Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም 12ኛ ቀን

ዐቢይ ጾም 12ኛ ቀን

Lent-main-imageማንን ይመስላል?

የሰው ልጅ በባሕርይው የሚመስለውን ነገር ይፈልጋል፤ በመሆኑም አዲስ ሕጻን ሲወለድ ሰዎች ሕጻኑ ይበልጥ እናቱን ወይም አባቱን ይመስል እንደሆነ ለማየት ይጓጓሉ። “እናቱን ቁርጥ!”፣ “አባትየው ራሱን ደገመ!” ወይም ደግሞ ዐይኖቹ የእናቱን፣ አፍንጫው የአባቱን ወዘተ እየተባለ ሕጻኑ በሁለንተናው መልኩ ማንን እንደሚመስል ይተነተናል። ከወላጆቹ ባሻገር የቤተ ሰቡ አባላት ሁሉ በልጁ ላይ ራሳቸውን የሚመስል ነገር እየፈለጉ ገና ጨቅላውን ልጅ የእጅ ጣቶቹ የአያቱን ይመስላል፤ ደም ግባቱ ወደ እኛ ቤት ነው ይላሉ፤ ወይም ደግሞ አለፍ ሲል “አይይ አፍንጫ የለውም! ወደዚያኛው ቤት ነው የእኛ ቤት አይደለም” ወዘተ በማለት ሕጻኑን ወደ ራሳቸው መልክ እና ምናባዊ ማንነት ይወስዱታል። ይህ የተለመደ የሰው ልጅ መስተጋብር ምናልባት ጥቂት ቆም ብለን ካሰብነው በውስጣችን አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ይጭራል። ይህ እርሱን ከሚመስለው የሰው ልጅ ላይ የራሱን ሽራፊ መልክ የሚፈልገው የሰው ልጅ ራሱ በማንነቱ ማንን ይመስላል? “Ubi imago Dei?”[1]

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረ ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ካለው ዓላማ የተነሳ የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ይመስላል ማለታችን ስሕተት አይሆንም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በሆነበት ምሥጢር ውስጥ ስለ ማንነቱ ሲመሰክር “እርሱም ለማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው” (1ተሰ 1፡15) በማለት እግዚአብሔር በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆን ምሥጢር ውስጥ ራሱን ገልጦ እንደታየን፤ በቋንቋችን እንዳነጋገረን ይመሰክራል። በመሆኑም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረበትን እውነተኛ መልኩን መመልከት እና መረዳት የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የመልበስ ምሥጢር በኩል ነው። ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተፈጠረበት መልክ ምን ያህል የከበረ የእግዚአብሔር ፍጹም ምሳሌ እንደሆነ ይመለከታል። የሰው ልጅ እውነተኛ መልኩን የሚመለከተው ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በሆነው፣ የእግዚአብሔር “የክብሩ ጸዳል የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ” (ዕብ 1፡3) በተገለጠው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው።

የእግዚአብሔር ማደርያ የሆነው የሰው ልጅ ልክ የብሉይ ኪዳኑ ታቦት በሰማያት ባለው ታቦት መልክ እንደተቀረጸ (ዘጸ 25:9፣ 40፣ 25:30፣ 27:8) እንዲሁ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ከብሮ ባለው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልጅ የመሆን መልክ አርአያ እና አምሳል ተፈጥሯል። የእግዚአብሔር ቅዱስ ታቦት በሰማይና በምድር ለመለኮታዊ ክብር አገልግሎት እንደተሰራ እንዲሁ የሰው ልጅም በኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ልጅነት በኩል በሰማይ እና በምድር ስፍራ ያለው እግዚአብሔርንም በማምለክ እውነተኛ መልኩን በምሥጋናው ክብር የሚገልጥ ፍጥረት ሆኗል። ይህ የሰው ልጅ የተፈጠረበት መልክ ከዘላለም ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ቃል[2] እና ፍጥረት ሁሉ ተገጣጥሞ የተዋቀረበት የዘላለማዊ ብርሃን ነጸብራቅ፤ የእግዚአብሔር ሥራ መስተዋት፤ የደግነቱም ምስል[3] እየተባለ የተጠራው “ጥበብ”  ነው።  

የሊዮኑ ቅዱስ ኤሬኒዮስ ይህንን ምሥጢር በሚመለከት ሲናገር “የሰውን ልጅ በእግዚአብሔር መልክ አበጀው፤ የእግዚአብሔርም መልክ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ስለዚህ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯል። በመሆኑም በዘመን ፍጻሜ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ እንደራሱ የሆነውን እውነተኛውን መልክ ያሳየው ዘንድ በመካከላችን ተገለጠ”[4] በማለት የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ልጅነት መልክ የእግዚአብሔር አምሳል ነጸብራቅ ሆኖ መፈጠሩን ያስገነዝባል። ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመን ፍጻሜ የተገለጠው ምን እንደምንመስል ለእያንዳንዳችን ጥያቄያችንን ሊመልስ እና እውነተኛውን መልካችንን አሳይቶን ወደ ተፈጠርንበት መልክ ክብር ያስገባን ዘንድ ነው።

ሌላው የቤተ ክርስትያን ሊቅ ጤርጡሊያን በበኩሉ የአዳምን ከመሬት አፈር መፈጠር ሲያስረዳ “Quodcumque enim limus exprimebatur, Christus cogitabatur”እግዚአብሔር በምድር ላይ የቀረጸው የሰው ልጅ መልክ በቃልነት ለዘላለም ከእርሱ ጋር ያለው የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ሐሳብ ነው[5] በማለት ይህንን የሰውን ልጅ ድንቅ ተፈጥሮ ምሥጢር ውብ አድርጎ ይገልጸዋል። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በራሱ አርአያ እና አምሳል ፈጠረው ስንል ፍጹም ሰው ሆኖ በተገለጠው በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ የልጅነት መልክ የሰውን ልጅ አበጀው ማለታችን ነው።

የሰው ልጅ እግዚአብሔርን የሚመስለው በፍጥረቱ ማንነት ሳይሆን ይልቁንም በኢየሱስ ክርስቶስ ልጅነት በኩል በተካፈለው መልክ እና አምላክ ሰው በመሆኑ ምሥጢር በኩል ነው።[6] ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ እንደሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ የባሕርይ ልጁ ነው፤ መልኩም ከአባቱ ጋር ፍጹም ነው፤ የሰው ልጅ ደግሞ ክርስቶስን በመምሰል የእግዚአብሔር መልክ ሱታፌ አለው”።[7] በዚህ አይነት በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት በኩል በእውነትም የእግዚአብሔር ልጆች (ገላ 4:5፣ ሮሜ 5:15፣ 8:17–29፣ ኤፌ 1:3፣ ዮሐ 1:12; 1 ዮሐ 3:1)፣ የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ የጌታ ኢየሱስ ወንድሞች እና እኅቶች፣ ከእንግዲህ ወዲህ ባርያ ሳይሆን ስለ አባቱ ማወቅ የሚገባንን ያህል የተነገረን የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጓደኞች ተብለን የምንጠራ ምሥክሮች (ዮሐ 15፡15) እና የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደሶች እንሆናለን። በመሆኑም ለሰው ልጆች እግዚአብሔርን የሚመስሉበት መልክ በእምነት አማካኝነት ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሚካፈሉት የጸጋ ልጅነት በኩል ነው።

የሰው ልጅ እውነተኛ መልኩን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመስልበት ዐቢይ ቁም ነገር ትህትና ነው። ትህትና ኢየሱስ በእኛ መልክ እኛን ሆኖ የተገለጠበት፣ እግዚአብሔር ወደ እያንዳንዳችን ፊቱን የመለሰበት፣ የእኛን ቋንቋ የተናገረበት እና ከኃጢአት በስተቀር በሁለንተናው እንደ እኛ ሰው የሆነበት ፍቅር ነው። እርሱ በእኛ መካከል ሰው ሆኖ ስላደረ እና በአባቱ ፊት ስለ እኛ በፍጹም ሰውነቱ ምሥጢር መካከለኛ ስለሆነ እኛም ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት በተፈጠርንበት ዓላማ ስልገለጥ የበለጠ እውነተኛውን መልካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል እናድጋለን። ትህትና በተፈጠርንበት ማንነት በእግዚአብሔር ፊት መገኘት ነው። አንድ ዛፍ ዛፍ መሆኑ፣ አሳ በባሕር ውስጥ መዋኙቱ፣ አእዋፍ በሰማያት በተዘረጋላቸው ስፍራ ከፍ ብለው መብረራቸው ትህትና ነው፤ ትህትና በእግዚአብሔር ፊት እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ በሚያውቀን እውቀት መገለጥ ነው። ቅዱሳን ከሌሎቻችን የሚለዩበት ኃይል ትህትና ነው። በሌላ አነጋገር ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት እግዚአብሔር በሚያወቃቸው ማንነት እንጂ በሌላ ሰው ሠራሽ ማንነት ተመሳስለው የሚቆሙ አይደሉም ማለት ነው።

ዐቢይ ጾም  እንዲህ ያለውን በእግዚአብሔር ፊት በተፈጠርንበት ማንነት መቅረብ የምንለማመድበት የጸጋ ወቅት ነው። ልብን እና ኩላሊትን በሚመረምረው አምላክ ፊት በራሳችን ማንነት እና መልክ ቀርበን “ጌታዬ እና አምላኬ” (ዮሐ 20፡28) የምንልበት የንሥሐ ዘመን ነው። ዐቢይ ጾም ማንን ትመስላለህ? ስንባል ከጸጋ ሥጦታው ክብር፣ ከልግሥናውም በጎነት በሆነ ሥጦታ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን የምንልበት፣ በእግዚአብሔር ምሕረት እና ፍቅር ልጅ የሆንበት ምሥጢር የሚከብርበት የተሃድሶ ዘመን ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ሮም 8፡17-30

“ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ከእርሱ ጋር የክብሩ ተካፋዮች እንድንሆን ከእርሱ ጋር መከራ ብንቀበል የእግዚአብሔር ወራሾችና ከክርስቶስም ጋር አብረን ወራሾች ነን። የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ወደ ፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም ዋጋ እንደሌለው እቆጥረዋለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃልና። ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ ይኸውም በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእርሱ ፈቃድ ነው። ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው የከበረውን ነፃነት እንዲያገኝ ነው። እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ አብሮ በመቃተትና በምጥ ሥቃይ እንደሚኖር እናውቃለንና። ፍጥረት ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን እኛ ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት በናፍቆት እየተጠባበቅን እኛ ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋው የሚታይ ከሆነ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፥ በትዕግሥት እንጠባበቃለን።

እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ይረዳናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ያማልድልናል፤ ልቦችንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስ ሐሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፥ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ያማልዳልና።

እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ዓላማውም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። 29አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፥ ይህም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው፤ 30አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህንም ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውን እነዚህንም ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን እነዚህንም ደግሞ አከበራቸው”።

ጸሎት

አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፥ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ጉዞዬንና መኝታዬን አንተ መረመርህ፥ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥ የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ። ከኋላና ከፊት ጠበቅኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እውቀትህ እጅጉን ያስደንቃል፥ ከከፍታውም ብዛት ልደርስበት አልችልም።

ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ቢሆን፥ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፥ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። 

አቤቱ፥ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፥ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዐይኖችህ አዩ፥ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። አቤቱ፥ ሐሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቁጥራቸውም እንደምን በዛ! ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፥ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ። አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፥ ፈትነኝ መንገዴንም እወቅ፥ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፥ የዘለዓለምንም መንገድ ምራኝ። አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. ማንን እመስላለሁ? በእግዚአብሔር ፊት የምደብቀው ማንነት ይኖረኝ ይሆን?
  2. የትኛው ማንነቴ ያሳፍረኛል? ጌታ እንዳይደርስበት የዘጋሁት የልቤ እና የሕይወቴ በር ይኖር ይሆን?
  3. እኔን በማይመስል ግንኙት የተጠመድኩበት ሕይወት ይኖር ይሆን?
  4. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ ጾም ጉዞ!

ሴሞ

[1] ንጽ Augustine, De Trin. XII, 7, 12.

[2] ንጽ ዮሐ 1፡1

[3] ንጽ ጥበብ 7፡26

[4] ንጽ Irenaeus, Demostratio, no. 22.

[5] ንጽ Tertullian, De Res., 6:3–4.

[6] ንጽ Tertullian, Adv. Praxeam, 12, 4.

[7] ንጽ John Damascene, De imaginibus, or. 3, 8. እንዲሁም J. J. Meany, The Image of God in Man According to the

Doctrine of Saint John Damascene (Manila: San Jose Seminary, 1954).

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።