እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፲፱ - የጥበብ መጻሕፍት ጥናት (መኀልየ መኀልይ)

ክፍል ሁለት - ትምህርት ዐሥራ ዘጠኝ

የጥበብ መጽሐፍት ጥናት - መኅልየ መኅልየ

song-of-solomon1► መኀልየ መኀልየ በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ በማን የተጻፈ ነው? የመልእክቱ ይዘት ምን ይመስላል?

በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ መጽሐፍ መኀልየ መኀልየ ዘሰሎሞን በመባል ይጠራል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ "ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጠው የሰሎሞን መዝሙር" ማለት ነው፡፡ በአንዳንድ መጻሕፍት "የመዝሙሮች መዝሙር" በመባል ይጠራል፡፡ ስለዚህ መኀልየ መኀልየ ማለት "ከሙዝሙር ሁሉ የሚበልጥ መዝሙር" ማለት ነው፡፡ የጸሐፊው ማንንት በትክክል ባይታወቅም ብዙዎች ሰለሞን እንደሆነ መላ ይመታሉ፡፡ በእርግጥ በመጽሐፉ ውስጥ ሰለሞን ሰባት ጊዜ ያህል ስሙ ተጠቅሶአል፡፡ በተጨማሪም መጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ነገሮች ለምሳሌ አበባ ፣ ቅጠላ ቅጠል ፣ የዱር ዛፎች ፣ ተራራና ሸለቆ እንዲሁም የተጠቀሱ መንደሮች ሰለሞን ቀድሞ በጻፋቸው ጽሑፍ ውስጥ የሚንጸባረቁና ተመሳሳይነት ያላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሰለሞን በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ እያለ የጻፈው ሊሆን እንደሚችል ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ መጽሐፈ ምሳሌ በጎልማሳነቱ ጊዜ የጻፈው ሲሆን መጽሐፈ መክብብ(ሁሉም ከንቱ የሚለውን አሳብ የሚያንጸባርቀው) መጽሐፍ ደግሞ በሽምግልናው ጊዜ የጻፈው ሊሆን እንደሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት አክለው ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ ከክ.ል በፊት በ950 ዓ.ዓ አካባቢ የተጻፈ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ገጸ ባሕርያትም ሦስት ናቸው፡፡ እነዚህም ሦስት ዓይነት ሰዎች በተራ ይነጋገራሉ፡፡ ቈንጆዋ 17 ጊዜ ፣ ፍቅረኛዋ የሆነው ወንዱ 11 ጊዜ ፣ እነደዚሁም በመካከል የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት 4 ጊዜ በመቀባበል ተነጋግረዋል፡፡

► የመጽሐፉ ይዘት ምን ይመስላል?

ይዘቱ በምናይበት ጊዜ መጽሐፉ የፍቅር ቅኔዎች ቅንብር ነው፡፡ ከእነዚህም ቅኔዎች አብዛኛዎቹ የተጻፉት በመዝሙር መልክ ሲሆን ወንዱ ለሴቲቱ ፣ ሴቲቱም ለወንድየው ያቀረቡአቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የሁለት ፍቅረኞች ንግግር ነው፡፡ የፍቅረኞች ንግግር ግጥም ነው፡፡ አነጋገሩ ከተለመደው የአነጋገር ዘይቤ የተለየ ነው፡፡ ትርጓሜውም ብዙ ጊዜ ያስቸግራል፡፡ በሙሽራው ዓይን ሙሽራዪቱ በገጽዋ ነውር ፈጽሞ የሌለባት እጅግ በጣም ውብ ናት(መኀ 4፡ 1-15፤ 6፡ 4-10)፡፡ እንደዚሁም ሙሽራዪቱ ሙሽራውን ስትመለከት ፈጽሞ ያማረ ፣ እኩያ የሌለው ፣ ከእልፍ የተመረጠ ሆኖ ታገኘዋለች(መኀ 5፡ 9-16)፡፡ ይህም ሁሉ በፍቅረኞች አነጋገር በመነገሩ አንዳንድ ሰዎች ምሥጢሩን ባለማስተዋል ይነቅፉታል፤ ነገር ግን ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ብዙ መልእክቶች የያዘ ነው፡፡ ሁለቱ ፍቅረኞች የሚጠቀሙዋቸው ቃላትና በመካከላቸው ያለው የመፈላለግ ስሜት በብዙ መልኩ እየተተረጐመ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ይቀርባል፡፡ {jathumbnail off}

የመጽሐፉ ጸሐፊ ሰለሞን ከሆነ መጽሐፉ ውስጥ የተካተተው ታሪክ ከሰለሞን ሕይወት ጋር በተያያዘ መልኩ እንዴት ይተረጐማል?

እንደሚታወቀው ንጉሥ ሰለሞን ብዙ ባዕዳን ሴቶች አፈቀረ፤ የነገሥታት ልጆች የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት(1 ነገ 11፡ 3)፡፡ በወቅቱ ከንጉሥ ቤተሰብ ጋር ወዳጅነት መፍጠር በጣም ድንቅ ስለነበር ሰዎች ልጆቻቸው የነገሥታት ዘሮች እንዲያገቡላቸው ይመኙ ነበር፡፡ በመኀልየ መኀልየ የተጠቀሰችው ሙሽራ የሹኔም አገር ሰው እንደሆነች ተገልጿል(መኀ 6፡ 13)፡፡ ንጉሥ ሰለሞን ከዚህች ልጅ ጋር በፍቅር ይወድቃል፤ የልጅትዋም ቤተሰቦች ለንጉሥ ሰለሞን ይድርዋታል፡፡ ንጉሥ ሰለሞንም ወደ ቤተ መንግሥቱ ይወስዳታል፡፡ የተንደላቀቀ ኑሮ እንድትኖርም ያደርጋታል፡፡ ነገር ግን ይህች ወጣት ከሕፃንነትዋ ጀምራ የምታፈቅረው የመንደርዋ ልጅ ነበር፤ ይህ ልጅ እረኛ ነበር፤ በኑሮውም ብዙ የደላው አልነበረም፡፡ እረኛነቱንም ውዴ ሆይ ! እስቲ ንገረኝ፤ የበጎችህን መንጋ የምታሠማራው የት ነው? በቀትርስ ጊዜ ዕረፍት ያገኙ ዘንድ እንዲመሰጉ የምታደርገው የት ነው? አንተን በመፈለግ የጓደኞችህን መንጋ በመከተል የምቅበዘበዘው ለምንድን ነው? እያለች ትገልጻለች(መኀ 1፡ 7፤ 6፡ 2)፡፡ ይህች በቤተሰብዋ ተጽእኖ በግዴታ ለንጉሡ የተዳረችው የሹኔም ወጣት ከሕፃንነትዋ ጀምራ ስታፈቅረው የነበረውን እረኛ ወዳጅዋን ለማግኘት ትመኛለች፤ ትፈልጋለች፤ ቀንና ሌሊት እየባዘነች ፍለጋዋን ትቀጥላለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እረኛ ወዳጅዋ በበኩሉ እርስዋን በመፈለግ ይንከራተታል፡፡ በተቻለው ሁሉ ሊያገኛት ይሞክራል፤ ውበትዋን እያደነቀ ቀንና ሌሊት ሊያገኛት ይመኛል፡፡ በአጠቃላይ ታሪኩ ውስጥ ንጉሥ ሰለሞን ተሳታፊ ቢሆንም ዋናው የፍቅር ታሪክ የሚያተኩረው ግን በሁለት ፍቅረኞች መካከል ነው፡፡

የመኀልየ መኀልየ መልእክት እንዴት መረዳት ይቻላል? ከአነጋገሩ በስተጀርባ ምን ዓይነት ትርጓሜ ወይም ምሥጢር አለው?

የመኀልየ መኀልየ ትርጓሜ በተመለከተ በሊቃውንቶች ዘንድ ብዙ የተለያዩ አሳቦች ይንጸባረቃሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አይሁዶች በመኀልየ መኀልየ ውስጥ የተገለጹት ሁለቱ ፍቅረኞች "እግዚአብሔርና እስራኤል" ናቸው ይላሉ(ሕዝ 16 ፤ ሆሴዕ 1-3)፡፡ አንዳንድ ሊቃውንቶች ደግሞ "ሰሎሞንና እረኛን የወደደችው ከሹነም ሀገር የመጣችው ልጃገረድ ናቸው" ይላሉ ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሙሽሮቹ "ሰሎሞንና ንግሥተ ሳባ" ናቸው ይላሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ በእነዚህ ሁለት ሰዎች የተመሰሉት ጥበብና የጥበብ ፈላጊዎች ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ክርስቲያኖች ደግሞ ሙሽሮቹ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች ናቸው ይላሉ፡፡ ሁሉም ሊቃውንት የየራሳቸው ምክንያት በማቅረብ አስተያየታቸው ይሰጣሉ እንጂ በትክክል እነዚህን ሁለት ሰዎች የሚወክሉዋቸው ማንነት ግን ወስነው በእርግጠኛነት እገሊ ነው አይሉም፡፡ ከምክንያቶቹ መካከል የተወሰኑት እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡፡

1. እግዚአብሔርና እስራኤል፦ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር የእስራኤል ብቸኛው አምላክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔርን ትቶ ጣዖታትን ማምለክ እንደ አመንዝራነት ይቈጠር ነበር፡፡ በዚህም እግዚአብሔር አምላክ የእስራኤል አፍቃሪና ተንከባካቢ ወዳጅ እንደነበር ተገልጿል፡፡ በመካከላቸውም ብዙ ቃል ኪዳኖች አድርገዋል፤ አንዱ ለሌላው በታማኝነት ለመኖር ብዙ ጊዜ ቃል ተገባብተዋል፡፡ እግዚአብሔር በነቢዩ ሆሴዕ አማካይነት እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፤ እስራኤል ሆይ ! እኔ ሚስቴ አደርግሻለሁ፤ ቅንና ታማኝ እሆንልሻለሁ፤ የማያቋርጥ ፍቅርና ምሕረት አሳይሻለሁ፤ ለዘላለም የእኔ ሚስት እንድትሆኚ አደርግሻለሁ፡፡ ቃል ኪዳኔን በመጠበቅ ሚስቴ አደርግሻለሁ፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቂያለሽ(ሆሴ 2፡ 19-20)፡፡ እግዚአብሔር በድጋሚ ለነቢዩ ሆሴዕ እንዲህ አለው፤ ሂድ ከውሽማዋ ጋር በማመንዘር ላይ የምትገኘውን ያቺን የቀድሞ ሚስትህን እንደገና ፍቅር አሳያት፤ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ሌሎች አማልክት ዘወር ቢሉም የዘቢብ መሥዋዕት ለጣዖቶች ማቅረብ ቢፈልጉም እኔ አሁንም እንደምወዳቸው አንተም ውደዳት(ሆሴ 3፡ 1)፡፡ በብዙ ቦታ የእግዚአብሔርና የእስራኤል ወዳጅነት በባልና ሚስት ምሳሌነት ተገልጾ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚፈላለጉት ሁለቱ ፍቅረኞች የእግዚአብሔርና የእስራኤል ወዳጅነትና አንዱ ለሌላው ያለው ጽኑ ፍቅርና መፈላለግ እንደሚያመለክት ይታመናል፡፡

