የቅዱስ ጳውሎስ ማንነነት (ስብእናው)

ማንነቱ

ሀ. የጳውሎስ ስብእናና ሥነ ልቦናዊ መልኩ

ከዚህ ሁሉ አስትንትኖ በኋላ ስለ ሐዋርያው ጳውሎስ ማንነትና ሰብአዊ ሁኔታን ማየት ግድ ይሆንብናል። ይህ የጳውሎስ ስብእና (personality) በጣም የበረታና የተለያየ ዓይነት ቀለም የሚያሳየን ቢሆንም እንኳ ምን ዓይነት እንደሆነ ልናነበው እንችላለን። የአንድ ጸሐፊን ስብእና ማወቁ ጽሑፉን ለመረዳት ጥሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። የእሱ ክርስቶስን ማግኘት፣ ወይም ደግሞ ራሱ እንደሚለው የእሱ በክርስቶስ መገኘት፤ ዝንባሌዎቹን፣ ጠባዮቹንና ስሜቶቹን ሁሉ አንድ የሚያደርግ፤ የሚያዋህድ ክስተት ሆኖ እናገኘዋለን። የጳውሎስን “መታወቂያ” በፊልጵ.3፤5-7 ውስጥ እናገኘዋለን። ስለ ስሜቶቹን ተናገር፤ ሳውል የነበረው ጳውሎስ መሠረታዊ ማንነቱ አልተቀየረም፤ ለምሳሌ በእግዚአብሔር ታግዞ ኃይሉና ዓላማው ሁሉ ወደ አንድ ዓላማ ብቻ እንደሚያተኩር አደረገው እንጂ ኃይለኛ ጠባዩን አልተወም፤ አልጣለውም። በክርስቶስ ከተማረከ በኋላ፤ አሁን እሱ ራሱ ክርስቶስን ሊማርክ (ፊልጵ.3፤8) ይሞክራል።

የሰው ልጅ የደስታውና የሰላሙ ምሥጢር እዚህ ላይ ነው ያለው - ማለት ሕይወትህን የሚሸከም መሠረት፣ ወይ ደግሞ ሁሉንም የሕይወትህን ጎኖች በአንድ የሚያስርና የሚጠምር አንድ ዓላማ ሲኖርህ።

ጳውሎስ የፍላጎት ኃይል የነበረው ሰው ነው። በደማስቆ መንገድ ላይ ሰውነቱ በከባድ ፈተና ላይ ወድቆ ነበር። እዚህ ደግሞ የጳውሎስ ቅንነት በግልጽ ታየ። ብቅኑ መንፈስ ያገለግል ነበር። እውነት ስትገለጽለት ወዲውኑ መንገዱን ቀየረ። ያ የነበረው የፍላጎት-ኃይል ከተቃዋሚዎቹ ጋር ሲከርከር በግልጽ ይታያል። በጥላቻ ሳይሆን፤ በእውነተኛ ፍቅር ስለ እውነት ያደረገው የነበረ ነው። “ከእግዲህ ውዲ በሰዎች ሽንገላና በአታላይነት ተንኰል በተዘጋጀ በአሳሳች የትምህርት ነፋስና ወዲያና ወዲህ እንደሚወሰዱ ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን ራስ የሆነውን ክርስቶስን ለመምሰል በሁሉ ነገር እናድጋለን” (ኤፌ.4፤14-15)።

በሁለተኛ ደረጃ በጣም ስሜታዊ(ም) ነበር። ይህ ደግሞ ለጥሩም ለመጥፎም ነው። “…ከዚህ ቀደም ክርስቶስን ክርስቶስን የሰደምሁና ያሳደድሁ፣ ያዋረድኩ . . .” (1ጢሞ. 1፤13) በማለት የበፊት ሕይወቱን ይገልጻል። አሁን ጳውሎስ ሐያልነቱን ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲያውለው እንመለከታለን። ከበባድ ፈተናዎችንና ችግሮችን ለመታገስና ለማሸነፍ ካሳየው ጋር የሚመሳከር ነው (2ቆሮ.11፤16…)።

ከጽሑፎቹ እንደምንገነዘበው ጳውሎስ ልዩ የአእምሮ-ችሎታ የነበረው ሰው ነው። እውነትን ፈልገው በቅንነት ከሱ ጋር ይከራከሩ ለነበሩ እንዴት አድርጎ እንደሚመልስላቸው የሚያውቅ፣ የብሉይ ኪዳን ጽሑፎችን በትክክል የሚተረጉም፣ በክርስቶስ እንዴት ፍጻሜ እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ችሎታ ነበረው። ወንጌልን በቃሉ የሚናገር፣ በሥራው የሚያሳይ፣ በወኔ መዝሙሮችንና ቅኔዎችን የሚጽፍ፣ ሐዋርያዊ እቅዶችን የሚያወጣ፣ በተፈጥሮና በጸጋ ልዩ ችሎታ የተሰጠው፣ ሁለቱንም አስማምቶ ወንጌልን ለምስበክና እውነትን ለማገልገል ያዋለ ነው።

በግእዝ ሥርዓተ-ማኅሌት ስለ ዮሐንስ ወንጌላዊ ሲናገር “ዮሐንስ ታኦሎጎስ” “ዮሐንስ አቡቀለምሲስ” እያለ ይጠራዋል። እኛም “ጳውሎስ ታኦሎጎስ” ማለት “የእግዚአብሔር ሥጢር ነጋሪ” የሚያስብለው ነገር እንዳለ እንረዳለን። ሌኣ ሳይሆን ለምሥጢረ ክርስቶስና የእግዚአብሔርን እቅድ ጠለቅ አድርገህ መረዳት ማለት ነው። ይህ ደሞ ጳውሎስ በተሰጠው ጸጋ ሊፈጽመው የቻለው ነገር ነው። ከዚህ ጋር ደግሞ እሱ አእምሮአዊ ችሎታውን፣ የልቡን ስፋት፣ ተቀባይ የሆነ እምነቱን ሲሰራበት ተገኘ። ኢየሱስ ናዝራዊ የተሰቀለ፣ የሞተ፣ የተነሣ፤ እሱ ለብቻው የዓለም አዳኝ ነው። ጳውሎስ ይህንን ነው የሚሰብከው።

ለ. ጳውሎስ በጳውሎስ ዓይን ሲታይ

ለአንድ ሰው የውስጡን የሚያውቀው ከራሱ በላይ ሊኖር አይችልም። ደካማውና ጥሩውን ጎድኑን የሚያውቀው እሱ ነው። ሌላ ሰው የሚሰጠው ግምት ውጫዊ ነው። በዚህ ዓይነት የጳውሎስን እውነተኛ ማንነትና ሁኔታ የሚነግረን፤ ጳውሎስ ስለራሱ ከሚጽፈው በላይ ሌላ ሊኖር አይችልም። እሱ ስለ ራሱ ከሚጽፈው (autobiography) ተራ በተራ ቀጥ ብለን ካነበብነው፤ የጳውሎስ ማንነት ግልጽ ሆኖ ሊታየን ይችላል።

ጳውሎስ ስለ ራሱ ከተናገረበት ገጾች ወይም ጽሑፎች፤ የበለጠችውና አስፈላጊዋ ፊልጵ.3፤1-14 ናት። በዚህ ጽሑፍ እንደምናነበው፤ ጸሐፊው(ጳውሎስ) ሕይወቱን በሦስት ደረጃዎች ከፋፍሎ ያቀርበዋል። ያለፈው ሕይወቱ (3፤4-6)፣ የአሁኑ ሕይወቱ (3፤7-11)፣ የወደፊት ሕይወቱ (3፤12-14)፤ ጳውሎስ ያለፈው ሕይወቱንና አይሁዳዊ ማንነቱን አይክደውም። በተለያየ መልኩ በበለጠ ይዘረዝረዋል እንጂ፤ “እኔ በተወለድሁ በስንተኛው ቀን ተግርዣለሁ፤ በትውልዴም ከብንያም ዘር የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከዚህም በቀር ጥርት ያልሁ ዕብራዊ ነኝ። የአይሁዳውያንን ሕግ ስለሚጠበቅም ቢሆን ፈሪሳዊ ነበርሁ።ስለ ሃይማኖት በመቅናትም ቢሆን፤ በኢየሱስ ክስቶስ የሚያምኑትን የማሳድድ ነበርሁ” (3፤5-6) በማለት ሁኔታውን ይገልጸዋል።

እንደ መኩሼው የመጀመርያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል፤ ጳውሎስም ከብንያም ዘር ነው። ይህ ዘር ለዳዊት ቤት ታማኝ የሆነ፤ በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ክብርን ያገኘ ነው። ጳውሎስም በትውልዱና እንደ ግዜዎቹ ልጆቹና በእግዚአብሔር አምልኮ በጣም አክራሪ ሰው ነው። ዕብራዊ መሆኑን ልክ እንደ ልዩ ዕድል አድርጎ የሚያስብና የሚመካ ነው። እንደ ሌሎቹ ፈሪሳውያን ደግሞ የኦሪትን ሕግ እንደ ጣዖት የሚያመልክ፤ የኦሪት ሕግ ባርያ እስከመሆን የደረሰ ነው።

ህልው ሁኔታዎችን በሚመለከት ጳውሎስ ሲናገር ጳውሎስ ሌላ መመዘኛ ይጠቀማል። እንደ ዋና ነገር አድጎ የሚያስበውና የሚያተኩርበት የነበረው ሁሉ ሲለዋወጥበትና ሲገለባበጥበት የትገኘበት ሁኔታ ነው። “ከዚህ በፊት ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ አምንባቸው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ብዬ ዋጋ እንደሌላቸው ከንቱ ነገሮች አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ” (ፊልጵ.3፤7) በመቀጠል ደግሞ “ከዚህም በቀር ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቅ የበለጠ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ ስለማምን ሁሉን ነገር እንደ ኪሣራ እቆጥራለሁ። ስለ እርሱም ሁሉህ ነገር አጥቻለሁ። ክርስቶስንም ለማግኘት ስል ሁሉን ነገር እንደ ቤት ጥራጊ እቈጥራለሁ።” (ፊልጵ.3፤8) ይላል። እዚህ ላይ ሊስተዋልበት የሚገባው የሕይወትህ ዋነኛ ምሶሶ ማየት ነው። የዚህ ሁሉ መፈለጋችን ዓላማው ምንድነው? ኢየሱስ ዋና ምሶሶና መፈለጋችን ከሆነ፤ ሕይወታችን አዲስ ትርጉምና ዓላማ አለው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለሰብአዊ እድገታችን፣ ክርስቲያናዊ ብስለታችን  በሚሰጠው አበርክቶ ነው የሚመዘነው።

የወደፊቱን በሚመለከት ጳውሎስ በጣም ሩቅ ወዳለው ሳይሆን፤ የወደፊቱን ከአሁኑ (ከህልው) ሁኔታ ጋር በማያያዝ ነው። “ይህን ሁሉ ገና አላገኘሁም፤ ወይም በዚህ ሁሉ ፍጹም ሆኜአልሁ ለማለት አልችልም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ የእርሱ አድርጎ ያዘጋጀልኝን ሽልማት ለማግኘት ወደፊት በመሮጥ እተጋለሁ” (ፊልጵ.3፤12)። ይህንን ሁሉ ስናነብ ሳለን፤ ጳውሎስ የወደፊቱን እየተመለከተ መሆኑን እንመለከተዋለን። የወደፊቱ በእግዚአብሔር ስጦታዎች የተሞላ በእግዚአብሔርምሕረት የማይጎድል ነው።

በሌሎቹ የጳውሎስ መልእክቶች እሱን በሚመለከት ጽሑፎችን አሉ። ይህ ሁሉ ግን የጳውሎስን ማንነትና ውስጣዊና ውጫዊ መንፈሳዊ መልኩን የሚያቀርብልን እንጂ እንደ ታሪክ የሚታይ አይደለም።

ሐ. ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ ዓይን

የሐዋርያትን ሥራ የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ ነው። ሉቃስ ወንጌልን ከጻፈ በኋላ ወዲያውኑ የሐዋርያትን ሥራ እንደጻፈ በሁለቱ መጻሕፎች ያለው ግንኙነትና ቀጣይነት በቂ ማስረጃ ነው። በተጨማሪም ለጳውሎስ ታማኝ ተማሪዎቹና ተባባሪዎቹ ከነበሩት አንዱ ሉቃስ ነው። በአንዳንድ ሐዋርያዊ ጉዞዎቹ ከጳውሎስ ጋር እንደነበረ ግልጽ ነው። እንደ ተከታዩና አጋዡ መጠን የጳውሎስን ስብከቶችና ትምህርት ሰምቶ በልቡ የያዘው፣ ሃብትና ርስት ያደረገው እንደሆነ ነው። ስለዚህ ከጳዎሎስ እግር ሥር ሆኖ ያደገ እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም። ከወንጌል በተጨማሪ ሌላ ጽሑፍ ሊያበረክት መፈለጉ፤ በአንድ በኩል ለስነ ጽሑፍ የሚሆን ይዘት አለው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአስተማሪውን ሥራዎችንና ትምህርትን ለሰሚዎቹ ለማስተላለፈ ስለፈለገ ይመስላል።

ስለዚህ ሉቃስ የሚያቀርብልንን ለየት ያለ የጳውሎስን ሥእል መመልከቱ ያስፈልገናል። ይህ ሥእል ጳውሎስ በመልእክቶቹ ከሚያቀብልን ለየት ያለ፤ ምለት ረጋ ያለ፣ ብዙ ለየት ያሉ ባህሪዎችና ነገሮች የማይታይበት ጳውሎስ ነው የምናየው። ጳውሎስ ሲከራከር የሚያሳየን ሉቃስ፤ የሚደነቅበት አስተማሪው እንደ ሐዋርያው መጠን ፍቅሩን የሚገልጽለት ነው። በሰብአዊነቱ (personality) በጣም የተማረከ ይመስላል። ይህ ለሉቃስ የሚያስደንቀው የጳውሎስ ባሕሪ በዝርዝር ማየቱ ያስፈልጋል።

ጳውሎስ ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ነገሮች አሉት። ይህ ደግሞ በሁለተኛው ክፍል የሐዋርያት ሥራ በጳውሎስ ሐዋርያዊ ጉዞዎች በሚናገር ክፍል ነው። ጳውሎስ ልክ እንደሌሎቹ ሐዋርያት ያየውንና የሰማውን የሚናገር ነው (የሐዋ.22፤15)። እሱ ሌሎቹ ያዩትን ያየ አይደለም (የሐዋ.1፤22)። የጳውሎስን መለወጥ

የሚያመለክተው ግልጸት ከሌሎቹ ግልጸቶች ጋር የተያያዙ ናቸው(የሐዋ.26፤16፣ 1፤3)።

በሁለተኛ ደረጃ በሉቃስ ጽሑፍ ውስጥ የምናገኘው ጳውሎስ፤ በመኳንንትና ባለሥልጣኖች ፊት ቀርቦ የሚናገር የሚያስተምር ነው። በአይሁድ ባለሥልጣኖች ፊት (22፤1)፣ በሮማ ባለሥልጣኖች ፊት (24፤10፣ 25፤10፣…26፤2) ማለት ነው። ይህ ግን በመልክቶቹ ከምናገኘው የጳውሎስ ሥእል የበለጠ ወይም የደከመ ለማለት ሳይሆን፤ በተለያየ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚታይ የጳውሎስ ሁኔታ የሚያመለክት ነው። በጳውሎስ ላይ፣ ከጳውሎስ ጋር፣ ወይም ደግሞ በጳውሎስ አድርጎ ክርስትና ያለፋቸው መንገዶች፤ የእስራኤልንም ድንበሮች ብቻ ሳይሆን፤ የዓለምን ጎዳናዎን ሲያበራና በምሁራኖች መካከል ሊስፋፋ መቻሉ ነው። ይህ የጳውሎስ ትልቁ አበርክቶ ነው። የወንጌል አጻጻፍ አዲስና ለየት ያለ ሲሆን፤ የጳውሎስ መልእክቶች ግን የተለመደውን የአጻጻፍ ስልት ተከትሎ የመጣ ሲሆን፤ እንደ ሥነ ጽሑፍ መጠን ከነ ሴኔካ ላቲናዊ ጽሑፍ የማይተናነስ ነው።

ሉቃስ ጳውሎስን ሲያቀርበው ልክ እንደ አንድ የስበከተ ወንጌል  ምሳሌ የሚቀርብ አድርጎ ነው። ይህ እንዲ ከሆነ ሉቃስ ልክ እንደ ጳውሎስ ስለ ስብከተ ወንጌል ብሎ የደከመ፣ ሥቃይ የተቀበለ ይሆን? እስከ ማለት ሊደረስ የሚችል . . . ባይ ይመስላል።

“አሁንም እዚያ ስደርስ ምን ኣንደሚደርስብኝ ሳላውቅ፤ በመንፈስ ቅዱስ ታዝዤ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዴ ነው። ይሁን እንጂ እስራትና ችግር እንደሚገጥመኝ በየከተማው መንፈስ ቅዱስ ነግሮኛል” (የሐዋ.20፤22-23)

ከሐዋርያት ሥራ የምናገኘው ሌላ ስእል ጳውሎስ ቤተክርስቲያኖችንም መሥራች (plantation ecclesiae) ነው። በአሕዛብ መካከል እልክሃለሁ (22፤21)። ጳውሎስ የቤተክርስቲያንች ተካይና አብቃይ እንጂ የሚያንጽና የሚኰሰኵስ አስተባባሪ ግን አልነበረም። የተከላቸውን ቤተክርስቲያኖች የሚመሯቸው አጋዦቹ ወይም ተማሪዎቹን ሐላፊነት ሰጥቶ ይሄዳል። በመልእክቱ ደግሞ ይከታተላቸዋል።

የጳውሎስ ጥልቅ መንፈሳዊነትና ሐዋርያነት ግልጽ የሚሆንልን፤ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች በሚሌቱስ የተናገረው የመሸኛ ቃል ነው (20፤18-35)። ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሰባኪ ወንጌል እንደነበረ የሚያሳይ ነው። ለጳውሎስ የወንጌል መልእክተኛ መሆን ማለት፤ ከባሪያ ወይም አገልጋይ የማይለይ (1ቆሮ.9፤16-18)፤ ስለ ወንጌል ሁሉንም ፈተዎችን መሸከም፤ ሁሉንም እንደ ኪሣራ አድርጎ ምቁጠር ነው። ዣክ ዲዩፖንት (Jaques Dupont) የተባለ የአዲስ ኪዳን ተመራማሪ እንደሚለው፤ ለኤፊሶን ሰዎች ያደረገው ንግግር የጳውሎስ ሐዋርይዊ አደራ ነው።  የሐዋርያዊ ሥራዎች መመሪያዎች በንግግሩ ላይ ይገኛል። የጳውሎስ መንፈስ ብዙ ሳትሄድ በደንድብ አድርጎ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፤ ለወደፊቱ የወንጌል መልእክተኛና የነፍሳት እረኛ እንዴት መሆን እንዳለበት የሚያመለክት ንድፍ ነው።