እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘክረምት 2ኛ

 ዘክረምት
ምስባክ:- ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፤ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፤ ዘያበቁል ሣዕረ ውስተ አድባር............እርሱ ደመናትን በሰማይ ላይ ይዘረጋል፤ ለምድር ዝናምን ይሰጣል፤ ተራራዎችንም በለምለም ሣር ይሸፍናል። መዝ. 147:8 
የዕለቱ የቅዳሴ ንባባት ሙሉ ጥቅሶቹን በመጫን ያንብቧቸው ፦ 
 
ይህ ሰንበት ክረምት ተብሎ የሚጠራው ወቅታዊ ዑደት መጀመሩ በጸሎት ሥርዓት የሚታወጅበት ሲሆን ንባባቱና ወንጌሉም በዚህ ወቅት ምሳሌነት የሰውን ልጅ ወደ ደኅንነት የሚጋብዙ ናቸው። የዛሬው ወንጌል ኢየሱስ የተናገረውን አንድ ምሳሌ ማእከል በማድረግ የእግዚአብሔር ቃልን መስማት አንድ ነገር በተግባር ላይ ማዋሉ ደግሞ ፍጹም ሌላ ነገር እንደሆነ አጉልቶ ለማሳየት ይሞክራል። በተለያየ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይከተሉት እንደነበር ክርስቶስ ያውቅ ነበርና ይህ ብዙ መስሎ ይታይ የነበረው ቁጥርን ቢያንስ በአራት ክፍል ለይቶ ለማስረዳት በጣም ሊገባቸው በሚችል ሁኔታ ዘርን በሚዘራ ገበሬና በተቀባይዋ መሬት ምሳሌ አስተማረ። በዚህም የእግዚአብሔርን ቃልና የሰውን ልጅ ልብ፣ ቃሉን የመቀበልና የመመለስን ሁኔታ አስረዳ። 
በዚህ ምሳሌ ውስጥ በእግዚአብሔር ቃል ፊት ምን ዓይነት ምላሽ የሰው ልጅ እንደሚሰጥ የሚያስረዱ አራት ዓይነት ሰዎችን እናገኛለን፤ ትንሽ ካሰብነው ግን አምስተኛ ዓይነትን መጨመር እንችላለን። ያም የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ምንም ፍላጎትና ፈቃደኝነት የሌላቸው፣ የእግዚአብሔር ስም ሲጠራ፣ የቤተ ክርስቲያን ነገር ሲወራ፣ የምሥጢራት ነገር ሲወሣ ልክ ቆርቆሮ በጥፍር የተቧጠጠ ያህል ለመስማት የሚከብዳቸው ሲሆኑ እነዚህ ወንጌሉ መጀመሪያ ላይ ካስቀመጣቸው ዘሩ ሲዘራ በ"መንገድ ዳር" ከተመሰሉትም ሊወዳደሩ የማይችሉ ናቸው። ይህን መሰል ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ተጋፍጠው በፊቱ እስካልተንበረከኩ ድረስ ይህ "ሰቅጣጭ" ድምጽ ዕረፍት እንደነሣቸው ይኖራል - ሲቀበሉት ግን ዕረፍቱን ያበዛላቸዋል። 
ወንጌሉ ወደሚያቀርብልን የአዳማጭ ዓይነቶች ስንመለስ ለሁሉም እውነት የሆነው ነገር የእግዚአብሔር ቃል (ዘሩ) ለሁሉም እንደተዘራ ማለትም ሁሉም እንደሰሙ እናነባለን፤ በዚህ ወንጌል ውስጥ መስማት የሚለው ቃል ዘጠኝ ጊዜ ሲጠቀስ ሁነኛ ትርጉሙም አዳምጦ ወደ እምነትና የተግባር ፍሬ የሚያደርስ ዓይነት መስማት እንጂ ሰምቶ እንዴት ደስ ይላል ወይም  ያሳዝናል...ወዘት በማለት እንደ አንድ ዜና  ወይም ትምህርት ወይም ወሬ ነገር የሚነፍስበት ዓይነት መስማት አይደለም። በዚህም መሠረት መስማት የሚያስከትለው እምነትና ፍሬ ጋር እንዳይደርሱ ከዲያብሎስ ጋር ሊዋጉ ያልወሰኑ ግን ቃሉን የሚሰሙ በመንገድ ዳር ዓይነት መሬት ሲመሰሉ፤ በጭንጫማ መሬት የሚመሰሉትም በስሜታዊነት፣ በሆሆታና በሞቅታ ስሜት ለቃሉ ምላሽ ለመስጠት የሚወስኑና ወደ ዕለታዊ ሕይወት ሲመለሱ ያ ሁሉ ስሜት በንኖ የተለመደ ዓይነት ፍቅር የሌለበት፣ ሌሎች ላይ የመፍረድና በስሜታዊነት የሰሙትን ቃል እያጣቀሱ የሚመጻደቁትን ሊያመለክት ይችላል። 
በእሾኻማ ቂጥቋጦ መካከል የወደቀው ዘር ቃሉን ሰምተው በንስሐ ወደ አምላካቸው እንዳይመለሱ ከሀብትና ዝና ጥማት፣ ከጊዜያዊ ደስታዎች ፍለጋ ነጻ መሆን አቅቷቸው የአናኗር ዘይቤያቸውን መለወጥ ያልፈለጉ ቃሉን እያወቁ በሌሎች ነገሮች የታነቁትን ይወክላል። በመጨረሻም በመልካም መሬት የተመሰሉት ወንጌሉ በቅን ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁ ይላችዋል። ይህ ቅን ልብ ምንድነው ካልን፤ በውስጣችው ያለውን የእግዚአብሔር ድምጽ የሚያከብሩ፣ በክርስቲያንነታቸው የትምና ከማንም ጋር ቢሆኑ የማያፍሩ፣ እምነታቸውን የማያደራድሩ፣ የኅሊናቸውን ድምጽ ጩኸት ሳይቀንሱና ሳያስተባብሉ፣ ጆሮ ዳባ ልበስ ሳይሉ እንደመንገድ መሪ የሚከተሉ ዓይነት ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የተቀበሉት የቃሉ መብራት ላይ እንቅብ ሊደፉበት የማይፈቅዱ ናቸው። ወንጌሉ በመጨረሻ ቁጥሮች ላይ (ቁጥር 21) "ኢየሱስም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚፈጽሙት ሁሉ ኣነርሱ እናቴና ወንድሞቼ ናቸው አለ" ይለናል፤ ይህን ሲል በመልካም መሬት የተመሰሉትን በሌላ አባባል ለመግለጽ እንደተጠቀመበት አያጠራጥርም።
ብዙ ጊዜ ይህን መሰል ምሳሌዎች ስንሰማ ፈተና የሚሆንብን እገሌና እገሊትን በየጎራው ለማስገባት የምናደርገው ጥረት ነው። ግን የእግዚአብሔር ቃል ራሳችንን ነው መጀመሪያ የሚጋፈጠን። ስለዚህ በዚህ ሰንበት የእግዚአብሔርን ቃልና የዕለታዊ ሕይወት ምላሻችንን እንመርምርና ለቃሉ ቅን ልብ እንዲኖረን እንትጋ።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት