እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የሕይወት ታሪኩ ምንጭ፣ ትውልዱና ስሙ

 

የቅዱስ ጳውሎስ የሕይወት ታሪክ 

 

የቅዱስ ጳውሎስ ታሪክ ምንጭ

 

         ስለ ቅዱስ ጳውሎስ የሕይወት ታሪክ ከሚናገሩ ጽሑፎች የመጀመርያ ቦታ የሚይዙት መልእክቶቹ ሲሆኑ፤ በተለይ ደግሞ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ሁለተኛና የሐዋርያት ሥራ ሰፋ ያለ የሕይወት ታሪኩን ይተርካሉ። የጴጥሮስ መልእክትም ስለ ቅዱስ ጳውሎስ የሕይወት ታሪክ በአጭሩ ይነግረናል። ከዚህ በተረፈ እንደ ምንጭ የምንጠቀመውየአበው ጽሑፎችን ነው ። የቤተ ክርስቲያን አበው የሚባሉት ከሐዋርያት በኋላ የመጡ፣ የሐዋርያት ተማሪዎችና ተከታዮች የነበሩ፣ ወይም ደግሞ ተከታዮቻቸው የነበሩ ናቸው። ብዙ ግምት ባይሰጠውም ግን እንዳለ መታወቅ የሚገባው መጻሕፍተ “አዋልድ” (apocrypha) የሚባል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር ውስጥ የማይገቡ፣ ደራሲዎቹ የማይታወቁ፣ ትምህርቱና ታሪካዊ እውነቱ እስከዚህም የሆኑ መጻሕፍቶች አሉ። በነዚህ ጽሑፎች ውስጥም የጳውሎስ የሕይወት ታሪክ ተጽፎ ይገኛል።

         “የጳውሎስና የቴክላ ገድል” ከአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ነው። የቅዱስ ጳውሎስንና የቅድስት ቴክላን የሕይወት ታሪክና ሥራ ይተርካል። ይህቺ ቴክላ የተባለች ክርስቲያን ሃገሯ ኢቆንያ ሲሆን ጳውሎስ ወደ ኢቆንያ ሲሄድ ወደ ክርስትና እምነትን የተቀበለች ናት። ይህ መጽሐፍ ዋና የሚጠቀስበት ምክንያት ስለ ቅዱስ ጳውሎስ አካላዊ ቁመና ስለሚናገር ነው። እንደዚህ መጽሐፍ አገላለጽ ቅዱስ ጳውሎስ “አጠር ያለ፣  ራሰ በራ . . . ደልዳላ፣ ዓይኖቹ ገባ ያሉ፣ አፍንጫው ትልቅ ግን ግርማ ሞገስ ያለው ነበረ። አንዳንድ ጊዜ ሰው ሆኖ ይታይሃል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መልአክ ይዞ የሚመጣ ይመስላል።”

 

 

ምዕራፍ 1

 

አስተዳደጉ

 

ሀ. ጠርሴስ (ትንሿ ኤስያ)፣ ሃገሩና ትውልዱ

         መቼ ተወለደ? ቀኑን ወሩንና ዓመቱን ልናውቅ አንችልም፣ አንዳንድ ከሚባለው በመነሳት ግን ግምት ሊኖረን ይችላል፣ ወደ ፊልሞና በጻፈው አጭር መልእክት (ፊሊሞ.9) “እኔ ሽማግሌው ጳውሎስ …” ይላል፤ በሐዋርያት ሥራ 7፤58 ላይ እንደምናነበው፤ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ ሲገደል “ሳውል የሚባል ጐልማሳ” ልብሳቸውን ይጠብቅ ነበር። ስለዚህ ከኢየሱስ ልደት ጥቂት ዓመታት በኋላ የተወለደ ይመስላል።

         ኢየሱስ በ748 ዓ.ዓ. ከተወለደ፤ በልምድ እንደሚታወቀው (1 ዓ.ም.) 6 ዓመት አስቀድሞ  እንደሆነ ማሰብ አለብን። ስለዚህ ጳውሎስ ከ5 በማያንስ ከ8 በማይበልጥ ዓመት ያንሰዋል ማለት ነው። በኋላ በተደረገው የዓመቶች አቆጣጠር ጥናት እንደሚያመለክተው፤ የ5/6 ዓመት ስሕተት ስለተገኘበት፣ የኢየሱስ ልደት በተለምዶ 1 ዓ.ም. የሚባለው 5/6 ዓመት መቅደም እንደነበረበት ተገመተ።

 

ስሙ ጳውሎስ ነው ወይስ ሳውል?

