ዐቢይ ጾም 1ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Monday, 24 February 2025 04:58
- Written by Samson
- Hits: 276
- 24 Feb
ዐቢይ ጾም
በመጀመርያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት በጥንታዊቷ ቤተ ክርስትያን ክርስትያኖች ለፋሲካ በዓል የሚያደርጉት ዝግጅት ከሁለት እስከ ሦስት ቀን ቢበዛ ደግሞ ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ መንፈሳዊ ዝግጅት ነበር። የሊዮኑ ቅዱስ ኤሬኒዮስ (140-202 ዓ.ም.) በጽሑፎቹ የጥንት ክርስትያኖችን ልምምድ በሚመለከት የ40 ሰዓት የጾም-ጸሎት ዝግጅት ያደርጉ እንደነበረ ያወሳል። ዐቢይ ጾም ለዐርባ ቀናት የሚዘልቅ የጾም-ጸሎት ጊዜ ሆኖ በቀኖና ቤተ ክርስትያን የተወሰነው በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባዔ ነው። ከዚህም በመነሳት ከ፬ተኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አንስቶ ዐቢይ ጾም አሁን ባለው ይዘት ለዐርባ ቀናት ያህል የሚዘልቅ የቤተ ክርስትያን የጾም-ጸሎት ጊዜ ሆኖ በቤተ ክርስትያን ሕይወት ውስጥ ተገልጦ ይገኛል።
ይህ የጾም-ጸሎት ወቅት በተለይ አዲስ ወደ ቤተ ክርስትያን ሕብረት የሚጨመሩ ንዑስ ክርስትያኖች ምሥጢረ ጥምቀት ከሚቀበሉባት ከትንሳኤ ሌሊት ሥርዐተ አምልኮ ጋር ተያይዞ ቤተ ክርስትያን በልዩ መንፈሳዊ ተጋድሎ የምትጓዝበት የጸጋ ወቅት ሆኗል። በዚህ አይነት የተጠመቁ እና የቤተ ክርስትያን ሕብረት ውስጥ የሚገኙት በምሥጢረ ጥምቀት ለሚሆነው የአዲስ ልደት ሕይወት ከሚዘጋጁት ወንድሞች ጋር የጾም-ጸሎት ሕብረት የሚያደርጉበት፣ የቤተ ክርስትያን አይነተኛ መልክ የሚገለጥበት መንፈሳዊ ሱታፌ ሆኗል። ከዚህ ጊዜ ጅምሮ ዐቢይ ጾም አሁን ያለውን ገጽታ እንደያዘ ቀስ በቀስ በቤተ ክርስትያን እና በአማኞች ሕይወት ውስጥ ይበልጥ ሕያው እየሆነ መጥቷል።
ጾም ከመደበኛው የጊዜ ቀመር ዑደት በጸጋ ወደሆነው የጊዜ ዑደት የሚደረግ ጉዞ ነው። ጾም ከሕይወት አንድ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው የጸጋ ሕይወት ምዕራፍ የምንጓዝበት የእምነት፣ የተስፋ እና የፍቅር ልምምድ ወቅት ነው። የዚህ ጉዞ አይነተኛ ገጽታ በጽሞና፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በቅዱሳት ንባባት፣ በሥርዐተ አምልኮ ንቁ ተሳትፎ የተሞላ ሆኖ የሚገለጥ፤ ሕይወት ፊቷን ወደ እግዚአብሔር ፊት የምታስተካክልበት፣ የቀደመውን ፍቅሯን የምታድስበት፣ ከጸጋ ሙላት የምትካፈልበት፣ በንስሐዋ መንበርከክ የምትታደስበት፣ የምትጎበኝበት ዘመኗ፣ የተወደደችው የእግዚአብሔር ዓመት ናት።
ጾም፣ ጸሎት፣ ንስሐ እና ምጽዋት ከፍ ብለን የምንበርባቸው መንፈሳዊ ክንፎች ናቸው። በእነዚህ መንፈሳዊ ክንፎች ታግዘን፣ በአእምሮአችን መታደስ እየተለወጥን እና በላይ በሰማያት ያሉትን፣ ከፍ ያሉትን ሐሳቦች በልባችን ጠብቀን እያሰላሰልን ወደ እግዚአብሔር ልብ እንጠጋለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ክፍለ ሀገር ያደረገው ጥሪ በዚህ በዐቢይ ጾም ወቅት ለእያንዳንዳችን በተለየ መልኩ ይቀርብልናል። ይኸውም “ዘመኑ ተፈጸም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ” (ማር 1፡ 14-15) የሚለው የንስሐ እና ራስን በእግዚአብሔር ቃል ብርኀን የማስተዋል ጥሪ ነው። ይህ ጥሪ የዐቢይ ጾም መክፈቻ አዋጅ እና የጾም-ጸሎታችን መሰረታዊ ቁም ነገር ነው።
ዐቢይ ጾም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንጦስ ያደረገውን ጾም-ጸሎት በገዛ ሥጋችን የምንለማመድበት እና ጌታን በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው የምንመስልበት የመንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ አብነት ትምህርት ቤት ነው። ዐቢይ ጾም የጸጋ ወቅት እንደመሆኑ መጠን ነፍስ ለእግዚአብሔር ጸጋ የተዘጋጀች፣ በንስሐ የተሞሸረች፣ ለአዲስ የትንሳኤ ሕይወት ዐይኖቿ በእግዚአብሔር ቃል የተኳሉ፣ እግርቿ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የተተከሉ፣ ኅያው እና ዘላለማዊ የሚያደርጋትን በዔደን ገነት መካከል የተተከለውን የሕይወት ዛፍ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሥዋዕተ ቅዳሴ ገበታ ያለማቋረጥ የምትመገብበት፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት እስከ ዓለም ዳርቻ የምትሰብክበት፣ የሕማሙ፣ የሞቱ እና የትንሳኤው ምሥክር እና ሐዋርያ ሆና የምትሰራበት የጸጋ ሙላት ዘመን ሥጦታ ነው። በዚህም ለኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እና ምሥጢር ራሳችንን ዕለት ዕለት በእምነት መታዘዝ እያስገዛን፣ እርሱ በእኛ ውስጥ እኛም ደግሞ በእርሱ ውስጥ ኅያዋን እንሆን ዘንድ ይህንን ዐቢይ ጾም በሰላም። በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር እንጓዝ።
መልካም የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ
ሴሞ