2. ሰለሞንና ንግሥተ ሳባ፦ ንጉሥ ሰለሞን በወቅቱ በነበረው ጥበብ ተደንቀው ብዙ ነገሥታት ከተለያየ የዓለማችን ክፍል እየሄዱ ይጐበኙት ነበር፡፡ የሚሄዱትም የንጉሥ ሰለሞን ጥበብ የተሞላበት ንግግር ለማድመጥና በተለያየ ጉዳይ ሊያማክሩት ነበር፡፡ ንግሥተ ሳባ ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ንግሥት ወይም ሌሎች እንደሚሉት የየመን ንግሥት የነበረችው የንጉሥ ሰለሞን አስደናቂ ጥበብ ለመስማትና አስቸጋሪ በሆኑ የእንቆቅልሽ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም ረጅም ጉዞ አደረገች(1 ነገ 10፤ 2 ዜና መዋዕል 9)፡፡ እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጠ፤ ንግሥት ሳባም ጥበብ የተሞላበትን የሰለሞን አነጋገር አደመጠች፤ እርሱ ያሰራውንም ቤተ መንግሥር አየች፤ በሰለሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውንም የምግብ ዓይነት ፣ የመኳንንቱ የመኖሪያ አካባቢዎች ፣ የቤተ መንግሥቱን ሠራተኞች የሥራ አደረጃጀት ፣ የደንብ ልብሳቸውንም ዓይነት አደነቀች፡፡ በዚህም ሁሉ የተሰማትን አድናቆት ከጠበቀችው በላይ ነበር( 2 ዜና መ 9፡ 3-4)፡፡ ንግሥተ ሳባ ያመጣችውን እጅግ በጣም ብዙ ስጦታ ለንጉሥ ሰለሞን አበረከተችለት፤ እርስዋ ያበረከተችለት የሽቶ ዓይነት ከዚያ በፊት ከቶ ታይቶ አይታወቅም(2 ዜና መ. 9፡ 9)፡፡ ይህ የንጉሥ ሰለሞንና የንግሥት ሳባ ግኑኝነት በኋላ ወደ ፍቅር ወዳጅነት ሊመራቸው እንደሚችል ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡ በእርግጥ ሙሽራው ስልሳ ነገሥታት ፣ ሰማንያ ቁባቶችና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቈነጃጅት አሉኝ፤ እኔ ግን የምወደው አንዲትዋን ብቻ ነው፤ ቈነጃጅትም እርስዋን እየተመለከቱ ያወድሱአታል፤ ነገሥታትና የንጉሥ ቁባቶች ያሞግሡአታል ይላል(መኀ 6፡ 9)፡፡ ንግሥት ሳባ ወደ አገርዋ ስትመለስ ሜኒልክ የተባለ ወንድ ልጅ እንደወለደች በኢትዮጵያ ትውፊት ይነገራል፡፡ ስለዚህ መኀልየ መኀልየ ውስጥ የተጠቀሱት እነርሱ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል መላ ምት አለ፡፡

3. ጥበብና የጥበብ ማደሪያ የሆኑ ሰዎች፦ ንጉሥ ሰለሞን ከምንም በላይ ጥበብ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ለመነ(1 ነገ 3)፡፡ ጥበብን ከምንም በላይ ወደድኳት፤ ከጤንነትና ከውበት ሁሉ በላይ ተመኘሁዋት ይላል መጸሐፈ ጥበብ(ጥበ 7፡ 10)፡፡ ጥበብ የዘላለማዊ ብርሃን ነጸብራቅ ነች(ጥበ 7፡ 24-26)፡፡ በማከልም ጥበብ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ፈለግኋት፤ በፍቅርዋም ተማርኩኝ ይላል(ጥበ 8፡ 2-3)፡፡ ጥበብ ከሁሉ በፊት ተፈጠረች፤ እግዚአብሔርም የሥራው ተቀዳሚ አደረጋት፤ ጥበብ ዓለምን በሙሉ ትገዛለች(ጥበ 8፡ 1)፤ ጥበብ ያለፈውን ታውቃለች ፤ የወደፊቱን ትተነብያለች((ጥበ 8፡ 8)፡፡ ስለዚህም ጥበብ በሁሉም ትፈለጋለች፤ በሁሉም ትወደዳለች፤ ሁሉም ይመኝዋታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጥበብ ራስዋ በሰዎች ዘንድ ማደሪያዋ ትፈልጋለች፤ ድምፅ አውጥታ ትጣራለች(ምሳ 8፡ 1-36)፡፡ ጥበብ ግብዣ አዘጋጀች፤ ፍሪዳ አረደች፤ የጣፈጠ የወይን ጠጅም ጠመቀች፤ ገበታም ዘርግታ ማእድ ሠራች፡፡ ገረዶችዋም በከፍተኛ ቦታ ላይ ቆመው ወደ ግብዣው እንዲጣሩ አደረገች(ምሳ 9፡ 1-6)፡፡ በአንድ በኩል ሰዎች ጥበብን ይመኙዋታል፤ ይዘፍኑላታል፤ ያወድሱዋታል፤ የራሳቸው ሊያደርጉዋትም የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጥበብ ራስዋ በሰው ተመስላ ወደ ከተማ ወጥታ ሰዎችን ትጠራለች፤ ማደሪያዋ በሰዎች መካከል ትፈልጋለች፤ ጥበብ የሚፈልጉትንም ታደንቃለች፡፡ ስለዚህ በመኀልየ መኀልየ የተገለጹት ሁለቱ ፍቅረኞች ጥበብና ፈላጊዎችዋ ሊሆኑ ይችላል በማለት ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡

4. ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያን፦ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ወደዳት፤ ራሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ ሰጠ(ኤፌ 5፡ 22-25)፡፡ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ይንከባከባታል፤ ስለ እርስዋም ያለው ፍቅር ጽኑና የማይናወጥ ነው(ኤፌ 5፡ 29)፡፡ ይህም ማለት ወንድዮው ሴትዮዋን እንደ ወደዳት ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ወደደ፤ ይወዳታልም፤ ሴትዮዋም ወንድዮውን እንደ ወደደችው ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን መውደድ ይገባታል እንደ ማለት ነው(ኤፌ 5፡ 25-33፤ ራእ 19፡ 7፤ ራእ 21፡ 2 እና 9)፡፡ በመኀልየ መኀልየ ውስጥ የተጠቀሱት ሁለት ፍቅረኞች ፍቅራቸው እጅግ በጣም ጥልቅና የጸና ነው፡፡ ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያን አይለያዩም፤ አንድ ናቸው፡፡ ልክ ሙሽራዪቱ እንደተሰደበችና እንደተደበደበች ሁሉ ቤተ ክርስቲያን በምታደርገው ጉዞ ፈተና ይደርስባታል፤ ብዙ አገልጋዮችዋም በሰማዕትነት ያልፋሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ፍቅር በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ወዳጅነት ያመለክታል፤ አንዱ ለሌላው ያለው ጽኑ ፍቅር ይገልጻል በማለት ክርስቲያን የሆኑ ሊቃውንት ያስገነዝባሉ፡፡

► በመኀልየ መኀልየ ውስጥ ያሉት ሁለቱ ፍቅረኞች የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ያመለክታል ካልን በመጽሐፉ የተዘረዘሩት አንዳንድ ነገሮች እንዴት መረዳት ይቻላል? ለምሳሌ "እንብርትሽ በወይን ጠጅ የተሞላ ብርሌ ይመስላል"(መኀ 7፡ 2) የሚሉትንና ተመሳሳይነት ያላቸው አገላለጾች እንዴት መረዳት ይቻላል?

የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ተምሳሌነት በመጥቀስ መኀልየ መኀልየን የሚያብራሩ ሊቃውንት ለእያንዳንዱ ነገር የራሱ የሆነ ትንታኔ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ በዚህም መሠረት "እንብርትሽ" ሲል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው መንበረ ታቦት ነው፤ ምክንያቱም እምብርት ከሰውነት ክፍሎች ውስጥ የሆድ ማእከል የሆነ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ "ወይን ጠጅ የተሞላ ብርሌ" በሚልበት ጊዜ የክርስቶስ ደም በጽዋ ተሞልቶ በመንበረ ታቦት ላይ መቀመጡን ለማመልከት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ በመኀልየ መኀልየ የተገለጸው እያንዳንዱ ነገር ከምልክትነቱ በስተጀርባ ሌላ ትርጉም እንዳለው ያስገነዝባሉ፡፡ ሌላ አንድ ምሳሌ ለመጨመር "ውዴ በጡቶቼ መካከል ሲያርፍ መዓዛው እንደተቋጠረ ከርቤ ነው" የሚለውን እንዴት እንደሚተረጉሙት እንመልከት(መኀ 1፡ 13)፡፡ መዓዛው ያማረው የተቋጠረ ከርቤ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ሁለት ጡቶች የሚገኙበት ደረት የሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ሁለቱ ጡቶች ደግሞ ብሉይና አዲስ ኪዳን ናቸው፤ ብሉይና አዲስ ኪዳን የቤተ ክርስቲያን ሁለት እጆች "ጡቶች" ናቸው፤ ብሉይ ኪዳን አስቀድሞ ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ይናገራል፤ አዲስ ኪዳን ስለ ክርስቶስ በግልጽ ይናገራል በማለት ይተነትኑታል፡፡ በተጨማሪም ሙሽራው "ውዴ ሆይ ! ከከንፈሮችሽ የማር ወለላ ይፈስሳል፤ ከአንደበትሽም ማርና ወተት ይፈልቃል" ይላል(መኀ 4፡ 11)፡፡ ይህ ከሙሽራዪቱ ከንፈር የሚፈልቀው ማርና ወተት "የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት" እንደሆነ ሊቃውንት እየተነተኑ ያስገነዝባሉ፡፡ ማርና ወተት እጅግ ከሰው አፍ ሊፈልቅ በፍጹም አይችልም፤ አነጋገሩ ምሳሌያዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ምሳሌ ቤተ ክርስቲያን የምታድላቸው ምሥጢራትና የምታስተምረው ትምህርት የሚመለከት ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መንፈሳዊ ሕይወትን መመገብና የሰውን ሕይወት ማደስ የሚችሉ ናቸው፡፡

► በመኀልየ መኀልየ የተገለጸው ዋናው ትልቁ ነገር ወይም ከመጽሐፉ መማር የሚቻለው ትልቁ ትምህርት ፍቅር ነው፡፡ ይህ ፍቅር ጽኑ ፣ ንጹሕ የሆነና ታማኝ ፍቅር ነው፡፡ ይህ ፍቅር በሙሽራውና በሙሽራይቱ አማካይነት በተለያየ መልኩ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ከተገለጸባቸው መንገዶች መካከል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው ይጠቀሳሉ፡፡

1. ፍለጋ፦ ሙሽሮቹ ቀንና ሌሊት ይፈላለጋሉ፡፡ አንዱ ሌላውን አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ ሌሊት ከቤታቸው ወጥተው ምንም ሳይፈሩ አንዱ ሌላውን ይፈልጋል(መኀ 3፡ 1-2)፡፡ ሌሊት ከተማ ውስጥ በፍለጋ ላይ የነበረችው ሙሽራዪቱ በከተማው ጠባቂዎች ድብደባ ደርሶባታል፤ ልብሶችዋ ገፍፈው ወስደውባታል(መኀ 7፡ 1)፡፡ አንዱ ሌላውን በመፈለግ ላይ እያለ በዝናብ ይረሰርሳል(መኀ 5፡ 2)፡፡ የአንበሳና የነብር መኖርያ የሆኑት ተራራዎች እንኳ አይበግራቸውም(መኀ 4፡ 8)፡፡ ይህ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ፍለጋ በብዙ መልኩ ይተረጐማል፡፡

ሰው እግዚአብሔርን አጥብቆ መፈለግ አለበት፦ በመጀመሪያ ሰው እግዚአብሔር ለመፈለግ ያለው ፍለላጎት ሁሌም የተነቃቃና ከልብ የመነጨ መሆን አለበት፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማግኘት ወይም ከእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ጸጋ ለመቀዳጀት የሚያደርጉት ፍለጋ ውጤት እስኪያስገኝ ድረስ ሳይሰለቹ ቀንና ሌሊት በትጋት ማከናወን አለባቸው፡፡ ዘማሪው በመኝታዬም ሆኜ አስታውስሃለሁ፤ ሌሊቱንም የአንተን ነገር አስባለሁ እያለ እግዚአብሔር የመፈለግ ጥልቅ ስሜቱን ይገልጻል(መዝ 63፡ 6)፡፡ በተጨማሪም ዘማሪው ሁለንተናዬ አንተን ይመኛል፤ ውሃ በማጣት ደርቆ እንደተሰነጣጠቀ መሬት ነፍሴ አንተን ተጠማች በማለት እግዚአብሔርን መናፈቁን ይናገራል(መዝ 63፡ 1)፡፡

ሰው ወዳጁን በፍቅር መፈለግ አለበት፦ እኛ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ወዳጆቻችንን ለመፈለግ የዘገየን ነን፡፡ እንዲያውም እርሱ ወይም እርስዋ ፈልጋኝ ትምጣ እንጂ እኔ አልሄድም በማለት ራሳችንን እናዋድዳለን፡፡ ሰዎች እኔን ፈልገውኝ ይምጡ ብለን ስንቆይ ይልቅ ከወዳጆቻችን ጋር ተለያይተን እንቀራለን፡፡ አንዳንዴ ስልክ እንኳ ደውለን መጠየቁ ይከብደናል፤ እነርሱ ካልደወሉልኝ እኔ አልደውልም በማለት እልህ ውስጥ እንገባለን፡፡ እውነተኛ ፍቅር ግን ሰዎችን ፍለጋ ይሄዳል፤ እስኪፈልጉት ድረስ ቁጭ ብሎ አይቀመጥም፤ አይጠብቅም፡፡ ስለዚህ ዘመድ ወዳጆቻችን ለመፈለግ ጊዜ ወይም ሁኔታ ሊገድበን እንደማይገባ የሙሽራውና የሙሽሪት የመፈላለግ ሕይወት ያስተምረናል፡፡

2. ታማኝነት፦ ሙሽራው ለሙሽራዪቱ ታማኝነቱ ጽኑ ነው፤ እንዲሁም ሙሽራዪቱ ለሙሽራው ያላት ታማኝነት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ እርስዋ ሁሌም የምታስበው እርሱን ብቻ ነው(መኀ 3፡ 1፤ 5፡ 2)፤ በንግግርዋም እኔ የውዴ ነኝ፤ እርሱም የእኔ ነው እያለች ትናገራለች(መኀ መኀ 2፡ 16፤ 7፡ 10)፡፡ የሙሽራዪቱ ታማኝነት ወዳጆችዋ እስኪደነቁባት ድረስ ነበር፡፡ ወዳጆችዋም አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተዋብሽ ሆይ ! በውኑ የአንቺ ወዳጅ ከሌሎች የተለየ ነውን? ስለ እርሱ ይህን ያህል ዐደራ የምትዪን እርሱ ከሌሎች የሚለይበት ነገር ምንድን ነው? እያሉ ይደነቁባት ነበር(መኀ፡ 9)፡፡ ከሙሽራውና ከሙሽራዪቱ ሕይወት የምንማረው ለቤተሰባችን ፣ ለትዳር አጋራችን ፣ ለወዳጆቻችን ፣ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ፣ ለተሰጠን ኃላፊነታችን ፣ ለተሰለፍንበት ዓላማችንና ለኅሊናችን ያለን ታማኝነት እንድንመረምር ይጋብዘናል፡፡

3. ግልጽነት የተሞላበት የፍቅር ወዳጅነት፦ ሙሽራውና ሙሽራዪቱ እየተፈራረቁ ከሚናገሩት ነገር መረዳት እንደሚቻለው አንዱ ለሌላው ግልጽ መሆኑ ነው፡፡ ስሜቱን መሸፋፈን ወይም መደበቅ የለም፤ እንደሚዋደዱ እርስ በርሳቸው በንጹሕ ልቦና ይገላለጻሉ፡፡ ለወዳጆቻቸውም ቢሆን አንዱ ስለ ሌላው ያለውን ፍቅር ይናገራል(መኀ 5፡ 9)፡፡ ከእነርሱ ዘንድ ሀሜት ፣ መወቃቀስ ፣ መጨቃጨቅና አንዱ ሌላውን ማጥላላት የለም፡፡ እርስዋ በንጹሕ ልቦናና አንደበት እርሱን ታደንቃለች፤ እርሱም በተመሳሳይ መልኩ ያደንቃታል፡፡ ስለዚህ እኛ ሰዎች በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ከወዳጆቻችን ጋር በምናደርገው ግኑኝነት ውስጥ የሽንገላ ቃላት አስወግደን ፣ ግልጽነትን ተላብሰን በቅን ልቦና እየተመካከርንና እየተደጋገፍን እንድንጓዝ ያስተምሩናል፡፡ አንዳንዴ በግልጽ ለመናገር እንፈራ ይሆናል፤ ሰው የምናስቀይም መስሎንም እንጠነቀቅ ይሆናል፤ ግልጽ በመናገራችን ምክንያት ወዳጆቻችን የምናጣቸውም መስሎ ሊታየን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ግልጽነት የራሳችንም ሆነ የሌላውን ሕይወት ለመገንባትና ከሰዎች ጋር ጥሩ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት ፍቱን መፍትሔ ነው፡፡

► በመኀልየ መኀልየ ታሪክ ውስጥ ሙሽራዪቱ የፀሐይ ቃጠሎ መልክዋን እንዳጠቈረው ፣ የእናትዋ ልጆች የሆኑ ወንድሞችዋ እንደጠልዋትና የወይን ተክል ጠባቂ እንዳደርግዋት ትናገራለች፡፡ ሙሽራዪቱ ለምን በገዛ ወንድሞችዋ ተጠላች?

አስቀድሞ ከላይ እንደተገለጸው ይህች የሹኔም ወጣት ሴት በወቅቱ በነበረው ባህል መሠረት እርስዋ ሳትፈልግ ወላጆችዋ ለንጉሥ እንደሰጡና በግዴታ እንደተዳረች ይታመናል፡፡ እርስዋ ግን የንጉሥ ቤት የድሎት ኑሮ አልነበረም የምትፈልገው፤ የእርስዋ ልብ የነበረው ከሕፃንነትዋ ጀምራ የምትወደውን ፣ አብሮ አደግዋ ምስኪኑ እረኛ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሥ ጥላ በመጥፋት ከልብ የምታፈቅረውን እረኛ ወዳጅዋን ለማግኘት ብላ የንጉሡን ቤት ጥላ እንደጠፋችና ወደ ቤተሰቦችዋ ዘንድ እንደተመለሰች ይታመናል፡፡ ይህንን ድርጊትዋ ቤተሰቦችዋ የሚያሳዝንና የሚያስቈጣም ይሆናል፤ ምክንያቱም ከንጉሥ ጋር ተዛምደው ፣ ክብርና ጥቅማ ጥቅሞችን አግኝተው መኖር ይፈልጉ ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ድርጊትዋ የተበሳጩት ወንድሞችዋ በጣም ስለጠልዋት የወይን ተክል ጠባቂ አደረግዋት(መኀ 1 ፡ 6)፡፡ የወይን ተክል በወፎችና በተለያየ ምክንያት እንዳይጐዳ በፀሐይ ቁጭ ብላ ቀኑን ሙሉ መጠበቅ ነበረባት፤ መልክዋንም ሆነ ሰውነትዋ ለመንከባከብ ጊዜ አልነበራትም(መኀ 1፡ 6)፤ እንዲያውም ፀሐዩ ቀድሞ የነበረውን መልክዋ አጠቈረው(መኀ 1፡ 6)፡፡ ሙሽራው ግን የሙሽሪት መልክ መጥቈር ወይም መጐሳቈል ምንም አያሳስበውም፤ እንዲያውም ከቀድሞ ይልቅ ውብ እንደሆነች በተለያየ መልኩ ደጋግሞ ይገልጸዋል፤ እንዲያውም "ከሴቶች ሁሉ ያማርሽ ውብ ሆይ !" እያለ ይጠራታል(መኀ 1፡ 8)፡፡ በእርግጥ እርሱ የወደደው የእርስዋ ውጫዊ መልክ ወይም ውበት ሳይሆን እሷነትዋን ነው፤ ይህ ደግሞ በምንም መልኩ የሚቀየር አይደለም፤ ምንያቱም ጽኑ በሆነ ሁኔታ ልብ ለልብ ተዋሕደዋልና ሰዎች በመካከል ገብተው የሚያደርጉት ምንም ዓይነት መሰናክል የሚለያያቸው አይሆንም፡፡

►ሙሽራዪቱ የእውነተኛ ፍቅር ምንነት በድርጊትና በንግግር በተለያየ መልኩ ደጋግማ ገልጻለች፤ ይህንን ከገለጸችባቸው አነጋገሮችና ታላላቅ አባባሎች መካከል የትኞቹ ናቸው የአንባቢን ትኩረት የሚስቡ ሆነው የተገኙት?

ሙሽራዪቱም ሆነች ሙሽራው በተለያየ መልኩ ነድርጊትም ሆነ በንግግር መልክ ፍቅር ታማኝ ፣ ቅን ፣ በእውነተኛ መንፈስ የሚከናወን ፣ መስዋዕትነት የሚጠይቅና በምንም ዓይነት ፈተና ሊደናቀፍ የማይችል መሆኑን ተናግረዋል፤ አሳይተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሙሽራዪቱ የተናገረችው ትልቁ አባባል መጥቀሱ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም "ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናት፤ ቅንአትም እንደ መቃብር የከፋች ናት"(መኀ 8፡ 6)፡፡ ሌላው ደግሞ "የውሃ ብዛት የፍቅርን እሳት ሊያጠፋ አይችልም፤ ጐርፍም ጠራርጎ ሊወስዳት አይችልም፤ ሰው ባለው ሀብት ሁሉ ፍቅርን ለመግዛት ቢሞክር ፍቅር በገንዘብ ስለማትገኝ ሰዎች ይንቁታል" የሚሉት ይገኙበታል(መኀ 8፡ 7)፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ አስተባባሪ ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1. መኀልየ መኀልየ ማለት ምን ማለት ነው? የመጽሐፉ ጸሐፊስ ማን ነው?

ሀ)መኀልየ መኀልየ ማለት መዝሙር ማለት ሲሆን ጸሐፊው በትክክል ማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ለ) መኀልየ መኀልየ ማለት ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ መዝሙር ማለት ሲሆን ንጉሥ ሰለሞን በወጣትነቱ ጊዜ የጻፈው እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሐ) መኀልየ መኀልየ ማለት የፍቅር ቅኔ ማለት ሲሆን የጻፈውም ንጉሥ ሰለሞን ነው፡፡ መ) መኀልየ መኀልየ ማለት ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ መዝሙር ማለት ሲሆን ንጉሥ ሰለሞን በጎልማሳነቱ ጊዜ የጻፈው እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሠ) መኀልየ መኀልየ ማለት ሙሽሮች እየተቀባበሉ የሚዘፍኑት የሠርግ ዘፈን ነው፡፡

2. መኀልየ መኀልየ ውስጥ የሚገኙት ሙሽራውና ሙሽሪት በሊቃውንት ዘንድ በተለያየ መልኩ እየተመሰሉ ይገለጻሉ፡፡ የሙሽራውና ሙሽሪት ወዳጅነትና የእርስ በርስ ፍለጋ ምሳሌነት ከተነገረባቸው መንገዶች ውስጥ የማይካተተው የትኛውን ነው?

ሀ) የክርስቶስና የማርያም ወዳጅነትና አንድነት ለ) የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ፍቅርና አንድነት ሐ) የእግዚአብሔርና የእስራኤል ሕዝብ አንድነትና ወዳጅነት መ) ጥበብና ፈላጊዎችዋ ሠ) ንጉሥ ሰለሞንና ንግሥተ ሳባ፡፡

3. መኀልየ መኀልየ ውስጥ ከሚሰጡት ዋና ዋና ትምህርቶች ውስጥ "ፍቅር" በብዙ መልኩ ትልቁን ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡ ከሙሽራውና ከሙሽራዪቱ ንግግርና ሕይወት ብዙ መማር እንደምንችል ከላይ በትምህርቱ ውስጥ ተጠቅሶአል፡፡ ከላይ በትምህርቱ በተገለጸው መሠረት ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ከምንማራቸው ብዙ ነገሮች ውስጥ የማይመደበው የትኛውን ነው፡፡

ሀ)ሰዎች እግዚአብሔርን ለማግኘት ወይም ከእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ጸጋ ለመቀዳጀት በብርቱ መፈለግ አለባቸው፡፡ ለ) ሰው ዘመድ ወዳጁን ለመፈለግ ጊዜ ወይም ሁኔታ ሊገድበው አይገባም፡፡ ሐ) ሰው ለቤተሰቡ ፣ ለትዳር አጋሩ ፣ ለወዳጆቹ ፣ ለመንፈሳዊ ሕይወቱና ፣ ለተሰጠው ኃላፊነትና ለተሰለፈበት ዓላማና ለኅሊናው ታማኝ መሆን አለበት፡፡ መ) ሰው በማኅበራዊ ሕይወት ከወዳጅ ዘመዱ ጋር በሚያደርገው ግኑኝነት ውስጥ የሽንገላ ቃላት አስወግዶ ፣ ግልጽነትን ተላብሶ በቅን ልቦና እየተመካከረና እየተደጋገፈ መጓዝ አለበት፡፡ ሠ) መልሱ የለም፡፡

4. ከሚከተሉት ውስጥ ሙሽራውን በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው? ይህንን ለመመለስ መኀልየ መኀልየ ከምዕራፍ 1 እስከ 8 ያለውን በአስተውሎ ማንበብ ያስፈልጋል፤ ይህ ንባብ ጥያቄ ቁጥር 5 ለመመለስም ይረዳል)፡፡

ሀ) የሙሽራው ዐይኖቹ በወንዝ አጠገብ እንደሚታዩና በወተት የታጠቡ እንደሚመስሉ ርግቦች ያምራሉ፡፡ ለ) ሙሽራው ዋልያ ወይም የአጋዘን ግልገል ይመስላል፡፡ ሐ) ሙሽራው አፉ እንደ ማር የጣፈጠ ነው፤ ሁለንተናውም የደስ ደስ አለው፡፡ መ)ሙሽራው ከሌሎች ጎልማሶች ጋር ሲነጻጸር በዱር ዛፎች መካከል አምሮ እንደሚታይ የቀርከሃ ዛፍ ነው፡፡ ሠ)እናቱ አምጣ የወለደችው በፖም ዛፍ ሥር ነው፡፡

5. ከሚከተሉት ውስጥ ሙሽራዪቱን በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው? ይህንን ለመመለስ መኀልየ መኀልየ ከምዕራፍ 1 እስከ 8 ያለውን በአስተውሎ ማንበብ ያስፈልጋል፤ ይህ ንባብ ጥያቄ ቁጥር 4 ለመመለስም ይረዳል)፡፡

ሀ) ሙሽራዪቱ ጥቁር ነች፤ ነገር ግን ውብ ነች፡፡ ለ) በጥርሶችዋ መካከል ምንም መኻን ሳይኖርባቸው መንታ መንታ እንደሚወልዱና በውሃ እንደታጠቡ ነጫጭ የበጎች መንጋ ደስ ያሰኛሉ፡፡ ሐ) ሙሽሪትዋ ሁለንተናዋ ውብ ነው፤ ምንም አንኳ አንዳንድ እንከን ቢወጣላትም፡፡ መ) ቁመናዋ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፡፡ ሠ) በሴቶች መካከል ስትታይ በእሾኽ በካከል እንደሚታይ ውብ አበባ ናት፡፡

6. በተለያየ ባህል ውስጥ ወላጆች የልጆቻቸውን ስሜት ሳይጠብቁ ፣ ፍላጎታቸውን ሳይጠይቁ ፣ የዕድሜ ደረጃቸውን ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡና ወደፊት ደስተኛ የሚሆኑበት ሕይወት መሆን አለመሆኑን በደንብ ሳያጤኑ ልጆቻቸውን ሲድሩ ይስተዋላል፡፡ ወላጆች ይህንን የሚያደርጉት ብዙ ጊዜ የሌላውን ወገን ሀብት ፣ ዝምድና ወይም ዝናና ክብር በማየትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ለራሳቸውና ለልጆቻቸው እንዲያገኙ በማሰብ ነው፡፡ ልጆችም በባህል ተይዘው ፣ የወላጆች ፍራቻና አክብሮት አድሮባቸው የወላጆቻቸውን ውሳኔ ሲቀበሉ ይታያል፡፡ የልጆች ፍላጎትና ምኞት ሳይጠበቅ ፣ ከልጆች ጋር ስምምነት ሳይደረግ እንዲያው ሀብት ፣ ዝናና ዝምድና በማየት የሚደረገው የጋብቻ ሕይወት ሲታይ ጋብቻው ዕድሜ ሊኖረው ይችላልን? ተጋቢዎቹስ ደስተኛ ሆነው ይኖራሉ ብለው ያምናሉን? በተጋዎቹ ሕይወትና በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳትና ችግር በዝርዝር ግለጽ⁄ግለጪ፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት