እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ኀዘንተኛ ማዘን ይፈቀድለት ይሆን?

ኀዘንተኛ ማዘን ይፈቀድለት ይሆን?

in-loving-memory-candle-gifሞት የማይለመድ የሕይወት አካል ነው። ልጅን ማጣት ያውም የመጀመርያ ልጅን ማጣት ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጽ ቋንቋ የለም። የሕማሙን ማንገብገብ፣ የስቃዩን ልክ፣ የባዶነቱን ጥልቀት፣ የተስፋ መቀረጡን ጨለማ የሚለካ የሰው ልጅ ጥበብ አይገኝም። ኀዘን በዕንባ በኩል የሚፈስ ከነፍስ ጥልቅ ማንነት ውስጥ የሚመነጭ የጣር ደም ነው። ኢየሱስ በጌተ ሰማኒ የአትክልት ስፍራ “የደም ላብ” እንዳላበው ስናነብ የደም ላብ ምን አይነት እንደሆነ ጥያቄ ይፈጥራል። የሰው ልጅ እንዴት የደም ላብ ያልበዋል? ኀዘን የደም ላብ፣ የደም ዕንባ እንዲወርሰን የነፍሳችንን ንፍቀ ክበብ ለስቃይ የሚከፍት ኃይለኛ እሳት ነው። በዚህ እሳት የተለበለበ ሰው በውስጡ ያለውን መንገብገብ በዕንባው አይገልጸውም፤ ጮሆ አይወጣለትም፤ ሞት ምን ማለት እንደሆነ በነፍሱ እና በስጋው መካከል የተካፈለ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ ሌላ ሰው ሆኗል። ይህ የሰው ልጅ የሕይወት ጉዞ እንደ ባህሉ እንደ ሥርዐቱ እንደ ደንቡ በየአካባቢው በተለያየ መንገድ ይገለጣል።

በሀገራችን ባሕል ለቅሶ መድረስ፣ ኀዘንተኛን ማጽናናት እጅግ ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው ማኅበራዊ እሴቶች መካከል አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ነው። ለቅሶ ባለበት ሠፈር ሠፈርተኛው ሁሉ አብሮ ኀዘን ይቀመጣል፣ ኀዘኑን ተባብሮ ያወጣል፣ ጎረቤት ኀዘኑ እስኪሽር ወትሮ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ይቆጠባል፣ የሰፈር ወጣቶች ድንኳን ተክለው፣ ወንበር ተሸክመው፣ ለቀስተኛ አስተናግደው፣ ሌሊቱን ደግሞ ድንኳን ሲጠብቁ ያድራሉ። ቀብር እንደ እምነት፣ እንደ ሥርዐቱ ተፈጽሞ፣ ሠልስት እንደ አዲስ ተለቅሶ፣ ሰባት፣ አሥራ ሁለት፣ አርባ፣ ሰማንያ ተብሎ ለቀስተኛ ጥቁር ልብስ እንዲያወልቅ ተመክሮ ተጽናንቶ ኀዘን ያልፋል።

ነገር ግን ኀዘንተኛ የሚያጽናና ሰው ኀዘን በነፍስ ውስጥ የሚገለጥባቸውን ባሕርያት ሊያውቅ እና እነዚህን በሚመለከት ኀዘን የደረሰበትን ሰው ሊያጽናናው ይገባል። በዚህም ኀዘንተኛውን ሲያጽናና ኀዘኑን ከማቃለል፣ ኀዘንተኛውን ከመቆጣት፣ “የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው!” ብሎ ለነገሮች አቋራጭ መውጪያ መንገድ ከመፈለግ፣ “ኀዘን ሲበዛ ጥሩ አይደለም! ተው አታልቅስ!” ወ.ዘ.ተ. በማለት ኀዘንተኛውን ከተፈጥሮአዊ እና ባሕርያዊ የኀዘን ዑደት እንዳይከለክለው መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እንዲህ ያሉት ንግግሮች እና ምክሮች ኀዘንተኛውን ከማረጋጋት ይልቅ የበለጠ ወደ ጥልቅ ኀዘን ውስጥ የሚጨምሩት እና ራሱን እንዲጠራጠር የሚያደርጉት በመሆናቸው ልናስወግዳቸው ያስፈልጋል። ይልቁንም ኀዘኑ ጤናማ ሰብዓዊ እና ባሕርያዊ መሆኑን ማሳወቅ ኀዘንተኛውን የበለጠ ይረዳዋል። ምንም እንኳን ኀዘን በውስጡ ስቃይ ያዘለ ቁም ነገር ቢሆንም ቅሉ ከሰው ልጅ የሕይወት መልኮች አንዱ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል።

ኀዘን የሰውን ልጅ በመላ ማንነቱ የሚነካ ቁም ነገር ነው፤ ኀዘን በነፍሳችን ላይ ከሚያደርሰው ስነ ልቡናዊ ቀውስ በተጨማሪ በአካላዊ ማንነታችን ላይ በግልጽ ተገልጦ ይነበባል። ምንም እንኳን ትክክልኛ ቁስል ወይም ህማም ባይሆንም ኀዘን በአካላዊ ማንነታችን ላይ የመደበት እና ከፍተኛ የሆነ አቅም የማጣት ነገር ያስከትላል። ተክለ ሰውነታችን በሸክም የተጎዳ ይመስላል፣ የፊታችን ገጽታ ይጠወልጋል፣ ሕያውነት የተነጠቀ ገጽታ ይታያል፣ የሆነ ከሕይወታችን ተቆርሶ የተወሰደ ምን እንደሆነ በውል ያላስተዋልነው ባዶነት ወደ አንድ ጎን ዘንበል አድርጎን ይስተዋላል፤ የምናደርገው ነገር ሁሉ ልምሻ ያለበት፣ ለምንም የማይሆን እና እዚህ ግባ የማይባል ነገር ይሆናል፤ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ በትዳር መካከል ከትዳር አጋር ጋር የፍቅር ጊዜ ለማሳለፍ መቸገር፣ ከሰዎች ጋር ለመቀላቀል፣ ለመጫወት ፍላጎት ማጣት ወ.ዘ.ተ. እነዚህ ኀዘኑ የሚገለጥባቸው መልኮች ከኀዘንተኛው ጋር ለረጅም ጊዜ የሚቆዩበት ሁኔታ ሲፈጠር ኀዘንተኛው ሊገነዘበው በማይችለው መልኩ ምንም ሳይሰራ በእጅጉ ይደክመዋል፣ እንቅልፍ ለመተኛት ይቸገራል፤ ተሳክቶለት እንቅልፍ ቢያሸልበው እንኳን ጥልቅ የሆነ እንቅልፍ ሳይተኛ ተመልሶ በድካም ይነቃል፣ ቀኑን በሙሉ ፍዝዝ እንዳለ፣ ነገሮች እንደተዘበራረቁበት እና አንድ ነገር ላይ ማስተዋል እንደተሳነው ጊዜ ይሄዳል። ከዚህም ባሻገር በኀዘንተኛው ፊት ላይ በሚታይ መልኩ የፊት ገጽታ መለወጥ፣ የአፍ መድረቅ፣ የራስ ምታት፣ የወገብ ህመም፣ የአንጀት ባዶ መሆን፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ፍጹም ባዶነት ወ.ዘ.ተ. ይስተዋላሉ።

በኀዘን ወቅት ኀዘንተኛውን በመላው ማንነቱ ፊት ለፊት የሚጋፈጡት ስሜቶች ማዕከላዊውን ስፍራ ይይዛሉ። በኀዘን መኮራመት፣ ረዳት የሌለው እንደሆነ መሰማት፣ ብቸኝነት፣ የመተው ስሜት እና በሞት ያጣውን ወዳጅ በመናፈቅ ውስጣዊ መቃተት ይያዛል። ነገር ግን የዚህ ወዳጅ ሞት ለረዥም ጊዜ ሲታገለው የቆየው በሽታ ያስከተለው ሲሆን ኀዘንተኛው በተወሰነ መልኩ በቶሎ የሚጽናናበት ዕድል ያገኛል።

እነዚህ ስሜቶች በእነርሱ እውነታ ውስጥ ከቆመው ሰው ውጪ ሌሎች ሰዎች የሚረዷቸው እውነታዎች ባለመሆናቸው የለቀስተኞች ምክር እና ተግሳጽ ወይም ትርጓሜ አያስፈልጋቸውም። ኀዘንተኛው ራሱ በውስጡ እየተከናወነ ያለውን ነገር በቅጡ የማይረዳበት፣ እንግዳ የሆኑ ድንገቴ ስሜቶች በዚህ ጊዜ ይከሰታሉ፤ በዚህም የቁጣ፣ የኃይለኝነት፣ የጸጸት፣ የጥፋተኝነት ስሜቶች እና ቅጽበታዊ እርምጃዎች የሚጠበቁ ክስተቶች በመሆናቸው ሊያስተዛዝኑ የሚሄዱ ሰዎች የኀዘንተኛውን ነጻነት በማይገታ መልኩ ነገር ግን ኃላፊነትን እና ጥንቃቄን በተሞላበት አኳኋን ኀዘንተኛውን በዕይታቸው ውስጥ አድርገው እንቅስቃሴውን በንቃት መከታተል ያስፈልጋል።

አብዛኛውን ጊዜ ኀዘንተኛው በቁጣ፣ በእልህ እና በኃይለኝነት ስሜት ይረበሻል። እነዚህ ቅጽበታዊ ባሕርያት ለሚያጽናኑት ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለኀዘንተኛው ለራሱ እንግዳ ስሜቶች በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል። ይህ የቁጣ፣ የእልህ እና የኃይለኝነት ስሜት በአንድ በኩል ምንም ማድረግ ካለመቻል ቁጭት የሚመነጭ ራስን ጥፋተኛ በሚያደርግ ከፍተኛ ጸጸት የሚነሳ ኃይል ነው። የዚህን ሰው ሞት ማስቀረት አለመቻሉ ኀዘንተኛውን ያንገበግበዋል፤ ይህ ውስጡን የሚበላ ከፍተኛ ቁጭት በመሆኑ ኀዘንተኛው በቁጣ፣ በእልህ፣ በኃይለኛ ጸጸት ይሰቃያል።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አይነቱ ድንገተኛ ባሕርይ ከፍርሃት የሚነሳ ነው። የሚወደው ሰው ሞት ኀዘንተኛውን ልክ እንደ ህጻን ረዳት አልባ እና ለብቻው የተተው እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል። በሆኑም ከሞተው ሰው ውጪ በዚህ ምድር እንዴት ብሎ ለብቻው እንደሚኖር አያውቅም፤ ስለዚህ “እኔ ካለ እርሱ”፤ “እኔ ካለ እርሷ” አልኖርም የሚል ፍርሃት ይይዘዋል። ትቶት የሄደውን ወዳጁን መውቀስ አይሆንለትም፤ በመሆኑም ይህ ፍርሃት እና ይህ ለምን ተውከኝ? ለምን ጥለኸኝ ሄድክ? የሚል ቁጣ ለሟች ለማቅረብ የማይቻል ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ይህ ቁጣ፣ ይህ እልህ እና ፍርሃት ወደ ሌሎች ሰዎች ይዘዋወራል። ሌሎች ሰዎች የሞቱ መንሴዎች ተደርገው ይታያሉ፤ በዚህ አይነት ለመጨረሻ ጊዜ ሟችን ያየው ሐኪም፣ ስልክ ያላነሳው ባለ መኪና፣ ነግሩን ብዙም ትኩረት አልሰጡትም የሚባሉት ሰዎች፣ በውስጠ ታዋቂነት ለፈውስ ያደረግሁትን ጸሎት ተቀብሎ ሞቱን ያላስቀረው እግዚአብሔር እዚህ ውስጥ ይካተታሉ። ይህ ቁጣ፣ እልህ እና ኃይለኝነት ከዚህ ባሻገር ኀዘንተኛው በራሱ ላይ ሊያደርገው ይችላል። ራሱን የወዳጁ ሞት መንስኤ አድርጎ በመቁጠር ራሱን ከመውቀስ ባለፈ ራስን እስከማጥፋት ድረስ ሊደርስ ይችላል።  

ኀዘን ዘወትር ከጥፋተኝነት እና ራስን ከመውቀስ ስሜት ጋር የተያያዘ ገጽታ አለው፤ ኀዘንተኛው በሞት የተለየውን ወዳጅ እያሰበ በነገሮች ራሱን ይወቅሳል። እንዲህ ባደርግ ወይም ባላደርግ ኖሮ፣ ጊዜ ሰጥቼ አዋርቼው፣ አጠገቡ ሆኜ፣ እንደምወደው ነግሬው ቢሆን ኖሮ ወ.ዘ.ተ. በማለት በዚያ ሰው ሞት ውስጥ ራስን ጥፋተኛ አድርጎ የማቅረብ እውነታ ብዙ ጊዜ ይስተዋላል። ይህ በመሰረቱ በሞት የተለየውን ሰው በሕይወት እንዳለ አድርጎ ከማሰብ እና ሞቱን አምኖ ለመቀበል ከመቸገር ጭምር የሚመነጭ ችግር ነው።

በኀዘን ውስጥ ጎልቶ የሚታየው እና የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ነገር “ፍርሃት” ነው፤ ፍርሃት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመነሳት ኀዘንተኛውን ተስፋ እንደሌለው እና ከሟች ባሻገር ያለው “የብቸኝነቱ ነገ” የማይገፋ እጅግ አስፈሪ ዘመን እንደሆነ አድርጎ ያቀርብለታል። የፍርሃት የመጀመርያው መልክ የባይተዋርነት ስሜት ነው፤ በመሆኑም ኀዘንተኛው በገጠመው ክፉ ኀዘን ምክኒያት ዓለም የተገለባበጠች እና የእርሱ ነገር ሁሉ ያከተመ መስሎ ይሰማዋል። በሞት ከተለየው ወዳጁ ተነጥሎ ኑሮውን መግፋት  ትርጉም የማይሰጥ ሕይወት ይሆንበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ በሞት የተለየው የቅርቡ ሰው እንደዚህ ባለ መልኩ ማለፉ የራሱን ዕጣ ፈንታ እና የሌሎች ወዳጆቹን ዕጣ ፈንታ እንዲጠይቅ ግድ በሚል ክስተት ከሞት እውነታ ጋር ፊት ለፊት ያጋፍጠዋል። ይህ የቅርብ ወዳጁ ሞት የሰውን ልጅ በቀላሉ ተሰባሪነት እና የሞትን ምሕረት አልባ ድንገተኛነት ፍንትው አድርጎ ስለሚያሳየው ራሱን እና ሌሎች የቅርብ ሰዎቹን ምን ያህል ጊዜ እንዳላቸው ስለማያውቅ እጅግ ጥልቅ ፍርሃት እና ስጋት ውስጥ ይገባል። በዚህም ከፍተኛ የስሜት መዘበራረቅ እና ነገሮችን ቅደም ተከተል የማስያዝ ቀውስ ውስጥ ስለሚወድቅ በቶሎ ሆድ ይብሰዋል፤ የራሱን ዕድል እና የሞተውን ወዳጁን አለመኖር በማሰብ በነገሮች ሁሉ መኃል በድንገት ከፍተኛ የኀዘን ስሜት ውስጥ ገብቶ እንደ አዲስ ለቅሶ እና ራስን መውቀስ ሊጀምር ይችላል። እነዚህ ስሜቶች በውስጣቸው ለምን ከሕመሙ መዳን አልቻለም? ወይም ለምን እርሱ ወይም እርሷ በዚህ በሽታ ተያዘች? ለምን እንዲህ በድንገት? ለምን እንዲህ በቶሎ ሆነ...? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ የያዙ ቁም ነገሮች ናቸው።

ከሞት መከሰት በኋላ ኀዘንተኞች በሞት የተለየውን ሰው በቅርበት አብሮአቸው እንዳለ ይሰማቸዋል። እንዴት እንደሆነ ለሰው ሊያስረዱ በማይችሉት ምሥጢራዊ፣ ነገር ግን አዎንታዊ በሆነ መልኩ በሞት የተለያቸው ሰው አብሮአቸው ያለ የሚመስላቸው፣ ጠረኑ፣ መገኘቱ አንዳንድ ጊዜ ድምጹ ወ.ዘ.ተ. የሚሰማቸው ብዙኀን ናቸው፤ የሞተው ወዳጅ በሕልም ዓለም ዳግም አብሮአቸው ሆኖ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ በሆነ መልኩ ጊዜ ሲያሳልፉ ወ.ዘ.ተ. ይመለከታሉ። እነዚህ ስሜቶች እና ሕልሞች በአእምሮአችን ውስጥ በቂ ትኩረት ያላገኙትን የኀዘን ገጽታዎች የሚያሳዩ ሲሆኑ በመጽናናት እና ኀዘንን በአግባቡ በማስተናገድ ሒደት ውስጥ የሚፈጠሩ ነገሮችን ማድበስበስ እና አባብሎ ማለፍ ወደዚህ አይነቱ የኀዘን አቅጣጫ ያመራል።

ኀዘንተኛን ለማጽናናት የሚሞክር ማንም ሰው አስቀድሞ ኀዘን ምን ማለት እንደሆነ ጊዜ ወስዶ ማሰብ ይገባዋል። ኀዘን በራሳችን ነፍስ እና ሥጋ ውስጥ አልፎ ካልቀመስነው በስተቀር በውጫዊ ምልከታ ብቻ ልንረዳው የሚቻለን ቁም ነገር አይደለም! በሀገራችን “የደረሰበት ያውቀዋል!” ይባላል፤ ኀዘን የደረሰበት እና በሚገባ በነፍስ ውስጥ ሲያልፍ የተሰማው ካልሆነ በስተቀር ሌላው የሚረዳው ቁም ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልጇን ሞት በሚመለከት በትንቢት ሲናገር የኀዘንን ጥልቀት እና ሕማም በተወሰነ መልኩ በቃላት እያስቀመጠ ኀዘን ምን መሆኑን በጭላንጭልም ቢሆን እናስተውል ዘንድ “የአንቺንም ነፍስ የኀዘን ሰይፍ ሰንጥቆት ያልፋል” (ሉቃ 2፡34-35) እያለ የኀዘንን ጥልቅ ቁስል ያስገነዝበናል።    

በመሆኑም ኀዘን በእያንዳንዳችን ነፍስ መካከል ሰንጥቆ የሚያልፍ ቁም ነገር እንደመሆኑ መጠን ማንም ሰው የማንንም ሰው ኀዘን ሙሉ በሙሉ መረዳት፣ መጠኑን መለካት፣ ጥልቀቱን መገመት አይቻለውም። ኀዘን በራሱ ወርቀ ዘቦ የሆነ ምሥጢር ነው።  ከኀዘንተኛው ጋር ፊት ለፊት መገናኘት እና እርሱን ለማጽናናት መሞከር ከራሳችን የኀዘን ትዝታ ጋር ፊት ለፊት ያጋፍጠናል፤ ምናልባትም የአብዛኛው ለቀስተኛ እንባ ከራሱ የኀዘን ቁስል የሚመነጭ የገዛ ራሱ ኀዘን የሚቆሰቁሰው አዲስ እንባ ነው። በመሆኑም በራስ እንባ እና ብዥታ ውስጥ ቆሞ የሌላኛውን ሰው ኀዘን ለመረዳት፣ ለመተርጎም እና ለማረም ወይም በቶሎ ለማጽናናት መሞከር የሰውየውን ኀዘን እንደ መዝረፍ፣ መብቱን እንደመግፈፍ እና በነፍስ ውስጥ ያለውን እውነታ በጭካኔ እንደ መካድ ነው። ይልቁንም ከኀዘንተኛው ጎን መቆም፣ ጊዜ ወስዶ ኀዘኑን እንዲያወጣ መፍቀድ፣ በአጭር ጊዜ በቶሎ ተጽናንቶ ወደ መደባኛ ማንነቱ እንዲመለስ አለማስጨነቅ፣ የራሳችንን የመጽናኛ ጊዜ ገደብ ለክተን ኀዘንተኛው በዚያ ወሰን እንዲንቀሳቀስ ግድ አለማለት እጅግ መሰረታዊ እና አስፈላጊ ነገር ነው። በመሰረቱ በኀዘን መካከል ያለፈ ሰው ሙሉ በሙሉ እንደ ቀደመው ማንነቱ ሊመለስ አይቻለውም! ከሞተው ወዳጁ ጋር ተቆርሶ የሞተ ማንነት እንዳለው ማስተዋል እና በዚህ ማንነቱ መቀበል እጅግ አስፈላጊ ነው።

ሰዎች ከሞት እውነታ ጋር ተጋፍጠው ኀዘን ሲቀመጡ በቶሎ ከኀዘናቸው እንዲወጡ እንደውም እንዳያለቅሱ፣ እንደሚገባቸው እንዳያዝኑ፣ ኀዘን እና ለቅሶ ማብዛት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ነገር እንደሆነ እንዲያስቡ እና የጸጸት ስሜት እንዲኖራቸው በሚያደርግ መልኩ ማጽናናት የሚመስል ወቀሳ ማቅረብ፣ መቆጣት፣ ጥቁር ልብስ እንዲያወልቁ ማስገደድ ወ.ዘ.ተ. ለኀዘንተኛው መጽናናት እና ወደ መደበኛ ሕይወቱ መመለስ የታሰቡ ተግባራት ቢመስሉም ቅሉ፤ ጠለቅ ተብሎ ሲታዩ ግን ለቀስተኛው የኀዘንተኛውን ኀዘን እና ምሬት የሚቋቋምበት እና የሚሸከምበት ትከሻ ስለሌለው ኀዘኑ በቶሎ አልቆ እንዲገላገል ኀዘንተኛውን ይቆጣል፣ ይገስጻል፣ ነገሩን ሁሉ መንፈሳዊ አድርጎ ኀዘንተኛውን ከሰው ባሕርያዊ ማንነት ባሻገር መልዕልተ ባሕርያዊ መረዳት እንዲኖረው ግድ ይለዋል። እንደነዚህ ያሉ ቁም ነገሮች በተለይም ኀዘንን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር አለፍ ሲልም እንደውም በኀዘንተኛው ላይ እንደተገለጠ እንደ እግዚአብሔር ቁጣ እና ቅጣት አድርጎ ከመመልከት እጅግ አደገኛ እና ስንኩል ከሆነ መረዳት የሚመነጩ ነገሮች ናቸው። በመሆኑም ነገሮችን መንፈሳዊ ገጽታ ስናላብስ፣ የኀዘንተኛውን ነፍስ ጥልቅ መቃተት በእኛ የተወሰኑ ቃላት ብቻ ለመፈወስ መነሳት፣ ብሎም  “የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው! በቃ ምን ማድረግ ይቻላል?” ወ.ዘ.ተ. በሚሉ ቃላት የራሳችንን ኀዘን የመሸክም ስንፈት በመንፈሳዊ ካባ መጠቅለል ምን አይነት የእግዚአብሔር መልክ በሰዎች ልብ እና አእምሮ ውስጥ እየቀረጽን እንደሆነ እና አንዳንዶቹ ንግግሮች ከኀዘኑ በላይ የሚያቆስሉ ጥራዝ ነጠቅ አምባ ገነን ፍረጃዎች በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድናደርግ ያስፈልጋል። በመሆኑም እነዚህ ቁም ነገሮች ኀዘንተኛውን ከማጽናናት ይልቅ የበለጠ የሚያቆስሉት እና የበለጠ የሚሰብሩት መሆኑን መረዳት እና በተቻለ መጠን ማስወገድ ያስፈልጋል።

ኀዘንተኛውን እንድንረዳው፣ በአሁናዊ ማንነቱ እንድንቀበለው፣ ኀዘኑን እንድንፈቅድለት ያስፈልጋል! ኀዘን አሁናዊ መብቱ እና ማንነቱ ነው፤ በመሆኑም የማጽናናታችን በጎነት የኀዘንተኛውን ሉዓላዊ ድንበር የሚያከብር ስለመሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። “እስቲ ትንሽ ወጣ በል፣ እስቲ ትንሽ ዞር ዞር በይ፣ እዚህ ቤት ውስጥ ተቀምጦ መዋሉ እኮ አይጠቅምም...” ወ.ዘ.ተ. የሚሉት ምክሮች በዋናነት ኀዘንተኛው ኀዘኑን እንዲረሳ የሚያደርጉ ሙከራዎች ናቸው እንጂ ኀዘንተኛው እንዲጽናና የሚያግዙት ግብዐቶች አይደሉም። ኀዘን የሚረሳ፣ ሊረሳ የሚችል የሆነ የሕይወት ክፍል ገጠመኝ አይደለም። ከኀዘን መጽናናት እንጂ ኀዘንን መርሳት አይቻልም! መጽናናት ደግሞ አለማልቀስ፣ አለመድከም፣ ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ወ.ዘ.ተ. ማለት አይደለም። መጽናናት ፈውስ ነው። እያንዳንዱ ፈውስ ደግሞ የራሱ የሆነ ማንም ሊሰፍርለት የማይቻለው ጊዜ ያስፈልገዋል። ለኀዘንተኛው ኀዘኑን የሚወጣበት የራሱን ጊዜ ከመፍቀድ እና ጊዜ ከመስጠት የበለጠ የሚያጽናናው ነገር የለም። ለምንወደው ሰው የምንሰጠው እጅግ ውድ ስጦታ መሰረቱ ጊዜ ነው።

በለቅሶ ባሕላችን ውስጥ ኀዘንን መፍቀድ መለማመድ ያስፈልጋል፤ ስንቱ በለቀስተኛ ቁጣ እና ተግሳጽ በጊዜው እንደሚገባው ኀዘኑን ሳያወጣ እና ሳይጽናና ቀርቶ ዛሬም ድረስ ከኀዘን ድባቴ እና ጠባሳ ነጻ ያልወጣ እንዳለ ቤት ይቁጠረው። እንደ ማኅበረሰብ በለቅሶ እና በኀዘን ዙርያ ያሉን ባህሎች፣ እምነትቶች እና ስነ ልቦናዊ ቁም ነገሮች የሚያቀርቧቸው በርካታ ሀገር በቀል ውብ እሴቶች አስፈላጊ ሆነው ሳሉ ኀዘንተኛን በማጽናናት ጉዳይ ላይ መሰረታዊ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ኀዘንተኛው አብዛኛውን ጊዜ እኛ በሰፈርንለት የጊዜ ሰሌዳ ኀዘኑን እንዲወጣ ይገደዳል። ኀዘኑ፣ ስብራቱ፣ በነፍሱ መካከል ያለፈው ሰይፍ፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችለው ባዶነት ወ.ዘ.ተ. መንፈሳዊ ገጽታ ተችሮት የማይታገለው፣ የማይከሰው፣ የማይወቅሰው ነገር ሆኖ ከኀዘኑ ባሻገር ከዚህ ማኅበረሰባዊ የደቦ ፍርድ ጋር ደግሞ ይጋፈጣል። አልፎ ተርፎ “ሰው እንደ ቅጠል እየረገፈ ነው!” እንደውም አንተ፣ አንቺ አስታምመህ፣ አስታምመሽ ወ.ዘ.ተ. እየተባለ ኀዘኑ በሌሎች ሰዎች ኀዘን እና ስቃይ ልክ ዋጋ ይተመንለታል፤ ወይም ደግሞ እንደውም “ይህን ያህል ዓመት ኖረው፣ ወግ ማዕረግ አይተው ነው ያለፉት ማመስገን ነው የሚገባው!” ተብሎ ይገሰጻል። የምሥጋና ንፉግ እንዳይሆን ከኀዘኑ ደጃፍ ምሥጋናውን የሚቆጥር እና የሚሰበስብ አምላክ መኖሩ በተዘዋዋሪ ይነገረዋል። አልያም ልጅ የሞተባቸው ወላጆች “እናንተ እኮ ገና ወጣቶች ናችሁ! ዳግም ሌላ ልጅ ደግሞ መውለድ ትችላላችሁ!” ወ.ዘ.ተ. እየተባለ ለማጽናናት ይሞከራል፤ ነገር ግን እንዲህ ያሉት ንግግሮች ከሚያጽናኑት በላይ የሚያቆስሉት ይበልጣል። በለቅሶ ባሕላችን ውስጥ የሰውን ኀዘን ሰፍሮ መስጠት፣ ኀዘንተኛው ሊኖረው የሚገባውን የስሜት አይነት እና ይዘት መለካት ወ.ዘ.ተ. የተለመደ ነው። ኀዘኑ ተሰፍሮ፣ ስሜቱ ተቆጥሮ ይሰጠዋል! ይህ ኀዘንተኛውን መፈናፈኛ የሚያሳጣ፣ ኀዘኑ እንዳይወጣለት የሚያግድ እና በገዛ ራሱ ኀዘን እንኳን ነጻነት እንዳይኖረው የሚያደርገው ስለሆነ ለከፋ የስነ ልቦና ቀውስ ብሎም አለፍ ሲል ራስን ወደ ማጥፋት እና ለዚህ ሁሉ ስቃይ መጨረሻ ወደ ማበጀት ሐሳብ ሊያመራው ስለሚችል ለቀስተኛው ይህን አይነት ቁም ነገሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኀዘንተኛውን የሚያጽናናባቸውን መንገዶች እንደገና መለስ ብሎ መከለስ ይገባዋል።

ከኀዘንተኛው ጋር የሚደረጉ ንግግሮች ጥንቃቄ የተሞላባቸው እና የኀዘንተኛውን የስሜት ደረጃ፣ የኀዘኑን ጥልቀት እና የምሬቱን ጥግ ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን ይኖርባቸዋል። “ኀዘንህ ይገባኛል! እረዳሃለሁ!” ወ.ዘ.ተ. የሚሉ ንግግሮችን ማስወገድ ተገቢ ነው። እንዴት ብለን ነው የኀዘንተኛው ነፍስ ውስጥ ያለውን ስቃይ መረዳት የምንችለው? እንዴት ብለን ነው የኀዘንተኛው ነፍስ ጥልቅ ስብራት እና ኀዘን የሚገባን? ኀዘንተኛው በሚያሳየው ውጫዊ ቁም ነገር መረዳት የምንችለው ወደ ውጪ ማውጣት እና ማሳየት የቻለውን ያህል ብቻ ነው። በውስጡ እየሆነ ያለውን፣ ነፍሱን እያንገበገበ ያለውን ኀዘን ማየት፣ መረዳት፣ መስፈር የሚሞከር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከኀዘንተኛው ጋር የሚደረጉ ንግግሮች እና ለማጽናናት የሚደረጉ ሙከራዎች በሙሉ የኀዘንተኛውን ነባራዊ እውነታ ማዕከል ያደረጉ ቢሆኑ የበለጠ ኀዘንተኛዉን ይረዳሉ፤ የንግግሩ፣ የማጽናናቱ እና ለቅሶ የመቀመጡ ዋነኛ ነጥብ የእኛ ስነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ መልእክት ሳይሆን ይልቁንም መካከለኛው ነጥብ ኀዘንተኛውን በአሁናዊ ማንነቱ መቀበል እና ኀዘኑን መፍቀድ መቻል ነው።

በዚህ ውስጥ በጊዜ ሂደት ከኀዘንተኛው ጋር የሚደረጉ ንግግሮች ሦስት መሰረታዊ ቁም ነገሮችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። እነዚህም ቁም ነገሮች በየትኛውም አይነት ኀዘን ውስጥ ያለን ሰው ለማጽናናት በምናደርገው ጥረት በእጅጉ ሊያግዙ የሚችሉ ናቸው። እነርሱም፡- 1.  ኀዘንተኛውን በአሁናዊ ማንነቱ መቀበል እና ኀዘኑን ማክበር፤ 2 ሐቀኛ የሆነ ማስመሰል ያልተቀላቀለበት ማስተዛዘን፤ 3 የኀዘንተኛውን ሁኔታ እና ስሜቱን መረዳት ናቸው።

1.  ኀዘንተኛውን በአሁናዊ ማንነቱ መቀበል እና ኀዘኑን ማክበር፡-

የመጀመርያው ቁም ነገር ኀዘንተኛውን በአሁናዊ ማንነቱ ተቀብሎ ኀዘኑን እንዲያወጣ መፍቀድ ነው። ኀዘኑን አለማቃለል፣ አለማጣጣል፣ ኀዘኑን አለመገመት፤ ይልቁንም ኀዘኑን ማክበር፣ ተገቢውን ጊዜ እና ነጻነት መስጠት ያስፈልጋል። በመሆኑም ኀዘንተኛውን በሞራላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ስነ ልቦናዊ ምክሮች ሐሳቡን ለማስቀየር ከመሞከር ይልቅ ኀዘንተኛው የራሱን ኀዘን በቅጡ እንዲወጣ ጨዋነት እና ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ ልንገናኘው ያስፈልገናል። የለቀስተኛው ድርሻ ኀዘን የደረሰበትን ሰው በሌሎች ሞራላዊ ነገሮች ከመመዘንና ኀዘኑን ከመስፈር ይልቅ ኀዘኑን እንዲወጣ አካባቢውን ለኀዘኑ ነባራዊ ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በመሆኑም ኀዘንተኛውን በኀዘን ጉዞው መከተል፣ አብሮ መጓዝ፣ የኀዘንተኛውን ስቃይ አብሮ መሸከም ኀዘንተኛው በዚህ ጉዞው ኀዘኑን በወደደው መንገድ እንዲወጣ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል። ኀዘንተኛው ስሜቱን፣ ተስፋ መቁረጡን፣ ፍርሃቱን፣ ጩኸቱን ወ.ዘ.ተ. በነጻነት እንዲገልጽ ዕድል የሚሰጥ ማስተዛዘን ጤናማ ማስተዛዘን ነው፤ በመሆኑም “ተው! እንደዚህ አይባልም! እግዚአብሔር አይወድም! ምነው አንተ? ምነው አንቺ?” ብሎ ኀዘንተኛውን መውቀስ ተገቢ አይደለም።

2 ሐቀኛ የሆነ ማስመሰል ያልተቀላቀለበት ማስተዛዘን፡-

ኀዘንተኛውን ለማጽናናት የምንናገራቸው ነገሮች እና የምናነሳቸው ቁም ነገሮች በዚህ የኀዘን ወቅት ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባሻገር ከኀዘንተኛው ጋር ባለን የሕይወት ግንኙነት በሕይወታችን በተግባር የሚገለጡ ስለመሆናቸው መገንዘብ ያስፈልገናል። በንግግራችን፣ በማጽናናታችን እና በተግባራችን መካከል በጤናማ መስተጋብር የተያያዘ ተመጋጋቢነት ከሌለ ኀዘንተኛው የበለጠ ይሰበራል። ኀዘኑን የተካፈልኩ፣ ሕማሙን የታመምኩ በማመሰል የምናገረው ነገር እውነተኛ ካልሆነ መገለጡ የማይቀር በመሆኑ ኀዘንተኛው የበለጠ ባይተዋር እንዲሆን፣ ማንም የለኝም ብሎ እንዲያስብ እና በጥልቅ ብቸኝነት እንዲሰቃይ መንገድ ይጠርጋል። መጽሐፈ ምሳሌ ይህንን በሚመለከት የሚከተለውን ኃይለ ቃል ይናገራል፤ “ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤ ጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል” (ምሳሌ 15፡4)። በመሆኑም ሐቀኛ የሆነ ማስተዛዘን ኀዘንተኛው የበለጠ ልቡን እንዲከፍት፣ ስቃዩን እንዲያካፍል፣ ሸክሙን እንዲያጋራ፣ የነፍሱን ሲቃ እንዲተነፍስ የበለጠ መተማመን ስለሚሰጠው ለቀስተኛው ከኀዘንተኛው ጋር ባለው መስተጋብር በቃል እና በሥራ በሚገለጥ ወዳጅነት አብሮ ሊጓዝ ይገባዋል።

3 የኀዘንተኛውን ሁኔታ እና ስሜቱን መረዳት፡-

ኀዘንተኛን ማጽናናት ኀዘንተኛው በዚያ ቅጽበት ነገሮችን በሚያይበት ዐይን እና ኀዘኑን በሚረዳበት አእምሮ ውስጥ መቆምን ይጠይቃል። ለማጽናናት የሚሞክረው አካል በኀዘንተኛው ማንነት ውስጥ ራሱን ለመተካት እና የኀዘንተኛውን ነባራዊ እውነታ ያለማደባበስ እና ያለ ስም መስጠት ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለበት። በኀዘንተኛው ምሬት፣ ቁጣ፣ ፍርሃት፣ ለቅሶ እና በኀዘንተኛው “ለምን­?” ውስጥ መቆም የሚችል ለቀስተኛ ለኀዘንተኛው ሰው የመጽናናትን የተስፋ ጭላንጭል ለማሳየት ከማንም የበለጠ እድል አለው። በመሆኑም የኀዘንተኛውን ማንነት የራስ አድርጎ በመልበስ ውስጥ የምንካፈለው ስቃይ ኀዘንተኛውን ከወረደበት ሸለቆ ውስጥ ቀስ በቀስ ወደ ተስፋ ብርሃን ለመምራት ዕድል ይሰጠናል። ይህ “ከንፈር ከመምጠጥ” እና ከ “አዞ ዕንባ” የሚሻገር መከራን በነፍስ መካፈል፣ የኀዘን ሰይፍን መቋቋም የሚጠይቅ አገልግሎት ነው።

ኢየሱስ በኤማሁስ መንገድ ይጓዙ የነበሩትን ሁለት ደቀ መዛሙርት ያጽናናቸው በመንገዳቸው እና በጉዟቸው፣ በፍርሃታቸው እና በተስፋ መቀረጣቸው፣ በኀዘናቸው እና ሁሉ ነገር አበቃለት በሚል ማንነታቸው ውስጥ እስከ እውነት እና እስከ መጽናናት ብርሃን ድረስ አብሯቸው በመጓዝ ነው።

በመሆኑም ኀዘንን የሚፈቅድ፣ ኀዘንተኛውን በማንነቱ እና በአሁናዊ ሁኔታው አክብሮ የሚቀበል፣ ሐቀኛ የሆነ እና ማስመሰል ያልተቀላቀለበት፣ የኀዘንተኛውን ሁኔታ እና ስሜቱን፣ ፍርሃቱን፣ ጥያቄዎቹን፣ ለምን? የሚለውን ምሬቱን ወ.ዘ.ተ ያለማድበስበስ እና ያለማሳነስ፣ የሌላውን ኀዘን ባለመስፈር እና ለሌላው ኀዘን ወሰን ባለማበጀት፣ ሁለን ነገር መንፈሳዊ፣ ሞራላዊ እና ባሕላዊ ነገር አላብሶ እውነታን ባለመካድ ላይ የተመሰረተ ለቅሶ ደራሽነት እና ማጽናናት እንድንማር እግዚአብሔር ያግዘን።

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት