መንፈስ ቅዱስ
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Sunday, 12 June 2022 17:39
- Written by Super User
- Hits: 936
- 12 Jun
መንፈስ ቅዱስ
የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር "ሩዋህ" (רוּחַ) የሚል የዕብራይስጥ ቃል ይጠቀማል። ይህም እስትንፋስ፣ ነፍስ፣ ነፋስ ወይም አየር የሚል ሰፋ ያለ ዐውዳዊ ፍቺ ያለው ቃል ሲሆን፤ ይህ ቃል በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ 378 ጊዜያት ያህል ተጠቅሶ እንመለከተዋለን። ሩዋህ የሚለው ቃል እንደ አገባቡ በሦስት ዘርፎች ሊተረጎም ይችላል። ዐውዳዊ ፍቺውን በሚመለከት በመጀመርያ ደረጃ ነፋስ ወይም እስትንፋስ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በሌላ በኩል በሁለተኛው ዐውዳዊ ፍቺ ሩዋህ የሚለው ቃል የሰውን ልጅ ሕያው የሚያደርገው መለኮታዊ ኃይል ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል። በዚህም የሰው ልጅ ሕላዌ ምንጭ እና የሰው ልጅ ሕያው የሆነበት ጥበብ ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሦስተኛ ደረጃ ሩዋህ የሚለው ቃል የእግዚአብሔር ሕይወት፣ እግዚአብሔር ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር የሚጠራበት ኃይል ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል።
ስለዚህ ሩዋህ የሚለው ቃል አካልን ሁሉ ሕያው የሚያደርገው እስትንፋስ፣ የሕይወት እና የሕልውና ምንጭ የሆነ፣ እግዚአብሔር ረቂቁን መንፈሳዊ ዓለም እና እንደዚሁም ደግሞ በገሃድ የሚታየውን ግዙፉን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር የጠራበት የፈጣሪነቱ ኃይል ነው። በመሆኑም ይህ የእግዚአብሔር እስትንፋስ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው ነገር ሁሉ በገሃድ የሚገለጥበት ታላቅ ብርሃን ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችን መኖሩ የሕልውናችን ዋስትና ነው።
ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ እያንዳንዳችንን ለተፈጠርንበት ዓላማ የሚቀድሰን እና ወደዚያውም እንደርስ ዘንድ የሚያነሳሳን፣ የሚመራን፣ የሚያጸናን እና የሚያጽናናን ትጉህ ወዳጅ ነው። ይህ ወዳጅ የሰውን ልጅ ሁሉ ወደተፈጠረበት ክብር ምልዓት ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ የሰው ልጅ ራሱን በሚያይበት ዕይታ እና ራሱን በተቀበለበት መረዳት ሳይሆን ፈጣሪው ቅድስት ሥላሴ የሰውን ልጅ በሚያይበት ዕይታ እና የሰውን ልጅ ከዘላለም ጀምሮ በተቀበለበት መረዳት ራሱን እንዲመለከት እና እንዲቀበል ቀስ በቀስ ወደዚህ መለኮታዊ ምልዓት ያሳድገዋል። ። መንፈስ ቅዱስ ከውሱንነታችን ባሻገር አዕምሮን ሁሉ እየማረከ ወደ እግዚአብሔር ክብር ከፍ የሚልበትን የጥበብ ብርሃን የሚሰጠን መንፈስ ነው።
መንፈስ ቅዱስ የሰውን ልጅ በሁሉ ነገር ሙሉ የሚያደርገው፣ በሰማያዊ በረከት ሁሉ የሚባረከው መንፈስ ነው። የኦሪት ዘጸአት መጽሐፍ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥጦታ ስለመሞላት ሲናገር በምዕራፍ 31:3-5 የእግዚአብሔርን ማደርያ ለመገንባት ስለተመረጠው ስለ እጅ ሞያተኛው ስለ ባስልኤል እንዲህ ይላል " በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሰራ ዘንድ፥ ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ"። ይህ መለኮታዊ ሥጦታ ባስልኤል በሰው ሁሉ ፊት ሙሉ የሚሆንበት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ባስልኤል በእግዚአብሔር ነገር ሁሉ የተካነ፣ ለሰው ሳይሆን ይልቁንም ለእግዚአብሔር በሚሆን ክብር እንደሚገባ ይሰራ ዘንድ በሁሉ ነገር የሚቀድሰው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነው። እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባን መሠረታዊ ቁም ነገር ባስልኤል በእግዚአብሔር መንፈስ የተሞላው ለግል ጥቅም ሳይሆን የእሥራኤል ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኝቶ ይቀደስበት ዘንድ ነው።
የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ዓላማ ሁሉ ሰዎችን በነፍስ ወከፍ ተአምረኛ እና ዝነኛ የማድረግ ጉዳይ አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ ዝነኞችን የማፍራት ተልዕኮ የለውም። ይልቁንም ለአንዱ በሚሆነው ሥጦታ ሌላው እንዲታነጽ፣ ያው አንዱም ደግሞ በሌሎች ሥጦታ እንዲታነጽ፤ በዚህም የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ መንፈሳዊ ቤት ሆኖ እየተቀደሰ ያድግ ዘንድ ነው። መንፈስ ቅዱስ ሥፍራውን ባልያዘበት አገልግሎት ሁልጊዜ የዓላማ እና የተልዕኮ መፋለስ አለ፤ በመሆኑም እንድናገለግላቸው የተሰጡን የእግዚአብሔር ሕዝቦች መገልገያዎች ሆነው ወደ ባርነት ይወርዳሉ። የእግዚአብሔር ልጅ በደሙ ዋጋ አርነት ያወጣውን ሕዝብ አስጨንቀን በቀንበር ጠምደን ለራሳችን ተልዕኮ ማስፈጸምያ እናደርጋቸዋለን።
ባስልኤል እርሱ ራሱ እየለካ እና በራሱ ዕውቀት ብቻ እየቆረጠ እንዳይገነባ የእግዚአብሔር መንፈስ ልክን፣ ወሰንን፣ ድንበርን እና መጠንን የማወቅ መንፈስ እንደሰጠው እናነባለን። ከዚህም በመነሳት በወርቅ መሰራት ያለበትን በወርቅ ብቻ እንጂ በሌላ በምንም ነገር እንዳይሰራ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእርሱ ጋር ነበር። በመሆኑም ጥምቀታችን እና በመንፈስ ቅዱስ መሞላታችን እንደ ተራ እንድንመላለስ ሳይሆን ይልቁንም በየተጠራንበት ጥሪ እና በየተሰማራንበት የሥራ ዘርፍ የእግዚአብሔር ተልዕኮ ይፈጸም ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንደሚፈልገው እንዲሰራ በእምነት መታዘዝ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እየተባበርን እንደ እግዚአብሔር ልጆች ክብር እንድገለጥ ነው። በዚህ የእምነት መታዘዝ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት ማድረግ እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ እንደ እግዚአብሔርነቱ ክብር ይገለጥ ዘንድ ሥፍራ ያዘጋጃል። እግዚአብሔር በውስጣችን እንደ ፈቃዱ እንዲገለጥ ከፍ ያለውን የሚደለድል፣ ሸለቆውን የሚሞላ የእግዚአብሔር መንፈስ በነፍሳችን ውስጥ ነጻ ሥፍራ ሊያገኝ ይገባዋል። በመሆኑም እያንዳንዱ ክርስትያን በምሥጢረ ጸጋ አማካይነት ወደዚህ የመንፈስ ቅዱስ ሕብረት ተጠርቷል።
መንፈስ ቅዱስ ለነፍሳችን የዘላለም ሕይወትን ራዕይ የሚሰጥ መንፈስ ነው። 1ሳሙ 9:9 ላይ እንምናገኘው ነብዩ ሳሙኤል ነብይ ተብሎ ከመጠራቱ አስቀድሞ ባለ ራዕይ እየተባለ ይጠራ ነበር። ሳሙኤል ባለ ራዕይ እየተባለ የሚጠራው ከእግዚአብሔር በተቀበለው ራዕይ መሰረት በመንፈስ ቅዱስ በተኳሉ፣ በመንፈስ ቅዱስ በጠሩ፣ በመንፈስ ቅዱስ እሳት በተወለወሉ ዐይኖች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይመለከት እና ያስተውል ስለነበር ነው። መንፈስ ቅዱስ እንደ አዲስ ሕያው አድርጎ የሰው ዐይን ባላየው፣ የሰው ጆሮ ባልሰማው፣ የሰው ልብ ባላሰበው መልኩ የሚለውጠን መንፈስ ነው።
መንፈስ ቅዱስ እውነትን፣ ቅን ፍርድን እና በነገሮች መካከል መለየት የምንችልበትን ጥበብ የሚያጎናጽፈን መንፈስ ነው።
ይህ መንፈስ ያለመኑት እንኳን ስለ እግዚአብሔር ኃያልነት ይመሰክሩ ዘንድ ስለ እውነት ግድ የሚላቸው መንፈስ ነው። ስለዚህም በዘፍ 41:38 ላይ እንደምናነበው ፈርኦን ሳይቀር ስለ ዮሴፍ ሲመሰክር "በእውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን እንደዚህ ያለ ሰው እናገኛለንን?" እያለ ይጠይቃል። ፈርኦን እንኳን በዮሴፍ ላይ የነበረው መንፈስ ከግብጽ አማልክት ጋር ሊወዳደር የማይችል ታላቅ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደሆነ ይመሰክራል። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እንዲመላለስ በፈቀድንለት መጠን ጌታችን ኢየሱስን በውስጣችን እየቀረጸ በሰው ሁሉ ፊት በጥበብ እና በሞገስ እየተገለጥን የስሙ ምስክሮች እንድንሆን ያደርገናል፤ በዚህም ሌሎች ሰዎች፣ የማያምኑ እንኳን ቢሆኑ እግዚአብሔርን የሚቀበሉበት ጸጋ በውስጣቸው ያብባል። ስለዚህ ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ በሥጦታዎቹ ሁሉ እንዲባርከን ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ዐደራ አሳልፈን እንስጥ!
መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና! የምዕመናንን ልብ ሙላ፤ የፍቅርህን እሳት በልባችን አንድድ፤
የእውነተኛነት ምንጭ የሆንህ መንፈስ ቅዱስ ሆይ በልባችን ውስጥ ግባ፤
ሕዝቦችህ ትህትና በሞላበት እምነት ደስ እንዲያሰኙህ ብርሃህን አድላቸው፤
አሜን።!
ሴሞ