እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘጽጌ 3

ዘጽጌ 3 -          ሞኝነት ወይስ ስኬት?

ኤፌ.6:1-9       ራእይ 12:1-12        ሐዋ.7:23-29       ሉቃስ 12:16-31

ZeTsigeየዛሬውን ወንጌል ምሳሌ ማለትም እርሻው በጣም ያፈራለት ሀብታም ሰውዬ ያለውን ጎተራ አፍርሶ ተለቅ ያለ ለመሥራት ማቀዱንና በዚያም እህሉን አከማችቶ ነፍሱ በደስታ ለዓመታት እንድታርፍለት መመኘቱን፤ እግዚአብሔርም ይህን ሰው እንደሞኝና ሰነፍ መገሰጹን ስናነብ ሞኝነት ምንደነው ብለን መጠየቁ ሞኝ ያለመሆን ዕድላችንን ያሰፋዋልና በዚህ ዙሪያ ትንሽ እናስተንትን።

የእግዚአብሔር ቃል ሀብታሙን ሰውዬ <<አንተ ሞኝ>> ብሎ ሲገስጸው እንሰማለን። በእኛ ዘመን ይህን የወንጌል ክፍል ለሚያነብ ሰው ወንጌሉ ሰውየውን ሞኝ ማለቱ ራሱ ሞኝነት ሊመስል ይችላል። አንድ ሰው ሠራ፣ ሀብት አጠራቀመ፣ መደሰት ጀመረ ደስታውም ቀጣይ እንዲሆንለት በልፋቱ ፍሬ ተስፋ አደረገ ታዲያ ይሄ ስኬት እንጂ ሞኝነት ሊባል ይችል ይሆን?

በርግጥ ወንጌል ውስጥ ያለው ሰው ሀብታም በመሆኑ ብቻ ሞኝ ቢባል ኖሮ ዛሬ ሀብታም የሆኑና ለመሆን የሚጥሩ ሁሉ ሞኝ እንዲሁም ድኻ የሆነው ሁሉ አስተዋይ፣ ብልህ በተባሉ ነበር። ልዩነት የሚፈጥረው ነገር ሀብታምነትና ድህነት በራሱ ሳይሆን እግዚአብሔርን ከዕለት ኑሮው፣ ከሕይወቱ፣ ከአጀንዳው፣ ከፕሮግራሙ ወይም ከእቅዱ... ውጭ ባደረገና ባላደረገ ሰው መካከል ነው።

አብዛኛዎቻችን እግዚአብሔርን ከሕይወታችን ውጭ አድርገናል የሚል ግንዛቤ ላይኖረን ይችላል። ቢያንስ በእቅድ ደረጃ ከርሱ መራቅ አንፈልግም። ትምህርቴን ስጨርስ፣ ትንሽ ፋታ የሚሰጥ ሥራ ላግኝና፣ ትዳር ስይዝ...ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር እቀርባለሁ፣ ቤተ ክርስቲያኔን እከታተላለሁ፣ ምሥጢራትን አዘወትራለሁ...ወዘተ እያልን እናስብ ይሆናል። ሆኖም ግን ለሥጋዊ ነገሮቻችን ቀጠሮ እንደማንሰጥ ሁሉ ለመንፈሳዊነታችንም ቀጠሮ መስጠቱ ሞኝነት ነው። አልበላም አልጠጣም አልተኛም አልተነፍስም...ብለን አይደለም ለዓመታት ለቀናት ቀጠሮ ብንይዝ ሞኝነታችን ምስክርም አያሻውም። በተመሳሳይ ሁኔታም ለተወሰኑ ጊዜያት አልጸልይም፣ ስለ ክርስትናዬ ማሰብ አልፈልግም፣ የእግዚአብሔርን ቃል አላነብም...ስንልም የዛሬው ወንጌል <<ሞኝ>> የማለቱ እውነት ይገባናል። ሀብታም ሆነ ድኻ፣ ተማሪ ሆነ ሠራተኛ፣ ባለትዳር ሆነ ላጤ በሕይወቱ እግዚአብሔርን ከሚያርቅ ሰው ሌላ ሞኝ የለም።

ስለዚህ ከዛሬው ወንጌል አንድ ነጥብ ብቻ እንኳ እንውሰድ ካልን ክርስትናችንን ካለንበት የአናኗር ሁኔታ ጋር እንዴት አስማምተንና አዋህደን እንደምንጓዝ ማስተዋልን ያመለክታል። እግዚአብሔር በተፈጥሮው ከቦታ ወይም ከጊዜ ውጭ ሊሆን የሚችል፤ እንዲሁም በጊዜና በቦታ ብቻ ሊወሰን የሚችል ማንነት የለውም። እሱን ያራቅነው ሲመስለን ራሳችንን ነው ከርሱ የምናርቀው። እኛ ባለንበት እሱ አለ፣ በዛሬዋ ዕለትና በአሁኑ ሰዓት አለ። ይህ ለኛ አስጭናቂ እውነታ ሳይሆን ዕረፍት ሰጪ ስጦታ ነው። እሱን ለማግኘት መኳተንና ጊዜያት መጠበቅ አያስፈልገንም። እኛ እንወስን ብቻ እርሱ ዝግጁ ነው።

እግዚአብሔርን ለማግኘት የሚደረገው ረጅሙ ጉዞ ወደ ልባችን የምናደርገው ጉዞ ነው ይባላልና በየዕለቱ ልባችን ውስጥ የመግባት ውሳኔንና ልምድን ካዳበርን ከውጫዊው ሀብት ባርነት ነጻ መሆን እንችላለን። ገንዘብና ሀብት እግዚአብሔርን ከማግኘትና ከማምለክ ከገታን ሞኝ የሚለው ስም ያንሰናል። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር ገንዘብ በኛ ላይ የሚፈጥረው አስተሳሰብ ቀላል ያለመሆኑን ነው። ሀብት ወይም ገንዘብ ሲኖረን የምናስበውን የማድረግ፣ የፈለግንበት ቦታ የመሄድ፣ ባሰብነው መልክ የመኖር...እድላችን የሚጨምር ስለሚመስለን ገንዘብ በያዝን መጠን ለእግዚአብሔር አሳቢነትና አድራጊነት ከመስገድ ይልቅ ለገንዘብ ጉልበት ራሳችንን ማስገዛት እንጀምራለን፤ በዚህም በነገሮች ሁሉ ቅድሚያ ለእግዚአብሔር መስጠቱን እየቀነስን እንመጣለን። በነፍሳችንና በሥጋችን ሙሉ ስልጣን ያለው ክርስቶስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ ስለነፍሳችን እንድናስብ ጠርቶናል። በናኝ ለሆነ ነገር እስከ ዘላለሙ ብን እንዳንል ያሳስበናል፤ "አንተ ሞኝ! ዛሬ በዚህች ሌሊት ነፍስህ ከአንተ ትወሰዳለች"፤ ስለነፍሳችን ሳንወስን አንድ ሌሊት አናሳልፍ።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት