ት/ርት ፴-፴፩ - የትንቢተ ናሆምና ዕንባቆም ጥናት

ክፍል ሦስት (ትምህርት ሠላሳ አንድ) - የነቢያት መጽሐፍት ጥናት

ትንቢተ ናሆም እና ትንቢተ ዕንባቆም

Nahum Habakkukናሆም ማለት “መጽናናት” ማለት ነው፡፡ ናሆም ከይሁዳ ከተሞች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ከሚገመተው ልዩ ስሙ ኤልቆሽ ከተባለ መንደር እንደሆነ ቢገለጽም ይህ መንደር የት እንደሚገኝ ትክክለኛ የሆነ ተጨባጭ መረጃ ስለሌለ ማወቅ አልተቻለም(ናሆ 12) ፡፡ መጽሐፉ ውስጥ ናሆም መቼ እንደኖረና የነቢይነት ተግባሩም መቼና በማን ዘመነ መንግሥት ጊዜ እንደተወጣ፣ ከየትኛው ወገን ወይም ቤተሰብ እንደሆነ፣ የራሱ ቤተሰባዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል መረጃ የለም፡፡ መጽሐፉም መቼና የት ቦታ እንደተጻፈ ምንም ዓይነት ፍንጭ ከመጽሐፉ አናገኝም፡፡ ቢሆንም መጽሐፉ ውስጥ በተካተቱት ጥቂት መረጃዎች መሠረት ነቢዩ ናሆም ይሁዳ ውስጥ በተለይም ኢየሩሳሌም አካባቢ እንደኖረና የነቢይነት ተግባሩም እዛው ኢየሩሳሌም አካባቢ እንደተወጣ ይታመናል(ናሆ 115)፡፡ በእርግጥ ናሆም ስለ ይሁዳ በጎነት ወይም ይሁዳን በመልካም አቀራረብ እየገለጸና መልካም ዜናን እያበሰረ ደጋግሞ ይናገራል፡፡ በተጨማሪም መጽሐፉ ውስጥ ዓመት በዓሎቻቸውንና ስለቶቻቸውን ለእግዚአብሔር ማቅረባቸውን የሚያበረታታ ሁኔታ ይንጸባረቅበታል፡፡ ስለዚህ ናሆም ምንአልባትም ቤተ መቅደስ አካባቢ የሚኖርና የነቢይነት ተግባሩንም እዛው ቤተ መቅደስ ውስጥ ይወጣ እንደነበር ይታመናል(ናሆ 114-15)፡፡

ናሆም የአሦር ዋና ከተማ ስለነበረችው ስለነነዌ ውድቀት ሲናገር ከተማዋ እጅግ በጣም በልጽጋ እንደነበረች፣ ዙርያዋም በቅጽሮች የታጠረችና የጦር ሹማምንቶችዋም ገናና ስለነበሩበት ወቅት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህ የነነዌ የብልጽግናና የኃያልነት ጊዜ የነበረው በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በመሆኑ ነቢዩ ናሆም በዚህ ወቅት በተለይም በ620 ዓ.ዓ አካባቢ እንደኖረና የትንቢት ቃሉ እንዳስተላለፈ ይታመናል(ናሆ 21-12)፡፡

መጽሐፉ ገና ከጅማሬው የነቢዩን ስምና መንደር ከጠቀሰ በኋላ ስለሚናገረው የትንቢት ቃል ዋና ፍሬ አሳብ ግልጽ በሆነ ሁኔታ  ያስረዳል፡፡ በዚህም መሠረት የትንቢቱ ዋና ተዋናይ ወይም ማዕከል የነነዌ ጥፋት ወይም የነነዌን ውግዘት እንደሆነ ስለ ነነዌ ጥፋት ኤልቆሻዊው ናሆም የተናገረው ቃልና ያየው ራእይ ይህ ነው በማለት ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም ገና ከመልእክቱ መጀመሪያ እግዚአብሔር ተቀናቃኞቹን የማይታገሥ፣ ጠላቶቹንና የሚቃወሙትን ሁሉ የሚቀጣ፣ ቁጣውንና መዓቱን የሚያወርድ አምላክ እንደሆነ ይናገራል(ናሆ 12)፡፡ እግዚአብሔር ኃያል፣ የሁሉም ፍጥረታት ገዥ፣ ቁጣው በነደደ ጊዜ ተራሮች የሚንቀጠቀጡ፣ ኮረብታዎች እንደ ሰም የሚቀልጡ፣ አለቶች ተሰነጣጥቀው የሚበተኑና ምድርም የምትናወጥ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ እግዚአብሔር ሁሉንም ገዥ በመሆኑም በትእዛዙ ባሕርና ወንዞች የሚደርቁ፣ ዕፅዋት ሁሉ የሚጠወልጉ፣ የሊባኖስ አበቦችም የሚረግፉ፣ ዓለምና በውስጥዋም ያለው ነገር ሁሉ የሚንቀጠቀጥ ተደርጎ በሚያስፈራ ሁኔታ ተገልጿል(ናሆ 14-6)፡፡ በተጨማሪም በእግዚአብሔር ላይ የሚያሤር እስከ መጨረሻው እንደሚደመሰስ፣ ተቃዋሚዎቹም ወደ ድቅድቅ ጨለማ እንደሚወርዱና እንደሚያጠፋቸው ይተርካል(ናሆ 19-10)፡፡ ይህ ሁሉ ግን የአሦር መናገሻ ስለነበረችው ነነዌን ለማስፈራራትና እግዚአብሔር ወደፊት ሊፈርድባት እንደሆነ ለመግለጽ ነው፡፡

ስለዚህ በወቅቱ ኃያልና ብርቱ እንዲሁም ዙሪያዋን በቅጽር ታጥሮ የነበረው ነነዌ ምንም እንኳ የጦር ሹማምንት፣ ወታደሮችና የጦር ሠረገላዎች ያሉዋት፣ በብዙ ሀብትና ንብረት የከበረችና ለመጠጊያነት የሚመቹ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ቢኖርዋትም ትጠፋለች፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ይደመስሰዋል በማለት ነቢዩ የተለያዩ ነገሮች በመጠቀም ያብራራል(ናሆ 21-12)፡፡ ከዚህም በላይ ነነዌ ነፍስ እንዳጠፋች፣ በሐሰት እንደተሞላች፣ በዘረፋና በቅሚያ ሀብት እንደበለጸገች፣ በዝሙት ሥራዋ እንደታወቀች በተለያየ መልኩ እያብራራ ወደፊት ስለምትቀጣበት ምክንያቶች ይዘረዝራል(ናሆ 3)፡፡ በአጠቃላይ የመጽሐፉ ዋና ትኩረት የነነዌን ውድቀትና ቅጣት ሆኖ ይህንን ቅጣት ለምን እንደሚገባት በተለያየ መልኩ ውብ በሆነ የአጻጻፍ ስልት እየተጠቀመ ይገልጻል፤ እንዲሁም የነነዌን መጥፎ ጎን ነው ያለውን እያጋነነና እግዚአብሔርም በጠላትነት እንደሚነሣባት እያረጋገጠ ይናገራል፡፡

መጽሐፉ አልፎ አልፎ በግጥምና አንባቢን በሚስብ መልኩ በጥሩ ሁኔታ የተቀነባበረ ነው፡፡ ለምሳሌ ነነዌን ሲያስጠነቅቃት የብዙዎች ነፍስ ላጠፋች፣ በሐሰት ለተሞላች፣ በዘረፋና በቅሚያ ሀብት ለበለጸገች ለነነዌ ከተማ ወዮላት! ይልና የአለንጋና የመንኰራኩር ድምፅ፣ የፈረስ ግልቢያና የሠረገላ መኳንንት ይሰማል፡፡ ፈረሰኛ ይጋልባል፣ ሰይፍ ይንቦገቦጋል፣ ጦርም ይብለጨለጫል በማለት ስለሚመጣባት ቁጣ አስፈሪነት በግጥም መልክ ይናገራል(ናሆ 31 እና 3)፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ ከጥንት ጀምሮ የእስራኤል ቀንደኛ ጠላት የነበሩት የአሦራውያን ዋና ከተማ ስለነበረችው ስለ ነነዌ መደምሰስ የቀረበ የደስታ ቅኔ ነው፡፡

ከሁሉም በማስቀደም ነቢዩ ናሆም የእግዚአብሔር ኃያልነትና ቁጡነት በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች በመጠቀም በተለያየ መልኩ እየገለጸ አድማጩን እንዲረዳ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ምንም እንኳ ኃይሉ ታላቅ ቢሆንም ለቁጣ የሚቸኩል አምላክ እንዳልሆነ ያረጋግጣል(ናሆ 13)፡፡ ቀጥሎም እንደ ነቢዩ ናሆም አገላለጽ እግዚአብሔር ተቀናቃኞቹን የማይታገሥ፣ ጠላቶቹንና የሚቃወሙትን የሚቀጣ፣ ኃይሉ ታላቅ የሆነ፣ በዐውሎ ነፋስና በሞገድ መካከል እንኳ መንገድ ያለው ሆኖ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ቁጡ፣ ቁጣው እንደ እሳት በነደደ ጊዜ በፊቱ ማንም መቆም የማይችል፣ እንደ አንበሳ አስፈሪዎች የሆኑ ወታደሮች ያሉትና በሰይፍ የሚያጠፋ አምላክ አድርጎ ይገልጸዋል(ናሆ 12-3፤ 213)፡፡

በተጨማሪም በእርሱ ላይ ለሚያሤሩበት እስከ መጨረሻው ይደመስሳቸዋል፤ ለሚቃወሙት በጠላትነት ይነሣባቸዋል፤ ጠላቶቹን በጎርፍ አጥለቅልቆ ያጠፋቸዋል፤ ተቃዋሚዎቹን ወደ ድቅድቅ ጨለማ ያሳድዳቸዋል ዳግመኛ መነሣት በማይችሉበት ሁኔታ ያጠፋቸዋል፤ ያዋርዳቸዋልም(ናሆ 19፤35)፡፡ በተጨማሪም ኃያላን ነን ብለው ሕዝቡን ለሚያስጨንቁት እግዚአብሔር ሠረገላዎቻቸው ሁሉ በእሳት ያቃጥላል፤ እንደ አንበሳ አስፈሪዎች የሆኑትን ወታደሮችም በሰይፍ ያጠፋል(ናሆ 213)፡፡ ነቢዩ ናሆም እግዚአብሔር በእንደዚህ ሁኔታ የሚገልጸው በወቅቱ ኃያል የነበረችውና በማን አለብኝነት የጭካኔ ተግባር በሕዝቦችዋ ላይ ትፈጽም በነበረችው አሦርና ዋና ከተማዋ ነነዌን ለማስፈራራትና እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ ኃያል የሆነ አምላክ እንደሆነ ለማስገንዘብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር በእርሱ የሚተማመኑትን እንደሚጠብቅና በመከራም ጊዜ መሸሸጊያ በመሆን እንደሚንከባከባቸው ሲገልጽ እግዚአብሔር ቸር ነው፤ በመከራ ጊዜም ለሕዝቡ ጠንካራ መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚተማመኑትን ሁሉ ይንከባከባል ይላል(ናሆ 17)፡፡

ነነዌ በወቅቱ በኃያልነትዋ እጅግ ገናና፣ ከተማዪቱም በምሽግ የታጠረችና ከብዙ የጦር ሹማምንቶችዋና ወታደሮችዋም የተነሣ አስፈሪ ልዑለ ኃይል ነበረች፡፡ ነነዌ በኃያልነትዋ በመመካት በይሁዳና በአጎራባች አገራት ላይ በፈጸመችው በደል እግዚአብሔር እንደሚቃወማትና እንደሚቀጣት እንዲሁም ከተማዋ እንዳልነበረች እንደሚደመስሳት ነቢዩ ናሆም ይተነብያል፡፡ በዚህም መሠረት ነነዌን ቀጥቅጦ የሚገዛ ጠላት ይነሣል፤ የጠላት ወታደሮች እየሮጡ ወደ ከተማዪቱ ቅጽር ይወጣሉ፤ ከተማዪቱም ትዘረፋለች፤ ፈራርሳም ምድረበዳ ሆና ትደመሰሳለች፤ ቤተ መንግሥቱም በሽብር ይሞላል(ናሆ 2)፡፡ ከዚህም በላይ ንግሥቲቱ ተማርካ ትወሰዳለች፤ የነነዌ ሕዝብም ከከተማዪቱ ጥርግርግ ብለው ይወጣሉ፤ የሰው ሁሉ ልብ በፍርሃት ይቀልጣል፤ የሰው ሁሉ ወገብ በአስጨናቂ ሕመም ይታወካል፤ ፊቱም ሁሉ ይገረጣል(ናሆ 2)፡፡

በሌላ በኩል እግዚአብሔር ራሱ በነቢዩ ናሆም አማካይነት ለነነዌ ከተማ በቀጥታ በመናገር ወደፊት ከባድ ቅጣት እንደሚያመጣባት ይናገራታል፡፡ በዚህም መሠረት ውርደትዋና ውድቀትዋ እጅግ በጣም የከፋ መሆኑን ለመግለጽ ነነዌ ሆይ! እነሆ በጠላትነት ተነሥቼብሻለሁ፤ ልብስሽን ከላይሽ ላይ እገፍፋለሁ፤ ዕርቃነ ሥጋሽ ለአሕዛብ፣ ነውርሽም ለመንግሥታት እንዲጋለጥ አደርጋለሁ፡፡ የቆሻሻ መጣያ አደርግሻለሁ፤ በንቀት እመለከትሻለሁ፤ ሰው ሁሉ እንዲጸየፍሽ አደርጋለሁ በማለት እግዚአብሔር ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ ለነነዌ ይናገራል(ናሆ 35-6)፡፡ ነነዌ በሚደርስባት ቅጣት ምክንያት የሚያዝንላትና የሚያጽናናት አንድስ እንኳ አይኖርም፤ እንዲያውም የሚያያት ሁሉ በመሠቀቅ ከእርስዋ ይሸሻል(ናሆ 37)፡፡

ነነዌ ካላት ሀብትና የጦር ሠራዊት የተነሣ ብርቱ፣ ከተማዋም በደንብ የተጠበቀ፣ ጠረፎችዋም በብርቱ በሮች የታጠሩ፣ ለጠላት በቀላሉ የማትበገር ጠንቃቃ ከተማ መሆንዋን ነቢዩ በደንብ ተረድቶት ያውቅ ስለነበር የቱንም ያህል ብትጠነቀቂ በእሳት መቃጠልሽና በሰይፍ መመተርሽ አይቀርም፤ በአንበጣ እንደተበላ ሰብል ትጠፊያለሽ በማለት ስለሚመጣባት ቅጣት እርግጠኛ ሆኖ ይናገራል(ናሆ 315)፡፡ ነነዌ ምንም እንኳ ኃያል ነኝ ብላ ብትመካም ብዙ ወዳጆችና ብርቱ የሆኑ ጎረቤቶች ከነበሩዋት ከግብጽ ዋና ከተማ ከቴብስ እንደማትበልጥ በማነጻጸር ቴብስ እንኳ በጠላት ተወርራ ሕዝቦችዋ መሰደዳቸው እያረጋገጠ ነነዌ ደግሞ ከዚህ የባሰ ቅጣት እንደሚጠብቃት ይናገራል(ናሆ 38-10)፡፡ የነነዌ ወታደሮች በሙሉ እንደ ሴት ፈሪዎች ይሆናሉ፤ የጠረፍዋ በሮችም ለጠላቶች ክፍት ይሆናሉ፤ መዝጊያዎቹንም እሳት ይበላቸዋል፤ ነጋዴዎችዋም ሳይቀሩ ይጠፋሉ በማለት በወቅቱ ነነዌ ደርሳበት የነበረውን ከፍተኛ የእድገትና የሥልጣኔ ደረጃ እየጠቀሰ ከተናገረ በኋላ ይህም ሆኖ ከሚመጣው ቅጣት ሊያድናት የሚችል ግን ምንም ነገር እንደማይኖር የትንቢት ቃሉን ይናገራል፡፡ 

በአጠቃላይ ነነዌ በአስከፊ ሁኔታ ትወድቃለች፤ ቅጣትዋም እጅግ በጣም የበረታ ይሆናል፡፡ ይህ በአሦራውያን የሚደርሰው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ሕዝቡ እስራኤልን ከመንከባከብና ከወደቀባቸው የጭቆና ቀንበር ነፃ ለማውጣት በማሰብ መሆኑን ሲገልጽ አሦራውያን በእናንተ ላይ የጫኑትን የጭቆና አገዛዝ አስወግዳለሁ፤ እናንተንም ያሰሩበትን እግር ብረት እሰብራለሁ፤ የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ክፉዎች ጠላቶችህ ፈጽሞ ስለ ተደመሰሱ ከእንግዲህ ወዲህ አገርህን ከቶ አይወሩአትም ይላል(ናሆ 113 እና 15)፡፡ ስለዚህ በነቢዩ ናሆም አመለካከት አይዳውያንን ሲያስጨንቁ የነበሩ አሦራውያን ለአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔርም ጭምር ጠላቶች ተደርገው ተቈጥረዋል፤ ስለዚህ መቀጣታቸው ትክክለኛ ፍርድ መሆኑን ለማሳየት የፈጸሙትን በደል በመዘርዘር ያስረዳል፡፡     

ዕንባቆም የሚለው ስምትርጓሜውአስቸጋሪቢሆንምብዙዎችካደረጉትየስሙትንታኔዕንባቆም ማለት “በእጆችማቀፍ”ወይምበእጆችመካከልአድርጎአንድንነገርመያዝ”ወይም “አንድን ነገር ጭብጥ አድርጎ መያዝወይምበእቅፍ ውስጥማኖር” ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ዕንባቆም የሚለው ስም ከአካድያን የተገኘና በአካዶች ቋንቋ “አንድን ተክል” እንደሚያመለክት ይገልጻሉ፡፡ዕንባቆምመችእንደኖረናየነቢይነትምተግባሩመችእንደተወጣበግልጽባይታወቅምበጽሑፉውስጥ ስለ ይሁዳ መወረርም ሆነ ስለኢየሩሳሌምቤተመቅደስመፍረስምንምዓይነትመረጃስለማይሰጥቤተመቅደስከመፍረሱበፊትማለትም በ586 እና612 ዓ.ዓ አካባቢእንደኖረይገመታል፡፡በእርግጥዕንባቆም የአሦራውያን ኃያልነት በማብቃትና የባቢሎናውያንገናናነት ጅማሬላይ የነቢይነት ተግባሩን እንደተወጣ ከጽሑፉ መረዳት ይቻላል፡፡ የባቢሎናውያን ኃያልነት ጅማሬም እንዲህበማለትይገልጻልእነሆእነዚያንጨካኞችናፈጣኖችባቢሎናውያንንአስነሣባችኋለሁ፤እነርሱየራሳቸውያልሆነውንምድርሁሉበጦርኃይልለመያዝበየአገሩይዞራሉ(ዕን 1፡ 6)፡፡

መጽሐፉ ውስጥ ነቢዩ ዕንባቆም በየትኛው መንግሥት ወቅት፣ ከየትኛው አካባቢና ከየትኛው ወገን እንዲሁም ከየትኛው ቤተሰብ እንደተገኘ ምንም መረጃ የለም፤ ነገር ግን ጽሑፉ ውስጥ ከተካተቱት ጥቂት መረጃዎች እንደምንረዳው ዕንባቆም በይሁዳ ውስጥ በኢየሩሳሌም አካባቢ የነቢይነት ተግባሩን እንደተወጣ ይታመናል፡፡ ከመጽሐፉ መጀመሪያ ዕንባቆም ነቢይ እንደሆነ ከመገለጹም አልፎ በመጽሐፉ መጨረሻ ክፍል ውስጥ በተካተተው ጸሎት በድጋሚ ነቢይነቱን ተጠቅሶ እናገኘዋለን(ዕን 1፡1፤ 3፡1)፡፡ ዕንባቆም በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራዎች የሚገረምና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው መሆኑን ከጽሑፉ መረዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በእግዚአብሔር ጥበቃ ላይ የሚተማመን፣ በዓለም ውስጥ በሚከናወኑ ነገሮች እየተገረመ ለእግዚአብሔር ጥያቄውን የሚያቀርብ፣ ጥያቄ አቅርቦ መልስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለማግኘት በትዕግሥት የሚጠባበቅና ያየውን ራእይ በጽሑፍ የሚያሰፍር ነቢይ እንደነበር ከጽሑፉ እንረዳን፡፡

መጽሐፉ ገና ሲጀምር እግዚአብሔር ሆይ! እንድትረዳኝ ወደ አንተ ስጮኽ የማትሰማኝ እስከ መቼ ነው? በማለት በጥያቄ ይጀመርና ብሶቱን ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፡፡ ቀጥሎም እግዚአብሔር የሚሰጠው መልስ ይጠባበቃል፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምላሽ ካገኘ በኋላ በድጋሚ ሌላ ጥያቄ ለእግዚአብሔር አቅርቦ ሌላ ምላሽ ይጠብቃል፡፡ ከዚህ ጥያቄና መልስ ውጪ መጽሐፉ በአምስት “የወዮላችሁ ዛቻዎች” የተጠናከረ ነው፡፡ ዛቻዎቹም እንደሚከተለው ተገልጸዋል፡፡

-       የራሳችሁ ያልሆነውን ሀብት የምትሰበስቡ የባለዕዳዎችን ንብረት በግፍ በመቀማት የምትበለጽጉ ሁሉ ወዮላችሁ(28)፤

-       በግፍ የተሰበሰበሀብት ቤታችሁን የሞላችሁ አደጋም እንዳይደርስባችሁ መኖርያችሁን ከፍ ባለአምባ ላይ ያደረጋችሁ ወዮላችሁ(29)፤

-       ከተማን በዐመጽ ለምትመሠርቱና በሰው ደምም ለምትገነቡት ወዮላችሁ(2 12)፤

-       ተዋርዶ ሐፍረተ ሥጋው ሲገለጥ ለማየት ለባልንጀራህ ጠንካራ መጠጥ የምታጠጣው አንተ ሰው ወዮልህ (215)፤

-       ከእንጨት ተጠርቦ የተሠራውን ነገርንቃከድንጋይ ተቀርጾ የተሠራውንም ነገርተነሥለምትል ለአንተ ወዮልህ (219) የሚሉት ናቸው፡፡

በዚህ በሦስት ምዕራፎች ብቻ በተጠናከረ ጽሑፍ ውስጥ ዕንባቆም ነገሮችን ግልጽና ምሳሌያዊ በሆኑ አነጋገሮች እየተጠቀመ መልእክቱን ለአንባቢው በሚስብ ሁኔታ አጠናቅሮታል፡፡ በተጨማሪም መጽሐፉ አንድ ከእግዚአብሔር ጋር የተደረገ ውይይትና ሌላ ረዘም ያለ የነቢዩ ዕንባቆም ጸሎት አካቶ ይዞአል(ዕን 12- 21፤ ዕን 3)፡፡ በጹሑፉም የቤት እንስሳቶች፣ የዱር አራዊቶች፣ የባሕር ዓሣዎች፣ በደረታቸው እየተሳቡ የሚሄዱ ፍጥረቶች፣ ደኖች፣ ተራራዎች፣ ወንዞች፣ ፀሐይና ጨረቃ በሙሉ ተካተው መልእክት በሚያስተላልፉ መልኩ ተጠናቅረዋል፡፡ ከሰዎች ባሕርይም ውስጥ ዐመፀኞችና ደጋግ ሰዎች፣ በቅንጦት የሚኖሩ ሀብታሞችና ድኾች፣ ዘራፊዎችና ንጹሓኖች፣ ሐሰተኞችና እውነት ወዳዶች፣ ክብርና ውርደት፣ ፍርሃትና ድፍረት፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ተዋጊ ሠራዊቶችንና ምርኮኞች የመሳሰሉ ተጻራሪ ነገሮች ተጠቅሞ የነቢይነት መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

በአጠቃላይ መጽሐፉ ምንም እንኳ አጭር ቢሆንም በአጻጻፍ ስልቱ በተለይም በጥያቄ መልክ ነገሮችን መግለጹ ቀጥሎም እግዚአብሔር ለሚሰጠው ምላሽ በቂ ጊዜና ቦታ ሰጥቶ፣ የጊዜው ወቅታዊ የሆኑ ነገሮች በምሳሌያዊ አነጋገሮች ተጠቅሞ ብዙ መልእክቶች በሚያስተላልፍ መልኩ የተጠናቀረ መጽሐፍ ነው፡፡

ነቢዩ ዕንባቆም እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ሳይዘገይ እንዲቀጣቸው በጽኑ ይመኛል፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር ለምን እንደሚታገሥና ፍርዱን እንደሚያዘገይ ይጠይቃል፡፡ ለነቢዩ ዕንባቆም ኃጢአተኞች የሚባሉት፦

-   በሕዝብ ላይ ግፍ የሚፈጽሙ (ዕን 13)፤

-   አምባጓሮና ጭቅጭቅ የሚያስነሡ (ዕን 13)፤

-   ፍትሕን በማጓደል ፍርድን የሚያጣምሙ (ዕን 14)፤ 

-   ደጋግ ሰዎችን በመክበብ የሚያስጨንቁ (ዕን 14)፤

-   ፍርሃትና ሽብር የሚፈጥሩ (ዕን 17)፤

-    በጉልበታቸው የሚመኩ ናቸው (ዕን 111)፡፡

በተጨማሪም ኃጢአተኞች የሚባሉት ዐመፀኞች(ዕን113)፣ ጣዖት አምላኪዎች(ዕን 116)፣ ሕዝብን ያለ ርኅራኄ የሚፈጁ ናቸው(ዕን 117)፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሀብት የሚስገበገቡ(ዕን 25)፣ ትዕቢተኞች(ዕን 25)፣ ሕዝቦችን የሚማርኩ(ዕን 25)፣ የሌሎችን ሀብት በግፍ በመቀማት የሚበለጽጉ(ዕን 26) እንዲሁም ከተማን በዐመፅ የሚመሠርቱና በሰው ደምም የሚገነቡት ናቸው(ዕን 212)፡፡ እንደ ነቢዩ ዕንባቆም አገላለጽ እነዚህ ሰዎች ኃጢአተኞች ናቸውና መቀጣት አለባቸው፡፡ ደጋግ ሰዎች በእነዚህ ኃጢአተኞች ምክንያት መጨነቅና መሸበር የለባቸውም፤ እግዚአብሔር እንዲበቀልላቸው ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ግን እሺ እቀጣቸዋለሁ በማለት መቼዉንም ስምምነቱን አልገለጸም፡፡

በሌላ በኩል እንደ ነቢዩ አገላለጽ እነዚህ ኃጢአተኞች የተባሉት ሰዎች እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን የሚበቀላቸው ሕዝቡም ጭምር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ እነዚህ ሲጨቆኑ የነበሩት ሰዎች በተራቸው ተነሥተው በእግዚአብሔር ረዳትነት ጨቋኞቻቸውን ባለ ዕዳ በማድረግ ያንቀጠቅጧቸዋል፤ ንብረታቸውም በተራቸው ይዘርፏቸዋል(ዕን 27-8)፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግፍ በንጹሓን ላይ ሲፈጽሙ የኖሩ የእጃቸውን ያገኛሉ፤ ምክንያቱም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህንን ለማድረግ ወስኗልና(ዕን 213)፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ኃጢአተኞች የሚሠሩት ሁሉ በእሳት ይወድማል(ዕን 212)፤ በክብር ፈንታ ውርደት ይከናነባሉ(ዕን 216)፤ የሚጨነቁበትም ጊዜ ይመጣል(ዕን 217)፡፡

በአጠቃላይ እንደ ነቢዩ ዕንባቆም አገላለጽ አሁን ተበድለው ወይም በምርኮ ላይ ሆነው በማራኪዎቻቸው እየተሠቃዩና እየተጨቆኑ ያሉት ወደፊት ከእነሱ መካከል የተረፉትን ለበቀል እንደሚነሣሡና በተራቸው ማራኪዎቻቸውን እንደሚያንቀጠቅጧቸው ይናገራል(ዕን 2፡6-8)፡፡ ሲዘርፉ፣ የንጹሐን ደም ሲያፈሱ፣ ሲበዘብዙ፣ ሲጨቁኑ፣ ሲቀሙና የሌሎችን ሀብት ሲሰበስቡ የነበሩት ማራኪዎች(ባቢሎናውያን) በተራቸው ይህንን ሁሉ ይደርስባቸዋል(ዕን 2፡15-16)፡፡ በማረኩዋቸው ሰዎች ላይ ስላደረሱት ግፍ ብቻ ሳይሆን በእንስሳትና በደንም ጭምር ስላደረሱት ጥፋት ሁሉ ይጠየቁበታል፤ ይቀጡበታልም፡፡ ነቢዩ እንዲህ ይላል የሊባኖስ ዝግባዎች እንደ ቈረጥህ አንተም ትቈረጣለህ፤ የዱር አራዊትን በግፍ ፈጅተህ ነበር፡፡ አሁንም ደግሞ እነርሱ አንተን በማስፈራራት ያስጨንቁሃል፤ ይህም ሁሉ የሚደርስብህ የብዙ ሕዝብ ደም ስላፈሰስህና በመላው ዓለም ከተሞች በሚኖሩ ግፍ ስለፈጸምህ ነው(ዕን2፡17)፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው እግዚአብሔር በዚህ ዓይነት የብቀላ መንፈስ እንደተስማማ ነቢዩ አይገልጽም፤ ይህ የነቢዩ ትንቢታዊ ቃል ነው እንጂ የእግዚአብሔር የስምምነት መንፈስ በቃሉ ውስጥ አይንጸባረቅም፡፡

- ነቢዩ ዕንባቆም ስለ ጻድቅ የሕይወት አኗኗርና ወደፊት ስለሚያገኘው በረከት የሚገልጸው በምን ዓይነት መልኩ ነው?

ዕንባቆም ብዙ ነገሮች እግዚአብሔርን ቢጠይቅም ወይም በስደት ስላለው ሕዝቡ ብዙ ውይይት ከእግዚአብሔር ጋር ቢያደርግም የእግዚአብሔር ምላሽ የነበረው “ጻድቅ ሰው በእምነቱ ሕይወትን ስለሚያገኝ” ጸንቶ መቆምና በትዕግሥት መጠበቅ እንዳለበት ነው፡፡

ይህየእግዚአብሔርምርጫናውሳኔነቢዩኤርምያስስለሕዝቡስደትናመከራደጋግሞእግዚአብሔርንበጠየቀውጊዜከተሰጠውምላሽጋርይመሳሰላል (ኤር 1519-21)፡፡ ለነቢዩ ዕንባቆም እግዚአብሔር ማለት ቅዱስና ዘላለማዊ አምላክ፣ የሕዝቦቹ መጠጊያና ኃይልንም የሚሰጥ፣ ዐይኖቹ እጅግ ንጹሓን የሆኑ፣ ክፉ ነገርን የማይመለከቱና ክፉ ነገር ሲሠራ አይቶ የማይታገሥ አምላክ ነው(ዕን 112-13)፡፡ በተጨማሪም የእግዚአብሔር ክብር ሰማያትን ይሸፍናል፤ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል፤ ውበቱ እንደ ፀሐይ ያበራል፤ ኃይሉ ከተሰወረበት እጁም የብርሃን ጨረር ያንጸባርቃል(ዕን 33-4)፡፡  እግዚአብሔር እንደ ቁጡ አምላክ ተደርጎም ተገልጿል፡፡ እግዚአብሔር በተቆጣ ጊዜ በፈረሶቹና በድል ሠረገላዎቹ ተቀምጦ ይጋልባል፤ ቀስቱ ከሰገባው ያወጣል፤ ፍላጻዎቹም ለመወርወር ያነጣጥራል፤ ከሚወረወሩት ፍላጻዎቹ ብልጭታና ከሚያብረቀርቀው ጦሩ ነጸብራቅ የተነሣ ፀሐይና ጨረቃ በየቦታቸው ይቆማሉ (ዕን 39-11)፡፡ እግዚአብሔር የሚቆጣው ኃጢአተኞች በሚያከናውኑት መጥፎ ተግባር ስለሆነ ሕዝቡን ለማዳንና የመረጠውን ንጉሥ ለመታደግ ይመጣል፡፡ እግዚአብሔር በተቆጣ ጊዜ የኃጢአተኞቹንም መሪ ይቀጠቅጣል፤ ተከታዮቹንም አጥፍቶ እርቃኑን ያስቀረዋል(ዕን 312-13)፡፡ ቁጣውን በተለይም ደካሞችን አፍነው በመጨቈን የሚደሰቱት ላይ ይገለጣል፤ በፍላጻዎቹ ይወጋቸዋል(ዕን 314)፡፡ እግዚአብሔር ከግርማው አስፈሪነት የተነሣ በፈረሶቹ ባሕሩን እየረገጠ ሲያልፍ የውሃዎቹ አረፋ ይኩረፈረፋል (ዕን 315)፡፡     

በአጠቃላይ በነቢዩ አገላለጽ እግዚአብሔር ኃያል፣ ተዋጊና በተቀደሰ መቅደሱ የሚኖር እንዲሁም የዓለም ሕዝቦች በፊቱ ጸጥ የሚሉ አምላክ ነው፤ ነገር ግን ይህ አምላክ ትዕግሥተኛና ትዕግሥትን የሚያስተምር አምላክ ነው(ዕን 220)፡፡ ይህንን የእግዚአብሔር ታጋሽነት የተረዳው ነቢዩ ዕንባቆም እግዚአብሔር የሚያስጨንቁንን ሰዎች እስከሚቀጣበት ጊዜ ድረስ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ ይላል፡፡ በመቀጠልም ትዕግሥቱ የጸና መሆኑን ሲገልጽ ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣ በወይን ተክል ላይም ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ዛፍም ምንም ፍሬ ባይሰጥ፣ በእርሻዎች ላይ ሰብል ቢጠፋ፣ የበግ መንጋዎች ሁሉ ቢያልቁ፣ በበረት ውስጥ ምንም ከብት ባይገኝ፣ ይህም ሁሉ ቢሆን እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ እርሱ መድኃኒቴ ስለሆነም ሐሤት አደርጋለሁ ይላል(ዕን 317-18)፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነቱ የጸናና በምንም ነገር ሊበገር የማይችል ከመሆኑም በላይ በትዕግሥት የእግዚአብሔርን ምላሽ መጠበቁ ከምንም በላይ ሕይወትን የሚያስገኝለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ ኃይልን ይሰጠኛል፤ እግሮቼንም እንደ ዋልያ እግሮች ያጠነክርልኛል፤ በተራራዎችም ላይ በሰላም እንድመላለስ ያደርገኛል በማለት ያረጋግጣል(ዕን 319)፡፡ 

በአጠቃላይ ነቢዩ ዕንባቆም ንጽሓን ለምን በግፍ አድራጊዎች እንደሚሠቃዩ፣ እግዚአብሔርም ለምን ቁጣውን እንደማያወርድባቸው በጥያቄ መልክ ይገልጻል፤ ቀጥሎም ሁሉም ነገር ጊዜውን ጠብቆ እንደሚከናወንና እግዚአብሔርም የጻድቃን መጠለያ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ 

         የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

 የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

  1. የነቢዩ ናሆም ሕይወት፣ የመጽሐፉ ጥንቅር፣ ይዘትና ዋና መልእክት በተመለከተ ትክክለኛው የትኛውን ነው?

ሀ) የናሆም ቤተሰባዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል መጽሐፉ በቂ መረጃ ይሰጣል፡፡ ለ) መጽሐፉ የአሦራውያን ዋና ከተማ ስለነበረችው ስለ ነነዌ መደምሰስ የቀረበ የደስታ ቅኔ ነው፡፡ ሐ)እግዚአብሔር ተቀናቃኞቹን የሚታገሥ፣ ጠላቶቹንና የሚቃወሙትን ሁሉ ከመቅጣት የዘገየ አምላክ ነው፡፡ መ) ነነዌ ከተማ በዘረፋና በቅሚያ ሀብት የበለጸገች ከዝሙት ኃጢአት ግን የራቀች ነበረች፡፡ ሠ) መጽሐፉ በግጥም መልክ የተጻፈ ቢሆንም አንባቢን የሚስብ አይደለም፡፡

  1. ከሚከተሉት ውስጥ የነቢዩ ናሆም የትንቢት ቃል በተመለከተ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?(ይህንን ለመመለስ ትንቢተ ናሆም ሦስቱም ምዕራፎች ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

ሀ) እግዚአብሔር በሚገለጥበት ጊዜ ምድር ትናወጣለች፤ ዓለምና በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራሉ፡፡ ለ) በነነዌ ከተማ ውድቀት ጊዜ የነነዌ ሕዝብ ከከተማዪቱ ጥርግርግ ብለው ይወጣሉ፤ ቁሙ ! ቁሙ ! እያሉ ቢጠሩአቸው ግን ወደ ኋላ ይመለሳሉ፡፡ ሐ) ነነዌ ምንም ያህል ብትጠነቀቅም በእሳት መቃጠልዋና በሰይፍ መመተርዋ አይቀርም፤ በአንበጣ እንደተበላ ሰብል ትጠፋለች፡፡ መ) የነነዌ ወታደሮች ሁሉ እንደ ሴት ጀግኖች ሆነው አገራቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ሠ) የአሦር ንጉሥ ሹማምንቶች ጸንተው ይቆማሉ፤ አንዳንዶችም ከጦርነት ይድናሉ፤ መሸሸጊያም ያገኛሉ፡፡

  1. የነቢዩ ዕንባቆም ሕይወት፣ የመጽሐፉ ጥንቅርና ይዘት በተመለከተ ትክክለኛ የሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ) ዕንባቆም ከየትኛው አካባቢና ከየትኛው ወገን እንዲሁም ከየትኛው ቤተሰብ እንደተገኘ መጽሐፉ በቂ መረጃ ይሰጣል፡፡ ለ)መጽሐፉ ውስጥ ዕንባቆም ነቢይ እንደሆነ የሚገልጽ ምንም ፍንጭ የለም፡፡ ሐ) ዕንባቆም ለጠየቀው ጥያቄ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምላሽ ለማግኘት ትዕግሥት የለሽ ሆኖ በመጠበቅ የኖረ ነቢይ ነው፡፡ መ)መጽሐፉ የጊዜው ወቅታዊ የሆኑ ነገሮች በምሳሌያዊ አነጋገሮች ተጠቅሞ ብዙ መልእክቶች በሚያስተላልፍ መልኩ የተጠናቀረ ነው፡፡ ሠ) ዕንባቆም ያየውን ራእይ በጽሑፍ ከማስፈር የሚቆጠብ ነቢይ ነበር፡፡

  1. ነቢዩ ዕንባቆም በኃጢአተኞች ላይ ስለሚመጣው ቅጣት፣ ስለ ጻድቅ ሕይወትና ስለ እግዚአብሔር ማንነትና አሠራር ከሚገልጸው ውስጥ ትክክለኛ የሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ)ነቢዩ ዕንባቆም እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንዲቀጣቸው አይፈልግም፡፡ ለ)ከእግዚአብሔር ከሚወረወሩት ፍላጻዎቹ ብልጭታና ከሚያብረቀርቀው ጦሩ ነጸብራቅ የተነሣ ፀሐይና ጨረቃ ወደ መሬት ይወድቃሉ፡፡ ሐ)እግዚአብሔር ግርማው ያስፈራል፤ በፈረሶቹ ባሕሩን እየረገጠ ያሲያልፍ ውሃዎቹ ጸጥ ይላሉ፡፡ መ)ኃጢአተኞች ብዙ ክፋት ያደርጋሉ፤ በደጋግ ሰዎች ሕይወት ላይ ግን ጣልቃ አይገቡም፡፡ሠ)እንደ ዕንባቆም አገላለጽ ሁሉም ነገር ጊዜውን ጠብቆ ይከናወናል፤ እግዚአብሔርም የጻድቃን መጠለያ ይሆናል፡፡

  1. ነቢዩ ዕንባቆም አጠር ባለ መልኩ “ልቡ የሚታበይ ዐመፀኛ” ምን ሊሆን እንደሚችል፣ በአንጻሩ ደግሞ “ጻድቅ ሰው” ምን ሊያገኝ እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ይህ አገላለጽ ምን የሚል ነው? በየትኛው ምዕራፍና ቁጥር ላይ ይገኛል፡፡
  2. ትንቢተ ዕንባቆም 3፡ 17-18 ላይ “ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፤ የወይን ተክል ላይም ፍሬ ባይገኝ፤ የወይራ ዘፍም ምንም ፍሬ ባይሰጥ፤ በእርሻዎች ላይ ሰብል ቢጠፋ፤ የበግ መንጋዎች ሁሉ ቢያልቁ፤ በበረት ውስጥ ምንም ከብት ባይገኝ፤ ይህም ሁሉ ቢሆን እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ እርሱ መድኃኒቴ ስለሆነም ሐሤት አደርጋለሁ” ይላል፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው ሀብትና ንብረቱ በሙሉ በሰው ሠራሽ ወይም በተፈጥሮ አደጋ ቢጠፋ በእግዚአብሔር ደስ ብሎት ሕይወቱን እንደሚቀጥል ይናገራል፡፡

-    ዕንባቆም በዚህ ሁሉ መከራና ሥቃይ ውስጥ ቢሆንም “በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል” የሚለው ለምን ይመስልሃል⁄ይመስልሻል? የደስታው ምክንያት ምንድን ነው? ወይም ደስ ይለኛል ሲል ምን ማለቱ ነው?

-    በእውነቱ እኛስ በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ሰዎች ነንና ምላሻችን ምን ይሆን ነበር? ለምን?