እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የመቶ አለቃው እምነት - (ማቴ. 8፡5-13) ዘክረምት 3ኛ

ዘክረምት 3ኛ

የመቶ አለቃው እምነት - (ማቴ. 8፡5-13)

faith of the centurion 1በዚህ የወንጌል ክፍል ቅዱስ ማቴዎስ በጥልቀት የመቶ አለቃውን እምነት ያሳየነናል። “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሠቃየ በቤት ተኝቶአል” (ቁ.6) አለው። መቶ አለቃው ከአገልጋዩ የበለጠ ኃይልና ሥልጣን ያለው ቢሆንም የአገልጋዩን ሥቃይ ተመልክቶ ስያዝንለት እናያለን። ለአገልጋዩ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ውስጣዊ ጭንቀት መኖሩን በግልጽ ይገልጽለታል። ፍቅሩንም ለመግልጽ በኢየሱስ ፊት ዝቅ አለ፤ ተዋረደ፤ አለቃነቱንና የበላይ መሆኑን ትቶ በእርሱ (በክርስቶስ) ፊት ሙሉ በሙሉ ታመነ። ይህም በኢየሱስ ላይ ያለውን የፍቅሩን፣ የእምነቱንና የትህትናውን ጥልቀት ግልጥ አድርጎ ያሳያል።

ኢየሱስም የእምነቱን ጥልቀት ስላየ በቁጥር 7 ላይ “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” የሚል ታላቅ ተስፋ ይሰጠዋል። መቶ አለቃውም “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ብቻ ተናገር” (7-8) ሲል መለሰለት። ይህ ክፍል በላቲን መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ዘወትር ይደገማል። ኢየሱስ ሁል ጊዜ ወደ እኛ ይመጣል፤ ለመምጣትም ዘወትር ፈቃደኛ ነው። በቃሉም ይፈውሳል፤ በቃሉም ያድናል፤ በቃሉም ይመጣል። ቁምነገሩ ወደኛ ሲመጣ እንቀበለዋለን ወይ? ሲመጣስ እንዴት ያገኘናል? ለሮማዊው መቶ አለቃ በኢየሱስ ራሱ ስለ እምነቱ “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም” ተብሎ ተመሰከረለት (10)። በእኛ ሕይወት ላይም ፈጣሪ ታላላቅ ነገሮችን ያደርጋል፤ ይፈጽማል፤ ያከናውናልም። ቆም ብለን በጽሞና ማሰላሰል ስንችል በእርግጥ በታሪካችን ውስጥ እግዚአብሔር አስደናቂ ነገሮችን እንዳከናወነልን መረዳት፣ ማመስገንና ለካ ይህ ሁሉ በርሱ ነው የሆንልን ለማለት ድፍረት እናገኛለን። ምናልባት በእኛ በኩል የሚያስደንቅ ሥራ ለመሥራት ብዙ ጊዜ ሊወስድብን ይችላል እንጂ በእርግጥ ከልብና በእምነት ከለመነው እርሱ ቶሎ ይሰማናል፤ መልስም ይሰጠናል። ስንት ጊዜ ነው ፈጣሪ የሰማን? የታዘዘን? ሸክማችንን ያቃለለልን? የፈወሰን?

የመቶ አለቃው ጸሎት በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ አልነበረም። ነገር ግን ጸሎቱ በልበ ሙሉነት፣ በፍቅር፣ በትህትናና በእምነት ላይ የተመሠረተ ነበር። እምነት እውነተኛ ዕውቀት ነው። በእምነት ልባችን ይከፈታል፤ ዓይኖቻችን ይበራሉ። ይህ ሲሆን ማዳመጥ ጥበብና ዕውቀት ነው። ከጆሮ ይልቅ በልብ ብዙ እናዳምጣለን። ጆሮ ድምጾችን ይሰማል። ልብ ደግሞ ዝምታን ያዳምጣል። (Listening is an art. We listen more with the heart than with the ear. The ear hears sounds. The heart listens to silence.) ለዚህም ነው ኢየሱስ ራሱ “ሂድና እንደ እምነትህ ይሁንልህ” (13) ያለው።

እምነት ማለትም በዕብራውያን 11፥1 በግልጽ እንደምናገኘው “ተስፋ ስለምናደርገው ነገር እርግጠኞች የምንሆንበት፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ” ነው። ሰው በእምነት ወደ ልቡ፣ ወደ ሕይወቱ፣ ወደ ቤቱና ወደ ህሊናው በገባ ቁጥር ያኔ ኢየሱስን ያገኛል፤ ይድናል፤ ከነፍስና ከሥጋ ደዌ ይፈወሳል። ውስጥን መመልከት፣ ልብን መፈተሽ፣ ህሊናን ማየት በእምነት ያጠነክራል፤ ፈጣሪን ለማየትም ያስችላል። ሐዋርያው ቅዱስ ዼጥሮስ “ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” (ዮሐ. 6፥68) አለው። መቶ አለቃውም ቢሆን ባየሁት ጊዜ አምናለሁ አላለም። ኢየሱስ ራሱ “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” (ዮሐ. 20፥29) ብሎናልና። ክርስቲያን በእምነት ማየት ሲጀምር በእውነት ማየት ይጀምራል። እንደ ሰው አንዳንድ ጊዜ ጤና ማጣት፣ ሥራ ማጣት፣ ኑሮ ራሱ ሲያጨናንቀንና ተስፋ ቢያስቆርጠንም እንደ ክርስቲያን ደግሞ ተስፋችን እግዚአብሔር ነውና ሁሉን ቻይ በሆነው በአምላክ እጅ መጣል ይገባናል። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዼጥሮስ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” (1ዼጥ. 5፥7) የሚለን።

ጸሎታችንን የሚሰማና የሚመልስ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለሆነም በርሱ ሙሉ በሙሉ በመተማመን መጸለይ ይኖርብናል፤ ባንተ ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት እንዲጥል አድርገኝ በማለትም ዘወትር መጸለይ ያስፈልጋል። ኢየሱስ የመቶ አገልጋዩን (ሽባውን) ሰው የፈወሰው (ይህ ሽባ ዝቅተኛ ማህበራዊ ተሳትፎ የነበረው አገልጋይ) በቅፍርናሆም ከተማ ነበር። ዛሬ ላይ ቅፍርናሆም ከተማችንና መንደራችንም ናት። በዚች ከተማ የታመሙ፣ የተረሱ፣ ተስፋ የቆረጡ፣ በመንፈስና በሥጋ የታሰሩ፣ በልዩ ልዩ ዓይነት ችግሮችና ሱሶች የተጠመዱ በርካታ ሰዎች አሉባት። ለዚህም ነው ወደ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ መቅረብና ተስፋ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት። ምናልባት ዝነኛ፣ ሀብታም፣ ተዋቂ ሰው ቢፈወስ ኖር ብዙም አያስደንቅም ነበር። ነገር ግን ይህ የተረሳውና የተናቀው አገልጋይ በመፈወሱ ታሪኩን ልዩ አድርጎታል። በእኛ ታሪክም ዝነኞች፣ ሀብታሞች፣... ባንሆንም በፈቃደኝነት ላይ በተመሠረት እምነት ፈጣሪ ወደ ልባችን ጓዳ ይገባል፤ የልባችንን ቁስል ይፈውሳል፤ በሕይወታችንና በኑሮአችን ጣልቃ ይገባል፤ በከባድ ሕመም አልጋ ላይ ሆነው ተስፋ ወዳጡት ይመጣል፤ ባላሰብነው ሰዓትም ከተፍ ይላል። የኢየሱስ ጣልቃ–ገብነት የጊዜ ገደብ፣ የቦታ ርቀት፣የሥራ ብዛት እንቅፋት አይሆንለትም። በቃሉ ብቻ ይፈውሳል።

በቅዱስ ቁርባን ሥነ–ሥርዓት ኢየሱስ ዘወትር ይሰዋል፤ ራሱንም በሙላት ይሰጠናል። በእያንዳንዱ አማኝና ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ኢየሱስ በጌቴሰማኒ በተሰቃየው መጠን ያህል በሥቃይ ውስጥ ይገኛል። ወደዚህ ሥቃይና ፍቅር ውስጥ ጠልቆ ለመግባት ልክ እንደ መቶ አለቃው በትህትናና በጥልቅ እምነት መሆን አለበት። በዚህ መንገድ የክርስቲያን ሁሉ ተግባር ወደ ሆነው የክርስቶስን የመዳን ተስፋና ሕይወት በመጠበቅ፣ የእርቅና የሰላም መንገድ በመከተል፤ ለሌሎችም የመዳንና የደስታ ምክንያት ለመሆን እንችላለን።

ሰው ሁሉ ወደ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንዲመጣ፣ ዘወትር ሳይሰለች እርሱን እንዲፈልግ በፍቅር ተጋብዟል። ኢየሱስ የመፈወስና በቃሉ የማዳን ኃይል እንዳለው አውቀን፤ ጥልቅ ፍቅር፣ እምነት፣ ትህትናና፣ ርኅራኄ ሊኖረን ይገባል።

ከዚህ ከወንጌል ክፍል በተጨማሪ የምንማረው ዐቢይ ጉዳይ በሥራችን፣ በዙሪያችን የሚገኙትንና የሚሰሩትን ሠራተኞች ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል። ለምሳሌ የወጥ ቤት ሠራተኞቻችን፣ የጥበቃ ሠራተኞቻችን፣ የት/ቤታችን ሠራተኞቻችን፣ የቢሮ ሠራተኞቻችን... በአጠቃላይ ለሥራዎቻችን ስኬት ይጠቅሙናል ብለን የቀጠርናቸውን የሥራ አጋሮቻችንን በሙሉ ያካትታል። ለነዚህ ሁሉ የልፋታቸውንና የላባቸውን ዋጋ በትክክል እንከፍልላቸው ይሆን? የሰሩበትንስ የጉልበታቸውንና የዕውቀታቸውንስ ዋጋ በቅንነት እንከፍልላቸዋለን ወይ? ደመወዛቸውንስ በወቅቱ እንከፍላለን ወይ? “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” (ሉቃ. 10፥7 ፣ 1ጢሞ. 5፥18) “ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና” (ማቴ.10፥10) ይለን የለም ወይ ቃሉ?

"የሚሠራ ሰው የሚያገኘው ደመወዝ÷ ተገቢ የጉልበቱን ዋጋ ነው እንጂ ስጦታ አይደለም።" (ሮሜ 4÷4) ቢልም ቅሉ በብዙ ቦታ በእኛ አገር ሰው ለፍቶም ቢሆን የሚገባውን በወቅቱ ሳያገኝ ይቀራል። እነዚህን ሠራተኞች እኮ በዙሪያቸው በርካታ የሚጠብቁአቸው እንዳሉአቸው መገመት አይከብድም። ሆኖም ግን በወቅቱ መክፈል የሚገባንን ባለመክፈልና ባለመስጠት በብዙ እንበድላለን።

ለምሳሌ ምንም የሌላት፣ በልመና የተሰማራችና 7 ልጆችዋን ለማሳደግ በእግዚአብሔርና በሰው እጅ ላይ ብቻ ተስፋ የምታደርግ አንዲት ደሃ ሴት ማሰብ ከቻልን፤ ስታገኝ የምትደሰት፣ ስታጣ ደግሞ ለልጆቿ ዛሬስ ምን ላበላቸው ነው? በማለት አበክራ ትጨነቃለች። እኛ ግን ደመወዝ ለምንከፍልላቸው ሰዎች ይህን እየተረዳን አንዳንድ ጊዜ በእርግጠኝነት እንበድላቸዋለን። "እነሆ እርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኸል። የአጫጆቹም ጩኸት የሠራዊት ጌታ ጆሮ ደርሶአል" (ያዕ 5÷4)። የወይን አትክልት ሠራተኞች ምሳሌ (ማቴ. 20፥1–16) ስናነብ በሦስት፣ በስድስት፣ በዘጠኝና በዐስራ አንድ ሰዓት ላይ ለተቀጠሩት ሠራተኞች ጌታው እኩል እንደከፈለላቸውና እንደራራላቸው ማየት እንችላለን። ይህ የወንጌል ክፍል የተጻፈው ለእኛም ጭምር ነውና በአትኩሮት ሊናሰላስለውና ከሕይወታችን ጋር ሊናሰናስነው ይገባል። በሌላ መልኩም ቃሉ “…እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል” (1ቆሮ. 3፥8) ይለናል።

የእግዚአብሔር እናት እመቤታችን ድንግል ማርያም፤ የእምነት መምህርት፣ የተስፋና የፍቅር እናት ናትና ወደ እርሷ እንማጸን፤ እንቅረብም።

አባ ያዕቆብ ማርቆስ ሲታዊ - ሆሣዕና ገዳም ዘቅ. ሥላሴ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት