እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ - ትምህርት አንድ

Bible scrollበዚህ ክፍል ውስጥ በቀጣይነት የሚቀርቡት መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ከእምድብር አገረ ስብከት ካህናት ሲሆን ዋና አዘጋጅ አባ ምሥራቅ ጥዩ፣ ምክትል አዘጋጅና አስተባባሪ ካህን ደግሞ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ ናቸው። ሐዋሪያዊ አገልግሎታቸውን እግዚአብሔር ይባርክ ዘንድ በጸሎታችን እንደግፋቸው እያልን ይህን ለዚህ ድረ ገጽ ስላበረከቱልን ደግሞ ምስጋናችን ብዙ ነው።የመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ - ትምህርት አንድ

► መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ምን ማለት ነው? የቃሉስ አመጣጥ ከወዴትና ምንስ ያመለክታል? 

መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ እንደሚያመለክተው መጽሐፍ እና ቅዱስ የሚሉ የሁለት ቃላት ጥምረት ነው ፡፡ በግሪክ ቋንቋ ቢብሎስ (byblos) ከደንገል በተሠራ ወረቀት ወይም በብራና ከተጻፈ በኋላ በሁለት በትሮች የሚጠቀለል መጽሐፍ ያመለክታል ፡፡ ቢብሎስ በእንግሊዘኛው ባይብል ተብሎ ሲተረጎም በአማርኛው ደግሞ መጽሐፍ በሚለው ቃል ተተረጐመ ፡፡ የግሪኩ ቃል ቢብሎስ (byblos) እራሱ ቢብሎስ (byblos) ከተባለ ከተማ ስም የተገኘ ነው ፤ እርሱም ከኒቂያ ወደቦች መካከል በቤይሩት  25 ማይል ያህል ርቆ የሚገኝ አገር ነው ፡፡ ለመጽሐፍ ያገለግል ዘንድ ፓፒረስ (ደንገል) የተባለውን ተክል እንደ ወረቀት አድርገው ይሠሩበት የነበረ ቦታ ነው ፡፡ 

ሁለተኛው ተጠማሪ ቃል “ቅዱስ” የሚለው ሲሆን ትርጓሜውም የተለየ ማለት ነው ፡፡ ሰው ወይም ማንኛውም ነገር ለእግዚአብሔር አገልግሎት ሲለይ ቅዱስ ይባላል ፡፡ ሰዎች (ዘጸ 28, 41) ፣ እንስሳት (ዘጸ13, 2) ፣ ቦታዎች (ዘጸ 3, 5) ቀኖች (ዘፍ 2, 3) ፣ ማናቸውም ነገር ቅዱስ ሊባል ይችላል (ኢያሱ 6, 19) ፡፡  የመጽሐፍ ቅዱስ ጥምረት ወደሆነው “ቅዱስ” ወደሚለው ቃል ስንመጣ ደግሞ ይህ መጽሐፍ እንደማንኛውም ተራ መጽሐፍ የሚታይ ሳይሆን የተቀደሰና የተለየ መሆኑን ከማሳየቱም አልፎ የጻፉት ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተውና ተመርተው እንደነበር ያስገነዝባል ፡፡ በእርግጥም የጻፉት ሰዎች ከራሳቸው ልቦና ፈጥረው ወይም አንቅተው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነትና በእግዚአብሔር እየተመሩና እየታዘዙ የጻፉት ነው (ዮሐ 14, 26) ፡፡ 

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ህልውናውንና ፈቃዱን ረቂቅ ባሕሪውን በተወሰነ መልኩ የምንረዳበትንና ፈቃዱንም ምን እንደሆነ ማወቅ የምንችልበት በእግዚአብሔር በራሱ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ለሰው ልጆች የተሰጠ(የተገለጸ) ቅዱስ ቃል ነው ፡፡ 

ቅዱስ ዮሐንስ እንደሚለው “ከመጀመሪያው ስለነበረው ስለ ሕይወት ቃል እንጽፍላችኋለን ፤ ይህ የሕይወት ቃል የሰማነውና በዐይኖቻችን ያየነው የተመለከትነውና በእጆቻችን የዳሰስነው ነው ፡፡ ይህ ሕይወት ተገልጦአል ፤ እኛም አይተነዋል ፤ እንመሰክራለንም ፡፡ በአብ ዘንድ የነበረውንና ለእኛም የተገለጠውን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን ፡፡ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተም እንነግራችኋለን ፡፡ ኅብረታችንም ከአብና ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው ፡፡ ደስታችንም ሙሉ እንዲሆን ይህን እንጽፍላችኋለን” (1 ዮሐ 1, 1-4) ፡፡ 

በአጠቃለይ መጽሐፍ ቅዱስ “ዘላለማዊ ሕግ” ሲሆን ዓላማውም ሰዎችን ለሰማያዊ መንግሥት ማብቃት ነው ፡፡ ስለዚህ ከሌሎች የሳይንስ ፣ የልቦለድና የፍልስፍና መጽሐፍት ፈጽሞ ይለያል ፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት ከመጻፉ አልፎ የሚያነቡትና የሚሰሙትን የሚመክር ፣ የሚገስጽ ፣ የሚያረጋጋና ወደ ደኅንነት ሊያደርስ የሚችል ጥበብ ያለው በመሆኑ ነው (2 ጢሞ 3, 14-17 ፣ ሐዋ 13, 16) ፡፡ ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ጣፋጭ የሆነ የሚበላ ሰማያዊ ስንቅ (ሕዝ 3, 1-3) ፣ ብርሃን ሆኖ የሚመራ (መዝ 119, ቁ. 105) ፣ አጽናኝና መካሪ መሆኑን በተለያዩ ቦታዎች ተገልጾ ይገኛል ፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የተገኘና እርሱ በመረጣቸው ቅዱሳን ሰዎች በራሱ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ከሰው ልጅም ጋር ቃል ኪዳን ያጸናበት ቅዱስ ቃል ነው ፡፡ 

በጥንት ዘመን ግን (እስከ 100 ዓ. ም ድረስ) የቅጠል ዓይነት መጽሐፍት (አሁን ያለው ዓይነት) ስላልነበር መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ቃል “ጥቅልል” በሚል ስም ይታወቅ ነበር ፡፡ የጥቅልል ርዝመት ዐሥር ሜትር ሊደርስ ይችል ነበር፡፡ ጽሕፈቱም በዐምዶች ላይ ነበር (ኢሳ 34, 4 ፣ ኤር 36, 2 እና 20-23 ፣ ሕዝ 3, 1-3 ፣ ሉቃ 4, 17-19 ፤ 2ዮሐ 12 ፣ ራእ 5, 1 ፣ 2ጢሞ 5, 13)፡፡ ባጠቃለይ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ዘመን በወረቀት ወይም በብራና የተጻፈውን ሲያመለክት የጥቅልል መጽሐፍ እንጂ በቅጠል ላይ የተጻፈ መጽሐፍ አልነበረም ፡፡

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳት መጻሕፍት መዝገብ ነው ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ናቸው ፡፡ ብሉይ ኪዳን ከ1400 - 400 ከክ.ል.በ በልዩ ልዩ ቦታዎች አርባ በሚያህሉ ልዩ ልዩ ጸሐፊዎች እንደተጻፈ ይነገራል ፡፡ አዲስ ኪዳን ከ45-96 ዓ. ም በስምንት ሰዎች ተጻፈ ፡፡ 

► መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር በራሱ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው ተብሏል ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍ የእግዚአብሔር መንፈስ ለምን አስፈለገ ?

የእግዚአብሔር መንፈስ ካስፈለጉባቸው ጥቂት ምክንያቶች ውስጥ ለመጥቀስ ያህል ፦ 

 • የሰው ልጅ አስቦ ሊደርስባቸው የማይችላቸውን እጅግ በጣም ጥልቅና ረቂቅ  የሆኑ ነገሮችን የያዘ መጽሐፍ በመሆኑ
 • ያለ ስህተትና ምንም ዐይነት ልዩነት ሳያንጸባርቅ እንዲጻፍ (የዘር ፣ የቀለም ፣ የጎሳ ፣ የጾታ )
 • አንድ ዓይነት የሆነ የሃይማኖት የሥነ ምግባር ሥርዐት እንዲኖር ለማድረግ
 • እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች እንዲጻፉና የማይፈልጋቸው ጉዳዮች እንዳይጻፉ ለማድረግ ፤ ይህም ማለት በመንፈሱ በመመራት ትክክለኛውን ቃሉ መጻፍ እንዲቻል
 • የሰው እውቀትና ችሎታ እጅግ በጣም የተወሰነና የተገደበ ነው ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን ምስጢራዊ ፣ ከሰው አእምሮና ጠቅላላ ችሎታ በላይ ስለሆነ ይህንን ቃል ለመጻፍ የእግዚአብሔር መንፈስ ድጋፍ እጅግ በጣም ያስፈልግ ነበር ፡፡ 
 • ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር “ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካኝነት ምስጢሩን ገልጦልናል ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ዕቅድ እንኳ ሳይቀር ሁሉን ነገር ይመረምራል ፡፡ ስለ ሰው የሆነ እንደሆነ ከገዛ ራሱ መንፈስ በቀር በእርሱ ያለውን አሳብ የሚያውቅ ሌላ ማንም የለም ፤ እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ ማንም የለም” (1 ቆሮ 2, 10-11) ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የተናገረውን ተረድቶ ለመጻፍ የራሱ መንፈስ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ፡፡

► ቅዱሳት መጽሐፍት የጻፉት በምን ዓይነት መልኩ ነው ይህንን የእግዚአብሔር ቃል የተቀበሉት ? እንዴት ነው ይህ ቃል ወደ እነሱ ሊመጣና ሊጽፉት የቻሉት ? በምን ዐይነት መልክ ነው እግዚአብሔር ቃሉን ወደ እነሱ እንዲደርስ ያረገው?

እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ቃሉን ወደ ሚያደምጡት ቅዱሳኖች አስተላልፏል ፡፡ ቃሉ ለእነሱ ከመግለጹ በፊት ግን የእነሱ በጎ ፈቃደኝነት ይጠይቃል ፡፡ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ተገዶና ነጻነቱ ተነፍጎ አይደለም የሚጽፈው ፡፡ ጸሐፊው በበጎ ፈቃደኝነቱና በነጻነት ራሱን ያዘጋጃል ፤ ከዚያም እግዚአብሔር የገለጸለትን ቃል በራሱ ቋንቋ ፣ ባሕልና የአጻጻፍ ዘይቤ መሠረት ቃሉን ይጽፋል ፡፡ እግዚአብሔርም ቃሉን በሚከተሉት መንገዶች ለጸሐፊዎች ይገልጻል ፦

 • ቃል በቃል በማነጋገር ፦ ሙሴን አንዳነጋገረው እግዚአብሔር ቃሉን በንግግር መልክ ይገልጻል ፡፡ ለምሳሌ “በድንገትም እግዚአብሔር ሙሴን ፣ አሮንና ሚርያምን እናንተ ሦስታችሁ እኔ ወደ ምመለክበት ድንኳን ኑ አላቸው ፤ እነርሱም ሄዱ ፤ እግዚአብሔርም በደመና ዐምድ ወርዶ በድንኳኑ ደጃፍ በመቆም አሮን ሚርያም ብሎ ጠራቸው ፤ ሁለቱም ወደ ፊት ቀረቡ ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለ እነሆ እኔ የምነግራችሁን አድምጡ…..እኔ ከእነርሱ ጋር ቃል በቃል በግልጥ እነጋገራለሁ” (ዘኁ 12, 4-8) ፡፡ 
 • በሕልም በመግለጽ (ዘፍ 37, 5)
 • በትንቢትና በራእይ ራሱን በመግለጥ ፦ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል “እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታሁ” (ዘኁ 12, 6) ፡፡ “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈሕ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ” (ዮሐ 1, 10-11) ፡፡ 
 • ያዩትንና የሰሙትን ልብ ብለው አስተውለው ያንኑ እውነታ ብቻ እንዲጽፉ በማድረግ ፦ ቅዱስ ዮሐንስ እንደጻፈው “ገና የምነግራችሁ ብዙ ነገር አለኝ ፤ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል ፤ ምክንያቱም እርሱ የሚናገረው የሰማውን እንጂ የራሱን አይደለም ፡፡ እርሱ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ይነግራችኋል” (ዮሐ 16, 12) ፡፡  

► መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ዋና ዓላማው ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉባቸው ዓለማዎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል ፦

 • የእግዚአብሔርን ማንነት ለማወቅና ለመረዳት እንዲሁም እውነተኛና ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን ተገንዝበን እንድናመልከውና ፈቃዱን ፈጽመን በሕይወት እንድንኖር (1 ዮሐ 1, 1-4 ፣ ማቴ 28, 20 ፣ ሮሜ 15, 4) ፡፡
 • ሥጋን ለብሶ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ ጌ.ኢ.ክ እግዚአብሔር እንደሆነ አምነን በስሙም ዘላለማዊ ሕይወትን አንድናገኝ (ዮሐ 20, 30-31 ፣ 1 ዮሐ 5, 13) ፡፡
 • “እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚሰማና በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” (ዮሐ 5, 24) እንዳለው በእግዚአብሔርና በልጁ በጌ.ኢ.ክ አምነን የዘላለም ሕይወት እንድንወርስ ፡፡ 
 • የሰው ልጅ በጥሩ ሥነ ምግባር ማደግ ወይም መታነጽ እንዲችል የተጻፈ ነው ፡፡ የሰው ልጅ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ሥነ ምግባራት በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ተገልጸዋል (ዘጸ 20, 7-17 ፣ ማቴ 5, 21) ፡፡ ባጠቃላይ የሰዎች ሥነ ምግባር ጥሩ መሆን ብቻ ሳይሆን ከክፋት መራቅና ፈተናን ማለፍ የሚችለው በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጸው እግዚአብሔርን በማወቅና እርሱን በመፍራት ላይ ሲመሠረት ነው፡፡ 

► መጽሐፍ ቅዱስ የብዙ መጻሕፍት መዝገብ ወይም ስብስብ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን እንዴት አድርጋ ነው እነዚህ መጻሕፍት ሁሉ አግኝታ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ የሰበሰበቻቸው?

 • ከመጀመሪያ ጀምሮ ቤ∕ክ አይሁድ ያወቁአቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተቀበለች፡፡ ቀጥላም በሐዋርያት ወይም በሐዋርያት ሥልጣን የተጻፉትን መጻሕፍት ሰብስባ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀበለቻቸው ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እየጠቀሱ አስተማሩ ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ በ367 ዓ.ም በጻፈው በፋሲካ ዕለት ቃለ በረከት ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሃያ ሰባት ብቻ መሆናቸውን ተናግሯል ፡፡ እንደዚሁም በ397 ዓ.ም በሰሜን አፍሪካ በካርታጎ (በካርቴጅ በቱኒዚያ) የተደረገው ሲኖዶስ ሃያ ሰባቱን መጻሕፍት አጸደቀ፡፡
 • በሌላ መልኩ በዕብራይስጥ የተጻፉ ብዙ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች የነበሩ ቢሆንም የመጀመርያው ቅጂ በ200 ከክ.ል.በ ገደማ ተጻፈ ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት በጥንት ዘመን በጥቅልል እየተጻፉ በልዩ ልዩ ምኩራብና ቤ∕ክ ይሰበሰቡና ይነበቡ ነበር ፡፡ ቅደም ተከተላቸውም ልዩ ልዩ ነበር ፡፡ ለምሳሌ አትናቴዎስ ሰባቱን መልእክታት ከጳውሎስ መልእክታት አስቀድሟል ፡፡ የካርታጎ ሲኖዶስ ግን የመጻሕፍቱን ተራ እንደ አሁኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተራ አድርጎ አጽድቋል ፡፡ 

► የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ማለት ምን ማለት ነው? ቤ/ክ የቅዱሳት መጻሕፍት ብዛትና ይዘት ተቀብላ ከማጽደቋ ጋር ምን ግኑኝነት አለው ?

 • “ቀኖና” የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም መቃ ወይም መለኪያ ሸምበቆ ማለት ነው ፡፡ ቀኖና የሚለው ቃል በጥንት ዘመን የታሪክ ሰዎች ጥሩ ቁመና ላለው ሰው ወይም ቀጥ ላለ ነገር ይጠቀሙበት ነበር ፡፡ የቤ/ክ ቀኖና ሲባል የቤ/ክ ሕግ ወይም ትክክለኛ (ቀጥተኛ) እምነት ማለት ነው ፡፡
 • የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ሲባል ቤ/ክ የሃይማኖትን ትምህርት ለመግለጥና ለማስተማር በማለት የተለያዩ መስፈርቶች በመጠቀም ቅዱሳት መጽሐፍትን ይዘታቸው በደንብ አድርጋ አጥንታና መርምራ በጉባኤ (በሲኖዶስ) አቅርባ የምትወስንበት ሂደት ነው ፡፡ ይህም ማለት የመጻሕፍቶቹን ይዘት አብጠርጥራ ካየች በኋላ ቅዱሳት መጽሐፍትን በብዛታቸውና በአቀማመጣቸው ወስና የምታጸድቅበት ሂደት ማለት ነው ፡፡ ለምሳሌ የማቴዎስ ወንጌልን እንውሰድ ፤ ቤ/ክ ይህን መጽሐፍ አንብባ ይዘቱን በደንብ ከተረዳች በኋላ በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ አካተተችው ፤ የቶማስ ወንጌል የተባለውን ግን አላካተተችውም ምክንያቱም በቅዱሳት መጽሐፍት ቀኖና (ካኖን) ሕግ መሠረት ያላሟላቸው ነገሮች ስላሉ ነው ፡፡ ቤ/ክ የቅዱሳት መጽሐፍትን ቀኖና ተጠቅማ መወሰን የፈለገችበት ሌላው ምክንያት በሐዋርያቶችና በቅዱሳን ስም የተለያዩ የሐሰት መጻሕፍቶች እየተበራከቱ ስለመጡ እውነተኞቹ በሐዋርያትና በቅዱሳን አባቶች የተጻፉትን መጻሕፍቶች ለይቶ ለማስቀመጥ በማሰብ ነው ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ ከሞተ በኋላ አንዳንድ ሰዎች እሱ ያልጻፈውን እራሳቸው በመጻፍ ይህ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ነው እያሉ በመምጣታቸው ቤ/ክ ትክክለኞቹን የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቶች መለየትና በቀኖናዋ ማካተት ጀመረች ፡፡ 
 • ቀኖናዊ ሆነው የሚቆጠሩትን የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ለመወሰን የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶስ ተቀምጠው የየራሳቸው ውሳኔዎች ወስነዋል ፤ በዚህም ምክንያት በቁጥር ብዛቱ አንድ ወጥ የሆነ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መጽሐፍ እንዳይኖር አድርጓል ፡፡ በእርግጥ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የየራሳቸው መስፈርቶች በመጠቀም ስለወሰኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥር ላይ ልዩነት ሊፈጥር ቻለ ፡፡ ለምሳሌ ካቶሊካዊት ቤ/ክ 73 መጽሐፍት ስትቀበል ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ 81 እና የፕሮቴስታንት ደግሞ 66 በመሆን ለዩነት ፈጥሯል ፡፡       

► ከመቼ ጀምሮ ነው መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍና በቁጥር ተከፋፍሎ መነበብ የጀመረው ? 

 • መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የጻፉት ሰዎች በክፍል ፣ በምዕራፍና በቁጥር አልለያዩትም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፎች የተከፈለው በ1228 ዓ.ም. በእንግሊዝ ሀገር ሲሆን ምዕራፎቹ ደግሞ በቁጥር የተከፈሉት በ1543 ዓ.ም በፈረንሳይ ሀገር ነው ፡፡ አከፋፈሉ እስካሁን ድረስ ይሠራበታል ፡፡ 

► መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመርያ ጊዜ የተጻፈው በምን ቋንቋ ነው? አዲስ ኪዳንና ብሉይ ኪዳን በመባል የመከፈሉ ምክንያትስ ምንድን ነው? 

 • መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አካትቶ የያዘ ሲሆን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከክርስቶስ በፊት የተጻፉ ፣ እስራኤል የተቀበሉአቸው ፣ በክርስቶስም የጸደቁ ቅዱሳት መጻሕፍት ሲሆኑ የተጻፉትም በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው ፡፡ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈው ብሉይ ኪዳን ከጌታችን ልደት በፊት ወደ ግሪክ ቋንቋ ተተርጉሞ ነበር ፤ ትርጉሙም ሴፕቱአጂንት (የሰባ ሊቃናት ትርጉም) ተብሎ ይጠራል ፡፡ አልፎ አልፎ በጥቂቱም ቢሆን አራማይስጥ በውስጣቸው ያካተቱ እንደ ትንቢተ ዳንኤል ዐይነቶች ይገኛሉ ፡፡   
 • አዲስ ኪዳን ግን በብሉይ ኪዳን የተተነበየ (ኤር 31, 31-34) እና ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ ያቆመው ቃል ኪዳን ነው (ሉቃ 22, 19-20) ፡፡ በሐዋርያት ሥልጣን የተጻፉት ቅዱሳት መጻሕፍት አዲሱን ኪዳን ስለሚገልጡ አዲስ ኪዳን ተብለዋል ፡፡ አዲስ ኪዳን ብሉይ ኪዳንን ፍጹም አድርጎታል ፤ በአሮጌውም ፈንታ አዲሱ ተተክቷል (ዕብ 8, 13) ፡፡ የተጻፈውም በግሪክ (በጽርእ) ቋንቋ ነው ፡፡ በእርግጥ አዲስ ኪዳን በድንጋይ ላይ ሳይሆን በልብ ፣ በቀለም ሳይሆን በመንፈስ ተጻፈ ፤ የኩነኔ ሳይሆን የጽድቅ አገልግሎት አለው ፤ ለጊዜው ሳይሆን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል ፡፡ ስለዚህ ክብሩ ከፍ ያለ ነው (2ቆሮ 3, 4-18)፡፡  

► መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሀገራችን ቋንቋዎች (ግእዝና አማርኛ) መቼና በማን ተተረጎመ?

 • በኢትዮጵያ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጡ ተሰዓቱ ቅዱሳን (ዘጠኙ ቅዱሳን) ቅዱሳት መጻሕፍት ወደ ግእዝ እንዲተረጐሙ አደረጉ ፡፡ ከእነርሱ ዘመን ቀደም ብሎ አንዳንድ መጻሕፍት በእነ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ጥረት በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተተርጒመዋል ፡፡ በ1548-1549 አባ ተስፋጽዮን የተባሉ ከአንድ የመነኮሳት ቡድን ጋር በመሆን በቫቲካን ግቢ (ሮማ) ለመጀመርያ ጊዜ አዲስ ኪዳንን አሳተሙ (ለህትመት አበቁ) ፡፡ እነዚህ መነኮሳቶች የአህመድ ግራኝን ወረራ በመሸሽ በሮም ተጠልለው እንደነበር ይታወቃል ፡፡ 
 • መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ በነጠላ ትርጓሜ ወደ አማርኛ የተረጐመ አብርሃም (አባ ሮሜ) የሚባል መነኩሴ ነበር ፡፡ ይህም ትርጉም በመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በኩል በ1816 ዓ. ም አራቱ ወንጌላት ፣ በ1821 ዓ. ም አዲስ ኪዳን ፣ በ1832 ዓ. ም ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ ወጣ ፡፡  የዕብራይስጥንና የግሪክን ቋንቋ የሚያውቁ አንዳንድ የውጭ አገር ዜጎች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር ትርጒሙን ካሻሻሉት በኋላ በ1878 ዓ.ም እንደ ገና ታርሞ ታተመ ፤ ከዚያም ወዲህ በየጊዜው ታትሞ ወጥቷል ፡፡
 • ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ የቀድሞው ትርጒም እንዲታረም ስለታሰበ ብዙ ሊቃውንት ከደከሙበት በኋላ በ1953 ዓ.ም አዲሱ ትርጉም ታተመ ፡፡ ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኀበር ቀለል ባለ አማርኛ በ1980 ዓ. ም አዲስ ትርጒም አሳተመ ፡፡

 

የትምህርቱ ዋና አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

ምክትል አዘጋጅና አስተባባሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

ጸሐፊ ፦ ሲስተር አበበች ጃቤ

ጥያቄዎች

 1. ከሚከተሉት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍ የእግዚአብሔር መንፈስ ካስፈለጉባቸው ምክንያቶች ውስጥ የማይመደበው(የሌለው) የትኛው ነው? ሀ)ያለ ስህተትና ምንም ዐይነት ልዩነት ሳያንጸባርቅ እንዲጻፍ ለ)እግዚአብሔር የተናገረውን ተረድቶ ለመጻፍ ሐ) የእግዚአብሔር ቃል ምስጢራዊ ፣ ከሰው አእምሮና ጠቅላላ ችሎታ በላይ ስለሆነ መ) ሰው አመፀኛ ስለሆነ
 2. መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመርያ ጊዜ በምን ቋንቋ ተጻፈ? ሀ) ብሉይ ኪዳን በግሪክ አዲስ ኪዳን በአራማይስጥ ለ) ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ አዲስ ኪዳን በአራማይስጥ ሐ) ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ አዲስ ኪዳን በግሪክ መ) ብሉይ ኪዳ በግሪክ አዲስ ኪዳን በዕብራይስጥ
 3. ቤ/ክ የሃይማኖትን ትምህርት ለመግለጥና ለማስተማር በማለት የተለያዩ መስፈርቶች በመጠቀም ቅዱሳት መጽሐፍትን ይዘታቸው በደንብ አድርጋ አጥንታና መርምራ በጉባኤ (በሲኖዶስ) አቅርባ የምትወስንበት ሂደት ምን በመባል ይታወቃል ? 
 4. መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት የሚለይበት ዋናው ምክንያት ምንድን ነው ?
 5. እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ቃሉን ወደ ሚያደምጡት ቅዱሳኖች አስተላልፏል ፡፡ ቅዱሳኖችም ይህንን ቃል በጽሑፍ አስፍረውታል ፡፡ እግዚአብሔር ቃሉን ወደ ሚያደምጡት ቅዱሳኖች መልእክቱን ለማስተላለፍ ከተጠቀመባቸው መንገዶች ውስጥ ሕልምና ራእይ ይገኙበታል ፡፡ ለመሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አኳያ ሕልምና ራእይ ልዩነታቸው ምንድን ነው ? 
 6. ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው ውስጥ አለመተማመን ሲጠፋ ወደ መማማል ይደርሳሉ ፤ በአንዳንድ ቦታዎች በተለይም በፍርድ ቤቶች ውስጥ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ሲምሉ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ሲያስምሉ ይታያል ፡፡ ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ መማል ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ማስማል ምን ትርጉም አለው ? ለምንስ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ይምላሉ ?

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት