ዐቢይ ጾም 15ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Monday, 10 March 2025 09:01
- Written by Samson
- Hits: 156
- 10 Mar
ዐቢይ ጾም 15ኛ ቀን
እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ሲፈጥረው በማስተዋል ሥጦታ ባርኮታል፤ ይህም ማስተዋል እግዚአብሔርን የምናሰላስልበት፣ በልብ እና በአእምሮ ከእርሱ ጋር ኅብረት የምናደርግበት መለኮታዊ ሥጦታ ነው። ቅዱስ ኒኮላስ ካባሲላስ “ማስተዋል ክርስቶስ ኢየሱስን በውስጣችን የምንሸከምበት ኃይል ነው”[1] በማለት የማስተዋልን ሥጦታ ብቻ ሳይሆን ልናስተውለው የሚገባንን ቁም ነገር አስተባብሮ ያመለክተናል። የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ትዝታ ውስጥ ይመላለሳል፤ እግዚአብሔርም በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ያለማቋረጥ ዘላለማዊ ትዝታው ይሆን ዘንድ ማስተዋል አለው። አንድ ክርስትያን ለዘላለም የማይቋረጥ እግዚአብሔርን የማሰላሰል ጥሪ አለው።[2] የኑሲሱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ በበኩሉ “ከምንተነፍስበት ቅጽበት ይበለጥ እግዚአብሔርን ልናስበው ይገባል፤ አንድ ክርስትያን በመሰረቱ ከዚህ ውጪ ሌላ ሥራ የለውም”[3] እያለ እግዚአብሔርን ማሰብ የተፈጠርንበት ዓላማ እና የፍጻሜያችን ጥሪ መሆኑን ያስታውሰናል።
እግዚአብሔርን የማሰብ የመጀመርያው ደረጃ ወደ እርሱ የሚያቀርቡንን ከእርሱ ጋር አንድ የሚያደርጉንን የተቀደሱ ምክሮች ማሰላሰል ነው፤ በዔደን ገነት ለአዳም እና ሔዋን የተሰጡትን ትእዛዛት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ለታደሰው ለአዲሱ ሰው የተሰጡትን ሕግጋት ማሰላልሰል የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ያሳየናል። ቅዱስ ዳዊት በበኩሉ “ትእዛዛትህን አሰላስላለሁ፤ መንገድህንም እፈልጋለሁ” (መዝ 119፡15) እያለ የእግዚአብሔርን ሕግ በማሰብ ስለሚገኝ ሕይወት ይዘምራል።የእግዚአብሔር ሕግ የክርስትያትያን ልብ ደስታ ነው፤ አማኝ የአምላኩ ፈቃድ ያለበትን ምሥጢር እያሰላሰለ በእግዚአብሔር ፊት ከቃሉ የተነሳ ሕያው ይሆናል።
እግዚአብሔርን ማሰላሰል ምሥጋናውን ማሰብ ነው፤ እግዚአብሔርን ማሰላሰል የሕይወት ታሪኬን በዐይኖቼ ፊት ለፊት አድርጌ እያንዳንዱን ቀን በእግዚአብሔር ምሕረት አስተውሎት መኖር ነው። እግዚአብሔርን ማሰላሰል ለልብ የምሥጋናን መዝሙር ይሰጣል፤ ዳዊት እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ አስተውሎት በሚመለከት “በመኝታዬ አስብሃለሁ፤ በማለዳም እናገርልሃለሁ” (መዝ 63፡6) እያለ ከአስተውሎቱ ጥልቀት በልቡ የሞላውን የእግዚአብሔርን ነገር በማለዳ ደግሞ እንደሚናገር፤ ማልዶ በልቡ የፈሰሰውን ፍቅር ለመመስከር እንደሚወጣ ይናገራል።
ቅዱስ ጳውሎስ “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና” (1ተሰ 5፡17) እያለ የክርስትያናዊ ሕይወት መርሐ ግብር ይሰጠናል። ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ምክር እግዚአብሔር ሠርክ አዲስ ትዝታችን ሆኖ ልባችንን እንዲሞላ፤ ልባችንን የሚገዛ ሌላ ጽኑ ሐሳብ እንዳይኖር የሚያስተምረን ነው። እግዚአብሔር የሕይወታችን የማያቋርጥ ጸሎት፣ የልባችን ዘላለማዊ ትዝታ እና የአእምሮአችን ሁሉ አመክንዮ አልፋ እና ኦሜጋ ነው።[4] ጸሎት የሰው ልጅ አእምሮ የተፈጠረበት የመጀመርያው ዓላማ ነው፤ እግዚአብሔር ፈቃድ እና እውቀት የሰጠን የመልካም ነገር ሁሉ ፍጻሜ እና የዕውቀት ሁሉ ራስ የሆነውን እርሱን በማሰብ፣ ልባችንን እና አእምሮአችንን ወደ እርሱ ከፍ በማድረግ በሥጋዊ ማንነታችን በዚህ ዓለም የምንደክም ብንሆን እንኳን በሐሳባችን ድንግልና በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሕያው እንድንሆን ነው። አእምሮ ለጸሎት ዓላማ የሰው ልጅ የባሕርይ ገንዘቡ ሆኗል። ጸሎት ለአእምሮአችን የተገባ ቀዳሚ ተግባሩ እና መዳረሻው ነው። አዳም እግዚአብሔርን ከማሰብ ኃይል እና በጸሎት ከመሆን ተመስጦ የተነሳ በእግዚአብሔር ላይ ባለው ፍጹም ትኩረት ሕያው ሆኖ ይኖር ነበር።[5] በዚህ አይነት አዳም በዔደን ገነት ባልተቋረጠ ጸሎት እና በእግዚአብሔር ፊት መገኘት ይመላለስ ነበር።[6] በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ የታደሰው አዲሱ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ እና በማሰላሰል ከኢየሱስ ስም ሥልጣን የተነሳ በነገር ሁሉ ተጠብቆ ሕያው ይሆናል፤ በሰማያት የከበሩት ቅዱሳን የማያቋርጥ አምልኮ ትኩረት እና የልባቸው ሐሳብ፤ በምድር ላይ የምትገኘው ቤተ ክርስትያን የሠርክ ጸሎት፤ በንስሐ ሥፍራ ያሉት ነፍሶች የመንግሥተ ሰማያት ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሰው ክርስቶስን በማሰብ ልቦናውን በእግዚአብሔር ፊት ሕያው ያደርጋል፤ በልቡ መዝገብ ክርስቶስ ኢየሱስን በአምልኮ ኃይል በማሰላሰል ልቡን ከጌታ ልብ ጋር አንድ ያደርጋል። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ሕይወት መዳረሻው ምን እንደሆነ ሲናገር የእግዚአብሔርን ምሥጢር የሚያውቅ የክርስቶስ ኢየሱስ ልብ አለን እያለ ይመሰክራል (1ኛ ቆሮ 2፡16)። ይህም ልብ በክርስቶስ የነበረውን ሐሳብ በእኛም ዘንድ ደግሞ የሚያደርግ ነው (ፊል 2፡5)። ነገር ግን ይህ የክርስቶስ ሐሳብ ምንድነው?
የክርስቶስ ሐሳብ በልቡ ሁሉ አባቱን ማፍቀር፤ በእውቀቱም ሁሉ አባቱን ማሰላሰል ነው፤ ይህ ለሰው ልጅ የተሰጠው የመጀመርያው ትዕዛዝ ነው፤ ይኸውም “እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኃይልህ ውደድ” የሚለው ትዕዛዝ ነው። በመሆኑም በክርስቶስ ኢየሱስ ልብ፣ በእርሱ የነበረውን ሐሳብ ሁሉ የምናውቅበት እና የምንማርበት የጸጋ ወቅት ዐቢይ ጾም ይባላል።
ዐቢይ ጾም የኢየሱስን ልብ የምናጠናበት፣ ከጌታ ልብ ጋር የምንጋጠምበት፣ በጌታ ልብ ማሰብ እና ማፍቀር የምንለማመድበት የጸጋ ወቅት ነው። በመሠረቱ ጾም ወደ ልቡና መመለስ ነው፤ እንደ ክርስትያን የምንመለስበት ልቡና እንድንመለስ ወደ ሚጠራን ወደ ጌታ ልብ ነው። ልባችን ከዚህ ልብ ጋር እንዲጋጠም፣ የተሰጠን የክርስቶስ ልብ በውስጣችን የጌታን ደም መርጨት እንዲጀምር፣ ሕይወታችን ሁሉ ከዚህ ልብ በሚፈልቀው ምሕረት እና ፍቅር እንዲረሰርስ ይህ የዐቢይ ጾም ወቅት የጌታ ልብ ጥናት ዘመን ሆኖ ተሰጥቶናል። በዚህ ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ እንድናስተውል እርሱ በመስቀል ላይ ሳለ በተወጋው ቁስል ልቡን ከፍቶልናል፤ እኛም ደግሞ በጾም ጸሎት ጦር ልባችንን ከፍተን ጌታ ወደ ውስጥ እንዲመለከት እንጋብዘው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (መዝ 119፡ 1-18)
በመንገዳቸው እንከን የሌለባቸው፥ በጌታም ሕግ የሚመላለሱ ምስጉኖች ናቸው። ሕጉን የሚጠብቁ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፥ 3 ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ።4 ሕጎችህን በሚገባ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ።5 ደንቦችህን ለመጠበቅ መንገዶቼ ምነው በቀኑ። 6 ትእዛዞችህንም ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርምና። 7 አቤቱ፥ ትክክለኛ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። 8 ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፥ በፍጹም አትጣለኝ።9 ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። 10 በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። 11 አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። 12 አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። 13 ከአፍህ የሚወጡትን ፍርዶች ሁሉ በከንፈሮቼ ደገምኳቸው። 14 በብልጽግና እንደሚደሰቱ ሁሉ በሕጎችህ መንገድ ደስ አለኝ። 15 ደንቦችህን አሰላስላለሁ፥ መንገዶችህንም እመለከታለሁ። 16 በድንጋጌዎችህ ደስ ይለኛል፥ ቃልህንም አልረሳም። 17 ለአገልጋይህ መልካም አድርግለት፤ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ። 18 ዐይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተአምራትህን አያለሁ።
ጸሎት
አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፥ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ጉዞዬንና መኝታዬን አንተ መረመርህ፥ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥ የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ። ከኋላና ከፊት ጠበቅኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እውቀትህ እጅጉን ያስደንቃል፥ ከከፍታውም ብዛት ልደርስበት አልችልም። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ቢሆን፥ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፥ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። አቤቱ፥ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፥ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዐይኖችህ አዩ፥ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። አቤቱ፥ ሐሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቁጥራቸውም እንደምን በዛ! ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፥ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ። አሜን!
አስተውሎት
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- የልቡናዬ ሐሳብ እና የማስተዋሌ ትኩረት አቅጣጫው ወደ የት ነው?
- ልቤን በጌታ ልብ ለመመልከት እና ለእርሱም የእኔን ለማሳየት ምን ይከለክለኛል?
- በሕይወቴ የምመራበት፣ የማስታውሰው፣ የምወደው የእግዚአብሔር ሕግ የቱ ነው?
የተባረከ የጾም ጉዞ!
ሴሞ
[1] ንጽ Nicolas Cabasilas, the life in Christ VI. 91.
[2] ንጽ Basil the Great, Letters XXII, Long Rules 5.
[3] ንጽ Gregory of Nyssa, Oration XXVII.4.
[4] ንጽ I. Hausherr, The Name of Jesus (Kalmazoo, Michingan: 1978), p. 158.
[5] ንጽ Dorotheus of Gaza, Incstructions I.1.
[6] ንጽ Diadochus of Photike, On Spiritual Knowledge and Dikrimination 56.