እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ጳውሎስና ኢየሩሳሌም፤ ትምህርትና አስተዳደግ፣ የእጅ ጥበብ ሥራ፣ ኑሮና ትዳር

 ለ. ኢየሩሳሌምና፤ ትምህርትና አስተዳደግ

       

  እኔ እስራኤላዊ ነኝ፣
 በኪልቂያ ከተማ በጠርሴስ ተወለድኩ፣ 

 በዚህች ከተማ (ኢየሩሳሌም) አደግኩ 

 በገማልኤል እግር ስር ሆኜ የአባቶቼን ሕግ ተማርኩ። (የሐዋ.22፤3) 

 

 

          ይህ አባባል ስለ ነቢዩ ሙሴ የሚባለውን (የሐዋ.7፤20-22) የሚያንጸባርቅ ነው። ሙሴ በሕጻንነቱ ለሦስት ወር ያህል ከወላጆቹ ጋር እንደነበር፣ የቀረውን የሕይወቱን ግዜ በፈርዖን ልጅ እንደ ግብጻውያን ባህልና ልማድ እንዳደገ ይናገራል። የሐዋ.22፤3 ደግሞ ጳውሎስ በጠርሴስ እንደተወለደ፣ስለ ትምህቱንና አስተዳደጉም ሲናገር በኢየሩሳሌም እንደሆነ ይገልጻል። በኢየሩሳሌም ባለትዳር የሆነች እህት እንደነበረችው የታወቀ ነው (የሐዋ.23፤16)።  

         የሐዋ. 23፤3 የሚለውን ተከትለው ጳውሎስ ሕጻን እያለ ወላጆቹ ጠቅለለው ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱ ይመስላሉ በማለት ግምታቸውን የሚሰጡ አሉ። ይህ ግን ጳውሎስ በጠርሴስ ካላደገ፤ እሱ ላይ የሚታየው ግሪካዊ አስተሳሰብ  ከየት መጣ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ያስቸግራል። ሊሰጥ የሚችለው መልስ ግን፣ የጳውሎስ ግሪካዊ ዕውቀት በልማዳዊ አባባል ላይ የተመርኮዘ እንጂ የግሪክ ትምህርርት ለመማር ወደ ትምህርት ቤት እንዳልሄደ የሚያመለክት ነው። በስብከተ ወንጌሉ ላይም ቢሆን ይህ ግሪካዊ ዝንባሌው በጣም ተጋኖ የሚታይ አይደለም።

         ግሪካዊ የፍልስፍና ትምህርት ሊማር ወይም ሌላ የትምህርት ዓይነትን ለመቅሰም ወደ ትምህርት ቤት ሄዶ የተማረም አይመስልም። አባቱ በፈሪሳዊነቱ የሚመካ እስራኤላዊ ስለነበር ይህንን ነገር ይፈቅዳል ብሎ መገመት አይቻልም። ትንሽ ቆየት ብሎ በጻፋቸው መልእክቶቹ ከአረማውያን ደራሲዎች የተወሰዱ ጥቅሶች እናገኝበታለን።

 
1.   “እኛ ሁላችን የእርሱ ልጆች ነን” (የሐዋ.17፤28) የሚለው ጥቅስ አራቱስ በተባለ አረማዊ ደራሲ ከጻፈው “ፋይኖሜና” ከተባለው መጽሐፉ የተወሰደ ነው።
2.   “መጥፎ ጓደኛ ጥሩውን ጠባይ ያበላሻል” (1ቆሮ.15፤33) የሚለው “ታይስ” ከተባለ መናንደር የሚባል ደራሲ ከጻፈው መጽሐፍ ሳይሆን እንደማይቀር፤ በኋላ ግን እንደ አባባል ሆኖ በማንኛውም ሰው የሚዘወተር የነበረ ንግግር ይመስላል።
3.   “የቀርጤስ ሰዎች ሁል ጊዜ ውሸታሞች፣ ጨካኞች፣ አውሬዎች፣ ሥራ ፈቶችና ሆዳሞች ናቸው።” (ቲቶ1፤12) የሚለው ደግሞ፣ ጳውሎስ አንድ ሰው ከእነሱ እንዳለው ነው የሚጠቅሰው፤ እነዚህ ብቻ ግን  ጳውሎስ ግሪክ ቋንቋ ሊማር ትምህርት ቤት ገብቶ ነበር ለሚለው በቂ መረጃ ሊሆኑ አይችሉም።
4.   “De Mundo” የሚባል ደራሲው ማን እንደሆነ የማይታወቅ መጽሐፍ የሚከተለውን ይላል፦ “ስለ አምላክ ሊባል የሚችለው ይህ ነው፦ በኃይል ካየነው ከሁሉ የበለጠ ኃያል፣ በውበት ካየነው ሁሉ በጣም ቆንጆ፣ በሕይወት ከተመለከትነው በራሱ ሕይወት የሆነ፣ በመንፈሳዊነት ካየነው ፍጽምና በምልአት ያለው፤ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ፣ በግዙፍ ዓይን የማይታይ ሆኖ ሳለ በስራው ግን ይታወቃል፤ይታያል። . . . በምድር ላይና በባሕር ውስጥ ያለ ሁሉ ደግሞ በዓለም ላይ የሚነግሠው አምላክ ሥራ ናቸው። ኤምፔደክሎስ የተባለ ፈላስፋ እንደሚለው ደግሞ፤ ፍጥረት ሁሉ - ያለና የነበረ የሚኖር- ማለት ዛፍ፣ እንስሶች፣ ሰው - የማደግ ኃይልና ችሎታ የሚያገኙት ከእርሱ ነው። (“De Mundo” 399 b)። እንደዚህ ዓይነት ጽሑፍ ስታገኝ ሳለህ፣ ጳውሎስ በአርፋግዮስ ካደረገው ንግግር ጋር (የሐዋ.17፤24-27)፣ እንዲሁም ለልስጥራ ሕዝብ የተናገረው ንግግር (የሐዋ.14፤16-17) በመጨረሻ ደግሞ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ፦ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለሰዎች የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፤ የኸውም ዘላለማዊው ኀይሉና አምላክነቱ እርሱ በፈጠራቸው ነገሮች ግልጥ ሆኖ ታይቶአል፤ ” ካለው ጋር ሲነጻጸር፣ አንድ አይነት መሆኑ በአጋጣሚ የሆነ ነገር ነው ተብሎ የሚታለፍ አይደለም።

በጠርሴስ ከተማ ብዙ አይሁዳውያን ይኖሩ ስለነበር፤ የአባቶቻቸው ሥርዓት በሚያዘው መሠረት ሳውል 6 ዓመት ሲሞላው ወደ “ቤት-ሃ-ሰፈር” (=መጽሐፍ ቤት) እየተባለው በሚጠራው፤ ከምኵራብ አጠገብ ወደሚገኘው ትምህርት ቤት ሄዶ መማር ነበረበት። ወላጆቹ ፈሪሳውያን ስለነበሩ ልጃቸው እንደዚህ አይነት መንፈሳዊ ትምህርትና ትውፊት ሳይማር እንዲቀር ኣይፈልጉም። ስለዚህ በሕጻንነቱ ካጠናው የግሪክ ቋንቋ ጋር የወላጆቹን ቋንቋ- ዕብራይስጥ - እንዲማር ማድረጋቸው የተለመደ ነገር ነው የነበረው። “እኔ በተወለድኩ በስምንተኛው ቀን ተገርዣለሁ፤ በትውልዴም ከብንያም ዘር የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከዚህም በቀር ጥርት ያልሁ ዕብራዊ ነኝ” (ፍሊጵ.3፤5) የሚል ሰው ነው።

ጳውሎስ በተወለደበት ቤተሰብ ውስጥ ጸሎት ይዘወተር እንደነበር የሚያጠራጥር አይደለም። በሕጻንነቱ የለመደው ከምግብ በፊትና ከምግብ በኋላ የሚደገመውን ጸሎት በመልእክቱ አልፎ አልፎ ይደግመዋል (1ቆሮ.10፤30፣ ሮሜ 14፤6፣ 1ጢሞ.3፤4)። ለብዙዎቹ የክርስትና ማኅበሮች ሲጽፍ ደግሞ ስለነሱ ብሎ አምላክን በተደጋጋሚ እንደሚያመሰግን ይናገረል (1ቆሮ.1፤2፣ 2ተሰ.1፤3፣2፤13፣ 1ቆሮ.1፤4፣ ፊልሞ.4፣ ቆላ.1፤3)። የፈሪሳውያን ልጆች ከሕጻንነታቸው ጀምረው በቀን 3ጊዜ መጸልይ ይማሩና ይለማመዱ ነበር።

ጳውሎስ ከወላጆቹ የወረሰው ጸሎትን በሚመለከት ብቻ ሳይሆን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት የሚመራ እምነትም ወርሶዋል። ልክ እንደ አንድ አካል (person) የሚገለጸውን አምላክ አምኖ መቀበል፣ በአምላክ ታላቅ ኃያልነትና ችሎታ መታመን (ሮሜ.9-11)፣ እሱ ከሰዎች የሚፈልገውን ነገር መፈጸም (ሮሜ 1፤18-3፤20)፣ ፈሪሳውያን ይበልጥ የሚታወቁበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ሕግን በደንብ አድርጎ መፈጸም ነው።

በጠርሴስ ይሰጥ የነበረውን የትምህርት ደረጃ ጨርሶ፤ “የሕግ መምህር” መሆንን የሚመኝ፤ ያቺ የሕግ ምንጭ ወደሆነችው፣ የትልልቅ መምህራን መንበር ወደ ሆነችው ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ ያስፈልገዋል። ስለዚህ ሳውልም በታዋቂው መምህር (ረቢ) ገማልኤል ሊማር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ (የሐዋ.22፤3)። ገማልኤል ራሱ በታዋቂው መምህር ሂለል ነው የተማረው። የሕግ ትርጉምንና የእስራኤልን ትውፊት በማስተማር የታወቁ ሁለቱ አስተማሪዎች ሂለልና ሻማይ ይባላሉ። ስለዚ ሳውል በገማልኤል እግር ስር ሆኖ የአባቶቹን ትውፊትና መጽሐፍ ቅዱስ እንደፈሪሳውያን መንፈስ አጠና።  

 ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ወደ ጠርሴስ ተመለሰ ወይስ በኢየሩሳሌም ተቀመጠ የሚታወቅ ነገር የለም። እስጢፋኖስ በድንጋይ ተውግሮ በሰማዕትነት ሲሞት የሳውል በኢየሩሳሌም መገኘት በምን ምንክንያት እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ እስጢፋኖስ ሲወገር ሳውል የነረውን ቦታ ሲጠቅስ ተባባሪና የድርጊቱ ደጋፊ እንደነበር ሊያመለክት የፈለገ ይመስላል። 

  

 ይህ የጳውሎስ እስራኤላዊና ግሪካዊ ባህልና መገኛ፤ በመልእክቶቹና በስብከቶቹ ላይ በግልጽ የሚታዩ ናቸው። ግን ማንኛውም አንባቢ መጠንቀቅ ያለበት ነገር አለ፤ ያም በርሱ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርስበት የቻለ ያልነው ነገርን እንደ ወሳኝ ነገር አድርጎ መመልከት የለበትም፤ በሱም መወሰን የለበትም። ምክንያቱም የጳውሎስ አመጣጡ የተለያየ ቀለምና ስእል የሚያሳይ ቢሆንም እንኳ ዋና ሐሳቦቹና ትምህርቱ ግን ሁልጊዜ የእርሱ ሆነው፤ ዋና ምንጩና አፍላቂው የክርስቶስ ብርሃን ነው። ስብከቱና ሐሳቡ እዚህ ላይ ይመረኮዛሉ። ክርስቶስ እንደ ሕግ ፍጻሜ፣ ልክ እንደ ትንቢተ ኤርምያስ (ኤር.31፤31-34) ክርስቶስ በድንጋይ ሳይሆን በሰዎች ልብ ላይ የተቀረጸችው አዲስ ኪዳን ተካይ፤ “የድንጋይን ልብ” ወደ “የሥጋ ልብ” የሚለውጥ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጥ (ሕዝቅ.36፤26-28)፣ ክርስቶስ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስታርቅ (ሮሜ 3፤21-26)፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠውን (ኤፌ.5፤2) የአዲስ ሕይወት መሠረትና ምሳሌ አድርጎ ያቀርበዋል።  

 

ሐ. የእጅ ጥበብ ሥራ፣ ኑሮና ትዳር

         የእጅ ጥበብ ሥር በእስራኤል የተለምደ፤በተለይ ደግሞ መምህራን (ረበናት) ሲያጠኑና የሕግ ትምህርት እየተማሩ የሚሰሩት ሥራ የእጅ ጥበብ ነው የነበረው። ስለዚህ እንደ ድንኳን የመስፋት ሥራ ጳውሎስ ከልጅነቱ ጀምሮ የሠራውና የለመደውን ሥራ በመስራት ለኑሮው የሚሆነው ገንዘብ ያገኝ ነበር። ድንኳን የመስፋት ሥራ በሜዲትራኒያን ባሕር በሚገኙ ሃገሮች ይዘወተር የነበረና ብዙ ገበያ የነበረውና ተፈላጊም ስለነበር ጳውሎስ ራሱን እንዲችል ዕድል ከፈተለት። (የሐዋ.20፤34፣ 1ቆሮ.4፤2፣ 1ተሰ.2፤9፣ 2ተሰ. 3፤8 ተመልከት)

         ስለ ኑሮና ትዳር ምን ማለት ይቻላል? ጳውሎስ አግብቶ ነበር? ይህንን ጥያቄ እንዲነሱ የገፋፉ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች አሉ። ውጫዊ የሚባለው፣ እንደ እስራኤላውያን ልምድና ትውፊት መሠረት ጋብቻ ወይም ትዳር ግዴታ ብቻ ሳይሆን፣ መንፈሳዊና ሰብአዊ ኃይል ነው። ስለዚህ በዚህ ተገዶ አግብቶ ይሆን? የሚል ነው ጥያቄው። ውስጣዊ ምክንያት ደግሞ ከፊልጵስዩስ 4፤3 በመነሳት ነው “ኦ “ታማኝ” ጓደኛዬ። በዚ አባባል መሠረት ወደ ሚስቱ ነው የጻፈው የሚሉ አሉ። ከዘመናችን ተመራማሪዎች አንዳንዶቹ ጳውሎስ አግብቶ እንደነበር፤ ሚስቱ ስለሞተች ወይም ደግሞ እሱ ወደ ክርስትና እምነት ስለገባ፣ ወደ ክርስትና ልትገባ ያልፈለገችውን ሚስቱን ትቶ በክ ሆኖ መኖር ፈለገ በማለት ግምታቸውን የሚሰጡ አሉ።

         የእስራኤል መምህራን (ረበናት) እንዲያገቡ ቢገደዱም እንኳ ጳውሎስን በሚመለከት ግን ምንም ማረጋገጫ ያለ አይመስልም። “ታልሙድ ባቢሎን” የሚባል የረበናትን ትምህርትንና ትውፊትን የሚዘረዝር መጽሐፍ (በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ የሕግ መምህራን ያዘጋጁት) ስለ አንድ ያላገባ ለብቻው ይኖር ስለነበረ አስተማሪ ይተርካል፤ ረቢ ቤን-አዛይ ይባላል። ባለማግባቱ ይወቅሱት ለነበሩት ሰዎች “እውነታችሁን ነው! ነፍሴ የሕግ (ኦሪት) ፍላጎት ካሳደረች እኔ ምንድነው የማደርገው? ዓለም እንደሆነ በሌሎች ልትጠበቅ ትችላለች” ይል ነበር ይላሉ። ወደ ጳውሎስ ስንመለስ፤ በተለይ ደግሞ 1ቆሮንቶስን በጻፈበት ጊዜ ጥንቃቄ በሞላበትና በተረጋጋ ሁኔታ ብቻውን የሚኖር ራሱን ለስፋተ-ወንጌል የሰጠ እንደነበር ግልጽ ነው። በፊልጵ. 4፤3 ያለው ወይ የሰው ስም ነው፤ ወይም ደግሞ ወንጌልን በመስበክ ይተባበሩት ለነበሩት የሚያመለክት እንጂ ሚስትን የሚመለከት አይደለም። 

 

 

 

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት