ዘጽጌ 4ኛ

ዘጽጌ 4ኛ

1ቆሮ.10:1-18            ራእይ 14:1-5           ሐዋ.4:19-30           ማቴ.12:1-21

flower-field-summer1ክርስቲያኖች ሁሉ የእግዚአብሔር ምሕረት ምስክሮች እንሆን ዘንድ መሠረታዊ ጥሪያችን ነው። በማንኛውም ዓይነት ጎዳና ላይ የእሱ ፍቅር ገደቦችን የሚሻገር መሆኑን ደግሞ የዛሬው ወንጌል ያሳየናል። ፈቃድና ዝግጁነቱ ካለስ የእሱ ምሕረት ላይነካው የማይችለው ዓይነት የሰው ልብ የለም። ጽዩፍ፣ ያልተገባ፣ ደካማ፣ ኃጢአተኛ...ብለን ራሳችንን የምናይ ከሆንን ደግሞ ይበልጥ ለፍቅሩና ለምሕረቱ የተመቸን ነን። "እሱ የተቀጠቀጠ ሸንበቆ እንኳ አይሰብርም" (ማቴ.12:20) ይለናል። ምሕረቱን በውጫዊ መስፈርት መገደብ ማለት ራሱ እግዚአብሔርን የመገደብ ያህል ነውና ክርስቶስ ይህን እውነት በወንጌል ታሪኮች ያስተምረናል።

ማንም ሰው ቢሆን በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነው። ይህን እውነት ስንዘነጋ ነገሮች መዛባት ይጀምራሉ። ደስተኛ ያለመሆን፣ ሰላምን ማጣት፣ የትርጉም የለሽ ስቃይ ሰለባ መሆን ይጠናወተናል። እውነቱ ግን ሁሌም ከፍ ላለ ነገር የተፈጠርን፣  ከምንም ነገር በላይ ክርስቶስ የሚያስቀድመንና የሚወደን ፍጡራን መሆናችን ነው።

ቶማስ ሜርተን (ሲታዊ) የሰው ውስጣዊ ክብርን መገንዘብ ብንችል ለራሳችንም ሆነ ለሰዎች ሁሉ ያለን እይታ ልዩ ይሆን እንደነበር ሲያስረዳ እንዲህ ይላል:- "በህላዌያችን ማእከል፣ በ ልባችን የውስጥ ውስጥ ጋር ማለትም በማንነታችን ቁልፍ ቦታ ላይ የሚገኝ አንድ ቦታ አለ። በኃጢአትም ሆነ ራስን በማታለል የማይደመሰስ፣ ሁልጊዜ የንፁሕ እውነት መቀመጫ የሆነና ሙሉ ለሙሉ የእግዚአብሔር ርስት የሆነ፣ እኛ ምንም ልናደርግ የማንችልበት ቦታ አለ። እግዚአብሔር ከዚያ ውስጠ ውስጣችን ሆኖ ሕይወታችን እንዴት መሆን እንዳለበት ይመራናል። አእምሯችንና ፈቃዳችን ይህንን ውሳጣዊ ድምጽ ዝም ማሰኘት አይቻላቸውም። ይህች ነቁጥና ንጹሕ የሆነች የእግዚአብሔር ግዛት፤ በውስጣችን የእሱ ክብርና የስሙ ማኅተም ናት። እንደ እንደ ደካማ ድኻና ጥገኛ ሆኖ በውስጣችን አለ። ልክ እንደ ክቡር ንጹሕ ዕንቍ በሰማያዊ ጮራ በውስጣችን ያበራል። ይህ ክቡር ጮራ በሰው ሁሉ ውስጥ አለ፤ ይህን በሰዎች ሁሉ ያለ ክቡር ጮራ ማየት ብንችልና በቢሊየን የሚቆጠሩ የዚህ ጮራ ፍንጣቂ ስብስቦች በአንድ ላይ ሆነው በገጽታዎች ላይ እንደ ጸሐይ ሲፈነጥቁ ብናይ የከበቡንን ጨለማዎችና የሕይወት ጭካኔዎች ሁሉ ጠራርጎ ባጠፋልን ነበር...የመንግሥተ ሰማይ ደጃፍ በሁሉም ቦታ ይገኛል።" ይላል።

