ዘጥምቀት - አስተር እዮ 2ኛ

"ውሃ አጠጭኝ!"

ዮሐ.4:1-26 ሮሜ 9:1-16 1ጴጥ.2:20-25 ሐዋ.11:1-18

የዛሬው ወንጌል ረዘም ባለ መልኩ ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ያደረገውን ንግግር ይተርክልናል። ሁለቱን ያገናኛቸው ነገር የኢየሱስ "መጠማት" ነበር፥ ጥማት ለሰው ልጅ አዲስ ነገር አይደለም። አዲስ ሊሆን የማይችለውም አንድ ጊዜ ጠጥተን ለሁልጊዜ መርካት ስለማንችልና በየቀኑ አሁንም አሁንም ተመላላሽ ነገር ስለሆነ ነው። ይህ ለሥጋዊ ጥማታችን እውነት ነው፤ ሰው ግን ከሥጋም በላይ ወሰብሰብ ያለ መዋቅር ያለው ፍጡር ነውና ጥማቱም በውሃ ብቻ ሊረካ አይችልም። እንደውም ምናልባት ቀላሉ የመጠማት ዓይነት የሥጋ ነገሮች ጥም ሳይሆን አይቀርም ማለት ይቻላል።

ሥጋችንን በምንሰማው፣ በምናየውና ልናገኝ በምንችለው ነገር ሁሉ ብናረካው ቋሚ እፎይታን አይሰጠንም፤ ይልቁንም የበልጥ ከፍ ያለ ሌላ የህልውና ኃይለኛ ጥማት በውስጣችን መኖሩን ወዲያው እንረዳለን። በዚህ መሠረታዊ ሃሳብ ተመርኩዘን የሳምራዊቷን ሴትና የኢይሱስን ሃሳብ ልውውጥ ስናነበው እኛም በተወሰነ ደረጃ ላይ ልክ እንደርሷ "ጌታ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ውሃ እንዳይጠማኝና ወደዚህም ለመቅዳት እንዳልመጣ እባክህ እንዲህ ዓይነቱን ውሃ ስጠኝ" ለማለት ይገፋፋናል።

ታሪኩ ሲጀምር "አንዲት የሰማርያ አገር ሴት" ይላል። ይህች ሴት በስም አልተጠቀሰችም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስም ማለት ራሱ ግለሰቡን የሚወክል ነገር ነው። የዚች ሴት ስም ያለመጠቀስ የሚያሳየው እውነታም በማኅበረሰቧ መስፈርት መሠረት ማንነቷ ብዙም ግድ የሚል ዓይነት ሰው እንዳልሆነች ነው። ይህች ሴት ውሃ ልትቀዳ የሄደችበት ሰዓት ቀትር መሆኑን ስናነብና ያ ሰዓት ደግሞ በነበረው ባህል መሠረት ውሃ የመቅጃ ሰዓት ያለመሆኑን ስናስተውል ይህች ሴት ሰው ውሃ በማይቀዳበት ሰዓት ማንም ሳያገኛት ቀድታ መመለስ ይመቻት ዘንድ ያደረገችው መሆኑንና ራሷን ከሰው አርቃ የምትኖር መሆኗን ያመላክታል። ኢየሱስ ለእንደዚች ዓይነት ኑሮ ለታከታት ነፍስ ጥማቱን ገለጸላት፤ እሷም ከርሱ ጋር በተነጋገረች መጠን የእሱን ማንነት ይበልጥ እያወቀች መጣችና ለማኝና የተጠማ ሆኖ ራሱን የገለጠላት ተለማኝና እስከወዲያኛው ጥምን የሚያረካ የነፍስ ባለቤትና አዳኝ መሆንኑ አወቀች።

አንድ "አይሁዳዊ" ብላ ንግግሯን የጀመረችው ሴት ቀጥላ "ጌታ ሆይ"፣ ከዚያም "ነቢይ" እያለች በመጨረሻም መሲሕነቱን ለሌሎች ለመመስከር ስትሮጥ እናያለን። ከኢየሱስ ጋር መነጋገር ሳንጀምር፤ ወይም እርሱን ለመስማትና በርሱ ፊት እውነተኛ ምላሽን ለመስጠት ሳንደፍር ኢየሱስን ማወቅ እንደማንችል ማስተዋል አለብን። ከርሱ የመሸሽን ሕይወት እየኖርን በሄድን ቁጥር አታካች ሕይወት ውስጥ እየጠለቅን እንሄዳለን። ይሄን ግን ኢየሱስ አይመኝልንም፤ ስለዚህም "ውሃ አጠጭኝ!" በማለት እሱን የመስማት ፈቃዳችንን ይለምነናል።

ሳምራዊቷ ኢየሱስን "እኔን ሳምራዊቷን ውሃ አጠጭኝ ብለህ ትጠይቀኛለህ?" አለችው ግርም ብሏት፤ ለዛውም ይህን ስትል አይሁዳዊነቱን እንጂ መድኃኔ ዓለምነቱን ገና አላወቀችም ነበር፤ የኛ ግን ይለያል አሁን ማድረግ የምንችለውን ትንሽ ነገር የሚጠይቀን እሱ ራሱ አዳኝ ጌታ መሆኑን እናውቃለን። ፈቃዳችንን፣ ምኞታችንን፣ አናኗራችንን እንመርምር፤ ዛሬ ኢየሱስ ከኛ የሚፈልገውና የነፈግነው ነገር ምን ይሆን?

የኋላ ኋላ "እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘላለም ከቶ አይጠማም" ያለው እሱ ኢየሱስ መጀመሪያ ላይ "ውሃ አጠጭኝ!" አላት፤ እኛንም በሕይወታችን የሚጠይቀን የሆነ ነገር ካለ ያን ነገር ሊቀማንና ባዶ ሊያስቀረን ሳይሆን በዘላለማዊ ዋጋ ሊለውጥልን አስቦ ነው፤ እሱ አያታልልም።

ይህች ሳምራዊት ኢየሱስን "ጌታ ሆይ! አንተ ነቢይ እንደሆንህ አሁን አወቅሁ" ያለችው "ባል የለኝም ማለትሽ ልክ ነው፤ ምክንያቱም አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁንም ከአንቺ ጋር ያለው ሰው ባልሽ አይደለም ስለዚህ እውነቱን ተናግረሻል" በማለት እሱ የማያውቀው የመሰለ ታሪኳን ሲነግራት ነው። የኛም ታሪክ ከርሱ ሊሰወር አይችልም፤ ውስጣችንንም ስለሚያውቅ ነው የበለጠ ነገርን ሊሰጠን ዛሬ በፊታችን ለማኝ የሆነው። ስለዚህ በፊታችን ሆኖ ጥማቱን ለሚገልጽልን ጌታ ግላዊ ምላሻችንን እንስጠው፤ አይ ገና ከዓለም ጉድጓድ ውሃን መቅዳቱ አልታከተኝም፣ አሁን እሱን ለመስማት ጊዜም ፍላጎቱም የለኝም ብንልም እንኳ ክርስቶስ እኛን ለመስማቱ ጊዜም ሆነ ፍላጎት እንዳለው ቃሉ ይነግረናልና ፈቃዳችንን ያዳከመውን ኃይል አሸንፈው ያለፉ ቅዱሳን አማላጅነትና የእመቤታችን ድጋፍ ለውሳኔያችን ኃይል ይሁኑን።