         በሐዋርያት ሥራ በተደጋጋሚ ሳውል በመባል ነው በተደጋጋሚ የሚጠራው። ጳውሎስ ተብሎ መጠራት የሚጀምረው ቆጵሮስ ደሴት ከደረሰ በኋላ ነው። (የሐዋ. 13፤9) ሳውል የሚለው ስም እንደ እስራኤላዊ መጠን ትልልቅ እስራኤላውያንን የሚያስታውስ ስም ነው። ስለዚህ ወላጆች ያወጡለት ስም ነው ሊባል ይችላል። ታዲያ ጳውሎስ የሚለው ስም ከየት የመጣ ነው? ለምንስ በሱ ተጠራ? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ የግድ ነው። አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚያስቡት ከሆነ፤ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለ ሮማዊ ሹምን ሰብኮ ወደ ክርስትና እምነት እንዲመጣ ስላደረገው ሳይሆን አይቀርም፤ አንዳዶቹ ደግሞ የታወቀ ሓዋርያና ደልዳላ ሰውነት፣ ማለት አጠር ያለ ስለነበር እንደ መለያ ተብሎ የተሰጠው ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አሉ። በዚህም በዚያ በሁለት ስም መጠራቱ፤ በሁለት ስም መጠራት መቻል እንደ ልምድ የተወሰደ ይመስላል። በተለይ ጳውሎስን ከተመለከትን፣ ሳውል የሚለው ስሙ አይሁዳዊ ማንነቱን የሚያሳይ፤ ጳውሎስ የሚለው ደግሞ ሮማዊ ዜግነቱ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

         የወላጆቹን ስም ባናውቀውም እንኳ የአይሁድ እምነት የሚከተሉ እስራኤላውያን እንደነበሩ የሚያጠያይቅ አይደለም። ይቺ ቤተሰብ የአይሁድን እምነት ትምህርት ቃል በቃሉ በመፈጸሟ የምትመካ፣ ከገሊላ ወገን  የሆነች ፈሪሳዊት ትሁን እንጂ (ፊልጵ.3፤5-6)፣ ጳውሎስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ከአባቱ የወረሰው ሮማዊ ዜግነት ነበረው (የሐዋ. 16፤37-39,25፤10-12)። በዚህ ምክንያት ጳውሎስ ተከሶ በሮማውያን ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ፤ “ይግባኝ” በማለት በቀጥታ በሮማዊ ንጉሠ ነገሥት እንዲዳኝ ጠየቀ፤ ተፈቀደለትም (የሐዋ. 25፤1-2)። ሌሎች ክርስትያኖችም ይህንን እድል ተጠቅመውበታል። (የትንሹ ፕልንዩስ መልእክት ወደ ትራያኑስ ቁ.10፤96 ተመልከት)። ይህቺ መልእክት በሁለተኛው ክፍለዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፈች ናት።

         ጳውሎስ የተወለደበት ቦታ ጠርሴስ ይባላል። በዚያን ጊዜ በኪልቅያ ክፍለሃገር (ትንሿ እስያ) በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በቱርክ ደቡባዊ ምስራቅ ማለት ነው (የሐዋ. 9፤11,21፤39,22፤3 ተመልከት)። ቅዱስ ሄሬኒሞስ እንደሚለው ከሆነ ጳውሎስ የተወለደበት ቦታ “ጊስሐላ” (Giscala) የሚባል በገሊላ (እስራኤል) አካባቢ የሚገኝ የማይታወቅ ቦታ ነው። ይህ ግን ምን ላይ ተመርኵሶ እንዳለው የሚያስረዳ ነገር የለም። ስለዚ እሱ የሚለውን እንደ መነሻ ነጥብ ተወስዶ፣ እንዲሁም ትውፊት የሚለውን ተመክተህ ጳውሎስ የተወለደበት ቦታ ጠርሴስ እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም።

         ጳውሎስ የልጅነቱንና የወጣትነቱን ግዜ ያሳለፈው በጠርሴስ ነው። ስለዚ ጳውሎስ በግሪካዊ (hellenistic) ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ሥነ ስርዓትና ልምድ ተከቦ ያደገ እስራኤላዊ ነው። በዚያን ጊዜ ይህቺ ከተማ ዋናና አስፈላጊ ከተማ ነው የነበረችው። ምክንያቱም የምዕራብና የምስራቅ ባህልና ንግድ የሚገናኙባት፣ ሁለቱም ነገር የሚታዩባት ሆና ስለተገኘች ነው። ስትራቦነ የሚባል ግሪካዊ ደራሲ ጠርሴስ በፍልስፍና ሆነ በአጠቃላይ እውቀት እነ አቴንስ ከመሳሰሉ ከተሞች ጋር የምትወዳደር የታወቀች ከተማ እንደነበረች በጽሑፉ ያትታል። የስቶይክ ፊሎዞፊ ይከተሉ የነበሩ ፈላሶፎች መንበር የነበረች ከተማ ናት። “ሞራላዊ ሕሊና፣ ባሕሪ፣ ነጻነት” የሚሉ ቃላት፣ አምላክን በሥራዎቹ ማወቅ (ሮሜ 1፤20)፣ “ያልተጻፈ ሕግ” (ሮሜ 2፤14)፣ እንዲሁም “ባሕርይ” ወይም “ተፈጥሮ” እንደ መሪና መማርያ (1ቆሮ.11፤14)፣ ይህንና ይህንን የሚመለክቱ ሐሳቦች በጊዜው ከነበረው የፍልስፍና ሐሳብ የወሰደው ነው።

         ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቶቹ ውስጥ የሚሰጣቸው ምሳሌዎች አስተዳደጉ እንዴት እንደነበረ የሚያመለክት ነው። የሩጫ ተወዳዳሪዎች የሚያደርጉት ልምምድ (1ቆሮ.9፤24…)፣ የቦክስ ውድድር (1ቆሮ.9፤26)፣ የነበረበትን ግሪካዊ ዓለም ሲያመለክት ደግሞ የአራዊት ትርኢት (1ቆሮ.15፤32)፤ በሌላ ቦታ ደግሞ ያልቦካ የፋሲካ ዳቦ (1ቆሮ.5፤7)፣ የሚያበራየውን በሬ አፉን ማሰር እንደማይገባ (1ቆሮ.9፤9)፣ እንዲሁም “አባባ” እያለ የሚጠራ ልጅ (ሮሜ.8፤15፣ገላ.4፤6)… ይሄ ሁሉ የብሉይ ኪዳን ዕብራዊ ባህልንና አካሄድን ያመለክታል። ጳውሎስ በዚ ሁሉ እንዳለፈ የሚያስረዳ ነው። የጠርሴስ ከትማ ምሥራቃዊ ባህልና ልምድ በብዛት የነበረባት እንደነበረች ግልጽ ነው። ጳውሎስ ሴቶችን በጉባኤ ጊዜ መሸፈን እንዳለባቸው አደራ ሲል (1ቆሮ.11፤2-16)፣ በልጅነቱ በጠርሴስ ከተማ ያየውን ጥሩ ልምድ በማስታወስ እንጂ በግሪክስ (ቆሮንቶስ የምትገኝበት) መሸፈን ወይም አለመሸፈን ያህን ያህል አስፈላጊ አልነበረም።

         ሃይማኖትንም በሚመለከት ጠርሴስ ወደ ምሥራቅ ያዘነበለች ናት። ምሥራቃዊ አረማዊ ባህሎችና ጣዖቶች ይዘወተርባት ነበር። በምሥራቃዊ የሮም ግዛት “አምልኮ ቄሳር” የሚል በጣም ተጋኖ ነበር። ይህ ልምድ ቄሳር በሕይወቱ እያለ እንደ መለኮት የሚመለከት፤ እስከ “አዳኝ” ድረስ የሚቆጥር የነበረ አስተሳሰብ ነው። በዮሐንስ ራእይ ላይ በደንብ ተብራርቶ ይገኛል። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መልእክቱ (3፤20) ሃገራችን በሰማያት እንደሆነ፣ እንደ አዳኝ ደግሞ እየሱስን እንደምንጠብቅ ሲያመልክት ይህንን የተሳሳት ልማድ (አምልኮ ቄሳር) በመቃወም ይመስላል። 

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት