ሰሙነ ሕማማት
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Thursday, 21 April 2022 09:08
- Written by Super User
- Hits: 991
- 21 Apr
2. በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል
በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምኑ ሁሉ በአዲስ ሕይወት ይመላለሱ ዘንድ ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፤ ይህም አዲስ ሕይወት በእግዚአብሔር ጸጋ የሚኖር “መለኮታዊነት” (Theosis) ነው። ይህ አዲስ ሕይወት ፍጥረት የተጠነሰሰበት እርሾ እና የፍጥረት ፍጻሜ ምልዓት ነው። ከዚህም የተነሳ ፍጥረት ሁሉ የተፈጠረበትን ዓላማ እውነተኛ ፍጻሜ እና ምልዓት ያገኘው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ሰው በመሆኑ ምሥጢር ውስጥ ነው። ይህም ማለት የአምላክ ሰው መሆን በኃጢአት መውደቃችንን ተከትሎ የመጣ ቁም ነገር ሳይሆን ይልቁንም አምላክ ከመጀመርያው አስቀድሞ በአርአያው እና በአምሳሉ የተፈጠረውን የሰውን ልጅ እንዴት በአምላካዊ አርአያ እና አምሳል በሙላት መኖር እንዳለበት እስከፍጻሜው ይገልጥለት ዘንድ ሰው መሆን ይፈልግ እንደነበር ያሳየናል።
“የማይታየው አምላክ የሚታይ መልክ” (ቆላ 1፡15) የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና እውነትን ለብሶ በመካከላችን በተገለጠ ጊዜ የመላእክት ወይም ሌላ የሰማያዊ ፍጥረትን አካል ሳይሆን አስቀድሞ መልኩን ያለበሰውን እና አርአያውን ያጎናጸፈውን የሰውን ልጅ አካል ወስዷል። ይህም ለእርሱ እንግዳ እና የማያውቀው ነገር ሳይሆን በእርግጥም ከበጎ ፈቃዱ የተነሳ ለሰው ልጅ ያለበሰው የራሱ የቀደመ መልክ ነው! የሰው ልጅ አስቀድሞ የተፈጠረበት መልክ የወልደ እግዚአብሔር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ነውና። በዚህም የሰው ልጅ ቀድሞ የተፈጠረበትን እውነተኛ መልክ አሁን በመካከላችን በተገለጠው በጌታ መልክ በኩል መመልከት እና ወደዚያውም ማደግ ይችላል። በዚህም ኢየሱስ በኃጢአት ምክኒያት ተቋርቶ የነበረውን የሰውን ልጅ “ሰው”ነት እና መለኮታዊነት ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመሆኑ ምሥጢር ውስጥ አስታርቋል። በዚህም ምሥጢር አምላክ ሰውን ስለመሰለ የሰው ልጅ አምላክን ይመስል ዘንድ የከበረ ጥሪ አለው[1]።
እግዚአብሔር ጊዜው በደረሰ ጊዜ (ገላ 4፡4) የልጁን ሥጋ ለብሶ መገለጥ እና በዚህም መገለጥ የሰው ልጅ በመለኮታዊ ማንነቱ ክፍል እንዲኖረው በማሰብ የሰውን ልጅ በአምሳሉ (ĸατ‘ είκόνα) እና በአርአያው (καθ‘ όμοίωσιν) ፈጥሮታል። የሰው ልጅ በመለኮታዊ ባሕርይ (Theocentric)፣ በአምላካዊ እና ሰብዓዊ (Theandric) ግብር በመፈጠሩ ራሱን ሲሆን እና ከሰው ልጆች ጋር ባለው ፍጥረታዊ ሕብረት ሲገለጥ ይበልጥ የተፈጠረበትን መልክ እየመሰለ ወደ ቅድስት ሥላሴ ኅብረት ያድጋል። ይህ መለኮታዊ እና ሰብዓዊ የሰው ልጅ ማንነት የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ ለብሶ የተገለጠበት ምሥጢር ዋነኛ ምክኒያት ነው። አምላክ እና ሰው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ታርቀዋል፤ አዳም እና እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ መገለጥ በኩል በአንድ ቤት ተገኝተዋል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ መገለጥ ውስጥ ሰው እና አምላክ እርስ በእርሳቸው ዐይን ለዐይን ተያይተዋል። በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ውስጥ የሰው ልጅ እንደተፈጠረበት ክብር ሙላት እንዴት መኖር እንደሚገባው ከአምላክ ተምሮአል። በመሆኑም የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን የተጠመቀ ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ጭምር እንጂ እንደ ሰው ልጅ ፈቃድ ብቻ እንዳይመላለስ ኢየሱስ ምሳሌ ሆኖለታል። ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” (ኤፌ 2፡6-7) እያለ የተሰጠንን ክብር ይገልጽልናል።
3. ተአዝዞ እና ነጻነት
ሥጋ የለበሰው የእግዚአብሔር ልጅ “የአዲሱ ፍጥረት በኩር” (ቆላ 1፡15) እንደ “አዲሱ አዳም” ሆኖ ራሱን የገለጠው የሰው ልጆችን ከታሰሩበት የሞት ቀንበር ነጻ አውጥቶ የተትረፈረፈ ሕይወት በመስጠቱ ነው፤ ይህንን ሁኔታ ቅዱስ ኤሬንዮስ እንዲህ እያለ ይገልጸዋል፡- “መጨረሻውን ከመጀመርያው ጋር ያጋጥም ዘንድ፤ ይህም ማለት እግዚአብሔርን እና የሰው ልጆችን ያገኛኝ ዘንድ በሰው ልጆች መካከል እንደ ሰው ሆኖ የተገለጠው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ግን ይሄ ነው፤ ስለዚህም የትንቢትን መንፈስ እና ሥጦታ የተቀበሉት ነብያቱ ሁሉ የአምላክ ልጅ በሥጋ መገለጥ እና አምላክ በሰው ልጆች መካከል ማደሩ ከዘላለም ጀምሮ የአብ ፈቃድ እንደነበር ተንብየዋል”[2]
በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ፍጥረት እና ድኅነት ሁለት የተለያዩ የመዳን ታሪካችን እውነታዎች ሳይሆኑ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ መገለጥ ውስጥ በሰመረ ግንኙነት አብረው የተገመዱ የአብ ዘላለማዊ ዕቅድ ወርቀ ዘቦ ገጽታዎች ናቸው። የመጀመርያው የአምላክ መገለጥ ዓለም እና ሞላዋ የተፈጠሩበት፣ የሰው ልጅ የአምላክን አርአያ እና መልክ የለበሰበት እንዲሁም ፍጥረትን በሙሉ እንዲያለማ እና እንዲንከባከብ የክህነት ኃላፊነትን የተቀበለበት እንደነበር ሁሉ ሁለተኛው የአምላክ መገለጥም የሰው ልጅ አስቀደሞ የተፈጠረበትን የእግዚአብሔርን መልክ ያየበት፣ በሁለተኛው አዳም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ቀደሞ የተሰጠው የክህነት ማንነት እና ኃላፊነት ምልዓቱን ያገኘበት መገለጥ ነው።
የቀደመው አዳም ነጻነቱን ያለ አግባብ በመጠቀሙ እና ባለመታዘዙ ኃጢአት የፍጥረትን ተዋረድ እና ጤናማ ግንኙነት ስላዛነፈ የቀደመው አዳም ስለተሰጠው ነጻነት እና ኃላፊነት ተጠያቂ ሆኗል። እንዲያለማው እና እንዲንከባከበው በኃላፊነት የተሰጠውን ነገር ነጻነቱ በማይፈቅድለት መልኩ "ራሱን በመስጠት" ፈንታ "ለራሱ ሊሰጥ" ስለወደደ በፍጥረት መካከል የነበረው ሰላም ሥፍራውን ለቋል። የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዓላማ በተዛነፈ እና መንገዱን በሳተበት የሕይወቱ አቅጣጫ በኩል የተፈጥሮ ጤናማ ሚዛን ይዛነፋል።
ተፈጥሮን ሊበዘብዝ እና ላልተፈጠረበት ዓላም ባርያ አድርጎ ሊገዛው የሚፈልገው ክፉ መንፈስ በዚህ በሰው ልጅ ስብራት ወይም ኃጢአት ምክኒያት ዕድል ያገኛል፤ ይህንን ዕድል እንዳያገኝ እና በተፈጥሮ ላይ ገዢ እንዳይሆን በንቃት እየጠበቅን እንዋጋው ዘንድ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” (ያዕ 4፡7) እያለ ያበረታታናል። ሰይጣን በራሱ ኅልውና መገለጥ እና በእግዚአብሔር ኅላዌ ፊት መቆም ስለማይቻለው ሁልጊዜ የሚጠጋው፣ የሚሸሸግበት እና የሚታከክበት ቁሳዊ ነገር ይፈልጋል። በመሆኑም በሰው ልጆች መካከል ይገለጥ ዘንድ የሚገለጥበት ግለሰብ ወይም ድርጊት ይፈልጋል፤ ጌታ በወንጌል ሲናገር “ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም። በዚያን ጊዜም ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል” (ማቴ 12፡43-45) እያለ የሰይጣን ዕቅድ እንዴት ባለ መልኩ እንደሚገለጥ ያመላክተናል።
ክፉ መንፈስ ክፉ የሆነው ማፍቀር እና ራሱን አሳልፎ መስጠት ስለማይችል ነው! በመሆኑም ማፍቀር የማይችል ከሆነ ሕይወት በእርሱ ዘንድ የለችም። ስለዚህ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ለግል ጥቅሙ እና ለግል ዓላማው ብቻ ያውል ዘንድ ያለውን ምርጫ ሁሉ ተጠቅሞ ሕይወትን ሊነጥቅ ያደባል። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ይህንን የሰይጣንን ባሕርይ በመረዳት እንዲህ እያለ ይመክራል፡- “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” (1ጴጥ 5፡8)። ሰይጣን ሕይወት ያለበትን ነገር እና የሕይወት መዓዛ የሚሸትበትን ሥፍራ ሁሉ ሊበዘብዝ ዘወትር ዝግጁ ነው። ስለዚህ በድብቅ አድብቶ ይቀመጣል እንጂ በግልጽ ወደፊት አይወጣም፤ እርሱ እጅግ በጣም በምንፈልጋቸው እና ለዘመናት በጸለይንባቸው ጉዳዮቻችን እንጂ ትርፍ በሆኑ ነገሮቻችን አያጠምደንም። ስለዚህ በእነዚህ ነገሮች ውስጥ ለእርሱ ሥፍራ የሚሰጥ የሕይወት ልምምድ ሲያገኝ ሥፍራውን ይዞ ይሸሸጋል። እርሱ በቀድሞው ዘመን በእባቡ በኩል ወደ አዳም እና ሔዋን እንደመጣ ሁሉ በነገሮች ተሸሸጎ እና በሚሸከሙት ነገሮች ውስጥ ተደብቆ እንጂ በግልጽ የእግዚአብሔርን ክበር በሚነካ አኳኋን አይገለጥም።
በሰይጣን ዘንድ የሕይወት መዓዛ የለምና እርሱ ሕይወትን በየትኛውም መልኩ ሊያጠፋ እና ሊሰርቅ ዝግጁ ነው። በእርሱ ዘንድ ሕይወት ስለሌለች እርሱ የሰው ልጆችን የሕይወት ጥያቄ መመለስም ሆነ የሰው ልጆችን መሻት መፈጸም አይቻለውም (ንጽ ዮሐ 4፡14)። ሰይጣን የእግዚአብሔር መገለጥ እና የሕይወት ጠላት ነው፤ እርሱ እግዚአብሔርን ስለሚጠላ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ ዋነኛ ጠላቱ ነው። እግዚአብሔርን የሚያከብር እና የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ አንደበት ሁሉ የሰይጣን ጠላት በመሆኑ ሰይጣን ይህንን አንደበት ዝም እስከሚያሰኝ እና የእግዚአብሔርን ክብር እስከሚሸሽግ ድረስ ዕረፍት የለውም። በመሆኑም የሰው ልጅ ከእግዚብሔር ጋር ባለው በየትኛውም ግንኙነቱ ፍሬ እንዳያፈራ ከማደናቀፍ አይቦዝንም[3]። ጌታ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ስም ለማመስገን ድምጹን ከፍ ባደረገበት ወቅት ሰይጣን በፈሪሳውያን በኩል ወደ ጌታ ቀርቦ “መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” (ሉቃ 19፡39) ሲል እንሰማዋለን። የሰው ልጅ ሰይጣንን በሚቃወምበት የሕይወቱ አቅጣጫ ሁሉ የበለጠ ፍሬ እያፈራ እና በመንፈሳዊ ሕይወቱ እየጎለመሰ ይገለጣል።
እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ከዚህ ቀንበር ነጻ ያወጣው ዘንድ ሰይጣን የማይሰጠውን ነገር እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ይሰጠው ዘንድ የዘላለም ፍቃዱ ነበርና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን የእግዚአብሔርን ሥጦታ ሲመሰክርልን “ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ይላል (ዮሐ 3፡16)።
ሰይጣን ማፍቀር አይችልም፤ ምክንያቱም ፍቅር መታዘዝ ያለበት ራስን ለሌላው አሳልፎ የመስጠት መታመን ነው። የሰው ልጆችን በሙሉ ከሰይጣን ባርነት እና ከሞት ጨለማ ነጻ ያወጣቸው ዘንድ አምላክ ራሱ በመስቀል ላይ ያዋለው በዚህ ፍቅር ካልሆነ በስተቀር የምንድንበት ሌላ መድኃኒት ባለመኖሩ ነው። በዚህ የመስቀል ምሥጢር እግዚአብሔር አምላክ ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር ዘላለማዊ የፍቅር ቃልኪዳን አድርጓል። የአሌክሳንድርያው ቅዱስ ቀለሜንጦስ ስለ መዳናችን ምሥጢር ሲጽፍ “ቃለ እግዚአብሔር ሰው የሆነው እኛም እያንዳንዳችን እንዴት እንደ አምላክ መሆን እንደምንችል ከሰው ዘንድ እንድንማር ነው”[4] በማለት ጥሪያችን በመለኮት ባሕርይ በሰው አምሳል በዓለም ፊት የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሆነን እንድንገለጥ መሆኑን ያብራራልናል። የእግዚአብሔር ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ መገለጡ፤ የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲቀምስ እና ምላሽ እንዲሰጥ በር ይከፍትለታል፤ ሥጋ የለበሰው የእግዚአብሔር ልጅ ለሰው ልጆች በሙሉ ራሳቸውን የሚያዩበትን አዲስ ዐይን ይሰጣቸዋልና ከእንግዲህ ራሳቸውን እንደ ክርስቶስ ምስል እንዲመለከቱ እና በእርሱ ዘላለማዊ ልጅነት በኩል ልጆች ሆነው እንደተወደዱ እንዲያውቁ አዲስ አእምሮ ሰጥቷቸዋል። ስለዚህ ኢሳያስ የተናገረው ትንቢት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእያንዳንዳችን ሆኗል፡- “በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና” (ኢሳ 43፡4)።
የሰው ዘር ልደት
ምሥራቃዊቷ ቤት ክርስትያን የጌታን ሰው መሆን የኃጢአታችን ውድቀት ብቻ ተከትሎ የተከናወነ የአምላክ መለኮታዊ ውሳኔ አድርጋ አትመለከተውም፤ ይልቁንም ትስብዕቱ የእግዚአብሔር አብ ዘላለማዊ ዕቅድ እንደሆነ ትገነዘባለች[1]። የሰው ልጅ በኃጢአት ባይወድቅ ኖሮ እንኳን ከቅድስት ሥላሴ ጋር ፍጹም የሆነ ኅብረት ሊያደርግ የሚችለው የወልደ እግዚአብሔርን ባሕርይ ተካፋይ ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር ሲጋጠም ነው፤ የዔደን ገነት አዳም እና ሔዋን ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ኅብረት ለማድረግ ጉዞ የጀመሩበት እንጂ የፍጻሜ ሥፍራቸው አልነበረም። የሰው ልጅ በፍጥረቱ ብቻ ፍጽምናውን ሊያገኝ አይቻለዉምና የፈጠረው ይልቁንም የተፈጠረበት መልክ ከእርሱ ጋር ኅብረት ማድረግ እና እርሱን ወደ ተፈጠረበት ምልዓት ማድረስ ያስፈልገው ነበር። የሰው ልጅ ሰው ሆኖ የመፈጠሩ ፍጻሜ እና ምልዓት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ መወለድ ምሥጢር ውስጥ የሚጠቀለል ቁም ነገር ነው፤ ስለዚህ ባሲሊዮስ ታላቁ የጌታን መወለድ “የሰው ዘር ልደት” እያለ ይጠራዋል። መዳን ማለት ከኃጢአት ዕዳ ነጻ መሆን ማለት ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር በሙሉ ወደ ተፈጠረበት አርአያ እና አምሳል ፍጻሜ መድረስ እና ከዘላለም ጀምሮ በከበረበት መለኮታዊ ማንነቱ በምልዓት መገለጥ (Theosis) ማለት ነው።
የግሪክ መንፈሳውያን አበው የሰው ልጅ በኃጢአት የወደቀበትን ቅጽበት በማስታወስ ያቺ ቅጽበት የሰው ልጅ የተፈጠረበትን መለኮታዊ መልክ ያጣበት እና የእርሱ ያልነበረውን በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ለእርሱ ያልታሰበውን በገዛ ነጻ ፈቃዱ ኃጢአት ምክንያት የባርያን መልክ የለበሰበት ቅጽበት እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን የሰው ልጅ በኃጢአት ምክኒያት ይጠውልግ እንጂ በነፍሱ ላይ ያለው የእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል እንዲሁም ደግሞ ነጻ ፈቃዱ (αύτοεξουσία) ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። በኃጢአት የጠወለገ ቢሆንም የተፈጠረበት መልክ ከእርሱ ጋር ነበር[2]። በመሆኑም የእግዚአብሔር ቃል የሰው ልጅ የሆነበት ምሥጢር በኃጢአት የመውደቃችን እውነታ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ከሁሉ አስቀድሞ እንደ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ፈቃድ እና ለሰው ልጅ እንዳለው በጎ ዓላማ፣ የሰው ልጅ የቀደመው የአምላክ ልጅነት ነጻነቱ ታድሶለት፣ ከበፊቱ በበለጠ ክብር ተሸልሞ በመለኮታዊ ክብር መኖር ስለሚገባው ነው[3]። በጎልጎታ ከተፈጸመው የመዳን ምሥጢር የተነሳ የሰው ልጅ በአዲስ ማንነት አዲስ ሕይወት ያውም መለኮታዊ ባሕርይ ያለው መንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር እና የተፈጠረበትን መልክ እንዲሁም ሰው የመሆን ፍጻሜ እና ምልዓት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይመሰል ዘንድ ታድሷል። በክርስቶስ ኢየሱስ እና ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የሰው ልጅ ወደ ተፈጠረበት ክብር እና ወደ ቀደመው እውነተኛ መልኩ ምልዓት ይደርሳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ኃጢአትን በመረጠበት እና የእግዚአብሔርን ፍቅር ባልተቀበለበት የሕይወቱ ክፍል ሁሉ ዕለት ዕለት ይበልጡን ወደ ተጎሳቆለ የባርያ መልክ ይወርዳል።
ይቀጥላል...
ሴሞ
[1] D. Gnau, person werden. Würzburg, 2015, ከገጽ 88 ጀምሮ
[2] የኑሲሱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ፣ Das Leben des Mose II, 32 (PG 44, 336B)
[3] ዮሐንስ ካስያን፡- Concl. XXIII, 12 ንጽ ቅዱስ ኤሬኒዮስ ዘሊዮን፡- Adv. hear. V 21።
[1] ቀለሜንጦስ ዘአሌክሳንድርያ፡ Stromatum. VI, 9.
[2] ቅዱስ ኤሬኒዮስ ዘሊዮን፡- Adv. hear. IV 20፡4
[3] D. Staniloae, Orthodoxe Dogmatik. I. Zürich. 1985, 411.
[4] ቀለሜንጦስ ዘአሌክሳንድርያ፡ protr. I. 8,4