እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፴፮ - የአዲስ ኪዳን መግቢያ - 2

New Testament p2ወንጌል የሚለው ቃል አመጣጡ እንዴት ነው? ትርጓሜውስ እንዴት ይገለጻል?

ወንጌል የሚለው ቃል “ዩአጌሊዮን” ወይም “ኧዩአጌሊዮን” ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ነው፡፡ ቃሉም “ኧዩ” እና “አጌሎ” የሚሉት የሁለት ቃላት ጥምረት ነው፡፡ “ኧዩ” መልካም ወይም “ጥሩ” ማለት ሲሆን “አጌሎ” ደግሞ “ዜና”፣ “የምሥራች ቃል” ወይም “በወሬ መልክ የሚነገር አንድ ደስ የሚያሰኝ መልእክት” ማለት ነው፡፡ በጥንት ዘመን ይህ ቃል ከጦርነት መልስ የድል ዜና ለሕዝብ ወይም ለአንድ መሪ ለመንገር ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ከጦርነት የድል ዜና ጋር በተያያዘ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ ቃል በመጽሐፈ ሳሙኤል ውስጥ እናገኛዋለን፡፡ የሳዶቅ ልጅ አሒማዓጽ ኢዮአብን እግዚአብሔር ከጠላቶቹ እንዳዳነው የሚገልጠውን ወሬ ይዤ ወደ ንጉሡ ልሩጥ አለው፡፡ ኢዮአብም አይሆንም ! ዛሬ አንተ ይዘኸው የምትሄድ ምንም ዓይነት መልካም ወሬ የለም በማለት መለሰለት(2 ሳሙ 18፡ 19-20)፡፡ ይህ አሒማዓጽ የተባለው መልእክተኛ የንጉሥ ዳዊት ሠራዊት ከነበረበት ጦር ሜዳ መልካም ወሬ መስሎ የታየውን ዜና ወደ ንጉሥ ዳዊት ለማድረስ ይሄድ ዘንድ የጦር አለቃውን ጠየቀ፡፡ በእርግጥ በጦርነቱ የሞተው የራሱን ሠራዊት አደራጅቶ በዳዊት ማለትም በወላጅ አባቱ ላይ እንደ ጠላት ተነሥቶ ይዋጋ የነበረው የዳዊት ልጅ አቤሴሎምን ነው(2 ሳሙ 18፡ 9)፡፡ ስለዚህ ኢዮአብ ሲመልስለት ይዘኸው የምትሄድ ምንም ዓይነት “መልካም ወሬ” የለም አለው፡፡

በብሉይ ኪዳን ውስጥ “ኧዩአጌሊዮን” የሚለው ቃል ቀስ በቀስ ነቢያት መንፈሳዊ መልእክቶችን ወይም የእግዚአብሔርን ቃል ለማስተላለፍ ይጠቀሙበት ጀመር፡፡ ከነቢያት መካከል ነቢዩ ኢሳይያስ በተደጋጋሚ የምሥራቹን ቃል ማብሠር ወይም መንገር የሚለውን ለመግለጽ ተጠቅሞበታል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ኢየሩሳሌም ሆይ ! ከፍ ወዳለው ተራራ ውጪ፤ የምሥራቹን ቃል ዐውጂ፤ የምሥራቹን ቃል አብሥሪ፤ ተናገሪ፤ አትፍሪ እያለ ይናገራል(ኢሳ 40፡ 9)፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ሰላም የሚገኝበትን የምሥራች ቃል የሚያበሥር መልእክተኛ ተራራዎችን አቋርጦ ሲመጣ ማየት እንዴት ደስ ያሰኛል ይላል(ኢሳ 52፡ 7)፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዘማሪው ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ አመስግኑትም፤ የአዳኝነቱን መልካም ዜና በየቀኑ አብሥሩ ይላል(መዝ 96፡ 2)፡፡ በዚህ ዓይነት ቀድሞ የጦርነት ድል ወይም ዜና ለመንገር ይጠቀሙበት የነበረው ቃል በነቢያት ዘመን መሠረቱ ከእግዚአብሔር የሆነ መልካም ዜና ወይም የምሥራች ቃል ለሕዝብ ለመንገር መጠቀም ጀመሩ፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ቃሉ ትርጓሜውንና የሚያስተላልፈው መልእክት እየተቀየረ ሄደ፡፡

በአዲስ ኪዳን ዘመን ይህ ቃል በተለይም በማርቆስ ወንጌልና በሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ በተደጋጋሚ በተለያየ መልኩ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህ ቃል ወንጌል ውስጥ በሰፊው ተጠቅሶ የምናገኘው ጌ.ኢ.ክ ከሚያበሥረው “የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ቃል” ቃል ጋር በተያያዘ መልኩ ነው ፡፡ ይህ የምሥራች ቃል ወይም መልካም ዜና እንደ ብሉይ ኪዳን ዘመን ለነገሥታት ብቻ የሚነገር ሳይሆን በመጀመሪያ ደረጃ ለድኾች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለታሠሩትና ለተጨቈኑት እንዲሁም ለመላው ሕዝብ የሚነገር ሲሆን የሚናገረውም ጌ.ኢ.ክ እንደሆነ ተገልጿል(ማቴ 11፡ 5፤ ሉቃ 4፡ 18)፡፡

ጌ.ኢ.ክ በዚህ ዓለም ተመላልሶ የማዳን ሥራውን ጨርሶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ “መልካም ዜና” ወይም “የምሥራቹ ቃል” የሚለውን ሌላ ተጨማሪ ትርጉም አገኘ፡፡ ይህም ጌ.ኢ.ክ ያደረገውን የማዳን ሥራ ለሕዝብ ማብሠርን የሚመለከት ነው፡፡ ወንጌላውያንም ሆኑ ሌሎች በሐዋርያዊ ሥራ የተሠማሩ አገልጋዮች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን፣ መከራ ተቀብሎ፣ ሞቶ፣ ተቀብሮ ከሞት የተነሣውን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና የሕዝቡ ሁሉ አዳኝ መሆኑን እንደ “መልካም ዜና” ያበሥሩ ጀመር(ማር 1፡ 1፤ ሐዋ 17፡ 3)፡፡ በአጠቃላይ ጌ.ኢ.ክ ወደዚህች ዓለም መምጣቱንና ሕዝብን ለማዳን ሞቶ መነሣቱን እንደ “የምሥራቹ ቃል” አድርገው ሲናገሩ ይህንን ቃል ይጠቀሙ ነበር፡፡

- ወንጌል የሚለው ቃል በሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ውስጥ እንዴት ተገልጾ ይገኛል?

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ቃል በተለያየ መልኩ በተደጋጋሚ ስለ ጌ.ኢ.ክ ሲናገር ተጠቅሞታል፡፡ ለሐዋርያው ጳውሎስ የምሥራቹ ቃል የእግዚአብሔር ልጅ በሰብአዊነቱ በኩል ከዳዊት ዘር መወለዱንና ወደ እኛ ወደ ሰዎች መምጣቱን የሚያበሥር ነው(ሮሜ 1፡ 3)፡፡ ይህንን የምሥራች ቃል የማይቀበሉ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደሆኑ ይቈጠራሉ(ሮሜ 11፡ 28)፡፡ በአጠቃላይ ለሐዋርያው ጳውሎስ የምሥራቹ ቃል ማለት ስለ ኢየሱስ የሚነገረውን ነው(ሮሜ 10፡ 17)፡፡ እንደ አንድ ሐዋርያ ይህንን የምሥራች ቃል እንዲያበሥር ክርስቶስ ልኮታል(1 ቆሮ 1፡ 17)፤ ማብሠር ይችልም ዘንድ ጸጋ ተሰጥቶታል(ሮሜ 15፡ 16)፤ በተሰጠው ጸጋ እየታገዘ ይህንን የምሥራች ቃል በተለያየ ቦታ እየሄደ እንዳበሠረውም ይናገራል(ሮሜ 15፡ 19)፡፡

ስለዚህ ለሐዋርያው ጳውሎስ መልካም ዜና የተባለው ስለ ክርስቶስ ማንነት በተለይም ስለ ትንሣኤው የተነገረውን ሲሆን ይህም ዜና በሁሉም ቦታ፣ ለሁሉም ሕዝብ መበሠር ያለበት የምሥራች ቃል ነው፡፡ ይህ ቃል የሚያምኑትን ሰዎች ሁሉ ማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ኃይል ነው(ሮሜ 1፡ 16)፡፡ በእርግጥ ክርስቶስ ራሱ ለሐዋርያት ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ለሰው ሁሉ ወንጌልን አስተምሩ በማለት ልኮአቸዋል(ማር 16፡ 15)፡፡

- ወንጌል የሚለው ቃል ትርጉም በኋለኞቹ ዘመናት በምን ዓይነት መልኩ መገለጽ ጀመረ?

ከኢየሱስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ዓመት ወንጌል የሚለው ቃል አዲስ መልክና ትርጓሜ መያዝ ጀመረ፡፡ ትርጓሜውም የክርስቶስ የልደት ታሪክ፣ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በተመላለሰበት ጊዜ ያስተማረው ትምህርት፣ ያከናወናቸው ተአምራት፣ ሞቱና ትንሣኤውን እንዲሁም ወደ ሰማይ መውጣቱን የሚገልጽ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ይህ ቃል በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተለያየ ሰዎች ተጻፈ፡፡ ይህንን በጽሑፍ የሰፈረውንና የኢየሱስ ማንነትና ተግባር የሚገልጸውን ቃል “ወንጌል” በሚል መጠርያ ስም ታወቀ፡፡ የተጻፈውም በተለያዩ ወንጌላውያን ሲሆን እነርሱም ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማታዊ ሁኔታ ውስጥ ለነበረው ሕዝብ ያስተማሩት ቃል ነው፡፡ ወንጌላውያን ያበሠሩት የምሥራች ቃል መሠረቱ የጌ.ኢ.ክ ትምህርት፣ ተግባርና የትንሣኤ ነው፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት