ትምህርት ፲፩ - የታሪክ መጻሕፍት ጥናት - ክፍል ሁለት

የታሪክ መጻሕፍት ጥናት - ክፍል ሁለት 

ትምህርት ዐሥራ አንድ

Samson anbessa

መሳፍንት ማለት ምን ማለት ነው?

            መሳፍንት የሚለው ቃል በነጠላ መስፍን ከሚለው ቃል የተገኘ ነው፤ መስፍን ወደ ብዙ መደብ ሲቀየር መሳፍንት ይሆናል፡፡ መስፍን ማለት አዳኝ ፣ ጀግና ፣ ተዋጊ የሆነ ነገር ግን ንጉሥ ባይሆንም አንድን ሕዝብ የሚያስተዳድር እንዲሁም ለሕዝብ ፍርድን የሚሰጥ ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ ብዙ መስፍኖች ሕዝቡን ከጠላት የጭቆና እጅ ነፃ እንዲያወጡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለተነሡ መጽሐፉም “መጽሐፈ መሳፍንት” ተብሎ ተጠራ፡፡  

መጽሐፈ መሳፍንት በማን ተጻፈ? ስለምን ይናገራል?

            መጽሐፈ መሳፍንት ተብሎ የሚጠራው መጽሐፍ የመሳፍንትን ታሪክ ይተርካል ፡፡ መጽሐፉ ማን እንደጻፈው ፣ ምን ጊዜ እንደተጻፈ በእርግጠኝነት ባይታወቅም እንኳ የጻፈው ሳሙኤል ወይም በሳሙኤል ዘመን ከነበሩት ከነቢያት ወገን አንዱ እንደሆነ ይታመናል (1 ሳሙ 10፡ 10-12 እና 25) ፡፡ መጽሐፉ ሦስት ክፍሎች አሉት ፡፡

1) መሳፍንት የተነሡበት ምክንያት (መሳ 1-2)

2) የመሳፍንቱ ታሪክ (መሳ 3-16)

3) ስለ ዳን ጭቆናና ስለ ብንያም ኃጢአት (መሳ 17-21) ናቸው ፡፡

መጽሐፈ መሳፍንት ስለ መሳፍንቶች የሚተርክ ከሆነ መሳፍንት የሚለው ጽንሰ አሳብ በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ እንዴት ሊፈጠር ቻለ ?

በብሉይ ኪዳን ዘመን ነገሥታት በእስራኤል ከመሾማቸው በፊት መስፍን የተባለው ከንጉሥ ዘር የሆነ ሰው ሳይሆን አገሪቱን ከጠላት ወረራ የሚያድን አዳኝ ጀግና ነበረ ፡፡ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ርስት አገራቸው ከገቡና ኢያሱ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ትተው የአገሩን አማልክት በማምለክ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ ፤ እግዚአብሔርም ተቈጣቸው ፤ ወደ እርሱም ሊመልሳቸው ብሎ ለሚማርኩአቸው ወራሪዎች አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር ፡፡ ወራሪ በመጣ ቁጥር እስራኤላውያን ተጨንቀው ተጸጽተውም ወደ እግዚአብሔር ይጮኹና ይጸልዩ ነበር ፡፡ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ይምራቸውና መስፍንንም አስነሥቶ ከሚማርኩአቸው እጅ ያድናቸው ነበር (መሳ 2፡ 11-19 ፤ 3፡ 9-15) ፡፡ እነዚህ የሚያድኑ መሳፍንት 12 ሲሆኑ ከኢያሱ መሞት ጀምሮ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ እስኪሾም ድረስ 300 ዓመት ያህል አገሪቱን ጠበቁ ፡፡

በአጠቃላይ የመሳፍንት ዘመን በጣም አስፈሪና ጭካኔ የተሞላበት ጊዜ ነበር ፡፡ እስራኤላውያንና በአካባቢያቸው የነበሩ ጣዖት አምላኪዎች ለመኖር ሲሉ ደም በማፍሰስ ይታገሉ ነበር ፡፡ በመጽሐፈ መሳፍንት ያለው ታሪክ ምንአልባት በታሪካዊ ሁኔታዎች የተመሠረተ ይሆናል ፤ በተለይም በአፈ ታሪክና በአባቶች እምነት በሚያምር ሁኔታ የቀረበው የሶምሶን ታሪክ መነሻ እውነታ ይዞ የተተረከ ይመስላል ፡፡ መሳፍንትን የሚያነብ ሰው የሤራ ትረካንና ነፍስ ማጥፋትን (መሳ 3፡ 15-30) ፣ ማታለልንና ግድያን (መሳ 3) ፣ ጦርነትን (መሳ 6-8) ፣ አገር መክዳትና እኅትን ወይም ወንድምን የመግደል ወንጀልን (መሳ 9) ፣ ቅጽበታዊ ስለትን (መሳ 11) ፣ የእርስ በርስ ግጭትን (መሳ 12) ፣ ጥፋት ፣ ክህደትና ራስን ማጥፋትን የመሳሰሉት ያጋጥመዋል ፡፡

መሳፍንቱ የሚከተሉት ናቸው ፦ ዖትኒኤል (መሳ 3፡ 7-11) ፣ ግራኙ ናዖድ (መሳ 3፡ 12-30) ፣ ሰሜጋር (መሳ 3፡ 31) ፣ ነቢይት ዲቦራና ባራቅ (መሳ 4፡ 1-5) ፣ ጌዴዎን (መሳ 6፡ 1-8) ፣ አቤሜሌክ (መሳ 9፡ 1-57) ፣ ቶላ (መሳ 10፡ 1-2) ፣ ኢያዕር (መሳ 10፡ 3-5) ፣ ዮፍታሔ (መሳ 10፡ 1-2) ፣ ኢብጻን (መሳ 12፡ 8-10) ፣ ኤሎም (መሳ 12፡ 11-12) ፣ ዓብዶንና (መሳ 12፡ 13-15) ሳምሶን (መሳ 13፡ 1-16) ናቸው ፡፡  

በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ዲቦራና ባራቅ ማን ናቸው ?

            ዲቦራ በእስራኤል ውስጥ በመሳፍንት ዘመን የምትኖር ነቢይት ነበረች ፡፡ በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆናም ታገለግል ነበር  ፡፡ ዲቦራ በተራራማው በኤፍሬም ሀገር በራማና በቤቴል መካከል በሚገኘው በተምር ዛፍ ሥር ተቀምጣ ትፈርድ ስለነበር የእስራኤል ሕዝብ ውሳኔ ለማግኝት ወደ እርስዋ ይሄዱ ነበር (መሳ 4፡ 4-6) ፡፡ በጥንት ዘመን በአይሁዳውያን ባህል ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ብዙም ቦታ አልነበራቸውም፡፡ ዲቦራ ግን ለየት ባለ መልኩ ብዙ የጀግንነት ተግባራት አከናውናለች፡፡ ዲቦራ ነቢይት ስለነበረች ባራቅ ለተባለው እስራኤላዊ አስጠርታ የእግዚአብሔር የትንቢት ቃል ነገረችው ፡፡ ቃሉም ወታደሮች አዘጋጅቶ እስራኤላውያንን ያስጨንቅ ወደ ነበረው ወደ ሲሣራ እንዲዘምት ነበር ፡፡ ባራቅ ግን ዲቦራን አንቺ ከእኔ ጋር ወደ ጦር ግንባር ከዘመትሽ ብቻ ነው ሄጄ የምዋጋው በማለት አመነታ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በጠላቶቼ ላይ ድል የምቀዳጅበት ቀን መች እንደሚሆን ማወቅ አልችልምና አላት ፡፡ ዲቦራም ወደ ጦር ሜዳ አብራው እንደምትሄድ ቃል ገባችለት ፡፡ ቀጥሎም ዲቦራ ከባራቅ ጋር ዘመቻው ወደሚከናወንበት ወደ ታቦር ተራራ ቀጥሎም እስከ ሐሮሼት ድረስ በመሄድ ባራቅን ምን ማድረግ እንዳለበት እየመራችው ከቆየች በኋላ በድል ወደ ነበረችበት መንደርዋ ተመለሰች (መሳ 4፡ 8-16)፡፡ ሲሣራ በተባለው ጦረኛ ይመራው የነበረው የጠላት ጦር በሙሉ ተደመሰሰ(መሳ 4፡ 14-16)፡፡ ዲቦራም የምስጋና መዝሙርም ለእግዚአብሔር ዘመረች (መሳ 5) ፡፡

ከዚህ ከዲቦራና ባራቅ እንዲሁም የጠላት ጦር መሪ ከነበረው ከሲሣራ ጋር በተያያዘ መልኩ የምትጠቀስ አንዲት ሴት አለች፡፡ ይህችም ሴት ያዔል ትባላለች፡፡ የጠላት ጦር መሪ የነበረው ሲሣራ መሸነፉን በተረዳ ጊዜ ሸሽቶ የሔቤር ሚስት ወደ ሆነችው ወደ ያዔል ድንኳን ገባ፡፡ ያዔልም ሲሣራን ልትበቀለው ትፈልገው ነበር(መሳ 4፡ 17-18)፡፡ ሲሣራም “እባክሽ የምጠጣው ውሃ ስጪኝ፤ በጣም ጠምቶኛል” አላት፤ እርስዋም ከቆዳ የተሠራውን የወተት ዕቃ ከፍታ አጠጣችውና እንደገና ደበቀችው፡፡ ሲሣራም ለያዔል “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ አንድ ሰው መጥቶ ከዚህ ሌላ ሰው እንዳለ ቢጠይቅሽ ማንም የለም በዪው” አላት፡፡ ሲሣራ በጣም ደክሞት ስለነበር ከባድ እንቅልፍ ወሰደው፤ ከዚህ በኋላ ያዔል መዶሻና የድንኳን ካስማ ወስዳ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ካስማውንም በጆሮ ግንዱ ላይ በመዶሻ መትታ ራሱን ከመሬት ጋር አጣበቀችው፡፡ ባራቅ ሲሣራን እየፈለገ ሲመጣ ያዔል ልትቀበለው ወጥታ “ወደዚህ ና፤ አንተ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው፡፡ ስለዚህም ከእርስዋ ጋር ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ የድንኳኑ ካስማ በጆሮግንዱ ላይ እንደተቸነከረ ሬሳውን በመሬት ላይ ተጋድሞ አየ(መሳ 4፡ 21-23)፡፡              

ጌዴዎን በመሳፍንቶች ታሪክ ውስጥ በብሉይ ኪዳን ሲታወቅ በአዲስ ኪዳንም በእምነቱ ተመስክሮለታል (ዕብ 11፡ 32)፡፡ የጌዴዎን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት ይገለጻል ?

            ጌዴዎን ከእስራኤላውያን መሳፍንቶች አንዱ እንደሆነ ከላይ ተጠቅሷል (መሳ 6፡ 1-9, 6) ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ቀርቦ “አንተ ኀያልና ብርቱ ሰው ! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሂድ ! ባለህ ብርቱ ኀይል ሁሉ በመጠቀም እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ታደግ፤ እነሆ እኔ እራሴ ልኬሃለሁ” ሲል አዘዘው፡፡ ስለዚህ ጌዴዎን እስራኤልን ከምድያማውያን ሊያድን ተጠራ (መሳ 6፡ 11-24) ፡፡ ነገር ግን ጌዴዎን መልእክት ይዞለት ለመጣው “በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ አንተ በእርግጥ እግዚአብሔር መሆንህን የሚያስረዳ ምልክት ስጠኝ” በማለት እግዚአብሔርን ጠየቀ(መሳ 6፡ 17)፡፡ ጌዴዎን ያቀረበው መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚያረጋግጥ እሳት ከአለት ላይ ተነሥቶ መሥዋዕቱን በላው(መሳ 6፡ 21)፡፡ ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን በተገነዘበ ጊዜ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ ! የአንተን መልአክ ፊት ለፊት አየሁ” አለ፡፡ እግዚአብሔር ግን “ሰላም ለአንተ ይሁን ፤ አይዞህ አትፍራ ፤ አትሞትም” አለው፡፡ ጌዴዎንም በዚያ መሠዊያ ሰርቶ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው” ብሎ ሰየመው(መሳ 6፡ 24)፡፡   

ቀጥሎም ጌዴዎን ተልኮውን ተቀበለ፡፡ የበዓልን መሠዊያ ካፈረሰ በኋላ ይሩበኣል ተብሎ ተጠራ (መሳ 6፡ 25-32) ፡፡ ጌዴዎን 32, 000 ሰዎች ሲወጡለት በእግዚአብሔር ትእዛዝ 300 ሰዎችን ብቻ አስከትሎ ምድያማውያንን በማባረር አሸነፋቸው (መሳ 6፡ 33-8፡ 21) ፡፡ ጌዴዎን ዝናው እጅግ በጣም ስለገነነ ሕዝቡ ንገሥልን ቢሉት እምቢ በማለት ተቃወማቸው ፡፡ ነገር ግን ጌዴዎን ለአርባ ዓመታት ያህል በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ (መሳ 8፡ 22-35) ፡፡ ጌዴዎን በምድያም ላይ በተቀዳጀው ድል ለእግዚአብሔር የመታደግ ተግባር በምሳሌነት ይጠቀሳል (ኢሳ 9፡ 4 ፤ 10፡ 26) ፡፡ ጌዴዎን ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሴኬም የምትኖር ቁባት ነበረችው፤ እርስዋም ወንድ ልጅ መለደችለት፤ ስሙንም አቢሜሌክ ብሎ ጠራው(መሳ 8፡ 31)፡፡

 በመሳፍንት ታሪክ ውስጥ የጌዴዎን ልጅ አቢሜሌክ ክፉ ሥራ በመፈጸሙ ምክንያት ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ አቢሜሌክ የፈጸመው ተግባር ምንድን ነው?

አቢሜሌክ በሴኬም ትር ከነበረች ከአንዲት የጌዴዎን ቁባት የተወለደ ነበር፡፡ እርሱም ወደ ዘመዶቹ በመሄድ “የቱን ትመርጣላችሁ? በሰባውም የጌዴዎን ልጆች መገዛትን ወይስ በአንድ ሰው መገዛትን? አቢሜሌክ ለእናንተ የቅርብ የሥጋ ዘመድ መሆኑን አትዘንጉ” አላቸው(መሳ 9፡ 1-3)፡፡ ቀጥሎም አቢሜሌክ ወደ አባቱ ቤት ወደ ዖፍራም ሄዶ የጌዴዎን ልጆች የሆኑትን ሰባውን ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የጌዴዎን መጨረሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተደብቆ ስለነበር ከሞት ተረፈ፤ ከዚያን በኋላ የሴኬምና የቤትሚሎ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስበው በሴኬም ወደሚገኘው ወደተቀደሰው ወርካ ዛፍ ሄዱ፤ በዚያም አቢሜሌክን አነገሡ(መሳ 9፡ 4-6)፡፡ አቢሜሌክ በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ነገሠ፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አቢሜሌክና የሴኬም ሰዎች እርስ በርሳቸው በጠላትነት እንዲተያዩ አደረገ፤ ስለዚህ የሴኬም ሰዎች በእርሱ ላይ ዐመፁበት፡፡ ይህም የሆነው አቢሜሌክ ወንድሞቹን ስለገደለ ቅጣቱን እንዲቀበልና እንዲሁም አቢሜሌክ የጌዴዎንን ሰባ ልጆች እንዲገድል ያደፋፈሩት የሴኬም ሰዎች ስለ ሠሩት ግፍ ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ ነው(መሳ 9፡ 22-24)፡፡ {jathumbnail off}

አቢሜሌክ በጦርነት እየተዋጋ እያለ አንዲት ሴት በራሱ ላይ የወፍጮ ድንጋይ ናዳ በመጣል አናቱን ፈጠፈጠችው፡፡ እርሱም የጦር መሣሪያ አንጋቹን ወጣት በፍጥነት በመጥራት “ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ፤ ሴት ገደለችው እንድባል አልፈልግም” ሲል አዘዘው፡፡ ስለዚህ ወጣቱ በሰይፍ መትቶ ገደለው፡፡ በዚህ ዐይነት አቢሜሌክ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል በአባቱ ላይ በፈጸመው በደል እግዚአብሔር ፍዳውን ከፈለው(መሳ 9፡ 56)፡፡  

በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ዮፍታሔ የሚወዳት ሴት ልጁን ለእግዚአብሔር እንደሰዋ ይታወቃል ፡፡ ዮፍታሔ ማን ነው ? የሚወዳት ሴት ልጁን ለምንድን ነው መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው ?

            ዮፍታሔ ማለት “እግዚአብሔር ይከፍታል” ማለት ነው ፡፡ ዮፍታሔ ከእስራኤል መሳፍንቶች አንዱ ነበር ፡፡ ዮፍታሔ አንዲት ጋለምታ ሴት ገለዓድ ለሚባለው ሰው የወለደችለት ልጅ ነበር ፡፡ የአባቱ ሚስት ልጆች ካደጉ በኋላ አባረሩት ፡፡ በወንድሞቹ ከተባረረ በኋላ ተከታዮችን ሰበሰበ ፡፡ አሞናውያን በእስራኤል ላይ በተነሡ ጊዜ የገለዓድ ምድር አለቆች ወደ ዮፍታሔ ሄደው አለቃችን ሁን አሉት ፡፡ ዮፍታሔ መልእክተኞችን በመላክ የአሞንን ንጉሥ እንዲመለስ መከረው ፡፡ ነገር ግን ሊሰማው አልፈለገም፡፡ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ዮፍታሔም በገለዓድና በምናሰሴ ግዛቶች መካከል አቋርጦ ሄደ፡፡ ለእግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተሳለ “በዐሞናውያን ላይ ድልን ከሰጠኸኝ ድል አድርጌ ከዘመቻ ወደ ቤቴ ስመለስ ከቤት ወጥቶ ሊቀበለኝ የሚመጣው ለአንተ ይሆናል፤ እርሱንም ለአንተ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ” አለ (መሳ 11፡ 29-31)፡፡  አሞናውያንን በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል መትቶ አሸነፋቸው ፤ ይህንንም ያደረገው በእምነት ነበር (ዕብ 11፡ 32) ፡፡ የእግዚአብሔርንም ሕግ ካለማወቁ የተነሣ የተሳለውን ስለት እንዲፈጸም የሚወዳትን ሴት ልጁን ሠዋ ፡፡ የኤፍሬም ሰዎች በተነሡበት ጊዜም አሸነፋቸው ፡፡ ጌዴዎን ለስድስት ዓመታት በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆኖ ኖረ (መሳ 10፡ 17-12, 7) ፡፡  

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት የእስራኤል መሳፍንቶች ውስጥ ሶምሶን ወይም ሳምሶን ትልቅ ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡ የሳምሶን አወላለድ እንዴት ነው?

ጾርዓ በምትባል የገጠር ከተማ የሚኖር ማኑሄ የሚባል አንድ ሰው ነበር፡፡ ሚስቱ መኻን ስለነበረች ልጆች አልወለደችም፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ እንዲህ አላት “እስከ አሁን ልጆች መውለድ አልቻልሽም፤ ነገር ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፀንሰሽ ወንድ ልጅ ትወልጂአለሽ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ማንኛውም የተከለከለ ምግብ ከመብላት ተጠንቀቂ፡፡ ልጅሽም ከተወለደ በኋላ ጠጉሩን በፍጹም እንዳትላጪው፤ ምክንያቱም እርሱ ከሚወለድበት ቀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል”፡፡ ሴቲቱም ሄዳ ለባልዋ ሁሉንም ነገር ነገረችው፡፡ ከዚህ በኋላ ማኑሄ “እግዚአብሔር ሆይ ! ሕፃኑ ሲወለድ ምን ማድረግ እንደሚገባን  ይነግረን ዘንድ ያ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደገና ተመልሶ ወደ እኛ እንዲመጣ አድርግልን” ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደገና ወጥቶ ሴቲቱን በእርሻ ውስጥ እንደተቀመጠች ተገለጠላት፡፡ ማኑሄም መልአኩን “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም የሚወለደው ልጅ ምን ማድረግ አለበት? መኖር የሚገባውስ እንዴት ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡ መልአኩም በድጋሚ ለሚስቱ ነግሯት የነበረውን ሁሉ ነገረው፡፡ ማኑሄም “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም ምስጋና እናቀርብልህ ዘንድ ስምህ ማን እንደሆነ ንገረን” አለው፡፡ መልአኩም “ስሜን ለማወቅ የፈለግኸው ለምንድን ነው? ስሜ ድንቅ የሆነ ምስጢራዊ ነው” ሲል መለሰለት፡፡ 

 ከዚህ በኋላ ማኑሄ አንድ የፍየል ጥቦትና የእህል ቁርባን ወስዶ በአለቱ መሠዊያ ላይ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ማኑሄና ሚስቱም እየተመለከቱ ሳለ እግዚአብሔር አስደናቂ ነገር አደረገ፡፡ የእሳት ነበልባል ከመሠዊያው ወደ ላይ በሚወጣበት ጊዜ ማኑሄና ሚስቱ የእግዚአብሔር መልአክ በነበልባሉ ውስጥ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ማኑሄም በዚህ ጊዜ ያ ሰው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ተገነዘበ፤ እርሱና ሚስቱም በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፉ፤ ዳግመኛም መልአኩን አላዩም(መሳ 13፡ 1-24)፡፡

የሳምሶን ሕይወት ምን ይመስል ነበር? ለሕዝቡና ለአገሩ ያከናወናቸው ተግባራትና የፈጸማቸው የጀግንነት ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

            ሳምሶን የእስራኤል አዳኞችና ፈራጆች ከተባሉት መሳፍንት ውስጥ የመጨረሻው ነበር ፡፡ አባቱ የዳን ነገድ የሆነ ማኑሄ የሚባል ሰው ነበር ፤ እናቱ መካን ነበረች ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ “እስራኤልን ከፍልስጤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል” ብሎ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት ፡፡ ልጃቸው ሳምሶን ከልደቱ ጀምሮ ናዝራዊ ነበረ (መሳ 13) ፡፡ ናዝራዊ ማለት የተቀደሰ የተለየ ማለት ነው ፡፡ አንድ እስራኤላዊ ልዩ አገልግሎት ለመስጠት ሲፈልግ የናዝራዊ ስእለትን ይሳል ነበር ፡፡ ናዝራዊ ሲሆን የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም ነበር ፤ ጠጉሩ ከመቈረጥ ፣ ሬሳ ከመንካት ራሱን ይከለክል ነበር ፡፡ የስእለቱ ዘመን ሲፈጸም ጠጉሩን ቈርጦ ልዩ ልዩ መሥዋዕትና ሥርዓት ይፈጽማል ፡፡ የስእለቱ ዘመን ቢያንስ ለሠላሳ ቀናት ቢረዝምም ሙሉው የሕይወት ዘመን ሊሆን ይችል ነበር ፡፡

            በሳምሶን ዘመን ፍልስጤማውያን አንዳንዶቹን የእስራኤል ከተሞች ወስደው ይመኩባቸውና ይገዙአቸው ነበር (መሳ 13፡ 1 ፤ 1 ሳሙ 7፡ 13-14) ፡፡ እስራኤላውያን ግን ሊዋጉአቸው አልደፈሩም (መሳ 15፡ 11) ፡፡ ሳምሶን ግን እግዚአብሔር በሰጠው ልዩ ብርታትና ኃይል ብቻውን ይቃወማቸው ነበር እንጂ እንደ ጌዴዎን ሊዋጋ ሠራዊትን አልሰበሰበም ፡፡ አስቀድሞ በፍልስጤማውያን ላይ ምክንያት በመፈለግ አንዲት ፍልስጤማዊት አገባ ፤ በእርስዋም ምክንያት በተጣሉ ጊዜ እህላቸውን አቃጠለ ፤ ብዙዎቻቸውንም ገደለ (መሳ 14፡ 1-15፡ 8) ፡፡ የይሁዳ ሰዎች የተቈጡትን ፍልስጤማውያን ፈርተው አሳልፈው ሊሰጡት ተስማሙ ፡፡ ሳምሶን ግን የአህያ መንጋጋ ይዞ ከጠላቶቹ አንድ ሺ ገደለ (መሳ 15፡ 9-19) ፡፡ እስከ ሃያ ዓመት ድረስ በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ (መሳ 15፡ 20) ፡፡ አንድ ጊዜ ጠላቶቹ በጋዛ ከተማ ሊይዙት ሲጠባበቁ የከተማዪቱን በር መዝጊያ ነቅሎ በመውሰድ አመለጠ ፡፡

            ሳምሶን ኃይለኛ ጀግና የሆነው በእምነት እንደነበር ተጠቅሷል (ዕብ 11፡ 32-34) ፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ራሱን ካለመግዛቱ የተነሣ ተያዘ (መሳ 16፡ 1-4) ፡፡ ደሊላ የተባለች ሴት ናዝራዊነቱን እስኪገልጥላት ድረስ ከነዘነዘችው በኋላ ለፍልስጤማውያን መኳንንት አሳልፋ ሰጠችው ፡፡ እነርሱም ዐይኑን አሳውረው በጋዛ አሰሩት (መሳ 16፡ 4-22) ፡፡ አምላካቸው ዳጎንን ሊያመሰግኑ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳምሶንን አስመጥተው ተዘባበቱበት ፡፡ እርሱም ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ የቤቱን ምሰሶዎች ገፋ ፤ ቤቱ ሲወድቅ በውስጡ ከነበሩት ፍልስጤማውያን መካከል ብዙ ሰዎች ተገደሉ ፤ ሳምሶንም አብሮአቸው ሞተ (መሳ 16፡ 23-31) ፡፡

በአጠቃላይ ከመጽሐፈ መሳፍንት ዋና ትምህርት የሚሆነው የሰው ልጅ ደኅንነት እንደሚያስፈልገው ነው ፡፡ የሰው ልጅ ለራሱ ከተተወ ወደ ተሳሳተ የሕይወት ጐዳና ይገባል ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተካተቱት መጻሕፍት ውስጥ በቅደም ተከተላቸው መሠረት ከመጽሐፈ መሳፍንት በኋላ መጽሐፈ ሩትን እናገኛለን ፤ ይህ መጽሐፍ ስለምን ያትታል? ከመጽሐፈ መሳፍንትስ በምን ይለያል?

            ይህ መጽሐፍ ከመሳፍንት በኋላ የተቀመጠበት ምክንያት ክስተቱ የተፈጸመው “መሳፍንት ይፈርዱ በነበረ ጊዜ” (ሩት 1፡ 1) ስለሆነ የንጉሥ ዳዊት ቅድመ አያቶችን ታሪክ በሰፊው ስለሚዘረዝር እንዲሁም የመሳፍንት ዘመንና የእስራኤል ነገሥታት ዘመን እንደ ድልድይ ሆኖ ስለሚያገናኛኝ ነው ፡፡ መጽሐፉ ለዘመነ መሳፍንት መውደቅ ምክንያት የሆኑ ነገሮችንና የሰው ልጅ ድክመቶችን ይዘረዝራል ፡፡ የታሪኩ ዋና ተዋናይ ሆና የምትቀርበው ግን ሩት የተባለችው ሴት ነች ፡፡ ሩት በመሳፍንት ዘመን የነበረች የናዖሚ ልጅ ማሕሎንን ያገባች ሞአባዊት ነች ፡፡  

የታሪኩም ሂደት እንዲህ ነው፦

በእስራኤል አገር ነገሥታት መንገሥ ሳይጀምሩ መሳፍንት በሚያስተዳድሩበት ዘመን በአገሩ ላይ ረሀብ ሆነ፤ ከዚህም የተነሣ በትውልዱ ኤፍራታዊ ሆኖ በይሁዳ ክፍለ ሀገር በቤተልሔም ከተማ የሚኖር ኤሊሜሌክ የተባለ ሰው ናዖሚ ከተባለች ሚስቱና ማሕሎንና ኬሊዎን ከተባሉት ሁለት ወንዶች ልጆቹ ጋር የረሀቡን ዘመን ለማሳለፍ ወደ ሞአብ አገር ተሰደደ፡፡ እዚያም በሚኖርበት ጊዜ ኤሊሜሌክ ሞተ፤ ናዖሚም ከሁለት ልጆችዋ ጋር ብቻዋን ቀረች፤ ልጆችዋም ዖርፋና ሩት የተባሉትን የሞአብ አገር ልጃገረዶች አግብተው ነበር፤ ከዐሥር ዓመታት በኋላ ማሕሎንና ኬሊዎንም ሞቱ፤ ናዖሚም ባልዋንና ልጆችዋን አጥታ ብቻዋን ቀረች(ሩት 1፡ 1-5)፡፡ 

            ናዖሚ ባልዋና ልጆችዋ ከሞቱ በኋላ ወደ ሀገርዋ ለመመለስ አሰበች ፤ ናዖሚ ሁለቱ ምራቶችዋን ለመሰናበት ሳመቻቸው፡፡ ሩት ግን “ተለይቼሽ እንድመለስ አታስገጅጂኝ፤ አብሬሽ እንድሄድ ፍቀጂልኝ፤ አንቺ ወደምትሄጂበት ሁሉ እሄዳለሁ፤ አንቺ በምትኖሪበት እኖራለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ ሕዝብሽ ሕዝቤ ነው፤ አምላክሽም አምላኬ ነው፤ በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በምትቀበሪበትም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ የለም፤ ከአንቺ ለመለየት ባስብ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ” አለቻት፡፡ በዚህ ሁኔታ ሩትም እስራኤላዊ ለሆነችው ምራቷ እጅግ አስደናቂ የሆነ ታማኝነት ታሳያታለች ፤ እንዲሁም የእስራኤል አምላክ ለሆነው እግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር ያድርባታል ፤ ሩት በእግዚአብሔር ታምና ከናዖሚ ጋር ለመሄድ ወሰነች ፡፡ ሩት  ናዖሚንን እያገለገለች የቤተልሔሙን ቦዔዝን ለማግባት በቃች ፡፡ ተጋብተውም ኢዮቤድን ወለዱ ፤ ኢዮቤድ የእሴይ አባት ፤ የንጉሥ ዳዊት አያት ነበር ፡፡

            በመጽሐፈ መሳፍንት ያሉት ታሪኮች የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእግዚአብሔር በመራቃቸው የደረሰባቸውን ጥፋት ያሳያሉ ፤ በመጽሐፈ ሩት ውስጥ ያለው ታሪክ ደግሞ የእስራኤል አምላክ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ፊቷን የመለሰች አንዲት ባዕድ ሴት የምታገኘው በረከትና ታማኞች ከሆኑት ሕዝቡ መካከል አንዷ ልትሆን መብቃቷን ያሳያል ፡፡ መጽሐፈ ሩትም የሚተርከው ስለዚህች ታማኝ ሴት ስለ ሩት ነው ፡፡ ይህም እግዚአብሔር ከአሕዛብ ወገን የነበረችውን ሩትን በእምነትዋ ምክንያት እንደተቀበላትና (ሩት 1፡ 16-17) የዳዊትም ቅድመ አያት እንደሆነች ያሳያል (ሩት 4፡ 13-17) ፡፡

   የትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ ዋና አስተባባሪ ፦ ፀጋዬ ሀብቴ

 ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1. ከሚከተሉት ውስጥ “መሳፍንት” እና “መጽሐፈ መሳፍንት” የሚሉትን ቃላት በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ፡፡

ሀ) መሳፍንት የሚለው ቃል መስፍን ከሚለው ነጠላ ስም የተገኘ ሆኖ ብዙ መስፍኖችን የሚያመለክት ነው፡፡ ለ) መስፍን ማለት አዳኝ ፣ ጀግና ፣ ተዋጊና ንጉሥ ሆኖ አንድን ሕዝብ የሚያስተዳድር እንዲሁም ለሕዝብ ፍርድን የሚሰጥ ማለት ነው፡፡ ሐ)መስፍን የተባለው ከንጉሥ ዘር የሆነ ሰው ሳይሆን አገሪቱን ከጠላት ወረራ የሚያድን አዳኝ ጀግና ነበረ፡፡ መ) እስራኤላውያ ከኃጢአታቸው በተጸጸቱ ጊዜእግዚአብሔር ይምራቸውና መስፍንንም አስነሥቶ ከሚማርኩአቸው እጅ ያድናቸው ነበር፡፡ ሠ)የመሳፍንት ዘመን በጣም አስፈሪና ጭካኔ የተሞላበት ጊዜ ነበር ፡፡

2. ከሚከተሉት ውስጥ ዲቦራና ባራቅ በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነውን የትኛው ነው? (ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ መሳፍንት ምዕራፍ 4 እና 5 ማንበብ ያስፈልጋል)

ሀ) ዲቦራ ነቢይትና የእስራኤልን ሕዝብ ፍርድ በመስጠት በዳኝነት የምታገለግል ነበረች፡፡ ለ)ዲቦራ ነቢይት ስለነበረች ባራቅ ለተባለው እስራኤላዊ አስጠርታ የእግዚአብሔር የትንቢት ቃል ነገረችው፤ ወደ ጦርነት መሄድ እንዳለበትም አሳወቀችው፡፡ ሐ) ባራቅ ግን ዲቦራን አንቺ ከእኔ ጋር ወደ ጦር ግንባር ከዘመትሽ ብቻ ነው ሄጄ የምዋጋው በማለት አመነታ፡፡ ዲቦራም ወደ ጦር ሜዳ አብራው ዘመተች ፡፡ መ) በጦርነቱ መጨረሻ ላይ የጠላት ጦር መሪ የነበረው ሲሣራ በዲቦራ ተገደለ፡፡ ሠ) በጦርነቱ መጨረሻ ዲቦራ ለእግዚአብሔር የድል መዝሙር ዘመረች፡፡ በዝማሬዋም የጦርነቱ ታሪክ በዝርዝር ተረከች፡፡

3. ጌዴዎን ከመሳፍንቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ጌዴዎን ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ ለባዓል የተሠራውን መሠዊያ አፈረሰ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል ሰባብሮ ጣለ፡፡ ጌዴዎን ይህ ያደረገው በሌሊት ጨለማ ለብሶ ነበር፡፡ ጌዴዎን ይህንን ተግባር ለምን በሌሊት ማድረግን መፈለገ? (ይህንን ጥያቄ ለመመለስ መሳ 6 በአስተውሎት መነበብ ያስፈልጋል)

ሀ) የከተማዪቱን ነዋሪዎች ከመፍራቱ የተነሣ ነው፡፡ ለ) እግዚአብሔር በሌሊት እንዲያከናውነው ስላዘዘው ነው፡፡ ሐ) እነዚህ ጣዖታት በሌሊት ኃይል የላቸውም ብለው ያምኑ ስለነበር ነው፡፡ መ) ሌሊት የሰይጣንና የክፉ ሥራ ምልክት መሆኑን ያውቅ ስለነበረና ክፉ ሥራውን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ ስለፈለገ ነው፡፡ ሠ) ጌዴዎን ከቀን ይልቅ በሌሊት ኃይለኛ ስለነበር ነው፡፡

4. ለሥልጣን በማለት ወይም በሕዝቡ ዘንድ መሪ ሆኖ ምድራዊ ክብር አግኝቶ ለመኖር በማለት ቁጥራቸው ሰባ የሚያህሉ ወንድሞቹ ሁሉ በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይ አርዶ የገደለና በሕዝቡ ዘንድ መሪ መሆን የቻለ ነገር ግን ባደረገው ድርጊት ምክንያት በእግዚአብሔር የተቀጣና የመጨረሻ ሕይወቱ በአሳዛኝ ሁኔታ የተጠናቀቀው ማን ነው?

ሀ) ዖትኒኤል ለ) ኤሁድ ሐ) አቢሜሌክ መ) ሚካ ሠ) ቶላዕ

5. ከሚከተሉት ውስጥ የሳምሶንን ሕይወት በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነውን ምረጥ? (ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ከላይ ከተሰጠው ገለጻ በተጨማሪ መሳ 13 እና 14 በሚገባ ማንበብ ያስፈልጋል)

ሀ) ሳምሶን ከመወለዱ በፊት እናቱ መኻን ነበረች፤ ነገር ግን ፀንሳ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ የእግዚአብሔር መልአክ አሳወቃት፡፡ ለ)ሳምሶን ከልደቱ ጀምሮ ናዝራዊ ነበረ፡፡ ናዝራዊ ማለት የተቀደሰ የተለየ ማለት ነው፡፡ ሐ) ሳምሶን ናዝራዊ ስለነበር የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም ነበር ፤ ጠጉሩ ከመቈረጥ ፣ ሬሳ ከመንካት ራሱን ይከለክል ነበር ፡፡ መ) ሳምሶን ኃይለኛ ስለነበር አንበሳን እንኳ እንደ ፍየል ገነጣጥሎ ይጥል ነበር ሠ) ሳምሶን ፍልስጤማውያንን እንቆቅልሽ በጠየቃቸው ጊዜ ምላሹን ስላቃታቸው የሳምሶን እናት በማግባባት ጠይቀው ምላሹን አወቁት፡፡

6. ዮፍታሔ ወደ ጦር ሜዳ ከመሄዱ በፊት ለእግዚአብሔር “በዐሞናውያን ላይ ድልን ከሰጠኸኝ ድል አድርጌ ከዘመቻ ወደቤቴ ስመለስ ከቤት ወጥቶ ሊቀበለኝ የሚመጣው ለአንተ ይሆናል፤ እርሱንም ለአንተ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ” በማለት ተሳለ፡፡ ከጦርነት ሲመለስ ልጁ አታሞ ይዛ እየዘፈነችና እየጨፈረች ልትቀበለው ወጣች፤ ያለ እርስዋም ሌላ ልጅ አልነበረውም፡፡ ባያትም ጊዜ በሐዘን ልብሱን በመቅደድ “ወይ ልጄ ! ልቤን በሐዘን ሰበርሽው ! በእኔ ላይ ለሚደርሰው ሥቃይ ስለምን አንቺ ምክንያት ሆንሽብኝ? እኔ ለእግዚአብሔር በመሐላ ቃል ገብቼ ተስያለሁ፤ ልመልሰውም አልችልም ! አለ፡፡ ልጁንም አርዶ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ(መሳ 11፡ 30-40)፡፡

-    ዮፍታሔ መጀመሪያውኑ ለእግዚአብሔር መሳሉ ተገቢ ነውን?

 

-    ምንም ነገር ስለት ሳናደርግ እግዚአብሔር አንድ ነገር እንዲያደርግልን ብንለምነው አያከናውንልምን?

 

 

-    ዮፍታሔ ልጁን በሕይወት ቢተዋትና ስለቱን ባያቀርብስ ምን ሊከሰት ይችል ነበር? (አስቀድመው እነዚህን ንባባት ያገናዝቡ፤ ሌዋ 27፡ 1-34 ፤ ዘኁ 30፡ 3-5 ፤ ዘዳ 23፡ 22-23፤ መጽሐፈ መክብብ 5፡ 1-5፤ መዝ 66፡ 13-14)፡፡