እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘጰራቅሊጦስ

ዮሐ. 20:1-18-1.ቆሮ.15:120-1ጴጥ.1:1-12-ሐዋ.2:22-36

apostles at pentecostበዚህ ሰንበት ቤተ ክርስቲያን የጰራቅሊጦስን በዓል ታከብራለች። ጰራቅሊጦስ የግሪክኛ ቃል ሆኖ አቻ ትርጉሙ አጽናኝ ማለት ነው። ይህም ክርስቶስ ራሱ በዛሬው ወንጌል “እኔ አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘላለም ከእናንተ ጋር የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል” በማለት የገለጸውን የመንፈስ ቅዱስ ባሕሪይ ይገልጻል። መንፈስ ቅዱስ ለአንድ ክርስቲያን የሚያጽናና ብቻም ሳይሆን የሚያጸና፣ በእምነት ጉዞው ሁሉ ብርሃንንና ሙቀትን የሚሰጠው ነው።  ያለ መንፈስ ቅዱስ የክርስቲያን ሕይወት ማሰብ አይቻልም።

የዛሬዎቹን ምንባባት ካስተዋልን በቀጥታ የትንሣኤ በዓል ወቅት የተነበቡት ናቸው። ይህ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮ ሂደት ሲሆን ራሱን የቻለ ትርጉም ሊኖረው  ይችላል። ሆኖም ግን የክርስቶስ ትንሣኤ ለእምነታችን መሠረትና ወሳኝ መሆኑን ያህል ጰራቅሊጦስም ትልቅ በዓል መሆኑን ያሳየናል። የክርስቶስ ትንሣኤና መላ ሕይወት ለኛ ሕያው የሚሆንልን ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ነውና የትንሥኤን ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እንዲደገም ስታዘን የበለጠ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንድናስተውል ይጋብዘናል።

በአንድ ወቅት አንድ ሚስዮናዊ ካህን ወደ ሩቅ ገጠር ለስብከት ወንጌል ማእከል የሚሆናቸውን ቤት ይከፍታሉ፤ በዚያም መኖሪያቸውን አድርገው እየተንቀሳቀሱ ይሰብኩ ነበር። በዚያ አካባቢ እንኳንስ የኤሌክትሪክ መብራት ሊኖር ቀርቶ ማሰቡም አስቸጋሪ ነበር። እኚህ ሚስዮናዊ ጄኔሬተርን በመጠቀም በአስፈላጊ ሰዓቶች ለቤታቸውና እዚያው ለሚገኘው ቤተ ክርስቲያን መብራት ይጠቀሙ ነበር። በአንድ አጋጣሚ ራቅ ባለ አካባቢ የሚኖሩ ምእመናን ሚስዮናዊውን ለመጎብኘት አመሻሹ ላይ ሲመጡ ካህኑ እንግዶቻቸውን ለመቀበል ማብርያ ማጥፊያዋን ብቻ በመንካት መብራት ሲያበሩ እንግዶቹ ሁሉ ትልቅ ተአምር እንደተከሠተ ሁሉ ግርም አላቸው። ኋላም እንግዶቹ ወደየመጡበት ሊመለሱ ሲሉ አንደኛው እንግዳ አባን “እንደዚያ ዓይነት ነገር ካለዎት ይስጡኝ” በማለት አምፖሉን በማሳየት ጠየቃቸው። ካህኑም ኤሌክትሪክ የሚባል ነገር ምንም እንደሌለ ስለሚያውቁ ምናልባት እንደጌጥ ነገር ፈልጎት ይሆናል ብለው በማሰብ አንድ አምፖል ሰጡት። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ካህኑ ምእመናንን ለመጎብኘት ሲሄዱ ያ አምፖል ከርሳቸው ወደ ወሰደው ሰው ቤት ደረሱ። ወዲያውም ካህኑ በፊት ያላሰቡትና ያስገረማቸውን ነገር ተመለከቱ፦ ሰውየው ያንን አምፖል በተራ ገመድ ቤቱ ውስጥ አንጠልጥሎታል። ስለዚህም ካህኑ ለሰውየው አምፑሉ መብራት ካለበት የኤሌክትሪክ ኃይልና ሽቦ እንደሚያስፈልግ ማስረዳት ጀመሩ።...

ይህን ታሪክ በመጠኑ ከአንድ ክርስቲያን ሕይወትና የቅድስት ሥላሴ ህልውና አቅጣጫ ማየት ይቻላል። ክርስትናችን እንዲያበራ ወይም ትርጉምና ሕይወት ያለው መሆን ካለበት ውጫዊ ነገሮች ብቻ አይበቁንም፤ በውስጣችን ሊሠራ የሚችል ኃይል ያሻናል። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሌለበት የክርስቲያን ሕይወት በታሪኩ ውስጥ ያየነውን በተራ ገመድ የተንጠለጠለውን አምፖል ይመስላል፦ ሲታይ አለ ግን ትርጉም የለውም። ክርስቲያን ይባላል ግን የክርስቶስ መንፈስ የለውም። ክርስቶስ ስለራሱ ሲመሰክር “ያለእኔ ምንም ማድረግ አትችሉም” ይላል(ዮሐ. 15)፤  እንዲሁም “እኔ ግን እውነት እውነት እላቸኋለሁ፤ የኔ መሄድ ለእናንተ ይጠቅማችኋል፤ ምክንያቱም እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም” (ዮሐ. 16) በማለት የመንፈስ ቅዱስን ለኛ አስፈላጊነት በአጽንዖት ይናገራል። በሌላ አባባል ያለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምንም ማድረግ አንችልም ማለት ነው።

መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ከሌለ እውነት የሚባል ነገር በውስጣችን የለም፤ እውነት ደግሞ ክርስቶስ ነው። በኤፌ.4 ውስጥ  “በሰላም ተሳስራችሁ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” እንደሚለው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን በኑሯችን የማንለማመድ ከሆነ አንድነት አይኖረንም፤ ይህም አንድነት ከሁሉም በፈት ከራሳችን ጋር አንድ መሆን ማለት ነው። ሰው ኅሊናው፣ አእምሮውና ልቡ አንድ ሆኖ መኖር በጣም ከባድ ነው። በኅሊና ወቀሳ የተሞላ ሕይወት በቀጣይነት መኖር አንድን ሰው ከራሱ ጋር አንድ እንዳይሆን ይከለክለዋል።

ይህን የጰራቅሊጦስ በዓል ስናከብር ክርስቶስ ለናንተስ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል በማለት የመንፈስ ቅዱስን ጠቃሚነት የገለጸውን እውነት በማሰብና ለኔ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማነው? ክርስቶስ “የእውነት መንፈስ” (ዮሐ. 14:17) በማለት የተናገረለት መንፈስ ቅዱስ በሕይወቴ ምን ሚና አለው? ያለርሱስ እንዴት እውነተኛ ሕይወት ሊኖረኝ ይችላል?...ወዘተ በማለት  እናስተንትን። ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ክርስቶስ በመንበረ ታቦት ሕያው ሆኖ ወደ ሕያው ሕይወት ይጋብዘናል። ዛሬም ለያንዳንዳችን በላቀ ሁኔታ ከማንነት መፍረክረክ ወደ ምስጢራት ሕይወት ጽናት ለመሻገር በመወሰንና ፈቃዱን በማድረግ የርሱ ብርሃን ምስክሮች እንሆን ዘንድ በቅድስት ሥላሴ ውስጥ የፍቅርና የኅብረት አካል የሆነው መንፈስ ቅዱስ ኃይል ይሁነን።

መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ሆይ ና የምእመናኖችህን ልብ ሙላ የፍቅርህን እሳት በውስጣችን አንድድ - አሜን!!!

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት