ዐቢይ ጾም 2ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Monday, 24 February 2025 23:14
- Written by Samson
- Hits: 181
- 24 Feb
ዐቢይ ጾም 2ኛ ቀን
ቤተ ክርስትያን በዐቢይ ጾም ጉዞዋ የምትገለጥበት ሥርዐተ አምልኮ የጌታ ሕማም ማዕከላዊ ቁም ነገር ጎልቶ የሚታይበት ቢሆንም እጅግ ጥልቅ ከሆነ የትንሳኤ ተስፋ እና ደስታ የሚመነጭ ሥርዐተ አምልኮ ነው። የዐቢይ ጾም ጉዞ በጌታ ትንሳዔ ተስፋ የምንጓዘው የመስቀል መንገድ በመሆኑ ነፍስ በማይነገር ጥልቅ ምሥጢር ከጌታ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ጋር ኅብረት ታደርጋለች። ይህም የጌታ ትንሳዔ ምሥጢር ጌታ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በመስቀል ሥራው የኃጢአትን ጨለማ ያፈረሰበት የሕይወት ምሥጢር በመሆኑ በዚህ ምሥጢር ውስጥ የሚሳተፍ ሰው ሁሉ ዕለት ተዕለት ይበልጡን ኅያው እየሆነ ወደ ሰው‘ነቱ ምልዓት ያድጋል። ነፍስ ከጌታ ጋር በምትጓዘው በዚህ የመስቀል መንገድ በማይነገር የመንፈስ ቅዱስ መነካት ትጽናናለች፤ በዚህ ጉዞዋ ለኃጢአት በመጨከን ይበልጥ ዕለት ተዕለት ጌታዋን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ሕይወት ትለወጣለች።
ዐቢይ ጾም መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስትያን ነፍስ መካከል እንደ አዲስ የሚንቀሳቀስበት የቤተ ክርስትያን አዲስ ም ዕራፍ፣ የቤተክርስትያን አዲስ ልደት፣ የመኸር ወቅት፣ ዘመነ ጽጌ እና ዘመነ ፍሬ ነው። በዐቢይ ጾም ጸጋ ቤተ ክርስትያን በክርስቶስ ኢየሱስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ እድፍ እና ነቀፋ የሌለባት ሆና ትቀደሳለች። እግዚአብሔር በዚህ የጸጋ ወራት ቤተ ክርስትያንን እና ከእርሷም ጋር እያንዳንዳችንን “ብርሃንሽ መጥቷልና የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ አብሪ” (ኢሳ 60፡1) እያለ ጥሪውን ያቀርባል። በመሆኑም ዐቢይ ጾም የኀዘን፣ የመከልከል፣ የማድረግ እና ያለማድረግ ወቅት ሳይሆን ይልቁንም የእግዚአብሔር ጉብኝት ዘመን፣ የጸጋ ወራት፣ የተወደደችው የእግዚአብሔር ዓመት፣ የፈውስ እና የብርሃን ዘመን ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 2ኛ ቆሮ 5፡ 17-6፡2
“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል! 18ይህ ሁሉ የሆነው፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን፥ የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤ 19ይህ እግዚአብሔር የሰዎችን በደል ሳይቆጥርባቸው በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኑሯል። 20ስለዚህ እግዚአብሔር ጥሪውን የሚያቀርበው በእኛ በኩል በመሆኑ፥ እኛ ለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ስለ ክርስቶስ ሆነን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን። 21እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን ስለ እኛ ኃጢአት የሌለበትን እርሱን ኃጢአት አደረገው። 1እንግዲህ፥ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ እንደ መሆናችን፥ የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ እንለምናለን፤ 2እርሱ፥ “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፤ በመዳንም ቀን ረዳሁህ፤” ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳንም ቀን አሁን ነው። ”
ጸሎት
በትንሳኤህ እምነት፣ ሞትን ሁሉ በሚሻገረው የሕይወትህ ኃይል ሐሳቤን፣ ልቤን እና ጸሎቴን ሁሉ በፊትህ አቀርባለሁ። እውነተኛ የአንተ ደቀ መዝሙር የሚያደርገኝን የአንተን ቅዱስ መንፈስ ላክልኝ። በዚህ የጸጋ እና የተስፋ ወራት በሕማምህ ምሥጢር ውስጥ አንተን ስከተል ከሁሉ በላይ ስለ ሕይወት ሥጦታህ አመሰግንሃለሁ። ያንተን ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ በማሰላስልበት በዚህ የተቀደሰ ወቅት የራሴን መስቀል፣ ሕማም እና የትንሳኤ ተስፋ በእምነት እየተመለከትኩኝ በደምህ የቀደስከውን መንግሥት በሕይወቴ በምልዓት ለመመስከር ኃይል የሚሰጠኝን ቅዱስ መንፈስህን እለምናለሁ። ኢየሱስ ሆይ፣ የእኔ ክርስቶስ፣ የእኔ አዳኝ አምላኬ እና መድኃኒቴ ሆይ ሕይወቴን እና ሞቴን ሁሉ በእጆችህ እንደ ምሥጋና መሥዋዕት አሳልፈ እሰጥሃለሁ። አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በዐብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- የዐቢይ ጾም የጸሎት ርዕሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት የምንበረከክበት ሐሳብ ምንድን ነው?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
መልካም የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ
ሴሞ