ዐቢይ ጾም 14ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Sunday, 09 March 2025 08:49
- Written by Samson
- Hits: 69
- 09 Mar
ዐቢይ ጾም 14ኛ ቀን
ቁጣ ከነፍስ እና ከፈቃድ ማዕከላዊ ሥፍራ የሚነሳ ኃይል ነው። ይህ ኃይል በመሠረቱ የኃጢአትን ፈተና የምናሸንፍበት እና ክፉን የምንቃወምበት ጤናማ የነፍስ ኃይል ነው። የሰው ልጅ ኃይለኛነት በጤናማ ባሕርይው (በቅድመ ውድቀት የነበረው አዳም እና በክርስቶስ የታደሰው አዲሱ ሰው) ከእግዚአብሔር ጋር ሊለያዩት የሚፈልጉትን ነገሮች የሚቃወምበት የአሸናፊነት ክንድ ነው። በዚህም ባሕርያዊ ኃይለኝነቱ የሰው ልጅ በኃጢአት ላይ እየጨከነ እና ቁርጥ ፈቃድ እያደረገ በበለጠ ቅድስና ይመላለስ ዘንድ ይቻለዋል። ጤናማ ኃይለኝነት ዮሴፍ በግብጽ ሀገር ዝሙትን የረታበት፣ ዳንኤል በናቡከደነጾር ፊት እግዚአብሔርን ያመለከበት፣ ኢየሱስ በጲላጦስ የፍርድ ወንበር ፊት ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ በሁሉ ፊት ገዢ በሆነ ጽሞና የጸናበት ሐሞት ነው። ይህ ባሕርያዊ ኃይለኝነት የሰው ልጅ በኃጢአት ፊት የሚ‘መርበት እና ለክርስቶስ ወታደርነት ደም እስከማፍሰስ ድረስ የሚጋደልበት ቁርጠኝነት ነው።[1] በቅዳሴ ማርያም ይህ ጤናማ ኃይለኝነት ቅድስት ስላሴ የሰው ልጅ የሚያስችልበት ዐቅም ሆኖ “አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ያስጨክናሉ” እየተባለ ይጸለያል።
አዳም እና ሔዋን በዔደን ገነት ከእባቡ ጋር በነበራቸው መስተጋብር እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትዕዛዝ ለመጠበቅ ይህንን ኃይል መጠቀም ይችሉ ነበር፤ በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር ፈጥሮ ባስቀመጣቸው ማንነት እውነተኛ መልክ ጸንተው መቆም እና ከእግዚአብሔር ጋር መወገን ይቻላቸው ዘንድ ኃይል ነበራቸው። በዚህም እግዚአብሔር ለአዳም እና ለሔዋን ክፉውን ነገር ሁሉ የሚቃወሙበት ኃይል አስታጥቋቸው ስለነበር በኃጢአት ላለመውደቅ ሙሉ ሥልጣን እና ነጻነት ነበራቸው። እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ተፈጥሮ ውስጥ ለኃጢአት እምቢ የምንልበትን እና ለጽድቅ የምንጨንበትን ጤናማ ኃይል አኑሯል። ዐቢይ ጾም የዚህን ጤናማ ኃይል እውነተኛ እና ትክክለኛ ውኃ ልክ በነፍሳችን መካከል ደግመን የምናስተካክልበት እና በኃጢአት ፊት ዳግም በኃይል የምንገለጥበትን ውስጣዊ ተሃድሶ የምናረጋግጥበት የመሰራት፣ የመለወጥ እና መጠንን እንደገና የማግኘት ጉዞ ነው።
እግዚአብሔር የጠላትን ፍላጻ እንደምንመክትበት ጋሻ እና ክፋትን እንደምናፈርስበት ቀስት በነፍሳችን ላይ ያስቀመጠውን ጤናማ ኃይለኛነት መልሰን ገንዘባችን በማድረግ መጽሐፍ እንደሚል የላሉትን እጆች ለማበርታት፣ የሰለሉትንም ጉልበቶች ለማቅናት፣ ያነከሰውን ማንነት ለመፈወስ፣ የተናጋውን የሕይወት ክፍል በመንፈስ ቅዱስ ሰላም ለማረጋጋት፣ መንገዳችንን በቅን ጎዳና ለማድረግ፣ ለመቀደስ፣ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመሆን፣ ጌታን ለማየት፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ለመሞላት፣ የኃጢአትን መራር ሥር ነቅለን ለመጣል እና ከፍትወት ቁስሎች ሁሉ በጸጋ ዘይት ለመፈውስ (ዕብ 12፡12-16) ዐቢይ ጾም አይነተኛ የጸጋ ዘመን፣ የፈውስ እና የመጽናናት ወራት ነው።
በአዳም ኃጢአት ምክኒያት በድቀተ ባሕርይ የቆሰለው የሰው ልጅ ይህንን ኃጢአትን እና ክፉ ነገርን ይቃመምበት ዘንድ ከፈጣሪ የተሰጠውን ኃይል በባልንጀራው ላይ ሲጠቀመው፤ መልካም እና ለባሕርይው ተስማሚ የነበረው ኃይል አሁን ኃጢአት ይሆንበታል። በዚህ መሰረት ይህ የቁጣ ኃይል ላልተፈጠረበት ዓላማ ከባሕርይው ውጪ ውሎ የባሕርይ ሙስና ይደርስበታል። ይህ ጤናማ ኃይል ከተፈጠረበት ዓላማ በተቃራኒው ጥቅም ላይ ስለዋለ አሁን በነፍስ ውስጥ ያለ የምንታገለው ሕማም እና ቁስል ሆኗል። በሁሉ ነገሩ እግዚአብሔርን ለመፈለግ እና እርሱን ብቻ በማምለክ ሕያው ለመሆን የተፈጠረው የሰው ልጅ ከዚህ ከተፈጠረበት ዓላማ የሚያሰናክሉትን ነገሮች ይዋጋበት እና ይረታበት ዘንድ እግዚአብሔር ያስታጠቀው ኃይል አሁን በኃጢአት ቁስል ምክኒያት ወደ እግዚአብሔር እና ወደሚመኘው ዕረፍት ያልደረሰው የሰው ልጅ በባልንጀራው ላይ በመቆጣት እና በመምረር ውስጣዊ ጎዶሎነቱን እና የነፍሱን የድረሱልኝ ጩኸት በቁጣው በኩል ይገልጣል። ነገር ግን ስለራሱ ነፍስ ቁስል ዋይታ በባልንጀራው ላይ የሚገለጥ ቁጣ በምንም መልኩ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም።[2]
በኃጢአት ላይ መቆጣት እና ኃጢአትን መጥላት አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የከበረውን የሰው ልጅ የቁጣ ተደራሽ አድርጎ መመልከት ከባድ ኃጢአት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ትኩረታችን ምን ላይ መሆን እንደሚገባው ሲያስተምር “መጋደላችን ከደም እና ከሥጋ ጋር አይደለምና፤ ከአለቆች እና ከሥልጣናት ጋር፤ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዢዎች ጋር፣ በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” (ኤፌ 6፡12) እያለ ቁጣችን በማን ላይ ሊሆን እንደሚገባው፣ ተጋድሏችን ከማን ጋር መሆን እንዳለበት በግልጽ ያመለክተናል። በመሆኑም ሰው ከኃጢአት ጋር እንጂ ከኃጢአተኛው ጋር መዋጋት አይገባውም፤ በኃጢአቱ እና በኃጢአተኛው መካከል መሰረታዊ እና የማያዳግም ልዩነት እናደርግ ዘንድ ኃጢአተኛው ከኃጢአቱ ጉስቁልና በላይ በሚከብር በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠረ ነው። ስለዚህ ከእርሱ ጋር መዋጋት ከተፈጠረበት አርአያ እና አምሳል፣ መልኩን ወደዶ እና ፈቅዶ ከተካፈለው ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር መዋጋት ነው።
ቅዱስ አቡነ ቡሩክ (Benedict of Norcia) በኃጢአት እና በኃጢአተኛው መካከል መደረግ የሚገባውን መሰረታዊ ልዩነት እና ጥንቃቄ ሲያስረዱ “የጽዋውን ዝገት ለማስለቀቅ የምታደርገው ጥረት ጽዋውን ራሱን እንዳይሰብርብህ ተጠንቅቅ” በማለት የጽዋውን ውድነት ዘወትር በዐይኖቻቸን ፊት ማኖር እንደሚገባን ያስተምራሉ። ዐቢይ ጾም እንዲህ ያለውን ቅን ፍርድ እና ጥንቃቄ የተሞላበት የምሕረት ተግባር የምንማርበት የጸጋ ወቅት ነው። መለኮታዊ ጥንቃቄን እና ጽድቅ ያለበትን ፍርድ ለመማር ከጌታ ጋር በዚህ በዐቢይ ጾም ጉዞ ዕይታችንን፣ አንደበታችንን እና ተግባራችንን በሙሉ በእግዚአብሔር ምሕረት ለመግራት ከራሱ ከጌታ ጋር በገዳመ ቆሮንጦስ ሱባዔ እንያዝ።
ቁጣ እና ንዴት ከምን ይመነጫል? ለምንድነው በባልንጀራዬ ላይ የምቆጣው? የሚሉት ጥያቄዎች በእግዚአብሔር እና በራሳችን ኅሊና ፊት ታማኝነትን የሚጠይቁ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው። ለምንድነው በባልንጀራዬ ላይ የምቆጣው? ለምንድን ነው እንደዚህ የምመረው?
ቅዱስ ያዕቆብ ለክርስትያኖች በጻፈው ሐዋርያዊ መልእክቱ ለዚህ ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ ይሰጣል፡-
“በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጋው ከፍትወት ምኞት አይደለምን? ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም፤ ስለዚህ ትገድላላችሁ። በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም፤ ስለዚህ ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ። ስለማትለምኑ የምትፈልጉትን አታገኙም። የምትለምኑትም ለፍትወታችሁ በማሰብ በክፉ ምኞት ስለሆነ፥ ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም” (ያዕ 4፡1-4)።
የንዴት እና የቁጣ ምንጭ በውስጣችን ያለው ያልተመለሰ ጥያቄ፣ ያልረካ ጥማት፣ ያልተደረሰበት ምናብ እና የተንሸዋረረ ፍላጎት ነው። እነዚህ ነገሮች በአንድ ሰው ነፍስ ውስጥ የያዙት ሥፍራ መጠን ያ ሰው የሚቆጣበትን ኃይል ይወስናሉ። ቅዱስ ያዕቆብ በውስጣችን ውጊያ መኖሩን እና ይህም ውጊያ በቁጣ፣ በንዴት፣ በክርክር፣ በቅናት፣ የሰው ስም በማጥፋት ወ.ዘ.ተ. እንደሚገለጥ ይናገራል። እነዚህ በውስጣችን ያሉት የጤናማ ሕይወት ቅደም ተከተል ቀውሶች በምንፈልገው እና በሚያስፈልገን ነገር መካከል፣ በጸሎታችን እና ያ የጸለይነው ጸሎት ቢመለስልን በምንሆነው ነገር መካከል፤ በምንጠማው እና እውነተኛ እርካታ በሚሰጠን ነገር መካከል ያለው አለመግባባት ነጸብራቆች ናቸው። በመሆኑም ዐቢይ ጾም ከጌታ ጋር እውነተኛውን ደስታ፣ እውነተኛውን ምልዐት፣ እውነተኛውን መከናወን፣ እውነተኛውን ዕረፍት ለማግኘት ከእርሱ ጋር በገዳመ ቆሮንጦስ መንፈሳዊ ሕይወት እና ፍትወቶቻችንን መግራት ለመማር የምንመሽግበት ወቅት ነው፤ ዐቢይ ጾም ሕይወታችን ከኢየሱስ ጋር የሚሰወርበት እና የሚሰራበት የጸጋ ዘመን ነው።
አንዳንድ ጊዜ “እገሌ እኮ አፉ ነው እንጂ ውስጡ ምንም የለም” ሲባል እንሰማለን፤ ጌታ ደግሞ በወንጌል “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራል” (ማቴ 12፡34) እያለ ያስተምራል። በመሆኑም በዚህ ዐቢይ ጾም “እኔ እኮ ልቤ ንጹህ ነው፤ ከተናገርኩም ከተቆጣሁም ፊት ለፊት ነው፤ ደግሞም ቶሎ እረሳዋለሁ” ወ.ዘ.ተ. ከሚል መመጻደቅ እና ሽንገላ ባሻገር በእውነት ጌታ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራል” የሚለው እውነት እንደሆነ ልባችንን እንመልከት፤ እንመርምር፤ ከጌታ ጋር በሕይወት ታሪካችን ቀላይ ውስጥ እንመላለስ፤ ከእርሱም ጋር ቁስሎቻችንን እንመልከት፤ ጠባሳዎቻችንን ገልጠን እናሳይ፤ በዚያን ጊዜ ከጌታ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ደግሞ ይናገራል፤ ይህም ወንድምን የሚባርክ፣ ሕይወትን የሚናገር እና የሚያንጽ ቃል ነው። ጌታ በዚህ ቃል ይሞላን ዘንድ በዚህ በዐቢይ ጾም በገዳመ ቆሮንጦስ ከእርሱ ጋር አርምሞ እንግባ፤ ሱባዔ እንያዝ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ያዕ 4፡1-12)
በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጋው ከፍትወት ምኞት አይደለምን? ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም፤ ስለዚህ ትገድላላችሁ። በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም፤ ስለዚህ ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ። ስለማትለምኑ የምትፈልጉትን አታገኙም። የምትለምኑትም ለፍትወታችሁ በማሰብ በክፉ ምኞት ስለሆነ፥ ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም። አመንዝሮች ሆይ! ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላትነት መሆኑን አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። ወይስ “እርሱ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል” በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን? ስለዚህ፥ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” እንደሚል፥ የሚሰጠው ጸጋ ግን ከሁሉም ይበልጣል። እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። 8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች! እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። 9ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፥ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። 10በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፥ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።
ወንድሞች ሆይ! እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም። 12ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
ጸሎት
ጌታ ሆይ ባልንጅራዬን በአንተ ዐይን መመልከት እችል ዘንድ በአይኖቼ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣልኝ። የባልንጀራዬን ውበት እና አንተ እርሱ ላይ የወሰድከውን ጊዜ ማስተዋል እንድችል ልቤን እና አእምሮዬን ክፈትልኝ። ከዘላለም ጀምሮ የተሰወረውን ሁሉ የሚገልጠውን ብርኀንህን በልቤ ውስጥ አብራ፤ ጨለማን እና ኀዘንን ሁሉ ከልቤ ሥር ንቀል። እኔም በማንነቴ መጋረጃ በታጠረ ጎዶሎ የፍርድ ሚዛን ሳይሆን በጽድቅ እና በምሕረት ሚዛን በከበረው የፍቅርህ ልክ ሌሎችን እመለከት ዘንድ ጸጋህን ስጠኝ፤ የጽድቅህን ሚዛን በውስጤ እንዳዲስ ስፈር፤ የማዳንህን ውኃ ልክ በነፍሴ መካከል አጽና፤ እንዳልናወጥ የሕይወቴ ሁሉ መልሕቅ አንተ ሁን። አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል። በዛሬው የዐቢይ ጾም አስተንትኖ እስቲ ከጌታ ጋር ቁጭ ብለን ይህንን እንጠይቅ፡-
- ለምንድነው በባልንጀራዬ ላይ የምቆጣው?
- ያልተመለሰልኝ የሕይወቴ ጥያቄ ምንድነው?
- ውስጥ ውስጡን የሚበላኝ፣ የሚያንገበግበኝ ጥያቄዬ ምንድነው?
- ጌታን አንድ ነገር መጠየቅ ዕድል ሳገኝ ምንድን ነው የምጠይቀው?
የተባረከ የጾም ጉዞ!
ሴሞ
[1]ንጽ Evagrius, Thoughts 17, Diadochus of Photike, On Spiritual Knowledge and Discrimination 62. Hesychius the Priest, On Watchfulness and Holiness 31.
[2] ንጽ John Cassian, Institutes VIII.21, 22.