እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ፍቅር ክፍል ፫

ፍቅር ክፍል ፫

Rየወዳጅነት ፍቅር በተግባቦት ወይም በልውውጥ ላይ የተመሰረተ ኅብረት ነው፤ ነገር ግን ይህ ተግባቦት በባሕርያዊ የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የሚያተኩር ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ወዳጅነቱ ከራሱ ከባብያዊ ዐውድ ውጪ በሆነ ገዢ እውነት ላይ የተመሰረት ሊሆን ይገባዋል። በመሆኑም ወዳጅነቱ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ  ብቻ የተመሰረተ ቁም ነገር ሳይሆም ይልቁንም ሁለቱንም አንድ አድርጎ በሚገዛቸው በጎነት ላይ የተመሰረተ ነው። ወዳጅነት ዐይን ለዐይን በመተያየት ከሚገኘው የጋራ ደስታ ባሻገር ሁለቱ ሰዎች በጋራ በአንድ ዐይን በሚመለከቱት በጎነት ላይ ያተኩራል። በመሆኑም ሁሉን አንድ አድርጎ በሚያስተሳስር በጎነት ላይ በተመሰረተ ወዳጅነት እውነትን በጋራ ለመፈለግ እና ለመከተል በምናደርገው ጉዞ ውስጥ እውነተኛ ወዳጅነት ይወለዳል።

በባሕርያዊ ጓደኝነት ውስጥ ወዳጅነት የሚመሰረትባቸው የጋራ የሆኑ የምንጋራቸው በጎ ቁም ነገሮች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በዚህ ወዳጅነት መካከል የሚታየው የጋራ ፍጻሜ እውነተኛነት እና በጎነት በጨመረ መጠን ወዳጅነቱ በዚያው ልክ ሥር እየሰደደ እና እያደገ ይመጣል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በምንመርጣቸው ጓደኞች ዙርያ ጥንቃቄ እናደርግ ዘንድ ይመክራል፤ በዚህም መሰረት መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ቁም ነገር ያስተምረናል “ከጠቢባን ጋር የሚሄዱ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” (ምሳ 13፡20)። በመሆኑም አካሄድን ማስተካከል፤ ጓደኛን መምረጥ እና የሕይወትን መንገድ ማበጀት ጥበብ የሚጠይቅ ቁም ነገር ነው። 

ወዳጅነት ከኅብረት ጋር፣ ከልብ ለልብ ውይይት ጋር የተቆራኘ ምሥጢር ነው፤ በመሆኑም ሁለት ልቦች በአንድ ቁም ነገር ላይ ማረፍ ይገባቸዋል፤ ይህ በአንድ ገዢ ሐሳብ ላይ ማረፍ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ እና የጸጋ ሥራ ነው። ጓደኝነት የግል ምርጫ ከመሆኑ ባሻገር የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነው። ስለዚህ ለመልካም ጓደኝነት የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መለመለን አስፈላጊ ቁም ነገር ነው፤ ለዚህም የሚያበቃንን መንፈስን የመመርመር እና መንፈስን የመለየት ሥጦታ እንድናገኝ በብርቱ መጸለይ ያስፈልገናል።

ወዳጅነትን ፍሬያማ የሚያደርገው ቁም ነገር ሁለቱም ወዳጆች ልባቸው በእግዚአብሔር እስከሚያርፍ ድረስ እግዚአብሔርን በመፈልግ እውነት መተሳሰራቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ቁም ነገር ሲያሳየን “ዮናታንም ዳዊትን በደኅና ሂድ፤ እነሆ፥ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል አለው” (1ሳሙ 20፡42) እያለ ወዳጅነቱ ከእርስ በእርስ መተማመን ባሻገር ከእግዚአብሔር ጋር፣ በእግዚአብሔር ፊት፣ በእግዚአንሔር ስም የሚደረግ ቃል ኪዳን መሆኑን ጭምር ያመላክተናል። ከዚህ ቁም ነገር የተነሳ ወዳጅነቱ የሦስትዮሽ ትስስር ያለበት የመተማመን ፈትል መሆኑን መመልከት እንችላለን። ወዳጅነት ከዚህ እውነት ዝቅ ባለ ዋጋ ላይ ትኩረቱን ካደረገ እያደገ በሚመስል ውጫዊ ዕይታ ውስጥ ውስጡን እየከሰመ ይሞታል። ነገር ግን የዚህ ወዳጅነት ሞት ሰላማዊ ሞት ሳይሆን በርካታ የሕይወት ቁም ነገሮችን አበላሽቶ የሚያልፍ እና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል አላስፈላጊ ዕዳ ነው።

