እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም 4ኛ ቀን

ዐቢይ ጾም 4ቀን

Lent-main-imageበእግዚአብሔር ምሕረት መታመን

ጾም የእግዚአብሔርን ምሕረት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የበለጠ የምንለማመድበት የምሕረት ትምህርት ቤት ነው። ምሕረት ማለት አዲስ ፍጥረት መሆን ማለት ነው። የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ምሕረት  רחם ራሐም እያለ ይጠራዋል። ለምሳሌ በዘዳ 4:31 “ጌታ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተዋችሁም፥ አያጠፋችሁምም፤ ለአባቶቻችሁ የገባውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም” እያለ የእግዚአብሔርን ምሕረት ሁለንተናዊ ማዕቀፍ ያስታውሰናል። ይህ የእግዚአብሔር ምሕረት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሚያደርገው ይቅርታ እና ከዕዳ ነጻ የማውጣቱ በጎ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባሻገር ጠለቅ ብሎ የሚሄድ ቁም ነገር በውስጡ ይዟል። ምሕረትን  רחם ራሐም የሚለው የዕብራይስጡ ቃል በተመሳሳይ መልኩ “የእናት ማሕጸን” የሚል ትርጉም ያሰማል። ለምሳሌ የሊያ እና የራሔል ማሕጸን እንደተከፈተ እና ፍሬ እንዳገኙ የሚገልጸው ክፍል ተመሳሳይ רחם ራሐም የሚለውን ቃል ይጠቀማል (ዘፍ 29:31 እና 30:22)። ዳዊትም በመዝሙሩ ይህንኑ רחם ራሐም የሚለውን ቃል በመጠቀም “ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፥ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ” (መዝ 22፡11) እያለ ይዘምራል።

እግዚአብሔርም የእሥራኤልን ሕዝብ የተንከባከበበትን ጥንቃቄ ሲናገር በዚሁ አይነት አገባብ እንዲህ ይላል “ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁን፥ ስሙኝ። እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻችኋለሁ እኔም አነሣችኋለሁ፤ እኔ እሸከማችኋለሁ እኔም አድናችኋለሁ” (ኢሳ 46፡3-5)። በመሆኑም የእግዚአብሔር ምሕረት ከይቅርታ ባሻገር በፍጹም ደህንነት የምንጠበቅበትን መለኮታዊ ክብካቤ ያመለክታል። በእግዚአብሔር ምሕረት ከሁሉ ነገር በፍጹም መለኮታዊ ጥንቃቄ በምንጠበቅበት የእግዚአብሔ ፍጹም ደህንነት ውስጥ እንገባለን። በመሠረቱ እያንዳንዱ ንስሐ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በጌታችን በኢየሱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ልጅነት በኩል እንደ አዲስ የምንወለድበት ምሥጢር ነው።

ምሕረት ደህንነት ነው፤ ምሕረት በእግዚአብሔር ፊት ሕያው ሆኖ መኖር ነው፤ ምሕረት በንስሐ ትህትና እግዚአብሔር እንዲጠነቀቅልን ራሳችንን ለእግዚአብሔር መለኮታዊ ክብካቤ አሳልፈን የምንሰጥበት ኃይል ነው። እናት በማሕጸን ለተሸከመችው ለልጇ ሁሉን እንደምትሆን እና በሁሉ ነገር ራሷን አሳልፋ እንደምሰጥ እንዲሁ እግዚአብሔር በምሕረቱ ሥጦታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሁሉን ነገር ብቻ ሳይሆን ከሁሉ ነገር በላይ የሆነውን ራሱን ጭምር ሰጥቶናል። ጾም ይህንን የእግዚአብሔርን ሥጦታ እና ክብካቤ የምንለማመድበት የጸጋ ትምህርት ቤት ነው።

መለኮታዊ ምሕረት አዲስ ፍጥረት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት የሚወልደን በኃጢአት ላይ ድል የነሳው እና የሞትን መውጊያ የሰበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ መልክ የእኛ ገንዘብ የሚሆንበት ሁለንተናዊ ተሃድሶ ነው። ምሕረት የኃጢአት ሥርየት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የአዲስ ሕይወት ሥጦታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ምሕረት ሁለንተናዊ አዲስ ልደት እና መለኮታዊ ክብካቤ ለመግለጽ ከእናት ማሕጸን ጋር ያመሳስለዋል። ወላጅ ልጁን እንደሚንከባከብ፣ እንደሚያሳድግ፣ እንደሚገስጽ እና በሕይወት ጎዳና እንደሚመራ እንዲሁ እግዚአብሔርም ፍጥረትን በዘላለማዊ ቃሉ ወልዶ ይመግባል፣ ይንከባከባል፣ ይገስጻል፣ ይፈውሳል፣ ይመራል፣ ለመልካም ነገርም ያስጨክናል። ጾም ከኃጢአት ጨለማ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደተገለጠው መለኮታዊ የጽድቅ ብርኀን የምንወጣበት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ ጸጋ የኃጢአትን  ሰንሰለት በጥሰን ለጽድቅ ሕይወት የምንጨክንበት፣ ውሻ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ወደ ኋላ የማንመለስበት እና ለጽድቅ ሕይወት የምንጨክንበት የሕይወት ጉዞ ነው።

ሙሴ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ክብካቤ በመታመን ሕዝቡን ይዞ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደተነሳ፣ እሥራኤልም በጉዞው የእግዚአብሔር እንክብካቤ እና ጥበቃ እንዳልተለየው፣ ነብያትም የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ምሕረት በትውልድ መካከል እንደመሰከሩ፣ ዳዊትም በመዝሙሩ ያጽናናውን የእግዚአብሔርን ጥበቃ እና ምሕረት እንደወደሰ እንዲሁ በዘመን መጨረሻ ይህ የእግዚአብብሔር ምሕረት ሥጋ ለብሶ በኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ በመካከላችን ታየ። ጾም ይህንን የእግዚአብሔርን ምሕረት ኢየሱስ ክርስቶስን በነገር ሁሉ መምሰል እና በእርሱ የእምነት እና የክርስትና ትምሕርት ቤት ገብተን መስቀላችንን ተሸክመን በሚሄድበት መንገድ እና በሚገለጥበት የሕይወት መልክ ሁሉ እርሱን እስከ መጨረሻው መከተል ነው። በዚህ ጉዞ ከእያንዳንዳችን አንድ መሠረታዊ ቁም ነገር ይጠበቃል ይኸውም “የሰማይ አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ” (ሉቃ 6፡36) የሚለው የጌታ ምክር ነው። በመሆኑም ጾም ምሕረት የተደረገለት ሰው እርሱም ደግሞ ምሕረት ማድረግን ገንዘቡ የሚያደርግበት እና የምሕረት አምባሳደርነቱን በተግባር የሚለማመድበት የጸጋ ወቅት ነው።

ምሕረት ያለበት ጾም ኢሳ 58፡4-6

“ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም?” ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ለማሰማት ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነው? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነው? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ እንዲያደርግ፥ ማቅንና አመድንም በበታቹ እንዲያነጥፍ ነው? በውኑ ይህን ጾም፥ በጌታ ዘንድ የተወደደ ቀን ብለህ ትጠራዋለህ? እኔስ የመረጥሁት ጾም፥ የበደልን እስራት እንድትፈቱ፥ የቀንበርንስ ጠፍር እንድትለቁ፥ የተገፉትን አርነት እንድታወጡ፥ ቀንበሩን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? 

ጸሎት

ጌታ ሆይ የልቦናዬ ጆሮዎች ትእዛዝህን ለማድመጥ ተከፍተዋል። መንገድህን አስተምረኝ። ለወንድሞቼ እና ለእህቶቼ የምሕረትህ ምልክት በመሆን የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንድሆን ምሕረት ማድረግን አስተምረኝ። አንተ የእኔን ደካማ ጎን ሁሉ እንደምትቀበለኝ እና ድካሜን ሁሉ በጸጋህ እንደምታድስ እንዲሁ እኔም የእነርሱን ደካማ ጎን በምሕረትህ ትህትና እንድቀበል ጸጋህን ስጠኝ። ሁላችን የአንተ ጸጋ እና ምሕረት የሚያስፈልገን ደካማ ፍጥረታት መሆናችንን እረዳ ዘንድ ልቤን እና አእምሮዬን ክፈትልኝ። ወደ አንተ የምንደርስበት እውነተኛው መንገድ ምሕረት መሆኑን እንዳልዘነጋ በልቤ የምሕረትህን ልግሥና አትምልኝ። አቤቱ እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በልልን አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. የእግዚአብሔርን ምሕረት ሳስብ ወደ አእምሮዬ የሚመጠው ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝ ታሪክ የትኛው ነው?
  2. በሕይወቴ ይቅርታ ያላደረኩላቸውን ሰዎች ከመሸከም እሥራት ነጻ እንድወጣ በዚህ ጾም ጌታን ምን እጠይቀዋለሁ?
  3. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት