ት/ርት ፴፮ - የአዲስ ኪዳን መግቢያ - 3

ለምን አራት ወንጌል አስፈለገ?

New Testament p3ወንጌል አንድ የምሥራች ቃል ከሆነ ለምን በአራት የተለያዩ ወንጌላውያን የተጻፉ አራት የወንጌል ቃል አስፈለገ የሚለው ጥያቄ ይነሣል፡፡ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል የተወሰኑት በተለይም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ በዐይኖቻቸው ያዩትን፣ በጆሮአቸው የሰሙትንና ከኢየሱስ ጋር የኖሩትን ለሌሎች ከማስተማራቸውም በላይ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተደግፈው በጽሑፍ አሰፈሩት፡፡ ምንም እንኳ ወንጌል በመሠረቱ አንድ ቢሆንም እነርሱ የጻፉት የምሥራቹን ቃል በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ወቅታዊ የኑሮ ሁኔታና ችግር ውስጥ ለነበሩት ለተለያየ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ስለነበር በተወሰነ መልኩ ይለያያሉ፡፡

ወንጌላውያኑ ሰብአዊ የዕውቀት ደረጃቸው የተለያየ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ እንደ ደቀ መዝሙር ከኢየሱስ ጋር በነበራቸው ቀረቤታም በተወሰነ መልኩ ይለያይ ነበር፡፡ በመሆኑም በጻፉት የምሥራች ቃል ውስጥ የተለያየ ልዩነቶች ይንጸባረቃሉ፡፡ ለምሳሌ ማቴዎስ ለአይሁድ ክርስቲያኖች ያስተምር ስለነበር ኢየሱስ መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ልዩ ትኩረት በመስጠት ይናገራል፤ ምክንያቱም አይሁዳውያን ከጥንት ጀምሮ መሲሕ ይጠብቁ ስለነበር ኢየሱስ እውነተኛው መሲሕ” መሆኑን በተለያየ ምሳሌ ይገልጽላቸዋል፡፡ ሉቃስ ደግሞ ኢየሱስ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለተገለሉትና ለተናቁት ሰዎች ስለነበረው ርኅራኄና ፍቅር እንዲሁም ስለ ይቅርታና ንስሓ ልዩ ትኩረት በመስጠት ይጽፋል፡፡ ማርቆስ ደግሞ ኢየሱስ በፈሪሳውያን በኩል ስለደረሰበት ተቃውሞ ጎላ አድርጎ ይናገራል፡፡ ዮሐንስ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ደግሞ ኢየሱስ ገና ከቀድሞ ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ በቃል መልክ እንደነበረ፣ አሁን ግን ሥጋ ለብሶ ወደ ወገኖቹ እንደመጣ፣ ወገኖቹ ግን እንዳልተቀበሉት ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ወንጌላውያኑ የምሥራቹን ቃል ሲያስተምሩ በወቅቱ የሚያስተምሩት ሕዝብ ሊረዳው የሚችለው የተለያየ ምሳሌ፣ የቃላትና የቁጥር አጠቃቀም፣ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት፣ የቦታዎችና የጊዜ ዝርዝር፣ የበዓላት አከባበርና የመሳሰሉት በተለያየ መልኩ ስለተጠቀሙ አንዱ ወንጌል ከሌላው በተወሰነ መልኩ ይለያል፡፡ አንዱ ወንጌላዊ ዘርዘር አድርጎ ለሚያስተምረው ማኅበረሰብ የሚናገረው ነገር በሌላ ወንጌላዊ ዘንድ ብዙም ትኩረት ላይሰጠው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ልደትና ጥምቀት በዝርዝር የሚጽፈውን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ አይገኝም፡፡ እንዲሁም ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ የተጠቀሙዋቸው ምሳሌዎች ዮሐንስ ወንጌል ውስጥ አይገኙም፡፡ በእርግጥ ዮሐንስ ለየት ያለ የአነጋገር ዘይቤ፣ የአጻጻፍ ስልትና አቀራረብ ይጠቀም ነበር፡፡

ማቴዎስ ማርቆስና ሉቃስ የጻፉት የምሥራቹ ቃል በብዙ መልኩ ተመሳሳይነት አለው፡፡ ማርቆስ ከሁላቸውም በፊት ወንጌሉን እንደጻፈ ይታመናል፡፡ ማቴዎስና ሉቃስ ደግሞ ከኢየሱስ የሰሙትና ያዩትን፣ ማርቆስ ቀድሞ ከጻፈው የምሥራች ቃል የተወሰነውን በመውሰድና ከሌላ ከአልታወቀ ተጨማሪ ምንጭ ያገኙትን ተጨማሪ መረጃ በማገናዘብና በማመሳከር የየራሳቸውን ወንጌል እንደጻፉ ይታመናል፡፡ ይህ ያልታወቀ ምንጭ የተባለው ኢየሱስ ያስተማረውንና የሠራቸውን ተአምራት በጽሑፍ መልክ ከደቀ መዛሙርት መካከል በአንዱ ወይም ከእነርሱ ውጭ በሆነ ባልታወቀ ሰው የተጻፈ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፤ ሊቃውንት ይህን ያልታወቀ ምንጭኪው ሶርስ”(Q source) ብለው ይጠሩታል ፡፡

በመሆኑም በሦስቱ ወንጌላውያን ዘንድ በቃላት አጠቃቀም፣ በምሳሌዎች አገላለጽ፣ በሚያስተምሩት ትምህርት ይዘት፣ ለኢየሱስ ሥራዎች በሚሰጡት ትኩረት፣ ስለ ደቀ መዛሙርት ማንነትና እምነት ባላቸው አመለካከት እንዲሁም በሌሎች ርዕሶች ላይ ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሦስቱ ወንጌላውያን የጻፉት ወንጌል በሊቃውንት ዘንድበአንድ እይታ የቀረበ የምሥራቹ ቃልወይምሲንኦፕቲክ ጎስፕልበመባል ይጠራሉ፡፡ሲንኦፕቲክየሚለው ቃልሲንእናኦፐቲክየሚሉት የግሪክ ቃላት ጥምረት ነው፤ሲንማለት አንድ ወይም አንድነት ሲሆንኦፕቲክደግሞ እይታ እንደማለት ነው፡፡ ይህም በአንድ እይታየሚለውን ትርጓሜ ይሰጣል፡፡                 

ነገሩን ለማጠቃለል ወንጌል በመሠረቱ አንድ ቢሆንም በተለያዩ ሰዎች በመጻፉ ምክንያት የተወሰኑ ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ ማቴዎስ ያስተማራቸው ማኅበረሰብ ማርቆስ ወይም ሉቃስ ወይም ዮሐንስ ካስተማራቸው የተለዩ ስለነበሩ በተወሰነ ደረጃ ወንጌሉ የተወሰኑ ልዩነቶች ሊታይበት ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ዮሐንስ ያስተማረው ማኅበረሰብ በወቅቱ የነበረበትን ችግር ከሌሎች ማኅበረሰብ የተለየ ስለነበር ወንጌሉ ከሌሎች ለየት ይላል፡፡ በተጨማሪም ምንም እንኳ ወንጌላውያኑ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጻፉት ቢሆንም የተፈጥሮ ዕውቀታቸው እንዲሁም ክርስቶስ በሚያስምርበት ወቅት ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ቀረቤታና ያደረጉትን ጉዞ ወንጌላውያን በጻፉት የወንጌል ቃል ላይ ልዩነት ከመፍጠር አኳያ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በአጠቃላይ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በነበሩት ሠላሳና አርባ ዓመታት ውስጥ በተለያየ ቦታ ለተለያየ የክርስቲያን ማኅበረሰብ በሐዋርያት አማካይነት ስለ ክርስቶስ ማንነትና የማዳን ተግባር ይሰጥ የነበረውን ትምህርት በጽሑፍ ሰፈረ፤ ወንጌል ወይም የምሥራቹ ቃል ተብሎ ተጠራ፡፡ ወንጌሉም በቤተልሔም ተወልዶ፣ በናዝሬት አድጎ፣ በኢየሩሳሌም ሞቶ የተነሣውንና በቢታንያ ያረገውን .. መሠረት ያደረገ ሆኖ ሰዎችን ወደ እምነትና ደኅንነት የሚመራ የሕይወት ቃል ነው፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