Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም 9ኛ ቀን

ዐቢይ ጾም 9ቀን

Lent-main-imageራስን መካድ

ራስን መካድ ማለት ነገሮች በተፈጠሩበት ዓላማ እና ክብር ልክ ከላይ ሳይጨምር ከታች ሳይጎድል በፍትሐዊ ዐይኖች መመልከት መቻል ማለት ነው። ከዚህ በተቃራኒው ነገሮችን ባልተፈጠሩበት ዓላም መመልከት አእምሮአችንን ስለሚያጨልም ፍርዳችን የጎደለ፣ ሚዛናችን የተዛባ ሆኖ እውነት እውነት የሚሆነው ከማንነቱ በሚነሳ ገዢ ሐቅ ሳይሆን ከእኔ የግል ደስታ እና ነገሩ ከሚሰጠኝ ስሜት የሚታይ ይሆናል። በዚህ ዐይነት ነገሮችን ባልተፈጠሩበት ዓላማ መመልከት የዕይታችንን ጥልቀት እና በዐይናችን ውስጥ ያለውን የእውነትን ብሌን ስለሚያንሸዋርር መልካምን ከክፉ የመለየት መሠረታዊ ክርስትያናዊ አስተውሎታችንን ይነጥቀናል፤ በመሆኑም በሕይወታችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ በእጅጉ እንቸገራለን።

የኃጢአት ልምምድ በተራዘመ ቁጥር የራዕይ ንጹህነት እየደበዘዘ፣ ነገን አሻግረን መመልከት የሚለው እና ዛሬን በመዳናችን መጽናትን የሚጠይቀው ክርስትያናዊ ቁርጠኝነት አቅም እያጣ ይመጣል። ራዕይ በጾም-ጸሎት የሚታደስ የልብ እና የአእምሮ ድንግልና ነው። ራስን መካድ እንዲህ ያለውን ራዕይ መልሰን በማግኘት የሕይወትን ውኃ ልክ በድጋሚ ገንዘባችን የምናደርግበት ግብረገብ ነው። በዚህ አይነት ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸው ጸጋዎች ቢሆኑም እንኳን ራሳችንን በመካድ ግብረገብ ውስጥ ሆነን እንድንጠቀምባቸው እንዲህ አይነቱ ግብረግብ መሠረታዊ ክርስትና ነው። ስለ ስራችን እና ስለ አገልግሎታችን ሁሉ ታላቅነት፣ ስኬት እና አስፈላጊነት ፍርዱ ከእኛ ከራሳችን ሳይሆን ከጌታ ከራሱ ይሆን ዘንድ እኛ ግን በፊቱ ራሳችንን በመካድ እና እርሱ በእውነት ጌታ መሆኑን በማወቅ እንመላለስ ዘንድ በነብዩ ኤርሚያስ ቃላት ጌታ ራሱ እንዲህ ይላል፡

“ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ 24ነገር ግን የሚመካው፦ ጽኑ ፍቅርንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ ጌታ መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ ነገሮች እነዚህ ናቸውና” (ኤር 9፡24)።

ራስን መካድ እግዚአብሔር ለባሕርያችን ኅልውና መሠረታዊ አድርጎ ካልፈጠረው ፍጥረት እና ሁኔታ ጋር ጤናማ ባልሆነ ሰንሰለት የተገመድንበት የሕይወት ጥልፍልፍ የመፍታት ረጅም ጉዞ ነው። በዚህ ጉዞ ስኬታማ ለመሆን ዕለት በዕለት ባርያ አድርጎ ከሚበዘብዘን ነገር እየተላቀቅን፣ በአእምሮአችን መታደስ እየተለወጥን፣ የልባችንን ድንግልና በመጠበቅ የራዕያችን ብርኀን የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ያለማቋረጥ የምናሰላስልበት ውስጣዊ ጽሞናን መለማመድ ያስፈልጋል። ቅዱስ ጳውሎስ “ሳታቋርጡ ጸልዩ” (1ኛ ተሰ 5:17) እያለ የክርስትያን ልብ እንደ ዐይን ቅጽበት እንኳን በእግዚአብሔር ፊት መሆኑን ማቋረጥ እና ከእግዚአብሔር በታች በሆነ ነገር መገዛት እንደሌለበት ያስገነዝበናል። ዐቢይ ጾም እንዲህ ያለውን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ዐይን ቅጽበት እንኳን በማይቋረጥ የነፍስ አስተውሎት መኖርን የምንለማመድበት የጸጋ ወቅት ነው።

ዐቢይ ጾም እግዚአብሔር በፍጥረት መካከል ያስቀመጠውን ጤናማ ርቀት የምናከብርበት እና የትኛውንም ፍጥረት እግዚአብሔር ከወሰነለት ርቀት በበለጠ ቅርበት ወደ ልባችን እንዳናስጠጋው የሚያስችለንን መጠንን ማወቅ የምንለማመድበት የጸጋ ትምህርት ቤት ነው። ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸውን መልካም የጸጋ ሥጦታዎች እንኳን ቢሆን ከልክ በላይ ወደ ልባችን ባስጠጋናቸው መጠን ከእግዚአብሔር ሰርቀን የራሳችን ለማድረግ እየሞከርን ነው። እነዚህ ነገሮች እና ሥጦታዎች በሙሉ እግዚአብሔር እነርሱን ከፈጠረበት እና ለእያንዳንዳችን እንደ በጎ ፈቃዱ ልግሥና ከሰጠበት አባታዊ መጋቢነቱ አንጻር ሊታዩ እና የምሥጋና ምክኒያቶች ሊሆኑ ይገባል። ከዚህ በተቃራኒው እነዚህን ነገሮች ከራሳችን ማንነት አንጻር ብቻ የምንመለከታቸው እና ይገባኛል ብለን ባለቤት የምንሆንባቸው ነገሮች በሙሉ እሥራኤላውያን ከሠሩት የወርቅ ጥጃ የተለየ ማንነት አይኖራቸውም። እነዚህን ነገሮች የራሳችን ንብረቶች አድርገን ባለቤት ከሆንባቸው ምንጫቸው እና ፍጻሜያቸው የእኛ ሰብዓዊ ክብር እና ዝና ይሆናል። ፍጥረት ፈጣሪውን ያከብር እና ያገለግል ዘንድ እንደተፈጠረ እንዲሁ እኛም እነዚህን ነገሮች እግዚአብሔር እንሆንባቸዋለን። እኛን እና የእኛን ፈቃድ ብቻ እንዲያገለግሉ የተፈጠሩ እስኪመስል ድረስ እበዘብዛቸዋለን። በመሆኑም እነዚህ ነገሮች ባሉበት እና በሚገለጡበት ሥፍራ ሁሉ የእኛ ስም እንዲነሳ፣ እንዲጨብጨብልን እና የምሥጋና ማዕጠንት እንዲቀርብልን ግድ የሚል ክፉ መንፈስ ይገዛናል። ሥልጣን መልቀቅ፣ ኃላፊነትን በጊዜው ለተተኪ ማስረከብ፣ መታዘዝ፣ ትህትና የሚባሉት መሰረታዊ የክርስትና እሴቶች ፍጹም የማይታሰቡ የሚሆኑት በዚህ አይነቱ ራስን የማምለክ ክፉ ዝንባሌ ምርኮ ስንያዝ ነው። ጓደኞቻችን እና በዙርያችን ያሉት ሰዎች ሁሉ መገኘታትንን እንዲያውቁ፣ የክብር ስፍራ እንዲሰጡን፣ የእኛ መገኘት በሕይወታቸው ትልቁ ስኬት እንደሆነ አድርገው እንዲቀበሉ እና በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በእኛ ፊት የራሳቸውን ትንሽነት እንዲመሰክሩ እንጠብቃለን። ነገር ግን ይህንን ሁሉ እንኳን ብናገኝ ልባችን አይረካም። የምንከተለው ነገር የራሳችንን ቅዠት እንጂ የእግዚአብሔርን ሕልም ባለመሆኑ ቅዠቱ መቼም ቢሆን እውነት ሊሆን አይቻለውም። ይህንን በማስተዋል በራሳችን ዓለም እንዳንዋጥ እና የሁሉን ነገር ግለት ከራሳችን ትኩሳት አንጻር እንዳንለካ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ እያለ ጠንከር ያለ ተግሳጽ ያስተላልፋል፡-

“አንተን እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልከውስ ምን አለህ? እንግዲህ የተቀበልክ ከሆንክ፥ እንዳልተቀበልክ የምትመካው ስለ ምንድነው?” (1 ቆሮ 4፡7)

እንግዲያውስ ዐቢይ ጾም በሰጪ እና በተቀባይ መካከል የተዛባ ዕይታችንን የምናስተካክልበት፣ የተንሸዋረረውን ጤናማ መለኮታዊ የዐይን ብሌን በዐይናችን መካከል ተገቢውን ስፋራ ይዞ የእግዚአብሔርን አምላክነት እና የእኔን ምስኪን ፍጥረት እንዲያስተውል የሚገራበት ወቅት ነው። ዐቢይ ጾም ዕይታን የሚያስተካክል፣ ሚዛንን የሚያቃና፣ ፍርድን በመለኮታዊ ጽድቅ እውነተኝነት የሚለካ፣ የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ማንነት በመንፈስ ቅዱስ እሳት እያነጻ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ የሚቀድስ፣ በመንፈሳዊ ቁስሎቻችን ላይ ከጌታ መስቀል የሚፈልቀውን የምሕረት የወይራ ዘይት እያፈሰሰ በሂሶጵ ቅጠሎች የሚያጥበን፣ ጸጥ ብሎ ከሚፈሰው የሰሊሆም ውኃ የሚያጠጣን የጸጋ ዘመን ነው።

ራስን መካድ ይህንን መንገድ ለመጓዝ የመጀመርያው እርምጃ ነው። ራስን መካድ እግዚአብሔር በእኛ ሕይወት እግዚአብሔር ራሱን እንዲሆን መፍቀድ እና እግዚአብሔርን በእኛ ልክ ከመስፋት መቆጠብ ነው። ራስን መካድ እግዚአብሔር የሆንንባቸውን እና እንደ እግዚአብሔር የምንንቀሳቀስባቸውን የሕይወት ክፍሎች ለእውነተኛው እግዚአብሔር በእምነት አሳልፈን የምንሰጥበት ትህትና ነው። ራስን መካድ የተወሳሰበ ፍልስፍና ሳይሆን ቀላል የክርስትና መሰረታዊ አቋም ነው፤ ራስን መካድ ማለት ሁለተኛ ሊሆን የሚገባውን ነገር አንደኛ አለማድረግ እና የፍጥረትን መለኮታዊ ቅደም ተከተል ማክበር ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን በሚመለከት አንድ ክርስትያን ሊኖረው የሚገባውን የሕይወት መርሕ ሲያስተምር እንዲህ ይላል፡- “ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ” (1ጴጥ 4፡8)

እንግዲህ ራስን መካድ በተፈጠርንበት ልኬት፣ በመለኮታዊ ጥበብ በተሰፈረ መጠን፣ ሁሉን ነገር በልክ እና በወሰን ጠብቆ እግዚአብሔር በፍጥረቱ የተገለጠበትን ትህትና እና ጨዋነት ማክበር ነው። መጽሐፍ እንደሚናገር እግዚአብሔር በኃይሉ ሥልጣን ለሁሉም መስፈርያ ቀመር አበጅቶ፣ ወርዱ እና ቁመቱ፣ ክብደቱ እና ስፋቱ ከዘላለም ጀምሮ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በተለካ መለኮታዊ የጥበብ ሚዛን ተሰፍሮ፣ ሁሉ በሚገባው ሥፍራ፣ በሚገባው መጠን፣ ለሚገባው ዓላማ ተፈጥሮ ተሰይሟል። መጽሐፍ ጥበብ ይህንን ድንቅ መለኮታዊ ኃይል እንዲህ እያለ ይወድሰዋል፡- “ታላቁ ኃይልህ ሁልጊዜ በሥልጣንህ ሥር ነው፤ የክንደህን ኃይል ሊቋቋም የሚችልስ ይኖራልን? በምድር ላይ እንደሚወድቅ የማለዳ ጤዛ ጠብታ፥ መላው ዓለምም ላንተ እንደዚሁ በሚዛን ላይ እንደሚደረግ ኢምንት ክብደት ነው” (ጥበብ 11፡20)። መጽሐፈ ጥበብ ይህንን የእግዚአብሔርን ኃይል የሚገልጽበትን መደነቅ መዝሙራችን አድርገን እግዚአብሔርን ይበልጥ በማወቅ ይበልጡን ራሳችንን በመካድ እውነተኛ መልካችንን እንልበስ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፊል 2፡1 16

የክርስቶስ ትሕትና ምሳሌነት

“ስለዚህ ለእናንተ በክርስቶስ አንዳች መበረታተታት ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናትም ቢሆን፥ የመንፈስም ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄም ቢሆኑ፥ በአንድ አሳብ ተስማምታችሁና አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ኖሯችሁ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። ከራስ ወዳድነት ወይም ከትምክሕት የተነሣ አንድም ነገር አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በትሕትና ባልንጀራውን ከራሱ ይልቅ እንደሚሻል አድርጎ ይቁጠር፤ እያንዳንዱም ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኑር። እርሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ኖሮት ሳለ እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩልነትን እንደመንጠቅ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን እንደ ሰው ሆኖ በመወለድ የባርያን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በሰው አምሳል ተገኝቶ፥ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በዚህም የመስቀልን ሞት እንኳ በመቀበል እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ የሚበልጠውን ስም ሰጠው፤ በዚህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም እንዲንበረከኩና ምላስ ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር እንዲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ እንዲመሰክሩ ነው። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ ይበልጥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ በጎ ፈቃዱን እንድትፈልጉና እንድታደርጉ ሁለቱንም በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ሁሉንም ነገሮች ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ በዚህም በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ሆናችሁ በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት የምታበሩ፥ ያለ ነቀፋ የዋሆችና ነውርም የሌለባችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ትሆናላችሁ”

ጸሎት

ጌታ ሆይ በመመለስ እና በማረፍ አንተ እግዚአብሔር እንደሆንክ በሁለንተናዬ የማውቅበትን ትህትና እሻለሁ። አንተ የፈጠርከኝ፣ ካለ መኖር ወደ መኖር ሕይወት የጠራኸኝ አምላኬ ነህና በእኔ ላይ ላለህ ዓላማ በእምነት መገዛት የምችልበትን ጸጋ በውስጤ አፍስስ። አቤቱ እንደ አለማወቄ መጠን ለምኞቴ አሳልፈህ አትስጠኝ፤ ይልቁንም ከራሴ ጸሎት እና ከአላዋቂነቴ ምክር ጠብቀኝ። ጌታዬ እና አምላኬ ሆይ! ክብሬ እና ልዕልናዬ ከንጉሥነትህ ዙፋን ስር ዝቅ ብሎ መገዛት እንደሆነ እንዳልዘነጋ ልቤን በቃልህ ምክር አጽና፤ እግዚአብሔር በሆንኩባቸው የሕይወቴ ክፍሎች ሁሉ ወደ እውነተኛው ማንነትህ ብርኀን እደርስ ዘንድ ከፍርሃቴ እና ከጠባሳዎቼ ትዝታ የሚፈውሰኝ ቅዱስ መንፈስህ በልቤ ላይ ከልጅህ መስቀል የሚቀዳውን የማጽናናትህን ዘይት አፍስስልኝ። አቤቱ በነፍሴ መካከል በምሥጢረ ጥምቀት የተወለደውን እና በምሥጢረ ሜሮን ታትሞ ለዘላለም ያንተ መሆኔ የተያዘበትን የልጅህን የዋስትና ስም በነፍሴ ውስጥ ቀስቅስ። ከአንተ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሚከብር እና በሚነግሥ በአንድ ልጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም! አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. በሕይወቴ እግዚአብሔር ሆኜ የያዝኳቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? እነርሱን ለጌታ ለመግለጥ እፈልጋለሁኝ?
  2. የነገ ሕይወት ጭንቀቴ እና ዛሬን እንዴት አልፌ የምልበት የሕይወቴን እንቆቅልሽ ለጌታ አውርቼለት አውቃለሁ? ለምን ሁሉንም ልቤን በእርሱ ፊት አፍስሼ የሚለኝን አልሰማም?
  3. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።