ዘዮሐንስ (አዲስ ዓመት)

ቅዱስ ዮሐንስ (አዲስ ዓመት)

 2ቆሮ. 6:1-10 -- ያዕ. 5:8-10 -- የሐዋ. ሥራ 5:12-16 -- ማቴ. 11:1-19 

የታጨቁ የእግዚአብሔር ስጦታዎች

flower-field-summer1ጊዜያትና የዘመናት ጌታ አምላካችን ክረምት ብለን በጋ እንድንልና የወቅቶችን ዑደት አይተን እንድናመሰግነው ስላደረገን የተመሰገነ ይሁን! የምናመሰግንበት ዋነኛ ምክንያት ራሳችን እንዲመቸን ያደረግናቸው የቀናት ቁጥሮች ስለተቀያየሩ ሳይሆን ዛሬ ላይ ቆመን ቸርነቱን አስበን ይበልጥ ወደርሱ መቅረብን እንድንወስን የሚያግዝ ወቅት ላይ ስላደረሰን ነው።

ዳዊት <<ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ ምስጋናውንም ሁሉ አትርሺ፤ ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥ ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ፥ ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል…እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።>> (መዝ.103) በማለት አምላኩን ላለማመስገን ሰብብ እንዳጣ ይገልጽልናል። ምናልባት አዲስ ዓመት ብለን እግዚአብሔርን ለማመስገን ስናስብ ያለፈውን ዓመት በሙሉ በዓይነ ኅሊናችን ለመቃኘት እንሞክርና ብዙም አዲስ ነገር የለም፤ የተወሰነ ነገር ነው…እንደውም ብለን ደግሞ ጥሩ አልሆኑልንም ብለን የምናስባቸውን ነገርም እንደረድርና <<መጥፎ>> ነገሮቻችን ሚዛን የደፉ ይመስለን ይሆናል። ግን በአንድ ዓመት ሳይሆን በአንድ ቀን ውስጥ የታጨቁትን የእግዚአብሔር ስጦታዎች ለማየትና ለመቁጠር ልቦናችን ቢፈቅድና ብንወስን ለማመስገኑ ባተሌዎች አንሆንም።

በመሠረቱ ጊዜ ሲለዋወጥ የተለመደ ሁኔታ ስለሚመስለን አዲስ ነገርም የመጠበቅ ጉጉታችን ይዳከማል። ከሰኞ በኋላ ማክሰኞ እንደሚመጣ ስለምናውቅ እንደ አንድ አዲስ የጊዜ ስጦታ አንቆጥረውም። አሁንም አዲስ ዓመት ሲባል በፊታችን አንድ ዓመት ተሰጠን ማለት አይደለም፤ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ርግጠኛ መሆን የምንችለው አሁን ያለንባት ሰዓት ላይ መሆናችንን ነው። እውነቱ ያ ከሆነ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ያለን ጊዜ አሁን ነው ማለት ነው።

ቶማስ ሜርተን (ሲታዊ) ይህን እውነት በአንድ መጽሐፉ ሲገልጸው ከሰው በስተቀር ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ <<ጊዜ>> የሚባል ግንዛቤ (ሰዓት ወይም ካላንደር) ስለሌላቸው እያንዳንዷ ቀን ለነሡ ዳግም የመፈጠር ያህል ነው። ስለዚህም በማለዳ ጎሕ ሳይቀድ ከእንቅልፍ ሲነቁ ካለመኖር ወደ መኖር መጥተዋልና ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ። ሰው ግን ገና ማታ ሲተኛ ነገ የሚያደርገውን ነገር ስለሚያውቅ ጠዋት ሲነሣ የጠበቀውን ጊዜ የሚቀጥል እንጂ አዲስ ጊዜ እንደተሰጠው ብዙም አያስተውልም ስለዚህም ከማመስገን ወደ ኋላ ይላል በማለት የእግዚአብሔርን ስጦታ በዘልማድ እንደምንወስዳቸው ያስረዳል። ይህ ሀሳብ ከተረዳን አሁንም መዝ.148 ላይ ዘማሪው ከመላእክት ጀምሮ ፀሐይ፣ ከዋክብት፣ ጨረቃ፣ ብርሃናት፣ ሰማየ ሰማያት፣ የሰማያት በላይም፣ ተራራና ኮረብታ፣ አመዳይና ውርጭ፣ እሳትና በረድ…አራዊትና ወፎች፣ የምድር ነገሥታት አሕዛብም ሁሉ፥ አለቆች የምድርም ፈራጆች ሁሉ፥ ጕልማሶችና ቈነጃጅቶች፥ ሽማግሌዎችና ልጆች፤ <<እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት>> በማለት እያንዳንዷ ቀን በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደምትሰጠንና ለዚያም ውለታ ቢሶች መሆን እንደሌለብን ዘምሯል።

እግዚአብሔር ጊዜን የሰጠኝ ለምንድነው ብለን እያንዳንዳችን እናስብ። በአዲስ ዓመት በዓላችን የምናከብረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቁ ለርሱ ጊዜ የተሰጠው ስለእውነት ለመመስከርና ለመሞት ነበር። ይህን ታላቅ ቅዱስ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ስናከብረው ጥልቅ ትርጉም ይሰጠናል፤ የተሰጠን ጊዜ ለትልቅ ዓላማ መሆኑን ከርሱ መማር መቻል አለብን። ይህ ሊሆን የሚችለው በእግዚአብሔር ትምክህታችን ሲበዛ ነው። በእግዚአብሔር የሚመካ ሰው እሱን ያመሰግናል። ወደ ውስጣችን ከገባን እግዚአብሔርን እንዳናመሰግንና ለርሱ እንዳንቆም የሚያግደን ነገር ውጫዊ ነገሮች ስለጎደሉን አይደለም፤ ይልቁንስ መንፈሳዊ ሕይወታችን በሆነ ነገር ስለታነቀ ነው። ውስጣችንን የያዙትን ነገሮች በንስሐ ለማስወገድ እግዚአብሔር ዳግም ጊዜን ሰጥቶናልና የተመሰገነ ይሁን።