ይህ ሀሳብ ትንሽ ወሰብሰብ ያለ ይመስል ይሆናል፤ ነጥቡ ግን በሰው ውስጥ በምንም ሊደመሰስ የማይችል ክብር እንዳለና ይህንን ማየት ብንችል ደግሞ ሰው ለሰውም ሆነ ሰው ለእግዚአብሔር ያለን ግንኙነት በላቀ ሁኔታ ይለወጥ መሆኑን ለማስረዳት ነው። ይህን መሰል ውስጣዊ የእግዚአብሔር መገኘትን ችላ ማለት ሲጀምርና በሌሎችም ውስጥ ማየት ሲሳነው ሰው ለሰው መልካም መመኘት ይከብደዋል፣ የሰው መፈወስ፣ ደስተኛ፣ አስተዋይ፣ ጥሩ... መሆን ሁሉ ጥሩ ስሜትን አይፈጥርለትም።

በዛሬው ወንጌል ፈሪሳውያንም ከዚህ ብዙ የራቀ ዝንባሌን አይደለም ያሳዩት። ወንጌሉ እንደሚለን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት "ርቧቸው ስለነበር የስንዴ እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያን ይህን አይተው እነሆ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ" አሉት (12:1-2)። ለምን በሉ ነው ጥያቄው፤ እንዲሁም በምኵራባቸው ኢየሱስን ባዩት ጊዜ "በሰንበት ቀን በሽተኛን መፈወስ ተፈቅዷልን" (12:10) ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ የውጩን አጀብና ሆህታ ሳይሆን በተናቀና ቦታ የሌለው በሚመስል ሰው ሁሉ ውስጥ የከበረ የእግዚአብሔር ልጅነትንና አንጸባራቂ ክብርን ስለሚያይ እጀ ሽባውን በሁሉም ፊት በሰንበት ቀን በምኵራባቸው ውስጥ "እጅህን ዘርጋ!" በማለት በቃሉ ኃይል ፈወሰው። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጥተው ኢይሱስን እንዴት አድርገው እንደሚገድሉት ተማከሩ ይላል ወንጌሉ።

እናስተውል! እዚህ ላይ የፈሪሳውያኑን ድርጊት ለመፍረድና የኢየሱስ ደጋፊ መሆናችንን ማሳየት አይደለም ቁም ነገሩ፤ ጥሪው ለያንዳንዳችን ሕይወት ነው። በሌላ ሰው ውስጥ ያለውን ክብራዊ ጮራ በራሳችን ማየት እንጀምር፤ አካባቢያችን ማማር ይጀምራል። መልካም አደረግክ፣ ፈወስህ፣ የተራቡ ደቀ መዛሙርትህ ሲበሉ ዝምብለህ አየህ...ብሎ ሰው ክርስቶስን ሊገድለው እንደመከረ አይተናል። ክርስቶስ ከምንም በላይ የሚገደው ሰዎች ስለኛ የሚሉት ወይም ውጫዊና ማኅበረሰባዊ የሆኑ ተብትበው የያዙን ነገሮች ሳይሆን በውስጣችን ከዓለም መፈጠር በፊት ያስቀመጠው የመዳናችን ነገር ነው። ይህን በውስጣችን ያለ የርሱን እቅድ እናስተውል፤ ጊዜ እንስጠው። ለያንዳንዳችን ዘላለማዊነት ሩቅ አይደለምና ሌላ ውጫዊ ነገሮች ላይ ጊዜ አናባክን።

የእግዚአብሔር ቃል ኃይል ዛሬም ቢሆን ሊያነሣን፣ ሊፈውሰንና እውነተኛ ክብራችንን ሊያጎናጽፈን ይጠራናል። እጀ ሽባውን ሰው "እጅህን ዘርጋ!" ብሎ የፈወሰ ቃል አሁንም ልባችንን እናስገዛለት ዘንድ ይጠራናል። ለሀሳብና ለምክንያቶች ሳይሆን ለመዘርጋት ዝግጁ ስለነበር ሽባው ተፈወሰ። ክርስቶስ ዘርጋ ሲለው "እንዴት ልዘርጋ፣ ሽባኮ ነው..." የሚሉ መሰል መልሶችን ቢሰጥ ይችል ነበር። ግን የእግዚአብሔር ቃል ዘርጋ ብሎታልና ዘረጋ ተፈወሰም! እኛም የውስጣችንን ሽባነት ያለሌላ ሰበቦች በፊቱ እንዘርጋ። ሽባነታችንን በፊቱ እንናዘዝ፣ ደካማነታችንን በክቡር ሥጋ ወደሙ እንመግበው ያኔ እንበረታለን።