ዘጥምቀት

ዛሬ "ሰማይ" ስለኛ መርገም አያውጅልንም!

Buruktimketበዚህ የክርስቶስን ልደት ከጥቂት ቀናት ባከበርንበት መንፈስ የእሱን ጥምቀት እንድናከብር ሥርዓተ አምልኳችን ይጋብዘናል። ክርስቶስ በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ለመጠመቅ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እስኪጠመቁ እንደጠበቀ "ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ" በማለት ወንጌላችን ይገልጽልናል (ሉቃስ 3:21)። ይህ ከልደቱ ጀምሮ ራሱን ከሁሉ ዝቅ ማድረግ ያሳየን ክርስቶስ በጥምቀቱም ለዚያውም ኃጢአት የሌለበት እሱ መጠመቅ ሳያሻው ከሁሉ በኋላ በመጠመቅ አሁንም ለክርስትና ትሕትና ምን ያህል የመዳን በር መሆኑን ሊያሳየን ወደደ።

ያለትሕትና ደኅንነት ያለመኖሩን በመላ ሕይወቱ መስክሮልናል፤ እኛም ይህን እናስብ ዘንድ የርሱን ጥምቀት ከኛ ጥምቀት ጋር በማተሳሰር በትሕትና ማለትም እውነተኛ ማንነታችንን ለርሱ በመግለጥ እንድን ዘንድ ተጠርተናል። ጥምቀት የሞትና ትንሣኤ ማኅተም ነው፤ የተጠመቀ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር ሞቶ ተነሥቷል። ክርስቶሳዊ ትንሣኤ ደግሞ በጨለማ፣ በተዘጋ መቃብር፣ በተስፋ ቁርጠት ላይ መሰልጠን ማለት ነው። በጥምቀተ ጸጋ ክርስቲያን በመሆናችን ይህን ተስፋ ወርሰናል። ይህን ድልና ተስፋ በምን ሁኔታ እያሳለፍነው መሆኑን ማሰብ ይገባናል። ይህን ጸጋ ራሳችን እየኖርነውና ለሌሎች በማካፈል ወይስ ክፋትንና ምሬትን በመኖር ላይ ነን? የጠላታችን ሰይጣን ትልቅ ድል በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ በክርስቶስ ደስተኛና ተስፈኞች እንዳንሆን መጣር ነውና ዛሬ ጥምቀታችንን በማሰብ እንታደስ።

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ሲጸልይ "ሰማይ ተከፈተ፤...አንተ የተወደድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ" (ሉቃስ 3:22)። በመጀመሪያ ይህ የእግዚአብሔርን ቅርብነት ዳግም ያረጋገጠ ክስተት መሆኑን እናስተውላለን። በክርስቶስ ልደት የእግዚአብሔር ቅርብነት እንደተገለጠ ሁሉ፤ አሁንም ሰማይ ተከፍቶ ፍቅር ታወጀ፦ "አንተ የተወደድህ ልጄ ነህ" የሚል ድምፅ አስተጋባ። በምንም ዓይነት የሕይወት ልምድና ድርጊቶች እስከዛሬ ያለው ዕድሜያችን ያለፈ ከሆነም እንኳ ዛሬም "ሰማይ" ስለኛ ሌላ መርገም አያውጅልንም፤ "የምወድህ/ሽ ልጄ" ይለናል። ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር የያንዳንዳችንን ልባዊና ተግባራዊ ጆሮን ይጠብቃል።

ጥምቀታችንን በኖርነው ቁጥር ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ይለመልማል፤ ውሃ ባለበት ሁሉ ሕይወት አለና በውሃ የተመሰለውን መጠመቃችንን ሕያው ባደረግነው መጠን የሕይወት ጉዟችን ትርጉም ያገኛል። እግዚአብሔር "አንተ የተወደድህ ልጄ ነህ" ሲለን ተሳስቶ ወይም በደንብ ሳያውቀን እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ እርሱ አይሳሳትም አያሳስትም። በርሱ በኩልስ ሁሌም እንደተፈቀርን ነን። ምናልባት ይህ ነገር እውነት አልመስል ካለን እርሱ ስላላፈቀረን ወይም ስለጠላን ሳይሆን እንደተፈቀሩ ልጆቹ በሕይወት ካለመመላለሳችን ይሆናልና ዛሬ ላይ ቆም ብለን እንደፍቅሩ ለመኖር እናቅድ።

ጥምቀት፤ የኢየሱስን ማኅተም በነፍስህ ይዘሃልና ዳግም አስተውለው/አስተውዪው፣ አንተ/ቺ የክርስቶስ ነህ/ነሽ ይለናል። አይ የአንተ አይደለሁም ብንል እንኳ ክርስቶስ በቃሉም ሆነ በተለያዩ የዕለታዊ ሕይወታችን ክስተቶች "እኔ የአንተ/የአንቺ ነኝ" ስለሚለን እሱን ዝም ማስባል እንደማንችል ከሰማያት የተሰማውና በክርስቶስ ጥምቀት የተሰማው የአብ እወጃ ያስታውሰናል። በርግጥ እሱ የሰጠንን ጊዜ ሁሉ አላውቅህም፣ አልወድህም በሚል አናኗር ካሳለፍነው በአንድ ወሳኝ ወቅት ክርስቶስ "አላውቅህም/አላውቅሽም" ሊለን እንደሚችል ወንጌል አልሸሸገንም። አሁን ገና ጊዜው በእጃችን ሳለ "አንተ የተወደድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል" ሲለን የምድራዊ ኑሯችን ተልእኮ ለዚህ መልስ መስጠት ነውና በሙሉ ሕልውናችን እናስተናግደው።;