የወዳጅነት መሰረቱ በቅድስት ሥላሴ መካከል ያለው የፍቅር ልውውጥ በመሆኑ ሌሎች ሰዎችን የምናፈቅርበት ፍቅር ከዚህ የቅድሥት ሥላሴ ኅብረት እና አንድነት መካከል የሚመነጭ ፍቅር ነው። በመሆኑም የወዳጅነት የመጀመርያው ገዢ ቁም ነገር እኔ ወይም ደግሞ ወዳጄ በዚህ ጓደኝነት ውስጥ የምንጫወተው ሚና፣ ያለን ዋጋ ወይም የምንከፍለው መሥዋዕትነት ሳይሆን የወዳጅነታችን የመጀመርያው እና የመጨረሻው ቁም ነገር ቅድስት ሥላሴ ራሱ ነው። ቅድስት ሥላሴ መለኪያ የሆነው ወዳጅነት ከሰው ልጅ ሰብዓዊ ውሱንነት ባሻገር የመመልከት እና ሌላውን ሰው ሁሉ እንደ ቅድስት ሥላሴ የመገለጥ መልክ የመቀበል የጸጋ አቅም ያዳብራል። በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 13፡7-8 እንደሚያስተምረው እንዲህ ያለው ፍቅር፡-

“ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም”።

ፍቅር ለሌላው በጎ ነገርን የሚመኝ እና በሌላው ውስጥ የሚመኝለትን በጎ ነገር ፍጻሜ በተስፋ የሚመለከት የእምነት ጉዞ ነው። እግዚአብሔር እኛን ስላፈቀረን መልካሙን ነገር ብቻ ሳይሆን የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነውን ቁም ነገር ተመኘልን፤ ስለዚህም የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነውን ነገር፣ ይኸውም ራሱን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእኛ ሰጥቶናል። በመሆኑም በእውነት የሚያፈቅር ሰው ለሌላው የሚመኘው ፍጹም የሆነ በጎ ሥጦታ ራሱን ለሌላው አሳልፎ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ እግዚአብሔርን ለሌላው መስጠት፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር በሌላው ውስጥ ማቀጣጠል መቻሉ ነው። ነገር ግን “Nemo dat quod non habet” እንደሚባለው መጀመርያ በእኛ ውስጥ ያልነደደውን እሳት ሌላ ሰው ሕይወት ውስጥ መለኮስ እና ማቀጣጠል አንችልም። በመሆኑም እኔ በእውነት የማፈቅርበት ኃይል ከወዳጄ ጋር ወደዚህ እውነት ለመድረስ የምጋደልበት የመዳን ቁርጠኝነት ነው።

ፍቅር መልካም ነገር በመሆኑ የሚያፈቅር ሰው መልካም ነገርን ይመኛል፤ ነገር ግን መልካም ነገር የሚመኘው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር ነው። የፍቅር መልካምነት ለሌሎች ሁሉ የምመኝላቸው የሕይወት ዋጋ ክብር በመሆኑ ቁም ነገር ውስጥ ተገልጦ ይታያል። በመሆኑም ለሌሎች የምመኝላቸው መልካም ነገር “ይዘት” ሌሎችን የማፈቅርበትን የፍቅር ዋጋ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ቁም ነገር ነው። “አፈቅራለሁ” የሚል ሰው የሚያፍቅርበት የፍቅር ልክ ያለ ልክ ማፍቀር በመሆኑ ሌላው ሰው በሁሉ ነገር ከእርሱ የተሻለ እንዲሆን፣ በምድርም ብቻ የሚገደብ ሳይሆን ይልቁንም በሰማያት ከፍ ያለ ስፍራ እንዲኖረው እስከመጨረሻ ድረስ ይህንን የፍቅር መስቀል ተሸክሞ ይዘልቃል። እግዚአብሔር እኛን ላፈቀረበት እና ራሱን ስለ እኛ አሳልፎ ለሰጠበት ፍቅር የምንከፍለው ብቸኛ ዋጋ እርስ በእርሳችን በዚህ ፍቅር መዋደዳችን ነው። በዚህም የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንደሆንን ዓለም ያውቃል!

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናችን የሚገለጠው ኢየሱስ ለከፈለው ዋጋ በምንሰጠው ክብር እና ዐደራውን በምናከብርበት ግብረ-ገብ ነው። ይህንን ዋጋ የምንጠብቅበት ክብር ለወንድሞቻችን እና ለእኅቶቻችን ያለን በመስቀል የተፈተነ ፍቅር ነው። የኢየሱስ ፍቅር ከመስቀል ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑ መጠን በዕለት ተዕለት ኑሮ የሚገጥሙን ቁም ነገሮችን የዚህ መስቀል ልዩ ልዩ ገጽታዎች አድርገን በመቀበል እንደ ፈተና ብቻ ሳይሆን ለጌታ ፍቅር እንደምንሰጠው የእምነት ምሥክርነት በመመልከት እያንዳንዱን ፈተና እንደ ጸጋ ሥጦታ መቀበል እና ማስተናገድ ይቻላል። በዚህም ወንድሞቼ እና እኅቶቼ ለጌታ ፍቅር ምሥክርነት የምታጭባቸው የጸጋ ሥጦታዎች እና መዳኔን የምፈጽምባቸው መስቀሎች ናቸው እንጂ ያለ ዋጋ በከንቱ የተጫኑብኝ ሸክሞች አይደሉም።

ክርስትያን በአንድ በኩል እግዚአብሔርን የሚወድበት እና የሚያሰላስልበት በጸሎት የታጀበ የሕይወት ክፍል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ ነገር የሚያከናውንበት፣ እግዚአብሔርን እምብዛም የማይፈልግበት የሚባል በተቃርኖ የቆመ ሁለት የሕይወት ክፍል የለውም። ክርስትያን ሕይወቱ በክርስቶስ መልክ በአብ ፊት መመላለስ ነው፤ በአብ ፊት የሚመላለስ ክርስትያን ከፍቅር እና ከምኅረት የሚበልጥ ሌላ ጽድቅ የለውም፤ በመሆኑም ፍቅር ለክርስትያን ምርጫው ሳይሆን ክርስትያን የሆነበት የማንነቱ አስኳል ነው። በመሆኑም ፍቅር ሁሉንም የሕይወት ጉዞ ጠቅልሎ የሚይዝ ከመሆኑም ባሻገር በሰማያት ጭምር ያለማቋረት የምናድግበት መንፈሳዊ ልምላሜ ነው። ይህ ዕድገት በሕይወት ዘመን ሁሉ ዕለት በዕለት በመንፈሳዊነት እየጎለመስን የምንሄድበት በመሆኑ ትዕግሥትን የሚጠይቅ፣ ራስን መመልከትን፣ በእግዚአብሔር ቃል እና በምሥጢራት መጎልመስን የሚፈልግ ቁም ነገር ነው። በመሆኑም በሰው እና በእግዚአብሔር ፊት በሞገስ እና በጥበብ ከፍ ከፍ ካለው ጋር አብረን እንጓዝ ዘንድ እየጋበዘን እንዲህ ይላል፡-

“ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ 11፡29)።

ይቀጥላል...

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት