ጽሑፋት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንነት፣ የተለያዩ አከፋፈሎቹ፣ ስለ ደራሲው፣ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ስላለው ግንኙነት፣ እንዴትስ  መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብናመረዳት እንደምንችልና የያዛቸውን መጽሐፎች በጣም አጭር በሆነ መልኩ ለማየት ይሞክራሉ። በየጊዜውም ርእሶቹን እያሟላንና እየጨማመርን እንሄዳለን።

በአምስት ትንንሽ የገብስ እንጀራና በሁለት ትንንሽ ዓሣ ከአምስት ሺህ ሰው በላይ መመገብ እውነተኛ ታምር ወይስ አጠራጣሪ አስማት ? በሚል መሪ ሃሳብ ክቡር አባ ምሥራቅ ጥዩ ከእምድብር ሀገረስብከት በዮሐንስ ወንጌል 6፡1-15 ላይ ተመርኩዘው ያደረጉትን ጥናታዊ የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል እንደሚከተለው ስናቀርብ ለክቡር አባ ምሥራቅ ልባዊ ምስጋናችንን እያቀረብን እግዚአብሔር አሁንም የጥበቡንና የጤናውን ጸጋ እንዲያበዛላቸውና አገልግሎታቸው ፍሬያማ ይሆን ዘንድ ሁላችንም እንድንጸልይላቸው በማሳሰብ ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ ሓውርያ ሰማዕት - ሓጺር ታሪኽ ሕይወቱ ምስ መባእታ መልእኽታቱ - በሚል አባ ግርማይ አብርሃ ዘማኅበረ ሲታውያን (ማ.ሲ.) ካዘጋጁት መጽሐፍ በአባ ክፍሎም ዮሴፍ ማ.ሲ. የተተረጎመ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ታሪክ፣ ሰብአዊ ማንነቱና መልእክቶቹ ዙርያ የተለያዩ ጽሑፎችን በቀጣይነት የምናቀርብበት ክፍል ነው። ሙሉ ምዕራፎቹ ተጨምረው እስኪያልቅ ድረስ ደጋግመው ይጎብኙት። 

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት - ባጭሩ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት