Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም 10ኛ ቀን

ዐቢይ ጾም 10ቀን

Lent-main-imageደብሮኛል! (κηδία, Acedia)

አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) የሚለውን ቃል የሚሸከመውን ሐሳብ በቀላሉ ለመተርጎም በጣም አስቸጋሪ ነው። ቃሉ በውስጡ ሁለንተናዊ ድካምን፣ ስንፍናን፣ ስልቹነትን፣ ለምንም ነገር ፍላጎት ማጣትን፣ ምክኒያቱ የማይታወቅ ድባቴን፣ ራስን መጣልን፣ ተስፋ እና ወኔ አልባነትን ሁሉ ይይዛል። በመሆኑም አካል እና አእምሮ በማያቋርጥ ቋሚ ድካም እና ዝለት የሚያዝበት፣ ብሎም ቀኑን በሙሉ ምንም ሳይሰራ የዋለው አእምሮ እና አካል እንዲህ ነው ተብሎ ሊተረጎም በማይችል፣ ምክኒያት አልባ እንቅልፍ እና ድብርት የሚያዝበት ቁም ነገር በበረሃ አባቶች (The Desert Fathers) ቋንቋ አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) እየተባለ ይጠራል።

አኬዲያ ሊገለጽ የማይችል እና ምክኒያቱን ያላወቅሁት ሁለንተናዊ ድካም፣ ዕረፍት፣ ዕርካታ፣ ደስታ፣ አመስጋኝነት ወዘተ የሌለበት ሕይወት ማለት ነው። በዚህ ውስጥ የሚያልፍ ሰው ምንም ነገር ለማድረግ ፍላጎትም ይሁን ተነሳሽነት የለውም። ምንም ነገር ወኔውን ቀስቅሶ ለሥራ አያነሳሳውም። በሕይወቱ ምንም ነገር አይጠብቅም፤ ነገ ወይም ዛሬ የሚል የግዜ ግንዛቤም ይሁን አስተውሎት የለውም። አኬዲያ የሰውን ልጅ በሥጋ እና በነፍሱ ዕረፍት፣ ሰላም፣ ምልዐት እንዳይኖረው በሁለንተናው እስረኛ የሚያደርገው ክፉ መንፈስ ነው። በመሆኑም በምንም ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ መቆየት እና አንድን ነገር እስከ መጨረሻው ማሳካት አይቻለውም። በተመሳሳይ ጊዜ የተለያዩ ነገሮችን ያደርጋል፤ ከአንዱ ነገር ወደ ሌላው ነገር በፍጥነት ይለዋወጣል፤ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነቱም ቢሆን ቋሚ ወዳጅ፣ ቋሚ ጓደኛ፣ ቋሚ የቅርብ ሰው የለውም። ድርጊቶቹን የሚያመሳስላቸው ብቸኛው ቁም ነገር ሰውየው ለየትኛውም ድርጊቱ ትርጉም የሌለው እና ስሜት አልባ መሆኑ ነው። በተለይም ብቻውን በሚሆንበት ጊዜ ባለበት ሥፍራ ጸንቶ መቆየት በፍጹም አይቻለውም፤ በውስጡ አንዳች ስሜት ካለበት ሥፍራ ለቅቆ እንዲሄድ፣ በአንድ ሥፍራ እንዳይረጋ፣ እንዲባክን፣ በሁሉም ስፍራ እልፍ እልፍ እንዲል ያባክነዋል። አንዳንድ ጊዜ ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ መንገድ ይጀምራል፤ ሰዎችን በእጅ በእግር ብሎ ያገኛቸዋል፤ ነገር ግን አብሮአቸው አይዘልቅም። ግንኙነቶቹ በሙሉ ለጥቂት ጊዜ እርሱ ማዕከላዊ በሚሆንባቸው ርዕሶች ላይ ብቻ ያተኮሩ እና እዚህ ግባ የሚባል ውኃ የሚያነሳ ወይም ለሕይወት የሚሆን ርዕስ የሌላቸው ናቸው።

አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) ሰው ባለበት ሥፍራ ሰላም እና ዕረፍት፣ ምልዐት እና መከናወን እንዳይሰማው ስለሚያደርግ ሰውየው ያለበትን ሥፍራ የመጥላት፣ በእጅጉ የማማረር እና ሌላ ቦታ ቢሄድ የተሻለ ሰው እንደሚሆን የማሰብ አባዜ ይይዘዋል። በዚህ አይነት ሕይወት ቀለል ብሎት የሚኖርበት አዲስ ስፍራ ይናፍቃል። ነገር ግን ያ አዲስ ስፍራ ብዙም ሳይቆይ በፊት ከነበረበት ሥፍራ የበለጠ አስቀያሚ ሆኖ ስለሚያገኘው አስቀድሞ እንዳደረገው እንዲሁ ደግሞ ወደ አዲስ ቦታ ይነሳል። አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) ሰውየው የሚሰራው ሥራ እንኳን ብዙዎችን የሚጠቅም እና ብዙዎች ለሕይወት የሚሆን ነገር የሚያተርፉበት ቢሆንም ቅሉ፣ እርሱ ግን በነፍሱ ጥልቅ ውስጥ የከፋ ባዶነት፣ ትርጉም አልባነት፣ ዕርካታ እና ምልዐት ማጣት ያሰቃየዋል። በመሆኑም ሥራውን ትቶ አዲስ ስራ ይፈልጋል፤ አዲሱ ሥራ ነፍሱ የምትጠማውን ሰላም፣ ዕርካታ፣ ምልዐት እና መከናወን እንደሚሰጠው ያስባል። ነገር ግን አፍታም ሳይቆይ አዲሱ ሥራ ከቀደመው ስራ የከፋ እና የማያስደስት ሆኖ ያገኘዋል። እንዲህ ያለው የፍትወት ቀውስ ጥልቅ ከሆነ ጭንቀት እና ፍርሃት የሚነሳ በመሆኑ አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) የብዙ ነፍሳዊ ቁስሎች መግባቢያ ቋንቋ ነው።

አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) ክፉ መንፈስ ነው። ይህ ክፉ መንፈስ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡትን እና መንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር የሚታገሉትን ነፍሶች የሚያድን መንፈስ ነው። በመሆኑም ኃይል ካለበት ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ጋር ሕብረት እንዳይኖራቸው ያጠምዳቸዋል። በመሆኑም ድካም እና ሥራ የሚጠይቁ የመንፈሳዊ ሕይወት ቁም ነገሮችን ሽባ ስለሚያደርግ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት ወደ ፊት ፈቀቅ እንዳይል አስሮ ይይዘዋል። ጽሞና፣ በአንድ ስፍራ መርጋት፣ ሐሳብን መሰብሰብ፣ መጸለይ የሚባሉ ነገሮች ሲነሱ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ብርቱ ድካም እና እንቅልፍ በሰውየው ላይ ይሆናል። ቅዱስ ዮሐንስ ክሊማኮስ ይህንን የነፍስ ድባቴ እና የመንፈሳዊው ዓለም አሰራር ሲገልጽ “አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) የነፍስ ልምሻነት፣ የአእምሮ ሁለንተናዊ ድካም እና የተጋድሎ ስንፍና” ነው ይለዋል።[1] በዚህም መንፈሳዊው ሰው በሥራ ፈትነት ተጠምዶ አእምሮው በላይ በሰማያት ያሉትን ከፍ ያሉ ነገሮች ከማሰብ እንዲቦዝን፣ በአንድ ሥፍራ እንዳይረጋጋ እና ልቡ ሰላም እንዳያገኝ ያደርገዋል።[2]

አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) ቀንደኛ የመንፈሳዊ ሕይወት እና የጸሎት ሕይወት ጠላት ነው።[3] ይህ የአኬዲያ መንፈስ በተለይ በጸሎት ሰዓት አካልን እና አእምሮን ሁሉ በሁለንተናቸው የሚያደክም ድባቴ ነው። በመሆኑም ምንም ነገር ሳይሰራ በተቀመጠበት ደህና የነበረው ሰው “ጸሎት” ሲባል ሐሞቱ ይፈስሳል፤ ሁለንተናው ይደክማል፤ አንዳች ነገር ተጭኖ ይይዘዋል። እንደ ምንም ጸሎቱን ቢያደርስ እንኳን በሚደንቅ ሁኔታ ከጸሎቱ በኋላ ዐይኖቹ ይከፈታሉ፤ በድጋሚ ጉልበት ያገኛል፤ ከላዩ ላይ የተጫጫነው ነገር ተነስቶለት ምን ሆኜ ነው? እስከሚል ድረስ ይገረማል።[4] ነገር ግን ቀጣዩ የጸሎት ሰዓት ሲደርስ፣ ቅዳሴ ማስቀደስ ሲኖር ያ ንቁ የነበረው ሰውነት መልሶ ልምሻ ይይዘዋል፤ በቅዳሴ እና በጸሎት መሃል ሆኖ እንቅልፍ የሚመስል ነገር ልቡን ይሰልበዋል፤ ዐይኖቹን መክፈት እስከሚያቅተው ድረስ ይጫጫነዋል፤ ጸሎቱ እና ቅዳሴው ሁሉ በማዛጋቱ ድምጸት የተቃኘ ይሆናል።[5] በዚህ አይነት የአኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) መንፈስ የሰው ልጅ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ ድካሙ እና ሊገባው ያልቻለው ተራራ የሆነበት ቁም ነገር ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግ ጸሎት ፍጹም አሰልቺ እና ትርጉም የለሽ እንደሆነ እንዲያስብ ያደርገዋል። ከዚህ ጋር አያይዞ ጾምን ማስተው፣ “ዛሬ አልቻልኩም”፣ “በቃ ነገ እጀምራልሁ”፣ “በቃ ሰኞ እጀምራለሁ” እያለ የፋሲካ ዋዜማ ላይ መገኘትን ያለማምደዋል።

አኬዲያ (ἀκηδία, Acedia) በመንፈሳዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በሥራ ዓለም ውስጥም በስራችን አለመርካት፣ ንፉግነት፣ የሕይወትን ውብ መልክ ለማየት መቸገር፣ አካባቢን መጥላት፣ በውስጣችን ላለው ቀውስ እና ዕርካታ ማጣት አብረውን የሚኖሩትን ሰዎች ተጠያቂ በማደረግ ወ.ዘ.ተ. ራሱን ይገልጣል።[6]  በዚህ መንፈስ የታሰሩ ሰዎች መሠረታዊ የሆነ በአንድ ስፍራ፣ በአንድ ወዳጅነት የመርጋት ችግር የሚስተዋልባቸው፣ ሁሉም ነገር የሚያስጨንቃቸው፣ በውል የማያውቁት ነገር ደርሶ ስሜታቸውን ረብሾ የሚያስለቅሳቸው፣ ባጠቃላይ በሥጋ እና በመንፈስ በውል በማይታወቅ ድካም የተያዙ፣ ቀጣይነት ያለው መንፈሳዊ እና አካላዊ ድርቀት የሚስተዋልባቸው ናቸው። ይህንን ድባቴ እና ጭንቀት ለማስወገድ ያለ በቂ ምክኒያት መንገድ መሄድ፣ ሰዎችን ማግኘት፣ በአንድ ስፍራ አለመወሰን፣ ሁልጊዜ ውጪ ውጪውን ማለት፣ ዓለምን ሁሉ ያድኑ ይመስል ከራሳቸው የሕይወት ቁም ነገር ይልቅ ለሌላ ለሁሉም ነገር ጊዜ መስጠት ያዘወትራሉ። በዚህ ድርጊታቸው ድባቴው የሚለቃቸው ቢመስላቸውም ቅሉ፣ ኃላፊነትን ወደ ጎን በማድረግ በሥራ፣ በትምህርት፣ በትዳር፣ ባጠቃላይ በኑሮ እስከ አሥራ አንደኛው ሰዓት ድረስ አንዳች ፍሬ ያለው ነገር ሳይሰሩ በመጫረሻው ሰዓት አካል እና አእምሮአቸውን ከሚገባው በላይ በማስጨነቅ ኃላፊነቶታቸውን በመወጣት ሕይወታቸውን ለማስተካከል ይታገላሉ። እንደምንም ይህንን ካሳኩ “ከዚህ በኋላ በፍጹም እስከመጨረሻው ሰዓት አልጠብቅም ነገሮቼን በጊዜ አደርጋለሁ!” ብለው ለራሳቸው ቃል ቢገቡም ከዚያ መጥፎ ዑደት እና አዙሪት አይወጡም። ይህም ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ስለሚከታቸው አንዳንድ ጊዜ ምንም ነገር ለማድረግ የማያስችል ሁለንተናዊ ልምሻነት (burnout) ሊያጠቃቸው ይችላል።

የአኬዲያ መንፈስ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ አማኝ እንዳይፈራው የሚያስጠነቅቀው “የቀትር ጋኔን” ነው።[7] ይህ “የቀትር ጋኔን” ከምሳ ሰዓት በኋላ ያለ ክፉ ድካም፣ ከባድ የእንቅልፍ መንፈስ እና ለነገሮች ሁሉ ቅንጣት ፍላጎት የማጣት፣ ሥራ ፈት እና መኝታ ብቻ የሚናፍቅ ሰውነት ሆኖ ይገለጣል። ቅዱስ ዮሐንስ ካሲያን ስለዚህ ክፉ መንፈስ እንዲህ ይላል፡-

ይህ መንፈስ በተለይ በስድስተኛው ሰዓት ይበረታል።[8] ወቅቱን እየጠበቀ በአሳቻ ሰዓት እንደሚነሳ የወባ በሽታ ነፍስን በአሳቻ ሰዓት ጠምዶ ይይዛታል። አባቶች የ “የቀትር ጋኔን” እያሉ የሚጠሩት ይህ መንፈስ በዳዊት መዝሙር በ91ኛው ምዕራፍ የተገለጠው ነው።

ታላቁ የምሥራቅ መነኮሳን ኮከብ ቅዱስ ኢቫግሪዮስ በበኩሉ ይህንን “የቀትር ጋኔን” ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት ነፍስን የሚያሸብር መንፈስ እንደሆነ ይገልጻል።[9] አኬዲያ ምክኒያት አልባ የነፍስ መናወጥ ነው። ነገር ግን ምክኒያት አልባ ነው ማለት ምንጩ አይታወቅም ማለት አይደለም፤ ምንጩ የመንፈሳዊው ዓለም አሰራር ስለመሆኑ እስካሁን በዘረዘርናቸው ቁም ነገሮች ውስጥ ፍንትው ብሎ ይታያል። ነገር ግን መረሳት የሌለበት ዐቢይ ቁም ነገር ምንም እንኳን ይህ መንፈስ በሰው ላይ እንዲሰለጥን ሥልጣን የሌለው ቢሆንም ወደ ሰው የሚገባበት እና ቤቱን የሚመሰርትበት የቀደመ የኃጢአት ልምምድ ያስፈልገዋል። በመሆኑም በዚህ አይነት ችግር ውስጥ የሚያልፍ ሰው በሕይወቱ የተለማመደው ወይም ደግሞ በቀጣይነት እየተለማመደው የሚገኝ ገዳይ ኃጢአት አለ። በተለይ ዕርካታን፣ ምልዐትን፣ መከናወንን እና ስኬትን ከልክ በላይ የሚፈልግ፣ ከሚያጨናንቀው ነገር ዘወር ለማለት በተለያየ ሱስ የተገዛ ሰው በቀላሉ በአኬዲያ መንፈስ ይበዘበዛል። አኬዲያ በጌታ ላይ ከምንደገፈው ይልቅ በገዛ ራሳችን ማንነት ላይ ስንደገፍ፣ በልባችን እና በአእምሮአችን በምናብ ዕርካታ ስንናጥ እና መጠንን ከማወቅ ስንጎድል የሚያጠምደን ኃጢአት ነው። ጌታ በወንጌል “ከምታዩት እና ከምትሰሙት ነገር ጠጠበቁ” እያለ የሚያስጠነቅቀን ለዚሁ ነው።

አኬዲያ የነፍስ ህማም ነው፤ ነፍስ ይህንን ህመሟን በተለያዩ ከላይ በዘረዘርናቸው አካላዊ መገለጦች ታሳያለች። ከእነዚህ መካከል ዋነኞቹ መንፈሳዊ እውርነት፣ የመንፈስ ድርቀት፣ የአእምሮ (νοῦς) መታወር በመሆናቸው እነዚህ የነፍስን ብርኀን አደብዝዘው ነፍስ ልትረዳው በማትችለው የድባቴ ድባብ ይሸፍኗታል። በዚህም ነፍስ መሰረታዊ የሆኑትን ነገሮች እንኳን ለማስተዋል እና ተገቢውን ነገር ለማድረግ አቅም ታጣለች። ነፍስ ለእውነታ ማስተዋሏን ተነጥቃ የማትነቃበት የእንቅልፍ ሰመመን ውስጥ ትቃትታለች፤ በመሆኑም መንፈሳዊ እና መለኮታዊ የሆኑትን ነገሮች ለማሰብ ስትጀምር ልትገልጸው በማትችለው ድካም ትዝላለች። በዚህ መንፈስ ለረዥም ጊዜ ከተበዘበዘች ነፍስ እግዚአብሔርን የማወቅ ኃይሏ እየተዳከመ እግዚአብሔርን እስክትረሳው ድረስ ለመለኮታዊ ብርኀን ልትታወር ትችላለች።

ይህ የነፍስ ልምሻነት እና የአእምሮ መታወር የሰውን ልጅ ሥራ ፈት፤ ዓላማ ቢስ እና ለሕይወቱ ትርጉም ያጣ ፍጥረት ስለሚያደርገው ውሎ አድሮ ወደ ጥልቅ ኃዘን እና ወደ ተስፋ መቁረጥ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ይጥለዋል። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስን መሳደብ፣ የእግዚአብሔርን ነገር ማጥላላት፣ ፍጥረትን ሁሉ እንደ ጨለማ ሥራ የመመልከት ቁጣ ከውስጡ ይነሳል። አኬዲያ የነፍስን አስተውሎት እና ትኩረት ስለሚነጥቃት ሰው ለበለጠ መንፈሳዊ ጥቃት የተጋለጠ፣ ኃጢአት ሁሉ ቤቱ የሚሰራበት፣ ጌታ በወንጌል የሚናገረው አይነት ጸድቶ የተሰናዳ ወና ቤት ወደ መሆን ይወርዳል። አኬዲያ ነፍስ በምድር ሳለች የሲኦልን ጣዕም የሚያቀምሳት ክፉ መንፈስ ነው። አኬዲያ የሰው ልጅ ለመንፈሳዊ ሕይወት የሚያስፈልጉትን የነፍስ ኃይላት በሙሉ ከነፍስ ላይ የሚገፍፍ እና ሥጋንም ዐቅም አልባ አድርጎ የሚበዘብዝ መንፈስ ነው።

የአኬዲያ መድኃኒት ምሥጢረ ንስሐ ነው! ምሥጢረ ንስሐ ዘማዊውን ነፍስ ድንግል አድርጎ በአዲስ ልደት ይቀድሳል። ነገር ግን አኬዲያ በነፍስ ላይ ከመጣበቁ አስቀድሞ ምን ማድረግ እንደሚቻል እና ከእርሱም እንዴት ነጻ መውጣት እንደሚቻል በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ  ኤፌ 6፡10-19

“በተረፈ በጌታ በኃይሉ ብርታትም ጠንክሩ። የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም እንድትችሉ፥ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ። ተጋድሏችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ ነገር ግን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፥ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፥ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን የጦር ትጥቅ አንሡ። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ የሰላም ወንጌል ለማወጅ በዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የመዳንንም ራስ ቁር፥ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ። በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ እስከ መጨረሻው በጽናት ትጉ”

ጸሎት

ጌታ ሆይ ከአንተ ለአንተ ፈጥረኸናልና ልባችን ባንተ እስኪያርፍ ድረስ እረፍት የለንም። አቤቱ አንተን ከሚተካብኝ ነገር ጠብቀኝ፤ ለሞኝነቴ መሻት እና ላልተገራ ፍላጎቴ ምናብ አሳልፈህ አትስጠኝ። አቤቱ፥ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው፤ ስለዚህ አቤቱ መንገድህን አመልክተኝ፤ ፍለጋህንም አመልክተኝ፤ አቤቱ መንገድህን ምራኝ፤ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል። ነግር ግን ነፍሴ ወደ አፈር ተጠጋች፥ አንተ ግን እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ በዕንባ ተዋጠች፥ እንደ ቃልህ አጠንክረኝ። ልቤን ወደ ምስክርህ አዘንብል፥ ወደ ስስትም አይሁን። ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዐይኖቼን መልስ፥ በመንገድህ ሕያው አድርገኝ። እንዲፈራህ ባርያህን በቃልህ አጽና። ፍርድህ መልካም ናትና የምፈራውን ስድብ ከእኔ አርቅ። እነሆ፥ ትእዛዝህን ናፈቅሁ፥ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ፥ ምሕረትህና መድኃኒትህ ይምጡልኝ። አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. በሕይወቴ ደጋግሜ የምወድቅበት ኃጢአት ምንድነው? ይህ ኃጢአት ስለማንነቴ፣ ስለ ውሎዬ እና ስለ ዝንባሌዎቼ ምን ይነግረኛል?
  2. በጸሎት ጊዜ መሰልቸት፣ መድከም፣ በሥጋም በመንፈስም መዛል ይስተዋላል? የሚስተዋል ከሆነ በዚህ በዐቢይ ጾም ጉዞዬ ማየት ያለብኝ የሕይወቴ ክፍል የትኛው ነው?
  3. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ

ሴሞ

[1] ንጽ John Climacus, Ladder XIII.2.

[2] ንጽ John Cassian, Institutes X.2.1.

[3] ንጽ Arsenius, Letter 19. Isaac the Syrian, Ascetical Homilies 57.

[4] ንጽ John Climacus, Ladder XIII.11.

[5] ዝኒ ከማሁ

[6] ንጽ St. Poemen: “አኬዲያ የሰው ልጅ አንዳች ነገር ለመሥራት ሲነሳ የሚከሰት እስራት ነው” (Apophthegmata Alphabetical Series, Poemen 157).

[7] መዝ 91፡6

[8] ንጽ John Cassian, Institutes X.1.

[9] ንጽ Evagrius, Praktikos 12.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።