Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዐቢይ ጾም 17ኛ ቀን

የዐቢይ ጾም 17ኛ ቀን

can-you-not

 

የሐሳብ ማዕበል

ጸሎትን እና ፍቅርን በሚገባ መማር የምንችለው ጸሎት የማይታሰብ በሆነባቸው ጊዜያቶች እና ልባችን ዐለት የሆነ በሚመስሉን ወቅቶች ነው። በጸሎት ጊዜ ልባችሁ ካልተከፋፈለ፣ አእምሮአችሁ ካልዋለለ ጸሎት እንዴት እንደሚጸለይ ገና አላወቃችሁም ማለት ነው። የጸሎት ምሥጢር እግዚአብሔርን መራብ ነው። ይህ ርሃብ በቃላት እና በፍቅር ሊገለጽ የማይችል ከቋንቋ እና ከስሜት በላይ የሆነ ርሃብ ሲሆን፤ በዚህ ርሃብ እየተሰቃየ ያለ አማኝ እግዚአብኄርን በማግኘት ፈንታ አእምሮው እና ልቡ በየራሳቸው መንገድ ገበያ ወጥተው ውኃ በማያነሳ የሐሳብ ወጀብ ይንጡታል። አንዳንድ ጊዜ ሐሳቦቹ እንዴት በአእምሮአችን ውስጥ እንኳን እንደተቀረጹ ልንረዳው በማይችል መልኩ እጅግ አስቀያሚ ሐሳቦች እና ምስሎች ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ባለ ሁኔታ በአንድ በኩል እግዚአብሔርን በማግኘት  ርሃብ፤ በሌላ በኩል እጅግ ክፉ እና አስቀያሚ በሆኑ ሐሳቦች ማዕበል የምትናጥ ልብ በአእምሮው ነጻ ከሆነ ልብ በላይ በጸሎት የመቃተት ኃይል አላት።

በመሆኑም በጸሎት ጊዜ በሐሳብ ማዕበል መናወጣችን ሊያበሳጨን፣ “ቀሽም አማኝ ነኝ” ሊያስብለን እና የጸሎታችን ትርጉም ሊያንሸዋርርብን አይገባም። በመሰረቱ በጸሎት ሕይወት ውስጥ ያለውን የሐሳብ መከፋፈል ልናስወግደው የምንችለው ቁም ነገር አይደለም። በምንበረከክበት ጊዜ የሚያሰቃዩን ሐሳቦች፣ ምናባዊ ምስሎች እና በአንድ ጊዜ እጅግ አስፈላጊ እና የግድ በዚያ ቅጽበት መከናወን ያለባቸው ሆነው የሚቀርቡት ነገሮች ሁሉ የጸሎት ሕይወታችን አንደኛው ገጽታዎች ናቸው። እነዚህ ነገሮች ጸሎት የግል ችሎታ እና በግል መንፈሳዊ ጥንካሬ የሚደረግ ነገር ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ አነሳሽነት እና መሪነት፣ ነፍሳችንን እና አእምሮአችንን በእግዚአብሔር ሕልውና በሚሞላ መገለጥ በነፍሳችን ውስጥ የሚፈስ የመንፈስ ቅዱስ መቃተት ነው። 

ለጸሎት ስንዘጋጅ ሐሳባችን ለምን እንደሚበታተን አንድ ማወቅ ያለብን መሰረታዊ ቁም ነገር ሐሳብ፣ ምስል እና ምናብ በሥራ ላይ የሚሆኑት አእምሮአችንን ለመሰብሰብ እና የጽሞና ጊዜ ለመውሰድ በምንሞክርበት፣ የፈቃዳችንን ትኩረት ወደ ምንጩ ለማድረግ በምንዘጋጅበት ጸጥታ ውስጥ ነው። በዚህ ወቅት ፈቃድ ወደ እግዚአብሔር ከፍ ለማለት ሲዘጋጅ፣ በጽሞና እግዚአብሔርን በጸሎት ለማፍቀር ስንበረከክ በተመሳሳይ ጊዜ ሐሳብ፣ ምስል እና ምናብ ሥራ ፈትተዋል። በመሆኑም ከጥቂት ሥራ መፍታት በኋላ ከኅሊና የውስጠኛው ስውር ስፍራ (subconscious mind) መኖራቸውን እንኳን የማናውቃቸው ሐሳቦች፣ ጥያቄዎች፣ ትውስታዎች እና ምናባዊ ምስሎች ወ.ዘ.ተ. ወደ ፊተኛው የአንጎል ክፍል በመምጣት መኖራቸውን እና የእኛን ትኩረት እንደሚፈልጉ ያሳያሉ። በዚህ ወቅት ጠቃሚው ነገር እነዚህን ምስሎች ችላ ማለት እና የትኩረትን ማዕከል እግዚአብሔር ላይ እንዳደረግን መቆየት ነው። ሐሳቦቹ መምጣታቸው የእኛ ኃላፊነት አይደለም፤ ሐሳቦቹ ለምን መጡ ማለቱም ጥቅሙ እጅግም ነው፤ ነገር ግን ሐሳቦቹን የምናስናግድበት መንገድ የእኛን ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ላለማስተናገድ እና ትኩረታችንን ጠብቀን ለመቆየት ምርጫ አለን። በመሆኑም ይህ የሐሳብ ትዕንት በኅሊናችን መድረክ ጀርባ እየዋኘ እኛ ግን በኅሊናችን ማዕከል ከእግዚአብሔር ጋር መቆየትን መለማመድ እንችላለን።

እነዚህ በጸሎት ትኩረት ማዕከል ኅሊናችንን ሰቅዘው የሚይዙት እና በተለያዩ ምናባዊ ምስሎች የሚያስጨንቁት ሐሳቦች እኛ ትኩረት እስካልሰጠናቸው ድረስ የኅሊናችንን ማዕከል ተሻግረው፣ ከእግዚአብሔር ጋር በሰላም የምንቆይበትን የነፍሳችንን አደባባይ አቋርጠው የልባችንን አስኳል መማረክ አይችሉም፤ ነገር ግን የምስሎቹ እንግዳነት፣ ያልተጠበቀ እና በሰማይም በምድርም አስበነው የማናውቀው አይነት መሆን፤ የሚያስደነግጥ፣ ቅጽበታዊ እጅግ አስፈላጊ ነገር የሚያስታውስ ወ.ዘ.ተ. ሆኖ መገለጥ እና ያንን ለማቆም ምንም ማድረግ ያለመቻላችን እውነታ ሰላም ስለሚነሳን ሐሳቦቹን እናስቆማቸዋለን በሚል ተስፋ ትኩረታችንን ከእግዚአብሔር ላይ አንስተን ወደ እነዚህ ምናባዊ ትያትሮች በማድረግ ሐሳቦቹን ለማስቆም ግብግብ እንገጥማለን፤ ይህም በአእምሮ ውስጥ ያለውን የአንጎልን ጤናማ የሥራ እንቅስቃሴ ስለሚያስጨንቅ በአእምሮ ውስጥ የለየት ጦርነት እና ጭንቀት ይጀመራል።

መርሳት የሌለብን ዐቢይ ቁም ነገር እነዚህ ሐሳቦች በራሳቸው ጎጂ ባለመሆናቸው የኀሊናችንን ትኩረት ከእግዚአብሔር ላይ አንስተን ለእነርሱ በመስጠት ከዋጋቸው በላይ ማክብር ተገቢ አለመሆኑን ነው። አንዳንድ ጊዜ ሐሳቦቹ በዚያ መልክ ወደፊት በመምጣታቸው ፈገግ ብለን ማዕከላዊ የትኩረት ሕዋሳችንን በእግዚአብሔር ላይ እንዳደረግን የመንፈስ ቅዱስን እንቅስቃሴ በማስተዋል ለእርሱ ብቻ ፍጹም ትኩረት በመስጠት በነፍሳችን ውስጥ ከሐሳቦቹ ረብሻ የሚጠልቅ ድንቅ ሰላም እናገኛለን።

በተፈጠረው ነገር ሁሉ፣ የሐሳብ ማዕበል በሚያስጨንቀን ነገር ውስጥ ሁሉ ወሳኙ እና አስፈላጊው ነገር ለጸሎት ጊዜ መውሰዳችን፣ በእግዚአብሔር ፊት ለመገኘት ተስፋ አለመቁረጣችን እና ከድካማችን ባሻገር ለጸሎት መንበርከካችን ነው። እግዚአብሔርን ለማወቅ እና ለመውደድ  ፍላጎቱ እስካለን ድረስ ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ተሟልቷል፤ እግዚአብሔርን ለማወቅ እና ለማፍቀር ያለን ፍላጎት ስለ እግዚአብሔር ካለን በርካታ ድንቅ ሐሳብ የተሻለ የጸሎት ኃይል አለው። በምንም አይነት የሐሳብ ማዕበል ብንሰቃይም በእግዚአብሔር ፊት መሆን እና በትሕትና ለጸሎት መንበርከክ የእግዚአብሔር ጸጋ ከእኔ ድካም ይበልጣል የሚል የሕይወት ምሥክርነት ጸሎት ነው። በመሆኑም በልብህ ስውር ስፍራ ለሚያገኝህ እና ለሚያግዝህ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድህን በመስጠት በዙርያህ ካለው ወጀብ ባሻገር ከፊት ለፊትህ፣ በልብህ መካከል፣ በነፍስህ እኩሌታ ውስጥ ከማንነትህ በሚጠልቅ ፍቅር ከቀረበህ አምላክ ጋር መነጋገር ሰላም ይሰጣል። ቅዱስ ጴጥሮስ በዙርያው ያለውን ወጀብ በመፍራት ዕይታውን ከጌታ ላይ አንስቶ ወደ ወጀቡ እስካደረገበት እና የነፍሱን የትኩረት ማዕከል እስከለወጠበት ድረስ እርሱ ወዳለበት ሥፍራ ልክ እንደ ጌታ በውኃ ላይ እንደተራመደ ልብ በል (ማቴ 14፡ 28-32)። ዐቢይ ጾም ትኩረታችንን የምናስተካክልበት፤ ዕይታችንን የምንመርጥበት፤ ከሚያስፈራን ነገር ባሻገር የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ ከእኛ ጋር መሆኑን የምናስተውልበት (ቆላ 1:27)፤ አስፈላጊው ነገር አንድ ብቻ ነው፤ እርሱንም ከእርሷ የሚወስድባት የለም (ሉቃ 10:42 ) የሚለውን የጌታን የትኩረት አቅጣጫ የምንማርበት እና ከማርያም ጋር የተሻለውን የምንመርጥበት የጸጋ ወቅት ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ (ማቴ 14፡ 22-32)

ወዲያውም ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ደቀመዛሙርቱ ወደ ጀልባ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር። በዚህ ጊዜ ጀልባዋ ከምድር በጣም ርቃ ሳለች፥ ነፋስ በተቃራኒው አቅጣጫ ነበርና በማዕበል ትንገላታ ጀመር። ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ። ደቀመዛሙርቱ በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ “ምትሐት ነው” ብለው ደነገጡ፤ ከፍርሃትም የተነሣ ጮኹ። ወዲያው ኢየሱስ ተናገራቸው፥ “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንህ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ሲል መለሰለት። እርሱም “ና” አለው። ጴጥሮስም ከጀልባዋ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በውሃው ላይ ተራመደ። ነገር ግን የነፋሱን ብርታት አይቶ ፈራ፤ መስጠም በጀመረም ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ወዲያው እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ፥ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው። ወደ ጀልባዋ በወጡ ጊዜ ነፋሱ ፀጥ አለ።

ጸሎት

የሰላም አለቃ ተብለህ የምትጠራ ሰላማችንና ዕርቃችን የሆንከው፤ ማዕበሉን የምትገስጽ ወጀቡን የምታረጋጋ ጌታ  ኢየሱስ ሆይ መከፋፈልና የጥል ግድግዳን ባፈረስክበት በመስቀልህ ፊትህን ወደ እኔ መልስ፤ ልቤን፣ ሐሳቤን፣ አእምሮዬን እና ኅሊናዬን ሁሉ አረጋጋ፤ ጌታ  ኢየሱስ ሆይ፤ ሰላም ከአንተ ካልተሰጠ በስተቀር የሰው ድካም ከንቱ ነውና፤ ያንተ ሰላም ወዳለበት ወደ ነፍሴ ትኩረት እና ወደ ልቦናዬ እረፍት መልሰኝ። አቤቱ ለራሴ የሰላም መሣርያ እንድሆን አድርገኝ፤ ጥል ባለበት የሕይወቴ ክፍል ሰላም፤ በደል ባለበት ታሪኬ ይቅርታ፤ ስህተት ባለበት የሕይወት ምርጫዎቼ የአንተ መለኮታዊ እውነት፤ ጥርጣሬ ባለበት ደካማው እምነቴ በድካሜ የሚበረታ የማዳንህ ጸጋ፤ ተስፋ መቁረጥ ባለበት የዛሬ ውሎዬ እና የነገ እኔነቴ አንተን ተስፋ የሚያደርግ መጽናናት፤ ጨለማ ባለበት የመንገዴ እውር ድንብር ብርኅን፤ ኅዘን ባለበት የልቤ ጥግ ደስታ እንዲገኝ በየዕለቱ አስቀድሜ የራሴ የሰላም መሳርያ እንድሆን አበርታኝ። አሜን!

የዐቢይ ጾም አስተውሎት (Journal)

በዚህ በአብይ ጾም በየዕለቱ የጸሎት ሐሳቦችን እና አስተውሎቶችን መጻፍ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያግዛል። እውነተኛ የቀን ውሎ አስተውሎት እና የጸሎት ሐሳብን በነጻነት በማስፈር ለነፍስ ዕድል መስጠት በመንፈሳዊ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎችን ለራስ ውሎ በሚስማማ ሁኔታ በማስተካከል አስተውሎትን መጻፍ ይቻላል።

  1. የሐሳብ ማዕበል ጤናማ የጸሎት ሕይወቴ አንዱ ገጽታ እንደሆነ አውቃለሁ? ወይስ ሐሳቤ ስለሚበታተን ቀሽም ክርስትያን የሆንኩኝ ይመስለኛል?
  2. ትኩረቴን በእግዚአብሔር ላይ አድርጌ በዙርያዬ ያሉ ነገሮች በራሳቸው ዛቢያ እንዲሽከረከሩ ለመፍቀድ ምን መለማመድ እችላለሁ?
  3. እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ለመሆን የሚጠብቀኝ የነፍሴ ሥፍራ እና የልቤ ማዕከል ለእርሱ ለመሆን ይፈልጋል?
  4. የዐቢይ ጾም የጸጋ መሻቴ ምንድነው? የትኛው ጸጋ ዛሬ፣ አሁን እያለፍኩበት ባለሁት ሁኔታ ውስጥ በይበልጥ ያስፈልገኛል?

የተባረከ የጾም ጉዞ!

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።