እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ታማኙና መልካሙ አገልጋይ - ዘገብር ኄር

ዘገብር ኄር 

(2ጢሞ. 2÷1-13) (1ዼጥ. 5÷2) (የሐዋ. ሥራ 1÷6-11)  (ማቴ. 25÷14-30)

Parable of the Talentsይህ 6ኛው የዐቢይ ፆም ሰንበት በግዕዝ ዘገብር ኄር በመባል ይታወቃል። ገብር ኄር ማለት ቸር፣ በጎ፣ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው። ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን ጸጋ የምናስተነትንበትና መክሊቶቻችንን በመለየት የምናመሰግንበት ሰንበት ነው። ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሲፈጥር ጀምሮ ለእያንዳንዱ  እንደየዐቅሙ መክሊቶቹን ይሰጣል። ወንጌሉ "ወደ ሌላ አገር የሚሄድ አንድ ሰው አገልጋዮቹን ጠርቶ ንብረቱን አስረከባቸው፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በማካፈል...ሄደ" ይላል። ለአንዱ 5፣ ለአንዱ 2፣ እንዲሁም ለአንዱ 1 መክሊት ሰጣቸው።

የምሳሌው ትርጉም ግልፅ ነው፡፡ በምሳሌው ውስጥ ያለው ሰው ኢየሱስን ይወክላል፤ ሰጪውም መልሶ ተቀባዩም እራሱ ነው። በዐደራ የተቀበሉት ደግሞ አገልጋዮቹ ናቸው። አገልጋዮቹ  እኛንና በዓለም ሁሉ የሚኖሩትን ሰዎች በሙሉ ይወክላል። የቤተ/ያን መሪዎችን፣ ባለሥልጣናትን፣ ምእመናንን፣ ሀብታሞችን፣ ወዘተ ያካትታል።  መክሊቶቹ ጌታ በዐደራ የሰጠን ርስት ናቸው፡፡ ርስቱስ ምንድን ናችው? ቅዱስ ቃሉ ፣ ቅዱስ ቁርባን ፣ በሰማያዊ አባት ላይ ያለን እምነት ፣ ይቅር ባይነት፣ መልካምነት… “መክሊት” የሚለው ቃል እኛ እነሱን እንድናደርጋቸው በዐደራ የሰጠንን የጌታ ሀብትን ይወክላል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ትንተና መሠረት የአንድ መክሊት ግምት በዘመኑ የ20 ዓመት ደመወዝ ያህል ነው። መክሊቶቹ የሚሰጡን እኮ ሌሎችንም ለመጥቀም ጭምር ነው፡፡ ፍሬ እንድናፈራ፡፡ መሬት ውስጥ እንዳንቀብር። መቅበር በራሱ የፈጠራ ችሎታን፣ የፍቅር ፍሬያማነትን የሚያግድና አደጋን መፍራትን ያስከትላል። መክሊቶቻችንና ስጦታዎቻችን የተኞቹ ናቸው? ምናልባት ዕውቀት፣ ሀብት፣ ሥልጣን፣ ምንኩስና፣ ትዳር፣ ልጆች፣ ጤንነት፣ ጊዜ፣ ዕድሜ፣ ሰላም፣ ምህረት፣ ርህራሄ፣ ይቅር ባይነት፣ ክርስትና ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁሉ ከኛ የሆኑ አይደሉም፤ ከእግዚአብሔር የሚመነጩ ናቸው እንጂ። ከእኛ የሆነ አንዳች ነገር የለም። መልካምና በጎ ስጦታ ሁሉ ከላይ ነውና (ያዕ.1÷17)። በእምነታችን ምን ያህል “ታምነናል”? በተስፋችን ምን ያህል ሰዎችን አበረታተናል? ለጎረቤቶታችን ምን ያህል ፍቅር አጋርተናል? ለተሰጡን ልጆች ምን ያህል ፈጣሪን አመስግነናል? ዳዊት በመዝሙሩ 127÷3 “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” ይላልና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም 2ቆሮ. 9÷15 ላይ “ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን” ይለናል። ሰው በቤቱ፣ በትዳሩ፣ በሥራው፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የእግዚአብሔርን ለዛ ማጣጣም ካልቻለ፤ በመክሊቶቹና በስጦታዎቹ ኢየሱስን መመስከር ካልቻለ በመንፈሱ ሙት ነው። ሕይወቱም የስደት ሕይወት ነው።  መክሊቱ ደግሞ በእጃችን ነው፡፡ ይህን ከተረዳን በራሳችን ላይ መመካት ትተን በእግዚአብሔር ላይ መመካት/ መተማመን እንጀምራለን።

በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ፣ በግንኙነታችን ውስጥ፣ የኢየሱስን የፍቅርና የይቅርታ ጥግ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በየቀኑ እናያለን። የወንጌልን ቃል እንዳንቀብር!  የጥል ግድግዳዎችን የሚያስወግድልን ባለመክሊቱ ነውና እንፍቀድለት፡፡

ከምሳሌው ምን መማር እንችላለን?

1.  በመጀመሪያ ይህ ምሳሌ ስኬት የሥራችን ውጤት መሆኑን ያስተምረናል፡፡

በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር አዳምን እንዲሠራ እና እንዲንከባከበው በገነት ውስጥ እንዳስቀመጠው እናያለን፡፡ እኛም እንዲሁ እንድንሠራ ተፈጥረናል፡፡ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ጌታችን አሁን እንድናከናውን የሚጠብቀን ተልእኮ አለን፡፡

2.  የመክሊቶቹ ምሳሌ ሁላችንም እኩል መክሊት እንዳልተሰጠን ያስተምረናል፡፡

“ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው” ተሰጥዖ ተሰጥቷል፡፡ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ እንደ አምስት መክሊት አገልጋይ ማትረፍ የሚችል አለመሆኑን ጌታው ተረድቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሌሎቹም።

3. የመክሊቶቹ ምሳሌ የሚያስተምረን የምንሠራው ለራሳችን ዓላማ ሳይሆን ለመምህሩ እንደሆነ ነው፡፡ ለአገልጋዮቹ የተሰጣቸው መክሊት የራሳቸው አይደለም የተሰጡ እንጂ፡፡ ስለዚህ አያመጻድቁም፤ አያስመኩም፤ ሊወሰዱ ይችላሉና። ችሎታዎቻችንን ለግል ጥቅማችን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ለማክበርና ከፍ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡

4. የመክሊቶቹ  ምሳሌ በተሰጠን ስጦታ ማትረፍና ዐደራም እንዳለብን ያስተምረናል፡፡

ይህ የመክሊቱ ዐደራ  ለምእመኑ፣ ለቤተክርስቲያኑ - ለሰው ልጆች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ ዐደራ ነው። እግዚአብሔር በእኛ  ንብረት ሁሉ ላይ በተለይም እጅግ ውድ በሆነው በፍቅር ስጦታው ይተማመናል ። ነገር ግን ኢየሱስ እኛን በጥሬ ገንዘብ ብቻ አልተወወንም ፡፡ እርስ በርሳችን የመዋደድ ችሎታን፣ ጸጋንና ምህረትን ትቶልናል። ይህ ፍቅር ከገንዘብ የበለጠ ዋጋ ያለው ነው- ገንዘብ ፍቅርን ሊገዛ አይችልም። እስቲ ሌሎችን ለመርዳት፣  ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ለመስጠት፤ እግዚአብሔር የሰጠኝ ተሰጥዖ አለኝ እንበል። ለብቻዬ ከቀበርኩት መክሊቱ ይሞታል፡፡ በሌሎች ላይ ካዋልኩት ደግሞ ያድጋል፡፡ እግዚአብሔር እንድንወደውና እርስ በርሳችንም እንድንዋደድ ፈጥሮናል። እርስ በርሳችን ለመስማማት ፣ እርስ በርሳችን ፈገግታ ለመለዋወጥ ጊዜ አንውሰድ፡፡ የክርስቲያን ሕይወት ስለ ማግኘት ብቻ አይደለም፤ ስለ መስጠትም ጭምር ነው እንጂ፡፡

እግዚአብሔር አባታችን ሁል ጊዜም ስጦታዎችን በደስታና በነፃ ይሰጠናል። እኛም የመስጠትን ደስታ መፍራት የለብንም። ስጡ ይሰጣችኋል። ፍቅርን መቀበል ከፈለግን ለሌሎች ፍቅርን እንስጥ፡፡  ፍቅር በሰጠን መጠን በፍቅር እንሞላለን፡፡ ያለ ጥርጥር ከምንሰጠው በላይ እንቀበላለን። ደስተኛ ለመሆን ከፈለግንም፤ ለሌላ ሰው ደስታ ለመስጠት መሥራት ግድ ነው፡፡ ያኔ በማያልቅ ደስታ እንሞላለን፡፡

 ብዙውን ጊዜ  አትሌቶች፣ ተዋቂ ሰዎች፣ ተመራቂ ተማሪዎች... ስጠየቁ የስኬታቸውን ምስጢር ከመናገራቸው  በፊት “በመጀመሪያ እኔ ሁሉንም ክብር ለእግዚአብሔር እሰጣለሁ” ይላሉ። የመክሊት ሁሉ፣ የዕውቅት ሁሉ፣ የስኬትና የአሸናፊነት ሁሉ ባለቤትና ምንጭ እግዚአብሔር ነው። የስጦታዎች ሁሉ ለጋሽ ፈጣሪ ብቻ ነው። ለስጦታዎቻችን ማመስገን አስፈላጊና ትክክለኛ ነው። ክብር ሁሉ የእርሱ ነው።  ችሎታችን ሁሉ ፣ ስጦታችን ሁሉ ከእግዚአብሄር ይፈሳል፡፡ ካህኑ የክርስቶስን ሥጋና ደም በእጆቹ ይዞ  “ከእርሱ ጋር፤ በእርሱ ስም፤ በመንፈስ ቅዱስ አንድነት፤  ላንተ ሁሉን ለሚትችል እግዚአብሔር አብ፤ ክብርና ምስጋና ለዘላለም ይሁን” ሲል ሕዝቡም  “አሜን” ይላል። እግዚአብሔር የችሎታ ሁሉ ምንጭ ነው። አንድ ሰው “እግዚአብሔር ተሰጥዖን ሰጠኝ፤ ግን ችሎታውን ለማሳደግ ጠንክሬ መሥራት አለብኝ” ሊል ይገባል። የእኛ ተሰጥዖዎች በሙሉ ከእግዚአብሔር የመጡ ናቸውና  እግዚአብሔርን ለማገልገል ሁልጊዜ መጎልበት አለባቸው፡፡ መክሊቶቹ በሙሉ የእርሱ ናቸው እንጂ የእኛ አይደሉም ፡፡ ጌታ በምሳሌው ውስጥ ለእያንዳንዳችን የሰጠንን ልዩ ችሎታ እንዴት እንደምንጠቀምበት መምህሩ ለመተሳሰብ እንደሚመጣ ይነግረናል።

በምሳሌው ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሁለት አገልጋዮች በተቀበሉት መጠን ሌላ እጥፍ መልሰዋል። ይህም የጌታው ንብረት እንዲያድግ አስችሎታል። በዚህ መልኩ የእርሱ መንግሥት እንዲሰፋ፣ እግዚአብሔር የተሰጠንን እንድናዳብር፣ እንድናሳድግና እንድንጨምር እግዚአብሔር እየጠራን ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ስጦታዎች በየቀኑ  እያሳደግን ነው? መልሳችን ምናልባት አዎ ወይም አይደለም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለ ትክክለኛው ቀንና ሰዓት መጨነቅ ሊያሳስበን አገባንም፡፡ ያ የእኛ ጉዳይ አይደለም ፡፡ ግን ሊያሳስበን የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ በማንኛውም ጊዜ ሆነ በዘመናችን  ለጌታ መምጫ ቀን ለመዘጋጀት የበኩላችንን ማድረግ ነው፡፡ በዐደራ የሰጠንን መክሊት ካዳበርን “መልካም፣ ጥሩና ታማኝ አገልጋዮች” የሚለን ቀን ይመጣል።

የሌሎችን ሕይወት ለመቀየር ምን ያህል ሰርተናል? ያለንን ተሰጥኦ ለማህበረሰብ ግንባታ ምን ያህል ተጠቅመናል? ለልጆቻችን የተሻሉ ወላጆች ነን ወይ? ልጆችስ ለወላጆቻችን የተሻልን ነን ወይ? ለጎረቤቶቻችን መልካም ጎረቤቶች ነን ወይ? በእውነት ከእኔ የሚጠበቀውን አድርጌያለሁ ወይ? የእግዚአብሔርን መንግሥት በመገንባት ረገድ፣ ችሎታችንን ከመለየት አንፃር ምን ያህል ሰርቻለሁ? እንደ ክርስቲያን መጠን ጥሩ እና ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ እና ልጅ ነኝ ወይ?

የመክሊቱ ባለቤት ራሱ መልካም እረኛ ኢየሱስ ነው። ለልጆቻችን መልካም እረኞችና ጠባቂዎች ከሆን፤ በመልካምነታችን መክሊታችንን እናበዛለን። “በዐደራ የተሰጣችሁን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ...” (1ዼጥ. 5÷2)። በጌታ መምጫ ጊዜ መክሊቶቻችንን በማትረፍና በማበራከት ለመሸለምና የዘለዓለምን ሕይወት ለመውረስ ያብቃን። ሁላችንም “በኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጸጋ እንበርታ” (2ጢሞ. 2 ÷ 1)።

ምግባረ ሠናይቷ እመቤታችን ወደ ፈጣሪ የሚወስደውን መንገዱን ስለምታውቀው ትመራናለችና እንለምናት፡፡ ለአምላክ ፈቃድ አንድ ጊዜ “አዎ/ እሺ” አለች። ምንም ያህል ለመቀበል ከባድ ቢመስልም አዎ /እሺ ማለቷን አላቆመችም፡፡ እሽታዋንም አልቀለበሰችውም። እመቤታችን ያለ ገደብ  እግዚአብሔርን ታምናለች። በመክሊቷም ብዙ አትርፋለች፤ የብዙኀን እናትም ለመባል በቅታለች። ፈጣሪ መክሊታችንን ያበራክትልን፤ ያብዛልንም። አሜን።

አባ ያዕቆብ ማርቆስ - ገዳመ ቅ. ሥላሴ ዘሲታውያን - ሆሣዕና

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት