እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፴፮ - የአዲስ ኪዳን መግቢያ - 1

ክፍል አራት- ትምህርት ሠላሳ ስድስት (36)

የአዲስ ኪዳን መግቢያ - 1


Addis Kidan Megbia 1          አዲስ ኪዳን ሲባል ምን ማለት ነው? ለምን አዲስ ተባለ?

መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ እና አዲስ ኪዳን በሚል በሁለት ትልልቅ ክፍሎች የተመደበ ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ወይም የመጀመሪያው ኪዳን እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ በሙሴ አማካይነት የሰጣቸው ቃል ኪዳን ያመለክታል(ዘጸ 20፡ 1-17፤ 34፡ 28፤ ዘዳ 4፡ 13)፡፡ ሕዝቡ እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ሲሉ ሙሴ መሥዋዕትን ሠውቶ ደሙን በሕዝብ ላይ በመርጨት ቃል ኪዳኑን ያጸና ነበር(ዘጸ 24፡ 1-8)፡፡ ቃል ኪዳኑም እንዲፈጸም ትእዛዝ ሥርዓትና ፍርድ ተሰጡ(ዘዳ 5፡ 31)፡፡ በአጠቃላይ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከክርስቶስ በፊት የተጻፉ፣ እስራኤላውያን የተቀበሉዋቸው፣ በክርስቶስም የጸደቁ ቅዱሳት መጽሐፍት በአንድነት “ብሉይ ኪዳን” ይባላሉ(2 ቆሮ 3፡ 14)፡፡ ብሉይ ኪዳን “አሮጌው ኪዳን” በመባልም ይታወቃል፤ አሮጌ የተባለውም እንደ ግርዘትና የመንጻ ሥርዓት ያሉት በብሉይ ኪዳን ልዩ ትኩረት ይሰጣቸው የነበሩ የቀድሞ ልማዶች ብዙ ትኩረት እንደማይሰጣቸውና እነርሱን የሚተካና የጽድቅ መንገድ የሚያሳይ አዲስ በር መከፈቱን ለመግለጽ ነው፡፡  

አዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን የተተነበየ(ኤር 31፡ 31-34) እና ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ ያቆመው ቃል ኪዳን ነው(ሉቃ 22፡ 31-34)፡፡ አዲስ ኪዳን ብሉይ ኪዳንን ፍጹም አድርጎታል፤ በአሮጌው ፈንታ አዲሱ ተተክቶአል(ዕብ 8፡ 13)፡፡ አዲስ ኪዳን የጽድቅ  መንገድ የሚያሳይና ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር የሕይወት ቃል ነው፡፡ አዲስ ኪዳን የጌታችን ኢየሱስ ከክርስቶስ የትውልድ ሐረግ ጀምሮ፣ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ያስተማረውና ያደረጋቸው የማዳን ሥራዎች፣ ሕማማቱ፣ ሞቱና ትንሣኤው አካትቶ የያዘ ቅዱስ ቃል ነው፡፡ ይህ ቃል ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በነበሩት ሐዋርያት የተጻፈ ነው፡፡ ሐዋርያትም ከክርስቶስ ጋር አብረውት የተጓዙ፣ ተአምራቱን ያዩ፣ ሕማማቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤውና ዕርገቱን የተመለከቱ ናቸው፡፡ በእርግጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ከኢየሱስ ዕርገት በኋላ የተገኘ ሐዋርያ ነው፡፡ ቢሆንም እንኳ ያስተማረውና የጻፈው ከሰው ሳይሆን ከክርስቶስ ወንጌልን ተቀብሎ እንደሆነ ራሱ ይናገራል(ገላ 1፡ 11-17)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በብዙ ቦታ እያስተማረና ቤተ ክርስቲያናት እየመሠረተ ብዙ መልእክቶች እንደጻፈ ይታወቃል፡፡

አዲስ ኪዳን ሲባል አሮጌው ወይም ብሉይ ኪዳን ሙሉ በሙሉ ተሻረ ማለት ነውን?

ኢየሱስ ሲያስተምር “የሙሴን ሕግና የነቢያትን ትምህርት ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ እኔ ፍጹም እንዲሆኑ ላደርጋቸው መጣሁ እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም” አለ(ማቴ 5፡ 17)፡፡ አዲስ ኪዳን በምንልበት ጊዜ አሮጌው ኪዳን ሙሉ በሙሉ ተተወ ማለት አይደለም፡፡ ኢየሱስ ራሱ “ከሙሴ ሕግ ወይም ከኦሪት መጽሐፍት፣ ከነቢያት መጽሐፍትና ከመዝሙረ ዳዊት እየጠቀሰ ያስተምር ነበር(ሉቃ 24፡ 27፡ 44)፡፡ ዛሬም ቢሆን በአምልኮ ሥርዓት በተለይም በቅዳሴ ጊዜ እንዲሁም በተለያየ የጸሎት ጊዜያት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ይነበባል፤ በውስጣቸው ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ትምህርት ስለያዙም ከአዲሱ ኪዳን ጐን ለጐን ተቀምጦ ትምህርት ይሰጥበታል፤ ለተለያዩ መንፈሳዊ ንባባትም ይውላል፡፡ ስለዚህ አሮጌው ወይም ብሉይ ኪዳን ሙሉ በሙሉ በአዲሱ ተተካ ወይም ተሻረ ማለት አይቻልም፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ብሉይ ኪዳን ፍጻሜውን ያገኘው በአዲሱ ኪዳን ነው፡፡

አዲስ ኪዳን የተጻፈው ለምንድን ነው? በየትኛው ቋንቋና መቼ ተጻፈ?

          አዲስ ኪዳን የተጻፈው በግሪክ ቋንቋ ነው፤ ምክንያቱም በወቅቱ የግሪክ ቋንቋ ቀድሞ በታላቁ እስክንድር ጊዜ ተስፋፍቶ(ከ 333 ዓ.ዓ. ጀምሮ) በብዙዎች ዘንድ በስፋት ይነገር ስለነበር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በዕብራይስጥና በአራማይስጥ ቋንቋ ይናገር እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ከኢየሱስ ጋር አብረው የነበሩት ሐዋርያት ከኢየሱስ ዕርገት በኋላ በጰራቅሊጦስ ቀን መንፈስ ቅዱስ ተቀብለው በዓለም ሁሉ እየሄዱ ማስተማር ጀመሩ፡፡ ብዙዎችም በመሥዋዕትነት ሕይወታቸው አለፈ፤ ሕይወታቸው በተለያየ ምክንያት በተለይም በስደትና በግድያ እያለፈ ስለነበር ከእነዚህ ሐዋርያቶች መካከል የተወሰኑት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ታግዘው ያዩትንና የሰሙትን እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር የኖሩትን ለመጻፍ ወሰኑ፡፡ የሚጽፉትም ለመጪው ትውልድ በማሰብ ነው፤ ይህም መጪው ትውልድ ኢየሱስ መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አውቆ፣ ለምን ወደዚህች ዓለም እንደመጣ ተገንዝቦ፣ የማዳን ሥራውን ተረድቶ፣ ንስሓ ገብቶ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ፣ የዘላለማዊ ሕይወት ጉዞው እንዲጀምር በማሰብ ነው፡፡

          አዲስ ኪዳን ውስጥ የተካተቱት መጽሐፍት የተጻፉት ከ50 ዓ.ም. እስከ 150 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ ወቅት ሮማውያን ኃያላን የነበሩበትና አውሮፓን፣ መካከለኛው ምሥራቅን ትንሽዋ እስያንና የተወሰኑት የአፍሪካ አገራት ላይ መዋቅራቸውን ዘርግተው የሚመሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በመሆኑም አዲስ ኪዳን ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የእነርሱ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተጽእኖ ሲንጸባረቅ ይታያል፡፡ ለምሳሌ በኢየሱስ የፍርድ ወቅት የሚከናወኑ ነገሮች ላይ የእነ ጲላጦስና ሮማውያን ወታደሮች ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል(ዮሐ 19)፡፡

          አዲስ ኪዳን የተጻፈው በግሪክ ቋንቋ ሆኖ የሮማውያን ተጽእኖ ይኑረው እንጂ አብዛኛውን ክፍሉ መሠረት ያደረገው የአይሁዳውያንን ባህል፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የቀድሞ የአይሁዳውያን የእምነት ድርጊቶችን በተለይም ብሉይ ኪዳንን ነው፡፡ በእርግጥ በተወሰነ መልኩ የግሪክና የሮማውያን ባህልና ማኅበራዊ ሕይወት ያንጸባርቃል፡፡ ኢየሱስ ተወልዶ ያደገው በአይሁዳውያን ባህል ውስጥ ስለሆነ ሲያስተምርም የአይሁዳውያን ዕለታዊ አኗኗር እያገናዘበና ምሳሌዎችንም ከእነርሱ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ እየወሰደ ነበር፡፡ ወደ እነርሱ ምኵራብ(የጸሎት ቦታ) እየሄደም ያስተምር ነበር(ሉቃ 4፡ 16፤ 6፡ 6)፡፡

            የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ሃያ ሰባት (27) መሆናቸው የተወሰነው እንዴት፣ መቼና በማን ነው?

          ከመጀመሪያ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በአይሁዳውያን ዘንድ የነበሩትን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ተቀበለች፤ ቀጥላም በመንፈስ ቅዱስ እገዛ በሐዋርያት የተጻፉትን መጽሐፍት ሰብስባ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀበለቻቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ መስፈርቶች በመጠቀም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሐዋርያት የተጻፉት መጽሐፍት ለይታ መጠቀም ጀመረች፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍለ ዘመናት ብዙ መጽሐፍት ተገኝተው ነበር፤ እነዚህ መጽሐፍት በሐዋርያት የተጻፉ አስመስለው የተለያዩ ሰዎች ስም ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ታግዛ ጥበብ በተሞላበት መልኩ ሃያ ሰባቱ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ለየቻቸው፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ አትናቴዎስ በ367 ዓ.ም. በጻፈው መልእክት የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ሃያ ሰባት ብቻ መሆናቸውን ገለጸ፡፡ ቀጥሎም በ397 ዓ.ም. በሰሜን አፍሪካ በካርቴጅ(በቱኒዚያ) የተደረገው ሲኖዶስ ሃያ ሰባቱን መጽሐፍት አጸደቀ፡፡ እነዚህም በአራቱ ወንጌላውያን የተጻፉ አራት ወንጌል፣ የሐዋርያት ሥራ የሚገልጽ አንድ መጽሐፍ፣ ዐሥራ ሦስት የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቶች፣ ወደ ዕብራውያን ሰዎች የተላከ መልእክት፣ የጴጥሮስ(ሁለት መልእክቶች)፣ የዮሐንስ(ሦስት መልእክቶች)፣ የያዕቆብና የይሁዳ መልእክቶች እና የዮሐንስ ራእይ ናቸው፡፡ ከዚህ ትንታኔ ጠቅላላ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ቁጥር ሃያ ሰባት መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ከዚህ ውጭ የተለያዩ መጽሐፍት ነበሩ፤ ለመጥቀስ ያህል የይሁዳ ወንጌል፣ የጴጥሮስ ወንጌል፣ የማርያም ወንጌል፣ የያዕቆብ ወንጌልና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ መጽሐፍት በደንብ አድርጋ ካጤነቻቸው በኋላ ወደ ጐን በመተው በሌላ መልኩ እንዲቀመጡ አደረገቻቸው፡፡ ይህም ያደረገችው በቂ የሆኑ ምክንያቶች ስላሉዋት ነው፡፡

ቅዱሳት መጽሐፍት በተለያየ ክፍል የተከፈሉ ናቸው፤ ነገር ግን በ1228 ዓ.ም. በምዕራፍ እንደዚሁም በ1551 ዓ.ም. ደግሞ በቁጥር ተከፋፍሎ በቀላሉ ለመጠቀመ በሚያመች መልኩ ተዘጋጀ፡፡ ይህ በምዕራፍና በቁጥር የተከፈለው እስከ ዛሬም ድረስ እየተጠቀምንበት ነው፡፡ ይህንን መሠረት መባድረግ መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ “የማቴዎስ ወንጌል….ምዕራፍ 5…ቁጥር 17 እያልን እንጠቀምበታለን፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት