እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳፩ - የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - መግቢያ

ክፍል ሦስት - ትምህርት ሃያ አንድ

የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - መግቢያ

ProphetsPerugino1>> ነቢይ የሚለው ቃል አመጣጡ እንዴት ነው? የቃሉ ትርጓሜስ እንዴት ይገለጻል?

ነቢይ የሚለው ቃል አመጣጡ "ናቪ" ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም "መጥራት" እና "ማብሠርን" ያመለክታል፡፡ ሊቃውንት ይህንን ቃል ወደ ግሪክ ሲተረጉሙት "ፕሮፌቴስ" የሚለውን ትርጓሜ ሰጥተውታል፡፡ ይህም "ፕሮ" እና "ፌሚ" የሚሉት የግሪክ ቃላት ጥምረት ነው፡፡ "ፕሮ" የሚለው ቃል ቅድሚያ ወይም ከአንድ ነገር በፊት ማለትን ሲያመለክት "ፌሚ" ደግሞ መናገርን፣ ማብሠርንና ማሳወቅን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ "ፕሮፌቴስ" ማለት የወደፊቱን ነገር አስቀድሞ መናገር ወይም ማብሠር ወይም ማሳወቅ የሚለውን ትርጓሜ ይሰጠናል፡፡ ምዕራባውያን መጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ይህንኑ የግሪክ ቃል ቀጥታ በመውሰድ "ፕሮፌት" የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ፡፡ የሴሜቲክ ቋንቋ ቤተሰብ የሆኑት ግዕዝና አማርኛ ከዕብራይስጡ ቃል "ናቪ" የሚቀራረብ ትርጓሜ በመውሰድ ነቢይ የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ፡፡ {jathumbnail off}

>> ነቢይ ማንነቱ እንዴት ይገለጻል? ነቢይ ማን ነው?

ነቢይ ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ የሆነ ቀረቤታ ያለው ሆኖ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እሱ የመጣውን ቃል ለሰዎች በማስተላለፍና በማሳወቅ የሚያገለግል የእግዚአብሔር ሰው ነው። ነቢይ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተለያዩ መንገዶች ማለትም በራእይ፣ በሕልም፣ በመልአክት አማካኝነት የተቀበለውን መልእክት ለሰዎች የሚያደርስና የሰዎችንም ጩኸት ወደ እግዚአብሔር በማቅረብ እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል መልእክተኛ ነው(አሞ 5፡4፤ አሞ 7፡2)። ነቢይ የወደፊቱን ብቻ የሚናገር ሳይሆን ስለ ወቅታዊ ሁኔታዎችና ስለሚኖርበት ማኅበረሰብ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችም ጭምር የሚናገር ነው። ነቢይ አብዛኛውን ጊዜ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር መንገድ እንዲመለስና ንስሓ በመግባት ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቅ ጩኸቱን የሚያሰማ መልእክተኛ ነው። በአጠቃላይ ነቢይ በምድር ላይ እግዚአብሔርን ወክሎ በሰዎች መካከል የሚገኝ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ወዳጅነት ወይም ቀረቤታ ያለውና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን መልእክት "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል" በማለት ሰዎችን በማስተማር "የእግዚአብሔር መናገርያ አፍ" ሆኖ የሚያገለግል መልእክተኛ ነው፡፡

>> በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢይ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰውና ቃሉ አገልግሎት ላይ የዋለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢይ የሚለው ቃል ገና ከመጀመሪያው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምረን እናገኛለን፡፡ እግዚአብሔር በሕልም ለአቢሜሌክ ሲያናግረው አብርሃም ነቢይ እንደሆነና እንደሚጸልይለት ይገልጽለታል(ዘፍ 20፡7)፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ ወንድምህም አሮን እንደ ነቢይ ሆኖ ስለ አንተ ይናገራል ብሎታል(ዘጸ 7፡1)፡፡ እስራኤላውያን ከምድያማውያን እጅ ያድናቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በጮኹ ጊዜ እርሱም አንድ ነቢይ ወደ እነርሱ ላከ፤ ያም ነቢይ የእስራኤል አምላክ ከሆነው ከእግዚአብሔር ዘንድ ያመጣውን መልእክት ነገራቸው(መሳ 6፡8)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሴት ነቢያቶችም ገና ከጥንት ጀምሮ ከወንዶች ነቢያቶች ጎን ለጎን ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን፡፡ ከእነዚህም ነቢያቶች ውስጥ የአሮን እኅት ነቢይት ሚሪያም(ዘጸ 15፡20)፣ የላፒዶት ሚስት ነቢይት ዲቦራና(መሳ 4፡4) በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የነበረችው ነቢይት ሑልዳ ይገኙበታል(2 ነገ 22፡14)፡፡ ታልሙድ የተባለው የአይሁዳውያን አስተምህሮ የያዘው መጽሐፍ እንደሚያስረዳው በአይሁዳውያን ዘንድ የአብርሃም ሚስት ሣራ፣ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና፣ የንጉሥ ዳዊት ሚስት የነበረችው አቢጋይልና አስቴር እንደ ነቢይት ይቈጠራሉ፡፡

>> ከክርስትና እምነት ውጭ ባሉት አማኒያን ዘንድ ነቢይ ወይም ነቢያት እንዴት ይገለጻሉ?

በእስልምና ሃይማኖት ዘንድ ነቢያቶች የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው፡፡ ቅዱስ ቁርአን ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱ ሃያ አምስት ነቢያቶችና እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ስማቸው ያልተጠቀሱ ነቢያቶች ይገኛሉ፡፡ ከሃያ አምስቱ ነቢያት ውስጥ ለአራቱ ብቻ ቅዱሳን መጻሕፍት ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለተሰጣቸው ልዩ ቦታ ይዘው ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የኦሪት መጻሕፍት ለሙሴ፣ መዝሙራት ለዳዊት፣ ወንጌላት ለኢየሱስና ቁርአን ለሞሐመድ ናቸው፡፡ አይሁዶችና ሙስሊሞች አዳም የመጀመሪያው ነቢይ እንደሆነ ሲያምኑ ሙስሊሞች ግን ሞሐመድ ለሁሉም የተላከ የመጨረሻው ነቢይ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ለሙስሊሞች ኢየሱስ ነቢይ እንደሆነና የተወለደውም ከድንግል እንደሆነ ቅዱስ ቁርአን ይገልጻል፡፡

>> ነቢይ ከሚለው ቃል በተጨማሪ ነቢያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሌላ መጠሪያ ስም አላቸውን? ካላቸው የትኞቹ ናቸው?

በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ነቢያት ነቢይ በሚለው ስም ብቻ ሳይሆን በተለያየ ስም ሲጠሩ ይታያል፤ ነገር ግን አገልግሎታቸው አንድ ነው፤ ይህም እንደ ድልድይ ሆኖ የእግዚአብሔር መልእክት ለሕዝብ ማስተላለፍ እንዲሁም የሕዝብ ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ማድረስ ነው፡፡ ከእነዚህም መጠሪያ ስሞች መካከል የሚከተሉት ይገኝበታል፡፡

ባለራእይ፦ ነቢያቶች በአንዳንድ ቦታዎች ውስጥ በዚህ ስም ሲጠሩ እናገኘለን፡፡ ባለ ራእይ ማለት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጸለትን ራእይ ወደ ሕዝቡ የሚያስተላልፍ መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ ባለ ራእይ የሚለው ቃል የነቢይ ሌላ መጠርያ ስሙ እንደነበር ነው፡፡ ባለ ራእይ ሰው ሳያንቀላፋ በተመስጦ የሚያየው የእግዚአብሔር ቃል የሚገለጥበት ነው፡፡ ራእይ ከሕልም የተለየ ነው፡፡ ራእይ እግዚአብሔርን ለሚያውቁ የእግዚአብሔር መንፈስ ላደረባቸው ይሰጣል(ዘኁ 12፡6፤ ሐዋ 2፡17)፡፡ ከነቢያቶች መካከል ሕዝቅኤልና ዳንኤል ብዙ ራእይ አይተዋል፡፡

የእግዚአብሔርሰው፦ ነቢይ ማንነቱን ሲገልጹ ከተጠቀሙባቸው መጠርያ ስሞች ውስጥ አንዱ የእግዚአብሔር ሰው የሚለውን ነው፡፡ ይህም የተደበቁትን ወይም የተሰወሩትን ነገሮች የማወቅ፣ ለሌሎች የመግለጽና የማሳወቅ ልዩ ስጦታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠው መንፈሳዊ ሰው ነው(1 ሳሙ 9፡6-11)። ይህ የእግዚአብሔር ሰው በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ታላቅ ቅዱስ ሰው ተደርጎ ይታያል። እሱም ከእግዚአብሔር በተሰጠው ልዩ የጸጋ ኃይል ታምራቶች የማድረግ ችሎታ ስላለውና ድንቃ ድንቅ የሆኑ ነገሮች ሲያከናውን ስለሚታይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ታላቅ ከበሬታ ያለው ብቻ ሳይሆን የሚፈራም ጭምር ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የእግዚአብሔር ሰው በምድር ላይ ወይም በሰዎች መካከል ታላቅ የሆነ መለኮታዊ አምላክ ወክሎ እንደሚገኝ ስለሚቆጠርና አልፎ አልፎ ድንቃ ድንቅ የሆኑ ታምራቶችንም ስለሚያከናውን ነው፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤልሳ ውሃ ውስጥ ሰምጦ የነበረውን የተውሶ መጥረቢያ በተአምር ውሃው ላይ እንዲንሳፈፍ ሲያደርግ ይታያል (2 ነገ 6፡1-7)፡፡

የእግዚአብሔርአገልጋይ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢያት የእግዚአብሔር አገልጋይ በሚል ስም ሲጠሩም ይታያል፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት ውስጥ ነቢያት የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናቸውና በዚሁ ስም መጠራታቸውን ይታወቃል(2 ነገ 24፡ 2)፡፡ ነቢያቶች የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናቸው የታወቀ ቢሆንም የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚለው ግን እንደ መጠሪያ ስማቸው ሆኖ ሲያገለግል የምናገኘው በጥቂት ቦታዎች ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ነቢይ፦ ይህ ቃል ከነቢያትና ከአገልግሎታቸው ጋር በተያያዘ መልኩ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል፡፡ ነቢይ ለአንድ መንፈሳዊ አገልግሎት የተጠራ ወይም ሕዝብንና እግዚአብሔርን እንደ ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል ከሕዝብ መካከል በእግዚአብሔር የተመረጠ ሰው ነው። ነቢይ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ተወካይ በመሆንና ድምጹን ከፍ አድርጎ በመናገር ወይም በመጮኸ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መልእክት ለሕዝቡ የሚያስተላልፍ አገልጋይ ነው፡፡ በተለያዩ የነቢያት መጻሕፍት ውስጥ ከየትኞቹም የነቢያት መጠርያ ስሞች በላይ ነቢይ የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ነቢይ በእግዚአብሔርና በሕዝብ መካከል ሆኖ የሚያገለግል መልእክተኛ፣ አገልጋይ፣ እንደዚሁም የእግዚአብሔር መናገርያ አፍ ነው፡፡

>> ነቢይ መሆን የሚችል ማን ነው?

ከሁሉም በፊት ማወቅ የሚኖርብን ነገር ነቢይነት የእግዚአብሔር ጥሪ መሆኑን ነው። ስለዚህ ለነቢይነት ማን ሊጠራ ይችላል በምንልበት ጊዜ በጎ ፈቃድ ያለው ማንኛውም ሰው ሊጠራ ይችላል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ትእዛዛቱን ጠብቆ በቅድስና የሕይወት ጎዳና የሚመላለስ፣ መንፈሳዊ ብስለት ያለው፣ ውስጣዊ ዓይነ ልቦናው በእግዚአብሔር መንፈስ የበራ፣ እግዚአብሔርን ማድመጥ የሚችል፣ የእግዚአብሔርን ጥሪ ለመቀበል ዝግጁ የሆነና ሕዝቡን ለማገልገል ፈቃደኝነት ያለው ወንድም ሆነ ሴት በነቢይነት የአገልግሎት ተግባር ላይ መሠማራት ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ወንድም ሆነ ሴት በእግዚአብሔር መራጭነት በነቢይነት የአገልግሎት ተግባር ተሠማርቶ እግዚአብሔርንና ሕዝቡን ማገልገል ይችላል።

ለነቢይነት የሚመረጡት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የበሰሉ፣ ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር በሰላም የሚኖሩና ወቀሳ የሌለባቸው ናቸው፡፡ ነቢይነት በዘር ወይም በጎሳ ሲወርድ ሲዋረድ የሚመጣ የአገልግሎት ማዕረግ ሳይሆን በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድና ምርጫ የሚከናወን የተቀደስ የአገልግሎት ተግባር ነው፡፡

>> በቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነቢይ በሚል ስም የተጠሩት እነማን ናቸው? ነቢይ የሚለው ስም አጠቃቀም በቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ ውስጥ እንዴት ተገልጾ ይገኛል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመጀመርያው ነቢይ በመባል በእግዚአብሔር የተጠራው ልዩ የእግዚአብሔር ወዳጅ፣ የብዙሃን አባትና የእምነት አባት በመባል የሚታወቀው አብርሃም ነው(ዘፍ 20፡6-8)። ቀጥሎ በታላቅ ነቢይነቱ የሚታወቀው ዐሥርቱ ትእዛዛትን ጨምሮ የተለያዩ ሕግና ሥርዓትን ከእግዚአብሔር ዘንድ በመቀበል ወደ እስራኤል ሕዝብ ያስተላለፈና እግዚአብሔርንም ፊት ለፊት ያነጋገረው ነቢይ ሙሴ ነው(ዘዳ 34፡10)፡፡ እግዚአብሔር ከሙሴ በኋላ ሌላ ነቢይ ለሕዝቡ እንደሚያስነሣላቸውም እንዲህ በማለት ቃል ገብቶላቸዋል፤ ስለዚህም እንደ አንተ ያለ ሌላ ነቢይ ከሕዝባቸው መካከል አስነሣላቸዋለሁ፤ እርሱ የሚናገረውን ቃል እሰጠዋለሁ፤ እኔም የማዝዘውን ሁሉ ለሕዝቡ ይነግራል(ዘዳ 18፡18)።

የነቢይነት አገልግሎት ተግባር ከእስራኤላውያን ውጪ በሌሎች ሕዝቦች ዘንድም ይተገበር እንደነበርና እግዚአብሔርም በነቢያት አማካይነት ይናገር እንደነበር ከኦሪት መጽሐፍት እንረዳለን፡፡ ከእነዚህም መካከል በዓማው ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በፐቶር ከተማ ይኖር የነበረው የቢዖር ልጅ ነቢዩ በለዓም ይጠቀሳል(ዘኁ 22፡18)፡፡

ነቢዩ ሳሙኤል በኖረበት ጊዜ ግን የነቢይነት ሥራ እንደ አንድ የአገልግሎት ተግባር ሆኖ በግልጽ መታየት ጀመረ(1ሳሙ 10፡19)፡፡ ሳሙኤል እንደ መሪ፣ ሽማግሌና ዳኛ(1ሳሙ 7፡2-17) ሆኖ ሕዝቡ ከማገልገሉም በላይ እንደ ነቢይም ባለ ራእዩ የሚል የቅጽል ስም ሁሉ ተሰጥቶት(1ሳሙ 9፡12-13) "በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ" እያለ ያስተምር ነበር፡፡

ቀጥሎም ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ውስጥ በጣም ከታወቁት መካከል አንዱ የሆነውና በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ በሚገኘው ቴስቢ በሚባለው ቀበሌ የተወለደው ኤልያስ ነው፡፡ የነቢዩ ኤልያስን እግር በመከተል ለነቢይነት ተጠርቶ ያገለግል የነበረው የሣፋጥ ልጅ ነቢዩ ኤልሳዕ ነው፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ከእግዚአብሔር በተገለጠለት መሠረት ኤልሳዕን ለነቢይነት ጠራው፡፡ እንደተጠራም ኤልሳዕ ሥራውን ትቶ ኤልያስን እየተከተለ ያገለግለው ነበር (1 ነገ 19፡16-21፤ 2 ነገ 3፡11)፡፡

በአጠቃላይ የነቢይነት የታሪክ ሂደት በምናይበት ጊዜ ከጥንት ዘመን ጀምሮ እግዚአብሔር የሚያገለግሉትን ነቢያቶች ከሕዝቡ መካከል ሲያስነሣና እነሱም የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ሕዝቡ ሲያስተላልፉ ኖረዋል፡፡ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ነቢያቶች እንደነበሩና ዛሬም በሕዝቡ መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ የሚያሰሙና ሕዝቡን ወደ ንስሓ የሚጠሩ ነቢያቶች አሉ፡፡ ስለዚህ የነቢይነት አገልግሎት ታሪክ በአንድ ወቅት ብቻ ከአንድ ሕዝብ ጋር ተከናውኖ የተቋጨ ታሪክ ሳይሆን ቀጣይነት ያለውና ወደፊትም የሚከናወን ተግባር ነው፡፡

>> በነቢያት ታሪክ ውስጥ እውነተኛና ሐሰተኛ ነቢያት የሚባሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እውነተኛና ሐሰተኛ ነቢያት እንዴት መለየት ይቻላል?

የኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ አንድን ነቢይ እውነተኛ መሆኑን ተለይቶ የሚታወቅበትና ሕዝቡም ይህንን እውነተኛውን ነቢይ እንዲከተሉት የሚገባ መሆኑን ለመረዳት እንዲጠቅም በማለት ሁለት መስፈርቶች ይገልጻል። በመጀመሪያ ነቢዩ በሚያስተምርበት ጊዜ ወይንም የትንቢት ቃል በሚናገርበት ጊዜ የሠራዊት ጌታ በሆነው በእግዚአብሔር ስም መናገርና አለመናገሩን ተለይቶ መታወቅ አለበት(ዘዳ 18፡20)፡፡ ነቢዩ ሕልም የመተርጐምም ሆነ ታምራትንና አስደናቂ ነገሮች የማድረግ ችሎታ ቢኖረውም የሚያከናውናቸው ተግባራት ሕዝቡን የሠራዊት ጌታ ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር የማይመራ ከሆነ እንደ ሐሰተኛ ነቢይ ስለሚቆጠር ሕዝቡ እሱን መስማት እንደሌለባቸውና እንዲያውም መገደል እንዳለበት እግዚአብሔር አምላክ ያስገነዝባል(ዘዳ 13፡1-5)፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ሌላው መታየት ያለበትና አስፈላጊ የሆነው ነጥብ ነቢዩ የሚያስተምረው ትምህርት ሕዝቡን ወደተሳሳተ ጎዳና የሚመራ ነውን ወይስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ ነው የሚለውን ነው(ዘዳ 13፡5፤1 ነገ 18)፡፡

በተጨማሪም እውነተኛ ነቢይ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ ሕዝቡን ወደ እውነተኛው ጎዳና የሚመራ ትምህርትና እውነተኛውና ትክክለኛውን ከእግዚአብሔር ያገኘውን የትንቢት ቃል የሚያስተላልፍ መሆን ይኖርበታል እንጂ ከንቱ ተስፋ እየሰጠ ሕዝቡን የሚሸነግል መሆን የለበትም፡፡ የተናገረው የትንቢት ቃል እውነተኛና በእግዚአብሔር ፈቃድ መሠረት የተነገረ ከሆነ ነቢዩ በሕይወት እያለ ያስተላለፈውን የእግዚአብሔር ቃል አብዛኛውን ተፈጻሚነት ያገኛል(1 ነገ 18፡41-46)፡፡

አብዛኞቹ ነቢያቶች ሲያስተምሩ ሕዝቡን ወደ ንስሓ እንዲመለስ ሲመክሩ ይህ ካልሆነ ግን በሕዝቡ ላይ ቅጣት እንደሚመጣ ደጋግመው ተናግረዋል፤ የተናገሩትንና ያስተማሩት በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበር የተናገሩት አብዛኘው የትንቢት ቃል በሕይወት እያሉ ተፈጻሚነት ያገኝ ነበር(ኢሳ 1፡21-31፤ ሕዝ 9፤ ዮና 3)፡፡ ሌላው ነቢያት ስለ ራሳቸው የግል ጥቅም በማሰብ ነገሥታትንና ሕዝብን ለማስደሰት ከራሳቸው ፈጥረው ትንቢት የሚናገሩና ምንም ሰላም ሳይኖር "ሁሉ ነገር ሰላም ነው" እያሉ ሕዝቡን የሚሸነግሉ ከሆነ እውነተኛ ነቢይነታቸው እጅግ በጣም አጠራጣሪ ነው(ሕዝ 13፡3)፡፡

በመጨረሻም እውነተኛ ነቢይ የክፋትን መንገድ የማይከተልና የተሰጠውን የእግዚአብሔር ኃይል አግባብ ባለው ሁኔታ የሚጠቀም መሆን አለበት(ኤር 23፡10)። እውነተኛ ነቢይ ከምንምና ከማንም በላይ በእግዚአብሔር የሚታመን መሆን አለበት(ኤር 3፡2)፡፡ እውነተኛ ነቢይ መንፈሳዊ ሕይወቱ እግዚአብሔርን የሚያስደስት፣ የማያመነዝር፣ ሐሰት የማይናገር፣ የማይሰክር፣ እግዚአብሔር የገለጠለትን ራእይ የሚያስተውልና ሰዎችን ለክፉ ሥራ የማያነሣሣ መሆን አለበት(ኢሳ 28፡7-9፤ ኤር 23፡11-14)፡፡

>> በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሐሰተኛ ነቢያት ተናግሮአል፤ እንደ ጌ.ኢ.ክ አገላለጽ ሐሰተኛ መምህራን እንዴት ሊታወቁ ይችላል?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሰተኞች መምህራን ብቻ ሳይሆን እኔ መሲሕ ነኝ በማለት ጭምር ለማስተማር የሚነሡና ታምራትንም ጭምር ማከናወን የሚችሉ ሐሰተኞች መምህራን እንደሚመጡ በግልጽ ተናግሯል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነዚህ ሐሰተኞች መምህራን መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ከመናገሩም በተጨማሪ እነዚህ ሐሰተኛ መምህራኖች በሥራቸው ፍሬ እንደሚታወቁ አበክሮ ይገልጻል(ማቴ 7፡15፤ ማቴ 24፡4)። እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገላለጽ ሐሰተኞች መምህራን በውጪያቸው በግ የሚመስሉ በውስጣቸው ግን እንደ ነጣቂ ተኩላ ናቸው፡፡ በእርግጥ መጥፎ ዛፍ መጥፎ ፍሬ እንደሚያፈራ ሁሉ ሐሰተኞች መምህራንም መልካም ፍሬ ስለማያፈሩ በሥራቸው ተለይተው ይታወቃሉ(ማቴ7፡15-23)፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቶቹ ሲያስጠነቅቃቸው ሰዎች ሁሉ ሲያመሰግኑአችሁና ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸውም ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ አድርገው ነበር ይላል (ሉቃ 6፡26)። ነቢይ የሚያስተላልፈው መልእክት ወይንም የሚያስተምረው ትምህርት ለራሱ ውዳሴና ክብር ሳይሆን የእግዚአብሔር መልእክትና ስለ እግዚአብሔር ክብር የሚናገር ስለሆነ ሁሌም መጠንቀቅ አለበት፤ በእርግጥ የሰዎች መልካም ንግግርና ውዳሴ የነቢይነት ተግባሩ ላይ ተጽእኖ ሊያደርግበት ይችላል፡፡ ሰዎች ደግሞ ከጥንት ጀምሮ ለሐሰተኞች ነቢያት እንኳን ሲያመሰግኑና ሲያወድሱ በከንቱ ቃላትም ሲያሞካሹዋቸው እንደነበር ቃሉ ያስገነዝበናል(ሉቃ 6፡20-26)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ሐሰተኞች መምህራንና ሐሰተኞች ነቢያት በቀድሞ ዘመን እንደነበሩ፣ አሁንም እንዳሉና ወደፊትም እንደሚኖሩ ጥፋት የሚያስከትል ትምህርት ወደ ሕዝቡ ዘንድ እንደሚያስገቡና የዋጃቸውንም ጌታ እስከ መካድ እንደሚደርሱ አበክሮ ይገልጻል(2 ጴጥ 2፡1)። ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ በዓለም ላይ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ስለተነሡ መንፈሶች የእግዚአብሔር መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መርምሮ ማየት እንደሚገባ ከማስገንዘቡም በላይ መንፈሶች ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆናቸው ለይቶ ለማወቅ የሚረዳ ምክር ያበረክታል(1 ዮሐ 4፡1-6)።

እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አገላለጽ ሐሰተኞች ነቢያት የዓለም እንደሆኑ፣ የሚናገሩትም የዓለም ነገር እንደሆነና ዓለምም እነርሱን እንደሚሰማቸው ይገልጻል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እውነተኞቹ ነቢያት እግዚአብሔር የሚያውቅ ሁሉ እንደሚሰማቸውና የእግዚአብሔር ያልሆነ ግን እንደማይሰማቸው አበክሮ ይናገራል(1 ዮሐ 4፡5-6)፡፡

>> የነቢያት መጽሐፍት እንዴትና በስንት ይከፈላሉ?

በአይሁዳውያን ዘንድ እንዲሁም በአብዛኞቹ የክርስትና ሊቃውንት ጥናትና እምነት መሠረት ነቢያት በአጠቃለይ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይመደባሉ፡፡ እነዚህም ቀደምት ነቢያትና የኋለኞቹ ነቢያት ናቸው፡፡ ቀደምት የሚባሉትም መጽሐፈ ኢያሱ፣ መጽሐፈ መሳፍንት፣ መጽሐፈ ሳሙኤልና መጽሐፈ ነገሥትን ያካተተው ክፍል ሲሆን የኋለኞቹ ነቢያት በመባል የሚታወቁት ደግሞ ከነቢዩ ኢሳይያስ ጀምሮ እስከ ነቢዩ ሚልክያስ ያሉት ዐሥራ ስድስቱ የነቢያት መጻሕፍት ናቸው፡፡ ቀደምት ነቢያት የሚተርኩት ታሪክ ኢያሱ የከነዓን ምድር ከወረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስራኤላውያን በተስፋዪቱ ምድር ውስጥ እንደ ሕዝብ ተደራጅተው ኑሮአቸውን ያጠናከሩበት ሁኔታ ያትታል፡፡

የኋለኞቹ ነቢያት የሚባሉት ግን እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ወጥ ሥራ ወይም መጽሐፍት በስማቸው የተሰየመና በተለያየ ክፍለ ዘመን በተለያዩ ነቢያቶች የተነገሩ የትንቢት ቃልና የነቢያቶች አስተምህሮ ያካተተ ነው፡፡ እነዚህ ዐሥራ ስድስቱ ነቢያት በራሳቸው ስም የተሰየሙ መጻሕፍት አሉዋቸው፡፡

>> ጠቅለል ባለ መልኩ የነቢያት ትምህርት ዋና ትኩረት የሚያደርገው ምን ላይ ነው?

የነቢያት ትምህርት በአንድ ነገር ብቻ ላይ ያተኮረ ሳይሆን ሰፋ ያለ ይዘት ያለው ነው። ትኩረታቸው በእምነት ዙርያ የሚከናወኑ ነገሮች ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ጠቅላላ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ሕይወት የሚዳስስ ነው። በአጠቃላይ የነቢያት ዋና ትምህርት ወይም መልእክት በሦስት ነገሮች የሚያተኩር ነው፡፡

1. ሕዝቡንሥነምግባርንማስተማር፦ ነቢያት የትምህርታቸው ዋናው ትኩረት ሰው እንዴት ፈሪሃ እግዚአብሔር አድሮበት ትእዛዛቱን ጠብቆ መኖር እንዳለበትና ትእዛዛቶቹም በዕለታዊ ኑሮው እንዴት እየተገበረ መጓዝ እንዳለበት ሥነ ምግባርን በማስተማር እውነተኛውን የጽድቅ መንገድ ማሳየት ነው። በዚህም ሂደት የትምህርታቸው ዋና መሠረትና ማእከል አድርገው የሚንቀሳቀሱት በአንዱ እግዚአብሔር ነው።

2. ትንቢትመናገር፦ ትንቢት ሰፋ ያለ ትርጓሜ ቢኖረውም እዚህ ላይ ግን የሚያተኩረው ነቢያት በመልእክቶቻቸው የመዳን ቀን ቀርባለች ንስሓ ግቡ፤ የአዳኙም መምጫ ጊዜ ቀርቧል፤ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ በማለት ወደፊት ሊከናወኑ ስለሚችሉ ነገሮች የሚያስተምሩትን ነው። ይህ ገና ያልተፈጸመውንና እንደየ ወቅቱ ሁኔታ የተሰጠውን የእግዚአብሔር ቃል የሚያጠቃልል ሆኖ ዋና ትኩረቱ ግን የንስሓ ጥሪ ላይ ነው። ነቢያቶች ሕዝቡ ከተሳሳተው ጎዳና ተመልሶ በጽድቅ መንገድ እንዲጓዝ በማለት በትንቢታቸው "የእግዚአብሔር ቁጣ በላያችሁ ላይ ይመጣል"፤ "ተጸጸቱ"፤ "ንስሓ ግቡ" በማለት የማስፈራርያ ወይም ደግሞ የማነቃቂያ ስብከት ይጠቀማሉ፡፡

3. የሚኖሩበትማኀበረሰብፖለቲካዊሕይወትነክስለሆኑነገሮች መናገር፦ ማኅበረሰቡ የሚመሩ ነገሥታት ፍትሕ ባጓደሉ ጊዜ ነቢያት ሳይፈሩ ፍትሕ እንዲጓደል ያደረጉትን ነገሥታቶች በመገሠጽ የተጓደለውን ፍትሕ እንዲስተካከል በጩኸት ይናገራሉ። ከዚህም በላይ ነቢያቶች ነገሥታቶች ሲመረጡ ምክር በመስጠትና በተለያዩ አገልግሎቶች በመሳተፍ የራሳቸው አስተዋጾ ያበረክታሉ(1 ሳሙ 8-12 )። ነቢያቶች አንድ የአገር መሪ ወይንም ንጉሥ ሲሳሳትም ይመክራሉ(2 ሳሙ 7)። ዋናው ነቢያት ከሚያስተምሩት ወይም ከሚናገሩት የትንቢት ቃል ውስጥ ትኩረት ሰጥተውት በተደጋጋሚ የሚናገሩበት ጉዳይ ስለ ፍትሕ ነው፡፡ ይህም ማለት በማኅበረሰቡ ውስጥ በጥቂት መሪዎች ወይም ባለጸጎች አማካኝነት ሊፈጠር የሚችል አድሎአዊ አሰራርና ኢፍትሐዊነትን አጥብቀው ይቃወማሉ፡፡

>> በስማቸው መጠሪያ መጽሐፍት ያላቸው ዐሥራ ስድስቱ ነቢያት በመባል የሚታወቁት እነማን ናቸው? ለምን ታላላቅና ታናናሽ ነቢያት በመባል ይጠራሉ?

ከመጻሕፍቶቻቸው ስፋት፣ ከሚያትቷቸው ነገሮች ጥልቀትና ብዛት እንዲሁም በነቢይነት ካገለገሉበት ረዥም ዓመታት መሠረት ባደረገ መልኩ ነቢያት ታላላቅና ታናናሽ በመባል በሁለት ምድብ ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም አራት ታላላቅና አሥራ ሁለት ታናናሽ ነቢያት ናቸው። ታላላቅ ነቢያት የሚባሉትም ኢሳይያስ፣ ኤርሚያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ሲሆኑ ታናናሽ ነቢያት በመባል የሚታወቁት ደግሞ ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ኢዩኤል፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ሚክያስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው።

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ፤ መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ፤ የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1. የነቢይ ማንነት በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ)ነቢይ የሚለው ቃል የወደፊቱን ነገር አስቀድሞ መናገር ወይም ማብሠር ወይም ማሳወቅ ከሚለው ትርጓሜ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለ)ነቢይ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተለያዩ መንገዶች ማለትም በራእይ፣ በሕልም፣ በመልአክት አማካኝነት የተቀበለውን መልእክት ለሰዎች የሚያደርስ ነው፡፡ ሐ)ነቢይ ስለሚኖርበት ማኅበረሰብ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችም ጭምር የሚናገር ነው። መ)ነቢይ የወደፊቱን ብቻ የሚናገር መልእክተኛ ነው፡፡ ሠ)ነቢይ በምድር ላይ እግዚአብሔርን ወክሎ በሰዎች መካከል የሚገኝና ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ወዳጅነት ያለው መልእክተኛ ነው፡፡

2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ የነቢይ መጠሪያ ስሞች እንዳሉ ይታወቃል፤ ከእነዚህ ስሞች መካከል በተለያዩ የነቢያት መጽሐፍት ውስጥ ከየትኞቹም የነቢያት መጠርያ ስሞች በላይ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው የትኛውን ነው?

ሀ) የእግዚአብሔር ሰው ለ) ባለ ራእይ ሐ) ነቢይ መ) የእግዚአብሔር አገልጋይ ሠ) ሁሉም፡፡

3. የተለያዩ የነቢይ መጠሪያ ስሞች ከነተግባራቸው ከላይ ተብራርቶአል፤ ከእነዚህ መጠሪያ ስሞች መካከል አንዱ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ልዩ የጸጋ ኃይል ታምራቶች የማድረግ ችሎታ ስላለውና ድንቃ ድንቅ የሆኑ ነገሮች ሲያከናውን ስለሚታይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ታላቅ ከበሬታ ያለው ብቻ ሳይሆን የሚፈራም ጭምር እንደሆነ ተገልጾአል፡፡ ይህ በየትኛው መጠሪያ ስም የሚታወቀው ወይም የተጠቀሰው ነው?

ሀ) የእግዚአብሔር ሰው ለ) ባለ ራእይ ሐ) ነቢይ መ) የእግዚአብሔር አገልጋይ ሠ) መልሱ አልተሰጠም፡፡

4. በነቢይነት ተሠማርተው የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝብ እንዲሁም የሕዝብን ጩኸት ወደ እግዚአብሔር በማድረስ የአገልግሎት ሂደት ውስጥ ስለሚሳተፉት ሰዎች ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው፡፡

ሀ) ሴቶችም ሆኑ ወንዶች እኩል በነቢይነት ተሠማርተው ማገልገል ይችላል፡፡ ለ)ነቢይነት በዘር ወይም በጎሳ ሲወርድ ሲዋረድ የሚመጣ የአገልግሎት ማዕረግ ነው፡፡ ሐ)እግዚአብሔርን ማድመጥ የሚችልና የእግዚአብሔርን ጥሪ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ወንድም ሆነ ሴት በነቢይነት መሠማራትና ማገልገል ይችላል፡፡ መ)በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የበሰሉ፣ ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር በሰላም የሚኖሩና ወቀሳ የሌለባቸው ወንዶችም ሆነ ሴቶች ለነቢይነት ከተጠሩ ማገልገል ይችላል፡፡ ሠ)በጥሩ ሥነ ምግባር የሚኖርና በጎ ፈቃድ ያለው ማንኛውም ሰው ለነቢይነት ሊጠራ ይችላል፡፡

5. እውነተኛና ሐሰተኛ ነቢያት በተመለከተ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው?

ሀ) እውነተኛ ነቢይ ያስተላለፈውን ወይም የተናገረውን የትንቢት ቃል ወይም የእግዚአብሔር ቃል ሁሉም ነቢዩ በሕይወት እያለ ተፈጻሚነት ማግኘት አለበት፡፡ ለ) ሐሰተኛ ነቢያት ስለ ራሳቸው የግል ጥቅም በማሰብ ነገሥታትንና ሕዝብን ለማስደሰት ከራሳቸው ፈጥረው ትንቢት ይናገራሉ፡፡ ሐ) እውነተኛ ነቢይ መንፈሳዊ ሕይወቱ እግዚአብሔርን የሚያስደስት፣ የማያመነዝር፣ ሐሰት የማይናገር፣ የማይሰክር፣ እግዚአብሔር የገለጠለትን ራእይ የሚያስተውልና ሰዎችን ለክፉ ሥራ የማያነሣሣ ነው፡፡ መ)መጥፎ ዛፍ መጥፎ ፍሬ እንደሚያፈራ ሁሉ ሐሰተኞች መምህራንም መልካም ፍሬ ስለማያፈሩ በሥራቸው ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ሠ)ነቢዩ የሚያስተምረው ትምህርት ሕዝቡን ወደተሳሳተ ጎዳና የሚመራ ከሆነ እውነተኛ ነቢይነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡

6. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሰተኞች መምህራን ብቻ ሳይሆን እኔ መሲሕ ነኝ በማለት ጭምር ለማስተማር የሚነሡና ታምራትንም ጭምር ማከናወን የሚችሉ ሐሰተኞች መምህራን እንደሚመጡ በግልጽ ተናግሯል(ማቴ 7፡ 15-23)፡፡ ዛሬም ቢሆን ሐሰተኞች ነቢያት በተለያየ ቦታ በተለያየ ጊዜያት ሲነሡ ይታያል፡፡ በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ሐሰተኛ ነቢያቶች እንዴት ለይተን ልናውቃቸው እንችላለን?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት