እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም 5ኛ ቀን

ዐቢይ ጾም 5ቀን

Lent-main-imageበጌታ ነህ?

ትጾማለህ? ተብለን ስንጠየቅ “አዎን” ወይም “አይ አልጾምም” ከማለት ባሻገር ምናልባት በልባችን እና በአእምሮአችን የኋለኛው ክፍል ለአንድ ክርስትያን የምግብ ጾም ምን ፋይዳ አለው? የምግብ ጾም በማድረግ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚነሱ እሙን ነው። ጾም ሥጋን ሸንቃጣ አድርጎ ለፋሲካ ማዘጋጀት አይደለም። ነገር ግን ስንጾም ልናስተውል የሚገቡን፣ በምግብ ጾም በኩል ሥጋን ከመግራት ቁም ነገር የሚነሱ ነፍስ የምትራባቸው እና ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ራሷን በከፈተችበት መጠን የምትለማመዳቸው መልዕልተ ባሕርያዊ ቁም ነገሮች መኖራቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ጾም ከክርስቶስ ሕማም እና ሞት ጋር በምናደርገው ተግባራዊ ሱታፌ ሥጋችን እና ነፍሳችን ለትንሳኤው ክብር የሚጠበቁበት ክርስትያናዊ የኑሮ ዘይቤ ነው።

መመገብ የምችለውን ነገር ስለ ክርስቶስ ስም የመራቤ እና በፈቃዴ የእኔ የሆነውን ነገር አሳልፌ የመስጠቴ እውነታ ከክርስቶስ ራስን ባዶ የማድረግ ምሥጢር (κένωσις) ጋር የበለጠ ያስተሳስረኛል። እርሱ ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዮስ ክርስትያኖች እንደሚያተምረው “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኑር። እርሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ኖሮት ሳለ እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩልነትን እንደመንጠቅ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን እንደ ሰው ሆኖ በመወለድ የባርያን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በሰው አምሳል ተገኝቶ፥ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በዚህም የመስቀልን ሞት እንኳ በመቀበል እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ” (ፊል 2፡6-8)። በመሠረቱ እርሱ የተወውን እና ለእርሱ የነበረውን ክብር ስናስብ የጾም ግዜ ምግቦችን መተዋችን እና የምግብ ጾም ላይ መከራከራችን ሊያሳፍረን ይገባል። ኢየሱስ ራሱ አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ከምግብ መከልከሉ የጾም መርሐ ግብራችን አይነተኛ ምሳሌ ነው። እርሱ ያደረገው ነገር ሁሉ ለእኛ እርሱን ለምንከተል የሕይወት ፕሮግራማችን ነው፤ በመሆኑም የዐቢይ ጾም ጉዞ የቤተ ክርስትያን ሥርዐት፣ ሕግ፣ ትዕዛዝ ሳይሆን ከሁሉ አስቀድሞ ዐቢይ ጾም ክርስቶስን መከተል ነው። ዐቢይ ጾም ከዴታ ጋር በጌታ መሆን ነው!

በመሆኑም ትጾማለህ? ለሚለው ጥያቄ ተገቢ የሆነው ክርስትያናዊ ምላሽ “እንደ ዕድል!” የሚል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚኖረውን ሕይወት ሲናገር የክርስትናን ምሥጢር በሚደንቅ መልኩ ያሳየናል። ጳውሎስ የራሱን ማንነት ሲናገር “'ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ነው” (ገላ 2፡20) በማለት አሁን ክርስቶስ ኢየሱስ በመላ ማንነቱ በእርሱ ውስጥ እንደሚኖር ይናገራል። ይህ በመሠረቱ ለቅዱስ ጳውሎስ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን በምሥጢረ ጥምቀት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው ለመተባበር በእግዚአብሔር አብ ጥሪ እና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን የተወለደ የእያንዳንዱ ክርስትያን ሕይወት ነው። በመሆኑም ጾም ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ሲኖር በራሱ መልክ ይቀርጸን ዘንድ ነፍሳችንን እና ሥጋችንን ለትንሳኤ ክብር የሚገራበት እና የሚያሰለጥንበት መለኮታዊ ምክር ነው።

የሚጾም ክርስትያን ከጌታ ጋር በመንፈስ ቅዱስ ምሪት በገዳመ ቆሮንጦስ ጊዜ ለማሳለፍ፣ ከኢየሱስ ከራሱ ለመማር፣ እርሱን እየተመለከተ የበለጠ እርሱን በመምሰል ለማደግ የሚወድ ነው። በገዳመ ቆሮንጦስ ከጌታ ጋር በጾም በጸሎት ማሳለፍ ልብን እና አእምሮን ለእግዚአብሔር ድምጽ ክፍት ያደርጋል። መንፈስን መለየት እና በፈተና ውስጥ ጥበብን መማር ያስችላል። ከጌታ ጋር በገዳመ ቆሮንጦስ ጊዜ ማሳለፍ በጌታ ነህ? የሚለው ጥያቄ ሌላኛው ገጽታ ነው? በጌታ ነህ? ትጾማለህ? ይህንን ዐቢይ ጾም በገዳመ ቆሮንጦስ አርባ ቀናት በጌታ ለመሆን ትጨክናለህ? ወይስ ከበረሃ የተመለሰውን እና በትንሳኤ ያለውን ጌታ ብቻ ነው የምትከተለው? ዐቢይ ጾም ከጌታ ጋር፣ በጌታ፣ እንደ ጌታ መሆን ነው። ኢየሱስን መከተል ማለት መላ ማንነቱን መቀበል እና በመላ እርሱነቱ ወደሚሄድበት ሁሉ፣ በሚገለጥበትም ሁኔታ እና ስፍራ ሁሉ በሁሉ ነገር እርሱን መምሰል ማለት ነው። ኢየሱስ ያለፈበት እና የተገለጠበት መልክ ሁሉ እውነተኛ ክርስትያናዊ መልካችን እና ክብራችን ነው፣ ዐቢይ ጾም ከጌታ ሕማም ከፍለን የምንካፈልበት የጸጋ ሥጦታ በመሆኑ እግዚአብሔር በልጁ ሕማም እንሳተፍ ዘንድ እንዴት ባለ ጥሪ እንዳከበረን ተመልከት። ስለዚህ በጌታ ነህ? ይህንን ዐቢይ ጾም ከጌታ ጋር ነህ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ሉቃ 5፡34

“ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ቀኖች ይመጣሉ፤ በነዚያ ቀኖች ይጾማሉ”

ጸሎት

ጌታ ሆይ በሁሉ ነገር አንተን እመስል ዘንድ፣ በመንገድህ ሁሉ እከተልህ ዘንድ ስለጠራኸኝ እና ስላከበርከኝ አመሰግንሃለሁ። ይህ አንተን በሁሉ ነገር እንዳልመስልህ በሥጋዬ ምቾት የሚደልለኝን ልፍስፍስ ክርስትና በእምነት ክንድ የምረታበትን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ሙላኝ። በእነዚህ የዐቢይ ጾም ወራት የአባትህን ጥበብ እና የመንፈስ ቅዱስን ምክር አስተምረኝ። በገዳመ ቆሮንጦስ በሕወቴ ምድረ ባዳ ካንተ ጋር መሆኔን እንዳውቅ ከብቸኝነቴ ባዶነት ባሻገር የኅልውናህ ማጽናናት ነፍሰን ይሙላት። ጌታዬ እና መምህሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በጾም ርሃብ ውስጥ ከምሥጢርህ ምልዓት የሚፈልቀው መለኮታዊ ዘይት ቁስሎቼን ሁሉ ይፈውስ፣ ያንተ መልክ የማይስተዋልበትን የሕይወቴን መልክ አስቀድሞ በተፈጠርኩበት በእውነተኛ የአንተ ገጽታ አድስ። ነፍሴ ከመለኮታዊ ምክርህ ትጥገብ። ሰውነቴ አንተን በማግኘት ሥጦታ ቤተ መቅደስህ ሆኖ ይክበር፤ አንተ እንጂ ሌላ ነገር ገዢሆኖ እንዳይበዘብዘው በጾም የምገራውን ይህንን ሥጋዬን ፈውስ። አንተ ራስህ የወሰድከው እና የራስህ ያደረከውን ሥጋ ባከበርከው ክብር ልክ ለትንሳኤ ምሥክር አድርጌ እጠብቀው ዘንድ ኃይልህን ሙላኝ። ፈተናን ሁሉ በእምነት እቋቋም ዘንድ፣ በቃልህ የጠላትን ምክር ሁሉ አፈርስ ዘንድ፣ በጾምህ እና በጸሎትህ ትህትናን እና መታዘዝን ገንዘቤ አደርግ ዘንድ አንተ ራስህ ምራኝ! አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. ስለዚህ በጌታ ነህ? ይህንን ዐቢይ ጾም ከጌታ ጋር ነህ?
  2. ከኢየሱስ ጋር በሕይወትህ ምድረ በዳ ውስጥ ሱባኤ ለመያዝ፣ ከእርሱ ጋር የሕይወትህን ምዕራፎች ከጌታ ጋር ለለልከት፣ ለመምከር እና ለመግራት ጊዜ አለህ?
  3. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት