እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳፬ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ ኤርሚያስ-ክፍል ፪)

የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - ትንቢተ ኤርምያስ - ክፍል ፪ - ካለፈው የቀጠለ የመጨረሻው ክፍል

Ermias-2> በትንቢተ ኤርምያስ ውስጥ ትልቁ ቦታ ከያዙ አስተምህርቶች ውስጥ አንዱ "እግዚአብሔር የሚሰጠው የወደፊቱ ተስፋ" ላይ የሚያተኩር ነው፤ ይህ የወደፊቱ ተስፋ በምን ዓይነት መልኩ ነው የተገልጸውና የተብራራው?

አይሁዳውያን በናቡከደነፆር ከተሸነፉና ከተማረኩበት ጊዜ ጀምሮ የጭቆና ቀንበር ተሸክመው በባዕድ አገር ከባድ የሆነ የመከራ ኑሮ ሲመሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እነዚህ ስደተኞች እጅግ በጣም በመጸጸት በቀድሞ ኑሮአቸው እግዚአብሔርን አሳዝነው እንደነበርና ዳግመኛ የቀድሞው ዓይነት ሕይወት እንደማይኖሩና የእግዚአብሔር ትእዛዛት እየፈጸሙ እንደሚኖሩ ደጋግመው አሳወቁ፡፡ ይህንን ጸጸታቸው የተመለከተው እግዚአብሔር የወደፊት ሕይወታቸው ከድሮው እጅግ በጣም የተለየ እንደሚሆን በተለያየ መልኩ ይገልጽላቸዋል፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር ሕዝቡን አፍቃሪ፣ ይቅር ባይና በደልንም ሁሉ የሚረሳ መሆኑን በመግለጽ አሁንም ሆነ ወደ ፊት የበለጠ ፍቅር እንደሚያሳያቸው ሲገልጽ እስራኤል ሆይ! እጅግ የተወደድህና የማፈቅርህ ልጄ ነህ፤ ስምህን ባነሣሁ ቁጥር በፍቅር አስብሃለሁ፤ ልቤ አንተን ስለሚናፍቅ በደልን ይቅር ባይ እሆናለሁ ይላል(ኤር 31፡20)፡፡

በአጠቃላይ እግዚአብሔር ብዙ የሆኑ የተስፋ ቃሎች ለሕዝቡ በተለያየ መልኩ ይሰጣል፡፡ ከእነዚህም የወደፊት ተስፋ መገለጫ ከሆኑት ውስጥ ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያህል፦ {jathumbnail off}

- ከተበተኑባቸው አገሮች ሁሉ እንደገና ተሰብስበው አገራቸው ውሰጥ በሰላም ይኖራሉ፤ እግዚአብሔር አምላካቸው ይሆናል እነርሱም ዳግመኛ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተብለው ይጠራሉ (ኤር 32፡37-38)፡፡

- ሕዝቡ ወደ አገራቸው ተመልሰው ዳግመኛ የመሬት ባለቤቶች ይሆናሉ፤ ምድር ቤቶች፣ የእርሻ መሬቶችን የአትክልት ቦታዎችን ይገዛሉ፤ ይሸጣሉ፤ ይለውጣሉ፤ እረኞች ብዙ በጎች ይኖራቸዋል (ኤር 32፡1-44፤ 33፡12-13)፡፡

- እያንዳንዱ ቤተሰብ ከእግዚአብሔር ምሕረትን አግኝቶ በበረከት ስለሚሞሉ ቁጥራቸውም እጅግ የበዛ ይሆናል (ኤር 30፡18)፡፡

- ከተማቸው ኢየሩሳሌም በድጋሚ ትታነጻለች፤ ቤተ መንግሥቷም በድሮ ቦታው ተመልሶ ይታነጻል፤ ከተማዪቱም "እግዚአብሔር ጽድቃችን" ተብላ ትጠራለች (ኤር 30፡18፤ 33፡16)፡፡

- ጥንት የነበረው የሕዝብ ኃይል በእግዚአብሔር እንደገና ተመልሶ ይታደሳል፤ የደከሙት ሁሉ ኃይላቸው ይታደሳል፤ በረሀብ ዝለው የነበሩትንም ምግብ አግኝተው ይረካሉ (ኤር 30፡ 20፤ 31፡25)፡፡

- ገዥያቸው ከሕዝባቸው መካከል ተመርጦ ይሾማል፤ መስፍናቸውም ከወገናቸው መካከል ይገኛል (ኤር 30፡21)፡፡

- ከዳዊት ዘር በእስራኤል ላይ የሚነግሥ አንድ ጻድቅ ንጉሥ በእግዚአብሔር ይመረጣል፤ ያም ንጉሥ በአገሪቱ ላይ ቅን የሆነውን ነገር ያደርጋል፤ ትክክለኛ ፍትሕም ይሰጣል፤ የሌዊ ካህናት ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ይሆናል (ኤር 33፡14-22)፡፡

ከተስፋ ቃሎች ሁሉ እጅግ በጣም ለየት ያለው እግዚአብሔር ስለ "አዲሱ ቃል ኪዳን" የተናገረውን ነው(ኤር 31፡30-34)፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የሚገባበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ይህ ቃል ኪዳን እጅግ በጣም ለየት ያለና ከቀድሞዎቹ ቃል ኪዳኖች በፍጹም የማይመሳሰል በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል(ኤር 31፡32)፡፡ በዚህም መሠረት አዲሱ ቃል ኪዳን ወይም ሕግ እንደ ቀድሞው በድንጋይ የተቀረጸ ሳይሆን በሕዝቡ ልቦና የሚጻፍ ይሆናል(ኤር 31፡33)፡፡ ይህ ቃል ኪዳን እንደ ድሮው የሚጣስ ወይም የሚፈርስ ሳይሆን ጸንቶ የሚኖርና በምንም መልኩ የማይሻር ይሆናል፡፡

> ኤርምያስ የነቢይነት አገልግሎቱን በሚወጣበት ጊዜ ብዙ መከራና ጉስቁልና ደርሶበታል፤ በዚህም ከነቢያት ሁሉ ብዙ የተንከራተተና ችግር የደረሰበት ነቢይ እንደሆነ ይታወቃል፤ ነቢዩ መከራ እንደደረሰበት የሚገልጹ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

ኤርምያስ የነቢይነት ተግባሩን በሚወጣበት ጊዜ እግዚአብሔርን ተማምኖ ያገለግል ስለነበር ማንንም አይፈራም ነበር፤ ንጉሥም ሆነ ማንኛውም መሪ ሳይበግረው መናገር ያለበትን ነገር ይናገር ነበር፤ ያስተምር ነበር፡፡ ለምሳሌ ኤርምያስ እግዚአብሔር የተናገረውን የትንቢት ቃል ለንጉሥ ሴዴቅያስ ስላሳወቀ በንጉሡ ትእዛዝ በቤተ መንግሥት ውስጥ እስረኛ ተደርጎ ተቀመጠ(ኤር 32፡3)። ኤርምያስ የእግዚአብሔር መልእክት ለሕዝቡ በማስተላለፉ ምክንያት ብዙ ጊዜ በገዛ ሕዝቡ ተሰደበ(ኤር 15፡15)፤ አስወንጅለው አሳልፈው ሊሰጡት ብዙ ሤራ ሸረቡበትና የሚወድቅበትን ጉድጓድ ቆፈሩ(ኤር 18፡18-20)፤ በገዛ ወገኖቹ እንደውም የቤተ መቅደስ አለቃ በነበረው ሰው ተይዞ እንዲደበደብ ተደረገ(ኤር 20፡2)፡፡ ብዙ ጊዜ የትንቢት ቃል በመናገሩ ምክንያት ሞት ይገባሃል ተብሎ ተፈረደበት(ኤር 26 እና 38፡4)፤ እንደ ዕብድ ተቈጥሮ በሰንሰለት ሊታሰር ተሸረበበት(ኤር 29፡26)፡፡ የገዛ ወገኖቹ ተሰብስበው በመያዝ ጥልቅ በሆነ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ተወረወረ፤ ነገር ግን በጉድጓዱ ውስጥ ጭቃ እንጂ ውሃ ስላልነበረበት በጭቃው ውስጥ ሰመጠ እንጂ አልሞተም(38፡6)፡፡ በመጨረሻም በራማ በሰንሰለት ታስሮ ከወገኖቹ ከእስራኤላውያን ጋር ተማርኮ ወደ ባቢሎን ሊወሰድ እያለ የጦር አዛዡ ናቡዛራዳን ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን ለመውረድ ብትፈልግ እንደወደድህ አድርግ፤ እኔም ለአንተ እንክብካቤ አደርግልሃለሁ ወደዚያ ለመሄድ ካልፈለግክ ግን መቅረት ትችላለህ ብሎ ነፃ ለቀቀው(ኤር 40፡1)።

ኤርምያስም እዛው ቀረ። ኤርምያስ በስደትና በመከራ ለነበሩት ሕዝቦቹ ተስፋ እየሰጣቸው ያበረታታቸው ይጸልይላቸውም ነበር(ኤር 42)። በኋላም በስደት ወደ ግብጽ ተወሰደ(ኤር 43፡1-13)። ይህም ሆኖ እንኳ በባዕዳን አገር ማለትም በግብጽ ውስጥ ትንቢት መናገሩ አልተወም(ኤር 43፡8-44)፡፡ የኤርምያስ ሕይወት መጨረሻው ግን እንዴት እንደ ተጠናቀቀ ምንም አይታወቅም። ግብጽ ውስጥ በስደት እንዳለ ይገደል ወይም በተፈጥሮአዊ ሞት ከዚህ ዓለም ይለፍ ወይም ወደ ኢየሩሳሌም ዳግመኛ ተመልሶ ይሙት ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ግን ግብጽ ውስጥ በመሥዋዕትነት እንዳለፈ ቢገልጹም ለዚህ አባባለቸው ግን ምንም ዓይነት መረጃ የላቸውም፡፡

> ትንቢተ ኤርምያስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በምን ዓይነት መልኩ ተገልጾ ወይም ተጠቅሶ ወይም ተብራርቶ ይገኛል?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሐዋርያቶች ትኩረት ከሳቡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ትንቢተ ኤርምያስ ትልቅ ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የዮሐንስ ራእይ ትንቢተ ኤርምያስ በመጥቀስና ተመሳሳይ ሀሳቦችን በመውሰድ ረገድ ትልቁ ቦታ ይዞ ይገኛል(ኤር 50፡8፤ ራእ 18፡4፤ ኤር 50፡32፤ ራእ 18፡8፤ ኤር 51፡49-50 ፤ ራእ 18፡24)፡፡

ከነቢያቶች ሁሉ በላይ ነቢዩ ኤርምያስ ኢየሩሳሌምን ይወድ እንደነበርና ስለውድቀትዋም ምርር ብሎ እንዳዘነና እንዳለቀሰ ከትንቢት ቃሉ እንረዳለን፡፡ ይህንን ሀሳብ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ይመስላል ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ ማልቀሱን የሚገልጸው(ኤር 21፡13-15፤ ሉቃ 19፡41-44)፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተለያየ መልኩ ከተጠቀሱት የነቢዩ ኤርምያስ የትንቢት ቃሎች የሚከተሉትን ይገኙበታል፡፡ ከዳዊት ዝርያዎች መካከል ለንጉሥነት የሚመረጥበት ጊዜ እንደሚመጣ(ኤር 23፡5፤ ማቴ 2፡2)፣ የለቅሶና የብዙ ዋይታ ድምፅ በራማ መሰማቱና ራሔል ስለ ልጆችዋ መሞት ማለቅስዋና መጽናናትም እምቢ ማለትዋን በስፋት ተጠቅሷል(ኤር 31፡15፤ ማቴ 2፡18)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ወደ ሕይወትና ወደ ሞት የሚያደርሰውን መንገድ ማኖሩን(ኤር 21፡ 8፤ ማቴ 7፡14)፣ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ስለሚመሰርተው አዲሱ ቃል ኪዳን(ኤር 31፡31-34፤ ማቴ 26፡28) የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ከዚህም በላይ ዓይን እያላቸው ስለማያዩትና ጆሮ እያላቸው ስለማይሰሙት ሰነፎች፣ በሰንበት ቀን ምንም ዓይነት ሸክም መሸከም እንደሌለባቸው፣ መመካት የሚወድ ቢኖር በእግዚአብሔር ብቻ እንዲመካ የሚሉት ከብዙዎች ጥቂቶቹ ናቸው(ኤር 5፡21፤ ማር 8፡ 18፤ ኤር 17፡21፤ ዮሐ 5፡10፤ ኤር 9፡24፤ 1 ቆሮ 1፡31፤ 2 ቆሮ 10፡17)፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ፤ መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ ፦ የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለዚህኛውና ለክፍል አንዱ ጥናት የሚያግዙ ጥያቄዎች

1. የኤርምያስ ቤተሰባዊ ሕይወት፣ የነቢይነት ጥሪውና አገልግሎቱ በተመለከተ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው?

ሀ)ኤርምያስ የካህኑ የሕልቅያስ ልጅ ሲሆን ተወልዶ ያደገው ዐናቶት ተብሎ በሚጠራ መንደር ውስጥ ነው፡፡ ለ) ትንቢተ ኤርምያስ የአጻጻፍ ዘይቤው ዘርፈ ሰፊ ነው፤ ቅደም ተከተል ባለው መልኩ የተጠናከረም አይደለም፡፡ ሐ) ኤርምያስ ለነቢይነት ሲጠራ መንቀልና ማፍረስ፣ ማጥፋትና መገለባበጥ፣ ማነጽና መትከል እንዲችል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ መ) ኤርምያስ ሚስት እንዳያገባ፣ ወደ ግብዣም ሆነ ወደ ልቅሶ እንዳይሄድ በአገሪቱ ነገሥታት ተከለከለ፡፡ ሠ)ኤርምያስ የነቢይነት አገልግሎቱ በአንድ ሕዝብ ወይም አገር ብቻ ሳይወሰንና ድንበር ሳይገድበው አገልግሎቱ በብዙ ቦታ ተወጥቶአል፡፡

2. ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ጣዖት አምልኮ ብዙ እንደተናገረ ከላይ ተገልጾአል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን አድራጊ መሆኑን ተናግሮአል፡፡ ይህንን በተመለከተ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው?

ሀ) በነቢዩ ኤርምያስ ዘመን ነቢያቶች በበዓል ስም ትንቢት ተናገሩ፤ ከንቱ የሆኑ ጣዖታትንም አመለኩ፤ የሕዝብ ገዢዎችም በእግዚአብሔር ላይ አምፀው ነበር፡፡ ለ)እንደ ነቢዩ ኤርምያስ አገላለጽ እግዚአብሔር ከብዙ የትዕግስት ጥበቃ በኋላ ቁጣውን ይነዳል፡፡ ሐ)እንደ ነቢዩ አስተምህሮ እግዚአብሔር የሰውን አእምሮና የሰውን ልብ ይመረምራል፣ እያንዳንዱም ሰው በአካሄዱና በሥራው መጠን ይቀጣዋል፡፡ መ)በአመፃቸውና በእምቢተኛነታቸው የሚጸኑት እልኸኞች ሕዝቦችና የሚኖሩበት ከተማ ይደመሰሳል፤ መቅሰፍትም ያዘንምባቸዋል፡፡ ሠ) እስራኤላውያን እኔ እግዚአብሔር አምላክህ እጅግ ቀናተኛ ስለሆንሁ ተቀርጾ የተሠራውን ማንኛውንም ጣዖት አታምልክ፤ አትስገድለትም የሚለውን ትእዛዝ አክብረው ኖረዋል፡፡

3. ባቢሎን ውስጥ በስደት ይንከራተቱ የነበሩት እስራኤላውያን በቀድሞ ጥፋታቸው ተጸጽተው ንስሓ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ተስፋ እንደሰጣቸው ይታወቃል፡፡ ከተሰጣቸው ተስፋ ውስጥ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው? (ይህንን ለመመለስ ኤርምያስ ከምዕራፍ 30 እስከ 33 በሚገባ ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

ሀ)ወደፊት የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት በማቅረብ የሚያገለግሉኝ ካህናት ከሌዊ ወገን አልፈልግም ይላል እግዚአብሔር፡፡ ለ) የዳዊት ዘር የሆነ አንድ ጻድቅ ንጉሥ እመርጣለሁ፤ ያም ንጉሥ በአገሪቱ ላይ ትክክለኛ ፍትሕ ይሰጣል ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሐ)የደከሙት ሁሉ ኃይላቸው እንዲታደስ አደርጋለሁ፤ በረሀብ ዝለው የነበሩትንም ምግብ በመስጠት አጠግባቸዋለሁ ይላል እግዚአብሔር፡፡ መ)እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የሚገባበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ሠ) ሁሉም ትክክል ናቸው፡፡

4. ኤርምያስ የነቢይነት አገልግሎቱን በሚወጣበት ጊዜ ብዙ ስደት፣ መከራና ጉስቁልና እንደደረሰበት ይታወቃል፡፡ ብዙዎች በጠላትነት ተነሥተው እንዲገላታ አደረጉት፤ አንድ ጊዜ ተባብረው ሞት ይገባዋል በማለት ጥልቅ በሆነ በደረቅ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ወረወሩት፡፡ በዚህ ጊዜ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ያገለግል የነበረ አንድ ጃንደረባ ንጉሡ ዘንድ ቀርቦ በማስፈቀድ ኤርምያስ ከተወረወረበት ጉድጓድ እንዲወጣ በማድረግ ሕይወቱን እንዲተርፍ አደረገው፡፡ ይህ በቤተ መንግሥት ይሠራ የነበረውና የኤርምያስ ሕይወት እንዲድን ያረገው ሰው ስም ማን ነው?̱ ዜግነቱስ ምንድን ነው?(የየት አገር ዜጋ ነበር?)

5. ኤርምያስ በነቢይነት የአገልግሎት ሂደቱ ላይ በሚያያቸውና በሚደርሱበት ነገሮች እየተገረመ ብዙ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ከሚከተሉት ውስጥ ኤርምያስ ለእግዚአብሔር ከጠየቃቸው ጥያቄዎች ውስጥ የማይገኘው ወይም የማይካተተው የትኛውን ነው? (ይህንን ለመመለስ ኤርምያስ ከምዕራፍ 10 እስከ 15 ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

ሀ) ክፉዎች የሚበለጽጉት ስለምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር ሆይ ! እስከ መቼ ድረስ ሕዝብህን በስደትና በመከራ ትተወዋለህ? ሐ) ምድራችን ድርቅ የሚያጠቃውና በየመስኩ ያለውስ ሣር እንደደረቀ የሚቀረውስ እስከ መቼ ነው? መ) አታላዮች ሁሉ ነገር የሚሳካላቸው ስለምንድን ነው? ሠ) ከሥቃይ የማልላቀቀው፣ ቁስሌ የማይጠገነውና የማይፈወሰው ለምንድን ነው? በበጋ ወራት እንደሚደርቅ ምንጭ ተስፋ አስቈራጭ ልትሆንብኝ ነውን?

6. መጀመሪያ ትንቢተ ኤርምያስ 38፡ 14-28 በደንብ መነበብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ታሪክ መሠረት ንጉሥ ሴዴቅያስ ለነቢዩ ኤርምያስ "ይህን የተነጋገርነውን ነገር ማንም አይወቅ" አለው፡፡ በተጨማሪም ሴዴቅያስ ለነቢዩ ኤርምያስ ውሸት እንዲናገር ይመክረዋል(ኤር 38፡ 24-26)፡፡ የባቢሎን ባለ ሥልጣኖች መጥተው ኤርምያስን በጠየቁት ጊዜ ልክ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንደመከረው "ውሸት በመናገር" አሰናበታቸው፡፡ እዚህ ላይ ነቢዩ ኤርምያስ መዋሸት ነበረበትን? በዕለታዊ ማኅበራዊ ሕይወታችን ውስጥ "ለበጎ ነገር ነው" በማለት ውሸት መናገር ጥሩ ነው ብለን የምንልበት ጊዜ አለ ወይ? ካለ በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት