እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

2ኛ ጰራቅሊጦስ

2ኛ ሰንበተ ጰራቅሊጦስ

የቅዳሴ ንባባት - ኤፌ. 4:1-1-17 - 1ኛ ዮሐ. 2:11-18  - የሐዋ. ሥራ 2:1-14  - ወንጌል ዮሐ. 14:13-18


ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ (ዮሐ 14:15)

1. “ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም።” (ዮሐ 8:51)

2. “ እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። (ዮሐ 15:10)

3. “ አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸታም ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።(1 ዮሐ 2:4)

4. ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ። (ዮሐ 14: 21)



እግዚአብሔርን እንደምንወድ የሚያመለክተው ተግባራችን ነው። እግዚአብሔርን የሚወድ እግዚአብሔር የሚወደውን፣ እግዚአብሔር የሚያዘውንና እግዚአብሐር የሚፈልገውን ይፈጽማል። ከልጅነታችን በትምህርተ ክርስቶስ ከተማርንበት ጊዜ ጀምሮ የምናውቀው እውነት አለ፤ ያም እግዚአብሔር የፈጠረን እሱን እንድናውቅ እንድንወድና እንድናገለግል መሆኑ ነው ። ስለዚህ እግዚአብሔርን መውድድና መታዘዝ የተፈጠርንበት ዓላማና የክርስትና ጥሪያችን ነው።

አውቀንና ወደን ኃጢአትን ስንመርጥና ፍቅር የሆነው ሕጉንና ትእዛዙን በመጣስ ፈቃዱን ትተን ፈቃዳችንን በምንፈጽምበት ጊዜ እግዚአብሔርን በተግባራችን “አንወድህም” እንለዋለን ማለት ነው። እግዚአብሔርን መውደድ እንደሚገባን በደንብ እያወቅን ትእዛዙን በምንጥስበት ጊዜ ከሱ በላይ የምንወደው ነገር ወይም ሰው እንዳለን እንገልጻለን ማለት ነው። ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆነ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለን ክፉን ከመሥራት እግዚአብሔርን ከማሳዘን ርቀን፤ ነፃ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን በምንሄድበት መንገድ እንመላለሳለን።

እግዚአብሔርን የሚወድ ሁለመናውን ለሱ ስለሚሰጥ ከኃጢአት ባርነት ነጻ ይወጣል። ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ራሳችንን ከክርስቶስ ነጥለን ለአንድ ነገር ወይንም ለአንድ ሰው እንሰጣለን ማለት ነው። ክርስቶስን በሙሉ ልባችን፤ ነፍሳችን፡ አእምሮአችንና ኃያላችን ከወደድነው ግን ከክርስቶስ በፊት በፍቅር የምናሰልፈው ስለሌለ ሁለመናችን ለሱ ይሆናል እሱ ደግሞ የኛ ይሆናል።

አንዳንድ ጊዜ “ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት እንዲሉ ክርስቶስ ሰዎች መሆናችንን ያውቃል ይቅር ይለናል” የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችን እናገኛለን። ስለ እግዚአብሔር መሐሪነት አንጠራጠርም፤ ነገር ግን የምንወደው ከሆን ለምን እናሳዝነዋለን? ከኃጢአት ርቀን ከሱ ጋራ በሰላም መኖር ዛሬ በዚች ዓለም ነገም በሚመጠው በፍቅርና በሰላም ለመኖር እንችላለን። ስለዚህ እያሳዘነውና መሐሪ በመሆኑ ይቅርታን እየጠየቅን ከመኖር ኃጢአትን ከሕይወታችን አስወግደን ከፈተና ርቀን ከክርስቶስ ጋራ ዘላቂ አንድነትን ፈጥረን መኖርን እንደ ዓላማችን አድርገን በመምረጥ እንኑር።

ክርስቶስን መውደድ ስንሞት የሚሆን ነገር ሳይሆን በየዕለቱ ኑሯችን ውስጥ መለማመድ ያለብን ነገር ነው፤ ማለትም ሕይወታችንን በመቀየር፤ ወደ ኃጢአት የሚመሩ ነገሮችን፡ ሰዎችና ቦታዎችን መተው፡ ክፉ ልማዶችን ከነሥራችው ነቅሎ ከሕይወታችን ማራቅ፡ ክርስቶስ እኛን እንዳፈቀረንና እነደሚያፈቅረን ሁሉ እግዚአብሔርንና ባልንጀራዎቻችንን መውደድ ማስከተል አለበት። ክርስቶስ በኛ ፍቅር ምክንያት ምን ያህል እንደተሰቃየና የስው ልጅ ፍቅር በክርስቶስ ዘንድ ምን ያህል ክቡር መሆኑን ተገንዝበን እኛም በሱ ፍቅር ተወስነን እንኑር።

አእምሮአችንንና ልባችንን በክርስቶስ ፍቅር ካስገዛን ሰዎችንና ነገሮችን በሱ ዓይን ማየትና በሱ አንደበት መናገር እንችላለን። እግዚአብሔር አብንና ሰዎችን ለመውደድ ክርስቶስን ከልብ መውደድና ሕጉንም መፈጸም ያስፈልጋል።

የእግዚአብሔር ፍቅርና ኃጢአት ባንድ ላይ በልባችን መኖር አይችልም፤ ምክንያቱም ባንድ ጊዜ ለሁለት ጌቶች ልንገዛ ስለማንችል ሕይወታችን ይከፈፈላል። ክርስቶስን የሚወድ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየው ከሚችለው ነገር ሁሉ መለየት ይኖርበታል። ክርስቶስን መውደዳችን አስተሳሰባችንና አሠራራችንን ባጭሩ የኑሮ ዘይቤያችንን መለወጥ አለበት። ክርስቶስን መውደድ የክርስቶስን ፍቅራዊ ሕግ ከሁሉም በላይ ወደ ማስቀደም ይመራናል።

ክርስቶስን የመውደዳችን ዋና ምልክት ያለው ምን ያህል ቃሉን ማወቃችን ላይ ሳይሆን ምን ያህል ትእዛዙን መፈጸማችን ላይ ነው ክርስቶስ ራሱ በፈቀደው አሠራር መሠረት በቤተክርስትያኑ በኩል እነደሚመራን አድርገን መኖር ያስፈልገናል። ለሐዋርያቱ እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል እንዳላቸው ሁሉ ዛሬም ቤተክርስቲያንን የሚሰማ እሱን መስማት መሆኑን ሳናመነታ ይህንን ከፈጸምን ክርስቶስን እንወደዋለን ማለት ነው። ክርስቶስን እንወድሃለን እያልነው ካስተማረን ውጭ በሆነ መንገድ ከተጓዝን ግን ክርስቶስን ከሁሉም በላይ አላደረግነውም ሕጉን አልፈጸምንም ከሱም ዕጣ ክፍል የለንም።

ክርስቶስን መውደድና ሕጉን መጠበቅ ከሱ ጋር በሰላም መገኘትን ስለሚያስከትል ክርስቶስ በልባችን እንዲነግሥና የሕይወቱ ተካፋይ እንድንሆን በነጻ የተሰጠንን የክርስትና ሕይወት ጸጋ ሳናባክን እንኑረው። ኃጢአት በሟች ሥጋችን ላይ ከነገሠ ግን ክርስቶስ የሕይወታችን ንጉሥ ሊሆን አይችልም። በዚህ የምንጠየቀው እኛው ነን፤ ምክንያቱም ከክርስቶስ በኩል ለመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚሆን ሁሉ ስለተሰጠን በሱ በኩል ምንም የጎደለ ነገር የለም። ዛሬ በመንፈሳዊ ዓይናችን እግዚአብርን እያየንና እየታዘዝን ከተጓዝን በጊዜያዊና ሥጋዊ ኑሯችን የጀመርነውን ደስታ ነገ ከሱ ጋር ለዘለዓለም እንቀጥለዋለን።

ክርስቶስ ምን ያህል እንደሚወደን የምናየው በመስቀል ላይ እጆቹን ዘርግቶ “ይህን ያህል ነው የምወዳችሁ” እያለ ሕይወቱን ስለኛ ያሳለፈበትን የመስቀል መሥዋዕት ላይ ነው።

ስለዚህ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሆነን “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ 8፡35-39) ብለን በሱ እንመካ ፈቃዱንም እንፈጽም።


አባ ዓውተ ወልዱ ሲታዊ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት