Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዐቢይ ጾም 13ኛ ቀን

 የዐቢይ ጾም 13ኛ ቀን

Lent-main-image“እንግዲህ ልጁ ነፃ ቢያወጣችሁ በእውነት ነፃ ትወጣላችሁ” (ዮሐ 8፡36)

የሰው ልጅ በነጻነት ለነጻነት ተፈጥሯል፤ በፍጥረቱ አስኳል ነጻ ፈቃድ አለው፤ በዚህም የራሱን ምርጫ ለማድረግ እና ለመወሰን የሚያስችል ነፍሳዊ አቅም ተሰጥቶታል።[1] ነጻነት (ἐλευθερία) ከመለኮታዊ ባሕሪ ገንዘቦች አንዱ ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በአርአያው እና በአምሳሉ ስለፈጠረው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ከዚህ መለኮታዊ ገንዘብ አካፍሎታል።[2] የሰውን ልጅ ነጻነት በሚመለከት የኑሲሱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የሚከተለውን ያትታል፡

“የሰው ሕይወት በአንዳች አስገዳጅ ኃይል የሚከወን ነገር ቢሆን ኖሮ፤ ነጻነት የጎደለው ፍጹም ነጻ የሆነውን አምላክ መልክ ተካፍሏል ማለት ስለማይቻል የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ መባሉ ሐሰት በሆነ ነበር። በቀንበር የተያዘውን እና በአንዳች ነገር ግዴታ ሥር የሚኖረውን የሰው ልጅ ሉዓላዊ ባሕርይ ባለው አምልክ አምሳል ተፈጠረ ማለት እንደምን ይቻላል? ነገር ግን በሁለንተናው በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ በባሕርዩ ፍጹም ነጻ እና ራስ ገዝ የሆነ ፈቃድ ሊኖረው ግድ ነው”።[3]

እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ነጻ ፈቃድ ሰው በእግዚአብሔር ፍጽምና ውስጥ እንዲሳተፍ የሚያስችለው የእግዚአብሔር ፍቅር ምልክት ነው።[4] ራስ ገዝ መሆን እና ሉዓላዊነት የእግዚአብሔር ባሕርያት ሆነው ሳሉ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል በመፈጠሩ ጸጋ እነዚህን ባሕርያት ገንዘቡ አድርጓል።[5] የኑሲሱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የሰውን ልጅ ፍጥረት ክብር ሲያስረዳ ሰው በነጻነቱ ፍጹም እግዚአብሔርን  ይመስለዋል (ἴσόθεος)[6] ይላል። በመሆኑም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ከተፈጠረባቸው ቁም ነገሮች መካከል ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ቁም ነገር ነጻነት ነው። ሰው የበለጠ እግዚአብሔርን የሚመስለው በነጻነቱ ነው። የሰው ልጅ በነጻ ፈቃዱ ምርጫ (προαίρεσις) በማንም ባርነት ቀንበር ሳይጠመድ ነፍሱ በቀጥታ ከእግዚአብሔር በተጎናጸፈችው ዕውቀት እና ፍቃድ ይኖር ዘንድ በነጻነት ለነጻነት ተፈጥሯል።

እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያጎናጸፈው ፍጹም ነጻነት ለፍጥረቱ ቅድስና እና ለባሕርይው ክብር የሚመጥነውን ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ሕብረት በመጠበቅ የበለጠ የእግዚአብሔርን አርአያ እየመሰለ ወደ ፍጽምናው ያድግ ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃዱ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያጎናጸፈጸፈው ነጻነት መልካም እና ውብ የሆነውን ነገር በነፍስ ነጻ ፈቃድ ዕውቀት ኃይል ገንዘቡ እያደረገ፣ በራሱ ነጻ ፈቃድ መልካም የሆነውን መልካም ካልሆነው እየለየ እና መልካሙን እየመረጠ የመልካም ነገርን ዋጋ እና ውበት እያስተዋለ በእርሱም ደግሞ ደስተኛ ሆኖ ይኖር ዘንድ ነው።[7] በዚህ አይነት ከነጻ ፈቃዱ በሚነሳ የነፍሱ ዕውቀት የሚያደርገው ምርጫ ለምስጋናም ይሁን ለኩነኔ ተጠያቂ ያደርገዋል። 

የሰው ልጅ ነጻነቱን በተነፈገበት በየትኛውም ሁኔታ እግዚአሔርን የሚመስልበት መሰረታዊ እና ዋነኛ ቁም ነገር አደጋ ላይ ነው። የሰው ልጅ ነጻነት ከሌለው በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ተፈጠረ ማለት አንችልም። የሰው ልጅ ለጽድቅም ይሁን ለኩነኔ በእግዚአብሔር ፊት መልስ ይሰጥበት ዘንድ የሚጠየቀው ስለተጎናጸፈው ነጻነት መለኮታዊ ክብር ዋጋ ነው። በመሆኑም የእግዚአብሔርን ጸጋ እንኳን ለመቀበል የሰው ልጅ በነጻ ፈቃዱ መወሰን እና ለጸጋ ራሱን ክፍት ለማድረግ ያለ ማንም አስገዳጅነት በገዛ ራሱ ፈቃድ እና ዕውቀት ከእግዚአብሔር ጋር ለመተባበር ነጻ ነው። ጌታም በወንጌል ውስጥ የሚያገኛቸውን ሰዎች ነጻነት በማክበር “ልትድን ትወዳለህን?” (ዮሐ 5፡6፣) እያለ ይጠይቃል እንጂ ማንንም ሰው እጁን ጠምዝዞ አያድነውም።  የደማስቆው ቅዱስ ዮሐንስ አስገዳጅ ነገር በተቀመጠበት ሁኔታ ውስጥ ከነጻ ፍቃድ የሚወለድ መልካም ነገር ሊያብብ እንደማይችል በጽሑፉ ያስገነዝባል።[8] በመሆኑም ነጻነት የሰው ልጅ ሊያገኘው ወይም ሊያጣው የሚችለው ውጫዊ ነገር ሳይሆን ሰው ሆኖ የመፈጠሩ ለዛ እና የማንነቱ ጥለት ነው። ሰው “ሰው” የሚሆነው በነጻነት ለነጻነት በሆነበት ሥፍራ ብቻ ነው። ለሰው ልጅ ነጻነት ማንነቱ እና የፍጥረቱ ባሕርያዊ መገለጫ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚዛመድበት ባሕርይው ነው። በዚህም ማንነቱ የተነሳ በግለሰባዊ ፈቃዱ (θέλημα  γνωμικόν) እና በባሕርያዊ ፍቃዱ (θέλημα φύσικόν) መካከል በሰፈነው ጤናማ ተገናዝቦ ወደ መልካም ነገር ይሳባል፤ በመሆኑም የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ እና የነጻነት ባሕርይው ፍጻሜ ወደሆነው አምላክ ወደ እግዚአብሔር የሚናፍቅ ነፍሳዊ ማንነት አለው።

ነጻነት የሰው ልጅ ነፍስ መልካም እና ፍጹም ወደሆነው ነገር ሁሉ የምትሳብበት፣ በነገሮች ሁሉ ውስጥ የእግዚአብሔርን ፍጽምና ለማየት ከሚታየው ግዙፉ ዓለም ባሻገር ያለውን እውነታ ለመመልከት የምትዘረጋበት፣ ወደ ተፈጠረችበት ማዕከላዊ ቁም ነገር የምትመለስበት ኃይል ነው። በዚህ አይነት በእግዚአብሔር ወልድ የተገለጠው ፍጹም ሰውነት በእያንዳንዳችን ደግሞ ይረጋገጥ ዘንድ የነፍሳችንን ኃይሎች አቅጣጫ እና ትኩረት ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ወደ እግዚአብሔር አብ ከፍ በማድረግ በልጁ መልክ እየተሰራን እናድጋለን። ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ይህንን እድገት እና መለኮታዊ ናፍቆት ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “እንግዲህ ልጁ ነፃ ቢያወጣችሁ በእውነት ነፃ ትወጣላችሁ” (ዮሐ 8፡36)።

የሰው ልጅ እውነተኛ ተፈጥሮ በባሕርይው መልካምነት የሚገለጥ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ነው፤ በባሕርይው መልካምነት እና በነጻ ፈቃዱ ዕውቀት የሚያደርገው ቀጣይነት ያለው እውነተኛ፣ መልካም እና ውብ የሆነውን ነገር የመምረጥ ችሎታው የበለጠ የተፈጠረበትን መልክ እየመሰለ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በአብ ፊት እንደ ልጅ የሚሆንበት አርነት ነው። የሰው ልጅ መልካም የሆነውን፣ እውነት የሆነውን እና ውብ የሆነውን ነገር በሚመርጥበት ጊዜ ሁሉ ይበልጥ ራሱን ይሆናል፤ ይበልጥ እውነተኛ፣ መልካም እና ውብ የሆነውን በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ያለውን የፍጥረቱን ዋና ቅጂ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መልክ እየመሰለ ያድጋል። በዚህም አንዳች ውጫዊ ነገር ባርያ አድርጎ ሳይገዛው፣ በነጻ ፈቃዱ ላይ ሳይጣበቅበት በፍጹም ነጻነት እና ሉዓላዊነት፣ እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ ባሰበው እና በወደደው ሰው የመሆን መልኩ በነጻነቱ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት እያደረገ ይኖር ዘንድ ማንም ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ የሰውን ልጅ በነጻነት ሉዓላዊ ለሆነ ነጻነት ፈጥሮታል። ይህም የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እንደሚመሰክረው “ፍጥረት ራሱ ከጥፋት ባርነት አርነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት እንዲደርስ ነው” (ሮሜ 8፡21)። በዚህም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ፣ በጸጋ ሕይወት እና ለባሕርይው በሚስማማ ነጻነት ተሸልሟል።

እንግዲህ የሰው ልጅ ይህንን የነጻነቱን ሉዓላዊ ክብር ጠብቆ በኢየሱስ ክርስቶስ መልክ በአብ ፊት እንዲጸና በመንፈስ ቅዱስ ምክር የሚታረቅበት ይህ የጸጋ ወቅት ዐቢይ ጾም ይባላል። በዚህ ወቅት የጌታውን ምክር እና ትዕዛዝ በመስማት ይበልጥ በጸጋ ያድጋል፤ የእግዚአብሔር ትዕዛዛት የነጻነት ትእዛዛት ናቸው፤ እነዚህ ትእዛዛት ለነጻ ሰው የተሰጡ በመሆናቸው የሚተገብራቸው ሰው ይበለጠ ነጻነቱን እየተጎናጸፈ ይመጣል። እነዚህ የእግዚአብሔር ትእዛዛት እውነትን ወደማወቅ የሚያደርሱ የመንፈስ ቅዱስ ምክሮች ናቸው። ጌታም ይህንን እያረጋገጠ እንዲህ ይላል “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል፤” (ዮሐ 8፡31)።

ዐቢይ ጾም እንዲህ ያለውን ነጻ የሚያወጣ እውነት የምንማርበት የጸጋ ትምህርት ቤት ነው። ነጻነታችን ለእግዚአብሔር ልጆች ክብር በማይመጥን ሁኔታ ባርያ ተደርጎ የተያዘበት ነገር ቢኖር ከጌታ ጋር ወደ እውነት የሚያደርሰውን ጉዞ የምንጀምርበት፣ የሕይወታችንን ዙርያ ገባ የምናስተውልበት እና ነጻነታችንን መልሰን ሉዓላዊ የምናደርግበት፣ የልባችንን ድንግልና መልሰን የምንቀዳጅበት ዘመን ነው። ዐቢይ ጾም በእግዚአብሔር ነጻነት የመፈጠራችንን ክብር የምናከብርበት፣ የራሳችንንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ነጻነት የምንንከባከብበት፣ ሰዎች እግዚአብሔር በሰጣቸው ነጻነት ሕይወታቸውን ይኖሩ ዘንድ የምንፈቅድበትን ነጻነት የምንለማመድበት ወቅት ነው። በዚህ በዐቢይ ጾም ወቅት የነጻነታችንን ለዛ በመንፈስ ቅዱስ መዓዛ እንድናድስ፣ በልዩ ልዩ ነገሮች ከታሰርንበት እንድንፈታ፣ በእኛ መፈታት ጸጋ ደግሞ የታሰሩትን ሁሉ እንድንፈታ ጌታ ኢየሱስ የነጻነት ሐዋርያ አድርጎ ሾሞናል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ዮሐ 8፡31፣ ገላ 5፡1)

“እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል... በነጻነት እንድንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በባርነት ቀንበር እንደገና አትያዙ።”

 ጸሎት

የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ ጌታ ቀብቶኛል፥ ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፥ ለተማረኩትም ነጻነትን፥ ለታሰሩትም መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት እንዳውጅ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ እንዳጽናና፥ ጌታ ለክብሩ የተከላቸው ጽድቃዊ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች በአመድ ፋንታ አክሊልን እንዳደርግላቸው፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘን መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እንድሰጣቸው ልኮኛል። ከጥንትም ጀምሮ ባድማ የነበሩትን ይሠራሉ፥ ከቀድሞ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ይሠራሉ። መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፥ ባዕዳንም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። እናንተ ግን የጌታ ካህናት ትባላላችሁ፤ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በሀብታቸውም ትከብራላችሁ። በኀፍረታችሁ ፈንታ ሁለት እጥፍ ይሆንላችኋል፤ በውርደታችሁም ፋንታ ዕድል ፋንታችሁ ደስ ይለዋል፤ ስለዚህ የምድራቸውን ሁለት እጥፍ ይገዛሉ፥ የዘለዓለምም ደስታ ይሆንላቸዋል።

 የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. ነጻነቴን እንዴት እመለከተዋለሁ? ነጻነት ማለት ለእኔ ምን ማለት ነው?
  2. ነጻ በማያደርጉኝ ነገሮች፣ ግንኙነቶች፣ ልምምዶች ተይዤ ይሆን?
  3. ከተፈጠርኩበት ነጻነት በታች የተገለጥኩበት የሕይወቴ ክፍል የትኛው ነው?
  4. ነጻ እንደሆንኩ የሚሰማኝ፣ ዕረፍት፣ ሰላም፣ ደስታ ያለኝ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ስሆን ነው? ስሜቱ ምን ያህል አብሮኝ ይቆያል?
  5. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ!

ሴሞ

[1] Gregorry of Nyssa, On the Making of Man XVI (PG 44.184B)

[2] Cyril of Alexandria, Glaphyra on Genesis, (PG 69.24C)

[3] Gregorry of Nyssa, Catechetical Orations 5.

[4] Maximus the Confessor, Dispute with Pyrrhus (PG 91.304C.)

[5] Gregorry of Nyssa, Discourse on Death (PG 46.524A.)

[6] ዝኒ ከማሁ

[7] ንጽ Irenaeus, Against Heresies, IV.37.6

[8] John Damascene, An Exact Exposition oft he Orthodox Faith II.12.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።