እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳፭ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ ዳንኤል)

ክፍል ሦስት (ትምህርት ሃያ አምስት) የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - ትንቢተ ዳንኤል

Daniel»»  ነቢዩ ዳንኤል ማን ነው ? የነቢይት ተግባሩን ያከናወነው መቼና የት ነው? ሦስቱ ወዳጆቹስ እነማን ናቸው?

ዳንኤል የሚለው ስም "ዳን" እና "ኤል" የሚሉት የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን ትርጓሜውም እግዚአብሔር ፈራጄ ወይም ዳኛዬ ነው ማለት ነው፡፡ ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ የአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ክፍል የነበሩና ወደ ባቢሎን በምርኮ እንደ ተወሰዱ መጽሐፉ ያትታል(ዳን 1)፡፡ ዳንኤል በባቢሎን በነበረበት ጊዜ ብልጣሶር የሚል ተጨማሪ ስም ነበረው፡፡ በባቢሎናውያን ቋንቋ ብልጣሶር ማለት "ሕይወቱን ጠብቀው" ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል በይሁዳ አገር ከመሳፍንት ወይም ከንጉሣዊ ቤተሰብ የተወለደ፣ የባቢሎንና የፋርስ ሥልጣኔ እጅግ በጣም ባየለበትና ዓለም በእነዚህ ሥልጣኔዎች በተወረረችበት ጊዜ የኖረ ሰው ነው፡፡ ዳንኤል በወቅቱ ከነበሩት ታላላቅ ነገሥታት ከሚባሉት ከእንደእነ ናቡከደነፆር፣ ከቂሮስና ከሜዶናዊው ዳርዮስ ጋር የሠራ ጥበበኛ አገልጋይ ነው፡፡ በተጨማሪም ዳንኤል ታማኝና ቅን አገልጋይ፣ እምነተ ጠንካራ፣ ነቢይነት ከአስተዳዳሪነት ጋር  የተካነ ወጣት ነበር(ዳን 1፡3)፡፡ ዳንኤል የከለዳውያን ቋንቋና ባህል ተምሮ በንጉሡ ቤት እንደተሾመ ከመጽሐፉ እንረዳለን(ዳን 1፡3-21)፡፡ ዳንኤል የሚለው ስም በነቢዩ ሕዝቅኤል ውስጥ ከኖኅና ከኢዮብ ጋር ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ ስለተጠቀሰ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ያነበቡ ዳንኤል ጻድቅ እንደነበር በቀላሉ ይገነዘባሉ(ሕዝ 14፡12-23)፡፡

የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕርይ የሆነው ዳንኤል ግን በ605 በምርኮ ወደ ባቢሎን የተወሰደ በመሆኑ የኖረው ከ620 ዓ.ዓ እስከ 539 ዓ.ዓ ድረስ እንደሆነና ባቢሎን ውስጥ ሞቶ እንደተቀበረ ይገመታል፡፡ ዳንኤል ባቢሎን ውስጥ በስደት በሚኖርበት ጊዜ አብረውት የተሰደዱ ሦስት ወዳጆች እንደነበሩት ይታወቃል፡፡ በስደት በነበሩበት ጊዜ የዳንኤል ሦስቱ ወዳጆችም በተመሳሳይ መልኩ ስማቸው ተቀየረ፡፡ በዚህም መሠረት ዳንኤል ብልጣሶር፣ ሐናንያ ሲድራቅ፣ ሚሳኤል ሚሳቅ፣ ዐዛርያን አብደናጎ ተብለው ተጠሩ(ዳን 1፡7)፡፡ አብደናጎ የሚለውን ስም ላይ የመጨረሻው ክፍል "ናጎ" ባቢሎናውያን ከሚያመልኩአቸው አማልክት ውስጥ የአንዱ ስም ሲሆን "ሚሳቅ" የሚለው ደግሞ ሌላ "ሚሳቅ" የሚባል የባቢሎናውያን አማልክት ስም መሆኑን ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ በባቢሎናውያን ንጉሥ ባለሟሎች አለቃ አማካይነት የተቀየሩት ስሞች ከባቢሎናውያን አማልክቶች ጋር የተቆራኘ ትርጓሜ ያላቸው ናቸው፡፡

»»  ትንቢተ ዳንኤል መቼና በማን ተጻፈ? የመጻፉ ይዘት ምን ይመስላል?

መጽሐፉ የሚሸፍነው ረዥም ታሪክ ወይም ብዙ ዘመናት ውስጥ የተከናወኑ ድርጊቶችና በተለያዩ ጊዜያት ስለተነሡት ኃያላን ነገሥታት ስለሆነ በአንድ ጊዜና በአንድ ሰው የተጻፈ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ መጽሐፉ በብዙ ሊቃውንቶች ዘንድ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው መቶኛ ክፍለ ከመን ሊጻፍ እንደሚችል ቢያምኑም ሌሎች ግን ይህንን በመቃወም ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተጽፏል እንደሚሉት ሊቃውንቶች አገላለጽ፤ ትንቢተ ዳንኤል የተጻፈው እንዲያውም አንጥዮኩስ ኤጲፋኑስ አራተኛው የተባለው መሪ የግሪክን ሥልጣኔ በአይሁዳውያን ዘንድ የማስፋፋት ዘመቻውን ባጠናከረበት ወቅት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ አንጥዮኩስ ኤጲፋኑስ አራተኛው ቤተ መቅደስን በማርከስና የአይሁድን ሃይማኖት በመቃወም ከፍተኛ ዘመቻ ያደረገው ከ168 እስከ 164 ዓ.ዓ ባለው ጊዜ እንደሆነ ከጽሑፉ ይዘትና ከታሪክ መዛግብት ያረጋግጣሉ፡፡

ትንቢተ ዳንኤል በዕብራይስጥና በአራማይስጥ ቋንቋዎች የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በዕብራይስጥ ይጀምርና በምዕራፍ 2፡4 ላይ ወደ አራማይስጥ ቋንቋ ይቀየራል፤ በድጋሚ በምዕራፍ 8፡1 ላይ ወደ ዕብራይስጥ ቋንቋ ተመልሶ እስከ መጨረሻው በዚሁ ቋንቋ ይደመድማል፡፡ በእርግጥ አራማይስጥ በስደት የቆዩበት ቦታ ቋንቋ መሆኑ ሲነገር ዕብራይስጥ ደግሞ የስደተኞቹ የእስራኤላውያን ቋንቋ ነበር፡፡ ጸሐፊው በዕብራይስጥ መጻፍ ከጀመረ በኋላ በስደት ጊዜ የተወለዱ ብዙ እስራኤላውያን ከዕብራይስጥ ይልቅ የተሰደዱበት ቦታ ቋንቋ የሆነውን አራማይስጥ መረዳታቸው በመገንዘቡ ምክንያት ወጣት ስደተኞችንም ለመርዳት በማሰብ ጭምር በአራማይስጥ መጻፍ ጀመረ የሚል መላ ምት በአንዳንድ ሊቃውንት ቀርቧል፡፡

የመጽሐፉ ይዘት፣ ያጻጻፉ ስልት መለያየት፣ የተጻፈበት ቋንቋ ከአንድ በላይ መሆን፣ ያካተታቸው ታሪኮች ይዘት፣ የሕልሞችና ራእዮች ሁኔታ እንዲሁም የተጠቀመው የዘመን አቆጣጠር ሲታይ በአንድ ጸሐፊና በአንድ ወቅት የተጻፈ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ ምናልባት የታሪኩ ዋናው ክፍል ቀድሞ ተጽፎ በኋላ ሌሎች የቀድሞውን ጽሑፍ በመከለስ አዳዲስ ነገሮችን አካተው በድጋሚ ጽፈውት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ የመጽሐፉ ይዘት በምናይበት ጊዜ ሕልምና ራእይ፣ በደግና በክፉ መካከል የሚደረጉ ትግሎች፣ ምሳሌያዊ ቁጥሮች፣ ስለ ዓለም መጨረሻ ክንውኖች፣ የፍርድ ሂደቶች ከታሪካዊ ክስተቶች ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ መጽሐፉ የጻፈው ወይንም የጻፉት ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ያወቁና ያገናዘቡ እንደሆኑ ጽሑፉ ውስጥ ከተካተቱት ከቀድሞ የነቢያቶች፣ የጥበብና የኦሪት መጻሕፍት ጥቅሶች መረዳት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ በመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ልብ ሰቃይ የሆኑ የፍርድ ሂደቶችና እምነትን በመፈታተን ወደ ክህደት ሊመሩ የሚችሉ ክንውኖች ቢኖሩም የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕርይ የሆኑት ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ ግን በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው የእምነታቸው ጽናት አሸናፊዎች ሆነው በመወጣት ነገሩን በድል ሲያጠናቅቁ ይታያል፡፡ የመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል ግን(ዳን 7-14) አብዛኛው ትኩረቱ ዳንኤል በሚያያቸው ራእዮችና መላእክቶች በሚሰጡት የራእዮቹ ትርጓሜ ላይ ነው፡፡

»»  ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ በስደት ወደ ባቢሎን ተማርከው እንደተወሰዱ ይታወቃል፡፡ በሰው አገር ውስጥ በስደት እየኖሩ እንዴት ታዋቂና የንጉሥ አገልጋይ ሊሆኑ ቻሉ?

በወቅቱ የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር አይሁዳውያን ብልኾችና ጠንካሮች እንደሆኑ ያውቅ ስለነበር በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚያገለግሉት አይሁዳውያን ተመርጠው እንዲዘጋጁ አዘዘ፡፡ በዚህም መሠረት ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ በባቢሎን ውስጥ እያሉ ከእስራኤል ምርኮኞች መካከል ተመርጠው ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ ፊት ቀርበው ሥራቸውን እንዲጀምሩ ተወሰነ(ዳን 1)፡፡ ዳንኤልም ደስ የሚያሰኘው የንጉሡን ምግብ በመመገብና የወይን ጠጁንም በመጠጣት ራሱን ላለማርከስ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ የአትክልት ምግብ ብቻ ይመገብ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ለዳንኤልና ለሦስቱ ወዳጆቹ በማናቸውም ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤል ግን በተጨማሪ ራእይንና ሕልምን የመተርጐም ችሎታ ነበረው፡፡ በናቡከደነፆር ፊት ቀርበው ማገልገል ሲጀምሩም በማናቸውም ጥበብና ማስተዋል ንጉሡ ለሚያቀርበው ጥያቄና እንቆቅልሽ ሁሉ ፈጥኖ መልስ በመስጠት ረገድ በግዛቱ ካሉት ጠንቋዮችና አስማተኞች መካከል እነርሱ ዐሥር ጊዜ ብልጫ ያላቸው ሆነው ተገኙ፡፡ በዚህ ሁኔታ መጽሐፉ ገና ከጅምሩ ዳንኤልን በድሎትና በሥልጣን የማይበገር ጥበበኛ፣ ታማኝና የወገኖቹን ባህልና ሥርዓት ጠባቂ አድርጎ ያቀረበዋል፡፡ ይህ መሆኑን ለቀጣዩ ክፍል እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥ በቀጣዩ ክፍል ይህንን ጥበቡና ታማኝነቱ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደረሱትና ዝናውን የበለጠ የገነነ እንደሚያረጉት ያስገነዝባል፡፡

ቀጥሎም ዳንኤል ለንጉሥ ናቡከደነፆር ሕልሙ ከነትርጓሜው ገለጠለት(ዳን 2)፡፡ ይህ ጥበብ የተሞላበት ድርጊቱ በንጉሡ ታላቅ የክብር ቦታ እንዲቀመጥ፣ ብዙ ስጦታዎች እንዲያገኝ፣ በባቢሎን ግዛቶችም ሁሉ ላይ የበላይ ገዥ እንዲሆንና በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ አለቃ እንዲሆን አደረገው፡፡  ከዚህ በኋላ ለዳንኤል ሦስቱ ወዳጆች የመጀመሪያው የመፈተኛ ጊዜ ይሆናል(ዳን 3)፡፡ በዚህ አስቸጋሪ የፈተና ጊዜ ሦስቱ የዳንኤል ጓደኞች ለወርቁ ምስል ባለመስገዳቸው ተከሰሱ፤ በሞት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፤ በመጨረሻ ግን በእምነታቸው ጽናት ምክንያት ታሪኩ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ከእሳት ውስጥ ወጥተው ተሾሙ፡፡ ዳንኤል ሁለተኛውን የናቡከደነፆር ሕልም እንደ ተረጐመ፤ ናቡከደነፆርም ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረበ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ እግዚአብሔር በሰጠው ብልኀት፣ ዕውቀትና፣ ጥበብ በመመራት ዳንኤል ንጉሥ ቤልሻጻር ያየውን ምሥጢራዊ ጽሑፍ ነገር ግን ማናቸውም ጠቢባን አማካሪዎቹና አስማተኞቹ ሁሉ ሊተረጉሙት ያልቻሉትን ለንጉሡ ገለጠ፡፡ በዚህም ምክንያት የክብር ምልክት የሆነውን የወርቅ ሐብል በአንገቱ እንዲያደርጉለትና በመንግሥቱም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕረግ እንዲይዝ በዐዋጅ ተነገረ(ዳን 5)፡፡ በዚህ ምክንያት ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ ባቢሎን(የዛሬዪቱ ኢራቅ) ውስጥ ትልቅ የክብር ቦታ ተቀዳጁ፡፡

»»  በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ በልዩ ትኩረት በተደጋጋሚ ከተገለጹት ዐቢይ መልእክቶች ውስጥ አንዱና ትልቁ ትምህርት "ታማኝነት" ነው፡፡ ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ በምን ዓይነት መልኩ ነው ታማኝነታቸው የመሰከሩት?

በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ታማኝነት የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ስለሆነ ይህንን ታማኝነት ግልጽ በሆነና ትምህርት ሰጭ በሆነ መልኩ ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ ዳኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ ለእግዚአብሔርና ላደጉበት አይሁዳዊ ባህልና ሥርዓት ፍጹም ታማኝ መሆናቸውን በተለያየ መልኩ ተገልጿል፡፡ ዳንኤልና ወዳጆቹ በንጉሡ ቤት በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ ምግብና ወይን ጠጅ እየተመገቡና እየጠጡ እንዲያገለግሉ ቢፈቀድላቸውም መቀበል አልፈለጉም፡፡ የንጉሡን ምግብ በመመገብና የወይን ጠጁንም በመጠጣት ራሳቸውን ላለማርከስና አትክልት ብቻ እየተመገቡና ውሃ እየጠጡ ለመቆየት መምረጣቸውን ነው(ዳን 1፡8)፡፡ በእርግጥ በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ 11 ላይ እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን ለምግብነት መዋል ስለሚገባቸውና ስለሌለባቸው ወይም ስለ ረከሱ እንስሳትና አዕዋፋት በተመለከተ የአመጋገብ ሥርዓት ሲሰጥ ይታያል፡፡ ባቢሎናውያን ምንአልባት ከእነዚህ ከተከለከሉት እንስሳትና አዕዋፋት መካከል ውስጥ ይመገቡ ነበር፡፡ ዳንኤልና ወዳጆቹ ግን ለአይሁዳዊነት ባህልና ሥርዓት እንዲሁም ለእግዚአብሔር ሕግ ታማኝነታቸውና ታዛዥነታቸው የንጉሡን ምግብ ላለመብላት በመወሰን አሳይተዋል፡፡

ቀጥሎም ለእግዚአብሔር ታማኝነት የተገለጸው በሦስቱ የዳንኤል ወዳጆች ሲሆን ይህም ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል አንሰግድም በማለታቸው ምክንያት በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ እስከመጣል መድረሳቸውን ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ የዳንኤል ወዳጆችም እኛ የምናገለግለው አምላክ ከዚህ ከሚነድደው ከእሳቱ ነበልባልም ሆነ ከአንተ እጅ ሊያድነን ይችላል፤ ንጉሥ ሆይ! እርሱ ሊያድነን ፈቃዱ ባይሆን እንኳ አማልክትህን እንደማናመልክና ላቆምኸው የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ በማለት ቈራጥነታቸውንና ታማኝነታቸውን ለእግዚአብሔር ገለጹ(ዳን 3፡17-18)፡፡ ታማኝነታቸውና ከእግዚአብሔር የተደረገላቸውን ጥበቃ ንጉሡን ጭምር ያስደነቀ እንደነበር ሲገልጽ አስረን በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት ብቻ አልነበሩምን? እነሆ እኔ እሳቱ ምንም ሳይጐዳቸው ከእስራት ተፈትተው በነበልባሉ ውስጥ የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል ይላል(ዳን 3፡24-25)፡፡

ቀጥሎ የምናገኘው የዳንኤል መፈተንና ያሳየውን ጀግንነት የተሞላበት ታማኝነቱን ነው፡፡ የንጉሥ ዳርዮስ መሳፍንት ወደ ንጉሡ በመሄድ ዳንኤል አንተን አያከብርህም፤ ፈርመህበት የወጣውንም ዐዋጅ በመጣስ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል ብለው በመክሰስና ንጉሥ ያስተላለፈው ዐዋጅ ወይም ትእዛዝ መለወጥ እንደማይቻል ለንጉሡ በማረጋገጥ በአንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል አደረጉት(ዳን 6፡15-16)፡፡ ይህ ከመደረጉ በፊት ግን በድርጊቱ እጅግ በጣም ያዘነው ንጉሥ ዳርዮስ ዳንኤልን ሁልጊዜ በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ያድንህ በማለት አበረታታው(ዳን 6፡16)፡፡ የታመኑትን ሁሌም የሚታደገው አምላክ ዳንኤልን በአንበሶች እንዲቦጫጨቅ አልፈቀደምና አንበሶቹ እንዳይጎዱኝ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ አፋቸውን ዘጋ፤ ይህንንም ያደረገው እኔ ንጹሕ መሆኔንና አንተንም አለመበደሌን ስላወቀ ነው በማለት በውሳኔው ተረብሾ እንቅልፍ አጥቶ ላደረው ለንጉሡ ይገልጽለታል(ዳን 6፡21)፡፡ በዳንኤል ምስክርነትና ባዳነው አምላክ የተደነቀው ንጉሥ ዳርዮስ በመንግሥቴ የሚኖር ሕዝብ ሁሉ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር በዐዋጅ አዝዣለሁ፤ እርሱ ሕያውና ዘላለማዊ አምላክ ነው፤ እርሱ ዘላለማዊ ንጉሡ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም በማለት ለሕዝቡ ትእዛዝ አስተላለፈ(ዳን 6፡ 26-27)፡፡

በአጠቃላይ በዳንኤልና በሦስቱ ወዳጆቹ የተከናወኑት ጀግንነት የተሞላባቸው ምስክርነቶች አይሁዳውያን ሃይማኖታቸው፣ ባህላቸው፣ ሥርዓቶቻቸው ጠብቀው ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው ለማንኛውም አረማዊ ንጉሥ ሳይፈሩ፣ ሳይንበረከኩና በጥቅማጥቅምና በሥጋዊ ድሎት ሳይታለሉ መመስከርና በእምነታቸው መጽናት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፡፡

»»  ትንቢተ ዳንኤል ስለ ሙታን መነሣትና ስለ መጨረሻው ፍርድ ምን ያስተምራል?

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሞት በኋላ ስላለው ፍርድና የሕይወት ሁኔታ የሚገልጹ የመጽሐፍ ክፍሎች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ትንቢተ ዳንኤል ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ፍርድና የእያንዳንዱ ሰው የመጨረሻ እጣ ፈንታ ምንም በማያሻማ ሁኔታ ስለሚገልጽ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንደ ዋና መረጃ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

ትንቢተ ዳንኤል አገላለጽ ዳግመኛ ሕይወት ወይም ትንሣኤ በምንልበት ጊዜ ከሞት በኋላ በነፍስ ብቻ ሳይሆን በሥጋና በነፍስ ሕይወት ማግኘትን ያመለክታል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ መጻሕፍት ሰዎች ሥጋቸው በስብሶ መሬት ውስጥ እንደማይቀር፣ በሥጋ እንደሚነሡና ዘላለማዊ ሕይወት አግኝተው እንደሚኖሩ ያስገነዝባሉ(መዝ 16፡9-11፤ ኢሳ 26፡19)፡፡ እንደ ትንቢተ ዳንኤል አገላለጽ የዓለም ፍጻሜ ከመሆኑ በፊት ሕዝቡን ሁሉ የሚፈታተንና ለሥቃይ የሚዳርግ በምድር ላይ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይመጣል(ዳን 12፡1)፡፡ በምድር ላይ ምንም እንኳ አስቸጋሪ የሆነ የመከራ ጊዜ ቢከሰትም ስማቸው በእግዚአብሔር መጽሐፍ የተጻፉት ግን ይድናሉ(ዳን 12፡1)፡፡ እነዚህ በታማኝነት ጸንተው በመኖር የመከራ ጊዜን በብቃት የሚወጡትና ስማቸው በእግዚአብሔር መጽሐፍ የተጻፉት በፈተና ነጥረውና ጠርተው በመውጣታቸው እንከን የሌለባቸው ስለሚሆኑ ቢሞቱም ተነሥተው በመጨረሻው ቀን የክብር ድርሻቸውን እንደሚያገኙ መልአኩ ለዳንኤል ያረጋግጥለታል(ዳን 11፡35፤12፡ 10-13)፡፡ ስለዚህ አስቀድመው በሞት ተለይተው የነበሩት ተነሥተው እንደገና በሕይወት ይኖራሉ፤ ከእነርሱም እኩሌቶቹ የዘላለም ሕይወት አግኝተው ሲደሰቱ እኩሌቶቹ ለዘላለም በሐፍረትና በጉስቁልና ይሠቃያሉ(ዳን 12፡2)፡፡

የዘላለም ሕይወት አግኝተው ከሚደሰቱትም መካከል ውስጥ ጠቢባኖችና ብዙ ሰዎችን በማስተማርና ጥበባቸውን አገልግሎት ላይ በማዋል ሌሎችን ከክፉ መንገድ ወይም ከጥፋት ጐዳና ወደ ደግ ሥራ የመለሱ ሁሉ ብልጫ እንዳላቸው ይገልጻል(ዳን 12፡3 እና 10)፡፡

»»  በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ መላእክትና አገልግሎታቸው እንዴትና በምን ዓይነት መልኩ ተገልጸው ይገኛሉ?

መላእክት ተላላኪ መልእክተኞች፣ በፍጥረታቸው ረቂቃን የሆኑ፣ ብዛታቸው የማይቆጠር፣ ኃይላቸው ብርቱ፣ ቅዱሳን ጠባቂዎች፣ ስለ ታናናሾች በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ አልፎ አልፎ ራሳቸውን በሰው መልክ የሚገልጹና እግዚአብሔርንም የሚያመሰግኑ መሆናቸው በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በተለያየ መልኩ ተጠቅሶ እናገኘዋለን(ዘፍ 19፡1 እና 12፤ ኢዮ 1፡6፤ ዳን 8፡15-26፤ ኢሳ 6፤ ዘካ 14፡5፤ ማቴ 18፡10፤ ማቴ 22፡30፤ ማቴ 24፡36፤ ሉቃ 15፡10፤ ሉቃ 24፡39፤ ራእ 5፡11-12፤ ዕብ 1፡4)፡፡  በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ግን መላእክቶች ግልጽ በሆነ ሁናቴ በስማቸው እየተጠሩ የተለያዩ የአገልግሎት ተግባራት ሲወጡ ይታያል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው መላኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

መላኩ ገብርኤል ዳንኤል ወደነበረበት ቦታ በመድረስ ግራ የተጋባባቸውና መፍታት ያልቻላቸውን ራእዮች በመተንተን ያስረዳዋል(ዳን 8፡15-27፤ ዳን 9፡21-27)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዳንኤል ስለ እስራኤላውያን ኃጢአት እየተናዘዘ ምሕረትን ከእግዚአብሔር ሲለምን መላኩ ገብርኤል ወደ እርሱ በመቅረብ ገና መጸለይ ስትጀምር እግዚአብሔር ልመናህን ሰምቶአል፤ እርሱ ስለወደደህም የጸሎትህን መልስ ልነግርህ መጥቼአለሁ፤ እንግዲህ የራእዩን ትርጉም ስነግርህ በጥንቃቄ አድምጠኝ በማለት የእግዚአብሔር ተላላኪነቱና ራእይ ፈቺነቱ ይገልጻል(ዳን 9፡23)፡፡ በተጨማሪም መላኩ ገብርኤል እኔ ወደዚህ የመጣሁት የትንቢቱን ምስጢር እንድታውቅ ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ ነው በማለት ጥበብንና ማስተዋል እንዲሰጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መሆኑን ይገልጻል(ዳን 9፡22)፡፡ ከዚህ የምንረዳው መላኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ጋር ቀረቤታ እንዳለው፣ ሰዎች ግራ ተጋብተው ችግራቸውን ለእግዚአብሔር በጸሎት በሚገልጹበት ጊዜ የጸሎታቸውን ምላሽ በመያዝ በፍጥነት የሚደርስ፣ ራእዮችን በመፍታት ነገሮች ግልጽ የሚያደርግ ታማኝ መልእክተኛ ነው፡፡

ሌላው በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ በስም የተጠቀሰውና ብዙ የአግልግሎት ተግባራት የሚፈጽመው መላኩ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ዳንኤል በጤግሮስ ወንዝ አጠገብ በሐዘን ላይ ለሦስት ሳምንታት ሥጋም ሆነ ሌላ ምግብ ሳይበላ፣ የወይን ጠጅም ሳይጠጣና ቅባትም ሳይቀባ በቆየበት ጊዜ አስደናቂ የሆነ ራእይ አየ(ዳን 10፡2-8)፡፡ በዚህ ጊዜ ዳንኤል ኃይሉ ሁሉ ተሟጦ እጅግ በጣም ከመድከሙ የተነሣ መልኩ ተለዋውጦ ባየው ራእይ በመደንገጥ እንደ በድን ሆኖ መሬት ላይ ወደቀ፤ በፍርሃትም ተንቀጠቀጠ(ዳን 10፡9)፡፡ በዚህ ጊዜ በስም ያልተጠቀሰ መልአክ ወደ ዳንኤል ደርሶ ደጋግፎ በእጁና በእግሩ እንዲቆም ካደረገው በኋላ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሆይ! እነሆ እኔ ወደ አንተ ተልኬ መጥቻለሁ፤ ባለህበት ጸጥ ብለህ ቁም፤ የምነግርህም ጸጥ ብለህ አስተውል በማለት ካበረታታው በኋላ የሚነግረውን በጥንቃቄና በማስተዋል እንዲሰማው ያስገነዝበዋል(ዳን 10፡11)፡፡ በመላኩ ንግግር ውስጥ በፋርስ ብቸኛ መሆኔን አይቶ ከመላእክት አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ ካለ በኋላ በድጋሚ በንግግሩ መጨረሻ ላይ የእስራኤል ጠባቂ መልአክ ከሆነው ከሚካኤል በቀር እኔን የሚረዳ የለም በማለት ይደመድማል(ዳን 10፡13 እና 21)፡፡ ከዚህ የምንረዳው መላኩ ሚካኤል የመላእክቶች አለቃ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ብርቱ ጠባቂ፣ የእግዚአብሔር ታማኞች በብቸኝነት ኑሮ በተጎሳቈሉ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስና የሚረዳ መልእክተኛ እንደሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም መላኩ ሚካኤል የዓለም ፍጻሜ በሚሆንበት ጊዜ እንደሚገለጥ ሲናገር ሕዝብህን የሚጠብቀው ታላቁ መልአክ ሚካኤል በዚያን ጊዜ ይገለጣል ይላል(ዳን 12፡1)፡፡

»»  ትንቢተ ዳንኤል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በየትኛው መጽሐፍ ውስጥና በምን ዓይነት መልኩ ተጠቅሶ ይገኛል?

ከአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ውስጥ ትንቢተ ዳንኤልን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሰፊው የጠቀሰው ዮሐንስ ሲሆን ይህም በራእይ ውስጥ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ "አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ" በማለት ስለ አውሬው የሚዘረዝረውን ዳንኤል 7 ላይ ከተገለጸው አውሬ ጋር እጅግ በጣም ተቀራራቢ የሆነ ተመሳሳይነት አለው(ራእ 13)፡፡ በዮሐንስ ራእይ እንደ መለኮታዊ ተዋጊ፣ ትክክለኛ ፈራጅ፣ ዐይኖቹ በእሳት ነበልባል የተመሰሉት፣ በደም የተነከረ ልብስ የለበሰው፣ ስሙም "የእግዚአብሔር ቃል" ተብሎ የተጠራውና ክፋትን ሁሉ ድል ያደረገው በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ፈረሰኛ ተጠቅሷል፡፡ በትንቢተ ዳንኤል ደግሞ "የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ተከብቦ ሲመጣ አየሁ" ይላል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ገጸ ባሕርያት ተመሳሳይነትና ተዛማጅነት እንዳላቸው መረዳት አያዳግትም(ራእ 19፡ 11-21፤ ዳን 7፡ 13)፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተደጋጋሚ ራሱን "የሰው ልጅ" ብሎ ይጠራ እንደነበርና ይህም የሰው ልጅ የሚለው ቃል በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ቀድሞውኑ ተገልጾ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ የዮሐንስ ራእይ በብዙ መልኩ ከትንቢተ ዳንኤል ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ሀሳቦቹም ከዛው ጋር የተወራረሱ ስለሆኑ ጸሐፊው ትንቢተ ዳንኤልን እንዳነበበውና የሚጽፈውም ሁሉ በቂ የሆነ የትንቢተ ዳንኤል ተወራራሽ ሀሳባች እንደተጠቀመ መረዳት ይቻላል፡፡

»»  ትንቢተ ዳንኤል ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከዓለም መንግሥታት ጋር እያወዳደረ ይጽፋል፤ ይህ በሁለት መንግሥታት መካከል የሚደረገው ንጽጽር እንዴት ይገለጻል?

ትንቢተ ዳንኤል እነዚህ ኃያላን መንግሥታት በመጥቀስና ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር በማወዳደር ኃያሉና እውነተኛው መንግሥት የትኛው እንደሆነ አንባቢው እንዲረዳና የራሱን ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ለዳንኤል የተገለጠለት ስለ አራቱ አውሬዎችና ለዘላለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖረው ራእይ ይህንኑ የዓለም መንግሥታትና የእግዚአብሔር መንግሥት የማወዳደር ሁኔታ ይንጸባረቃል(ዳን 7)፡፡ በዚህ ራእይ እንደምንረዳው ከአራቱ ማእዘናት የተነሣው ነፋስ ታላቁን ባሕር ባናወጠው ጊዜ አራት የተለያዩ ታላላቅ አውሬዎች ከባሕሩ ወጡ፡፡ እነዚህም በአንበሳ፣ በድብ፣ በነብርና አንድ ኃይለኛ፣ አስቀያሚና አስፈሪ በሆነ እንስሳቶች የተመሰሉ ነበሩ፡፡ እነዚህ አውሬዎች ሥልጣናቸውን ተነጠቁ፡፡ በሌላ መልኩ የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ተከብቦ ሲመጣ ታየ፡፡ ይህ በሰው ልጅ የተመሰለው ግን ለዘላለም ሕያው ወደሆነው ፊት አቀረቡት፡፡ በልዩ ልዩ አገር የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ያገለግሉት ዘንድ ሥልጣን፣ ክብርና ኀይል ተሰጠው፤ ሥልጣኑ ለዘላለማዊ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም(ዳን 7፡1-14)፡፡

በመጨረሻም ከዳን 10-11 እንደምንረዳው ሌሎችም ታላላቅ ነገሥታት የተባሉትም ተነሥተው ለጥቂት ጊዜያት ከገዙ በኋላ ይወድቃሉ፡፡ ታላላቅ ከተባሉትም ውስጥ የሶርያ፣ የግብጽ፣ የሊቢያና የኢትዮጵያ ነገሥታት ይገኙበታል(ዳን 11፡43)፡፡ ነገር ግን ሁሉም ይጠፋሉ፤ የሚረዳቸውም አይገኝም(ዳን 11፡45)፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥትና በታማኝነት የሚኖሩት ሕዝቦቹ ግን ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ቢሞቱም እንኳ በመጨረሻው ቀን የክብር ድርሻቸውን ያገኛሉ(ዳን 12፡13)፡፡

ሌላው በዳንኤል ከተተረጐመው የመጀመሪያው የንጉሥ ናቡከደነፆር ሕልም እንደምንረዳው በዓለም ላይ ኃያላን የተባሉና በወርቅ፣ በብር፣ በነሐስና በብረት የተመሰሉ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፡፡ እነዚህም ባቢሎን፣ ሚድያ፣ ፋርስና ግሪክ ናቸው፡፡ የእነዚህም ሕልሞች ፍቺ እንደሚያስረዱት ለናቡከደነፆር የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፣ ሥልጣንና ክብርን እንደሰጠውና በሕልሙ ያየውን የወርቁ ራስ እንደሆነ ዳንኤል ያረጋግጥለታል(ዳን 2፡38)፡፡ ቀጥሎም ሌሎች ሦስት መንግሥታት እንደሚነሡ ከገለጸ በኋላ በነሐስና በብረት የተመሰሉት ሦስተኛውና አራተኛውን እጅግ በጣም ኃያላን ዓለምን ለመግዛትና ሁሉንም ነገር ለመሰባበርና ለማንኮታኮት የሚችሉ እንደሚሆኑ ያስገነዝባል፡፡ ነገር ግን በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ግዛቱም በሌላ ሕዝብ የማይደፈር መንግሥትን ይመሠርታል፤ ይህ መንግሥት ሌሎችን መንግሥታት እስከ መጨረሻው ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል(2፡ 44-45)፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ፤   የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1.      ከሚከተሉት ውስጥ በነቢዩ ዳንኤልና በመጽሐፉ በትንቢተ ዳኤል ዙሪያ ከላይ የተብራራውን መሠረት በማድረግ ትክክለኛ ያልሆነውን የትኛውን ነው? 

ሀ) ነቢዩ ዳንኤል ትውልዱ በይሁዳ አገር ከመሳፍንት ወይም ከንጉሣዊ ቤተሰብ ሲሆን የኖረው ግን በስደት ባቢሎን ውስጥ ነው፡፡ ለ) ዳንኤል ታማኝና ቅን አገልጋይ፣ እምነተ ጠንካራ፣ ነቢይነት ከአስተዳዳሪነት ጋር  የተካነ ወጣት ነበር፡፡ ሐ) ትንቢተ ዳንኤል ከምዕራፍ 2፡4 እስከ ምዕራፍ 8 ድረስ የተጻፈው በአራማይስጥ ቋንቋ ሲሆን የቀረው ክፍል ግን በዕብራይስት ነው፡፡ መ) መጽሐፉ በሕልምና ራእይ፣ በደግና በክፉ መካከል የሚደረጉ ትግሎች፣ ስለ ዓለም መጨረሻ ክንውኖች፣ በፍርድ ሂደቶችና ታሪካዊ ክስተቶች የተሞላ ነው፡፡ ሠ)ብልጣሶር፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጎ የዳንኤልና የሦስቱ ወዳጆቹ አይሁዳውያን ስሞች ናቸው፡፡

2.     ከሚከተሉት ውስጥ ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ ታማኝነታቸው ለእግዚአብሔር፣ ለባህላቸውና ለሕዝባቸው ከገለጹበት ድርጊት ውስጥ የማይመደበው የትኛውን ነው?

ሀ)በንጉሡ ቤት በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀው ምግብ አለመመገባቸውና የወይን ጠጅ አለመጠጣታቸው፡፡ ለ)ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል አለመስገዳቸው፡፡ ሐ)ነቢዩ ዳንኤል ንጉሥ ዳርዮስ ላወጣው ሕግ ተገዢ አለመሆኑንና በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ መጸለዩ፡፡ መ) ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ በባቢሎን ውስጥ እያሉ ከእስራኤል ምርኮኞች መካከል ተመርጠውና ለሦስት ዓመት ሠልጥነው ለማገልግል መስማማታቸው፡፡ ሠ) ዳንኤል በአንበሶች እንዲቦጫጨቅ ጉድጓድ ውስጥ መጣሉን፡፡

3.     ንጉሥ ናቡከደነፆር ሕልም እና የናቡከደነፆር ልጅ የነበረው ቤልሻጻር በቤተ መንግሥቱ ግንብ ላይ ስለጻፈው ጽሑፍ ትርጓሜ በተመለከተ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው? (ዳን ምዕራፍ 4 እና 5 በደንብ መነበብ አለበት)፡፡

ሀ) ዳንኤል የቅዱሳን አማልክት መንፈስ እንዳለበት ናቡከደነፆር ያውቅ ነበር፡፡ ለ) በሕልሙ ትርጓሜ መሠረት ናቡከደነፆር ከሕዝብ መካከል ተባረረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፤ ጠጉሩ እንደ ንስር ላባ አደገ፤ ጥፍሩም እንደ አሞራ ጥፍር ሆነ፡፡ ሐ) ዳንኤል ምስጢራዊውን ጽሑፍ ለንጉሥ ቤልሻጾር ተረጐመለት፤ ዳንኤል የክብር ምልክት የሆነ የወርቅ ሐብል ተደረገለት፤ ከዚያ በኋላ ቤልሻጾርም አገሪቱን ለብዙ ዘመናት በሰላም አስተዳደረ፡፡ መ)ንጉሥ ቤልሻጾር  በመሪነቱ ጊዜ ትሕትና አላሰየም፤ በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፡፡ ሠ) በጽሑፉ ፍቺ መሠረት ንጉሥ ቤልሻጾር በሚዛን ተመዝኖ ቀልሎ ተገኘ፡፡

4.     በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ስለ መላኩ ገብርኤልና ሚካኤል ከተነገረው መካከል ትክክል የሆነው የትኛውን ነው?(ዳን ከምዕራፍ 8 እስከ 12 ያለው ክፍል ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

ሀ)በዓለም ፍጻሜ ጊዜ የሰው ዘር ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ መከራ ይሆናል፤ ሕዝብን የሚጠብቀው ታላቁ መልአክ ሚካኤልም በዚያን ጊዜ ይገለጣል፡፡ ለ) ዳንኤልም እንዲህ አለ፤ በፋርስ ብቸኛ መሆኔን አይቶ ከመላእክት አለቆች አንዱ የሆነው ገብርኤል ሊረዳኝ መጣ፡፡ ሐ) ዳንኤል ያየውን ራእይ ትርጉም በማሰላሰል ላይ ሳለ በድንገት "ሚካኤል ሆይ ! ይህ ሰው የራእዩን ትርጉም እንዲረዳው አድርግ" የሚል ድምፅ ሰማ፡፡ መ) መላኩ ሚካኤል ወደ ዳንኤል መጥቶ "ዳንኤል ሆይ ! እኔ ወደዚህ የመጣሁት የትንቢቱን ምስጢር እንድታውቅ ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ ነው" አለው፡፡ ሠ) ዳንኤልም "የእስራኤል ጠባቂ መልአክ ከሆነው ከገብርኤል በቀር እኔን የሚረዳ የለም" አለ፡፡

5.     ዳንኤል በስደት ስለሚንከራተተው ስለ ወገኖች የእስራኤል ሕዝብ ከጸለየው ጸሎት ውስጥ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው?(ጸሎቱ የሚገኘው ዳን 9 ላይ ነው)፡፡

ሀ) ዳንኤል ማቅ ለብሶ፣ ዐመድ ላይ ተቀምጦ በመጾም እግዚአብሔርን በመማጸን በብርቱ ይጸልይ ነበር፡፡ ለ)ዳንኤል የእግዚአብሔር ምሕረት በመተማመን ይጸልያል፤ ሕዝቡ የሚመኩበት መልካም ሥራቸውንም እንዲያይ እግዚአብሔርን ይማጸናል፡፡ ሐ)እንደ ዳንኤል ገለጻ በምድር ካሉ አገሮች ሁሉ የኢየሩሳሌምን ያህል ቅጣት የደረሰበት ከቶ የለም፡፡ መ) ኢየሩሳሌም ፍርስራሽ ሆነ ለሰባ ዓመታት ትቆያለች፡፡ ሠ) ሁሉም ትክክል ናቸው፡፡

6.     ዳንኤልና ሦስቱ ወዳጆቹ እምነታቸውን እንዲክዱና ለጣዖታት እንዲሰግዱና የባቢሎናውያን የረከሰ ምግብ እንዲመገቡ የሚያስገድዳቸው ብዙ መከራ ደረሰባቸው፤ ነገር ግን በጥበብ፣ በድፍረትና ከምንም በላይ በእግዚአብሔር በነበራቸው እምነት በመታገዝ ሁሉንም ለማለፍ ቻሉ፡፡ የእሳት ኃይል፣ የአንበሳ ጉልበትና ጥርስ በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸውን እምነት ሊያስለውጣቸው አልቻለም፡፡ የቀድሞ አባቶቻችንም ስለ እምነታቸው ብዙ ሰማዕትነት ከፍለው፣ ደማቸው አፍሰው አልፈዋል፤ እምነታቸውንም ወደ እኛ አስተላለፈዋል፡፡ ዛሬ በእርግጥ ነገሥታትም ሆነ የውጭ ኃይሎች እኛን አስገድደው ጣዖት እንድናመልክና ሃይማኖታቸው እንድንከተል አያስገድዱንም፡፡ ሁላችንም የእምነት ነፃነት ስላለን በሰላም እንኖራለን፡፡ ነገር ግን ዛሬ ባለንበት ዘመን እምነታችንን እየተፈታተኑ፣ የአባቶቻችን እምነት ጠብቀን እንዳንጓዝ እንቅፋት የሚሆኑብንና ከካቶሊካዊነታችን ሊያርቁን የሚገፋፉንና በእምነታችን ጸንተን እንዳንራመድ የሚያደርጉን "የዘመኑ ጣዖቶች" አሉ፤ እነዚህ ትኩረታችንን የሚስቡ ጣዖቶች ወይም መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚፈታተኑትና እምነተ ቀዝቃዛ እንድንሆንና እንድንርቅ ከሚያደርጉን ነገሮች ውስጥ የተወሰኑትን ጥቀስ፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት