Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም 8ኛ ቀን

ዐቢይ ጾም 8ቀን

Lent-main-imageየንስሐ ልብ

ዛሬ ስለ ኃጢአት እና ስለ መመለስ የሚያወራ ሰው ለዘመናዊው ዓለም ጆሮ ንግግሩ “ልዩ ወንጌል” ነው። የእግዚአብሔር ማንነት እንደ ግሌ ስሜት እና መረዳት በሚተረጎምበት፣ እግዚአብሔርን በእኔ ልክ በሰፋሁበት በዚህ ዘመን ንስሐ፣ ተጋድሎ፣ ጾም-ጸሎት የሚሉት ሐሳቦች የሚደመጡ አይደሉም። በተመሳሳይ መልኩ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር፣ አዲስ ነገር በተገኘ ቁጥር “ከዚህ በኋላ...” ብለን ዕቅድ እናወጣለን፤ እንደምንለወጥ ለተሻለ ነገ ዛሬ ሁሉን በትዕግስት እየተቀበልን እንደምንታገል ለራሳችን ቃል እንገባለን። ለዘላለማዊ ነገ ማቀድ እና በዘላለማዊ ነገ ውስጥ በተትረፈረፈ ሕይወት ለመኖር ምን ያህል ማቀድ እና መዘጋጀት ያስፈልግ ይሆን? እዚህ ላይ መሠረታዊው ቁም ነገር ስለ ኃጢአት እና ስለ ክርስትያናዊ ኃላፊነት ያለን ግንዛቤ ነው። ኃጢአት ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ድኛለሁ! በሚል ትምክህት ስለተጋረደ የዕለት ተዕለት ሕይወቴን በምኖርበት ቁም ነገር ውስጥ በራሴ ዐይን፣ በራሴ ግንዛቤ፣ በራሴ መለኪያ እና በራሴ ፍርድ እንደዳነ ሰው እየኖርኩኝ ነው። ስለዚህ ማን ነው ኃጢአተኛ ነህ ሊለኝ የሚደፍር? ኃጢአቴንስ ለማን ነው የምናዘዘው? የእኔን ኃጢአት ለመፍታት ማን ምን ስለሆነ ነው ሥልጣን ያለው? ነገር ግን የትራፊክ ሕግ ከጣስኩኝ ለሚወሰንብኝ ቅጣት ሳላንገራግር እከፍላለሁ!

መንፈሳዊው ሰው በየዕለቱ ወደ እግዚአብሔር ምሕረት የሚመለስ ልብ እና በየዕለቱ የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚለምን ትሕትና ያለው ነው። ያለ ጸሎት፣ ያለ አርምሞ፣ ያለ ጾም፣ ያለ ኅሊና ምርመራ እና ያለ ምሥጢራት ሱታፌ የሚያብብ ውስጣዊ ሕይወት የለም። መንፈሳዊው ሰው ሁሉ ነገር እንደተፈቀደ ነገር ግን ሁሉ ነገር የማይጠቅም መሆኑን ስላወቀ ብቻ ሳይሆን በክፉዎች ምክር ላለመሄድ፣  በኃጢአተኞች መንገድ ላለመቆም እና በዋዘኞች ወንበር ላለመቀመጥ የጨከነ በመሆኑ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ለዚሁ ውሳኔው እስከመጨረሻው ያስጨክኑት ዘንድ በየዕለቱ ከዳዊት ጋር ድምጹን አስተባብሮ “አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፥ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ” (መዝ 51፡3-5)እያለ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን ያስተውላል።

በመሠረቱ አንድ ወዳጅ ለወዳጁ የሚሰጠው አስተውሎት እና ጊዜ ፊቱን ወደ ወዳጁ የመለሰበት እና በመላ እሱነቱ በወዳጁ ዘንድ ልቡን የከፈተበት የፍቅሩ እና የመሰጠቱ ክብር ምስክር ነው። በመሆኑም የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ልቡን በእግዚአብሔር ፊት ለማፍሰስ እና ነውሩን ላለመደበቅ የሚወድበት መጠን የወዳጅነቱን እና የእምነቱን ብስለት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር በሁለንተናው እንዲመለከተው በመጠማት “አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፥ፈትነኝ መንገዴንም እወቅ፥ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ” (መዝ 139፡23-24) እያለ እግዚአብሔር ልቡን እና ኩላሊቱን እንዲመረምረው ነውሩን ሁሉ ገበናውን በልጁ ደም በሚሸፍንለት በእግዚአብሔር ፊት ይገልጣል። ይህንንም የሚያደርገው እግዚአብሔር ራሱ “የዘለዓለምን መንገድ ይመራው” ዘንድ ነው። በመሆኑም ለዘላለም መንገድ የሚዘጋጅ እና የዘላለም መንገድ ተስፋ ያለው ሰው መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ወደሆነው ወደ እርሱ መመለሱ እና ኃጢአቱን መናዘዙ፣ የሕይወቱን መንገድ ዕለት ዕለት ማስተዋሉ እና መጋደሉ ባሕርያዊ ክብሩ እንጂ ከባሕርዩ ውጪ የተጫነበት ቀንበር አይደለም።

መንፈሳዊ ሕይወት እንደ እኔ የግል ፍላጎት፣ የግል ዕቅድ እና ፕሮግራም የሚመራ ቁም ነገር ሳይሆን በእኔ ውስጥ ያደረው የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ እንደሚመኘው፣ በእኔ ላይ ከዘላለም ጀምሮ እንዳለው ዓላማ፣ እርሱ እንደሚፈቅደው እና በእኔ ታላቅ ነገርን ለማድረግ በሚወደው በጎ ፈቃዱ ኃይል የሚ‘ኖር ሕይወት ነው። ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ እግዚአብሔር የሚመልስ፣ የሚገስጽ፣ ለኀሊናዬ ያለማቋረጥ መለኮታዊ እውነትን የሚመሰክር እና ለንስሐ የሚያበረክክ የትህትና፣ የልጅነት እና የሰላም መንፈስ ነው። በመሆኑም ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ኢየሱስ ራሱን ባዶ ባደረገባት ትህትና ምንምነቴን የሚያሳየኝ፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት ውጪ ምንም እንደሌለኝ የሚያስተምረኝ፣ እንደ ልጅ እንጂ እንደ አባት እንዳልንቀሳቀስ ልጅነቴን የሚያስታውሰኝ፣ ዐመጻን በማያውቅ መታዘዝ የሚያሳድገኝ መንፈስ ነው። ስለዚህ በዚህ መንፈስ ትህትና በተገራ ልቡና ከዳዊት ጋር አብሬ በሕይወቴ ስለሆነው፣ እየሆነ ስላለው እና ወደፊትም ስለሚሆነው ነገር ሁሉ “ለእኛ አይደለም፥ አቤቱ፥ ለእኛ አይደለም፥ ነገር ግን ለስምህ ስለ ጽኑ ፍቅርህና ስለ እውነትህም ክብርን ስጥ” እያልኩኝ እዘምራለሁ (መዝ 115፡1)።

ንስሐ፣ መመለስ እና በደልን በእግዚአብሔር ፊት መግለጥ እግዚአብሔርን የሚጠማ፣ በእግዚአብሔር ተራራ ለማደር የሚወድ፣ ዕለት ዕለትም የእግዚአብሔርን ምሕረት ለማየት በመቅደሱ መኖርን ብቻ የሕይወቱ ብቸኛ ጥያቄ አድርጎ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ሰው ልብ መሠረታዊ ቁመና ነው። እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ክብሩ ነው፤ ወደ እግዚአብሔር የሚወስደውን መንገድ ሁሉ በጥንቃቄ፣ በክብር እና በተቀደሰ ፍርሃት በልቡ ውስጥ ይጠብቀዋል። በመሆኑም ከእግዚአብሔር የሚያርቀውን ነገር ሁሉ እየተጸየፈ ዕለት ተዕለት ተጋድሎ ያደርጋል። በዚህ የተጋድሎ፣ የጾም-ጸሎት ጉዞ ስለ እግዚአብሔር ምሕረት እንጂ ስለራሱ ቅድስና የሚናገርበት ቋንቋም ይሁን ስለራሱ ጽድቅ የሚሰፍርበት ሚዛን የለውም። ነገር ግን ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው እና እንደ ፍቅሩ ልክ ዋጋውን የሚሰጠውን ጌታ በመታመን በምሕረቱ ተስፋ እያደረገ ዕለት ዕለት “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፥ ርኅራኄው አያልቅምና” (ኤር 3፡20) የሚለውን የነብዩ ኤርሚያስን ንስሐ በልቡ ያለማቋረጥ ያስታውሳል።

የንስሐ ልብ በእግዚአብሔር ፊት የማይመጻደቅ ትህትና ነው፤ በመሆኑም እንዲህ አይነቱ ልብ በእግዚአብሔር ፊት ማን እንደሆነ ያውቃል። የንስሐ ልብ እግዚአብሔርን በሚያፈቅርበት መታመን ራሱን በአምላኩ ፊት የሚያፈስስ እና ትልቁ ኃጢአት በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ መቀረጥ መሆኑን የሚያምን፤ ምሕረትን ለመለመን እና ለመቀበል በራሱ ጽድቅ የማይመካ ልብ ነው። ጾም የእያንዳንዳችን ልብ እንዲህ አይነት ግብረገብ ይኖረው ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የሚገራበት ልጓም ነው። መንፈስ ቅዱስ በጾም-ጸሎት ትህትና ልባችንን እየገረዘ የጌታን ልብ እስኪመስል ድረስ ያጠራዋል፤ በመጨረሻም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር በአንድ ድምጽ “እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን” (1ቆሮ 2፡16) ስንል መንፈስ ቅዱስ ራሱ የክርስቶስን ልብ በውስጣችን ስለመቅረጹ ምሥክር ይሆናል።  

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ መዝ 51፡3-6፣ 9-14

“አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፥ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ። ... በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፥ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ”።

ጸሎት

አቤቱ ፊትህን እሻለሁ፤ በሁሉ ነገር አንተን ማየት የምችልበትን፣ በሕይወቴ ምዕራፎች ሁሉ ውስጥ መገኘትህን ልብ የምልበትን፣ ከእኔነቴ ታሪክ ላይ አንተን የማነብበትን ማስተዋል እሻለሁ። አቤቱ ልቤ አይታበይብኝ፤ ዐይኖቼም ከፍ ከፍ አይበሉብኝ። ጌታዬ እና መምህሬ ሆይ አንተ የሰውን ደካማነት ታውቃለህና ኃጢአቴን እና መተላለፌን ሁሉ ይቅር በልልኝ። ምሕረትህ ከሕይወት የሚሻል አምላክ ሆይ እኔን ደካማውን ልጅህን በመንግሥትህ አስታውሰኝ። ስሜን የምታውቅ፣ ካለመኖር ወደ መኖር የጠራኸኝ አምላክ ሆይ የሕይወትን መንገድ አሳየኝ፤ እኔም በምትሄድበት መንገድ ሁሉ፣ ልትወስደኝ በምትፈልግበት ሁሉ ፈለግህን እከተል ዘንድ አለማመኔን እና ደካማነቴን እርዳው። በአንድ ልጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም። አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. የመጨረሻ ንስሐዬ መቼ ነበር? ንስሐ እንዳልገባ የሚከብደኝ ነገር ምንድነው? ማን ሊረዳኝ ይችላል?
  2. እግዚአብሔርን በዚህ በዐቢይ ጾም በየትኛው የሕይወቴ ክፍል የበለጠ እፈልገዋለሁ? በየትኛው የሕይወቴ ክፍል የእግዚአብሔርን መገለጥ እጠባበቃለሁ?
  3. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።