Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም 11ኛ ቀን

ዐቢይ ጾም 11ቀን

Lent-main-imageመድኃኒት

ቅዱስ ኢቫግርዮስ “አኬዲያ” የነፍስ ሚዛን መዛነፍ እንደሆነ ይናገራል፤ በመሆኑም መድኃኒቱ የዚህን የነፍስ ሚዛን መሳት የሚያቃና እና የነፍስን ጤናማ ውኃ ልክ እንደገና የሚያረጋግጥ መሆን እንዳለበት ያስተምራል። ለዚህም የሚረዳን የአኬዲያ መድኃኒት ጽናት ነው። ጽናት የአእምሮን እና የነፍስን ትኩረት የሚመልስ ኃይል ነው። በመሆኑም ነፍስ ይህንን ትኩረቷን ባገኘችበት ቁም ነገር ላይ ሁሉ አኬዲያ እና በእርሱ ውስጥ የሚገለጡትን ኃጢአቶች በሙሉ ለማሸነፍ አቅም ታገኛለች። በመሆኑም ባለንበት ሥፍራ መጽናትን መለማመድ፣ የአኬዲያ መንፈስ ሲመጣ ከመሸሽ ይልቅ ባለንበት ሥፍራ ሆነን የጌታን ስም እና ከእኛ ጋር የመገኘቱ ኅልውና ላይ ትኩረት በማድረግ አኬዲያን መጋፈጥ ነፍስን እና ሥጋን የበለጠ ጠንካራ ያደርጋቸዋል። በዚህም ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን እና በእሳት መካከል በማለፉ የበለጠ እንደሚጠራ እንዲሁ የአማኝ ልብ በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየጨከነ እና እየጠራ እውነተኛ የክርስቶስ ወታደር እየሆነ ያድጋል። በዚህ መሰረት አኬዲያ ነፍስ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ራሷን በእምነት በመጣሏ በምታገኘው ጽናት ይረታል። በመሆኑም ነፍስ ለፈተና ልፍስፍስ በመሆን ፈንታ ፈቃዷን መልሳ ስለምታገኝ የዲያብሎስን ሥራ ለመቃወም በጸጋ ብርቱ ትሆናለች።

ሌላኛው የአኬዲያ ፍቱን መድኃኒት በእግዚአብሔር ቃል መጸለይ ነው። ኢቫግሪቶስ በአኬዲያ መንፈስ ለሚጠቁ አማኞች የጌታን በዲያብሎስ መፈተን አያይዞ አማኞች የዲያብሎስን ፈተና፣ ክፉ ምክር እና ማስፈራርያ በእግዚአብሔር ቃል ማፍረስ እንደሚገባቸው ያሳስባል። ጌታ በበረሃ በዲያብሎስ በተፈተነ ጊዜ ዲያብሎስ ላቀረበለት ለሦስቱም ጥያቄዎች የሰጠው መልስ ከእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል። በመሆኑም የዲያብሎስን ሥራ የምናፈርስበት የእግዚአብሔር ቃል በልባችን ሊሞላ ያስፈልጋል፤ ስለዚህ አንድ አማኝ ከእግዚብሔር ቃል ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲያዳብር፣ ቃሉን በየዕለቱ እንዲያጠና እና የእመቤታችንን አብነት በመከተል የእግዚአብሔርን ቃል በልቡ ይዞ እንዲያሰላስል ያስፈልገዋል። ከዚህ ጎን ለጎን መዝሙረ ዳዊትን መጸለይ፣ መንፈሳዊ ዝማሬን በልብ መዘመር፣ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በታሪኩ ውስጥ ገብቶ ማሰላሰል፣ አእምሮ በሌላ ሐሳብ እንዳይጠመድ እና ትኩረቱን እንዳይማረክ እንደሚረዳው ኢቫግሪዮስ አበክሮ ያስገነዝባል።

ሦስተኛው አኬዲያን የምንመክትበት እና የምናሸንፍበት ኃይል “ቀስተ ጸሎት” ነው። ቀስተ ጸሎት አጭር እና በኃይል የተሞላ ጸሎት ሲሆን “ኢየሱስ” የሚለውን ስም ያለማቋረጥ መጥራት፣ የምሥራቅ አባቶች የኢየሱስ ጸሎትየሚሉትን “የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ” የሚለውን ጸሎት ከአተነፋፈሳችን ምት ጋር አዛምደን ሳናቋርጥ በልባችን መጸለይ ወ.ዘ.ተ. ቀስተ ጸሎት ይባላል። እንደዚህ አይነት አጭር ጸሎት መለማመድ እና በሥራም ይሁን በዕረፍት ጊዜ በዚህ ጸሎት ነፍስ እና ሥጋችንን በጌታ የኃይሉ ችሎት ማበርታት እና ማጠር አኬዲያን የምናሸንፍበት መለኮታዊ የጦር ዕቃ ነው።

ኢቫግሪዮስ በአራተኛ ደረጃ የተቀደሰ ዕንባ የአኬዲያ መንፈስን የምናሸንፍበት የእግዚአብሔር ምሕረት ጠል እንደሆነ ያስተምራል። በዚህም አማኝ በዕንባ በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ የእግዚአብሔርን ፊት በመሻት የነፍስን እና የሥጋን ሁሉ ትኩረት የእግዚአብሔርን ፊት በመፈለግ ላይ ያደርጋል። ኢቫግሪዮስ ስለ ቅዱስ ዕንባ ሲናገር “ኀዘን ነፍስን ይጫናታል፤ የአኬዲያ መንፈስም ለመዋጋት ቀላል ጠላት አይደለም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት በትህትና የሚፈስ ዕንባ ከሁለቱ ጠላቶች ይልቅ የበረታ ኃይል አለው” በማለት ዕንባ ነፍስን ነጻ የሚያወጣ ኃይል ያለበት የአሸናፊነት ምንጭ መሆኑን ይጠቅሳል። በዚህም አማኝ የቅዱስ ዕንባ ሥጦታ እንዲለምን እና ይህ ጸጋ ያለው አማኝ በዚህ ጸጋ ፍሬ እንዲያፈራበት ይመክራል። ይህ የኢቫግሪዮስ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ የስነ ልቡና ምሑራንም አይነተኛ መፍትሔ አድርገው ለታካሚዎቻቸው የሚነግሩት ቁም ነገር ነው። የአኬዲያ መንፈስ የነፍስን እንስፍስፍነት በማጨለም ልብን የሚያደነድን በመሆኑ ዕንባ ይህንን የምናፈርስበት ትልቁ መንፈሳዊ መሣርያ ነው። ኢቫግሪዮስ የዳዊትን መዝሙር ሲፈታ ዕንባ ነፍስን የሚያረሰርስ እና ደንዳናውን ልብ በእግዚአብሔር ፊት የሚያፈስ ትህትና በመሆኑ ዳዊት ሌሊቱን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በዕንባ ይቀርብ እንደነበር ይናገራል (መዝ 6፡6)። ከዕንባ ጎን ለጎን አማኝ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ከአቅሙ በላይ የሆኑ መንፈሳዊ ተግባራትን ከማከናወን እንዲቆጠብ እና ይልቁንም ትንንሽ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን በታላቅ እምነት እና ፍቅር እንዲያከናውን ይመከራል። አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ መደበኛ እና አጭር የጸሎት ጊዜ እና ሥፍራ ማዘጋጀት፣ የዕለት ተዕለት ኃላፊነቶችን አለማሳደር እና ራስን መታገሥ አኬዲያን የምናሸንፍባቸው ዘርፈ ብዙ የጸጋ አውታሮች ናቸው።

ኢቫግሪዮስ የዳዊትን መንፈሳዊ ልምምድ በመከተል አንድ አማኝ በመዝሙረ ዳዊት እና በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ራሱን መስበክ እንደሚችል ይጠቁማል። ለዚህም የሚጠቅሰው ክፍል የዳዊት መዝሙር ምዕራፍ 42 ላይ ያለውን ሐሳብ ነው፤ በዚህ ክፍል ዳዊት ከነፍሱ ጋር ጥልቅ በሆነ ጸሎት እየተነጋገረ ነፍሱን በእነዚህ ቃላት ይሰብካታል፡

“ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ”(መዝ 42፡6)።

አማኝ በእግዚአብሔር ቃል ራሱን እንዲህ እንዲሰብክ እና በቃሉ ሙላት እንዲጽናና ኢቫግሪዮስ የዳዊት መንፈሳዊ ልምምድ የሁላችን ይሆን ዘንድ ይጋብዘናል። በዚህ አይነት የአኬዲያ መንፈስ በሚያስጨንቀን ጊዜ የነፍሳችን እኩሌታ በእንባ እና በእግዚአብሔር ቃል ኃይል ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ጌታ የኃይሉ ችሎት ከፍ ሲል፤ ሌላኛው የነፍስ ክፍል ከመለኮታዊው ዙፋን በሚመጣው የመጽናኛ ብርኀን እየተሞላ በነፍስ ውስጥ ያረገረገውን የአኬዲያ ጨለማ በእግዚአብሔር ብርኀን ያሸንፈዋል።

ኢቫግሪዮስ በአምስተኛ ደረጃ የአኬዲያ መድኃኒት አድርጎ የሚያስቀምጠው አካላዊ ሥራ ወይም እንቅስቃሴ ነው። አእምሮአዊ ሥራ እንዳለ ሁሉ አካላዊ የጉልበት ሥራ አለ፤ በአእምሮአዊ እና በአካላዊ እንቅስቃሴ መካከል ጤናማ ተመጋጋቢ የሰመረ ግንኙነት ሊኖር ይገባል። ኢቫግሪዮስ እስካሁን የጠቀሳቸው መድኃኒቶች ማለትም ጽናት፣ የእግዚአብሔር ቃል፣ ቅዱስ ዕንባ፣ ቀስተ ጸሎት እና አካላዊ እንቅስቃሴ አኬዲያን በተለያየ መንገድ የሚያሸንፉ ቁም ነገሮች ናቸው። እያንዳንዳቸው የሚነኩት የተለየ የነፍስ ዝንባሌ አለ።  መጽሐፍ ቅዱስ ከጌታ ፈተና በመነሳት የፈተና ሁሉ ቀንበር መስበርያ ነው፤ ዕንባ የልብን መደንደን የሚሰብር እና የነፍስን ባተሌነት የሚያስቀር የምሕረት ጠል ነው፤ ቀስተ ጸሎት “ሳታቋርጡ ጸልዩ” የሚለው ሁለንተናን በጸሎት የማጠር የቅዱስ ጳውሎስ ምክር ነው፤ አካላዊ እንቅስቃሴ በአእምሮ ውስጥ የሚመላለሱትን ሐሳቦች የሚገታ እና የአካልን ኃይል በጤናማ መልኩ በሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርግ ሲሆን ጽናት ደግሞ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ለእግዚአብሔር እና ለዘላለማዊ ሕይወት አክሊል መታመንን እና ስኬትን የሚያለማምደን የክርስቶስ ወታደሮች አይነተኛ የቅብዐ ሜሮን ፍሬ ነው። በአጠቃላይ አኬዲያን ለመርታት የነፍስ እና የሥጋ ጤናማ ተገናዝቦ እና ስምረት ያስፈልጋል። በዚህም መሰረት ጾም የሥጋን ፍትወት በመግታት እና ሥጋን በመግራት፤ ጸሎት ደግሞ የነፍስን ኃይላት በማደስ እና በኃጢአት ላይ የአሸናፊነት ክንዷን እንድታነሳ የማስቻል አቅም አላቸው። እንግዲያውስ ዐቢይ ጾም እንዲህ አይነቱን ጾም-ጸሎት የምንለማመድበት የጸጋ እና የአሸናፊነት ወቅት ነው። 

ኢቫግሪዮስ ለመነኮሳን የሚያቀርብላቸው ቀላል የሕይወት ዘይቤ ለማንኛውም አማኝ መንፈሳዊ ሕይወት የሚጠቅም ነው። ይህንን ቀላል የሕይወት ዘይቤ በሚገባ ማስተዋል እና በየዕለቱ መለማመድ ያስፈልጋል። ይኸውም ሁለተኛ መሆን የሚገባውን ነገር አንደኛ አለማድረግ፤ በእያንዳንዱ ሥራ ውስጥ ለራሳችን አቅማችንን የሚመጥን፣ ተጨባጭ፣ ተግባራዊ የጊዜ ገደብ እና የሥራ ዕቅድ ማስቀመጥ፤ የዕለቱን ሥራ ለነገ አለማሳደር ነገር ግን ካልጨረስኩኝ አልለቀውም ከሚል ግትርነት መቆጠብ፣ በልብ እና በአእምሮ መጸለይ፤ ያለ ልክ ያልተራዘመ ጤናማ የዕረፍት እና የመዝናኛ ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም ተመጣጣኝ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው። በዚህ አይነት የእግዚአብሔር ጸጋ በውስጣችን ለሚያደርገው ተሃድሶ ቀና ተባባሪዎች በመሆን በነፍስ እና በሥጋ እግዚአብሔር በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባጎናጸፈን የእግዚአብሔር ልጆች ነጻነት እንመላለሳለን።

በቀደመው አስተንትኖ እንደተመለከትነው አኬዲያ ዕረፍት፣ ሰላም፣ ስኬት፣ ትርጉም እና ራዕይ ከማጣት የሚዛምድ ሲሆን በአንድ በኩል በሥራ ፈትነት መባከን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ነፍስ ያለው ማሽን ሆነን ያለ እረፍት በመስራት የሚገለጥ፣ አንድን ሰው በነፍስ እና በሥጋ የሚበዘብዝ እሥራት ነው። ቅጽበታዊ ደስታን ከመንፈሳዊ ዕድገት በላይ ተመራጭ እና አቋራጭ መንገድ አድርጎ በማቅረብ ነፍስን በአሁናዊ ደስታ ፍለጋ ብቻ የሚያጠምዳት ይህ ክፉ መንፈስ በእግዚአብሔር ቃል ንባብ፣ በቅዱስ ዕንባ፣ በጸሎት፣ በጤናማ አካላዊ እንቅስቃሴ እና በክርስትያናዊ ጽናት ይረታል። መንፈሳዊ ሕይወት ከአንድ ቤተ ክርስትያን ወደ ሌላ ቤተ ክርስትያን በመቀየር የሚስተካከል ሳይሆን ይልቁንም እንዲህ ያለውን የነፍስ ቁስል በሚገባ በመረዳት እና በዘመናት በተፈተኑ ተግባራዊ ክርስትያናዊ የጸጋ ልምምዶች በማደግ የሚፈወስ ቁም ነገር ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር ባስቀመጠን የእውነት ምልዐት ባለበት ሥፍራ በእነዚህ ክርስትያናዊ ልምምዶች በመበርታት እና የእግዚአብሔርን ፍጹም ጸጋ በመታመን መንፈሳዊ ውጊያችንን እስከመጨረሻው እንድንዋጋ እና መልካሙን ገድል እንድንጋደል ዐቢይ ጾም አይነተኛ የተሃድሶ ጊዜ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ መዝ 42

“ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ አንተን ትናፍቃለች። ነፍሴ እግዚአብሔርን፥ ሕያው አምላክን ተጠማች፥ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ? ዘወትር፦ አምላክህ ወዴት ነው? ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ሆነኝ። ይህን ሳስብ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ፈሰሰች፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና፥ በዓል የሚያከብሩ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ። ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፥ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ አስታውስሃለሁ። በፏፏቴህ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራታለች፥ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ። ጌታ በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል፥ የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው። እግዚአብሔርን፦ አንተ መጠጊያዬ ነህ፥ ለምን ረሳኸኝ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? እለዋለሁ። ጠላቶቼ ሁልጊዜ፦ አምላክህ ወዴት ነው? ባሉኝ ጊዜ አጥንቶቼን እየቀለጣጠሙ ሰደቡኝ። ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ”

ጸሎት

ጌታ እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፥ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል፤  ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፥ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል። በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ፤ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬንም እስከ አፉ ሞላህ። ቸርነትና ምሕረት በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘለዓለም እኖራለሁ።

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለኝ ግንኙነት ምን ይመስላል? በዚህ በዐቢይ ጾም ጉዞዬ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ባጠና የትኛውን መጽሐፍ እመርጣለሁ?
  2. የጸሎት ሕይወቴ ምን ይመስላል? በቤቴ ውስጥ እኔ እና ጌታ የምንገናኝበት የተለየ ስፍራ አለ? ለጸሎት የለየሁት የተቀደሰ ሰዓት ይኖር ይሆን?
  3. በቂ እንቅልፍ፣ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ፣ በቂ እና ጤናማ የመዝናኛ ጊዜ አለኝ?
  4. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ

ሴሞ

ተጨማሪ ንባብ እና ማጣቀሻ ለሚሹ

  • Cassian, John. 1997. The Conferences. Translated and Annotated by Bonifice Ramsey. New York: Paulist Press.
  • Evagrius, Ponticus. 1972. The Praktikos & Chapters on Prayer. Translated by John Eudes Bamberger. Collegeville: Cistercian Publications.
  • Evagrius, Ponticus. 2003. Eight Thoughts. In Evagrius of Pontus: The Greek Ascetic Corpus. Translated by Robert E. Sinkewicz. Oxford: Oxford University Press.         

 

 

 

 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።