ዐቢይ ጾም 3ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Wednesday, 26 February 2025 00:39
- Written by Samson
- Hits: 240
- 26 Feb
ዐቢይ ጾም 3ኛ ቀን
ጾም ነፍስ በቅዱስ ዕንባ መታጠብ የአዲስ ልደት ጥምቀት የምታገኝበት የጸጋ ወቅት ነው። ዕንባ የተነሳሂው ስነ ልቦናዊ አቋም ነጸብራቅ እና ለእግዚአብሔር ያለው ቀናዒ ፍቅር ምስክር ከመሆኑም ባሻገር ነፍሱን የሚያነጻት፣ የጸጋን ዘር ተቀብላ ፍሬ ታፈራ ዘንድ የሚያረሰርሳት የንስሐዋ ጠል ነው። እንዲህ ያለው ዕንባ የራስህን ሕይወት በእግዚአብሔር ፍቅር እና ምህረት መነጽር ከመመልከት ጥልቅ ትህትና ውስጥ የሚፈልቅ ደስታን የሚወልድ ቅዱስ ኀዘን ነው።
የክርስትና ውበት በአንድ በኩል የምንደገፍበት ማረፊያ፣ የመሸሸጊያ ጽኑ ግንብ የሆነ አምላክ እንዳለን ማወቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንኑ አምላክ በማሰብ በመናገር፣ በማድረግ፣ ተግባርን በሚገባ ባለመፈጸም ማሳዘናችንን አውቀን ከእርሱ ጋር ለዘላለም ባስታረቀን በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እና ሥልጣን፤ የመጠበቂያ ከተማ አድርጎ በሰጠን ቤተ ክርስትያን የማስታርቅ አገልግሎት በኩል ሠርክ አዲስ ወደ እግዚአብሔር ልብ መመለስ መቻላችን ነው። ወደ እግዚአብሔር ልብ በቀረብንበት ትህትና ልክ፣ በእግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ በወደቅንበት መተማመን ልክ፣ ወደ ራሳችን ልብ እና ወደ ተፈጠርንበት ዓላማ ማዕከላዊ ቁምነገር እንመለሳለን።
“አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ፥ ልቡም ተመልሶ፥ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙት” (ሉቃ 8፡35)።
በዚህም እውነትን በእውነትነቱ ክብር እና ዋጋ ልክ በመቀበል ብዥታን እውነታ ያደረግንበት፤ ብሎም ብዥታው እውነታ መስሎ ይታይ ዘንድ ራሳችንን የምናታልልበት ሞኝነት እና ኃጢአት በእግዚአብሔር ቃል እና ብርኀን እየተገረዘ ይጠራል።
ይህ የንስሐ፣ የቅዱስ ጸጸት፣ የቅዱስ ዕንባ እና የቁርጥ ፈቃድ ተጋድሎ ምንም እንኳን ቀላል ባይሆንም መዳረሻው ግን እውነት ነው። እውነት ውስብስብ ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን ሥጋ ለብሶ የተገለጠ፤ በዘላለማዊ፣ ፍጹም ሊደረስበት እና የጽሞናው ጥልቀት ሊመረመር በማይቻለው አርምሞ ወስጥ የሚኖረው እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ላይ፣ ስለ ሁሉም ነገር፣ ለፍጥረት ሁሉ በሚሰማ፣ ሙታንን ከጥልቅ እንቅልፍ ሰመመን በሚቀሰቅስ መለኮታዊ ድምጽ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተናገረው “ኢየሱስ” የሚለው ዘላለማዊ ቃል ነው።
ይህም ዘላለማዊ ቃል ከአብ ፍጹም ሐሳብ የሚመነጭ፣ ከዘላለም ጀምሮ ከአብ ጋር የነበረ፣ የአብ ሐሳብ ሁሉ ተገልጦ የሚታይበት፣ ፍጥረትም ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር የተጠራበት፣ ከጨለማ ወደሚያስደንቅ ብርኀን አርነት የወጣንበት፣ ፍጥረት ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የተዋወቀበት የእርቅ መልክ፣ ፍጥረት ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የተግባባበት የሰው እና የእግዚአብሔር ሰዋሰው፣ የመቃተታችንን ምጥ ሁሉ በቃልነቱ ኃይል ለአባቱ የሚተረጉም፣ የአባቱንም ሐሳብ እና ዘላለማዊ ዓላማ ለነፍሳችን ማንነት በወንጌል ምክር የገለጠልን ኢየሱስ ነው።
ጾም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከዚህ ከኢየሱስ ጋር እርሱ ብቻ ወደሚገልጠው አባቱ ልብ፤ ወደመጣንበት ዘላለማዊ የዕረፍት ሥፍራችን እና ወደ እውነተኛው የዔደን ገነት የምናደርገው ጉዞ ነው። እሾህ እና አሜኬላ በምታበቅለው ምድር መካከል በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ በታደሰ አእምሮ፣ በአዲስ ፍጥረት ማንነት የምንመላለስበት እና በሁሉ ነገር የእግዚአብሔርን ክብር የምንመለከትበት የተቀደሰ መረዳት እና የጽድቅ ፍርድ ውኃ ልክ ነው።
የተነሳሂ ክርስትያን ዕንባ እውነትን እና ትህትናን ከሚያስተውል ልብ የሚመነጭ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ የጌተሰማኔ ዕንባ ጋር ሕብረት የሚያደርግ ወደ እውነት እና ወደ ጽድቅ የሚያደርስ ዕንባ ነው። ይህ ከክርስቶስ ጋር ሕብረት ያለው ዕንባ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነው፤ በመሆኑም በዚህ በጾመ-ኢየሱስ ጉዞ መንፈስ ቅዱስ ይህንን ኃጢአትን የሚጠይፍ እና ለጽድቅ የሚያስጨክን ቅዱስ ዕንባ እንዲሰጠን በልባችን መቃተት እንለምነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ዘዳ 30፡15-20
“እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ። ጌታ አምላክህን በመውደድ፥ በመንገዱም በመሄድና ትእዛዙን፥ ሥርዓቱንና ሕጉን በመጠበቅ ያዘዝሁን ካደርግክ፤ በሕይወት ትኖራለህ፤ ትበዛለህም፤ ጌታ አምላክም ትወርሳት ዘንድ በምትገባበት ምድር ይባርክሃል። 1ልብህ ግን ርቆ አንተም ባትሰማ፥ ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድላቸውና ብታመልካቸው ግን፥ ፈጽመህ እንደምትጠፋ እኔ ዛሬ እነግርሃለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ እንድትወርሳትም በምትገባባት ምድር ረጅም ዘመን አትኖርም። ሕይወትንና ሞትን፥ በረከትንና መርገምን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ። ጌታ አምላክህን ውደደው፤ ለቃሉም ታዘዝ፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቅ”።
ጸሎት
አምላኬ እና ጌታዬ ሆይ ለአንተ እንድኖር ፈጥረኸኛልና ልቤ አንተን እስከሚያገኝ ድረስ ዕረፍት የለውም። በዚህ የሕይወቴ ጉዞ በእውር ድንብር ሳይሆን በማስተዋል እንድመላለስ ምክኒያታዊ በሆነች ነፍስ በውጤ ኅያው ሆነህ ትመራኛለህ። ዐይኖቼ በዙርያቸው ካለው ቅጽበታዊ እይታ ባሻገር ዘላቂ የሆነውን ለሕይወቴ ያለህን ዓላማ ውበት እንዲመለከቱ በየዕለቱ በቃልህ እና በምሥጢራትህ ለመለኮታዊ እውነት ክፈታቸው። ዐይኖቼ እውነተኛ ሰብዓዊ ማንነቴን እና መንፈሳዊ ፍጻሜዬን በጤናማ ዕይታ እንዲመለከቱ እና እንዲቀበሉ፣ ብዥታን ከእውነታ መለየት እንዲችሉ በቃልህ ኃይል ኳላቸው። በልጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ዕለት ዕለት ሳልሰስት እንዳፈቅርህ ልቤን ከውስንነቱ ባሻገር በምትወድበት ልክ ክፈተው። በዚህ የጾም-ጸሎት ጉዞዬ ሕይወቴን፣ ጥሪዬን፣ ተልዕኮዬን እና የተፈጠርኩበትን ዓላማ ሁሉ ዕለት በዕለት የበለጠ ግለጽልኝ። አቤቱ ጉልበቴ ሆይ እወድሃለሁ! አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- በሕይወቴ ብዥታ የሆኑብኝ ነገር ግን እውነታ አድርጌ የተቀበልኳቸው ቁም ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
- በዚህ በጾመ-ኢየሱስ ጉዞ ከጌታ ጋር በአዲስ መልክ ልከልሳቸው የሚጉቡ የሕይወቴ ክፍሎች፣ ልምምዶች እና ግንኙነቶች የትኞቹ ናቸው?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ
ሴሞ