ዘዕርገት

የቅዳሴ ንባባት


1ኛ ቆሮ.16:1-9
1ኛ ዮሐ. 2:12-15               የሐዋ. ሥራ 20:7-17               ወንጌል ዮሐ. 16:23-32

በኢየሱስ ስም መጸለይ

የእግዚአብሔር ስም ታላቅነት

አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ፥ ምስጋናህ በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሏልና። መዝ. 8:1

ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን። መዝ. 103:1

ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ የእግዚአብሔርንም ስም አመስግኑ። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን። ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የእግዚአብሔር ስም ይመስገን።መዝ. 113:1-3

በኢየሱስ ስም መጸለይ ምን ማለት ነው?

ዕርገትመጀመሪያ በኢየሱስ ስም ስለ መጸለይ ቅዱስ መጽሐፍ ምን እንደሚያስተምረን እንመልከት።

በኢየሱስ ስም መጸለይ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 14፡13 “እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” ዮሐ.14፡14

“በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል።” ዮሐ. 16፡23

“እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ።” ዮሐ 16፡24

“በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም” ዮሐ. 16፡26 በሚሉት የእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህም ምክንያት ነው በአብዛኛው ጸሎታችን ማጠቃለያ ላይ “በእግዚኢነ ኢየሱስ ክርስቶስ…”፤ “በአሐዱ ወልድከ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ...” ማለትም “በአንድ ልጅህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ…” እያልን የምንጸልየው።

በክርስቶስ ስም መጸለይ ማለት በእግዚአብሔር ፊት ከክርስቶስ ጋር መቅረብ፡ በሥልጣኑ መጸለይና፤ እግዚአብሔር አብን ስለምትወደው ልጅህ ጸሎቴን ስማልኝ ብሎ መጠየቅ ማለት ነው። በኢየሱስ ስም መጸለይ እንደ እግዚአብሔር አብ ፈቃድ መጸለይ ማለት ነው። “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።” (1 ዮሐ. 5፡14-15) በኢየሱስ ስም መጸለይ ማለት ለእግዚአብሔር ክብርና ሞገስ መጸለይ ማለት ነው። “በኢየሱስ ስም” ብለህ መጸለዩ ግን ለእግዚአብሔር ክብርና በሱ ፈቃድ ካልተጸለየ በስተቀር ቃሉን ብቻ መጥቀስ አይበቃም። በክርስቶስ ስም መጸለይ ማለት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ፈቃዳችንን አሰማምተን እንጸልያለን ማለት ነው።

በኢየሱስ ስም መጸለይ ማለት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መጸለይ ማለት ነው። ክርስቶስ የአባቱን ፈቃድና እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለሚያውቅ በስሙና ከርሱ ጋራ ሆነን ስንቀርብ ጸሎታችን ይሰማልናል።

በኢየሱስ ስም መጸለይ

· ስለሰው ልጆች መዳን መጸለይ ነው

· የቀራንዮን ድል የግል ማድረግ ነው

· በጥምቀት ጸጋ የተቀበልነውን ንጉሣዊ፡ ነቢያዊና ክህነታዊ ተልእኮውን ለመኖር መለመን

· በክርስቶስ ሙሉ ሥልጣን መጸለይ ማለት ነው

ለምን በኢየሱስ ስም መጸለይ ያስፈልጋናል?

በኢየሱስ ስም መጸለይ የሚያስፈልግበት ምክንያት “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊሊጵ 2፡ 6-11) ስለሚለን ነው።

አንድን ነገር በሌላ ሰው ስም መስራት ሁለት መሠረታውያን ነገሮች ያስከትላል፡

1. በስሙ የምንለምነውን ሰው የመሥራት ሥልጣን መብት መጠቀም። የገዛ ራስህ ሥልጣንና መብት ስለሌለህ መብትና ሥልጣን ኖሮት ትጠቀምበት ዘንድ ለመሥራት ሥልጣን በሰጠህ ሰውየ ሥልጣን ትሠራለህ ማለት ነው።ዳዊት ጎልያድን በተዋጋበት ጊዜ በስሙና በኃይሉ አልተዋጋም: “ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው። አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።” (1 ሳሙ 17፡45) ይሄ ነው ዳዊትን ድል ያቀዳጀው።

2. በሌላ ሰው ስም ተልከህ በሌላ ሰው ስም ስትመጣ እሱን ተክተህ እየሠራህ ነው ማለት ነው። እንደመልክተኛ የሚቀበልህም ሰው ልክ የላከህን እንደሚቀበል አድርጎ ተቀብሎ ያነጋግረሃል። ባንተ ማንነት ሳይሆን የላከህ ውክልናውን የሰጠህ ማን መሆኑን በማወቅ በሚገባ ይቀበልሃል። ዳዊት ወደ ናባል በስሙ የላካቸውን ባለመቀበልና በመስደብ ናባል ዳዊትን እንዳልተቀበለና እንደ ሰደበ ተቆጠረበት። “የዳዊትም ጕልማሶች መጡ፥ ይህንም ቃል ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነግረው ዝም አሉ። ናባልም ለዳዊት ባሪያዎች። ዳዊት ማን ነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? እያንዳንዳቸው ከጌቶቻቸው የኰበለሉ ባሪያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው። እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን? ብሎ መለሰላቸው…” 1 ሳሙ 25፡9….{jathumbnail off}

ስለዚህ በምንጸልይበት ጊዜ በእምነት በተስፋ በፍቅርና በኢየሱስ ስም መጸለይ አለብን። ስሙ ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን።

አባ ዓውተ ወልዱ ሲታዊ