ቅዱስ ዮሴፍ - ጽጌ ደንጎላት (መኃ ፪፡፩ )
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Saturday, 03 June 2023 06:53
- Written by Super User
- Hits: 853
- 03 Jun
ቅዱስ ዮሴፍ - ጽጌ ደንጎላት (መኃ ፪፡፩ )
አበቦች የእግዚአብሔርን መጋቢነት የሚመሰክሩ የፍጥረት ውበቶች ናቸው። እግዚአብሔር በየወቅቱ እንደ ፈቃዱ በጎነት ሸልሞ ያስጌጣቸዋል፤ እግዚአብሔር ያለበሳቸውን ውበት፣ ለዛ እና ፍጥረት ሆነው በመገኘታቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚገለጥበት ነገር እንዴት ያማረ እንደሚሆን ማሳያዎች ናቸው። አበቦች ፍሬ በማፍራታቸው፣ በውበታቸው፣ በተሰጣቸው መዓዛ ሁሉ የእግዚአብሔርን ክብር ያንጸባርቃሉ። ውበታቸው እና መዓዛቸው መንፈስን እና አእምሮን ወደ ፍጥረት ባለቤት ከፍ አድርጎ መልዕተ ባሕርያዊ በሆነው አምላክ ቸርነት እና ጥበብ ላይ እንድናሰላስል ይጋብዙናል። ኢየሱስ ራሱ በአበቦች ውበት እና ጸዳል በመገረም “አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ!... ሰሎሞን እንኳን በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም” (ሉቃ 12፡27) እያለ ስለ ድንቅ ተፈጥሮአቸው ይመሰክራል። አበቦች በማበባቸው ወይም ለተፈጠሩበት ዓላማ ሆነው በመገኘታቸው የእግዚአብሔር መጋቢነት ምስክሮች ናቸው።
“ጽጌ ድንጎላት” የሚለው ሐሳብ ከመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ፪፡፩ የተወሰደ ሐሳብ ነው። ጽጌ ደንጎላት ማለት የሱፍ አበባ ማለት ሲሆን የሱፍ አበባ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጦ ከምናገኘው ከቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት እና ምስክርነት ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። የሱፍ አበባ የጸሐይን አቅጣጫ እየተከተለ የሚዘዋወር እና ከጸሐይ አቅጣጫ ጋር በመጽናቱ ውበቱን ጠብቆ መኖር የሚችል አበባ በመሆኑ ከቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት ጋር በእጅጉ ይዛመዳል። ቅዱስ ዮሴፍ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየሰማ የሚመላለስ፣ የሚያደርገውንም ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ድምጽ የተነሳ ብቻ የሚወስን እና እግዚአብሔር ከተናገረው ነገር በተለየ አቅጣጫ የማይራመድ፣ የሕይወት ዘመን ዕይታውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረገ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ጻዲቅ ሰው” ብሎ የመሰከረለት ታላቅ የእምነት ሐዋርያ ነው። የሱፍ አበባ ውበት እና ፊቱን ወደ ጸሐይ አቅጣጫ አዙሮ ቀና ብሎ እየተመለከተ የሚኖር የመሆኑ ቁም ነገር የጽድቅ ጸሐይ የሆነውን ክርስቶስን እየተመለከተ የሚኖርን እያንዳንዱን አማኝ ሕይወት ይወክላል። በመሥዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታችን እኛም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ወደ ጽድቅ ጸሐያችን እንመለከት ዘንድ ዲያቆኑ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ!” እያለ ይጋብዘናል። ቅዱስ ዮሴፍ ምልከታውን ሁሉ በዚህ አቅጣጫ በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ ምሥጢር የሆነውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሕይወቱ በተግባር ተርጉሞ የተመላለሰ ቅዱስ ነው።
የሱፍ አበባ ወጥነት የቅዱስ ዮሴፍን ድንግላዊ ሕይወት ያመለክታል፤ ለእግዚአብሔር ዓላማ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ራሱን የሰዋ ቅዱስ መሆኑን እንድናስተውል ዕድል ይሰጠናል። የሱፍ አበባ ውበት፣ ንጽሕና እና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚመለከት ቁመና የቅዱስ ዮሴፍን ድንግልና፣ ንጽሕና እና የእግዚአብሔርን ድምጽ ለማድመጥ ያለውን ዝግጁነት ያመለክታል። ቅዱስ ዮሴፍ የሱፍ አበባ ተብሎ መጠራቱ ሕይወቱን ሁሉ ወደ ጽድቅ ጸሐይ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አድርጎ መመላለሱን ለማመላከት ነው። ከዚህም ባሻገር አበቦች የሚፈኩት፣ መልካም መዓዛ የሚሰጡት እና በልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት የተፈጥሮን ውበት የሚያንጸባርቁት ዕይታን ሁሉ በራሳቸው ላይ ለማድረግ ሳይሆን ይልቁንም የሰውን መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ለማድረግ ነው። ወደ ታሪካችን እና ወደ ሰውነታችን የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ይለብስ ዘንድ እና በእርሱም በኩል እኛ ሁላችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንችል ዘንድ ቅዱስ ዮሴፍ ድንግልም አባትም ሆኖ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ!” በሚል ሕይወት እይታችንን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ከፍ እናደርግ ዘንድ የሚጋብዘን መልካም መዓዛ ያለው አበባ ሆኖ ይታያል። ይህንን የቅዱሳን ሕይወት በሚመለከት በሀገራችን ሥርዐተ አምልኮ በዘመነ ጽጌ ወቅት ከምናደርሳቸው ጸሎቶች መካከል አንዱ “መዓዛሆሙ ለቅዱሳን ከመ ጽጌ ደንጎላት ፣ወከመ ሮማን ዘውስተ ገነት ፣ይትፌሥሑ ጻድቃን የውሃን ውሉደ ብርሃን ፣በትፍሥሕት ዔሉ ውስተ አድባር” የሚል ነው። ይህም በትርጓሜው “የቅዱሳን መዓዛ በደብረ ገነት (በአትክልት ሥፍራ) እንዳለች የሮማን ፍሬ፣ እንደ ሱፍ አበባ ነው፤ የብርኀን ልጆች የሆኑ የዋሃን ጻድቃን ደስ ይበላቸው በተራሮች ላይ ደስ እየተሰኙ ዞሩ” ማለት ነው።
አበቦች ውበትን፣ ንጽህናን፣ ራስን መስጠትን፣ ትዕግሥትን፣ ብስለትን፣ ፍቅርን እና በእግዚአብሔር መጋቢነት መታመንን የሚወክሉ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በጊዜ ሂደት መጠውለጋቸው የሰውነታችንን አፈርነት እንዲሁም ደግሞ እንደገና ማበባቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ያገኘነውን አዲስ ሕይወት የሚያመላክቱ ናቸው። በመሆኑም አበቦች የእግዚአብሔርን ጥበብ እንድናሰላስል እንደሚጋብዙን እና መንፈሳችንን ወደ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ እንደሚያደርጉት እንዲሁ ቅዱስ ዮሴፍ በድንግልናው፣ በታማኝነቱ፣ የእግዚአብሔርን ድምጽ በመስማቱ፣ በተዓዝዞው፣ በአባትነቱ እና እግዚአብሔር ለሰጠው ተልዕኮ እስከ መጨረሻው በመታመኑ እያንዳንዳችን ደግሞ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለተቀበልነው ጥሪ፣ ለተሰጠን አገልግሎት እና ተልዕኮ ሊኖረን የሚገባውን እምነት እና ተዓዝዞ እንድናስተውል ይጋብዘናል። ቅዱስ ዮሴፍ “የሱፍ አበባ” ተብሎ መጠራቱ ዕይታችንን ከራሳችን ላይ አንስተን የሕይወት ምንጭ በሆነው በእውነተኛው የጽድቅ ጸሐይ በኢየሱስ ክርስቶ ላይ አድርገን እንድንመላለስ፣ የሕይወታችንን አቅጣጫ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድናዞር የሚጋብዘን ቁም ነገር ነው።
መልካም የቅዱስ ዮሴፍ ዓመታዊ የንግሥ በዓል!
ሴሞ