ዐቢይ ጾም 16ኛ ቀን
- Category: የ ፵ ጾም አሰተንትኖ
- Published: Tuesday, 11 March 2025 08:51
- Written by Samson
- Hits: 69
- 11 Mar
ዐቢይ ጾም 16ኛ ቀን
ክርስትያን በሁሉ ነገር እግዚአብሔርን የሚፈልግ መናኝ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በአንድ በኩል በሁሉም ስፍራ ይገኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር ሥፍራ የማይወስነው፣ በየትኛውም ቦታ ተወስኖ የማይገኝ መልዕተ ባሕርያዊ ኅላዌ ነው። በሁሉ ሥፍራ ታዲያ ይህንን እግዚአብሔር መፈለግ እንዴት ይቻላል? በየትኛውም ሥፋራ የማይገኘውን አምላክ ማግኘት እንዴት ይቻላል? እግዚአብሔር በተመሳሳይ ጊዜ በአንድ በኩል በዚህ በተጨባጭ ዓለም ውስጥ በፍጥረቱ መካከል የተገለጠ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሊደረስበት የማይችል መልዕተ ባሕርይ ያለው ነው። በግዙፉ ዓለም ባለው መገለጥ እግዚአብሔር በፍጥረት ሁሉ ሕልውና ውስጥ ያለ የሕይወት ኅያውነት ምንጭ እና ኃይል ሆኖ የሚኖር እና የሚሠራ በሁሉ ሥፍራ የሚገኝ አምላክ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በመልዕተ ባሕርያዊ ኅላዌው እግዚአብሔር የሰው ልጅ አእምሮ በማይደርስበት ረቂቅ ሥውርነት ውስጥ የሚኖር፤ የሰው አእምሮ ሊያስበው ከሚችለው ፍጹም ረቂቅ የሆነ ሐሳብ በላይ የረቀቀ። ሊታሰብ፣ ሊገመት፣ ሊነጻጸር በማይችል ማንነቱ ዘላለማዊ የሆነ አምላክ ነው። ኅላዌው በምንም የማይገለጽ፣ ቋንቋ የማይገኝለት፣ ቀመር የማይሰፈርለት ለዘላለም ባለመታወቅ የሚኖር ጥበብ ነው።
እያንዳንዱ ክርስትያን በምሥጢረ ጥምቀት ከቅድስት ሥላሴ ሕይወት ጋር ባለው ኅብረት ይህ ምሥጢር የሕይወቱ ሁሉ አንደኛ እና ዋነኛ ምሥጢር ሆኗል። አንድ ክርስትያን በዚህ ምሥጢር ውስጥ ሲኖር እግዚአብሔርን በፍልስፍናዊ ጥበብ ሳይሆን በእምነት ሞኝነት ስለሚፈልገው እግዚአብሔር ራሱን ይገልጣል። ክርስትያን እግዚአብሔር በነብዩ ሆሴዕ አንደበት “ለዘለዓለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ፥ በምሕረትና በጽኑ ፍቅር ለእኔ አጭሻለሁ። ለእኔም እንድትሆኚ በታማኝነት አጭሻለሁ፤ አንቺም ጌታን ታውቂአለሽ” (ሆሴዕ 2፡21-22) ሲል የተናገረውን ቃልኪዳን የሕይወቱ እና እግዚአብሔርን የመፈለጉ መምርያ አድርጎ የተቀበለ የእምነት ነጋዲ ነው። ከእርሱ ጋር እንደ ጋብቻ ቃልኪዳን በሚጸና ኅብረት የምትታመን ነፍስ እንደምታገኘው እግዚአብሔር ቃል ይገባል። ይህም ኅብረት በጥምቀት ቃልኪዳናችን ጥሪ በታማኝነት መገለጥ ነው፤ ይህም ታማኝነት የማይታየውን እግዚአብሔርን በእምነት ዐይኖች መመልከት እና ማስተዋል የምንችልበት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። ይህ ክርስትና የራሳችንን ሻማ አስቀምጠን በእግዚአብሔር ብርኀን መራመድ እና የራሳችንን መተማመን አውልቀን በእግዚአብሔር ላይ ባለን እምነት መውጣትን ይጠይቃል። ክርስትና በራሳችን ጥበብ እና በ “እኛነታችን” ችሎታ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ እና ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ በምንኖረው ሕይወት የመገለጥን ትህትና ይፈልጋል። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያለውን እምነት ሲያመለክት “ከጌታ ጋር የሚተባበር ከእርሱ ጋር አንድ መንፈስ ነው” (1ቆሮ 6፡17) ይላል።
ስውር ከሆነው አምላክ ጋር አንድ መሆን መሰወርን ይጠይቃል፤ ቅዱስ ጳውሎስ “ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯልና” (ቆላ 3፡3) እያለ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረግነው ኅብረት መሰወርን የሚጠይቅ ጨዋነት በውስጡ እንደያዘ ያስገነዝበናል። ይህም መሸሸግን፣ መጠበቅን፣ ዘወር ማለትን፣ ከእግዚአብሔር ውጪ እዚህ ናቸው በምንባልበት በሌላ አድራሻ አለመኖርን፣ በዓለም አለመታወቅን ይጠይቃል። በእግዚአብሔር መኖር ማለት በእርሱ ኃይል መገለጥ፣ ወደማይደረስበት የምሥጢር እና የእውቀት ጥግ መድረስ፣ በእርሱ በእግዚአብሔር ዓላማ ሁሉን ነገር መቀደስ፣ የሰውን ሐሳብ እና በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሳውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ጥበብ እያፈረስን አእምሮን ሁሉ ለእግዚአብሔር መማረክ ነው (2ቆሮ 10፡5)። በእግዚአብሔር መኖር ማለት ለእርሱ መለኮታዊ መገለጥ ስውር መሣርያ መሆን፣ የማዳኑ አምባሳደር፣ የምሕረቱ ነጸብራቅ እና ወሰን የሌለው ፍቅሩ ሐዋርያ መሆን ማለት ነው።
ዐቢይ ጾም ለዚህ በእግዚአብሔር ዓላማ በክስቶስ የተሰወረ ሕይወት የሚያዘጋጀን ትምህርት ቤት ነው። ጾም፣ ጸሎት፣ ተጋድሎ፣ ጽሙና እና በእምነት የሚሆን መታዘዝን የምንማርበት፤ ከክርስቶስ ጋር የምንሰወርበት እና በትንሳኤው አዲስ ማንነት ለመገለጥ በሕማሙ እና በሞቱ ምሥጢር እርሱን እንመስል ዘንድ ከእርሱ ጋር በገዳመ ቆሮንጦስ ፍጹም የምንሰወርበት ወቅት ነው። ጾም በራሱ ይህንን መሰወር እና መለኮታዊ ኅብረት አያስገኝም፤ ነገር ግን በጾም ውስጥ ከጌታ ጋር የምንሆንባቸው እና ከጌታ ጋር የምናደርጋቸው የጸጋ ሕይወት ልምምዶች ነፍስን እንዲህ ላለው ስውር ማንነት እና መለኮታዊ ኅብረት ያዘጋጇታል። ነፍስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በገዳመ ቆሮንጦስ በምታሳልፈው የዐቢይ ጾም ጉዞዋ በእግዚአብሔር ፊት ራስን ባዶ ማድረግን ትማራለች፤ በዚህም ነፍስ በማንነቷ ከመሞላት ይልቅ ራሷን ከክርስቶስ ጋር ባዶ በማድረግ የመንፈስ ቅዱስን ሙላት በትህትና ትጠባበቃለች፤ ይህም ትህትና ነፍስን ከተጣበቀችበት እኔነት ያላቅቃታል። ነፍስ ለራሷ በራሷ ከሳለችው ውበት እና ዝና ተላቅቃ እግዚአብሔር በሚያውቃት ውበት እና ማንነት ዳግም በእግዚአብሔር ፊት ሕያው ትሆናለች፤ በዚህም ነጻነት ነፍስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወት ጋር ለመሰወር ለአዲስ ሕይወት እና ግንኙነት ክፍት ትሆናለች። ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ መሰወር በእግዚአብሔር ፊት እውነተኛ ማንነትን ማግኘት እና በእርሱ አዲስ ፍትረጥ ሆኖ መገለጥ ነው።
ይህ የነፍስ ድል ከምናባዊ ሕልም ወደ ተጨባጭ ክርስቶሳዊ እውነታ፣ ከሐሰተኛ የዓለም ማባበያ ተስፋዎች ወደ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃልኪዳን፣ ከውስብስብ አእምሮአዊ እውቀት በክርስቶስ ኢየሱስ ወደተገለጠው እውነተኛ ሕይወት መሻገር ነው። ነገር ግን ይህ ማለት አንድ ክርስትያን ውጫዊ ቁመናው ይቀየራል ማለት አይደለም፤ ይልቁንም ውስጣዊ እና ውጫዊ ሰውነቱ በክርስቶስ ኢየሱስ በታረቀ ማንነቱ እንደ አዲስ ተዋውቀው ሰላም ያወርዳሉ ማለት ነው። ውጫዊ ሰውነቱ፣ ጸሎቱ፣ ሥራው እና ሌሎች የእሱነቱ ክፍሎች እንዳሉ ናቸው፤ ዳሩ ግን ውስጡ በሁለንተናው ተቀይሯል፤ በውስጡ እግዚአብሔር በቅዱስ ጳውሎስ አነጋገር “ሁሉ በሁሉ” ሆኗል (1ቆሮ 15፡28)። በዚህ አይነት ከዚህ በኋላ የሕይወቱን ቁምነገሮች ሁሉ በራሱ ማንነት እና ስም ሳይሆን፤ ይልቁንም ከእርሱ ጋር ሕይወቱን በሰወረበት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይመለከታቸዋል። ስለዚህ ይህ ክርስትያን ከኢየሱስ ጋር በአንድ ድምጽ “የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ እኔም እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም” (ዮሐ 8፡29) ወደሚል መተማመን ያድጋል።
ይሁን እንጂ ይህ ክርስትያን ኃጢአት ከመሥራት ነጻ ሆኗል ወይም ወደዚያ ፍጽምና ደርሷል ማለት አይደለም፤ ይልቁንም በራሱ ማንነት በኃጢአት ላይ የሚበረታ ፈቃድ እንደሌለው በማመን ራሱን እና ፈቃዱን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ዐደራ ሰጥቷል ማለታችን ነው። በመሆኑም ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ይህም ክርስትያን “በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፤ ነገ ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሥጋዬ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ” (ሮሜ 7፡22-23) እያለ በእግዚአብሔር ፊት በትሕትና ይታመናል። በዚህ ትህትና “የክርስቶስ ኃይል ያድርበት ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሙ እየተመካ... ስደክም ያን ግዜ ኃይለኛ ነኝ” (2ቆሮ 12፡9-10) የሚል በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ የማይቆርጥ፣ ከድካሙ እና ከኃጢአት ውርደት ጋር እንደ ዐይን ቅጽበት እንኳን ሊነጻጸር በማይችል የእግዚአብሔር ጸጋ ይታመናል። እንዲህ ያለው መታመን እግዚአብሔር ከእኛ ድካም እና ኃጢአት ባሻገር በደካማው ነገር ውስጥ የበረታ ኃይሉን መግለጥ እንደሚችል እና እርሱ በሚያውቀን ልክ በፊቱ እንደ ትከሻችን ስፋት ፍጹም የምንሆንበትንና መስቀላችንን የምንሸከምበትን ጸጋ እንደሚሰጠን ማመን ነው።
ፍጽምና ፍጹም መስለው ለመታየት ለሚሽቀዳደሙ እና ቅዱስ ሳይሆኑ አስቀድሞ ቅዱስ ተብለው መጠራት ለሚፈልጉ የሚሰጥ ሳይሆን ይልቁንም ኃጢአተኛ እና የኃጢአተኛ ባንዲራ ያዥ መሆናቸውን በትህትና ለሚያምኑ፣ ኃጢአታቸውን ለሚናዘዟት እና ለሚጠሏት፣በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ ለማይቆርጡ እና ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጣቸው ለሚሰራው የጸጋ ተሃድሶ እሺ ብለው ለሚታዘዙ የሚሰጥ የትሑታን ገንዘብ ነው። ፍጽምና ማንም በማይደርስበት ቦታ ለተሸሸጉ እና እውነታን ለሚሸሹ የሚሰጥ ሽልማት ሳይሆን ከእርሱ ጋር ለመሰቀል ወደዚህ ዓለም እምብርት ገብተው ቀን ከሌሊት ከሕይወት ጋር ፊት ለፊት ለሚገናኙ፣ ኀዘንን፣ ብቸኝነትን፣ ፈተናን እና ልዩ ልዩ የሕይወትን መሪር መልኮች ለሚጋፈጡ፣ ዕለት ዕለት መስቀላቸውን ለመሸከም እና እግዚአብሔርን ተስፋ ለማድረግ ለማይደክሙ የክርስቶስ ጓደኞች የሚሰጥ ጸጋ ነው። ፍጽምና የፍቅር ሌላው መጠርያ ነው፤ ይህም እግዚአብሔርን በሁለንተና ማፍቀር እና ባልንጀራን በእግዚአብሔር ፍቅር የማፍቀር ትምህርት ቤት ነው።
ዐቢይ ጾም እንዲህ ያለውን ፍቅር እና ፍጽምና የምንለማመድበት፣ ከሕይወት እና ከእውነት ጋር ፊት ለፊት የምንጋፈጥበት፣ ከራሳችን ስም ይልቅ የጌታን ስም መጥራት እና በእርሱ ውስጥ መታወቅ የምንለማመድበት የጸጋ ወቅት ነው። ዐቢይ ጾም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በገዳመ ቆሮጦስ ራስን መካድ እና በእግዚአብሔር ብቻ መታወቅን የምንማርበት፣ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የምንሰወርበት፣ እግዚአብሔር አብ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ ምክር እያንዳንዳችንን በአዲስ ሕይወት ጸጋ የሚያድስበት የተሃድሶ ዘመን ነው። በዚህ በዐቢይ ጾም ከጌታ ጋር በገዳመ ቆሮንቶስ መሰወር የሚፈልግ ክርስትያን ከመናኙ ከመጥምቁ ዮሐንስ በተማረው የመንፈሳዊ ሕይወት ትህትና “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል” (ዮሐ 3፡30) ማለትን የሚለማመድ በራሱ ማንነት አንሶ በክርስቶስ ኢየሱስ ማንነት እና አእምሮ በትንሳኤው ክብር ለመገለጥ ራሱን የሚያዘጋጅ አማኝ ነው።
በዚህ በዐቢይ ጾም መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዳችንን በአብ ልብ ውስጥ ባለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ይቀርጸን ዘንድ ራሳችንን ለጸጋ ሥራ ሁሉ ክፍት የምናደርግበት፣ የጌታን ራስን ባዶ ማድረግ እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ መሞላት የምንማርበት፣ ፊታችንን እና የነፍሳችንን ፍጹም ትኩረት ወደ እግዚአብሔር የምንመልስበት ወቅት ነው። ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር በገዳመ ቆሮንጦስ መሰወር፣ መሸሸግ፣ ዘወር ማለት፣ ማረፍ፣ ጊዜ መውሰድ፣ መለየት (Disconnected መሆን)፣ በማረፍ እና በመመለስ እግዚአብሔርን በማወቅ ለነፍሳችን እረፍት የምናገኝበት የጸጋ ጉብኝት ጊዜ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ኤፌ 4፡1-32)
በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ እንድትመላለሱ... በትሕትናና በየዋህነት ሁሉ፥ በትዕግሥትም እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ... ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ፍጽምናው እስክንደርስ ድረስ ነው። ከእንግዲህ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል፥ በሰዎችም ማታለል ምክንያት፥ በነፈሰው የትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን፥ ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን፥ ሕፃናት መሆን አይገባንም። ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየተናገርን፥ በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ፤... በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን የሰውነት አካሎች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ፥ ኃጢአትን ግን አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖረው በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። እንደ አስፈላጊነቱ፥ ለሚሰሙት ጸጋን እንዲሰጥ፥ ለማነጽ የሚጠቅም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም፥ ጩኸትና ስድብን ሁሉ፥ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።
ጸሎት
አቤቱ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ፤ አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ልመናዬን አድምጥ፥ በታማኝነትህ፥ በጽድቅህም መልስልኝ። ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባርያህ ጋር ወደ ፍርድ አትግባ። የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፥ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፥ የእጅህንም ሥራ አስተዋልሁ። እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፥ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች። አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፥ መንፈሴ ዛለ፥ ፊትህን ከኔ አትሰውር... አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ጽኑ ፍቅርህን አሰማኝ፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አሳውቀኝ። አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማፅኛለሁና አድነኝ። አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፥ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ። አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፥ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ሁነኝ። አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም። አሜን!
የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)
በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።
- የዐቢይ ጾም ከተጀመረ በቀን ለ 10 ደቂቃ ከጌታ ጋር ለመሰወር ግዜ ወስጃለሁ?
- የስልክ እና የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሜ ይጾማል?
- የማርፍበት፣ የማዳምጥበት፣ ዘወር የምልበት፣ የምሸሸግበት ለራሴ ጊዜ አለኝ?
- የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?
የተባረከ የጾም ጉዞ!
ሴሞ