ት/ርት ፳፪ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ ኢሳይያስ)

ትምህርት ሃያ ሁለት - የነቢያት መጽሐፍት ጥናት

ትንቢተ ኢሳይያስ

Isaiah>> ኢሳይያስ ማን ነው? እንዴት ነቢይ ሊሆን ቻለ? ቤተሰባዊ ሕይወቱስ ምን ይመስል ነበር?

ኢሳይያስ የሚለው ስም "የሻያሁ" ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም "እግዚአብሔር ያድናል" ወይም "እግዚአብሔር አዳኝ ነው" ማለት ነው። አባቱም አሞጽ ይባላል። ኢሳይያስ በስምንተኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ በ765 ዓ.ዓ አካባቢ (ኢሳ 1፡1) ኢየሩሳሌም ውስጥ ተወልዶ ያደገና የነቢይነት ተግባሩም ከ742 እስከ 701 ድረስ እዛው ኢየሩሳሌም ውስጥ በተለይም ቤተ መቅደስ ውስጥና አካባቢዋ ዙርያ ላይ ያከናወነ ነቢይ ነው። ኢሳይያስ ባለቤቱ ነቢይት እንደነበረችና ሁለት ልጆችም እንደነበሩት ከመጽሐፉ እንረዳለን (ኢሳ 7፡3፤ 8፡3)። የልጆቹም ስም "ሺር ያሹቭ" ትርጓሜውም "የቀሩት ከምርኮ ይመለሳሉ" ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ማሄር ሻላል ሐሽ ባዝ" ትርጓሜውም "ምርኮ ፈጠነ፤ ብዝበዛ ቸኮለ" የሚሉት ናቸው።

ነቢይ የእግዚአብሔርን መልእክተኛ ሆኖ በነቢይነት ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል፤ ሙሉ ፈቃደኛነቱም በነጻነት የሚገልጸው ለነቢይነት በተጠራ ጊዜ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም በዚህ የአገልግሎት ተልእኮ እንዲሠማራ እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው(ኢሳ 6)፡፡ አስቀድመን ለማየት እንደሞከርነው ለነቢይነት አገልግሎት ለመጠራት አንድ ሰው በቂ የሆነ መንፈሳዊ ብስለትና በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸ ሕይወት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ ለአገልግሎት የተጠራውም ሰው ጥሪውን ምን እንደሆነ፣ ጠሪውንም ማን መሆኑንና የጥሪውም ዋና አላማ ምን መሆኑን ተረድቶ ትሕትና በተሞላበት መልኩ ወደ አገልግሎት መሠማራት ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ኢሳይያስን ለነቢይነት ሲጠራው በመንፈስ የተዘጋጀና ያየውን መለኮታዊ የሆነውን ፍጥረት ለይቶ የመረዳት መንፈሳዊ ብስለት የነበረው እንደሆነ ከጥሪው ታሪክ እንረዳለን፡፡

>> በነቢዩ ኢሳይያስ የሚጠራው መጽሐፍ ትንቢተ ኢሳይያስ ይባላል፤ ይህ መጽሐፍ ይዘቱና ጥንቅሩ ምን ይመስላል? መጽሐፉ ለምን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይገኛል?

ትንቢተ ኢሳይያስ በአይሁዳውያን ዘንድ ትልቅ ቦታ ይዞ በመገኘቱ፣ በክርስትናም እምነት ተከታዮች ዘንድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በብዙ ቦታዎች ማለትም በወንጌላትም ሆነ በመልእክቶች ውስጥ ከመጠቀሱ የተነሣ የአማኞችና የሊቃውንት ትኩረት የሳበ መጽሐፍ ነው፡፡

የነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ የ66 ምዕራፎች ጥንቅር ሲሆን መጽሐፉም ሦስት የተለያዩ ትልልቅ ክፍሎች አሉት፡፡ ከእነዚህም የመጀመሪያው ከምዕራፍ 1-39 ያለው በደቡባዊ መንግሥት ይሁዳ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዚህ ክፍል ነቢዩ ኢሳይያስ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ያላቸውን እምነት ስላጓደሉና በማኅበረሰቡ ውስጥ መሪዎችም በሚተገብሩት ኢፍትሐዊ አሰራራቸው እግዚአብሔርንም ስላሳዘኑ ፍርድ ይጠብቃቸዋል በማለት ይናገራል፡፡ በዚህ ክፍል ነቢዩ ወደፊት ዓለምን ፍጹም በሆነ እውነት፣ ሰላምና ፍትሕ የሚያስተዳድር ስሙም "ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ" ተብሎ የሚጠራ፣ ንጉሣዊ ሥልጣኑም ወሰን የሌለው መሪ እንደሚወለድ ይተነብያል፡፡

የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል የሚሸፍነው ከምዕራፍ 40-55 ያለውን ነው፡፡ ከ1-39 ያለው "የፍርድ ቃል" የያዘ ክፍል እንደሆነ ሁሉ ይኸኛው "የመጽጽናናት ቃል" የያዘ ክፍል በመባል ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ኢሳ 40 ሲጀምር ሕዝቤን አጽናኑ! አጽናኑ! የኢየሩሳሌም ሕዝብ አበረታቱ፤ ብዙ ዘመን በመሠቃየታቸው ምክንያት ኃጢአታቸው ይቅር እንደተባለላቸው ንገሩአቸው በማለት ነው፡፡ የይሁዳ ሕዝብ ባቢሎን ውስጥ እጅግ በጣም ከባድ የሆነ የስደት ኑሮ ላይ ስለነበር በዚህም መከረኛው ኑሮ ውስጥ የነበረው ሕዝብ ተስፋ ቆርጦ፣ አዝኖና ተክዞ እንደነበር ይተርካል፡፡

የመጽሐፉ ሦስተኛና የመጨረሻው ክፍል ከምዕራፍ 56-66 ያለው ነው፡፡ የዚህ ክፍል አብዛኛው ትኩረቱ ከስደት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ስለተመለሱት ሕዝብ ነው፡፡ እጅግ በጣም ከባድ የሆነ የስደት ኑሮ ባቢሎን ውስጥ ካሳለፈ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ በአዲስ መልክ ራሱን እያደራጀ የነበረው ሕዝብ እግዚአብሔር የሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሁሉ ይፈጽም እንደሆነ ማረጋገጫ ለማግኘት እንደሚሻ የሚተርክ ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የተለየ ትኩረት ከተደረገባቸው ነገሮች ውስጥ ጽድቅና ፍትሕ መተግበር፣ ዕለተ ሰንበትን መከበር፣ መሥዋዕት ማቅረብና በጸሎት መትጋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

መጽሐፉ በሦስት የተከፋፈለበት ዋናው ምክንያት የሆነው መጽሐፉ የተለያየ ይዘት ስላለው ነው፡፡ በመጀመሪያው ክፍል (1-39) ውስጥ ያሉት የቦታ፣ የሰዎች ስም፣ ታሪኮቹ የተከናወኑበት ጊዜያት፣ የአነጋገር ዘይቤዎች፣ የነቢዩ ዋና ዋና ትኩረቶች እንዲሁም ታሪኩ ውስጥ የተካተቱት ዐቢይና ንዑስ ገጸ ባሕርያቶች ከሌላው ክፍል እጅግ በጣም ስለሚለይ ነው፡፡

የነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ባካተታቸው ምሥጢረ ሰፊ የሆኑ የነገረ መለኮት አስተምህሮቶች ምክንያት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከመዝሙረ ዳዊት ቀጥሎ ከሁሉም ነቢያቶች በላይ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ትንቢተ ኢሳይያስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ ሊጠቀስበት ከቻለበት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ የዐማኑኤል የመወለድ ትንቢት(ኢሳ 7)፣ ስለ ሰባቱ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች (ኢሳ 11፡2-4)፣ መከራ ስለሚደርስበትና ስለሚሠቃየው አገልጋይ(ኢሳ 53) እንዲሁም የምህረት ሥራዎች በመባል ስለ ሚታወቁት (ኢሳ 58፡7) ስለሚናገር ነው።

>> ነቢዩ ኢሳይያስ ከሚያስተምረው ትምህርት ውስጥ ገና ከመጀመሪያው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚናገረው ስለ ፍትሕ ነው፤ ለመሆኑ ለነቢዩ ኢሳይያስ ፍትሕ ማለት ምን ማለት ነው? በትምህርቱ ውስጥ ለምንስ ልዩ ትኩረት ተሰጠው?

ነቢዩ ኢሳይያስ ለፍትሕ ልዩ የሆነ ትኩረትና ሰፋ ያለ ቦታ በመስጠት በተደጋጋሚ ይናገራል፤ ያስተምራል፤ ይሟገታል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ የነበረበት ማኅበረሰብ ውስጥ ኢፍትሐዊነት የተንሰራፋበት፣ ኀያላንና ባለጠጎች ነን ባዮች አቅመ ደካማውና ድኻው ሕዝብ ላይ የጭቆና በትራቸውን ያሳረፉበት፣ በአጠቃላይ ጥቂት የማኅበረሰቡ ክፍሎች ብቻ ገናናነትና ድሎት የሚንጸባረቅበት ስለነበር ነቢዩ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማኅበረሰቡ ውስጥ ድምፅ አልባ ስለሆኑት ይናገራል(ኢሳ 1፡1-17)። ለነቢዩ ኢሳይያስ ፍትሕ ከሁሉም በፊት መቅደም አለበት፤ ፍትሕ ለሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍል በተለይም ለአቅመ ደካማው መተግበር አለበት እንጂ የጥቂት ሀብታሞችና ባለ ሥልጣኖች ብቻ መጠቀሚያ በሚያደርግ መልኩ የሚተገበር መሆን የለበትም፡፡

በአጠቃላይ ለነቢዩ ኢሳይያስ ፍትሕ በማኅበረሰቡ ውስጥ መተግበር ማለት፦

- የተጨቈኑትን መታደግ (ኢሳ 1፡17)፤

- አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት መጠበቅ (ኢሳ 1፡17)፤

- ባሎቻቸውን የሞቱባቸውን ሴቶች አቤቱታ መስማት (ኢሳ 1፡17)፤

- ጉቦ አለመቀበል፦ ጉቦ ተቀብላችሁ በደል የሠራውን ሰው ነፃ በመልቀቅ በደል የደረሰበትን ሰው ፍትሕ ለምትነፍጉት ወዮላችሁ (ኢሳ 5፡23)፤

- የእስራኤል ቅዱስ የሆነ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሕግና ያስተማረውን ሥርዓት አለማቃለል (ኢሳ 5፡24)፤

- የጭቆናን ሰንሰለትና የፍትሕ መጓደልን ቀንበር በማስወገድ የተጨቈኑትን ነፃ ማውጣት (ኢሳ 58፡6)፤

- ሰው ካለው ሀብት ቀንሶ ለረሀብተኞች ማካፈል (ኢሳ 58፡6፤10)፤

- ሠራተኞችን አለመጨቆንና አለመበዝበዝ (58፡3)፤

- መጠለያ የሌላቸውን ድኾች በቤት ተቀብሎ ማስተናገድ፣ የተራቆቱትን ማልበስና ዕርዳታ ለሚፈልጉት ሁሉ ፊት አለመንሣት (ኢሳ 58፡7)፤

- ሕዝብን የሚጨቁን ግፍ የሞላበት ሕግ አለማውጣት የሚሉት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው (ኢሳ 10፡1)፡፡

>> ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ኃጢአትና ውጤቱ በተደጋጋሚ ይናገራል፤ በነቢዩ ኢሳይያስ አገላለጽ ኃጢአት ምን ማለት ነው? የኃጢአት ውጤትስ ምንድን ነው?

እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ አስተምህሮት የኃጢአት ወሰነ ትርጉም ሰፋ ያለ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሕግን መተላለፍ፣ ዓመፃ፣ በጎ ማድረግን ዐውቆ አለመሥራት፣ ፍትሕን ማዛባት፣ ጉቦ መቀበል፣ ለአድባር ዛፍ መስገድ፣ ባዕዳን አማልክትን ማምለክ፣ በምሽት ጊዜ የሙታን መናፍስትን ክፉ ምክር ለመጠየቅ ወደ ዋሻዎችና መቃብር ቤቶች መሄድ፣ የረከሰ ሥጋ መብላትም ሆነ መረቅ መጠጣት ይገኙበታል (ኢሳ 1፡21-31፤ ኢሳ 65፡4)፡፡

ኃጢአት እንደ ብር የጠራውን ሕይወት ወደ ዝገት፣ እንደ ወይን ጠጅ ብርቱ የነበረውን ውሃ እንደተበረዘበት ቅራሪ የሚለውጥና ሰውነትን ሁሉ የሚያረክስ እንደሆነ ነቢዩ ያስረዳል(ኢሳ 1፡22 እና 25)፡፡ ኃጢአት ሕይወትን ቅጠሉ እንደረገፈ የወርካ ዛፍና ውሃ እንደሌለው የአትክልት ቦታ አድርጎ መጨረሻው ወደ ጥፋት ይመራል (ኢሳ 1፡30)፡፡ ኃጢአት እግዚአብሔርን ያሳዝናል(ኢሳ43፡27)፡፡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ጥሩ ወዳጅነት ያበላሻል፤ ኃጢአተኛውም ራሱንም ከእግዚአብሔር ያርቃል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከኃጢአተኛ ጋር አይተባበርም፡፡

ኃጢአት ሰውን ከእውነት ጋር እንዲቃረንና እንዲርቅ ያደርጋል፤ በብርሃን ተሞልቶ የነበረውንም ሕይወት ወደ ጨለማና ድንግዝግዝ ወደ ሆነው ጎዳና ይመራል፤ በሰው ሕይወትም ውስጥ የፍርሃትና የሐዘን መንፈስ ያሳድጋል (ኢሳ 59፡9-11)፡፡ በኃጢአተኛ ሕይወት ውስጥ እውነት ተቀባይነት ታጣለች፤ ታማኝነትም ቦታ አይገኝላትም(ኢሳ 59፡14)፡፡

የእግዚአብሔር የንስሓ ጥሪ ሰምተው፣ ራሳቸውን መርምረው፣ ድክመታቸውን ዐውቀው በትህትና መንፈስ በመታዘዝና ወደ እርሱ በመቅረብ ንስሓ የሚገቡትን ምድር የምታስገኘውን በረከት ይወርሳሉ፤ በኃጢአታቸው ጸንተው የሚኖሩት ግን ሰይፍ ይበላቸዋል (ኢሳ 1፡19)፤ በብርቱም ይቀጣሉ(ኢሳ 9፡13-21)፤ ይዋረዳሉ፤ ጥፋትም ይደርስባቸዋል(ኢሳ 43፡28)፡፡

>> በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ ከምናገኛቸው ዐቢይ ትምህርቶች ውስጥ ወደፊት ስለሚወለደው አዳኝ ወይም መሲሕ የሚናገረው ክፍል አንዱ ነው፡፡ ይህ ይመጣል ተብሎ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ እንዴት ይገለጻል?

በትንቢተ ኢሳይያስ ሰፋ ያለ ቦታ ከተሰጣቸው አስተምህሮቶች ውስጥ የአዳኝ መምጣት የሚያበስረውን ትንቢታዊ ቃል ይገኝበታል፡፡ በእርግጥ ነቢዩ ኢሳይያስ በመጀመሪያው የመጽሐፉ ክፍል ወደፊት ስለ ሚወለደው አዳኝ ይናገራል፤ ነገር ግን ይህ አዳኝ አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት የተለያዩ የአዳኝነት ተግባር ሊያከናውኑ የሚችሉ እንደሚመጡ ወይም እንደሚነሡ ይናገራል፡፡ እነዚህም፦

ሀ) የዐማኑኤልመወለድ (ኢሳ 7፡1-16)

የአዳኝ መምጣት ከሚያበስሩት ከነቢዩ ኢሳይያስ የትንቢት ቃል ውስጥ የዐማኑኤል መወለድ የሚያበስረውን በተለይም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከክርስቶስ የመወለድ መልካም ዜና ጋር በተያያዘ መልኩ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል፡፡ የነቢዩም ቃል በተለምዶ እንዲህ ይጠቀሳል፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ብላ ትጠራዋለች (ኢሳ 7፡14)፡፡

ለ) ወደፊትየሚነሣውየሰላምንጉሥ (ኢሳ 9፡ 6)

ይህንን ትንቢት ከመነገሩ በፊት ያለው ሁኔታ ስንመለከት ሕዝቡ ተስፋ ቈርጠውና ተርበው በምድሪቱ ላይ እንደሚንከራተቱ እንዲሁም ከመራባቸው የተነሣ ተበሳጭተው ንጉሣቸውንና አምላካቸውን እስከ መራገም እንደደረሱ ይገልጻል፡፡ ይህንን ዓይነት የመከራና የጨለማ ጊዜ ላሳለፈ ሕዝብ ነው ነቢዩ ድንቅ የሆነው የምሥራች ቃል እነሆ ሕፃን ተወልዶልናል! ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል! እርሱም መሪ ይሆናል፤ ስሙም "ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ" ይባላል በማለት የሚያበስረው (ኢሳ 9፡6)፡፡

ሐ) ከዳዊትዝርያዎችመካከልስለሚነሣውአዲስንጉሥ (ኢሳ 11፡ 2-9)

ይህ ከዳዊት ንጉሣዊ ዘር የሚያቈጠቈጠው(የሚወለደው) ንጉሥ ከላይ ኢሳ 9 ላይ ከተነገረለት ንጉሥ ጋር በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይህ ንጉሥ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ስለሚኖር የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል(ኢሳ 11፡2)፡፡ በተጨማሪም ይህ ንጉሥ ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዛዥ፣ ፍርዱም ጥበብ የተሞላበት፣ ረዳት ለሌላቸው ወገኖችና የድኾች መብት አስከባሪ፣ የወገቡ መታጠቂያ እውነት፣ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል(ኢሳ 11፡3-5)፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ይወለዳሉ ወይም ይነሣሉ ተብሎ የትንቢት ቃል ከተነገረላቸው ከሁለቱ ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ በመንግሥቱ ውስጥ ፍጥረት ሁሉ እርስ በርሱ ሳይጎዳዳ ወይም አንዱ በሌላው ላይ ጥቃት ሳያደርስ ተስማምቶ እንደሚኖር መገለጹ ነው፡፡ እርስ በርሳቸው አዳኝና ታዳኝ ሆነው የሚኖሩት እንስሳት ጠላትነታቸው ትተው በሰላም መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ሰውም ከፍጥረት ጋር ተስማምቶ ምንም ዓይነት ክፋት ወይም ጎጂ ነገር ሳይገኝ ምድሪቱም ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ የተሞላች ሆና ትኖራለች(ኢሳ 11፡6-9)፡፡

በአጠቃላይ ነቢዩ ኢሳይያስ ይመጣል ስለተባለው መሢሕ በተለያየ መልኩ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ ይህ መሢሕ ከአንዲት ወጣት ሴት እንደሚወለድ(ኢሳ 7፡14)፣ መንግሥቱ ለዘለዓለም እንደሆነ (ኢሳ 9፡6-7)፣ ሌላው መንገዱን እንደሚያዘጋጅለትና (ኢሳ 40፡3-5)፣ በገሊላ እንደሚሠራ (ኢሳ 9፡1-2) ይናገራል፡፡ በተጨማሪም የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ እንደሚሆን (ኢሳ 61፡1)፣ ሕመምተኞችን እንደሚፈውስ (ኢሳ 53፡4)፣ በየዋህነት እንደሚሠራ (ኢሳ 42፡1-3)፣ የእምነት መሠረት እንደሚሆንና(ኢሳ 28፡16) አሕዛብን እንደሚያድን(ኢሳ 65፡1-2) ነቢዩ ኢሳይያስ በደንብ አድርጐ ገልጾታል፡፡

>> ነቢዩ ኢሳይያስ ከተናገራቸው ትንቢታዊ ቃል ውስጥ መከራ ስለሚደርስበት ወይም መከራን በትዕግሥት ስለሚቀበለው አገልጋይ የሚናገረው ክፍል ይገኝበታል፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ ከተናገራቸው ትንቢቶች ውስጥ መከራ ስለሚደርስበት አገልጋይ በአዲስ ኪዳን በተለይም ስለ ክርስቶስ ሕማማት በሚናገረው ቦታ ላይ በስፋት ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ አገላለጽ ይህ አገልጋይ ግርማ፣ ውበትም ሆነ የሚስብ የደም ግባት ስለሌለው ንቀን ገለል አደረግነው በማለት በወቅቱ የነበረ አገልጋይ በማስመሰል ይናገራል፡፡ በእርግጥ ነቢዩ በወቅቱ ከነበረበት ሁኔታ በመነሣት በወቅቱ ለነበሩ ሰዎች ትንቢት የሚናገር ቢሆንም የተናገረው ትንቢት ለወደፊቱም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ አገልጋይ ከየትኛውም አገልጋይ ለየት የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አገልጋዩ የተናቀ፣ እንደውም እንደ ኢምንት የተቈጠረ፣ የመከራና የሐዘን ሰው ነው፡፡ አንድ አገልጋይ በተለይም በጌታው ሊናቅና ማንም ትኩረት ላይሰጠው ይችላል፤ ነገር ግን ይህ አገልጋይ የተለየ የሚያደርገው እያንዳንዳችን ልንሸከመው የሚገባንን መከራና ሕማም እርሱ እንደተሸከመ፣ ተወግቶ የቈሰለውም ስለ ኃጢአታችን፣ በመገረፍ የደቀቀውም እኛ ስለፈጸምነው በደል መሆኑ ነው፡፡

ይህ ሕይወቱን በፈቃዱ ለሞት አሳልፎ የሰጠው "የእግዚአብሔር ፍጹም አገልጋይ" ለየት የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ምንም እንኳ ከክፉ አድራጊዎች ጋር ተቈጥሮ የብዙዎችን በደል ቢሸከምም ከብዙ መከራና ሥቃይ በኋላ ግን የሕይወትን ብርሃን በማየት እንደገና ወደ ደስታ እንደሚመለስ መገለጹ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የከበረ ቦታ በእግዚአብሔር እንደሚሰጠው፣ ረዥም ዘመን እንደሚኖርና የተቀበለውም መከራ በከንቱ እንዳልሆነ መነገሩ ነው(ኢሳ 53፡11)፡፡ በተጨማሪም ይህ አገልጋይ ብዙዎችን የኃጢአትን ይቅርታ ያገኙ ዘንድ ስለእነርሱ የሚጸልይ መሆኑን ተነግሯል፡፡

የዚህ አገልጋይ ማንነት በተመለከተ ከሊቃውንቶች ዘንድ የተለያዩ አስተያየቶች ቢሰነዝሩም አብዛኛዎቹ ግን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በተለይም ሕማማቱ የተመለከተ መሆኑን በማረጋገጥ ይተነትኑታል፡፡ በአጠቃላይ የዚህ አገልጋይ ማንነት በትክክል ለመወሰን ቢቸግርም ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ግን ብዙም የሚያስኬድ አይሆንም፡፡

>> ነቢዩ ኢሳይያስ "የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ" ምንነትና ስለሚያከናውናቸው ተግባር ጽፎአል፤ ይህ እንዴት ይገለጻል?

በብዙ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ በሰዎች ላይ እያደረ ለመልካም ተግባራት ሲያነሣሣ፣ ሲያበረታታ፣ ሲመራ እንዲሁም በሥራ ሂደት ውስጥ ተባባሪ በመሆን አብሮ ሲጓዝ ይታያል፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥም ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ የተለያዩ ተግባራት ያከናውናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ይሰጣል(ኢሳ 11፡2)፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በእግዚአብሔር መልካም አገልጋይ የሚያድር፣ መልካም አገልጋዩንም ልባቸው ለተሰበረ እንዲፈውስ፣ የተጨቈኑትን ነፃ እንዲያወጣ፣ ለታሰሩትም ነፃነትን እንዲያበሥርና ለሕዝቦች ሁሉ ትክክለኛ ፍትሕን የሚያስገኝ ኃይል ነው፡፡ ከዚህም በላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በሰዎች ሁሉ የሚወርድበት ጊዜ እንደሚመጣ ከተነበየ በኋላ ውጤቱም ምድረ በዳው ለም ይሆናል፤ ለሙም መሬት ብዙ ፍሬ ይሰጣል፤ በምድሪቱ ሁሉ ላይ እውነትና ፍትሕ ይሰፍናል በማለት ይገልጻል(ኢሳ 32፡15-16)፡፡

እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ አገላለጽ እግዚአብሔር መንፈሱ ይለግሳል፤ ይህ መንፈስ በእግዚአብሔር የታመኑትን ታዛዥ ሆነው ለመኖር የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በሰዎች መካከል በመሆን ድንቅ ድንቅ የሆኑትን ተግባራት ያከናውናል(ኢሳ 44፡3፤ 63፡10-14)፡፡ በአጠቃላይ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወት፣ ታላላቅ ተግባራትን የሚያከናውንና የሕዝቦች ልብ ወደ ታዛዥነት የሚለውጥ መንፈስ እንደሆነ ከነቢዩ ኢሳይያስ የተለያዩ ትምህርቶች እንረዳለን፡፡

>> ነቢዩ ኢሳይያስ የኢየሩሳሌም ከተማን እንዴት ይገልጻታል? በትምህርቱ ውስጥ በምን ዓይነት መልኩ ያብራራታል?

በትንቢተ ኢሳይያስ በሁለተኛውና በሦስተኛው ክፍል (ከምዕራፍ 40-66) ማለትም ከባቢሎን ስደት በኋላ ስለነበረው ኑሮ ትኩረት በተሰጠበት ቦታ ላይ ኢየሩሳሌም ሰፋ ያለ ትኩረት ይዛ ትገኛለች(ኢሳ 51፤ 52፤ 54፤ 60፤ 62)፡፡ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ከተማ ጽዮን፣ የእግዚአብሔር ከተማ፣ መከረኛዪቱ ከተማና ቅድስቲቱ ከተማ በመባል በተለያዩ መጠሪያ ስሞች ትጠቀሳለች(ኢሳ 54፡11፤ 60፡14፤ 62፡1፤ 52፡1)፡፡ ብዙ ጊዜ ኢየሩሳሌም ጽዮን በሚለው ስም ትጠራለች፡፡ በእርግጥ ጽዮን ኢየሩሳሌም ከተሠራችባቸው ተራራዎች አንዱ ሲሆን ቃሉ "አምባ" የሚለውን ትርጓሜ ይሰጣል፡፡ ለዚህም ነው ዘማሪው በእግዚአብሔር የሚታመኑ ሰዎች ከቶ እንደማይነቃነቅና እንደማይናወጥ እንደ ጽዮን ተራራ የጸኑ ናቸው በማለት የሚዘምረው (መዝ 125፡1)፡፡

ጽዮን ዳዊት ይዞት እንደነበረና ቀጥሎም ታቦቱን ወደ ጽዮን እንዳመጣ ይታወቃል (2 ሳሙ 5፡6-9፤ 6፡10-12)፡፡ በኋላ ግን ጽዮን ቤተ መቅደስ ለተሠራበት ሞሪያ ለተባለው ተራራ መጠሪያ ሆነ (ኢሳ 8፡18፤ 18፡7፤ 24፡23፤ 2 ነገ 19፡21፤ መዝ 48፡2፤ 69፡35)፡፡ ቀጥሎም ለመላዋ ኢየሩሳሌም መጠሪያ ስም ሆነ፡፡ ጠቅላላው የአይሁድ ሕዝብም በቦታው ስም ጽዮን እየተባሉ መጠራት ጀመሩ(መዝ 126፡1)፡፡ ስለዚህ ቀድሞ ኢየሩሳሌም በመባል ትታወቅ የነበረችው ከተማ በዳዊት መዝሙርም ሆነ በትንቢተ ኢሳይያስ ሌላ ተጨማሪ ስም አግኝታ ጽዮን በመባል መጠራት ጀመረች፡፡

ኢየሩሳሌም በእርግጥ ቤተ መቅደስ የሚገኝባት ከተማ ስለነበረች የነቢያቶችና ከተለያዩ ቦታዎች መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ ለሚመጣው ሕዝብም ዋና ትኩረት የሚሰጣት ቦታ ሆና ለብዙ ዘመናት ኖራለች፤ አሁንም ትኖራለች፡፡

>> በአዲስ ኪዳን ውስጥ በስፋት ከተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት መካከል ትንቢተ ኢሳይያስ አንዱ ነው፤ ትንቢተ ኢሳይያስ ለምንድን ነው ከሌሎቹ የብሉያ ኪዳን መጽሐፍት ለየት ባለ መልኩ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው፡፡

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ትንቢተ ኢሳይያስ በወንጌላውያንና በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ በእርግጥ የአዲስ ኪዳን ሰባኪዎች አድማጮቻቸውን ለማስተማርና ለማሳመን በተለይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም በነቢያት ተነግሮለት የነበረውና ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ ለብዙ ዘመናት የቆየው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለማረጋገጥ ደጋግመው ነቢያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡

በዚህም መሠረት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ትንቢተ ኢሳይያስ በተለያየ መልኩ በስፋት ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በምድረ በዳ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ በበረሓም ለአምላካችን ጥርጊያ ጐዳና አብጁ በማለት ስለ መጥምቁ ዮሐንስ የተነገረው(ኢሳ 40፡3፤ ማቴ 3፡3) ይገኝበታል፡፡ በተጨማሪም ስለ ዐማኑኤል መወለድ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ የማስተማሩ ምስጢር፤ ስለሚሠቃየው አገልጋይ ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢየሱስ በሽተኞችን ስለመፈወሱ(ኢሳ 53፡4፤ ማቴ 8፡17)፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና ተልእኮ ወይም አገልግሎት ጋር በተያያዘ መልኩ የተነገረውንና(ኢሳ 61፡1-3፤ ሉቃ 4፡14-21) የእግዚአብሔር መንግሥት ለአረማውያን ጭምር የተከፈተ መሆኑን ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው (ኢሳ 11፡10፤ ሮሜ 15፡12)፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1. የነቢዩ ኢሳይያስ ማንነትና በእርሱ ስም በሚጠራው ትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ)ነቢዩ ኢሳይያስ ባለትዳርና የልጆች አባት ነበር፤ ሚስቱም ነቢይት ነበረች፡፡ ለ) ትንቢተ ኢሳይያስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከመዝሙረ ዳዊት ቀጥሎ ከሁሉም ነቢያቶች በላይ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ መጽሐፍ ነው፡፡ ሐ) ትንቢተ ኢሳይያስ የ66 ምዕራፎች ጥንቅር ሲሆን መጽሐፉም ሦስት የተለያዩ ትልልቅ ክፍሎች አሉት፡፡ መ) ኢሳይያስ ማለት "እግዚአብሔር ያድናል" ወይም "እግዚአብሔር አዳኝ ነው" ማለት ነው። ሠ) ኢሳይያስ ባቢሎን ውስጥ ተወልዶ ያደገ ነቢይ ነው፡፡

2. ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ፍትሕና ስለ ኃጢአትና ውጤቱ ከሚያስተምረው ትምህርት ውስጥ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው?

ሀ) በኃጢአተኛ ሕይወት ውስጥ እውነት ተቀባይነት ታገኛለች፤ ታማኝነት ግን ቦታ አይገኝላትም፡፡ ለ) ፍትሕ ማለት አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶችን መብት መጠበቅ ነው፡፡ ሐ) ፍትሕ ማለት መጠለያ የሌላቸውን ድኾች በቤት ተቀብሎ ማስተናገድ፣ የተራቆቱትን ማልበስና ዕርዳታ ለሚፈልጉት ሁሉ ፊት አለመንሣት ነው፡፡ መ) ኃጢአት ሕይወትን ቅጠሉ እንደረገፈ የወርካ ዛፍና ውሃ እንደሌለው የአትክልት ቦታ አድርጎ መጨረሻው ወደ ጥፋት የሚመራ ነው፡፡ ሠ) የንስሓ ጥሪ የማይቀበሉና በኃጢአታቸው ጸንተው የሚኖሩ ሰይፍ ይበላቸዋል፡፡

3. የኢሳይያስ የነቢይነት ጥሪና ነቢዩ ኢሳይያስ ወደፊት ስለሚመጣው መሲሕ ከተናገረው የትንቢት ቃል ውስጥ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው? (ይህንን ለመመለስ ትንቢተ ኢሳይያስ ከምዕራፍ 6 እስከ 11 በሚገባ ማንበብ ያስፈልጋል)

ሀ) መለኮታዊ ድምፅ ማንን እልካለሁ? መልእክተኛ የሚሆንልስ ማን ነው? ብሎ በጠየቀ ጊዜ ኢሳይያስ "እነሆ ብዙ ነቢያቶች አሉ፤ እነርሱን ላክ" በማለት መለሰ፡፡ ለ) ወደፊት የሚወለደው ዐማኑኤል ክፉውን ነገር ትቶ መልካሙን ነገር ለመምረጥ የሚያስችል ዕውቀት በሚያገኝበት ጊዜ ሰማያዊ መና ይመገባል፡፡ ሐ) ወደፊት የሚነሣው የሰላም ንጉሥ ንጉሣዊ ሥልጣኑ ወሰን ይኖረዋል፤ ነገር ግን መንግሥቱ ዘላለማዊ ሰላም የሰፈነበት ይሆናል፡፡ መ) ከእሴይ ዘር የሚገኘው ንጉሥ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ይኖራል፤ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል፤ ክፉ ሰዎችም ከአፉ በሚወጣው ቃል ይገደላሉ፡፡ ሠ) ንጉሡ ሰላም የሰፈነበት መንግሥት ሲመሠርት የእግዚአብሔር ቅድስት ኮረብታ በሆነችው በጽዮን ሰውን የሚጎዳ ክፉ ነገር ይገኛል፡፡

4. በትንቢተ ኢሳ ምዕራፍ 49 ላይ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ "እናት የራስዋን ልጅ መርሳት ፣ የወለደችውንስ መጥላት ትችላለችን? ምንአልባት እናት ልጅዋን ልትረሳ ትችል ይሆናል፤ እኔ ግን እናንተን ከቶ አልረሳችሁም"፡፡ እግዚአብሔር ይህን የተናገረው ለማን ነው?

ሀ) ለእስራኤል ሕዝብ ለ) ለኢየሩሳሌም ሕዝብ ሐ) ለግብጻውያን መ) ለባቢሎናውያን ሠ) ለአሶራውያን፡፡

5. ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢት ቃሉ ውስጥ መከራ ስለሚደርስበት የእግዚአብሔር አገልጋይ ተናግሮአል፡፡ የዚህ አገልጋይ የአገልግሎት ተግባርና የመከራ ሕይወት በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው? (ይህንን ለመመለስ ኢሳ ከምዕራፍ 50 እስከ ምዕራፍ 55 ማንበብ ያስፈልጋል)

ሀ) አገልጋዩም "ለሚገርፉኝ ጀርባዬን ሰጠኋቸው፤ ሲሰድቡኝና ጢሜን ሲነጩ ፣ እየተፉም ሲያፌዙብኝ ፊቴን ከእነርሱ በማዞር አልሸሸግሁም" ይላል፡፡ ለ) አገልጋዩም "ልዑል እግዚአብሔር ራሱ ይከራከርልኛል፤ ታድያ ወንጀለኛ አድርጎ የሚፈርድብኝ ማን ነው?" ይላል፡፡ ሐ) እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል "እነሆ አገልጋዬ በክብርም እጅግ ከፍ ከፍ ይላል፤ ፊቱና የመልኩ ደም ግባት ከሰው ልጆች ሁሉ ይልቅ የተዋበ ይሆናል"፡፡ መ) ይህ አገልጋይ በአንደበቱ ሐሰት ባይገኝበትም በሞቱ ከክፉ አድራጊዎች ይቈጠራል፡፡ ሠ) ይህ አገልጋይ የብዙዎችን በደል ተሸክሞአል፤ የኃጢአትንም ይቅርታ ያገኙ ዘንድ ጸልዮላቸዋል፡፡

6. ለነቢዩ ኢሳይያስ ፍትሕ መተግበር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም ፍትሕ ማጓደለም ምን እንደሆነ ከላይ በትምህርቱ ተብራርቶአል፤ ዛሬስ እያንዳንዳችን በምንኖረው ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ፍትሕ መተግበር የሚጓደሉባቸው ሁኔታዎች ያጋጥሙናልን? ለምሳሌ እያንዳንዳችን በምንኖረው ሕይወት፣ በቤተሰብ ውስጥ፣ በጎረቤታችን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ፣ በሥራ ቦታችን የሚገጥሙን ኢፍትሐዊ ተግባራት መስለው የሚታዩን ነገሮች የትኞቹ ናቸው? እኛ በዕለታዊ ሕይወታችን ሲያጋጥሙን እንዴት ወይም በምን ዓይነት ሁኔታ ልናልፋቸው እንሞክራለን?