ዐቢይ ጾም 6ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Saturday, 01 March 2025 08:32
- Written by Samson
- Hits: 116
- 01 Mar
ዐቢይ ጾም 6ኛ ቀን
የአባት ፍቅር
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ወደ አብ ልብ የሚያሳየን መለኮታዊ መስታወት ነው። እግዚአብሔር አብ ለእያንዳንድችን ያለውን ወሰን አልባ ፍቅር ለመግለጥ በልቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ልቡን ሁሉ አፍስሶልናል። በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ በእግዚአብሔር አብ ልብ ውስጥ ለእያንዳንዳችን ያለው ፍቅር አሁን ፍንትው ብሎ ይታያል። እግዚአብሔር አብ ወደ ልቡ ያስጠጋን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጦታ በኩል ነው፤ በዚህም ጌታ በመስቀሉ ላይ ሳለ ጎኑ በጦር በመወጋቱ የተከፈተው ልብ ወደ እግዚአብሔር ፍቅር እና ወደ ቅድስት ሥላሴ ምሥጢር የምንመለከትበት የፍቅር መስኮት ሆኗል። በኢየሱስ ልብ መከፈት በኩል በትንሳኤው ኃይል በመንፈስ ቅዱስ በተኳሉ የእምነት ዐይኖች ወደ አብ ልብ መመልከት እና ለእያንዳንዳችን ያለውን ፍቅር ማንበብ እንችላለን።
በመሥዋዕተ ቅዳሴያችን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አኮቴተ ቊርባን ስለ ፍቅር ኃያልነት ሲናገር “ፍቅር ኃያሉን ወልድ ከሰማያት ስቦ እስከ ሞት አደረሰው” እያለ ከመሰከረ በኋላ “ይህን ያህል ሰው ማፍቀር እንዴት ያለ ፍቅር ነው” በማለት ይደነቃል። ፍቅር በባሕርዩ እኩል እና ትይዩ ሆኖ ከመቆም ይልቅ ዝቅ ማለትን፣ የወደደውን ነገር ከፍ ማድረግን፣ መሸላለምን፣ ማሳመርን ይወዳልና እግዚአብሔር አብ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆን ምሥጢር ውስጥ ከእኛ ጋር ዘመድ ለመሆን ያለውን መሻት በሚያስደንቅ መንገድ ገለጸልን። ፍቅሩ በማይገ’ባን መልክ አክብሮ ተቀበለን፤ አስቀድመን የተፈጠርንበትን የልጁን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መልክ ለእያንዳንዳችን እንደ አዲስ ሰጠን፤ በብዙ ክብር እና በብዙ እውነት በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር አምላክ እያንዳንዳችንን ያለ ቅድመ ሁኔታ ተቀበለን።
እምነት እኛ እግዚአብሔርን የምንቀበልበት ቅድመ ሁኔታ እንጂ እግዚአብሔር እኛን የሚቀበልበት መርሐ ግብር አይደለም። እምነት አስቀድሞ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተቀበለን እግዚአብሔር የእያንዳንዳችንን ልብ የሚያንኳኳበት ምሥጢር ነው፤ በመሆኑም እምነት አስቀድሞ የተቀበለንን እግዚአብሔርን የምንቀበልበት፣ የእርቃችን ሽማግሌ አድርጎ የላከውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን አክብረን ከአብ ጋር የምንታረቅበት የዕርቅ ምሥጢር ምላሻችን ዋስትና ነው።
በክርስቶስ ኢየሱስ ሰው የመሆን ምሥጢር በኩል እግዚአብሔር ዘመዳችን ሆኗል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የአባት ፍቅር ተገለጦ ታይቷል። በመሆኑም የእርሱ ፍላጎት እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ኃጢአታችንን ይቅር የማለት እና በደልን የማስወገድ ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም እኛን ማፍቀር፣ ከእኛ ጋር በልጁ ስም አዲስ ኪዳን ማድረግ፣ ዘመዳችን፣ ወገናችን መሆን ነው። በመሆኑም ማንም ዘመድ የለኝም፣ ማንም ሰው “ሰው” የለኝም እንዳይል ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው” የሆነልን ሰው ሆኗል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን በመካፈሉ ምሥጢር ዘመዳችን ሆኖ በእርሱ ልጅነት በኩል ከአባቱ ጋር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አዛምዶናል። በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እና እርሱ በመስቀል ላይ ባደረገው ቤዛነት በኩል ከእግዚአብሔር ጋር የደም ዝምድና አለን!
እግዚአብሔር ዘመዱ፣ እግዚአብሔር ወዳጁ፣ እግዚአብሔር ወገኑ ያልሆነለት ሰው የለም። በዚህ የዐቢይ ጾም ወቅት በዚህ ዝምድና እንድናድግ፣ ይበልጥ ሰው የሆነውን ክርስቶስን በመምሰል ሰው ወደመሆን ምልዓት እንድናድግ፣ ሰው በመሆናችን ምሥጢር ውስጥ ልጁ የተካፈለውን ሰውነታችንን ዕለት ዕለት እየቀደስን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የተቀደሰ መሥዋዕት አድርገን ማቅረብ እንድንለማመድ ተጠርተናል። አትግደል የሚለው የእግዚአብብሔር ሕግ እኛ በራሳችን ላይ የምናደርገውን ግዴለሽነት፣ ዕረፍት ማጣት፣ ራስን መበደል ሁሉ የሚመለከት በመሆኑ በዚህ በዐቢይ ጾም በመመለስ እና በማረፍ በሕይወታችን እያንዳንዱ ምዕራፍ የእግዚአብሔርን ፍቅር ማስተዋል እንድንችል ተጠርተናል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከጌታ ጋር መጾም ሉቃ 4፡1-4
“ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በምድረ በዳም በመንፈስ ተመራ። ለአርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ። በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ ቀኖቹም በተፈጸሙ ጊዜ ተራበ። 3ዲያብሎስም፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ፤” አለው። 4ኢየሱስም፦ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤ ብሎ መለሰለት”
ጸሎት
የተሰበሰብን እኛም፤ እሱ የማይሠቃይ ሲሆን የሱን ሥቃይ እንናገራለን፡፡ እሱ የማይሞት ሲሆን የሱን መሞት እንናገራለን፡፡ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ በተቀመጠበት በዚያች ሌሊት በአባቱ ፈቃድ፤ በራሱም ፈቃድ ሕይወቱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ እሱ ሁሉን የሚይዝ፤ ሁሉን የሚያሸንፍ ሲሆን ሰዎች አሰሩት፤ የሕያው አምላክን ልጅ አሰሩት፤ እነሱ በቁጣ ጎተቱት፤ እሱ ግን በፍቅር ተከተላቸው፤ ጠጉሩን በሚቆርጠው ሰው ፊት እንደማይናገር እንደ የዋህ በግ በኋላቸው እየተከተላቸው ወሰዱት፡፡ ይህን ያህል ትሕትና፤ እንዴት ያለ ትሕትና ነው? ይህን ያህል ትዕግሥት፤ እንዴት ያለ ትዕግሥት ነው? ይህን ያህል ዝምታ፤ እንዴት ያለ ዝምታ ነው? ይህን ያህል ደግነት፤ እንዴት ያለ ደግነት ነው? ይህን ያህል ሰውን ማፍቀር፤ እንዴት ያለ ፍቅር ነው? ፍቅር ኃያሉን ወልድ ከዙፋኑ ስቦ እስከ ሞት አደረሰው! ሞትን ለመሻር ሲል፤ የማይሞተው ሞተ የሞቱትን ለማዳን ሲል፤ እሱም ሞተ፡፡ ጌታ ሆይ ዓለም ሊቀበለው የማይችለውን መንፈስ ቅዱስህን በእኛ ላይ የምትልክልን መሆንህን ከአባቶቻችን ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር የተማማልኸውን ቃል ኪዳንህን አስታውስ፤ የማይመረመርና ጉድለት የሌለበት፤ ይህ መንፈስ ቅዱስ ከላይ ከሰማየ ሰማያት ይምጣ። አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- እግዚአብሔር እንዲያፈቅረኝ እና በፍቅሩ ወደሚወደው ሥፍራ እንዲመራኝ እፈቅድለታለሁ?
- በሕይወቴ ሰው የለኝም በምልባቸው ቁም ነግሮች የኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኔ "ሰው" መሆኑ ምን ይነግረኛል?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የጾም ጉዞ
ሴሞ